አዲስ አበባ፡- ከዛሬ ሁለት ዓመት በፊት በአዲስ አበባ ከተማ ልዩ ስሙ «ቆሼ» በተባለ ስፍራ በደረሰው የቆሻሻ መደርመስ አደጋ ቤት ንብረታቸውን ያጡ ወገኖች ከህዝቡ በተደረገልን የገንዘብ ድጋፍ ልክ መንግሥት አልደገፈንም ሲሉ ቅሬታቸውን ገለጹ።
በሞዛይክ ሆቴል ትላንት ጋዜጣዊ መግለጫ የሰጡት በወቅቱ አደጋው ሲደርስ የከፋ ተጋላጭነትን ለመቀነስ ሲባል መንግሥት ከአካባቢው ያነሳቸው ዘጠና ስምንት አባወራዎችና ቤተሰቦቻቸው ተወካዮች ናቸው።
የቅሬታ አቅራቢዎቹ ተወካይ አቶ እያሱ ገብረህይወት እንደተናገሩት ከሁለት ዓመት በፊት በአካባቢው በደረሰው የቆሻሻ መደርመስ አደጋ እሳቸውን ጨምሮ በርካታ ነዋሪዎች ቤትና ንብረታቸውን አጥተዋል። በወቅቱ በመንግሥትና በህብረተሰቡ በተደረገላቸው አስቸኳይ ድጋፍ ከአካባቢው ተነስተው በተዘጋጀላቸው ሁለት የተለያዩ መጠለያዎች በመኖር ላይ ይገኛሉ።
በወቅቱ በተጎጂዎች ስም ከመላው ሀገሪቱ በዓይነትና በገንዘብ በርካታ ድጋፎች ተሰባስበዋል። ይሁን እንጂ የተደረገውን የቁስ፣ የልብስና የምግብ ዕርዳታ በመጋዘን በማከማቸት ለተጎጂዎች ሳይደርሰ እንዲቀበር መደረጉን ያስታውሳሉ። ለዚህ ደግሞ ሰበቡ ያለምንም ጥቅም ለብልሽት መዳረጉና ጊዜው አልፎበታል የሚል ምክንያት መሰጠቱ ነው ብለዋል።
ሌላዋ የቅሬታ አቅራቢዎቹ ተወካይ ወይዘሮ ሶፍያ ሀሰን በበኩላቸው፤ በአካባቢው ከተነሱ በኋላ በመንግሥት አካላት የሦስት ወር ቀለብና ሃያ ስምንት ሺህ አንድ መቶ ዘጠና ብር መቀበላቸውን አስታውሰዋል። ከአደጋው በኋላ በሁለት የተለያዩ ቦታዎች ተጎጂዎቹ ኑሮ መጀመራቸውን ገልጸው፣ በህይወታቸው ደስተኞች አለመሆናቸውን አመልክተዋል።
እንደ እሳቸው አባባል ከነዋሪዎቹ መሀል አብዛኞቹ አካል ጉዳተኞች፣ አረጋውያንና ሕፃናት ናቸው። ሠርተው ማደር እንደማይችሉ እየታወቀም ጊዜያዊ ነው በተባለው አነስተኛ የቤት ኪራይ እንዲከፍሉ ተገደዋል። ቤቱ ለኑሮ የማያመችና ለበርካታ አደጋዎች የሚያጋልጥ ነው፤ ከተሰጠን አነስተኛ ድጋፍ የዘለለ ኑሯችንን የሚያይልን አካል ያለመኖሩ ችግራችን በመባባስ ላይ ነው ብለዋል።
ከተወካዮቹ መካከል አንዱ አቶ መስፍን እሱባለው፤በቺፑድና ቆርቆሮ የተሠራው ቤት አጥር የሌለው በመሆኑ ነዋሪው በስጋት ላይ ይገኛል። በቂ የሆነ የመጸዳጃ፣ የማብሰያና የልጆች መጫወቻ አለመዘጋጀቱም ለበሽታ እያጋለጣቸው እንደሚገኝ ጠቁመዋል።
የአዲስ አበባ ሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ በበኩሉ የተጎጂዎችን ቅሬታ በሚመለከት በቅርቡ ምላሽ እንደሚሰጥ አስታውቋል።
አዲስ ዘመን ቅዳሜ መጋቢት 21/2011
በመልካምስራ አፈወርቅ