የአመቱ አስራ ሁለተኛው ወር ነሃሴ ከክረምቱ ጋር ተያይዞ ብርዱ አንትን ያሳቅፋል እሚያስብል አይነት ነው። በነጩ ከያዘው ችፍ ችፍ ከሚለው ዝናብ ጋር ተደምሮ ቅዝቃዜው ከቤት መውጣት ከልክሏል፤ አትውጡ አትውጡ የሚለው አየር እጅ እግር ቀፍድዶ ይዟል። እምብዛም ከእናቱ ጉያ መውጣት የማያስደስተው ወጣት እንኳን እንዲህ ያለ ቀን አግኝቶ ወትሮም የቤታቸው መድመቂያ ጌጥ ነበር። ያን እለት ከሰል ተያይዞ ቡናው፤ ቦቆሎ ጥብሱ፤ ትኩስ ሽሮው ባጠቃላይ ሰውነትን ሞቅ ሞቅ የሚያደርጉ የክረምት ምግቦች በየተራ ሲሰለፉና ከእናቱ ጋር በፍቅር ሲቋደስ ነበር የዋለው።
ለቤተሰቡ ታዛዥ፤ ቤተሰብ አክባሪና ስራ ወዳድ ነው። ለትምህርቱ ቅድሚያ የሚሰጥ አመለ ሸጋ ወጣት በአመቱ የመጨረሻ የሚባለው ወር ላይ ቆሞ አዲሱን አመት በተስፋ ይጠብቃል። ከጓኞቹ ጋር ተገናኝቶ ሊጨዋወት ደግሞ በአዲሱ የትምህርት ዘመን አዲሱን ትምህርት ሊማር በራሱ አእምሮ ዝግጅቱን ቀጥሏል። የነገን ብሩህ ቀን በጉጉት የሚያይ ለእናቱም አንዳንዱን ሀሳብ ያጋራቸዋል። እሳቸውም በልጃቸው በጎ አሳቢነት እየተደሰቱም የእናትነት ፍቅራቸውን ይገልጹለታል። ይሄ ለአንተ አይገባም አይሆንም የሚሉትንም ምክር በመለገስ ልጃቸው የቤተሰቡን ባህሪ ተላብሶ ጎበዝ ተማሪ ሆኖ እንዲያድግላቸው ይተጋሉ። የእናትና የልጅን ትስስር የተመለከተ ከአይን ያውጣችሁ በሚል ምርቃት እንትፍ እንትፍ የሚልላቸው አይነት ናቸው ። ዛሬም እናትና ልጅ ተጣብቀው ነበር የዋሉት። ቀኑን ሙሉ ሲዘንብ የዋለው ዝናብ አመሻሹ ላይ ጋብ በማለቱ ከጉያቸው ተወሽቆ የዋለውን የአይናቸው ማረፊያ የሆነውን ልጅ እስኪ እቁብ ከፍለህ ና ብለው ላኩት። ታዛዡ ልጅም አላቅማማም። የእናት መልዕክት ነውና ደስ ብሎት ተቀበለ። ፈጣን ብሎ ሰጥቶ ወደ ቤቱ ሊመለስ።
ነሀሴ ወር 1998 ዓ.ም ምሽት ላይ፤ አዲስ አበባ አፋር ኬክ ቤት አካባቢ ከፒያሳ ወደ ሰይጣን ቤት በሚወስደው ቁልቁለት መንገድ ላይ የክረምቱ ዝናብ መውጫ መግቢያ አሳጥቶት የዋለው አዲስ አበቤ በየካፌውና በየሬስቶራንቱ ተጠልሎ ቆይቶ ዝናቡ ጋብ ሲልለት ነው ወደ አስፓልቶቹ ወጣ ያለው። በአንፃሩ ሌሎች በየቤታቸው ተቀምጠው የነበሩ ወደ ካፍቴሪያዎች ሞቅ ላለ ሻይ ጎራ ብለዋል። ጭር ያለው የክረምት ቀን ወደ ምሽቱ አከባቢ ደመቅመቅ ያለ ይመስላል።
ወጣት ስዩም የሀያ ሰባ አመት ወጣት ነው። ያን እለት ከእናቱ ጋር ነበር ቤት ውስጥ የዋለው። ወደ አመሻሹ ላይ ሲወጣ እቁብ ክፈል ተብሎ የተሰጠውን አንድ ሺ ብር ይዞ ነበር። እቁብ ለመክፈል የተላከው ልጅ እግር መንገዱን ወደ አፋር ኬክ ቤት ጎራ ይላል። ከሞቀ ቤቱ የወጣው ስዩም የደጁን ቅዝቃዜ ለመቋቋም ሻይ ለመጠጣት ነበር ወደ ኬክ ቤቱ የገባው። የስዩም ሰፈር እዛው አካባቢ ነው፤ ቴዎድሮስ አደባባይ አካባቢ ከሚገኙ ቀብር አስፈፃሚዎችና የመቃብር አበባ ሻጮች በዛ ብለው የሚታዩበት ስፍራ። የመቃብር አበባ የሚሸጥበት አከባቢ በመሆኑ የሰፈሩ ስምም በተለምዶ አበባ ሰፈር በማለት ይጠራ ነበር።
ስዩም ከአካባቢው ልጆች ጋር ጥሩ ግንኙነት የነበረው ቢሆኑም ብዙዎቹ የግሩፕ ፀብ የሚወዱ በመሆናቸው ብዙም ሊጠጋቸው አይፈልግም ። የዚህ ወጣት ስራ መማር፤ መስራት፤ ህይወቱን በአግባቡ መምራት ብቻ ነው። ለእያንዳንዱ ነገር ትኩረት የሚሰጥ ህይወቱን በጥንቃቄና በእቅድ የሚመራ አስተዋይ ባለ ራእይ ወጣት ነበር።
ከካፍቴሪያው ሻዩን ጠጥቶ ሲወጣ ከሶሰት የሚበልጡ ወጣቶች ቆመው አያቸው ፤ አያውቃቸውም። እነሱ ግን የሚያውቁት መስለው በአትኩሮት ይመለከቱታል። እሱ ግን አስተያየታቸው አላማረውም። ከምሽቱ ሁለት ሰአት ሆኗል። ቆም ብሎ በስጋት መልከት አላቸው።
ከዛ አንደኛው ̋ና ወደዚህ ̋ አለው። ስዩም ከቆመበት ሳይነቃነቅ አካባቢውን ቃኘት አደረገ። ብዙ ሰው የለም ፈራ። የጠሩት በሰላም እንዳልሆነ ገብቶታል። ነገር ግን አማራጭ አልነበረውም እና ተጠጋቸው። አጠገባቸው ከደረሰበት ደቂቃ ጀምሮ መጨረሻ እስከሆነው ነገር ድረስ ያዩ ሰዎች ነገሩን ለፖሊስ እንዲህ አስረድተዋል።
ስዩም ለጥሪያቸው ምላሽ ከመስጠት በስተቀር አማራጭ ስላልነበረው ተጠጋቸው። ከዚያም በላይ የተባለው የመጀመሪያው ተከሳሽ ወደ ስዩም ጠጋ አለና ምንም ሳይናገር በያዘው ጫፉ ላይ ብረት ባለው ዱላ አናቱን መታው። ስዩም ወደቀ። በወደቀበት ቦታ ጥለውት ይሄዳሉ ሲባል ከየት እንደመጡ ያልታወቁ አስራ አንድ ወጣቶች ድንገት ደረሱና በወደቀበት ተረባርበው እንደ እባብ አናት አናቱን ቀጠቀጡት።
ከደብዳቢዎቹ መካከል ጌቱ የተባለ አንድ ወጣት የስዩም እንደ እባብ መቀጥቀጥ አልበቃ ብሎት ድንጋይ አምጥቶ ጭንቅላቱን በረቀሰው። ስዩም ጣር ላይ ነበር። ድንገት በደመነፍስ ብድግ ብሎ ያንን ሁሉ ውርጅበኝ ለማምለጥ እግሬ አውጪኝ ብሎ ሮጠ። ዱላ የበዛበት ወጣት ከጭንቅላቱ እየፈሰሰ አይኑን የሚጋርደውን ደም እየጠረገ ተውተረተረ። ብዙ ርቀት ግን ለመጓዝ አቅም አልነበረውም፤ ተደናቀፈና ቦይ ውስጥ ወደቀ። ከወደቀበት ግን ለመነሳት አልቻለም እስከ ወዲያኛው አሸለበ።
ይሄንን ያዩና ሲሮጥ የተከታተሉት ደብዳቢዮቹ አሁንም ሊተውት አልፈቀዱም። እዚያው በወደቀበት በጭካኔ ደብድበው ጥለውት ሄዱ ። የእናቱ የአይን ማረፊያ የቤቱ ብርቅዬ ልጅ በተላከበት ባልታሰበ ቅፅበት እንደወጣ ቀረ። ያ ባለአለማ ባለ ብዙ ተስፋ ወጣት ከህልሙ ሳይገናኝ በአጭሩ ተቀጨ።
ይህ ሁሉ ውረጅብኝ ስዩም ላይ ሲደርስ ለማገላገል የሞከረ አንድም ሰው አልነበረም። በወቅቱ የቡድን ፀብ እጅግ በጣም ይፈራ ስለ ነበር ነገሩን በዝምታ ከመመልከት ውጪ ምርጫ ያለው አልነበረም። በቅፅበት ውስጥ የተከናወነው ድብደባም ፖሊስ ለመጥራት ፋታ የሰጠ አልነበረም።
የደብዳቢዎቹን መሄድ ተመልክተው ቱቦ ውስጥ የወደቀው ተደብዳቢ ለማንሳት የሄዱት በአከባቢው የነበሩ ሰዎች ወጣቱ እጅግ በሚዘገንን ሁኔታ ህይወቱ እንዳለፈች አወቁ። በጨለማው ድብደባ ወቅት ያጠለቀውን ሌዘር ጃኬቱን፤ የወርቅ ሀብሉንና ኪሱ ውስጥ የገኙትን እናቱ እቁብ እንዲከፍል የሰጡትን አንድ ሺ ብር ደብዳቢዎቹ ይዘው ተሰውረዋል።
ጥቂት ቀናትን ከወሰደ ምርመራና ክትትል በኋላ የተያዙት አስራ አንድ ተጠርጣሪዎች ግዲያውን አንዱ በአንዱ ሲያላክኩ ቆዩ ። በተለይም የገደልኩት እኔ አይደለሁም በማለት ከፍተኛውን የድብደባ ደረጃ ወደ ሌላው ለማዞር ጥረት እያደረጉም ነበር። ለፖሊሶች ጥያቄ የተገባ መልስ ከመስጠት ይልቅ አንዱ ሌላው ላይ ጣት መቀሰርን ምርጫቸው አደረጉ። ይህንን ቢያደርጉም ግን ማናቸውም ከተጠያቂነት ሊያመልጡ አልቻሉም።
ፖሊሶች ባደረጉት ምርመራ ወጣቱን ለሞት ያበቃው ጉዳይ፤ የግድያው መነሻ የተባለው ነገር ነው ለሁሉም አድማጭ ፣ተመልካች አስገራሚ የነበረው። ሁሉም ተጠርጣሪዎች ስዩምን አያውቁትም ነበር። ስዩምን የሚያውቀው መጀመሪያ ና ብሎ የጠራውና የመጀመሪያውን ዱላ የሰነዘረበት ወጣት ብቻ ነበር። ስዩም የአበባ ሰፈር ልጅ እንደሆነ ያውቃል፤ ስዩም ተማሪ ይሁን አስተማሪ ሰራተኛ ይሁን ስራ አጥ የሚያውቅ አንድም ሰው ከደብዳቢዎቹ መካከል አልነበረም። ነገር ግን አንድ እውነት አለ ስዩምን ለሞት ያበቃው። ያ እውነትም ስዩም የአበባ ሰፈር ልጅ መሆኑ ብቻ ነው።
በአበባ ሰፈር ነዋሪዎችና በእነዚህ ወጣቶች ሰፈር መካከል የተፈጠረው አለመግባባት ወደ ፀብ አምርቶ አሁን ሁለቱም ሰፈሮች ለጥቃት ተዘጋጅተው እና ቂም ቋጥረው ፀብን በፀብ ለማወራረድ የተቀመጡ ናቸው። አንዱ በአንዱ እንዳይጠቃ፤ አንዱ በአንዱ እንዳይሸነፍ በተጠንቀቅ ይጠባበቃሉ። በዚህም አንድም ወጣት ቢሆን ሰፈሩን ላለማስደፈር እንዲነሳ አድርጎታል። ይህም የቡድን ፀቡን አስፋፍቷል። ስዩም ግን ከእናቱ ጉያ ወደ ስራው ከስራው ወደ ትምህርቱ ስለነበረ እንብዛም ስለፀቡ እውቀት አልነበረውም። ይህ ምስኪን ወጣት በማያውቀውና በማይጠረጥረው መንገድ ህይወቱ ሲጠፋ ለሰሚ ግራ የሚያገባ ነበር። የቡድን ፀብ ተሳታፊ ሳይሆን አበባ ሰፈር የሚኖር ሰው በመሆኑ ብቻ የፀበኞቹ የጥል ጥማት ማስታገሻ መሆኑ ብዙዎችን አሳዝኗል።
በርካቶች ቀኑ ከዛ እትለፍ ቢባል ነው እንጂ ከቤቱ ወጥቶ ድምፁ ተሰምቶ የማያውቅ ወጣት እንዴት ይህ ይደርስበታል ቢሉም ይሄንን መሰል ክስተቶች ማመዛዘንና ማስተዋል በተሳናቸው ሰዎች የሚፈፀም የወንጀም ድርጊት መሆኑን ፖሊስ ተናግረዋል።
በወቅቱ የቡድን ፀብ የመዲናዋ አዲስ አበባ ዋና ችግር በነበረበት ጊዜ በመሆኑ በነስዩም አከባቢ ብቻ ሳይሆን በተለያዩ የከተማዋ ክፍሎች የሚፈፀሙ ወንጀሎች ተበራክተው እንደ ነበር ፖሊስ ተናግሯል። በእነዚህ የቡድን ፀቦችም የበርካቶች ህይወት መጥፋት አንስቶ እስከ አካል መጉደል ደርሷል። በርካታ ሀብት ንብረትም ባልተገባ ሁኔታ ባክኖዋል፤ ወድማል። ይህን ሙሉ አዲስ አበባን ያዳረሰውን ችግር ለመከላከል ፖሊስ ጠንካራ ስራ ሰርቷል ። የዛም ውጤት ነው እነዚህን አስራ አንድ ወጣቶች ዋነኛና ተባባሪ የወንጀል ፈፃሚ በማለት ክስ እንዲቀርብባቸው የሆነው። ፖሊስ ምርመራውን ጨርሶ ወደ አቃቤ ህግ በመላክ ውሳኔውን እየተጠባበቀ ነው።
ውሳኔ
አቃቤ ህግ ከአይን እማኞችና ከተለያዩ ምርመራዎች የተገኙ ማስረጃዎችና መረጃዎች ተጠናክሮ የቀረበለትን ማስረጃ በመያዝ ለፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ ችሎት አቅርቧል። ፍርድ ቤቱን መረጃዎችን ሲመረምር ቆይቶ በተከሳሾቹ ላይ የመጨረሻውን ፍርድ ለማሳለፍ በቀነ ቀጠሮ ተገኝቷል፡፡ ፍርድ ቤቱ ቀደም ሲል ተከሳሾቹ በቀረበባቸው ክስ ጥፋተኛ መሆናቸውን አረጋግጦ የክስ መከላከያቸውን እንዲያቀርብ ዕድል ሰጥቷል፡፡ ተከሳሹም ስለ ወንጀሉ ፈጽሞ አላስተባበሉም፡፡
ፍርድ ቤቱ በዕለቱ በሰጠው የመጨረሻ ውሳኔ ያለ ምንም በቂ ምክንያት የዛ ሰፈር ልጅ ነህ በማለት ያለአግባብ በአሰቃቂ ሁኔታ የስዩምን ነፍስ ያጠፉ ዋንኛ ወንጀል አድራጊዎች በአስራ አምስት አመት ፅኑ እስራት ተባበሪዎቹ ደግሞ በአስር አመት ጽኑ እስራት ‹‹ይቀጡልኝ›› ሲል ውሳኔውን በማሳለፍ መዝገቡን ዘግቷል፡፡
አስመረት ብሥራት
አዲስ ዘመን ሐምሌ 30/ 2014