ያኔ በልጅነት አንድ አይነት ባህሪ አለን ብለን ያመንን የሰፈር ህጻናት በራሳችን ተነሳሽነት ላወጣናቸው ህጎችም ሆነ ከታላላቆቻችን የወረስነውን የጨዋታ ደንብ ለመከተል ተስማምተን ጨዋታው ይጀመራል:: በዛ አቅማችን ከመሃላችን ህግና ደንቡን ተከትሎ ጨዋታውን ያልተጫወተ አካል ካለ ውሳኔያችን የሚሆነው ጨዋታው ፈረሰ ዳቦ ተቆረሰ በማለት ጨዋታውን ሳንጠግብ ወደየቤታችን መግባት ነበር:: ምናልባት ረባሹ ከመሃል አንድ ልጅ ብቻ ሊሆን ይችላል::
ያኔ የልጅነት ነገር ነውና ከመሃል አንድም ልጅ በመነጋገር ችግሩን ፈቶ ወደ ጨዋታችን እንድንመለስ የሚያደርግ አልነበረም:: ታዲያ ይሄን ያለፈ ልጅነቴን ያስታወሰኝ የአሁኑ የሀገሬ ሁኔታ ነው:: ምክንያቱም ጦርነት አልነው፤ ራስን የመከላከል ዘመቻም ሆነ፣ ባህላዊ ጨዋታ ብለን ብንሰይመው፤ በአጀማመሩም ሆነ በሂደቱ ምንም አስተዋጽኦ ያልነበራቸው አካላት ከመጠን በላይ የተጎዱበት በመሆኑ ነው::
ስለልጅነት ጸብና እርቅ ሳስብ ሁልጊዜ የማልረሳው የእኔና እኩያዬ ጸብ ነው:: በመሃላችን ወር ያልሞላ የእድሜ ልዩነት ከመኖሩ በላይ አንድ አጥር የምንጋራ በመሆናችን በአካልም በመንፈስም ቅርብ ነን:: ግን ምን ዋጋ አለው ለፍቅር ብቻ ሳይሆን ለጸብም ቅርብ ነን:: መጣላት ካሻን ምክንያት አናጣም፤ እራሳችን ጋር ሰበብ ካለቀብን ካንቺ አባት ይልቅ የኔ አባት ጀግና ነው በሚል የለየለት ድብድብ ውስጥ እንገባለን:: በዛው ልክ በፍቅራችን ጊዜም በአንድ ነጠላ ካላስቀደስን የምንል ነን::
ታዲያ ይሄ በረባውም ባልረባውም የሚያጣላ ፍቅር አይሉት ጥላቻ የመረራት የጋደኛዬ እናት አንድ ቀን ለሽምግልና በተቀመጠችበት አንድ ነገር አለችን:: አትታረቁ፤ እኔ የሰለቸኝ እናንተን ማስታረቅ ነው:: አስታርቄ ሳልጨርስ ለሁለተኛ የጥል ስሞታ እየመጣችሁ ስለተቸገርኩ አትታረቁ እንዲሁ እንደተጣላችሁ ሳትደራረሱ በሰላም ኑሩ ብላ ሸኘችን:: እውነት እንዳለችውም ለተወሰነ ጊዜ በጥል ውስጥ በሠላም ሰነበትን፤ ተጣልቶ አይቀርምና አላስታራቂ በቀጥታ ስንታረቅ በቀጣይ ሸምጋይ እንደሌለ አስቀድመን ስላወቅን እስካሁን በወዳጅነታችን አለን::
የሀገራችንም ሁኔታም ይሕ ይመስለኛል:: ሀገር፣ በወንድማማቾች መሃል ደም መፋሰስ ሲሆን ሃይ ባይ ገላጋይ ዳኛ ትሻለች:: ሆኖም በእኛ ሀገር ሁኔታ እንዲያስታርቋት ተስፋ ያሳደርንባቸው የሀይማኖት አባቶች ሳይቀሩ እርስ በእርስ እየተሻኮቱ በተቃራኒው ፖለቲከኞች ሊያስማሙ እላይ ታች ሲሉ ማየት እየተለመደ መጣ:: ይባስ ብሎ ቤተ እምነቶች የፖለቲካውን ጎራ ተከትለው ቀድመው ራሳቸውን ራስ ገዝ ሲያደርጉ ዝም ብሎ መስማትና ማየት እጣችን ሆነ:: ይሄን አይነት አካሄድና ሌላውም ጉዳይ ተደማምሮም በክርስትናውም ሆነ በእስልምናው የእምነት ተቋማት በኩል ከውስጥ ጉዳያቸው በዘለለ አገራዊ ችግሩን ለመፍታት የሚደረገው ጥረት እምብዛም ሆኖ አልታየም::
እናም ተው ልጆቼ የሚል የሀገር ሽማግሌም ሆነ የሃይማኖት አባት በጠፋበት ጊዜ በፌዴራሉ መንግስት ተደጋጋሚና ያለመሰልቸት ጥረት ሁለቱም ወገኖች ቆርጠው ለሰላም ውይይት ዝግጁ መሆናቸው ለዜጎች ተስፋን ያጫረ ሆኗል:: የኔ ስጋት ግን ግርግር ለሌባ ይመቻል እንዲሉ፤ ሀገር ሰላም ባለመሆኗ የእነሱ ኪስ የሞላ ራስ ወዳድ ግለሰቦች ቁጥር ቀላል ባለመሆኑ ይሄን ኪሳቸውን ላለማድረቅ ሲሉ ሂደቱን እንዳያደናቅፉት የሚል ነው:: በቅርቡ ወደ ትግራይ ክልል በህገ ወጥ መልኩ ሊገባ ሲል የተያዘው ከስምንት ነጥብ ስምንት ሚልየን ብር በላይ በጦርነት ወቅት የማትረፍ ሂደት አንዱ ማሳያ ነው::
ይህ ብቻ አይደለም የተፈጠረው ችግር በሰዎች መቸገር ውስጥ ጥቅማቸውን ለሚያሰሉ ደላሎችም ከፍ ያለ እንጀራን ይዞ የደረሰላቸው የመስላል:: ምክንያቱም ዘመዶቻቸው በትግራይ ክልል የሚገኙ ዜጎች ካላቸው ቀንሰው ለዘመዶቼ ለማድረስ ቢፈልጉ ሳይወዱ ህገወጥ ገንዘብ አዘዋዋሪዎችን በር መርገጥ ግዴታ ሆኗል:: በዚህ የተነሳም በርካቶች ተቸግረው ከሌላቸው ለወገኔ ልድረስ ሲሉ እስከ 40 በመቶ ኮሚሽን የሚቀበሉ የእኛው ወገኖች ተፈጥረዋል::
ታዲያ ሰላም ቢሰፍን ባንክ ቢከፈት ይሄ ሁሉ ብር ወገናቸውን እያስለቀሱ መሰብሰብ የለመዱ ሰዎች በቀላሉ የሥራ መስካቸው ሲዘጋ ደስ የሚሰኙም አይመስለኝም:: በማወቅም ባለማወቅም አንዱን ወገን ደግፈው ሌላውን ነቅፈው ሲተቹ የነበሩ ሰዎችም የበምን ይመጣብኛል ፍራቻ ሰላም መሆንን ሊፈሩ ይችላሉ:: ይሄ ሁሉ ለችግሩ ገፈት ቀማሽ የሀገር ልጆች ስቃይን እንጂ እፎይታን የሚሰጥ አይደለም፤ የተነጣጠሉ እናትና ልጆችን ለማገናኘት ለሚደረግ የሰላም ጥረት ተጨማሪ እንቅፋት እንጂ መፍትሄ አላስገኘም፤ አያስገኝምም:: በእነዚህ ቡድኖች የሰላም ገፊነት ምክንያት በዓለም አደባባይ በድል የነገሱ ኢትዮጵያዊ የትግራይ ልጆች እናቴ አሸነፍኩልሽ ብሎ የደስታቸው ተካፋይ ለመሆን ሲናፍቁ ማየት ያማል:: በድል ላይ ሌላ ድል በሽልማት ላይ ሌላ ሽልማት ተይዞ፤ ለተቸገረ ቤተሰብ ማካፈል አለመቻል የመኖር ትርጉሙ እስኪዛባ ድረስ ግራ ያጋባል::
አብዛኛው ህዝባችን ዘንድሮን ሳላርስ ለከርሞ ምን ልበላ ብሎ ቢሰቃይም፤ የተወሰነው ለሰብአዊ ርዳታ ተብሎ በነጻ የገባን እርዳታ ከመሸጥ ጀምሮ ብዙ አትርፏል:: ታዲያ ይህ ኃይል እንዴት ከጦርነት ይልቅ ስለ ሰላም አስቦ ሊሰራ ይችላል? በየቦታው ለተቸገሩ እርዳታ እናደርሳለን በሚል የት እንደገባ የማይታወቁ በርካታ ብሮችና የአይነት ድጋፎች ተሰብስበዋል:: ሆኖም ዛሬም የብዙዎች ሕይወት ተጎሳቁሏል:: በርካቶች የጀመሩት ህክምና ተቋርጧል፤ የነገ ተስፋዎቻቸው የሆኑ ልጆቻቸውን አጥተዋል:: በአንጻሩ በብዙሃኑ መጎሳቆል ውስጥ የተወሰኑ ግለሰቦች ሕይወት ተደላድሏል::
በመሆኑም በዚህ ጦርነት አትራፊ የሆኑ ቡድኖችና ግለሰቦች የሰላም ንግግር ሂደቱን እንዳያደናቅፉት ስጋቴ ነው:: ስለዚህ ተወያይ ወገኖች ህዝብን ያስቀደመ ውይይት እንድታደርጉ አደራ እላለሁ:: ለዚህም መፍትሄው በመነጋገርና በመተማመን ወደ ጋራ መፍትሄ መሄድ እንጂ ገና ሳይጀመር ይሄ ጉዳይ ሳይፈታ አንደራደርም በማለት በቅድመ ሁኔታ ሊሆን አይገባም:: እናንተ ፖለቲከኞች የምትመሩት ሕዝብ ከጦርነት ምንም አላተረፈም፤ ወደፊትም አያተርፍም:: ይህንን እውነታ መቀበል ካቃታችሁና የሰላም ውይይቱ በእኔ በልጥ እኔ በልጥ ስሜት ከተደረገ፤ የሰላም ውይይት መሆኑ ቀርቶ ጨዋታው ፈረሰ ዳቦ ተቆረሰ የሚባልበት ቀን ሩቅ አይሆንም:: ያኔ ማንም አሸናፊ ሳይኖር በርካታ ተሸናፊዎች ይፈጠራሉ:: ስለዚህ ጨዋታው አይፍረስ ዳቦውም አይቆረስ፤ ችግሮቻችንንም በንግግር መፍታት እንልመድ::
ከትዝታ ማስታወሻ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 29 ቀን 2014 ዓ.ም