መማር ለሚፈልግ ብዙ አስተማሪ ነገሮች በመጥፎም ይሁን በመልካም ጎኖች በየዕለቱ ይከሰታሉ። ምሳሌ ለማንሳት ያህልም፣ በአሜሪካ ኦሪገን በተደረገው 18ተኛ የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ላይ የተሳተፉ አትሌቶቻችን ያለምንም የዘር፣ የፆታ እና የሃይማኖት ልዩነት ሰንደቃችንን ከፍ በማድረግ አገርና ሕዝብን ከማኩራት ባሻገር፤ በውስጥ ባሉብን ፈተናዎች ተደራራቢ ጫና ምክንያት ተስፋ እንዳንቆርጥ፤ ዳግም ስለ አንድነትና ኢትዮጵያዊነት በሰንደቃችን ፊት በደስታ እንድንዘምር አድርገዋል። ውጤቱም እንደ ግለሰብም ይሁን እንደ ቡድን ለአገር ምን ያህል ኩራት መሆን እንደሚቻል ትምህርት ሰጥቶ ያለፈም ነበር።
ስለዚህም ልቡ ያልደነደነ፣ ለመደማመጥ፣ ለመነጋገር ነገን አብሮ በሠላም ለመኖር ፍላጎቱ ላለው ይህ ውድድር ብዙ ነገር ያስተምረዋል፤ ያስተምረዋልም። ምክንያቱም ይህ የአትሌቶቻችን ድል ዘር፣ ሃይማኖት ጾታ እና ሌሎች ልዩነቶችን ወደ ጎን በመተው በጋራ በመደማመጥ እና በመተጋገዝ በአንድነት ቢሠራ በዓለም ላይ በርሃብ እና በጦርነት ስሟ በተደጋጋሚ የሚጠራውን አገራችንን እንደ አትሌቶቹ በበጎ ማስጠራትም እንደሚቻል ከቃል በላይ ከፍ ብሎ የሚናገር በመሆኑ ነው። እንደ አገር ለብዙ ዓመታት የተከማቹም ይሁን በየቀኑ የሚፈጠሩ አዳዲስ ችግሮቻችን ብዙ ቢሆኑም፤ ዛሬም ድረስ የሰዎች ሞት፣ መፈናቀል፣ የሠላም እጦት ቢኖርም፣ ነገሩ ሁሉ ድቅድቅ ጨለማ ነው፤ ምንም ብርሃን የለም ብሎ መደምደም የሚቻልበት ደረጃ ላይ የሚያደርሱን አይደሉም። ይህ ደግሞ መልካም አጋጣሚ ነው። ይህንን ዕድል ያላገኙም ብዙ አገራት መኖራቸውንም ማስታወሱ ተገቢ ነው የሚል እምነት አለኝ።
በመሆኑም የነገ ተስፋዎቻችን ላይ አተኩሮ መሥራትን ከምንም ነገር በላይ ቅድሚያ የምንሰጠው ጉዳይ መሆንም አለበት። የሕዳሴ ግድባችን መጠናቀቅ ነገን በተሰፋ እንድንጠብቅ እና ነገን አሻግረን እንድንታገስ አድርጓል።ይህ ተስፋችን ግን በቀላሉ የተገኘ አይደለም። ብዙዎች ስለ ነገ አገራቸው መፃኢ ዕድል ሲሉ ሕይወታቸውን ገብረዋል፣ ብዙዎች ያላቸውን ጥሪት አሟጠው የአቅማቸውን አድርገዋል። በተቃራኒው ግን ጎረቤት አገራትም ይሁኑ የውስጥ ጠላቶቻችን በነገ ተስፋችን ላይ ውሃ ለመቸለስ ዛሬን ሳይተኙ ነጋችንን እንዲጨልምብን በዓለም አደባባይ እስከመክሰስ ደርሰው በብርቱ እየለፉ እና እየደከሙ መሆኑን በመገንዘብ ከምንም ጊዜም በላይ በአንድነት በመቆም ግድባችንን ማጠናቀቁ ችግሮቻችንን በብዙ ለመፍታት ዕድሉ ሰፊ ነው።
የሁለት ወንድማማቾች ጸብ ችግሩ ለቤተሰብ ነው። ምክንያቱም ፀቡ ጎራ ከፍሎ ከሁለቱ ከፍ በማለት ቤተሰብ እንዲበተን ዕድሉን ይፈጥራል። ይህ ሲሆን ደግሞ በቤተሰቡ መበተን የሚከፋና የሚያዝን ወገን ዘመድ ብሎም ጎረቤት እንዳለ ሁሉ፤ ለክፉ ጎረቤት ደግሞ ደስታ መሆኑ አይቀሬ ነው። እንደውም በገላጋይ ሰበብ ውጋው በለው እያለ ጦር የማማዘዙን ሥራ በደስታ እንዲወጣ ዕድሉን ያመለቻችለታል። በአንጻሩ ሁለት ወንድማማቾች ፍቅርን ከፍ አድርገው ፀባቸውን በእርቅ ለመቋጨት መሰናዳት ደግሞ ለቤተሰብ ደስታን፤ ለወዳጅ ዘመድ ሀሴት የሚያጎናጽፍ ሲሆን፤ ከክፉ ጎረቤት ደግሞ የመርዶው ያህል ነው።
በኢትዮጵያችን እየሆነ ያለውም ይሄው ነው። በወንድማማች ሕዝቦች መካከል በሚፈጠር ጸብ የሚጎዳው መላው ሕዝብ እና አገር ናት። በወንድማማች ሕዝቦች መካከል በሚፈጠር እርቅም የሚጠቀመው መላው ሕዝብና አገር ናት። በአንጻሩ ከፀባችን ጠላት ሲያተርፍ፤ ከእርቃችን ደግሞ የሴራ ሕልሙ ይጨነግፋል። ስለሆነም በመካከላችን የሚፈጠረው እርቅ የነገ ተስፋችን ነው። አንዱ አንዱን ለመወንጀል ከመሥራት ይልቅ እንዲህ ስለ ሰላም ቅድሚያ ሰጥቶና ስለ ሕዝብ ጥቅም ቅድሚያ ሰጥቶ መጓዙ ለሁሉም የሚበጅ መንገድ ነው። ምክንያቱም ለእርቅ ለሠላም እጅን መዘርጋት እንጂ መፈራረጁ አያዋጣም። ይሄን በመገንዘብ በወንድማማቾች መካከል ፍቅር እንዲወርድ የተቻለውን ሁሉ ማድረግ፣ አስፈላጊውን ዋጋና መስዋዕትነት መክፈልም የሚያከስር አይደለም። ሌሎች ባለድርሻ አካላትና አጋሮችም ስለ ሰላም ሲሉ የማወያየትና ማግባባቱን ሚና በገለልተኝነት መወጣት ይጠበቅበታል። በተጨማሪም በወንድማማቾች በኩል ጸብን ሊዘራ የሚኳትነውን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ማሳፈር እና መዋጋት ይገባል።
በመንግሥት፣ በሕወሓት፣ በዓለም አቀፍ ድርጅቶች እና በሌሎች ተቋማትም ለእርቅ ያለው ፍላጎትም ልብን በተስፋ የሚሞላ ሲሆን፤ ከጸብ ምንም ያተረፍነው ነገር አለመኖሩን በማጤን ነጋችን በሠላም የተሞላ እንዲሆን፣ ዜጎች ያለምንም ፍርሃት በመተማመን እርስ በእርስ ተከባብረው እና ተዋደው የሚኖሩባት አገርን እውን ለማድረግ ከሊቅ እስከ ደቂቅ የተቻለውን ማዋጣት ይኖርበታል።
ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ፣ የውጭ አገራት የእኛን እርቅ መፈለግ እሰየው የሚያስብል ነው። በትግራይ ክልል በጦርነቱ ምክንያት የደረሰውን ጉዳት ተረድተውና ሰብአዊነት ተሰምቷቸው ስለ ሰላም ብቻ በማሰብ የሚያደርጉትም ድጋፍም ካለ የሚያስመሰግናቸው እንጂ የሚያስተቻቸው አይሆንም። ይሁን እንጂ በእኛ መሃል የተፈጠረውን ጸብ ለማርገብ ከእኛ በላይም ሲደክሙ ሲጥሩ እና ሲለፉ መታየታቸውን ለተመለከተ ‹ግን ለምን?› ማስባሉ አይቀርም። ምክንያቱም አንዳንዶቹ በሰሜኑ ጦርነት ላይ ጦርነቱን መቀጣጠል ሚናቸው እስከምን ድረስ እንደነበር መዘርዘሩ ለቀባሪው እንደማርዳት ያለ ነው። የቤተሰብን ጸብ ቤተሰብ በሚገባ ያውቀዋልና እንደ ባህላችን እንደ አኗኗራችን ችግራችንን በራሳችን ለመፍታት መሞከሩም ብልህነት ነው። አገራችን በርካታ የእርቅና የይቅር መባባያ ሥርዓቶች ያሏት እንደመሆኗም የአገር ሽማግሌዎች ተሰሚነታቸውን ከግምት ውስጥ በማስገባት በሽምግልና ሥራቸው የነገው ትውልድን ሊታደጉት ይገባል።
‹ያልጠረጠረ ተመነጠረ› እንደሚባለው፣ በአሸማጋይ ስም ከላይ ታች የሚሉትን ምዕራባውያን፣ አንድ ነገር ማድረግ ሲፈልጉ ቅድሚያ የራሳቸውን ጥቅም እንደሚያስቀድሙ የምናውቀው ጉዳይ ነው። እናም ሠላምን ለማምጣት የሚደረገው መንገድ ንጹህና ከተንኮል የጸዳ መሆኑን በጥንቃቄ ማየት እና መመርመር አስፈላጊ ጉዳይ ይሆናል።
እንደ አጠቃላይ ዛሬ የነገ ድምር ውጤት መሆኑን በመገንዘብ፣ እንደ አገር መቅደም ያለባቸውን ጉዳዮች በማስቀደም፣ ዛሬን መሥራት ከዚህ ትውልድ ይጠበቃል። በዚህም ችግሮች አሁን ላለው ትውልድ እንቅፋት፣ ለመጪው ትውልድም ሸክም እንዳይሆኑ ማቅለል፤ ስለ ሰላም ሠርቶም ሠላማዊ አገር እንድትኖር ማድረግ የሁላችንም የዛሬ የቤት ሥራ ሊሆን ግድ ነው።
በምስጋና ፍቅሩ
አዲስ ዘመን ነሐሴ 1 ቀን 2014 ዓ.ም