“ምን አውቅልህ? ምን አውቅልሽ?” እንባባል፤
…እናም ሀገርን በክብር እንቀባበል::
በዚህ ጸሐፊ ግምትና ምልከታ መሠረት የዛሬዪቱ ኢትዮጵያ “ነፍስ አወቅ” ዜጎች በሀገራዊ ጉዳዮችና ተቆርቋሪነት መለኪያዎች ሲፈተሹ በአራት ዋና ዋና ምድቦች ቢቧደኑ አግባብ ነው ብሎ ያምናል:: “እንቆቅልህ/ሽ?” አሰኝቶ ለውይይት የጋበዘንም ይሄው የሀገራዊ ጉዳይ፣ መራርና የወቅታዊ ጉዳይ እውነታ ነው:: ይህ ምደባ ከጸሐፊው የረጅም ዓመታት ትዝብት የመነጨ እንጂ በሳይንሳዊ የጥናት ትንታኔ የተገኘ ውጤት ያለመሆኑ ቀድሞ ይታወቅ:: ደግሞም እኮ ጸሐፊው ለዓመታት ሲጽፍበት የኖረው ይህ ዓምድ መለያው “ነፃ ሃሳብ” የሚል ስለሆነ እጅግም ተሟጋች የሚበረታበት ርዕስ ሊሆን አይገባም::
የመጀመሪያው የዜጎች ምድብ፤
በዚህ በመጀመሪያው ምድብ ውስጥ የሚካተቱት ዜጎች ኢትዮጵያን ራሷን ተሸክመው የሚታትሩና የሚደክሙትን “ለሀገር ሙት፣ ለሕዝብ ክብር ተሟጋቾችን” የሚወክል ነው:: እነዚህ “የምር አፍቃሬ ሀገር” ዜጎች የቀን ተሌት ምኞታቸውና ናፍቆታቸው ኢትዮጵያ ወደ ተሻለ ከፍታ ደርሳ ማየት ነው:: እይታቸው በሩቅ ታዛቢነት ሳይሆን እነርሱ ራሳቸው የአቅማቸውንና የእውቀታቸውን እንጥፍጣፊ ሳያስቀሩ መልካም አሻራቸውን ለማኖር የማይሰስቱና ከንፍገት የጸዱ የምር የሀገር ልጆች ናቸው::
ቶድ ሄንሪ የተባሉ ደራሲ “Die Empty – (ያለህን መልካምነት ለሀገርህና ለሕዝብህ አንጠፍጥፈህ እለፍ”) በሚል ርዕስ በጻፉት መጽሐፍ ውስጥ ለማሳየት የሞከሩት እንደነዚህ ዓይነቶቹን የየሀገሩን ዜጎች ለማበረታታት በማሰብ ይመስላል:: ጸሐፊው የሚሞግቱት “ከእነ እውቀትህ ተቀብረህ ለምን አፈር ይበላሃል? ለምንስ ለበጎ ምግባር ንፉግ ሆነህ የምስጥ እራት ለመሆን ምርጫ ታደርጋለህ?” እያሉ ነው:: ይህ ዐምደኛ ከአሁን ቀደም በዚሁ ጋዜጣ ላይ ባስነበበው ጽሑፍ የዚህኑ መጽሐፍ መሪ ጭብጥ ተንተርሶ የንባብ ምልከታውን ማጋራቱ አይዘነጋም::
“ኢትዮጵያን ለመሸከም ታከተን የማይሉት” እነዚህን መሰል ዜጎች ከግል ጥቅም ማሳደድና “ከልታይ ልታይ” ልክፍትና ግፊያ የራቁ ስለሆነ በብዙዎች ዐይን ፈጥነው አይገቡም፤ ቢገቡም የሚፈረጁት እንደ ልክ-እልፍ (Fanatic) ተደርገው ነው:: የመሪነት ወንበር ላይ ተደላድለው የተቀመጡ “አለቆችም” ቢሆኑ ለእነዚህ ሀገር ወዳድ ዜጎች ቁብና አትኩሮት የሚሰጡ አይመስልም:: ምክንያቱ ደግሞ እጅግም የተሰወረ ሳይሆን ግልጽ ነው:: በዋነኛነት “በተግባራቸው ሳይሆን በጉልህ ድምጸ መረዋነታቸው” ቀድመው የሚታዩት “እኛ ብቻ” ባይ ተገዳዳሪዎቻቸው እነዚህን መልካሞቹን የሀገር ልጆች ስለሚጋርዷቸው ነው::
የግርዶሹ ምክንያትም አንድም ከእነርሱ በፊት ቀድመው በበጎነታቸው እንዳይታወቁ፣ ሁለትም የግርዶሹን ተዋንያን ተሰሚነትና ተቀባይነት የሚቀንሱ ስለሚመስላቸው በተቻለ መጠን ከዐይንም ከልብም እንዲርቁ የተቻላቸውን ሁሉ ከመፈጸም አይቦዝኑም:: ለበላዮቻቸው ሪፖርት የሚያደርጉትም ድክመታቸውን እየነቀሱና በመሐላ ጭምር እያረጋገጡ ነው:: ምክንያቱም የእነዚህ ቅን ዜጎች ከፍታ የሚያሳንሳቸው ስለሚመስላቸው ነው::
በእርግጠኝነት መመስከር የሚቻለው ግን ኢትዮጵያን በልባቸው፣ በመንፈሳቸው፣ በተግባራቸውና “በጀርባቸው” ተሸክመው የሚንገዳገዱት እነዚህ “የሕሊና ንጹሐን” በፍጹም ከሌሎች ጋር እየተሽቀዳደሙ “እኔ ብቻ” በማለት ራሳቸውን ለማስቀደም ያለመድፈራቸው ነው:: በአዘቦት ቋንቋቸው ኢትዮጵያን፣ በሌት ሕልማቸውና “በቀን መብሰልሰላቸው” ሁሌም ሀገራቸውን ስለሚያስቀድሙ ብዙ ወዳጅ ላይኖራቸው ይችላል:: ይኖራቸዋል ቢባልም እንኳን ወዳጅ ተብዬዎቹ “አንተን/አንቺን ብቻ ለኢትዮጵያ ተቆርቋሪ አድርጎ ማን ሾመህ? ሾመሽ? ደግሞስ ኢትዮጵያ! ኢትዮጵያ! ከማለት የግል ኑሮህን/ኑሮሽን መኖሩ አይበልጥብህም/ አይበልጥብሽም” በማለት የሚመክሯቸው ሊሆኑ ይችላሉ::
እነዚህ የበጎነት አውራና የሕይወት ምሳሌ ዜጎች ከኢትዮጵያ ጓዳ ሰርቆ ለመክበር፣ ዋሽቶ ለመወደድ፣ አስመስሎ ለመኖርና እየቀላመዱ ቀን ለመግፋት እምነታቸውም መሐላቸውም ስላልሆነ ብዙውን ጊዜ አጃቢም ይሁን ተከታይ ወይንም “በርቱ!” ባይ አትጊ ላይኖራቸው ይችላል:: ብቸኝነታቸው በሀገር ውስጥ እየኖሩ ባይተዋር እስከ መሆንም ቢያደርሳቸው አይገርምም::
የሚቀጥለው ማነጻጸሪያ (Analogy) እጅግም ተቀራራቢ ነው ባይሰኝም፤ ጉዳያችንን ለማጉላት ይረዳ ስለመሰለን አንድ ጥንታዊ ታሪክ እናስታውስ:: “ኢትዮጵያን እስከ እለተ እልፈታቸው ተሸክመው ለመኖር በራሳቸው የማሉት” እነዚህ የትውልድ ኩራቶች በጥንታዊው ግሪክ አፈ ታሪክ ውስጥ ደምቆ ከሚነገርለት ከአትላስ ጋር ይመሳሰላሉ ብንል አያስከፋም:: አትላስ በገናናው የግሪኮች አምላክ በዜውስ ጭካኔ ዓለምን ለዘለዓለም ከእነጉዳጉዷ እንዲሸከም የተፈረደበት የፈራጆቹ ቤተሰብ አባል ነበር::
ብሉዩ የግሪካውያኑ ፍልስፍና እንደሚተርክልን ከሆነ “አትላስ እስከ ዓለም ፍጻሜ ድረስ ምድራችንን በጫንቃው ላይ ተሸክሞ እንዲኖር በአማልክቱ ብይን ስለተላለፈበት ዛሬም ድረስ ዓለማችን ያለችው በእርሱ ጫንቃ ላይ ነው” ይባላል:: ምስኪኑ አትላስ “እነሆ ከዚያ የግፍ ፍርድ በኋላ የደም ላብ እያላበውም ቢሆን የተሸከመው የምድራችን ሸክም እያንገደገደው መከራውን እየገፋ ለመኖር ተገዷል” ይለናል የአፈ ታሪኩ መቋጫ:: ይኸው አፈ ታሪክ መነሻ ስለሆነም “አትላስ” የሚለው ስያሜ ለዓለም ካርታ መገለጫነት ሊውል ችሏል::
ዘለፋ፣ ትችት፣ ሴራና ጠለፋ ቢውጠነጠንባቸውም “ኢትዮጵያን ያሉ” ልጆቿ ዛሬም ሆነ ነገ ስለ ክብሯና ስለ ሕዝቧ ልዕልና ከመሟገትና የእጃቸውን ዘር ከመበተን ተሳንፈው “አጉራህ ጠናኝ” በማለት ሽንፈትን በማስተናገድ ራሳቸውን ለውርደት አይዳርጉም:: ሕልማቸውና ርዕያቸው ሁሌም አንዳች ዘለቄታ ያለው ተግባር ወይንም ቁምነገር ፈጽሞ ማለፍ ነው:: ቶድ ሄንሪ በመጽሐፋቸው ውስጥ ለመግለጽ እንደሞከሩት “ያላቸውን አንጠፍጠፈው ሳይሰጡ የመቃብራቸው በር እንደማይንኳኳ ምለዋል፤ ተገዝተዋልም::”
በዚህ የመጀመሪያ ቡድን ውስጥ የበርካታ የእውቀት ዘርፍ ባለሙያዎችና ቅን ዜጎች ስለሚካተቱና ዝርዝራቸውም የትዬለሌ ስለሆነ ጥቂቶችን ብቻ ጠቃቅሶ ማለፉ አግባብ ስላልሆነ እንዲሁ በደምሳሳው ኢትዮጵያን በልባቸው፣ በመንፈሳቸው፣ በተግባራቸውና በጥረታቸው ተሸክመው የሚቃትቱት ብዙዎች ስለሆኑ “ሞገስ ይሁንላቸው” ብለን እናጠቃልላለን:: ኢትዮጵያ ሆይ እነዚህን መሰል ልጆችሽን በእናትነት ፍቅርሽ “እንቱፍቱፍ ብለሽ” መርቂያቸው::
ሁለተኞቹ ምድብተኞች፤
በዚህ ምድብ ውስጥ የሚካተቱት ሁለተኞቹ ረድፈኞች “ኢትዮጵያ ራሷ የተሸከመቻቸው” ዜጎች ናቸው:: ወይንም ሀገራዊ ብሂላችንን እንዋስና “ከአንቀልባ እስከ ሽበት ጡጦ ተሞልቶ እንዲቀርብላቸው” የሚፈልጉ ዓይነት ዜጎች ናቸው:: የዘወትር ቋንቋቸውም፤ “እኔ ለሀገሬ ምን አደረግሁላት ሳይሆን ሀገሬ ለእኔ ምን ፈየደችልኝ” በማለት እያላዘኑ ቀናቸውን የሚገፉ ናቸው::
መታወቂያቸውም መራርነት፣ ተስፋ ቆርጠው ሌሎችንም ተስፋ ለማስቆረጥ የሚበረቱ ዓይነት ናቸው:: “ደህና ዋልክ? ደህና አመሸሽ?” የሚል ሰላምታ እንኳን ሲቀርብላቸው “ኢትዮጵያ ውስጥ እየኖሩ ምን ደህንነትና ሰላም አለ!” በማለት ተስፋን ያጨልማሉ:: ዋነኛው መለያቸው ማጉረምረም ነው:: በፈጣሪ ላይ ያጉረመርማሉ፣ በዕድላቸው ያማርራሉ፣ በሌላው ስኬት ይንተከተካሉ፣ በብራ ቀን ደመና ይጠራሉ፣ በሰላም ቀን ጦርነት ያውጃሉ…ወዘተ. ሊወክላቸው የሚችለው እንዲህ አይነቱ ገለጻ ብቻ ነው:: አብዛኛውን ጊዜ ጨለምተኝነት ስለሚያጠቃቸውም በሌላው ደስታ ከመደሰት ይልቅ የሚመርጡት ማንባትና ማስነባትን ነው:: ሁሌም ፍንትው ብሎ የሚታያቸው ፀሐያማው የሕይወት ጎን ሳይሆን ድቅድቅ ጨለማ ነው:: “የእናት ሆድ ዝንጉርጉር” ይሏል እንዲህ ነው::
ሦስተኛው ጎራ፣
በዚህ ጎራ ውስጥ የሚካተቱት “ባዕድ ባለሀገር” የሚል መለያ የሰጠናቸው ዜጎች ናቸው:: ነፍሰ ሄር ደበበ ሰይፉ እንደነዚህ አይነቶቹን ዜጎች የሚጠራቸው “ጥሬ ጨው” በማለት ነው::
“መስለውኝ ነበረ፣
የበቁ የነቁ፣ ያወቁ የረቀቁ፣
የሰው ፍጡሮች፤ ለካ እነሱ ናቸው፣
ጥሬ ጨው…ጥሬ ጨው፣
ጥሬ ጨዋዎች::
መፈጨት – መሰለቅ – መደለዝ – መወቀጥ-
መታሸት – መቀየጥ ገና እሚቀራቸው፤
“እኔ የለሁበትም!” ሁልጊዜ ቋንቋቸው::
የገጣሚው ጥበበ ቃላት በሚገባ ስለገለጻቸው ከዚህ በላይ ስለ ባዕድ ባለሀገሮች ብዙ ለማለት ያዳግታል:: ባዕድ ባለሀገርነት ክፉ ባህርይ ብቻም ሳይሆን ክፉ ደዌም ጭምር ነው – ያውም ፈውስ የሌለው እርግማን:: እንደነዚህ ዓይነት ዜጎች፡-
“እናት አባት ቢሞት በሀገር ይለቀሳል፣
እህት ወንድም ቢሞት በሀገር ይለቀሳል፣
ሀገር የሞተ እንደሁ ወዴት ይደረሳል::”
የሚለው የሀገረሰብ እንጉርጉሮ ለእነርሱ ትርጉም አይሰጥም፤ ትርጉም እንዳይሰጣቸውም ልባቸውን የዘጉና ያደነደኑ ናቸው::
ቡድን አራት – ሁለት ባላ ላይ ተንጠልጣይ ዜጎች፤
በዚህ ቡድን ውስጥ የሚካተቱ ጥቂት የማይባሉ “ዜጎች” ዋነኛ ባህርያቸው ከሌሊት ወፍ ጋር ይመሳሰላል:: የሌሊት ወፎች ሁለት ባህርይ ያላቸው ፍጥረታት ናቸው:: በአንዱ ባህርያቸው ከአእዋፍ ዝርያ ጋር ስለሚመደቡ በክንፎቻቸው ይበራሉ:: ሁለተኛው ባህርያቸው ደግሞ ከአጥቢ እንስሳት የሚመደብ ነው:: እንደ ሌሎቹ የአእዋፍ ዝርያዎች ሳይሆኑ ጫጩቶቻቸውን የሚያሳድጉት እያጠቡ ነው፤ በሽታን በማዛመትም የሚወዳደራቸው የለም:: አንዳንዶች የሌሊት ወፎች “ቫምፓየር” በመባል ይታወቃሉ:: ይህንን ስም ያገኙትም ምግባቸው ደም ስለሆነና በመናከስ ስለሚታወቁ ነው:: የፀሐይ ብርሃንን ስለማይወዱ እንቅስቃሴያቸው በሌሊት የተገደበ ነው::
የሁለት ባላ ተንጠልጣይ በርካታ ዜጎችን ይህን መሰሉ የሌሊት ወፍ ባህርይ በሚገባ ይገልጻቸዋል:: ፓስፖርታቸውን ለውጠው የሚኖሩት አብዛኛውን ጊዜ በተለያዩ ሀገራት ውስጥ መሆኑ ሌላው መታወቂያቸው ነው:: የሁለት ባላ ተንጠልጣዮች ወንድማማቾችን ማለያየት፣ የሀገርን መከራ ማብዛት፣ ውሎ አምሽቷቸውም መንግሥታዊ ሥርዓትን መቃወም፣ ለወጡበት ሕዝብ አክብሮት የሌላቸውና የተቃወሰ ሰብዕና ያላቸው ብጤዎችም ናቸው:: ስለ ኢትዮጵያ ሲነሳ አንዳችም መልካም ነገር የማይጠቅሱ፤ ቢጠቅሱም ጉስቁልናዋን በማግዘፍ የሚጮኹ ናቸው::
ሀገር መከራ በገጠማት ሰዓት እሳቱን የሚያራግቡ፣ ሀገር የተረጋጋ ሲመስል ደግሞ እየተሽቀዳደሙ በመምጣት “ከእኔ ወዲያ ላሳር” በማለት ለጥቅማ ጥቅምና ለመታየት ቀድመው ፊት የሚሰለፉ ዓይነቶች ናቸው:: በሚኖሩበት ሀገር መስፈርት መሠረትም ኢትዮጵያን እየመዘኑ አቃቂር በማብዛትና ትችት በማዥጎድጎድ የሚወዳደራቸው የለም::
በባዕድ ምድር ልክ እንደ እነርሱ የሚኖሩት የሀገር ልጆች ስለ ወገናቸውና ስለ ምድራቸው እምባቸውን፣ አንጡራ ሀብታቸውንና እውቀታቸውን ሳይሰስቱ ሲሰጡ ሲያስተውሉ ይቀናሉ ወይንም ያሰናክላሉ:: በማንኛውም የኢትዮጵያ ጉዳይ ሲከራከሩና ሲወያዩ “ከእኔ ወዲያ ላሳር” በሚል ትምክህት እብሪታቸውን ስለሚገልጹም ወዳጅም መካሪም የሌላቸው የውሃ ላይ ኩበት ይሏቸው አይነት ባይተዋሮች ናቸው::
ሀገር ለእነርሱ ማትረፊያ እንጂ ማረፊያ አይደለችም:: ስለዚህም በሁለቱ ቅርንጫፍ ባላዎች ላይ የተንጠለጠሉ ናቸው:: አንዱ ሲሰበር በአንዱ ለመንጠልጠልም ሁልጊዜ ዝግጁዎች ናቸው:: ሀገር ለእነርሱ ትርጉምም፣ እምነትም አይደለችም:: ቢችሉ በግል፣ ሲበረቱም በቡድን ሴራ “ሀገር ትፍረስ” ቢባል ቀድመው አካፋና ዶማ ለማቀበል አይሰንፉም፤ ሕሊናቸውም አይገስጻቸውም:: ቅዱስ መጽሐፍ እንደነዚህ ዓይነት ዜጎችን “ሆዳቸው አምላካቸው፤ ነውራቸው ክብራቸው ነው” በማለት ይገልጻቸዋል::
የኢትዮጵያ ማህጸን ያፈራው እነዚህን ሁሉ ነው:: “በጊት መንታ ወልዳ፤ አንዱ ለጧፍ አንዱ ለወናፍ” እንዲሉ መሆኑ ነው:: የዜግነታችን እንቆቅልሽ ተወሳሰበ ለማለት ያስደፈረንም ከሀገር አብራክ የተፈጠሩት እነዚህን መሰል ባህርይ ያላቸው “የቤት ውላጅ ልጆች” በስፋቷና በወርዷ ልክ በርክተው ስለምናስተውል ነው:: ዘላለማዊው እውነታ ግን አንድ ጉዳይ ብቻ ነው:: ትውልድ ይመጣል ትውልድ ይሄዳል:: መንግሥታዊ ሥርዓት ይወለዳል፤ ቀን ሲመሽበትም ለተረኛው አስረክቦ ያልፋል:: ቅን ዜጎች በቅንነታቸው ይቀጥሉ፤ ክፉዎችም እንደ ብጤታቸው ይንፈራገጡ፤ እናት ዓለም ኢትዮጵያ ግን ነበረች፣ አለች፣ እስከ ፍጻሜውም ትኖራለች:: ሰላም ይሁን!
(ጌታቸው በለጠ /ዳግላስ ጴጥሮስ)
gechoseni@gmail.com
አዲስ ዘመን ነሐሴ 1 ቀን 2014 ዓ.ም