‹‹በነባር ዕሴቶቻችን ኢትዮጵያን እናሻግር!›› በሚል መሪ ቃል የሚካሄደው አውደ ጥናት ሀገራዊ የነፍስ አድን ጥሪ መልዕክት ያነገበ ነው፤ ሀገራችንን ሳትፍገመገም ቀጥ ብላ ቆማ እንድትኖር ያደረጉ በርካታ ዕሴቶች አሉን፤ ዕሴቶቻችን በአንድ ቀን የተፈበረኩ አይደሉም፤ ዘመን ከተቆጠረ፣ የሰው ልጅ ኢትዮጵያ ውስጥ መኖር ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ በረጅም የጊዜ ሂደት እየተፈጠሩ በእያንዳንዱ ዜጋ ደምና አጥንት ውስጥ እየተዋሐዱ የዘለቁ የትውልድ ቅብብሎሽ ውጤቶች ናቸው፡፡
ዕሴቶች ሃይማኖት ወይም ርቱዕ አዕምሮ የፈጠራቸው ሊሆኑ ይችላሉ፤ ለምሳሌ ‹‹አትግደል›› የሚለውን አምላካዊ ትእዛዝ ያስተማሩን በክርስትናም በእስልምናም ያሉ ቅዱሳት መጻሕፍት ናቸው፤ ሐሜት፣ ስርቆትና በሐሰት መመስከር ኃጢአት መሆናቸውንም
እንዲሁ፡፡ የሰው ልጆች ማኅበራዊ ሕግጋትን መደንገግ ሲጀምሩ እነዚህንና መሰል ቁምነገሮችን የሕግጋት አካል አድርገው ወስነዋቸዋል፤ መነሻቸውም ሃይማኖታዊ ዶግማዎች ናቸው፡፡
ሃይማኖቶች ቢለያዩም አስተምህሮዎቻቸው ግን መልካም ድርጊቶችን እንድንፈጽም ያስገድዱናል፡፡ መግደል በነፍስ ለዘመናት ኩነኔ፣ በሥጋም በወንጀል የሚያስጠይቅ ውጉዝ ድርጊት ነው፤ እኛ ግን ‹‹የሆነው ይሁን›› ብለን ሃይማኖታዊውንም ሆነ ዓለማዊውን ሕግጋት በመጣስ ነፍስ እናጠፋለን፤ እንሰርቃለን፤ በሐሰት እንመሰክራለን፤ እንቀማለን፤ ከፍቅረ ቢጽ ይልቅ አፍቅሮ ንዋይ ተጠናውቶናል፤ ሁሉን ከፈጠረ አምላክ በላይ ገንዘብንና ሥልጣንን እናመልካለን፡፡ ገንዘብን ልንገበያይበት ብንፈጥረውም እኛኑ መልሶ እየገዛን ነው፡፡
ትልቅ አዕምሮ ያለው የሰው ልጅ በገንዘብ እየተገዛ ወንድሙን እንደ እንስሳ እያረደው ነው፤ ሌላው ቀርቶ የሁለት እና የሦስት ወር ሕፃናት በእናታቸው አንቀልባ ላይ እያሉ ከወላጆቻቸው ጋር ሲታረዱ ማየትን ያህል የሚዘገንን ድርጊት የለም፡፡ ነገሩን የከፋ የሚያደርገው በዓለም ቀዳሚ ፍጥረት ሆነን በሚሊዮን ለሚቆጠሩ ዘመናት የገነባነውን የመከባበር ድንቅ ዕሴታችንን በሠላሳ ዓመት ጊዜ ውስጥ ንደን የአራዊት ባሕርይ መላበሳችን ነው፡፡ ይሁዳ ጌታውን በ30 ብር ሸጠው፤ እኛም እንደ ብረት አፅንቶን የኖረውን የመከባበር ዕሴታችንን በ30 ዓመት ውስጥ ክፉኛ ገዝግዘነዋል፡፡
ድሮ ኢትዮጵያ እንኳንስ ለዜጎቿ ለባዕዳንም የችግራቸው ጊዜ ዋሻ መጠጊያ ነበረች፤ ተሥዓቱ ቅዱሳን (ዘጠኙ ቅዱሳን) በመባል የሚታወቁት የሃይማኖት አባቶች ከአውሮፓና ከኤሺያ ወደ ሀገራችን የመጡት ሰላማዊት ሀገር ፍለጋ ነው፤ የዚያን ጊዜዋ ኢትዮጵያም አላሳፈረቻቸውም፤ በክብር ተቀብላ አኑራ ሲሞቱም በየስማቸው ፅላት ቀርጻ፣ ቤተክርስቲያን አንፃ አሁን ድረስ ታከብራቸዋለች፡፡
በቁረይሾች (ጣዖት አምላኪዎች) የጭካኔ በትር ምክንያት በሀገራቸው የመኖር ዋስትናቸውን የተነፈጉት የነቢዩ መሐመድ ሰሃባዎች (ተከታዮች)ም ርኅሩኅ መሪና ሕዝብ ወዳለባት ኢትዮጵያ በስደት መጥተው በክብር ተስተናገዱ እንጂ እንደ ውሻ ‹‹ውጡ›› አልተባሉም፤ ዛሬም አጽማቸው ያረፈበት ቦታ በክብር ይጠበቃል፤ የዓለምአቀፍ ጎብኝዎች መስህብ ቅዱስ ቦታ በመሆንም የላቀ አገልግሎት እያበረከተ ነው፡፡
ከላይ የተጠቀሱትን ታሪካዊ እውነታዎች ቅድመ አያቶቻችን የፈጸሟቸው ነባሩ ዕሴታቸው ያንን እንዲያደርጉ ስለሚያስገድዳቸው ነበር እንጂ በቋንቋም ሆነ በሃይማኖት የሚተዋወቁ ሆነው አልነበረም፡፡
ዛሬ እምነትን ሰበብ በማድረግ እንደ ማግና ድር በፍቅር ተሰናስለው የኖሩትን የሁለቱን ታላላቅ ሃይማኖቶች ተከታዮችን ለማናከስ የማይሠራ ደባ የለም፤ ቅዱሳን አብያተ እምነታት በድፍረት እንዲጋዩ ይደረጋል፤ ክቡራን የሃይማኖቶች አባቶች በእምነት ቤታቸው ውስጥ እያሉ በግፍ ይታረዳሉ፤ ወላጅ አይከበርም፤ የአዛውንቶች ምክር አይተገበርም፡፡ የሀገር መሪዎች አይደመጡም፤ እምነት እንደ ባዘቶ ሳስቷል፤ ዕሴታችን ገደል ጫፍ ደርሷል፤ ቤተክርስቲያንም ሆነ መስጂድ የምንሄደው ለይስሙላ ይመስላል፡፡ የሃይማኖቱ አስተምሕሮ የሚያዝዘውን አምላካዊ ቃል በቅን ልቡና፣ በፍጹም ታዛዥነት ካልፈጸምን ቤተክርስቲያንና መስጂድ መመላለስ ምን ይፈይዳል?
አምላካዊው ትእዛዝ ‹‹አትግደል›› እያለን ወገኖ ቻችንን በፍፁም ጭካኔ የምናርድ፣ ‹‹አትስረቅ›› እያለን በላቡ ያፈራውን የድሃውን ገንዘብ የምንሞጨልፍ፣ ‹‹በሐሰት አትመስክር›› እያለን ‹‹ፌስቡክ›› በሚባለው ዘመናዊ የመረጃ መረብ አማካይነት የንፁሐንን ስም ስንበክል እየዋልንና እያደርን፣ ያልሞተውን እየገደልን፣ ያልሰረቀውን የወንጀል ድሪቶ እያከናነብን እንዴት ሰላም ይወርዳል? እንዴትስ ነባሩ ዕሴታችን ሊከበር ይችላል?
በመሠረቱ ማኅበራዊ የመረጃ መረቦች ለመረጃ ልውውጥ አስፈላጊነታቸው አያጠራጥርም፤ ይሁን እንጂ እኛ ደግሞ ለመዘላለፊያ ሕዝብን ከሕዝብ ማፋጃ በአጠቃላይም የእረኝነት ማሰልጠኛ
አድርገናቸዋል፡፡ የሠለጠኑ አገሮች ሕዝቦች የመረጃ መረቦችን የእውቀትና የትክክለኛ መረጃዎች መለዋወጫ አድርገው በወጉ ሲጠቀሙባቸው እኛጋ ደግሞ ሁሉም ተንታኝ፣ ሁሉም የረቀቀ ፖለቲካኛ፣ ሁሉም እንከን አልባ ምሑር ሆኖባቸዋል፡፡
ሆኖም በቋንቋም ሆነ በሃይማኖት ሽፋን የሚደረጉ ሕዝብን የመለያየት ሴራዎች ሁሉ እንደታሰበው ሊሳኩ ያልቻሉት በምንም ተዓምር አይደለም፤ የሁሉም ቋንቋዎች ባለቤቶች፣ የሁሉም ሃይማኖቶች ተከታዮች የገነቡት የአንድነት ግንብ ድንገተኛ ነፋስ በነፈሰ ቁጥር በቀላሉ የሚናድ ውሽልሽል ሕንፃ ባለመሆኑ ነው፤ ምክንያቱም ግንቡ የተገነባው በጠንካራ አለት ላይ እንጂ በድቡሽት አይለም፡፡
ቋንቋና ሃይማኖት በተፈጥሮ ስስነት አላቸው፤ በሃይማኖት ቀልድ የለም፤ ቋንቋን መሠረት አድርገው የሚነሱ ጉዳዮችም እንዲሁ የቋንቋውን ባለቤቶች የማነሳሳትና የተጠቃሁ ባይነትን ስሜት በቀላሉ ማራገብ ያስችላሉ፤ ሁለቱም ለሆደ ባሻ ሰው ጥሩ ማስለቀሻ፣ ሆድ ማስባሻ ዘዴዎች ስለሚመስሉ ነው አጥፊዎቹ በእነሱ ሽፋን የሚመጡት፤ ነገር ግን በሀገራችን እውነት አንዱ የሌላውን ቤተእምነት ሲገነባ፣ ሲጠብቅና ሲንከባከብ ኖረ እንጂ በተቃራኒው ስላልሆነ ለዓለም መልካም ምሳሌ ሆነን ኖረናል፡፡
ሆኖም ለሠላሳ ዓመታት ሆን ተብሎ በተሠራው የሃይማኖቶችን ዕሴቶች የመሸርሸር ሥራ አልፎ አልፎ ብልጭ ብለው የሚጠፉ ትንኮሳዎች አሉ፤ ተገቢው ጥናትና ምርምር ተደርጎ በጊዜ ሁነኛ መፍትሔ ካልተበጀላቸው ውጤቱ ‹‹ፀጉራም ውሻ አለ ሲሉት ይሞታል›› እንደሚባለው ይሆናል፡፡
መሠረቱ ቋንቋ መግባቢያ እንጂ መለያያ ሊሆን አይገባም፤ የተፈጠረውም ለዚህ ዓላማ መሆኑን የመስኩ ሊቃውንት የሚመሰክሩት ሐቅ ነው፤ አንዳንድ ባለሙያዎች ‹‹ቋንቋ መግባቢያ ብቻ ሳይሆን የማንነት መለያ ጭምር ነው›› ይላሉ፤ ግን አማርኛ፣ ኦሮምኛ ወይም ትግርኛ የሚናገር ሁሉ አማራ ወይም ኦሮሞ ወይም ትግሬ ነው ማለት አይቻልም:: የደቡብ ሱዳን፣ የጋምቤላ፣ የኬንያና የኡጋንዳ… አርሶ አደሮች እንግሊዝኛን አቀላጥፈው ይናገራሉ፤ ግን እንግሊዝኛ በመናገራቸው ብቻ እንግሊዞች አይደሉም ሊሆኑም አይችሉም:: በቃ እንደእናት ቋንቋቸው አፋቸውን ይፈቱበታል፤ የየዕለት ሥራቸውን ይከውኑበታል:: ስለሆነም ቋንቋ ሊያግባባ እንጂ በምንም መንገድ ቢሆን የልዩነት መሠረት ሊሆን አግባብ አይደለም::
ቋንቋ እና ሃይማኖት የሁሉም ሰው ሀብታት ናቸው፤ የፈለገ ሁሉ ሊጠቀምባቸው ይችላል፤ ሊያጠፋቸው ግን መብትም ችሎታም የለውም:: እንዲያውም የሃይማኖትም ሆነ የቋንቋ ልዩነት በደንብ ካስተዋልነው የአበባ ስብስብ ይመስላል፤ አንዱ ለሌላው ጌጡ እንጂ ጎጂው አይደለም፤ አንዱ ሌላውን ያስውበዋል እንጂ ውበቱን የማደብዘዝ ተፈጥሯዊ አቅም የለውም::
አንድን ውብ ባህላዊ ስፌት እንመልከት፤ በስፌቱ ውስጥ ቀይ፣ ቢጫ፣ አረንጓዴ፣ ነጭ፣ ሰማያዊ፣ ግራጫ፣ ጥቁር፣ ወዘተ ቀለማት አሉ፤ የቀለማቱ መለያየት ለስፌቱ ውበትና ድምቀት ይሆኑታል እንጂ አንዱ የሌላውን ውበት አያደበዝዝም:: የስፌቱ ውበት መነሻና መድረሻም የቀለማቱ ኅብር ነው:: ጥቁሩ ወይም ቀዩ ወይም ሌላው ብቻውን ቢሆን ላያምር ወይም ሊሰለች ይችላል፤ የበርካታ ቀለማት በአንድ ስፌት ላይ መገኘት ግን ስፌቱ እንዳይሰለች ከማድረጋቸውም በላይ የስፌቱ ውበት ሳይደበዝዝ እስከወዲያኛው እንዲዘልቅ ያደርጉታል::
በሀገራችን ያሉና የነበሩ የሃይማኖት ተቋማት ክርስቲያኑንም ይሁን ሙስሊሙን እንደ አንድ ቤተሰብ በፍቅር አስተሳስረው አኖሩን እንጂ በምንም መንገድ ልዩነትን ሲሰብኩ አልኖሩም፤ ዓላማቸውና ግባቸውም አንዱ ሌላውን አጥፍቶ በብቸኝነት መንገሥ አይደለም፤ ለዚህ ሕያው ማስረጃ አምጡ ከተባለ ከወሎ ውጭ የትም መሄድ አይቻልም፤ በዚህ አካባቢ የሙስሊሙን መስጂድ ክርስቲያኑ፣ የክርስቲያኑን ቤተክርስቲያን ሙስሊሙ በኅብረት ሲገነቡ፣ ሲጠብቁና ሲንከባከቡ እንደኖሩ ፀሐይ የሞቀው እውነት ነው::
ይህ ሲባል ሃይማኖትን ሽፋን ያደረጉ ችግሮች አልነበሩም ማለት አይደለም፤ በሃይማኖት ካባ ተጀቡነው ፖለቲካዊ ፍላጎታቸውን ለማሳካት የሞከሩ ፖለቲከኞች በተለያዩ ዘመናት ቢከሰቱም ሕዝቡ ከብረት የፀና መስተጋብር ያለው በመሆኑ የተሰናሰለበትን ማኅበራዊ ክር በቀላሉ ሊበጥሱት አልቻሉም::
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ‹‹ክርስቲያንና ሙስሊም ተቻችለው የኖሩ ናቸው›› የሚል ተረብ እንሰማለን፤ በእኔ እምነት ይህ አይነቱ አቀራረብ የሁለቱን ግዙፍ እምነቶች ክብር የሚያጎድፍ መሠሪ አባባል ነው፤ ‹‹መቻቻል›› ማለት ‹‹ምቹ ሁኔታ እስከሚገኝ ልቻለው፤ ጊዜ ሳገኝ የማረገውን አውቃለሁ›› አይነት ተበዳይነት፤ ግን ደግሞ የጊዜ ጠባቂነት መልዕክት የያዘና ከፖለቲካዊ ሸፍጥ ነፃ ያልሆነ አጠቃቀም ነው:: የሀገራችን እውነት እንደሚያስረዳው ክርስቲያኑም ሆነ ሙስሊሙ አንዱ የሌላውን ቤተእምነት ከመገንባት አልፎ በፍቅር ተጋብቶ እና ተጋምዶ የኖረ ነው:: ከዚህ የተነሳም ወሎ ውስጥ የቱ ሙስሊም የቱ ደሞ ክርስቲያን እንደሆነ መለየት አስቸጋሪ ነው:: ለዚህም እነቄስ መሐመድ ምስክር ናቸው::
በንፁህ ልብ ላስተዋለ ወሎ ያስቀናል፤ የወሎ ሕዝብ ለሀገራችን ብቻ ሳይሆን ለዓለም ጭምር አርዓያ የሚሆን ሕዝብ ነው፤ ይህ ለከንቱ ውዳሴ የተሰነዘረ የግብዝነት አባባል አይደለም፤ ፍጹም እውነት ነው:: ወሎዬ ፍቅሩም ሆነ ጥላቻው ሰው በመሆኑ፣ ከሰብአዊ ባሕርዩ የሚመነጭ እንጂ ከሃይማኖቱ ጋር እንዲያያዝ አይፈቅድም:: ፋጡማ እና ገብረሚካኤል ወይም ወለተማርያም እና መሐመድ ከተዋደዱ በይፋ ሊጋቡ ይችላሉ፤ ተጋብተውም በፍጹም ፍቅር ሊኖሩ ይችላሉ፤ ችለው ያሳዩንም በርካታ ናቸው:: ለዚህም ነው ‹‹ወሎ ለዓለም ሕዝብ ሳይቀር አርዓያነት አለው›› የምለው::
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የሚስተዋሉት ምልክቶች ግን ይህንን ወርቃማ አብሮ የመኖር ዕሴት እንዳይሸረሽሩት ያሰጋል፤ ድሮ እንደዛሬው ዘመናዊ ትምህርት ባይስፋፋም እምነትና ግብረገብነት ትልቅ ቦታ ነበራቸው፤ የሃይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች እና ወላጆች የሚናገሩት ይደመጥ፣ ተግሳጻቸው አጥፊን ይለውጥ ነበር፤ በነባሩ ዕሴታችን ላይ በተከፈተ ተከታታይ ዘመቻ የሃይማኖት አባቶች ተሰሚነት እንዲያጡ፣ አብያተ እምነታትም ወደንግድ መደብርነት እንዲለወጡ ብዙ ተሠርቷል፤ በዚህ የተነሳ አንዳንድ የሃይማኖት አባቶች ሳይቀሩ ካድሬዎችና ነጋዴዎች ሆነዋል፤ በእምነታቸው የጸኑ፣ በአምላካቸው የቀኑ ጥቂት አባቶችም በቤተእምነታቸው ውስጥ እንዲረሸኑ ተፈርዶባቸዋል::
የመልካም ምግባርና የሞራል ትምህርት ቤት የነበሩት የሃይማኖት ተቋማት፤ የመልካም ዕሴቶቻችን መነሻ መድረሻ የነበሩት አንጋፋ እምነቶች ከፍተኛ ፈተና ላይ ናቸው፤ ተሰሚነታቸው ቀንሶ፣ የሃይማኖት አባቶች ክብር ተንኳሶ ሲታይ የወደፊት ሁኔታችን ያሰጋል፤ በእርግጥስ የሃይማኖት አባቶች ካልተከበሩ፣ ነባር ዕሴቶቻችን ከተሸረሸሩ ነጋችን የሚናፈቅ ሳይሆን ‹‹ምነው ለዚያ ቀን ባልደረስሁ›› ማለት ሊመጣ ይችላል:: ቅዱሱ መጽሐፍ ‹‹ጨው አልጫ ከሆነ በምን ይጣፍጣል›› የሚለውም ለዚህ ይመስለኛል::
የተሳሰርንበት ድር ጠንካራ ሆኖ እንጂ እንደተሠራው ጥፋት ቢሆን ኖሮ እስካሁንም ተባልተን፣ ተናክሰን አልቀን ነበር፤ እርግጥ ነው ዛሬ በብዙ ፖለቲከኞቻችን ዘንድ አገራዊ እብደት አለ፤ አብዛኛው ፖለቲከኛ ከዕሴቶቻችን በተቃራኒው ከመቆሙም በላይ አያነብም፤ ባለማንበቡም የሚመራበት እና ተከታዮችን የሚያማልልበት ወይም የሚማርክበት ርዕዮተዓለም የለውም፤ በአብዛኛው አንድን አካባቢን ወይም ቋንቋን መሠረት አድርጎ የሚደራጀውም ለዚህ ይመስላል:: በብሔር ከተደራጀ በኋላ ‹‹እታገልለታለሁ›› ለሚለው ሕዝብ ዕድገት ማመልከቻ የሚሆን ርዕዮት ስለሌለው ነጋ ጠባ ‹‹ዕገሌ የሚባል ብሔር እንዲህ አርጎሃል፤ እገሌ ጠላትህ ነው…›› በማለት ሰላማዊውን ሕዝብ፣ በተለይ ደግሞ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎችን እንደ ቀልዝ መሬት ይጠቀምባቸዋል፤ ለዘመናት ሰምና ወርቅ ሆኖ የኖረውን ሕዝብም ቀስበቀስ ባላንጣ ያደርገዋል::
ደካማ ፖለቲከኞች ሕዝቡን ባላንጣ አድርገው በእሱ ደምና አላስፈላጊ መሥዋዕትነት ጀግና ይሆኑበታል፤ ከተሳካ በላዩ ይሾሙበታል፤ ተሾመውም ይገፉታል፤ ይዘርፉታል፣ ይገርፉታል እንጂ ጠብ የሚል ነገር አያስገኙለትም፤ ካልሆነም በስሙ እየለመኑ ይከብሩበታል፤ እነሱ ልጆቻቸውን ውጭ አገር ልከው በተሻሉ ትምህርት ቤቶች ያስተምሩበታል፤ የድሀው ልጆች ደግሞ አንድም በማያውቁት ዓለም፣ ለማይገባቸው ሥልጣን ያልቃሉ፤ ወይም አብሯቸው የኖረውን ጎረቤታቸውን፣ አፈር ፈጭቶ፣ ውኃ ረጭቶ አንድ ቤት በሚመስል ቅርርብ አብሯቸው ያደገውን ጓደኛቸውን ገድለው፣ ንብረት አውድመው የወጣትነት ዘመናቸውን በከርቼሌ ይገፋሉ:: በዚህም ቀዳምያን ተጎጂዎች እነሱና ድሃ ቤተሰቦቻቸው ይሆናሉ::
‹‹እንኳን እናቴ ሞታ እንዲያውም አልቅስ አልቅስ ይለኛል›› እንዲሉ ሰላም በጠፋ ቁጥር፣ በጥሞና ማሰብ በተሳነን ቁጥር፤ በግራም ሆነ በቀኝ የምትጎዳው ይች ምስኪን ሀገራችን ናት:: ወንድምን በመግደልም ሆነ በማሳደድና በመዝረፍ ያተረፈ አገር አልነበረም፤ ወደፊትም ይኖራል ተብሎ አይታሰብም፤ መፍትሔው አንዱ የሌላውን ወግ፣ ባህል፣ እምነትና መብት አክብሮ በፍቅር እና በሰላም መኖር ነው::
አንድ ባለፀጋ ባለፀጋ ነው የሚባለው ብዙ ወርቅ፣ ብር፣ አልማዝ፣ ዕንቁ እና የመሳሰሉት የሀብት አይነቶች ሲኖሩት ወይም እነዚህን መሰል በርካታ ቤቶች፣ ተሸከርካሪዎች፣ መሬት፣ በባንክ ያለ ገንዘብና ፋብሪካዎች፣ ወዘተ ሲኖሩት ነው፤ ባለፀጋው እኒህና መሰል የተለያዩ ንብረቶች ሲኖሩት የተሟላ ባለፀጋ ይሆናል እንጂ አንድም የሚያጣው ነገር የለም:: አንዳችን የሌላችንን ቋንቋ ብንማር ከበርን እንጂ አልከሰርንም፤ አንዳችን የሌላውን እምነት መርሕ ብናውቅ በእውቀት ላይ እውቀት ደረብን እንጂ አንዳችም ጉዳት አያገኘንም፤ አንዳችን የሌላውን ወግ፣ ባህልና ሥነልቡናዊ ሀብቱን ብናውቅለትና ብንጋራው የጎደለንን እንሞላለን እንጂ የሚጎድልብን አንዳች ነገር የለም::
የሚጎድልብንና የምንጎድለው ቆም ብለን ማሰብ ሲሳነን ነው፤ ዛሬ በርካታ የከፍተኛ ትምህርት ቋማት በመላ ሀገራችን አሉ፤ የተቋቋሙበት ዓላማ የሀገርን ችግር መፍታት የሚችሉ ሊቃውንትን ማፍራት እንጂ የሀገር ችግር እንዲሆኑ አይደለም:: ሀገር ከሁሉም ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የምትጠብቀው የላቁ፣ የመጠቁ እሙር ማዕምራን በብዛትም በጥራትም እንዲበዙ እንጂ በመቀምር/ላፕቶፕ እና መጻሕፍት ፋንታ ጩቤና ገጀራ ይዞ አብያተ መጻሕፍት ውስጥ የሚንጎራደድ ነፍሰ ገዳይ አይደለም::
ሳይማሩ ወርቃማ ዕሴቶችን፣ ባህልና ወጎችን የቀመሩልን ወላጆቻችን፣ እንከን አልባ እምነቶችን ያወረሱን ወይም ያስተማሩን አያት ቅድመ አያቶቻችን ዛሬ ‹‹ዘመንን፣ ተማርን፣ አወቅን፣ ሰለጠንን፣ መጠቅን…›› ብለን የምንመጻደቅ የኅሊና ድኩማን የምንሠራውን ጉድ ቢያዩ እንዴት ያፍሩብን ይሆን? ዋነኛው ችግራችን የኅሊና ድኩምነት ነው፤ ኅሊናችን ቢታከም በዙሪያችን ያለውን ጥቁር መጋረጃ መመልከት እንችላለን፤ ተመልክተንም ጥቁሩን መጋረጃ ቀዳድደን መጣል አያቅተንም፤ ዙሪያችንን ለመመልከት ደግሞ ዕሴቶቻችንን ማወቅ፣ አውቀንም ተግባራዊ ማድረግ ነው::
ወላጆቻችን በፍቅርና በሰላም የኖሩት ራሳቸው በቀመሯቸው፤ ቀምረውም ለዘመናት በተማሩባቸው የሃይማኖት፣ የቋንቋ እና የባህል ዕሴቶቻቸው ነው፤ እኛም ያውም በ21ኛው ክፍለ ዘመን የወላጆቻችን ጠቃሚ ቅርስና ውርስ የሆኑትን ዕሴቶች ሥራ ላይ ከማዋል እና ሰላማችንን የምናስከብርበት፣ ሀገራችንን ወደሚታሰበው ከፍታ የምንወስድበት ሌላ አማራጭ የለንም፤ ዋና ዋናዎቹ ዕሴቶቻችንም መከባበር፣ ሰላም፣ መተባበር፣ አንድነት፣ መተዛዘን፣ መረዳዳት፣… ናቸው::
መከባበር፣ ሰላም፣ መተባበር፣ አንድነት፣ መተዛዘን፣ መረዳዳት፣… ታዲያ ማንን ይጎዳሉ? ማንንስ ጎድተው ያውቃሉ? ዓይነ ኅሊናችንን በደንብ በገለጥን ቁጥር ዕድፍ ጉድፎቻችን ቁልጭ ብለው ይታዩናል፤ ዕድፍ ጉድፋችንን ካወቅን ደግሞ እሱን ማጽዳቱ ቀላል ይሆናል:: በመሆኑም በሰብዓዊነት እንጂ በጎጥ ወይም በሰፈርተኝነት ደዌ ሳንታመም በዚያም በዚህም ጉሸማ የበዛባትን ሀገራችንን ልንጠብቃት፣ ጠብቀንም ወደነበረ ክብሯ ልንመልሳት ይገባል::
‹‹የጨው ክምር ሲናድ ያወቁ አለቀሱ፤ ያላወቁ ላሱ›› እንዲሉ ለዕሴቶቻችን ተገቢውን ክብርና ቦታ ሰጥተን ካልተጠቀምንባቸው፣ ተጠቅመንም ለልጆቻችን ካላስተማርናቸው ውጤቱ ከዛሬውም የከፋ ሊሆን ይችላል፤ ዩኒቨርሲቲዎቻችንም ለንዑዳን ክቡራን ዕሴቶቻችን ተገቢውን ትኩረት በመስጠት ጥልቅ ጥናትና ምርምር እንዲደረግባቸው፣ ጥቅም ጉዳታቸው የበለጠ እንዲታወቅ በማድረግ ረገድ ጠንካራ ሥራ ይጠበቅባቸዋል::
እንዲህ ሲሆን የገጠሙንን ሀገራዊ ወቅታዊ ችግሮች ሁሉ በአሸናፊነት መወጣት እንችላለን፤ ‹‹ሰማይ ተቀደደ› ቢሉት ሽማግሌ ይሰፋዋል›› አለ እንደሚባለው ዕሴቶቻችን ለችግሮች ሁሉ ዘላቂ መፍትሔ የመስጠት አቅም አላቸው፤ ባለደምን ‹‹በቃ›› ብሎ የማስታረቅ፣ እንደ ጅረት የሚወርድን ደም የማድረቅ አቅም ያላቸው አበጋርን የመሰሉ ጥልቅና ነባር ዕሴቶች አሉን:: እንወቃቸው፣ እንጠቀምባቸው፤ ያለጥርጥር ችግሮቻችንን ሊፈቱልን ይችላሉ::
ማንኛውም ሃይማኖት ፍቅርን እንጂ ጥላቻን አይሰብክም፤ ማንኛውም ቋንቋ ያግባባል እንጂ አያራርቅም፤ የሚያራርቀው ሆነ ብለን ስናበላሸው ነው፤ ሌሎችን በጥሞና ለማዳመጥ ጆሯችንን በደፈንን ቁጥር እንደባቢሎን ግንበኞች ቋንቋችን ይለያይና ሰላማዊው ኑሯችን ይበጠበጣል:: የሌሎችን ባህል፣ ወግና ሥርዓት በአንቋሸሽን ቁጥር ‹‹የእኛ›› የምንለውም ለአደጋ ይጋለጣል::
ስለሆነም ባህለ ብዙህነታችን፣ ልሳነ ብዙ መሆናችን ለመለያየት ሳይሆን ለሰላም፣ ለዕድገትና ለጠንካራ ኢትዮጵያዊነት በእጅጉ አስፈላጊ ናቸው:: ቋንቋ፣ ሃይማኖትና ዕሴቶቻችን የዕድገት በሮቻችን ስለሆኑ እንጠብቃቸው፤ እንንከባከባቸው፤ እንጠቀምባቸው፤ እናተርፍባቸዋለን፤ አንከስርባቸውም፤ እንዲያውም ከገጠሙን አገራዊ ፈተናዎች ሁሉ በብቃት ያሳልፉናል::
ዕሴቶቻችን የታላቁ አዳራሻችን ምሰሶዎች ናቸው፤ ምሰሶ ከሌለ አዳራሽ መቆም አይችልም፤ ንዑዳን ዕሴቶቻችን ከጠፉም መሰባሰቢያችን፣ ብቸኛዋ አዳራሻችን ኢትዮጵያ ጠንክራ መቆም አትችልም፤ ቅዱሱ መጽሐፍ እንደሚለውም እናንተ ምሑራን የምድር ጨው ናችሁ፤ ጨው አልጫ ከሆነ በምን ይጣፍጣል? የሕይወት ምግባችን መራራ፣ ፍጻሜያችንም አሳርና መከራ ይሆናል::
ከዚህ ይሠውረን!!
በአበረ አዳሙ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 30 ቀን 2014 ዓ.ም