እንደ ወትሮው ገና በማለዳው አካባቢው በሰው ተጨናንቋል፤ በበረከተ ጩኸት ውስጥ ሆነው በተሰበሰቡ ሰዎች:: የዛሬው ለየት የሚያደርገው ሁሉም ሰው አንድን ሰው ከብቦ የቆመ መሆኑ ነው:: ለወሬ ሁሉም ጠጋ እያለ የተከበበውን ሰው ለማየት ይሞክራል፤ እርሱ ግን አያይም:: ግለሰቡ ሕይወቱ አልፏል:: ሁሉም እየዘገነነው ይመለሳል:: በድብደባ የተገደለ ሰው ነው፤ የአካባቢው ሰው:: ፖሊስ አካባቢውን ተቆጣጥሮ የምርመራ ሥራውን ለመጀመር እየተጠበቀ ነው:: መንገድ ላይ ስለወደቀው ሰው ሁሉም የየራሱን መላምት እየሰጠ ነው፤ የሚጠቅምም ሆነ የማይጠቅም ጩኸትን እያሰማ:: መላምት ለማቅረብ ማንም ችግር ያለበት በማይመስል ሁኔታ መላምቱ እንዲህ እየተሰማ ቀጠለ፤
አንዳንዱ “ሲሰርቅ ተገኝቶ ነው” ይላል:: እውነት ነው ስርቆት አስከፊ ነገር ነው:: በስርቆት ምክንያት ሕይወታቸውን ያጡ ይኖራሉ:: ሌባውም ሆነ ተሰራቂው ሕይወትን ያጡበት አጋጣሚ ጥቂት አይደለም::
ሌላው “ሰክሮ ሲደባደብ ነው” ይላል:: መጠጥ የፈጠረው ችግር እንዲሁ ለማንም ግልጽ ነው:: አንድ ሰሞን የቢራ ማስታወቂያ ሰማይ ምድሩን ባጥለቀለቀበት ወቅት በግራም በቀኝም ሰካራም መመልከት የተለመደ ሆኖም ነበር:: ስካር ለብዙ ነገሮች ችግር ምክንያት መሆን እስኪችል ድረስ ብዙ እርቀት የሚወስድ በሽታ ነው:: ራስን መቆጣጠር የሚያስችል ሳይሆን ቀርቶ በብዙ የሚያደክም::
ሌላው “ራሱን በራሱ ጎድቶ ነው” ይላል:: ራሱን በራሱ መጉዳት የፈለገ ሰው መቼስ አደባባይ መጥቶ የማድረግ እድሉ አነስተኛ ቢሆንም መላምቱ ግን ሊሆን የማይችልበት እድል አልነበረም:: በሕይወት ጉዞ ውስጥ አቅጣጫ ሲጠፋ ራስን መጉዳት ውስጥ የሚገቡ ሰዎች ጥቂት አይደሉምና ይህን ያለው ሰው አንዳች ፍንጭ ይኖረው ይሆናል::
ሁሉም የየራሱን መላምት እያቀረበ ወደየአቅጣጫው ይሰማራል:: ተረኛው ሰው እንዲሁ ቦታውን ከቦ ሁኔታውን ተመልክቶ መላምቱን ያስቀምጣል::
ያልተደመጠው ሰው
በወከባ ውስጥ በሆነች ዓለም ውስጥ ስንኖር ራስን ለማድመጥ ጊዜ አለመስጠት በሰፊው ይስተዋላል:: በአጭሩ ያለንበት ዘመን “የመርካት አለመርካት” ተቃርኖ ዘመን ነው ልንል እንችላለን:: በአንድ በኩል ሕይወትን ለማቅለል የሚረዱ እርካታን የሚፈጥሩ የበዙ ጥረቶች የሚደረጉበት ሲሆን በሌላ በኩል ደግሞ በተቃራኒው የውስጥ እርካታ ጥፋት የሰዎችን ሕይወት ትርጉም አልባ ያደረገበት:: በዚህ መካከል ራስን ፈልጎ ራስን ማድመጥ የተረሳበት:: ‘የሰው ልጅ ከእዚህ በኋላ እንዴት በቴክኖሎጂ ሊያድግ ይችላል?’ ተብሎ እስኪታሰብ ድረስ ቴክኖሎጂው አስደማሚ ሆኗ ከአንድ የአለም ጫፍ ወደ ሌላኛው የዓለም ጫፍ በምስልም በድምፅም መገናኘት መደማመጥ አስችሎ በውስጣችን ያለውን እኛን ግን ማድመጥ ያልቻልንበት::
አንድ እቃ ከአንድ አቅጣጫ ወደ ሌላ አቅጣጫ ለመውሰድ ትርጉም ባለው ሁኔታ አሠራሩ የተቀየረበት ቢሆንም ያልተደመጠውን ሰው ከአንድ የሀሳብ ከፍታ ወደ ሌላው ከፍታ ከመውሰድ ይልቅ ወደ ታች መጣል የተለመደ ሆኗል:: የእኒህ ነገሮች ድምር ውጤት የሰውን ልጅ አኗኗር በመሠረታዊ ደረጃ በአወንታዊ መልኩ የቀየሩት መሆኑን ብንረዳው ራስን በመግዛት፣ ራስን በማጥመድ፣ እንረዳለን:: ነገር ግን በውስጣዊ እርካታ ማጣት የሚበላሸው በዝቷል:: ራስን ማድመጥ ካለመቻል የሚነሳ ህመም::
ሰው ወደ ውስጡ መመልከት እንዳይችል የሕይወት ዘይቤን ከፈጣሪ በማዞር ወደ ራስ ለማድረግ የሚደረገው ትግል ከፍተኛ ነው:: የሰው ልጅ በፈጣሪ ላይ የሚያደርገውን መደገፍ እንደ ደካማነት በመቁጠር በራሱ ያለፈጣሪ ለመቆም የሚያደርገው ሙከራን አስተውለናል:: ‘ተፈጥሮን በቁጥጥር ስር እናደርጋለን’ በሚል አመለካከት ለፈጣሪ ጀርባን ለመስጠት የተሄደባቸው ዘመኖችም እሩቅ አይደሉም:: የሰው ልጅ በዚህም ተባለ በእዚያ የውስጥ እርካታው ጉዳይ ሚዛን ላይ ሆኖ መፍትሔን በሚሻበት ወቅት ላይ ሆኖ ሰሚ ስላጡ ድምፆች እናስባለን:: ከሁሉ ስለሚቀድመው ለግለሰቡ የራሱ ድምጽ::
የሌሎቹ ጩኸት
ከሰሞኑ በወለጋ የሆነው ነገር እንደ ሀገር ሁላችንንም አንገት ያስደፋ ነው:: ከሞት ጋር የሰው ልጅ እንደ ቀላል እንዲገናኝ ያደረገ ስብራት:: ያልተደመጡ ድምጾች በሞት ሜዳ ውስጥ:: በጭንቅ ላለችው ነፍስ የሚያደምጥ ቢገኝ ምንኛ እፎይታን ታገኝ ነበር:: በሞት ጥላ ውስጥ ለሚያልፉ የሚታደግ አካል ኮቴ ትርጉሙ ምን ያህል ይሆን:: ጆን ማእክስዌል የተባለው ፀሐፊ አንድ ጥያቄ ይጠይቃሉ እንዲህ በማለት፤ “ከአሜሪካ ተጽእኖ ፈጣሪ ሰዎች መካከል ዝርዝር ብትባል የማንን ስም ትጠቅሳለህ? ፕሬዚዳንቶቹን ትጠቅስ ይሆን? ወይንስ ማይክል ጆርዳንን? ወይንስ ቢል ጌትስን? እኔ ግን በዝርዝርህ ውስጥ ኦፕራ ዊንፍሬን እንድትጨምር እጠይቅሃለሁ::” ይላሉ:: ስለ ኦፕራ ሲጽፉም “ በ1985 እ.አ.አ ኦፕራን በተግባር የማትታወቅ ተራ ዜጋ ነበረች:: በቺካጎ አካባቢ ስርጭት ባለው የጠዋት ሾውን በመምራት ለአንድ ዓመት ወደ መድረክ ስትወጣ ትኩረት መሳብ ጀመረች:: የእርሷ ስኬት ጀርባ ያለው ጉዳይ የመናገር አቅሟ ጥሩ መሆኑ እንደሆነ በብዙ ሊታሰብ ይችላል፤ በእርግጥ ትክክል ነው:: በልጅነት ወቅት ማለትም የሁለት ዓመት ልጅ እያለች በቤተክርስቲያን መድረክ ላይ ንግግር አድርጋ ምእመናኑ ጥሩ ተናጋሪ ነሽ ብለዋት እንደነበር ታስታውሳለች:: ነገርግን ከመናገር በላይም የማዳመጥ አቅሟም ትልቅ ነው::
ከዘወትር ልምዷ መካከል ዋናው ለመማር ያላት ፍላጎት ነው:: የጸሐፊያንን ጥበብ በንባብ ውስጥ እንደሚገኝ በማዳመጥ ውስጥ በሰዎች ውስጥ ያለውን ጥበብ ለማግኘት ትወዳለች:: ሰዎች እንዴት እንደሚያስቡና እንደሚሰማቸው ለማወቅ ልብወለድ መጽሐፍትን፣ የግለታሪኮችን ወዘተ ለማወቅ ትጥራለች:: የአድማጭነት አቅሟ የሥራዋን መስመር አሳድጎታል:: በተግባርም በቴሌቪዥን መስኮት የምታቀርበውን ፕሮግራም ተወዳጅነት ጨምሮታል:: ጉዳዮቹን ለአየር ለማብቃት በተከታታይነት ነገሮችን መመልከት እና ማድመጥ ትወዳለች:: ወደ ፕሮግራሙ የምታቀርባቸውን ባለሙያዎች፣ ጸሐፊዎች፣ አርቲስቶች በትኩረትና ከውስጥ በሆነ መስማት ታደምጣቸዋለች:: ኦፕራ ባላት የአድማጭነት አቅም ተጽዕኖ ፈጣሪ ሰዎች ተርታ እንድትሰለፍ ሆናለች::
እርሷ የዓለማችን ከፍተኛው የመዝናኛ ዘርፍ ተከፋይ ባለሙያዎች ተርታ ትመደባለች፤ ግማሽ ቢሊዮን ዶላር የሚገመትም ሃብት አላት:: በአሜሪካ ብቻ የሳምንቱ ሰላሳ ሦስት ሚሊዮን ሕዝብ የእርሷን የቴሌቪዥን ፕሮግራም ይከታተላል::” በማለት የኦፕራን የማድመጥ አቅም ይናገራሉ::
ኦፕራ ያደመጠቻቸው በሞት ዋዜማ ላይ ያሉትን አይደለም:: በድረሱልን ጩኸት ውስጥ ያሉ አይደሉም:: ነገርግን በመደበኛ ሕይወታቸው ውስጥ ሆነው መደመጥን የሚፈልጉ:: መደመጥን ከዚህ ከፍ አድርገን በአደጋ ባለ ሰው ሕይወት ውስጥ ሆነን ስንመለከት የሚገባን ትልቅ ነው:: አቅማችንን አይተን ፈጽሞውኑ ወደ ኋላ እንድንል የማ ያደርጉ ድምፆች::
አቅሜን ሳየው
አዎን አቅምን ማወቅ ጥሩ ነው:: ነገር ግን ከአቅም በላይ መሄድ የሚገባበት ወቅት ግን አለ:: ሁሉንም በምቾት ቀጠና ውስጥ ሆነን በአቅማችን ልክ ካልን ትርጉም የማይሰጥ ሊሆን ይችላል:: ከቃላት ተግባቦት ወደ ትርጉም ያለው የሕይወት ተግባቦት::
በተግባቦት ትምህርት ውስጥ መደማመጥ ያለውን ትልቅ ቦታ እንረዳለን:: ከመናገር በፊት ማድመጥ መቻል እንደ ብልሃትም ይወሰዳል:: ብዙ የሚያደምጥ ብዙ ከሚያወራም በንግግሩ ከሚመጣ አደጋም የተጠበቀ መሆኑ ግልጽ ነው::
አቅምን ማየት መቻል “ማንን እናዳምጥ?” የሚለው ጥያቄ በአግባቡ እንድንመልስ እድልን ይሰጠናል:: ራሳችንን ባለብን ኃላፊነት ውስጥ ሆነን ዙሪያችንን ስንመለከት ማንን ማድመጥ እንዳለብንም እንድንወስን ያደርገናል:: በተግባር ሁሉንም ሰው ማድመጥ አንችልም፤ ለሁሉም ችግር የመፍትሔው መንገድ እኛ ጋር አይገኝ ይሆናል:: ነገርግን ከኃላፊነት የሚመነጭ አድማጭነት የግድ ሊደመጡ የሚገባቸውን አካላት እንድንለይ ግን ያደርገናል:: ከኃላፊነት የሚመነጭ አድማጭነት እርሱ ውጤታማ አድማጭነት ነው:: የተግባር እርምጃ ወደ ሚጮኸው እንድናደርግ የሚረዳ::
የተግባር እርምጃ ወደሚጮኸው
እኛ ባለንበት እና በሚጮኸው መካከል ያለው ክፍተት የሚሞላው በተግባር እርምጃ ነው:: የተግባር እርምጃ በሁለቱ መካከል ያለውን ክፍተት ይሞላል:: ክፍተቱን ለመሙላት ስንነሳ ለተገፋው ድምጽ እንሆናል፤ ለተራበው ምግብ፤ ለታረዘው ልብስ፤ ወዘተ::
በውስጠኛው ልብ ማድመጥ – የበዛ ጩኸት ባለበት ሁኔታ መፍትሔ ለመፈለግ የመጀመሪያው የተግባር እርምጃ በውስጠኛው ልብ ማድመጥ መቻል ነው:: ትኩረት መስጠት ለብዙ ነገሮች አስፈላጊ ነው:: መዘንጋት የሌለብን ነገር ግን ባለንበት ዘመን ትኩረት የሚነጥቁ የበዙ ነገሮች ያሉ መሆኑን ነው:: ትኩረትን የሚነጥቁ ነገሮች ባሉበት ሁኔታ በተበታተነ ትኩረት ውስጥ ማድመጥን በተግባር ማድረግ አስቸጋሪ ነው:: ማድመጥ ውጤታማ መሆን እንዲችል ልብንና ጆሮን እኩል መስጠታችንን እርግጠኛ መሆን አለብን:: ሰዎች ሁካታ በሌለበት ድባብ ውስጥ የተሰማቸውን ለመናገር ይበረታታሉ በአግባቡ በመደመጣቸው ውስጥም ደስታን ያገኛሉና ልብንና ጆሮን እኩል በመስጠት ውስጥ እንዲሆን ማድረግ ወሳኙ የተግባር እርምጃ ነው፤ እርሱም በውስጠኛው ልብ ማድመጥ:: በትኩረት ውስጥ ስንሆን አጀንዳ ተኮር፣ መረጃ ተኮር ወይንም የሆነ ይዘት ተኮር ሆነን ሙሉ ትኩረታችን ጉዳዩ ላይ ይሆናል:: ከእዚህ በተጨማሪ ግን ስሜት ተኮር የሆነ ድባብን ይፈጥራል:: ለመደመጥ አስፈላጊ የሆነ፤ በውስጠኛው ልብ::
መገኘት በስፍራው – የተራበውን ሰው የሰለለ ጩኸት ለማድመጥ ራስህን በቦታው ላይ ውሰድ:: ጊዜ ውድ የሆነበት ጊዜ የተረፈ መሆኑን በሚያሳብቅ በተቃርኖ ዘመን ውስጥ አለን:: ሰዎች በማኅበራዊ ሚዲያ ትርኪምርኪ ሲቃርሙ የሚውሉበትን ሁኔታ ስናይ ጊዜ ተረፈ እንላለን፤ ለመልካም ነገር እርስበርስ ለመደማመጥ ጊዜ ሲጠፋ ደግሞ የተቃርኖውን ሌላኛውን ገጽታ እናገኛለን:: ወደ ታች ወርዶ ስለ መፍትሔ ለመስራት የሌለው ጊዜ ለትርኪምርኪ ግን በብዛት ቀርቦ የሚታይበት:: ቤተሰብህን፣ ተከታዮችህን፣ ደንበኞችህን፣ ተፎካካሪዎችን እና የግል-መካሪህን ለመስማት ጊዜ ትመድባለህ? እርሱ በስፍራው የመገኘት ማሳያ ነው:: እኒህ አካላት በመደበኛነት በካላንደርህ ውስጥ ከሌሉ ለእነርሱ ትኩረት አልሰጠህም፤ ጩኸታቸውም ከጩኸትህ ጋር የተገናኘ አይደለም ማለት ነው:: በየእለቱ፣ በየሳምንቱ ወይንም በወር ውስጥ ከእነዚህ ጋር የምትገናኝበትን ጊዜ አስቀምጥ:: ይህን ማድረግ ለማድመጥ የሰጠኸውን ቦታ ያሳያል:: ስለሆነም ሁለተኛው ተግባራዊ እርምጃ ዛሬውን ልታደምጣቸው ለተገቡት ጊዜ መመደብ ነው፤ እርሱም መገኘት በጩኸታቸው ስፍራ::
እኔ ብሆን – በጦርነት ቤተሰቡ የተበተነ ሰውን ጩኸት ለመስማት ቀላሉ ጥያቄ እኔስ ብሆን ብሎ መጠየቅ ነው:: አድማጭነትን ተቀብለህ በጊዜ ሰሌዳህ ላይም መድበህ ያንን ሰው ስታገኘው በእርሱ ጫማ ውስጥ በተግባር መሆን እንድትችል እኔ ብሆን ብለህ ጠይቅ:: ለተግባር እርምጃ የሚረዳህ መንገድ ስለሆነ:: ይህን ለማድረግ ልታደምጠው የሚገባውን ሰው ከግንኙነታችሁ በፊት አስበው፤ስለ እርሱ ልትሰበስብ የምትችለውም መረጃ ይኑርህ:: ጥሩ አድማጭ የመሆን ቁልፉ የጋራ መቆሚያ ቦታን ማግኘት መቻል ነውና ቦታው ላይ ድረስ:: ግለሰቡን ለማወቅ በምታደርገው ጥረት ውስጥ የጋራ መቆሚያ ቦታን ማግኘት ትችላለህ:: በተጨማሪም በሚኖርህ ግንኙነት ወቅት ከግለሰቡ ራሱ በመጠየቅ በሰውዬው ጫማ ውስጥ መሆንን ልትለመድ ትችላለህ::
ከኃላፊነት ለሚመነጭ በመከተል ደግሞ ከሰውነታችን በሚመነጭ ለሚቀርቡልን ጩኸቶች የምንሰጠው ምላሽ መዳረሻው ለሚጮኸው አካል እፎይታ ብቻ ሳይሆን የእኛን እምቅ አቅም ማውጣት የሚያስችል ነው:: ለችግር መፍትሔ በመሆን ውስጥ የሚገኝ እድል::
እምቅ አቅምን ማውጣት መቻል
በዙሪያችን ላሉ ጩኸቶች ምላሽ ለመስጠት ስናስብ አቅም የለንም ብለን እናስባለን፤ ነገርግን አቅማችንን አሰባስበን በተዘረጋን ጊዜ አቅማችን እየጨመረ ይሄዳል:: ሰው እምቅ አቅሙን በአግባቡ ማውጣት የሚችልበት እድልን ቢያገኝ ውጤታማ መሆኑ ጥርጥር የለውም:: እንደ ኢትዮጵያ ባሉ የወጣት አገር ውስጥ እምቅ አቅምን ማውጣት አለመቻል ከሀገር እድገት አንጻር ያለው ኪሳራ በቀላሉ የሚታይ አይደለም:: የሰው ኃይል አንዱ የኢኮኖሚ ማሳለጫ ግብዓት በመሆኑ እምቅ አቅምን ወደ ውጤት መቀየር የመቻል አካሄድ ትርጉሙ ላቅ ያለ ነው:: ጠንካራ የሰው ኃይል ሲኖር ሌላውን የኢኮኖሚ ማሳለጫ ካፒታልን፣ መሬትን እንዲሁም ቴክኖሎጂን የሚያንቀሳቅስ ሆኖ እናገኘዋለን::
እምቅ አቅማችን እንዲወጣ የሚችለው ለመፍትሔ በተዘረጋንባቸው አጋጣሚዎች ነው:: ያን አጋጣሚ ዛሬ ያለበት የምቾት ቀጠና መዳረሻችን አድርገን ልንይዘው አይገባም:: በመሆኑም እምቅ አቅማችንን ለማውጣት ስናስብ ለጩኸቶች ምላሽ መስጠትን እናስብ:: በመገፋት ምክንያት እምቅ አቅማቸውን የሚገድሉትን አይተን ይሆናል:: ጆን ስትሪልንግ የተባሉ ሰው እንዲህ አሉ “ኃዘን የራሱ የሆነ ውድ የሆነ ሐሴት ነው፤ መንቀሳቀስ ሲጀምር ጠንካራ የሆነ የሕይወት ውስጣዊ ክፍል መንቀሳቀስ ይጀምራል::” ብለዋል:: መፍትሔን አስበን የተመለከትነው ኃዘን ወደ ተጨማሪ አቅም የሚያደርሰን ነው::
አንባቢ ሆይ እምቅ አቅም የሌለው ሰው የለም:: ሁሉም ሰው ሊወጣና ሊመነዘር የሚችል እምቅ አቅም አለው:: አቅሙን እንዴት ባለመንገድ ማውጣት እንዳለበት መረዳት አይኖረው ይሆናል እንጂ አቅም ሳይኖረው የሚኖር ሰው የለም:: ኃዘን ከሌለ ዘምባባ የለም፤ ወጀብ ከሌለ ዙፋን የለም፤ የሚያበሳጭ ሳይኖር ክብር የለም፤ መስቀል ሳይኖር አክሊል የለም ብለን ስናስብ የሚገጥመን እያንዳንዱ መገፋት ወደ ተሻለ ነገር ሊያስገባን ዋዜማው ላይ እንዳለን እንረዳለን::
በመነሻችን ላይ የተመለከትነው ግለሰብ ዙሪያ እንደሚሰማው መላምት ዛሬም ስላለንበት ጩኸት ብዙ መላምት አለው፤ ዋናው ነገር ከመላምት ባሻገር ለመፍትሔ የሚሆን እርምጃን መራመድ ነው::
ጩኸት ሲበረከት የራስህን ጩኸት አስቀድመህ አድምጥ፤ የሌሎችንም ጩኸት አትርሳ፤ አቅሜ ውስን ነው ብለህ አትቀመጥ፤ የምትችለውን በማድረግ ውስጥ ስትዘረጋ ስለ አንዲቱ ነፍስ ትርጉም ያለው ተጽእኖ ይዘህ ትገኛለህ፤ መዳረሻውም እምቅ አቅምህን እያወጣህ የበለጠ መፍትሔ መሆን ወደ ምትችልበት ምዕራፍ::
በአገልጋይ ዮናታን አክሊሉ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 30/ 2014