በቡድኖች ወይም በግለሰቦች መካከል የሚደረጉ ግጭቶች ወይም አለመግባባቶች ሁለት ነገሮችን ይዘው ሊመጡ እንደሚችሉ በመስኩ ጥናት ያደረጉ ምሁራን ይናገራሉ። አንደኛው አወንታዊ (ጥሩ ዕድል ) ሲሆን፤ ሌላኛው ደግሞ አሉታዊ (መጥፎ እና አጥፊ አጋጣሚዎችን) ነው:: ግጭትም በዚህ መልኩ የሚገለጹ መንታ ገጾችን የተላበሰ ሲሆን፤ ሊታወቅ የሚገባው አንኳር ጉዳይ ግን ግጭቱ ወይም አለመግባባቱ በአጭሩ ካልተቀጨ እጅግ ለማሰብ የሚከብዱ አውዳሚ ጦርነቶችን የሚፈጥር መሆኑ ነው:: ይሄንንም በዚሁ በአገራችን ተመልክተናል:: ነገር ግን በግጭቶች ሳቢያ የሚከሰቱ የትኛውንም ዓይነት አውዳሚ ጦርነቶች መደምደሚያቸው ቁጭ ብሎ መነጋገር፣ መወያየት በመጨረሻም ከስምምነት መድረስ ነው::
በርካታ የፖለቲካ ጠበብት በተለያዩ ጥናቶቻቸው ላይ እንዳመላከቱት፣ በሁለት ኃይሎች መካከል የሚፈጠርን አለመግባባት ወይም ግጭት ለማስቆም የሚደረጉ የውይይትና ድርድር ዓይነቶች በርካታ ናቸው:: እነኝህን የውይይትና ድርድር ዓይነቶች መቼ፣ በምን ሁኔታዎች ላይ እንጠቀማቸዋለን የሚለው እና የሚያስከትሏቸው ውጤቶች በተወያይና ተደራዳሪዎቹ ወቅታዊ አቋም እና ጥንካሬ የሚወሰን ነው:: ከተወያዮቹ ወይም ከተደራዳሪዎቹ አንዱ ጠንካራ ከሆነ፤ ጠንካራ የሆነው ተደራዳሪ ከግጭቱ ወይም በጦርነቱ ከተሸነፈው ወገን የተሻለ ጥቅም እንዲያገኝ በድርድሩ ላይ ጫና ስለሚያሳደር፤ በሚደረገው ውይይትና ድርድር ሂደት ብዙውን ጊዜ የተሻለ ጥቅም እንደሚያገኝ ይታመናል:: በአንጻሩ በግጭቱ የተሸነፈው አካል ህልውናው ከነጭራሹ እንዳይጠፋ በማሰብ በርካታ ጥቅሞችን እያጣ መሆኑን እያወቀም ለውይይትና ድርድር ይቀመጣል:: በውይይትና ድርድሩም ሳይወድ በግድ ይስማማል።
ለዚህም በናፖሊዮን ቦና ፓርት ዘመን የተሸነፈችው ፈረንሳይ በ1815 እ.ኤ.አ በተካሄደው በቬናው ጉባኤ ያጣቻቸው ግዛቶች እና ጥቅማ ጥቅሞች የሚታወቁ ናቸው። በዚህ ጉባኤ የተደረገው ድርድር ፈረንሳይ ከጦርነቱ በፊት በኃይል ይዛቸው የነበሩ የበርካታ አገራትን ግዛቶች እንድትለቅ በማድረጉ የአውሮፓ ካርታ እንደገና እንዲዋቀር እስከማድረግ የደረሰ የውሳኔ ስምምነት የተደረሰበት ነበር።
በጦርነት የአሸነፈ አካል በጦርነት የተሸነፈን አካል በድርድር ወቅት ከሚያገኛቸው ጥቅሞች የተሻሉ ስለመሆናቸው ሌላው ማሳያ ደግሞ በአንደኛው እና በሁለተኛው የዓለም ጦርነት የተሸነፉት ጀርመን እና አጋሮቿ በድርድር ሰበብ የተወሰነባቸውን ውሳኔ ብቻ ማየቱ በቂ ነው። ጀርመን እና አጋሮቿ በድርድር ሰበብ በጣም በርካታ ግዛቶችን ከማጣታቸውም በላይ እንዲከፍሉ የተወሰነባቸው የጦርነት ካሳ እጅጉን ከፍተኛ ነበር። ለዚህ ያበቃቸው ደግሞ በጦርነት ተሸነፍው ለድርድር በመብቃታቸው ነበር:: ጀርመን እና አጋሮቿ በርካታ ብሔራዊ ጥቅሞቻቸውን ቢያጡም በአሸነፊዎች ወገን ከነጭራሹ ከመጥፋታቸው በፊት የተጣለባቸውን ውሳኔ መቀበል የግድ ስለነበር ተቀብለውታል።
አንድ አንድ ጊዜም ሁለት በጉልበት ተመጣጣኝ ኃይሎች ከጦርነት በኋላ የሚያደርጉት ድርድር Collaborating ወይም ሁለቱም ኃይሎች ጥቅማቸውን የሚያስከብሩበት እና በተመሳሳይ ሁለቱም የሚያሸንፉበት ድርድር ይሆናል:: ይህ ማለት ግን ሁልጊዜም በጦርነት ያሸነፈ ወገን በድርድር የተሻለ ዋጋ ይኖረዋል ማለት ግን አይደለም። የዓለም ታሪክም የሚያሳየው ይህን እውነታ ነው::
ሰላም ለአንድ አገር እድገት የማይተካ ሚና እንዳለው ማስረዳት ሙቅ እንደማላመጥ ይቆጠራል:: በአንድ አገር ሰላም ለማምጣት መሪና ተመሪው ኃይል በርካታ ማይሎችን መጓዝ ይጠበቅባቸዋል:: በርካታ ማይሎችን መጓዙ ብቻውን በቂ ስላልሆነ የታሰበውን ሰላም በአንድ አገር ለማምጣት በበርካታ አድካሚ ማይሎች ጉዞ ውስጥ የጉዟችንን እያንዳንዱን እርምጃ በጥበብ መራመድ እንዳለብን የሚያሳይ ጥበበኛ መሪ እና በትዕግስት መሪውን የሚከተል ሕዝብም ያስፈልጋል:: ጥበበኛ መሪ ሰላምን ለማምጣት ከሚያደርጋቸው ጉዞዎች መካከል ውይይት ወይም ድርድር አንዱ ነው:: ምክንያቱም ሁሉንም ችግሮች በጉልበት መፍታት የሚጠበቀውን ውጤት ሊያመጣ አይችልም። እናም አንድ አገር የትኛውንም ያህል ጉልበት ቢኖራት ብሔራዊ ጥቅሟን ለማሟላት ሁልጊዜ ጉልበትን እንደ አማራጭ አትወስድም:: መውሰድም የለባትም::
በነገራችን ላይ በዓለም ላይ የሚገኙ አገራት ሁነኛ የአገራቸውን ፖሊሲ እና ስትራቴጂ የቀረጹት ከግጭት ማግስት ካደረጓቸው ስምምነቶች ወይም ድርድሮችን እንደመነሻ ተጠቅመው መሆኑን የፖለቲካ እና የታሪክ ምሁራን ያስረዳሉ። (major public policies are the outcome of a complex round of negotiation between interests, choices between values and competition between resources) … there are no single ‘best’ options for any player in this game, for the ‘best’ outcome depends on what others do and what deals are possible.”):: ይህ የሆነው ደግሞ አገራቱ ከውጭም ሆነ ከውስጥ ኃይሎች ጋር ያላቸውን ግጭት መነሻ አድርገው በሚደርሱት በሚከውኑት ውይይትና ድርድር እንዲሁም በሚደርሱት ስምምነት መሠረት ነው::
ኢትዮጵያም ዛሬ በውስጥ የገጠማትን ችግር በውይይት ተነጋግሮ በሰላም ለመፍታት እየሠራች ትገኛለች:: ይሁን እንጂ ሰላምን እንደጦር ወይም አውዳሚ ቦምብ አጥብቆ የሚፈራው ሕወሓት፤ የኢትዮጵያ መንግሥት ብዙ ሺህ ማይሎችን ተጉዞ ለሰላም እጁን ቢዘረጋም የተፈጠረውን ችግር በውይይትና ምክክር ለመፍታት የሚያሳየው ቁርጠኝነት እጅጉን የላላ ነው። በኢትዮጵያ መንግሥት ልክ ለሰላም ብዙ ማይሎችን መሄድ ባይችል እንኳን ለሰላም ብዙ ማይሎችን ተጉዞ ችግሮችን በውይይት ለመፍታት የሚፈለግን አካል ድካም ከምንም ባለመቁጠር በዚህ ልክ በድርድር መንገዱ ላይ የቅድመ ሁኔታ ጋሬጣዎችን በመደርድር አገሪቱ ሰላም እንዳትሆን አበክሮ መሥራት ምን የሚሉት «ግብፀኝነት» እና ግበተኝነት ነው?
በእርግጥ ውይይትና ድርድር ሲካሄድ ሊቀመጡ የሚገባቸው በርካታ ቅድመ ሁኔታዎች ሊኖሩ ይችላሉ:: ይሁን እንጂ ሕወሓት ከጀምሩም ወደ ውይይት እመጣለሁ ያለው ለሰላም አልወያይም አለ ተብሎ ዓለም አቀፍ ጫናዎች እንዳይደርሱበት በማሰብ ነው:: ለዚህም ነው ተደጋጋሚ በመንግሥት በኩል የተደረጉ የሰላም ጥረቶችና ጥሪዎች በቡድኑ በኩል በቅድመ ሁኔታና እንቢታ ምክንያት ሳይሳኩ የቆዩት:: አሁንም ቢሆን ሕወሓት ለውይይት ዝግጁ ነኝ ይበል እንጂ ለውይይት ከሚያደርጋቸው ዝግጅቶች ይልቅ አደናቃፊ ቅድመ ሁኔታዎችን በመደርደር ተጠምዶ ይታያል:: ምክንያቱም ምሁራን እንደሚስማሙበት ውይይት ወይም ድርድር የሚያደርጉ አካላት ከውይይት በፊት ሊያደርጓቸው የሚገቡ አራት ደረጃዎች አሉ:: እነዚህም ግንዛቤ (awareness)፣ ራስን ማዘጋጀት (self-preparation)፣ ግጭት ቅነሳ (conflict reduction) and ስምምነት (negotiation) የሚባሉት ናቸው። ሕወሓትም ውይይት ለማድረግ ያለውን ቁርጠኝነት ለመገምገም ይቻል ዘንድ እነኝህን አራት ቀድመ ሁኔታዎች ከእርሱ ባህሪ አኳያ አንድ ባንድ ማየቱ ተገቢ ነው::
የውይይት/ድርድር የመጀመሪያው ደረጃ ግንዛቤ (awareness) የሚባለው ነው:: ከዚህ አኳያ ሕወሓት ስለ ውይይት/ድርድር ያለው ግንዛቤ ከልጅነቱ ጀምሮ ውይይትንና ቁጭ ብሎ ስለ ሰላም ማውራትን እንደ ፍርሃት የሚቆጠር ነው:: ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ ግን ሕወሓት አንድ አንድ ጊዜ ውይይት/ድርድርን ለማጥፋት ዝግጅት እንደ ጊዜ መግዣ ሲጠቀምበት ነው የሚታወቀው:: ከዚህ ውጪ ከውይይትና ድርድር ፖሊሲዎችን እና ስትራቴጂዎችን መንደፍ የሚችል አቅም ሆነ ሞራል የሌላቸው የግብተኞች ስብስብ ነው::
ለዚህ እንደማሳያ አንድ ምሳሌ ላስታውሳችሁ፡- ሕወሓት የጨረቃ ምርጫ ከማድረጉ እና በመከላከያ ላይ ጥቃት ከመፈጸሙ በፊት በአገራችን «ዝናብ የሚያፍራቸው» አንቱ የተባሉ የአገር ሽማግሌዎችን መንግሥት መቀሌ ድረስ ልኮ ቢያስለምነው ለሰላም መለመንን እንደ ፍርሃት የሚቆጥረው ወያኔ እንኳንስ የሰላም ጥሪውን ሊቀበል ይቅርና ከኢትዮጵያ ባህል በፈነገጠ አኳኋን ለሽምግልና የተላኩ ሰዎችን ጦርነት በመጠማታቸው ወታደሮቹን በማስፈትሽ እና ክብራቸውን ዝቅ በማድረግ ሽማግሌዎችን አዋረደ::
ሌላው እና ሁለተኛው የሰላም ውይይት ደረጃ ራስን ማዘጋጀት (self-preparation) የሚባለው ነው:: ከዚህ አንጻር መጀመሪያውኑ ውይይትና ድርድርን እንደፍርሃት የሚቆጠር ድርጅት እንዴት ሆኖ ራሱን ለሰላም ውይይት ሊያዘጋጅ ይችላል? ሕወሓት ራሱን ለሰላም ውይይቱ እንዳላዘጋጀ ከምንመለከትባቸው መነጽሮች አንዱ ከውይይቱ በፊት የኢትዮጵያ መንግሥት ሊያሟላቸው የሚገባቸው ነገሮች ብሎ ያስቀመጣቸው ቅድመ ሁኔታዎች ናቸው:: እነኝህ ቅድመ ሁኔታዎች በውይይት የሚፈቱ ሆነው ሳለ፤ ሕወሓት ሆነ ብሎ የሰላም ውይይቱን ለማጨናገፍ በማሰብ ቅድመ ሁኔታዎችን በማስቀመጥ እነኝህ ቅድመ ሁኔታዎች ካልተሟሉ ውይይትን አታስቡት፤ በቅርቡ ጦርነት እከፍታለሁ እያለ የሚታወቅበትን የጦርነት ነጋሪት እየጎሰመ ነው:: የሽብር ቡድኑ ለድርድር ዝግጁ አለመሆኑን ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብም በተግባር እያየ ነው::
ለምሳሌ፣ ነዳጅ ወደ ክልሉ እየገባ ቢሆንም፤ ምንም ነዳጅ እየገባ እንዳልሆነ በማስመሰል እና የዓለም አቀፉን ማኅበረሰብ ለማታለል በማሰብ ነዳጅ አልገባልንም፤ ስለዚህ ቁጭ ብለን ስለሰላም ለመነጋገር እንቸገራለን ሲል ይደመጣል:: ይሄንና መሰል ቅድመ ሁኔታዎች ካልተሟሉ አይደለም ቁጭ ብዬ ስለሰላም ልወያይ በቅርብ ጊዜ ውጊያ እከፍታለሁ እያለ ነጋሪት ይጎስማል::
በሦስተኝነት የሚጠቀሰው ቅድመ ውይይት/ድርድር ዝግጅት ደግሞ ግጭት ሊያባብሱ ከሚችሉ ነገሮች ራስን መገደብ (conflict reduction) የተሰኘው ነው። ከዚህ አንጻር ሕወሓት የሚያደርገውን ለተመለከተ ስለ ሰላም ቁጭ ብሎ መወያየትን አንድም ቀን አስቦ የማያውቅ መሆኑን በግልጽ አሳይቷል:: በአፈ ቀላጤዎቹ እና የጥፋት ቡድኑ መሪዎች በየቀኑ ከሚሰጣቸው መግለጫዎች ባለፈ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ራሱን አስመስሎ በፈለፈላቸው የጥፋት እሳት ተሸካሚ ፈረሶች አማካኝነት የሚያደርጋቸው ጥፋቶች ኢትዮጵያውያንን ምን ያህል እንዳቆሰሉ የሚታወቅ ነው::
ከዚህ ባለፈም ግጭት ሊያባብሱ ከሚችሉ ነገሮች ራስን ከመገደብ አኳያ ስለ ሰላም ለመነጋገር ለአፍታም አስቦበት እንደማያውቅ ሁነኛ ማሳያው ደግሞ የትግራይ ክልል አዋሳኝ በሆኑት የአማራ እና የአፋር ክልሎች ከሚያደርጋቸው ትንኮሳዎች በተጨማሪ በቤኒሻንጉል፣ በወለጋ እና ሌሎች አካባቢዎች በወኪሎቹ አማካኝነት በዜጎች ላይ የሚያደርሰው አሳዛኝ የሆነ ጭፍጨፋ ነው:: በዚህም የሽብር ቡድኑ ሦስተኛውን የውይይት/ድርድር ቅደመ ሁኔታ ቀረጣጥፎ መብላቱን፤ ስለሰላም ለመነጋገርም ዝግጅት የሌለው ስለመሆኑ አሳይቶናል::
የመጨረሻው እና አራተኛው ደረጃ ደግሞ (negotiation) የሚባለው ነው። አራተኛው ደረጃ ላይ ለመድረስ መጀመሪያ ያሉትን ሦስት ደረጃዎች አምኖ መቀበል ይጠይቃል። የሽብር ቡድኑ ግን የሰላም ውይይትን እንደ አውዳሚ ቦምብ ፈርቶ የሚይዘውን የሚጨብጠውን አጥቶ እየተርመጠመጠ ይገኛል። ይሄንን ከሚያረጋግጡልን ተጨማሪ ማሳያዎች መካከል ደግሞ ውይይቱን የሚመሩት አካላት እኔ ያልኳቸው ብቻ ካልሆኑ ለውይይት አልቀርብም እያለ በየአጋጣሚው የሚያስተጋባው ጩኸት ነው::
እንደሚታወቀው በርካታ ዓይነት የግጭት ማቆሚያ ስልቶች አሉ:: አንደኛው negotiation የሚባለው ሲሆን፤ በዚህም የሦስተኛ ወገን ጣልቃገብነት ሳይኖር ሁለቱ የተጣሉ ወገኖች ብቻ እርስ በራሳቸው በመነጋገር ችግሮቻቸውን የሚፈቱበት ስልት ነው:: በዚህ ዘዴ የኢትዮጵያ መንግሥት እና የሽብር ቡድኑ ስምምነት ያደርጋሉ ተብሎ አይታሰብም:: ምክንያቱም ከላይ ለመጥቀስ እንደሞከርኩት ከጦርነቱ በፊት በአገራችን ዝናብ የሚያፍራቸውን የአገር ሽማግሌዎች እንዴት አድርጎ እንዳዋረደ ተመለክተናል:: በመሆኑም ይህ ግጭትን የማስወገጃ ዘዴ ጊዜው አልፎበታል::
ሌላኛው ግጭትን የማስወገጃ ዘዴ ደግሞ mediation የሚባለው ሲሆን፤ በዚህ ዘዴ ሦስተኛ ወገን በጉዳዩ ጣልቃ እንዲገባ ይደረጋል። ሦስተኛው ወገን ግን ሁለቱ ተደራዳሪዎች እንዲታረቁ ሁኔታዎችን ከማመቻቸት በስተቀር ይህ መሆን አለበት ብሎ ፍርድ ወይም ውሳኔ መስጠት አይችልም::
ብዙ ጊዜ ሦስተኛው ወገን የሚመረጠው በሁለቱ በተጣሉ ወገኖች ነው። ይሁን እንጂ ጉዳዩ ያሳሰበው አካል ላደራድር ብሎ መጠየቅ አይችልም ማለት ግን አይደለም። በአሁኑ ወቅትም የኢትዮጵያ መንግሥትን እና የሽብር ቡድኑ ለማደራደር ራሱን ዝግጁ የአደረገው እና ለድርድሩ በርካታ ማይሎችን የተጓዘው የአፍሪካ ህብረት በሁለቱ ወገኖች የተመረጠ ሳይሆን በኢትዮጵያ የተፈጠረው ችግር ስላሳሰበው ችግሩን ለመቅረፍ በመቆርቆር ነው:: ይህ ደግሞ ኢትዮጵያ ከያዘችው የአፍሪካ ችግር በአፍሪካ ማዕቀፍ ውስጥ መፈታት አለበት፤ ይሄን ማድረግ ይቻላል ከሚለው መርህ ጋር የሚስማማ ነው::
የአፍሪካ ህብረትም ችግሩ እልባት የሚያገኝበትን የመፍትሄ ሃሳብ ለማፈላለግ ብዙ ማይሎችን ከተጓዘ በኋላ ስለ ሰላም ቁጭ ብሎ ለመነጋገር የሚፈራው የሽብር ቡድኑ፤ የሰላም ውይይቱ እንዳይሳካ ለማድረግ የውይይት ሂደቱ በአፍሪካ ህብረት መደረግ የለበትም ሲል የእናቴ መቀነት አደናቀፈኝ እያለ ነው። የዚህ ጥረት ውጤት ደግሞ ምን እንደሚሆን ወደፊት የምናየው ይሆናል::
ምንም እንኳን አሁን ላይ በኢትዮጵያ ላለው ተጨባጭ ሁኔታ ሊያገለግል ባይችልም፤ ሦስተኛው የግጭት መፍቻ ዘዴ የሚባለውን ልጥቀስ:: ሦስተኛው የግጭት መፍቻ ዘዴ የሚባለው ደግሞ እንደ ሽምግልና የሚቆጠረውና Arbitration የሚባለው ሲሆን፤ በዚህም ሦስተኛው አካል ውሳኔ የሚያስተላለፍበት እና ሁለቱ ተደራዳሪ ወገኖች በሦስተኛው ወገን በሚያስተላልፈው ውሳኔ የግድ መስማማት ይጠበቅባቸዋል:: ለምሳሌ፣ የኢትዮ- ኤርትራ የአልጀርስ ስምምነት ለዚህ አንዱ ማሳያ ነው። እ.ኤ.አ በ1951/52 ኤርትራ በፌዴራላዊ አወቃቀር የኢትዮጵያ አካል እንድትሆን የተወሰነው ውሳኔ Arbitration በሚባለው የግጭት መፍቻ ዘዴ የተወሰነ ውሳኔ ነው:: እኔም ለዛሬው እዚህ ላይ ላብቃ! ወደፊት ሌሎች የግጭት መፍቻ ዘዴዎችን እና ፕሮሲጀሮችን ጨምሬ በማምጣት በመንግሥት እና በሕወሓት መካከል ሊደረግ ስለታቀደው የሰላም ውይይት የማስመለክታችሁ ይሆናል። እስከዚያው ቸር እንሰንብት፤ ሰላም!!
ሙሉቀን ታደገ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 29 ቀን 2014 ዓ.ም