አዲስ አበባ፡- በእነ አቶ አብዲ መሐመድ ዑመር (አብዲ ኢሌ) መዝገብ የተከሰሱ እና ያልቀረቡ 41 ተጠርጣሪዎችን የፌዴራል ፖሊስ አፈላልጎ በመያዝ ሚያዝያ 24 ቀን 2011 ዓ.ም እንዲያቀርብ የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ አራተኛ ወንጀል ችሎት ትዕዛዝ ሰጠ።
ፍርድ ቤቱ ትናንት የቀድሞው የሶማሌ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አብዲ ኢሌና ሌሎች ከፍተኛ ኃላፊዎች ጉዳይን ቀጠሮ ይዞ የነበረው በመዝገቡ ተከሳሽ ሆነው ያልቀረቡትን 41 ተጠርጣሪዎች ጉዳይ ለመመልከት እና ከማረፊያ ቤት እየተመላለሱ በመከራከር ላይ የሚገኙትን አብዲ ኢሌን ጨምሮ ስድስት ተጠርጣሪዎች የመጀመሪያ መቃወሚያ ለማዳመጥ ነበር።
በትናንት የችሎት ውሎውም ፌዴራል ፖሊስ በቀድሞ የሶማሌ ክልል ፕሬዚዳንት አብዲ ኢሌ መዝገብ የተከሰሱ 41 ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ስር ማዋል እንዳልቻለ ለፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት አስታውቋል። ከክልሉ ስፋት አኳያ ተጠርጣሪዎቹን አፈላልጎ ማግኘት አለመቻሉን ጠቁሟል። ከሶማሌ ክልል ፖሊስ ጋር ተጠርጣሪዎቹን ለመያዝ በቅንጅት እየሰራ እንደሚገኝ በመጠቆምም፤ ከቦታው ርቀትና ከክልሉ ስፋት አንጻር ረጅም ቀጠሮ እንደሚያስፈልገው በመጠቆም፤ ፍርድ ቤቱ ረጅም የጊዜ ቀጠሮ እንዲሰጠው ጠይቋል።
የተከሳሽ ጠበቆች በበኩላቸው፤ ለፖሊስ ተጨማሪ ጊዜ እንዳይሰጥ ተቃውመዋል። ፌዴራል ፖሊስ ተጠርጣሪዎቹን በቁጥጥር ስር እስካሁን ባለማዋሉ ምክንያት ጉዳዩ እየተራዘመ ነው ሲሉ አቤቱታቸውን አሰምተዋል።
ከ41 ተጠርጣሪዎች እስካሁን የተወሰኑትን መያዝ እንደነበረበት በማመልከት፤ አንድም ተጠርጣሪ አለመያዙ የፖሊስ ጥረት አናሳ መሆኑን ያሳያል ብለዋል። ሁኔታው ደንበኞቻቸውን ረጅም ጊዜ በእስር ላይ እንዲቆዩ እያደረገ እንደሆነ አመልክተዋል። ተጠርጣሪዎቹ ፍትህ የማግኘት ህግ መንግስታዊ መብታቸው እንዳይጣስ በጋዜጣ ጥሪ በማድረግ ወደ ክርክር ሂደቱ እንዲገባም አመልክተዋል።
ዐቃቤ ህግ በበኩሉ፤ ፌዴራል ፖሊስ በተገቢው መንገድ ስራውን እየሰራ አይመስለኝም ብሏል። ተጠርጣሪዎቹን ለመያዝ ተገቢ ጥረት እያደረገ ባለመሆኑ ፍርድ ቤቱ ጠንከር ያለ ትዕዛዝ ለፌዴራል ፖሊስ እንዲሰጥም ለፍርድ ቤቱ አመልክቷል። ለሶማሌ ክልል ፖሊስም ተጨማሪ ትዕዛዝ እንዲሰጥ ጠይቀዋል።
ፍርድ ቤቱ በበኩሉ፤ ፌዴራል ፖሊስ ከክልሉ ፖሊሶች ጋር በመቀናጀት እያከናወነ ያለው ስራ አድካሚና ውስብስብ መሆኑን እንደሚገነዘብ አመልክቷል። እስከ ሚያዚያ 24 ቀን 2011 ዓ.ም ተከሳሾቹን አፈላልጎ እንዲያቀርብና አቃቤ ህግ በመቃወሚያው ላይ ምላሽ ይዞ እንዲመጣ ትዕዛዝ ሰጥቷል።
የፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ የቀድሞ የሶማሌ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ አብዲ መሐመድን ጨምሮ በ47 የክልሉ የተለያዩ የሥራ ኃላፊዎች ላይ በፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት 4ኛ ወንጀል ችሎት ጥር 22 ቀን 2011 ዓ.ም. ክስ መመስረቱ ይታወሳል።
በተጠርጣሪዎቹ የቀድሞው የሶማሌ ክልል ርዕሰ መስተዳድር እነ አቶ አብዲ መሐመድ ዑመር (አብዲ ኢሌ) በክልሉ ጅግጅጋ ከተማን ጨምሮ በተለያዩ ዞኖችና ወረዳዎች በፈጠሩት ግጭት፣ 59 ሰዎች እንዲገደሉ አድርገዋል ሲል ዓቃቤ ሕግ በክሱ አስፍሯል። በጅግጅጋ ከተማና አካባቢው በተከሰተው ሁከትና ብጥብጥ በወንጀሉ ጠንሳሽነትና ተሳታፊነት መጠርጠራቸውም በክሱ ተጠቅሷል።
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን የእምነት ተቋማት፣ የመንግሥት ተቋማት፣ የግለሰቦች ቤቶችና የተለያዩ የንግድ ተቋማት ተቃጥለው እንዲወድሙ በማድረግ ከ412 ሚሊዮን ብር በላይ ጉዳት ማድረሳቸውን ዓቃቤ ሕግ በክሱ ገልጿል። በክልሉ ውስጥ የሚኖሩ ሌሎች ብሔር ብሔረሰቦች ከአካባቢው ተፈናቅለው እንዲሰደዱ ማድረጋቸውን ክሱ ያመለክታል። በክስ መዝገቡ ከተጠረጠሩት 47ተጠርጣሪዎች እስካሁን በቁጥጥር ስር የዋሉት ስድስት ብቻ ናቸው።
አዲስ ዘመን ቅዳሜ መጋቢት 21/2011
በዘላለም ግዛው