አዲስ አበባ፡- ከጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዓብይ አህመድ ወደ ሥልጣን መምጣት ወዲህ የግል መገናኛ ብዙኃን መነቃቃት ቢያሳዩም አሁንም በተግዳሮት ውስጥ መሆናቸው ተገለጸ።
የአዲስ ማለዳ ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ አቶ ታምራት አስታጥቄ በተለይም ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለጹት ባለፈው አንድ ዓመት ውስጥ በታየው የፖለቲካ ለውጥ አዳዲስ የመገናኛ ብዙኃን እንዲመጡ አድርጓል።አዲስ ማለዳ ጋዜጣም አንዱ መሆኑን አስታውሰው፤ ከአዳዲስ የመገናኛ ብዙኃን መፈጠር በተጨማሪም የፈለጉትን ጉዳይ የመዘገብ ነፃነት እንዳለ ይገልጻሉ።
የሃሳብ ነፃነት ቢኖርም የመረጃ ነፃነት ላይ ግን አሁንም ችግሮች እንዳልተቀረፉ ነው የሚናገሩት።የመንግሥትም ይሁን የግል መስሪያ ቤቶች ላይ መረጃ ተጠይቀው ያጉላላሉ።ደብዳቤ ጠይቀው ከተሰጣቸው በኋላ እንኳን መረጃውን ለመስጠት ብዙ ውጣ ውረድ ያበዛሉ።
መረጃ ላለመስጠታቸው ዋናው ምክንያት ፍርሐት ቢሆንም የብቃት ችግር፣ የተደራጀ መረጃ አለመኖርና መረጃውን አቀናብሮ የመስጠት ችግር አለባቸው። በተለይም ዛሬ ነገ እያሉ መገናኛ ብዙኃን በሚፈልጉት ጊዜ መረጃውን እንዳያገኙት ማድርጋቸው ዋናው ተግዳሮት እንደሆነባቸው ጠቁመዋል።
እንደ አቶ ታምራት ገለጻ የመገናኛ ብዙኃን ነፃነት ባለፈው አንድ ዓመት የተሻለ ቢሆንም አሁንም ድረስ የመንግሥት ደጋፊ እና ተቃዋሚ የሚለው ሃሳብ መኖሩ ለሥራ እንቅፋት ሆኗል።የጋዜጠኝነት ሙያ ዋነኛ መለያ የሆነው ሚዛናዊነት አሁንም ክፍተት በመኖሩ የአንድ ወገን ልሳን የመሆን አዝማሚያ እንደሚታይም ጠቁመዋል።
በማተሚያ ቤቶች አካባቢ ከፍተኛ ችግር እንዳለ የሚገልጹት አቶ ታምራት የቅዳሜ ጋዜጣ የሆነችው አዲስ ማለዳ አብዛኛውን ጊዜ ዕሁድና ሰኞ ነው የምትደርሰው።ይሄም የማተሚያቤቶች አለመዘመን አንዱ የህትመት መገናኛ ብዙኃን ተግዳሮት መሆኑን ነው የተናገሩት።
ህዳር ወር ተጀምራ በዚያው ወር የተቋረጠችው የአዲስ ዘይቤ ጋዜጣ ማኔጂንግ ኤዲተር አቶ አቤል ዋቤላ በበኩላቸው፤ አሁን ላይ የፕሬስ አፈና ባይኖርም ገበያው ከሃያ ዓመት በላይ በአፈና ውስጥ ስላለፈ የፕሬስ ኢንዱስትሪ አትራፊ ሊሆን አልቻሉም። የግል የህትመት ውጤቶች ማስታወቂያ ማግኘት አይችሉም።በዚህ ምክንያት አዳዲስ ጋዜጦች ገበያውን መቀላቀል ከብዷቸዋል። አዲስ ዘይቤ ጋዜጣም የተቋረጠችው በዚሁ ምክንያት መሆኑን ተናግረዋል።
እንደ አቶ አቤል ገለጻ መንግሥት የፕሬስ አፈናን ቢያስቀርም አሠራሩን ግን አላሻሻለም።ከዶክተር ዓብይ መምጣት ወዲህ የወረቀት ዋጋ 30 በመቶ ጨምሯል።የፕሬስ ኢንዱስትሪ እንደ የሽንኩርትና የቲማቲም ገበያ መሆን የለበትም፤ ፕሬሱን እንደመንግሥት አካል ማየት አለበት።ለዚህም ከማተሚያ ቤት ጀምሮ ያለውን የወረቀት ዋጋ መወደድ ማስተካከል እንዳለበት አሳስበዋል።
የአሐዱ ኤፍ ኤም 94.3 ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ጥበቡ በለጠ እንደሚናገሩት፤ ባለፈው አንድ ዓመት ውስጥ የፕሬስ ነፃነት ታይቷል።የታሰረ ጋዜጠኛ የለም፤ በይዘት ምክንያት የተዘጋ መገናኛ ብዙኃን የለም።ከዚህ በፊት የነበሩና የተዘጉ ጋዜጦችና መጽሔቶች እንደገና ሥራ መጀመር ባለፈው አንድ ዓመት የታየ ለውጥ መሆኑን ይገልጻሉ፡፡
‹‹ባለፉት 27 ዓመታት የህትመት ሚዲያው ሰዎች እየገቡ የሚተውት ነው።ታስረው ተንገላተው ነው ጥለውት የወጡት፤ ይሄንን ሁኔታ እያየ አንድ ወጣት 27 ዓመት ቆይቷል ማለት ነው›› በዚህም ምክንያት አስፈሪ ሁኔታ እንደፈጠረ ነው በመሆኑም ባለፈው የነበረው ሁኔታ በፈጠረው ፍርሐት አዳዲስ መገናኛ ብዙኃን የማቋቋም ፍላጎቱ አንደሚጠበቀው አለመሆኑን ተናግረዋል።
በሌላ በኩል የወረቀት መወዳድና የገበያው አስቸጋሪ መሆን በተለይም የህትመት መገናኛ ብዙኃን እንዳይስፋፉ ተግዳሮት ሆኗል።መንግሥት ይህን ችግር በቅርበት መከታተል እንዳለበትና ከግል የመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች ጋር መወያየት እንዳለበትም አሳስበዋል።
በኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለሥልጣን የኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ገብረጊዮርጊስ አብርሃ በበኩላቸው፤ በብሮድካስትም ይሁን በህትመት ሚዲያ ቀደም ሲል ከነበረው በተሻለ አዳዲስ የመገናኛ ብዙኃን እየመጡ ነው። በ2011 ዓ.ም 13 ጋዜጣ እና 13 መጽሔት በድምሩ 26 የህትመት ውጤቶች ፈቃድ ወስደዋል።እነዚህ የህትመት ውጤቶች ፈቃድ ይውሰዱ እንጂ አንዳንዶቹ በራሳቸው ምክንያት ሥራ ያልጀመሩም፤ አንዳንዶችም ጀምረው የተቋረጡ አሉ።በአሁኑ ወቅት የተጀመረውን የመገናኛ ብዙኃኑን ለውጥ ለማስቀጠል ጋዜጠኞች የሙያውን ስነ ምግባር ማክበር እንዳለባቸው አሳስበዋል።
አዲስ ዘመን ቅዳሜ መጋቢት 21/2011
በዋለልኝ አየለ