የዛሬዋ ‹‹የዘመን እንግዳ›› በኢትዮጵያ ግዙፍ የመንግሥት የልማት ድርጅት ከሆኑት ተቋማት መካከል አንዱ የሆነው ኢትዮ-ቴሌኮምን ላለፉት አራት ዓመታት በመምራት ከፍተኛ ለውጦችን እያስመዘገቡ ያሉት የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ሥራ አስፈፃሚ ፍሬሕይወት ታምሩ ናቸው:: ዋና ሥራ አስፈፃሚዋ ድርጅቱን ከዚህ በፊት ከመሩ የሥራ ኃላፊዎች መካከል በዕድሜ ቢያንሱም ድርጅቱን ወደ ከፍተኛ ደረጃ በማድረስ የሚደነቁ ናቸው :: አዲስ አበባ ከተማ ተወልደው ያደጉት ወይዘሪት ፍሬሕይወት የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ እንዲሁም ሁለተኛ ዲግሪያቸውን ደግሞ በኢንፎርሜሽን ሲስተም ከእንግሊዝ ሀገር ኦፕን ዩኒቨርሲቲ በቢዝነስ አድሚንስትሬሽን አግኝተዋል::
ወይዘሪት ፍሬሕይወት ወደ ኢትዮ ቴሌኮም ዋና ሥራ አስፈፃሚነት ከመምጣታቸው በፊት በድርጅቱ ውስጥ በተለያዩ የሥራ ኃላፊነቶች ለአምስት ዓመታት ያህል አገልግለዋል:: በገዛ ፈቃዳቸው ሥራቸውን ከለቀቁ በኋላ ዶክሳ.ኤቲ የተባለ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ የግል ድርጅት አቋቁመው በዋና ሥራ አስኪያጅነት ሲሠሩ ቆይተዋል:: በዶክተር ዐቢይ አሕመድ የሚመራው የለውጥ ኃይል ወደ ስልጣን መምጣቱን ተከትሎ ወደ እዚህ ከፍተኛ የአስተዳደር ስልጣን የመጡት ወጣቷ አመራር የኢትዮ ቴሌኮምን የመምራት ኃላፊነት እንደተረከቡ ተቋሙን ሪፎርም በማድረግና ዘመኑን የሚዋጁ አሠራሮችን በመዘርጋት የድርጅቱን ዓለምአቀፍ ተወዳዳሪነት ከፍ ማድረግ ችለዋል::
ዋና ሥራ አስፈፃሚዋ በአመራር ዘመናቸው ውጤት ካስመዘገቡባቸው ሥራዎች መካከል ኩባንያው ባለፈው በጀት ዓመት ካስጀመራቸው ፕሮጀክቶች ውስጥ ‹‹ቴሌ ብር›› የተሰኘው በኤሌክትሮኒክስ ዘዴ ገንዘብ የማስተላለፊያ መላ በዋናነት ይጠቀሳል:: ኩባንያው ሞባይል ያላቸው ሰዎች ሁሉ ቴሌ ብር በተሰኘው ቀልጣፋ የገንዘብ ማዘዋወሪያና ግብይት መፈጸሚያ መተግበሪያ ብዙዎች እየተጠቀሙበት ይገኛሉ:: አገልግሎት ገንዘብ ከማስተላለፍ፤ ከመቀበልና ክፍያ ከመፈፀም በተጨማሪ ከተለያዩ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ጋር ተሳስሯል:: እንደ ውሃ ፤ የኤሌክትሪክ አገልግሎት ክፍያና የትራንስፖርት ትኬት መቁረጥ እንዲሁም የትራፊክ ቅጣትን በዚሁ በቴሌ ብር መተግበሪያ መከወን ተችሏል::
የታታሪነትና የትጋት ተምሳሌት ተደርገው በብዙዎች ዘንድ የሚታመኑት ዋና ሥራ አስፈፃሚዋ በ2014 በጀት ዓመት በቴሌኮሙኒኬሽን ዘርፍ የ2022 የአፍሪካ ስመጥር ዋና ሥራ አስፈጻሚዎች ሽልማትን በቅርቡ ማሸነፋቸው ይታወሳል:: አዲስ ዘመን ጋዜጣም የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ሥራ አስፈፃሚ ፍሬሕይወት ታምሩን እንግዳችን በማድረግ ኩባንያው ዲጂታል ኢትዮጵያን ለመገንባት እያከናወነ በሚገኘው ሥራዎች ዙሪያ ያደረግነውን ቃለ-ምልልስ እንደሚከተለው ለንባብ አብቅተናል::
አዲስ ዘመን፡- ‹‹ሴት አትችልም›› የሚለውን ኋላቀር አስተሳሰብ ሰብረው ከወጡ ሴት አመራሮች አንዷ እንደሆኑ በተግባር አስመስክረዋል:: ለዚህ ስኬት ያበቃዎት ምስጢር እስኪ ይንገሩን ?
ወ/ሪት ፍሬሕይወት፡- በግል በስኬቴ ዙሪያ ባናወራ ደስ ይለኛል:: ግን እንደአጠቃላይ ሴት አትችልም ብሎ በድፍኑ ከመፍረድ ይልቅ ሁሉም ሰው በሠራው ሥራ መመዘን፤ በፍሬው ቢታይ መልካም ነው እላለሁ:: ተቋምም ሆነ ግለሰብ መለካት ያለበት በፍሬው ነው:: ፍሬው ይናገር ከማለት ውጪ እዚህ ጉዳይ ላይ ምንም ማብራሪያ አልሰጥም:: ከእኔ ተሞክሮ የሚማርና የሚጠቀም ካለ ደስ ይለኛል:: ከዚያ ባለፈ ግን በእኔ ስኬት ላይ ማውራት አልፈልግም::
አዲስ ዘመን፡- ኢትዮ- ቴሌኮም በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ከተቋማት ጋር በመቀናጀት ዲጂታል ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ ያለው ሚና ምን እንደሆነ ያብራሩልን?
ወይዘሪት ፍሬሕይወት፡- ኢትዮ ቴሌኮም በስፋት ሲሠራ የነበረው የቴሌኮም አገልግሎቶችን በስፋት ተደራሽ ለማድረግ ነው:: ባለፉት አራት ዓመታት የቴሌኮም መሠረተ ልማት ስናስፋፋ ነው የቆየነው:: ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን እንደምታዩት የዘረጋነውን የመሠረተ ልማት አቅም አሟጠን ከመጠቀም አንፃር እሴት ለመጨመር የፋይናንስ አገልግሎትን ለማሳለጥ፤ ደንበኞች በቀላሉ በስልካቸው ተጠቅመው ገንዘብ ለመላክ፤ ለመቀበል፤ ከፍያ ለመፈፀም የሚያስችል ሁኔታን ፈጥረናል:: ቴሌ ብር ተግባራዊ ከተደረገ አንድ ዓመት ከሁለት ወር ገደማ ነው:: በዚህ አጭር ጊዜ ውስጥ 21 ነጥብ 8 ሚሊዮን ብር መሰብሰብ ችለናል:: ይህም በኢንዱስትሪው ታሪክ ያልነበረና ትልቅ የሚባል ነው:: ሌሎች ሀገራት እዚህ ደረጃ ለመድረስ ከአስር ዓመት ያላነሰ ጊዜ ነው የፈጀባቸው:: እናም በአጭር ጊዜ የደንበኞቻንን ቁጥር ማሳደግ ብቻ ሳይሆን በዚህ ጊዜ ውስጥ ወደ 30 ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር መለዋወጥ ተችሏል::
በተጨማሪም ከ21ሺ በላይ የንግድ ተቋማት ከቴሌ ብር ጋር ተቆራኝተው በየቦታው ክፍያዎችን እንድንፈፅምና ገንዘብ ለማዘዋወር እንዲረዳን ምቹ ሁኔታ ፈጥሯል:: እንደሀገር ኢትዮ ቴሌኮም ዲጂታል ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ የቴሌኮም መሠረተ ልማት ማስፋፋት ብቻ ሳይሆን እሴትን የሚጨምሩ አገልግሎቶችን እያመጣን ነው ያለነው:: አሁን ላይ ቴሌ ብር እየሠራ ያለው ገንዘብ ማዘዋወር፤ መቀበል በተለይ ደግሞ በቅርቡ በሀገራችን የነዳጅ ሥርዓትን ወይም ነዳጅ ድጎማን ተግባራዊ ለማድረግ ከማንዋል ሥርዓት ወጥቶ ዲጂታላይዝድ መደረጉ ትልቅ እምርታ ነው:: ይህም በጣም ውስብስብና ብዙ ባለድርሻ አካላት የሚሳተፉበት አካባቢ እንደመሆኑ የታለመለትን ድጎማውን ወደ መሬት ለማውረድ አስቸጋሪ የነበረውን ሥርዓት ለማቅለል ተችሏል::
ከዚህ ጋር ተያይዞ አዲስ አበባ ላይ ‹‹ሐ›› ግብር ከፋይ በቴሌ ብር አማካኝነት ክፍያ እየፈፀሙ ነው ያሉት:: ይህም በጣም ጥሩ አፈፃፀም እያሳየ ነው:: የትራፊክ ቅጣትም በተመሳሳይ ወደዚሁ ሥርዓት እንዲገባ በመደረጉ ደንበኞቻችን በቀላሉ ቅጣታቸውን እንዲከፍሉ ምቹ ሁኔታ ተፈጥሮላቸዋል::
እንደሚታወቀው ኢትዮ ቴሌኮም 128 ዓመት ያስቆጠረና ከዓለም በ26ኛ ደረጃ ላይ የሚገኝ ግዙፍ ድርጅት ነው:: ከዚህ አኳያም የዘረጋውን ኔትወርክ ከመገናኛ ዘዴ ከመሆን ባለፈ ለማኅበረሰባችን ችግር ፈቺ የሆነ አጠቃላይ ለኑሮ የሚያግዝ ምርትና አገልግሎቶችን ልንሰጥበት ይገባል ብለን ነው የገባነው:: ስለዚህ አሁን ላይ ቴሌ ብር ገና ጅማሬውን ነው ያየነው፤ በቅርቡ ደግሞ በጣም ጥሩ ነገሮችን ይዘን ብቅ እንላለን:: በተለይ በፋይናንስ አገልግሎት ተደራሽ ያልሆነውን ሰፊውን የማኅበረሰብ ክፍል ተደራሽ ለማድረግ ከፍተኛ ሚና ይጫወታል ብለን እናስባለን::
ይህንና መሰል ሥራዎችን ሠርተን በተለይ ተቋማት በሲስተም ታዘው ለደንበኞች አገልግሎት በመስጠት፤ እንግልትና አላስፈላጊ ሰልፎችን ማስቀረት ይጠበቅብናል ብለን እናምናለን:: ለዚያም ነው መንግሥታዊ ተቋማትንም ሆነ ሌሎች ተቋማትን ከሥርዓታችን ጋር አስተሳስረን እየሠራን ያለነው:: በነገራችን ላይ በ21ኛው ክፍለ ዘመን ላይ ትልቁ ልንጠቀምበት የሚገባው አገልግሎትን ሁሉ ዲጂታል የማድረጉ እድል ነው:: ሌሎች የንግድ ተቋማትም ይህንን መልካም አጋጣሚ ተጠቅመው ምርታማነታቸውን እንዲያሳድጉ፤ በጣም በከፍተኛ ሁኔታ የኑሮው ዋጋ እየናረ በመሆኑ ይህንን ውስን ሃብት በአግባቡ ተጠቅመን ሰው የሚጠቀም ቦታ ላይ እንድናውለው ይገባል::
ደግሞም የአሠራር ሥርዓታችን ዲጂታል ባለመሆኑ የሥራ ማስፈፀሚያ ወጪያችን ሲጨምር ለሠራተኞቻችን አስፈላጊውን ጥቅማጥቅም ለማሟላት ጫና ይፈጥራል:: ነገር ግን ምርትና አገልግሎት ለደንበኞች የምናደርስበት ሥርዓታችን በተወሰነ ደረጃም ቢሆን በዲጂታል ብንተካ ብዙ ወጪ እንቀንሳለን:: ስለዚህ ከዚያ የሚገኘው ገንዘብ ደግሞ ለተለያዩ የልማት ሥራዎች ማዋል ያስችለናል:: ደግሞም ዲጂታላይዝድ ማድረጉ ምርታማነትን ይጨምራል፤ አዲስ የሥራ እድል ይፈጥራል:: በአሁኑ ወቅት ኩባንያችን ዲጂታል ኢትዮጵያን እውን በማድረጉ ሂደት ግንባር ቀደሚ ሚና እየተጫወተ እንደመሆኑ አዳዲስ አስቻይ ሁኔታ ይፈጥራል ብለን የምናስባቸው ዘመኑ የደረሰበትንም ቴክኖሎጂ ወደተጠቃሚዎች ለማድረስ እየሠራ ነው:: በአዲሱ በጀት ዓመትም ዘርፎችን እየለየን በ5ጂ አግዘን ምርታማነትን ለመጨመርና አዳዲስ የሥራ እድል ለመፍጠር እንሠራለን::
በመሆኑም ወደዚህ ሥርዓት ያልገቡ ተቋማት የአሠራር ሥርዓታቸውን ለመቀየር የሚያስችላቸው ቴክኖሎጂ እንዳለ ተገንዝበው ደፍረው ሊገቡ ይገባል:: በእርግጥ በኮቪድ ጫና ምክንያት የቴክኖሎጂን አስፈላጊነት ብዙዎቹ ተገንዝበዋል:: በመሆኑም የራሱ መጥፎ ጎኑ እንዳለ ብዙ ተቋማት ከኮቪድ በኋላ ዲጂታላይዜሽን አስፈላጊ እንደሆነ ተረድተዋል:: ይህም ለእኛም በቀላሉ ተግባራዊ ለማድረግ እድል ፈጥሮልናል:: ይህ ሲባል ግን የሥራ ባህል ለውጥ ስለሆነ የተወሰነ ጊዜ መውሰዱ እንደማይቀር መረዳት ይገባል:: በመሆኑም የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራ በሰፊው መሠራት ይኖርበታል::
አዲስ ዘመን፡- ዲጂታል የሆነ ሥርዓት መዘርጋት በራሱ ባህልን የመቀየር ያህል ከፍተኛ ሥራ የሚጠይቅ ነው፤ ከዚህ አንፃር የማኅበረሰቡን የቴክኖሎጂ አጠቃቀም ባህል ለማሳደግ ምን እየተሠራ ነው?
ወይዘሪት ፍሬሕይወት፡- እውነት ነው፤ ግን አሁንም ቢሆን የኅብረተሰቡ የቴክኖሎጂ አጠቃቀም እያደገ ነው ያለው:: ለምሳሌ ቴሌ ብርን ብናይ ወደ 22 ሚሊዮን የሚጠጋ ደንበኛ ተጠቃሚ መሆኑ ማኅበረሰቡ ፍላጎቱንም ጭምር ያሳየበት ነው:: አስቀድሜ እንዳነሳሁልሽ ሌሎች ሀገራት እዚህ ለመድረስ አስር ዓመት ፈጅቶባቸዋል:: ምንአልባት እነሱ የጀመሩበት ጊዜ የነበረው የቴክኖሎጂ ግንዛቤ እኛ ካለንበት ዘመን ጋር ስለሚለያይ አሁን ካለው የቴክኖሎጂ አጠቃቀም ጋር ልናወዳድረው አንችልም:: ሆኖም በአንድ ዓመት ደግሞ ይህን ያህል ምላሽ መገኘቱ በአጭር ጊዜ ውስጥ ያሰብናትን ዲጂታል ኢትዮጵያ እውን እንደምናደርግ ማሳያ ነው::
ስለዚህ ኋላቀር አጠቃቀም ነው ያለው ብለን ዝቅ የምናደርገው አይነት አይደለም:: ይህንን ያህል ቁጥር ያለው ሰው ወደ ሥርዓቱ ከገባ በኋላ እንዴት እንደሚጠቀምበት ግንዛቤ መፍጠር ያስፈልጋል:: ይሄ ደግሞ አንዴ ብቻ የሚደረግ ሳይሆን ቀጣይነት ያለው በርካታ ሲስተሞች ሲተሳሰሩ ከኑሯችን ጋር፤ ከዕለት ተዕለት እንቅስቃሴያችን ጋር ቴክኖሎጂን መጠቀም አስፈላጊ ብቻ ሳይሆን አስገዳጅ ሊሆን ይችላል:: አሁን ላይ በብዛት ወደ ማኑዋል ሲስተም የምናደላበት ምክንያት አማራጮቹ ስላሉ ነው፤ ወደፊት ግን እየቀረ ይመጣል:: ሰው ጥቅሙን እያወቀ ሲመጣ የገንዘብ ልውውጡም በዚያው ልክ ነው እየጨመረ የሚመጣው:: የማያቋርጥ ግን የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥርዓት ያስፈልጋል::
ከዚህ ጋር ተያይዞ በበጀት ዓመቱ ከሠራናቸው ሥራዎች አንዱ ማኅበራዊ ኃላፊነት ብለን ወደ 65 ትምህርት ቤቶች ላይ ዲጂታል ቤተ-ሙከራ አቋቁመን፤ የኮምፒውተርና የኢንተርቴት መሠረት ልማቶች በሙሉ
አሟልተን የሠራነው ሥራ አለ:: ይሄ ግን በቂ አይደለም ፤ በርካታ ሥራዎች መሠራት ይኖርባቸዋል:: ከታች ጀምሮ ተማሪዎች ኢንተርኔትና ቴክኖሎጂ አጠቃቀምን እየተማሩ እንዲመጡ ብለን ነው ይህን ሥራ የሠራነው:: ሌሎች ደንበኞቻችንም ከተለያዩ የሚዲያ አካላት ጋር የምንሠራው ሥራ እንደተጠበቀ ሆኖ በሰፊው ይህንን ማስቀጠል አለብን::
አዲስ ዘመን፡- በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ኩባንያው በከፍተኛ ደረጃ ወጪን መታደግ የቻለው ምን አይነት ሥራዎችን ቢሠራ ነው?
ወይዘሪት ፍሬሕይወት፡- እንዳልሽው በዚህ በጀት ዓመት 217 ፕሮጀክቶችን ተግብረን ወደ 5 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር ወጪ መታደግ ችለናል:: ፕሮጀክቶቹ በቁጥር በርካታ ቢሆኑም ለሥራ ማስፈፀሚያ ያዋልነው በበጀት ዓመቱ ወጪያችን ካስቀመጥነው በታች ሆኖ የጨረስነው ፕሮጀክቶቹ ተሠርተው ነው እንጂ ተቋርጠው አይደለም:: ይህም ሊሆን የቻለው በትንሽ ወጪ ብዙ መሥራት ብለን አቅደን በመነሳታችን ነው:: ለዚህ ደግሞ ማኔጅመንቱና ሠራተኛው ከፍተኛ ርብርብ አድርገዋል:: ከምቾት ቀጣና ወጥተን በቁርጠኝነት በመሥራታችን ነው ከፍተኛ ውጤት ያስመዘገብነው:: ለዚህ ደግሞ የአሠራር ሥርዓታችን ላይ ዲጂታላይዜድ ማድረጋችን በራሱ ከፍተኛ ሚና ነበረው:: ስለዚህ ሌሎችም መሰል ሥራዎችን ሠርተን 5 ነጥብ 4 ቢሊዮን ማግኘት ችለናል:: ይህም ትንሽ የሚባል ብር አይደለም:: እናም ደንበኞች እንዳይጉላሉ ከማድረግ ባሻገር፤ ወጪ በመታደግ ረገድ የላቀ ሚና አለው:: አሁንም በርካታ ተቋማት ወደዚህ ሥርዓት እየገቡ ነው:: ለምሳሌ ከአዲስ አበባ ውጭ ያሉ የውሃ ተቋማት በቀላሉ በቴሌ ብር አማካኝነት ትስስር ፈጥረዋል:: መብራትን ጨምሮ ሌሎችም የመንግሥት አገልግሎቶች ተሳስረዋል:: አሁንም ይህንን በስፋት እንሠራለን::
አዲስ ዘመን፡- ድርጅታችሁ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ከፍተኛ ገቢ አስገብቷል፤ ከእቅዳችሁ አንፃር ግን የሚቀረው መሆኑ በሪፖርታችሁ ተገልጿል፤ የዚህ ምክንያቱ ምንድን ነበር?
ወይዘሪት ፍሬሕይወት፡- በአጠቃላይ ስናየው የ2014 በጀት ዓመት አፈፃፀማችን እጅግ በጣም አመርቂ የሚባል ነው:: ይህንን የምንልበት ምክንያት የደንበኞቻችን ቁጥር ለማሳደግ እንዲሁም ለማስገባት ካቀድነው አንፃር ነው:: ከገቢ አንፃር ካየነው 61 ነጥብ 3 ቢሊዮን ማስገባት ችለናል:: ይህም የእቅዳችንን 87 ነጥብ 6 ማሳካት ችለናል:: በበጀት ዓመቱ በሰሜኑ የሀገሪቱ አካባቢ በተከሰተው ችግር በኢኮኖሚም ሆነ በደንበኞቻችን ላይ ከፍተኛ ችግር ፈጥሮብናል:: ከዚህ አንፃር በበጀት ዓመቱ 70 ቢሊዮን ብር ገቢ እናገኛለን ብለን አቅደን ያሳካነው 61 ነጥብ 3 ቢሊዮን ነው::
ይሁንና እንደምታስታውሱት ኢትዮ ቴሌኮም ከዚያ በፊት እቅዳችን የተጋነነ ቢሆንም 100 እና ከዚያ በላይ ሲያሳካ ነበር የቆየው:: በዚህም በጀት ዓመት የተለጠጠ ግብ ነበረን:: ሆኖም ግን 45 በመቶ (3ሺ 400) የሚሆኑት የሞባይል ጣቢያዎች በበጀት ዓመቱ በፀጥታ ችግር ምክንያት አገልግሎት መስጠት አልቻሉም:: ሆኖም ይህንን ያህል ማሳካት በመቻላችን ነው እጅግ አመርቂ የምንለው:: ይሁንና ከቁጥር ማሳካት ባሻገር በርካታ ችግሮች ገጥመውናል፤ ሠራተኞቻችን ብዙ ዋጋ ከፍለዋል:: በተለይ በጦርነቱ ምክንያት የተጎዱ አካባቢዎችን ጥገና ለማድረግ በርካታ ኢንቨስትመንትም ፤ ሠራተኞቻችንም ዋጋ እንዲከፍሉ አድርጓል:: ያም ቢሆን ፈጥነን ከ45 በመቶው ውስጥ 30 በመቶውን የጠገንን ሲሆን 15 በመቶ ደግሞ በፀጥታ ችግር ምክንያት የማንገባባቸው አካባቢዎች ናቸው::
በነገራችን ላይ በጀት ዓመቱን ስንጀምር ታሳቢ ያደረግናቸው ነገሮች ነበሩ:: በሰሜኑ የአገሪቱ አካባቢ ያለው ችግር በአጠረ ጊዜ ይፈታል ብለን ታሳቢ አድርገን ነው የገባነው:: ግን ታሳቢ ያደረግነው የሰሜኑ የፀጥታው ችግር ሳይፈታ ወደሌሎች አካባቢዎችም ተዛምቶ ብዙ ጣቢዎች አገልግሎት እንዳይሰጡ ሆነዋል:: ያም ሆኖ ግን ይህንን ያህል ማሳካት መቻላችን፤ በጦርነቱ የምናጣው ገቢም ደንበኞቻችን ላይ የፈጠረው ተፅዕኖ ከባድ እንደሚሆን ስላወቅን በርካታ አማራጮችን በእቅዳችን ውስጥ ያልተካተቱ ለመውሰድ ተገደን ነበር:: ማካካሻ የምንላቸውን ሥራዎች እየሠራን ነው እቅዳችን በዚህ ልክ ማሳካት የቻልነው:: በደንበኛ ልክ ከወሰድነው 104 በመቶ ነው ያሳካነው::
በበጀት ዓመቱ የቴሌኮም ገበያው ለውጭ ኩባንያዎች ክፍት ቢሆንም እስካሁን ድረስ የገባው ድርጅት አገልግሎት መስጠት አልጀመረም፤ ስለዚህ ብቸኛ አገልግሎት ሰጪ ተቋም ሆነን ነው በ2014 ያጠናቀቅነው:: ከዚህ አንፃር የደንበኞችን ቁጥር ኔት ወርኩን ተደራሽ በማድረግና አገልግሎቱን ያላገኙ ደንበኞች እንዲያገኙ ከማድረግ አንፃር ነው የምንሠራ የነበረው:: 64 ሚሊዮን እናደርሳለን ብለን 66 ነጥብ 59 ነው ያሳካነው :: ይሄ ካለፈው ዓመት በ18 በመቶ የጨመረበት ትልቅ እድገት ነው :: እነዚህንና ሌሎች ችግሮችንም ተቋቁመን ነው ገቢ ፤ የአገልግሎት ሽፋንን ማሳደግና ጥራትን ማሻሻል የተቻለው:: አሁንም ቢሆን ደንበኛ ተኮር የሆኑ አገልግሎቶች ማውጣት ይጠበቅብናል::
ከዚህ አንፃር ደንበኞቻችንን ለማርካት 144 ምርትና አገልግሎቶች ወደ ገበያ አቅርበናል:: በአንድ በጀት ዓመት ቀድሞ ከነበረን ተሞክሮ አንፃር ስናየው በጣም ብዙ ነው:: ከዚህ ውስጥ 67 የሚሆኑት አዲስ ናቸው:: እንዲሁም 77 የሚሆኑ ማሻሻያ የተደረገባቸው ምርቶች ወደ ገበያ ቀርቧል:: ይህም ገቢ ለማሳደግም፤ ደንበኞቻችንም ፍላጎት ለማርካት ትልቅ እድል ፈጥሮልናል:: ለዚህ አስቻይ ሁኔታ በርካታ ፕሮጀክቶች ተሠርተዋል:: 217 ፕሮጀክቶቻችን አፈፃፀማቻቸው 71 በመቶ ነው:: በተለይ ደግሞ አዲስ ምርት ለማውጣት የሚያችለን ትልቅ መዋለንዋይ ያፈሰስንበት የቀጣይ ትውልድ የምንለው የቢዝነስ ስፖርት ሲስተም ዋነኛው ነው:: የኔት ወርክ ማስፋፊያ በተለይ ኢንተርኔት 4ጂ በ136 ከተሞች ላይ ማስፋፋያ መደረጉ ትልቅ እምርታ ነው:: ይህ ስኬት የመጣው ግን ሠራተኛና ማኔጅመንት ተናበው በመሥራታቸው ነው::
አዲስ ዘመን፡- ድርጅታችሁ ለሀገር ከሚያስገኘው ጥቅም የውጭ ምንዛሪ ግኝት አንዱ ነው:: በዚህ ረገድ የተገኘው እምርታ ምን ይመስላል?
ወይዘሪት ፍሬሕይወት፡- በበጀት ዓመቱ 146 ሚሊዮን ዶላር ማግኘት ችለናል:: ከአቀድነው አንፃር ስናየው 83 በመቶ ገደማ ነው ማሳካት የቻልነው:: ይህ የሆነበት አንደኛው ምክንያትም አስቀድሜ ያነሳሁት የፀጥታ ችግር በዚህ አካባቢ ባሉ ቅርንጫፎቻችን ከውጭ ይመጣ የነበረው ጥሪ በመቋረጡ ነው:: ሆኖም የተገኘው የውጭ ምንዛሪ ካለው አጠቃላይ ሁኔታ አንፃር ቀላል የሚባል አይደለም:: ይህንን በቀጣይ ለማስፋትም በርካታ ሥራዎች ሠርተናል:: በተለይ ረጅም ጊዜ የወሰደብን መሠረተ ልማት መዘርጋት ሥራ ነው:: ኮንትራቱን ብንፈርምም ሥራው ወደ ቀጣይ ዓመት ስለሚሻገር አላካተትነውም:: አሁንም የውጭ ምንዛሪ ምንጮች ብለን የለየናቸው አሉ፤ እነዚያም ስለተጨመሩ ነው ያንን ያህልም ማሳካት የቻልነው:: ሆኖም 45 በመቶ የሚሆኑት ሳይቶች ሲዘጉ ወደ እነሱ ይመጣ የነበረው የውጭ ጥሪ በመቅረቱ ከፍተኛ ተፅዕኖ መፍጠሩን መካድ አይቻልም:: ለዚህም ማካካሻ ሥራ ተሠርቷል:: ከዚህም መካከል በቴሌ ብር አማካኝነት ከ37 ሀገራት የውጭ ምንዛሪ መቀበል ችለናል:: አሁንም ግን የውጭ ምንዛሪን የማግኛ ሥራዎቻችንን የማስተዋወቅ ሥራ በስፋት መሥራት ይጠይቃል::
ሁለተኛ ደግሞ ለውጭ ምንዛሪው ሥራ ፈቃዱን ያገኘነው ሁለተኛው መንፈቀ ዓመት አጋማሽ ላይ ነው:: ይህም በመሆኑ የተሻለ አስተዋፅኦ እንዳይኖረው አድርጓል:: በአጠቃላይ ያለፍንባቸው ችግሮች ብዙ ነገር የሚያሳጡ ነበሩ::ግን እነዚህን ችግሮች ለመጋፈጥ የወሰድናቸው እርምጃዎች መልካም ውጤት አምጥቷል:: ሌላው የአቅርቦት እጥረት ፕሮጀክቶቻንን በጊዜ እንዳናጠናቅቅ ካደረጉን ችግሮች አንዱ ነበር:: ለምሳሌ ለሚያስፈልጉን ግብዓቶች ማመላለሻ የሚሆነው ኮንቴነር ከፍተኛ እጥረት ነበር፤ በሌላ በኩል አማራጮች በኮቪድ ምክንያት የማምረት አቅማቸው ዝቅ ብሏል፤ በቴሌኮም ሴክተሩ አቅርቦት ከፍተኛ እጥረት ነበር:: ዓለም አቀፍ የግብዓት አቅርቦት ዝቅተኛ ስለነበር ለማግኘት የነበረውም ሽኩቻ ቀላል አልነበረም:: ድርድርና በጥምረት መሥራት ይፈልጋል:: ስለዚህ በአቅርቦት እጥረት ብዙ በመፈተናችን ፕሮጀክቶቻችንን በያዝነው ጊዜ እንዳናጠናቅቃቸው አድርጎናል:: ይህም በመሆኑ ልናገኘው የነበረውን ገቢ እንደሚያሳጣን እሙን ነው::
ከዚያም ባሻገር ግን የኢኮኖሚው ቀውስ ደንበኞቻችን ላይ የሚፈጥረው ጫና ምክንያት ተጠቃሚነታቸው መቀነሱ አይቀርም:: ይህ እንዳይሆን በርካታ እርምጃዎችን ወስደን ነው አፈፃጸማችንን አመርቂ ማድረግ የቻልነው:: ለምሳሌ ፓኬጆቻችን ላይ ቅናሽ በማድረግ ከአንድ ብር እስከ አለገደብ ድረስ በበጀት ዓመት ሥንሰራ የነበረው:: ደንበኞቻችን በአንድ ብር አገልግሎት እንዲያገኙ በማድረግ ተጠቃሚ እንዲሆኑ አድርጓል:: በነገራችን ላይ የገበያ ውድድር ካለ ብቻ ነው ተፎካካሪ ሆኖ መቀጠል የሚቻለው የሚለውን የማኔጅመንት መርሆ የሰበረ ሥራ ተሠርቷል:: ምክንያቱም የውድድር ገበያ ሳይኖር ተወዳዳሪነቴን አረጋግጫለሁ ብሎ ደረቱን ነፍቶ መናገር የሚችለው ኢትዮ ቴሌኮም ብቻ ነው::
በአጠቃላይ የቴሌኮም ዘርፉ ሪፎርም ሲደረግ የቆየው ተወዳዳሪነት ለማረጋገጥ ነው:: በአራት ዓመታት ውስጥ የኑሮ ዋጋ ንሯል ብለን ታሪፍ አልጨመርንም፤ ዋጋ በየዕለቱ እየጨመረ እንኳን እኛ ቀንሰን እየሠራን ነው :: የሥራ ወጪያችንን እየቀነስን ደንበኞች ተጠቃሚነታቸው እንዲረጋገጥ ሠርተናል:: በዚህ አጋጣሚ ፍሬሕይወት በዓለም አቀፍ ደረጃ ተሸለመች ሲባል እኔ በግሌ ታውቄ ሳይሆን በኢትዮ ቴሌኮም ፍሬ ነው :: የምንሠራው የማስፋፊያ ሥራ ሁሉ ትርፍ ለማግኘት ብቻ ሳይሆን ኅብረተሰቡን ለመጥቀም ጭምር ነው::
እንደአመራር የምከተለው ፍልስፍና ትርፍ ላይ የተንጠለጠለ ቢዝነስ መፍጠር ሳይሆን ደንበኞቻችንን በአቅማቸው ተጠቃሚ ማድረግ ነው:: ማኅበረሰብን ለማገልገል የግዴታ ውድድር መኖር አለበት ብዬ አላምንም:: ብቸኛ ተቋም ስለሆነ ብቻ አላግባብ ወይም የተጋነነ ትርፍ ማጋበስ አለበት ብዬ አላምንም:: ስለዚህ ወደ ተቋሙ እንደመጣሁ ነው ከ40 በመቶ በላይ የታሪፍ ቅናሽ እንዲሆን ያደረጉት:: ይህም የኅብረተሰቡን የመክፈል አቅሙን ታሳቢ ማድረግ ስለሚያስፈልግም ጭምር ነው:: ይህ ግን አልፈተነንም ማለት አንችልም:: ወጪዎቻችንን በመቀነስ ታሪፍ ላይ ግን ማሻሻያ ስናደርግ ነበር::
ከዚያ ባሻገር ግን በሀገራችን ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ እጥረት አለ፤ በምንፈልገው ልክ የቴሌኮም መሠረተ ልማቶችን ማግኘት አንችልም፤ ውስንነት አለብን:: እነዚህን ውስንነቶች ለመፍታት ቅደም ተከተሎችን በማስቀመጥ ከፍተኛ ውጤት ማምጣት ችለናል:: ከቁጥር ባለፈ የሀገራችን ኢኮኖሚ እንዲንቀሳቀስ ኢትዮ ቴሌኮም አስቻይ ሁኔታ ፈጥሯል:: ተቋማት በቴክኖሎጂ ታግዘው የኮቪድ ጫናን መቋቋም እንዲችሉ የድርጅታችን ሚና የጎላ ነው:: ዲጂታል ኢትዮጵያን እውን ማድረግ ስንል በምክንያት ነው:: ተቋማት ላይ አስቻይ ሁኔታ ፈጥረን በዲጂታል ትስስር እንዲፈጥሩ እያደረግን ነው:: ለዚህም ነው ተግባራችን ይቀደም ብለን ንግግሩን ወደኋላ ያደረግነው:: አሁን ግን ደፍረን ብንናገር ያምርብናል:: ይሄ ማለት ጨርሰናል ማለት አይደለም::
አዲስ ዘመን፡- ኢትዮ ቴሌኮም ከሀገር አልፎ በጎረቤት ሀገራት ተደራሽ ለመሆን እያደረገ ያለው ጥረት ከምን ደርሷል?
ወይዘሪት ፍሬሕይወት፡- ምንአልባት ይህንን ጥያቄ ላስተካክለውና ኩባንያችን ከአንድ ዓመት በፊት መሠረታዊ አገልግሎት ብቻ በሀገር ውስጥ እንዲሰጥ ነበር የተደራጀው:: አዋጁም የሚፈቅድለት በሀገር ውስጥ ብቻ ለመስጠት ነበር:: ቴሌ ብርን አገልግሎት ለማስጀመር ፍቃድ የጠየቅነው አንደኛው በሀገር ውስጥም ለያዝነው ራዕይ መሳካት አቅም ይፈጥርልናል ብለን ነው:: በዚህ መሠረት ኩባንያ ማቋቋም፤ ከሀገር ውጭም ወጥቶ እንዲሠራ በአዋጁ እንዲካተት ጠይቀን ነበር፤ ተፈቅዶልናል::
ይሁንና በተለይም ሀገራችን ከገጠማት ችግር አንፃር በዚህ በኩል አስፍተን ለመሄድ አልቻልንም:: አሁን አንዳንድ ሁኔታዎችን እያጠናን ነው ያለነው፤ ስንጨርስ ደግሞ ይዘን እንወጣለን:: ያለንን አቅም አጣምረን በሌሎች ሀገራትም በመሥራት የኩባያንችንንም ሆነ የሀገራችን በዘርፍ ያለንን ተሳትፎ ለማሳደግ የማስፋት ሥራ እንሠራለን:: አሁን ላይ አንዳንድ ንግግሮችን እያደረግን ነው፤ ጉዳዩ ሲበስልና ፍሬ ማፍራት ሲደርስ ለማኅበረሰባችንም እናሳውቃለን::
አዲስ ዘመን፡- የኢንተርኔት መቆራረጥ ኅብረ ተሰቡ አሁንም ከሚያነሳቸው ችግሮች አንዱ ነው:: ለመሆኑ ችግሩን በዘላቂነት መፍታት ያልተቻለበት ምክንያት ምንድን ነው?
ወይዘሪት ፍሬሕይወት፡- በአጠቃላይ በበጀት ዓመቱ እንዳልኩት 45 በመቶ ዝግ ነበሩ ስንል በበጀት ዓመቱ ትልቁ ተግዳሮት የነበረው የፀጥታ ችግር ነው:: ከዚህም ባሻገር የኃይል አቅርቦት መቆራረጥ በሥራችን ውጤታማነት የራሱን አሉታዊ ሚና ነበረው:: የኔትወርክ የኃይል አቅርቦት ችግሩን ለመፍታት እንዲያስችል በተወሰነ ደረጃ በራሳችን አማራጭ የኃይል አቅርቦት ተጠቅመናል:: አሁን ላይ 50 በመቶ የሚሆኑት ቪቲኤሶቻችን አማራጭ የኃይል አቅርቦት ይጠቀማሉ:: 22 በመቶ የሚሆኑት በሶላር ነው የሚሠሩት፤ እነዚህን አማራጮች እየተጠቅምን ነው አገልግሎት እየሰጠን ያለነው:: ይሄ የሆነበት አንደኛው ምክንያት ለቴሌኮም መስፋፋት መሠረታዊ ከሚባሉት ዋነኛ ግብዓት አንዱ የኃይል አቅርቦት ነው፤ ይህም የኃይል አቅርቦት እጥረት ጥራቱን የጠበቀ አገልግሎት ለደንበኞቻችን እንዳንሰጥና ማስፋፊያውን በሚገባ እንዳናከናውን እንቅፋት ሆኖብን ነበር:: ሆኖም የኃይል አቅርቦት የሚሰጠው ተቋም ራሱ በጦርነቱ ምክንያት የደረሰበት ጉዳት በመኖሩ ይህም ታሳቢ የሚደረግ ነው::
በነገራችን ላይ ከአላማጣ የኃይል አቅርቦት ይመጣላቸው የነበሩ የአማራና አፋር አካባቢዎች አሁንም ኃይል እያገኙ አይደለም፤ ቴሌኮም ታዲያ እንዴት ነው በእነዚህ አካባቢዎች እየሠራ ያለው ብሎ መጠየቅ ጥሩ ነው:: 18 ወር ገደማ በጀነሬተር ነው እየሠሩ ያሉት:: ሙሉ አፋር የኃይል አቅርቦት ባልነበረበት ጊዜ ቴሌኮም ሲሠራ ነበር፤ ይህ ደግሞ ወጪያችንንም ይጨምራል:: ይህንንም የምናደርገው በድጎማ ነው:: 52 በመቶ ቪቲኤሶቻችን ድጎማ ተደርጎባቸዋል የምንለው በዚያም ጭምር ነው:: ነገር ግን ማኅበረሰባችን አገልግሎት ማግኘት ስላለበት ነው የምንደጉመው::
በመሠረቱ የአገልግሎት ጥራት አንዴ ተሠርቶ የሚያልቅ አይደለም፤ በየጊዜው ማሳደግ ይፈልጋል፤ ያለማቋረት መሥራት ይጠይቃል:: ምክንያቱም በየጊዜው የደንበኛው ፍላጎትና አጠቃቀም ስለሚጨምር ነው:: ከዚህ ቀደም እንደገለፅነው አዲስ አበባም ሆነ በሌሎች አካባቢዎች ላይ ማስፋፊያ እየተደረገ ነው:: ከዚህ በተጨማሪ አሁን ላይ የዝናብ ወቅትም ስለሆነ በሶላር የሚሠሩት ላይ ተፅዕኖ ተፈጥሯል:: ያም ቢሆን የአገልግሎት ጥራትን ማሻሻል የማይቋረጥ ሥራ ነው::
አዲስ ዘመን፡- ውድ ጊዜዎትን ሰውተው ከእኛ ጋር ቆይታ ስላደረጉ ከልብ አመሰግናለሁ::
ወይዘሪት ፍሬሕይወት፡- እኔም አመሰግናለሁ::
ማህሌት አብዱል
አዲስ ዘመን ሐምሌ 30 ቀን 2014 ዓ.ም