‹‹ረጅም ርቀት መጓዝ፤በመኖርያ ቤቴ ውስጥ መንቀሳቀስ አልችልም። ደረጃ መውጣትም ይቸግረኛል። በአጠቃላይ እጄን ለመዘርጋት ወይም በጉልበቴ ለመንበርከክ ካለመቻሌም ባሻገር ጣቶቼን ተጠቅሜ የሆነ ነገር እጅግ ያዳግተኛል። ነገር ግን እስከ ተወሰነ ጊዜ ድረስ ራሴን ችዬ ባልንቀሳቀስም በመጠኑም ቢሆን ሰውነቴ ይታዘዝልኝ እንደነበር አስታውሳለሁ።
ብዙ ጊዜ ከቤት አልወጣም።ብወጣም በሸክም ነው። ዕድሜዬ እየጨመረ ሲመጣ በሸክምም ቢሆን መውጣቴ ቀረ። እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ትምህርት ቤትም መግባት አልቻልኩም ›› በማለት ሃሳቧን ያጋራችን ወጣት የውብ ዳር ታሪኩ ናት፡፡
ወጣቷ ወላጆቿ ትምህርት ቤት ያላስገቧት በአካል ጉዳተኝነት ምክንያት መሆኑን ትናገራለች። እቤት በመዋሏ በመጠኑም ቢሆን ይታዘዝላት የነበረው አካሏ መታዘዝ እየተሳነው መምጣቱን ትጠቅሳለች።አንዳንድ ትምህርት ቤቶች እንደ እኔ ዓይነት አካል ጉዳት ያለባቸውን ተማሪዎች ለማስተማር የሚያስችል ምቹ ቦታና ሁኔታም እንዳልነበራቸው ወላጆቼ ነግረውኛል ብላናለችም።
በሕገ መንግስቱ አንቀፅ 41 ንዑስ ቁጥር 5 መንግስት አቅም በፈቀደው መጠን ለአእምሮና ለአካል ጉዳተኞች እንክብካቤ ያደርጋል የሚል ሕግ መደንገጉን ወጣት የውብዳር ታስታውሳለች። በዚሁ ሕገ መንግስት አንቀጽ 90 ንዑስ አንቀጽ 1 ያለ ምንም ዓይነት ልዩነት ሁሉም ኢትዮጵያዊ የአገሪቱ የኢኮኖሚ አቅም በፈቀደው መጠን የትምህርት፤ የጤና እና ሌሎች ማህበራዊ አገልግሎቶች ተጠቃሚ መሆን እንደሚችልም መስፈሩን ትገልፃለች። ሆኖም ትምህርትን በተመለከተ እሷን ጨምሮ በርካታ እንደ እሷ የእንቅስቃሴ ችግር ያለባቸውና ሌሎች አካል ጉዳተኞች ለረጅም ዓመታት የትምህርት ዕድል ከማግኘት ተገልለው እንደቆዩ ታወሳለች።20 ዓመት እስኪሞላት ድረስ እሷ የትምህርት ዕድል ሳታገኝ መቆየቷንም እንደ ማሳያ ትገልፃለች።
እኛ አካል ጉዳተኞች ተጠቃሚና ተሳታፊ የመሆን መብታችን በሕገ መንግስቱም ሆነ በተለያዩ ሕጎች ቢሰፍርም ከወረቀት በዘለለ መሬት ወርዶ ሳይተገበርልን ለዘመናት ቆይተናል ያሉን ደግሞ አቶ እስጢፋኖስ ይህደጎ ናቸው። በዚህም ምክንያት የአካል ጉዳተኞች በከፋ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ስነልቦናዊ ጫና ውስጥ ለመኖር ተገድደው ይገኛሉም ይላሉ።
መሳለሚያ አካባቢ በሚገኘው ወረዳ 4 ነዋሪ መሆናቸውን እና እግራቸው በተፈጥሮ ምክንያት ከእንቅስቃሴ ውጪ እንደሆነ የሚናገሩት አቶ እስጢፋኖስ እንዲህ ዓይነቱን የጉዳት ሁኔታ ጨምሮ ማህበራዊና ባህላዊ ተፅዕኖ፤ ድህነትና ሌሎች ተደራራቢ ችግሮች የአካል ጉዳተኞች በግልም ሆነ ከሌሎች ሰዎች ጋር ሆነው ችሎታቸውን በመጠቀም ለህብረተሰቡ ልማት አስተዋፅኦ የሚያበረክቱበትን እንዲሁም ራሳቸውን የሚያግዙበትን ዕድል በመንፈግ ተመጽዋችና ሕይወታቸውን በፈተና የተሞላ እንዲሆን እንዳደረገ ይገልጻሉ፡፡
እሳቸው አካል ጉዳተኛ በመሆናቸው አይችልም በሚል የተዛባ አመለካከት ቁጭ ብሎ እንዲለምኑ መዳረጋቸውን ያወሳሉ። እስከ ተወሰነ ጊዜ የተዛባ አመለካከቱ ተላምዷቸው የኔ ቦታ ልመና ነው ብለው ራሳቸውን እስከ ማሳመን የደረሱበት ሁኔታ የነበረ መሆኑንም ያስታውሳሉ ።አሁን በአነስተኛና ዘርፍም ቢሆን የራሳቸውን ሥራ ከመፍጠር ባሻገር ለሌሎችም እየጠቀሙ መገኘታቸውን ሲያዩ ለራሳቸው የነበራቸው ዕምነትና ግምት የተሳሳተ እንደሆነ መረዳታቸውንም ነግረውናል።
አቶ እስጢፋኖስ ይቀጥላሉ፡፡ እኔ ሁለቱም ጆሮዎቼ አይሰሙም።በምኖርበት ማህበረሰብ ውስጥ የተዛባ አመለካከት ነበር። ከእንቅስቃሲያቸው እንደምገነዘበው በአካባቢያችን ያሉ ሰዎች ከአካባቢ ጽዳት ጀምሮ በርካታ በጋራ የሚያከናውኗቸው ሥራዎች አሉ። ሆኖም ከምን አንፃር ተረድተውና አይተውኝ እንደሆነ ባላውቅም በየትኛውም ተግባር አያሳትፉኝም። ግን ጆሮዬ ባይሰማም እጅግሬ ላይ የእንቅስቃሴ ችግር ስለሌለብኝ መሥራት እችላለሁ። ግን እስካሁን ከነዚህ ሰዎች ጋር የምግባባው በእጅ እንቅስቃሴ ነው።ሆኖም በዚህም መግባባት የቻልኩት በልምድ ነው።
አቶ ቱሉ ነገራ ዓይናቸውም ላይ ችግር አለባቸው። በአብዛኛው አጥርተው አያዩም።አንድን ነገር ማየትና መለየት የሚችሉት በጣም ቀርበውና ተጠግተው ነው። እንዲህም ሆኖ አካታችነት ትኩረት ተሰጥቶ ባለመሰራቱ እሳቸውን ጨምሮ በርካታ አካል ጉዳተኞች በአካባቢያቸው ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች አሁንም ድረስ ሙሉ በሙሉ ተሳታፊና ተጠቃሚ መሆን አልቻሉም። ግን ሙሉ ለሙሉ መሬት አይውረድና አይተግበር እንጂ አካታችነት በሁሉም መስክ እንዲተገበር የሚገልፅ ሕግ መኖሩን ያውቃሉ።
በኢትዮጵያ ውስጥ ከ20 ሚሊዮን በላይ የአካል ጉዳተኞች እንደሚገኙ ከሴቶችና ማህበራዊ ሚኒስትር ኮሚኒኬሽን ዳይሬክቶሬት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል። ሆኖም የብዛታቸውን ያህል የተለያዩ አገልግሎቶች ተደራሽ ፤ እንዲሁም በሕብረተሰቡ ውስጥ በተገቢውና በሚፈለገው መጠን ተሳታፊና ተጠቃሚ ሆነዋል ማለት የማያስችሉ የተለያዩ ችግሮች አሉባቸው። አንዱና ዋናው በሕብረተሰብ ውስጥ ያለው አመለካከት እንዲሁም በተጠቃሚነታቸው ዙርያ ያሉ ሕጎች በትክክል መሬት ወርደው እየተሰራባቸው አለመሆኑ ከብዙዎቹ ተግዳራቶች ጥቂቶቹ መሆናቸውን ከዳይሬክቶሬቱ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
እንደ መረጃው በአካል ጉዳተኞች ላይ ትልቁን ችግር የሚፈጥሩት የተዛቡ አመለካከቶች፣ የተሳሳቱ እምነቶች እና መድልዎ ናቸው።በኢትዮጵያ ውስጥ አካልጉዳተኝነት እንደ አሳፋሪና አሳዛኝ ክስተት ተደርጐ ስለሚወሰድ መገለልን ወይም ከልክ ያለፈ ከለላ ማድረግን ያስከትላል። አንዳንድ ጊዜም አካል ጉዳተኝነት እንደ እርግማንይቆጠራል፡፡
መድልዎን በመፍራት የአካል ጉዳተኛው ቤተሰቦች ግለሰቡን በቤት ውስጥ ተደብቆ እንዲቀመጥ ሊያደርጉ ይችላሉ።በተለይ በትምህርት፤በጤና፤በውሃ በጥቅሉ በማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ዙርያ ባለው አካታችነት ላይ በመመሥረት ለውጥ ማምጣትና አካል ጉዳተኛውን የሕብረተሰብ ክፍል እኩል ተጠቃሚና ተሳታፊ ማድረግ ይገባል በማለት ጽሑፋችንን ደመደምን። ፈጣሪ የሳምንት ሰው ይበለን
ሰላማዊት ውቤ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 28 ቀን 2014 ዓ.ም