ዛሬም እንደወትሮ መጠጥ ቤቱ በሰው ታጭቋል።የክረምቱ ቅዝቃዜ ውስጥ ከታጨቀው ሰው ትንፋሽ ጋር ተያይዞ መስተዋቱ አልቦታል። ተሰማ መንግስቴ እና ዘውዴ መታፈሪያ ከአሜሪካን ከመጣው አቶ ተገኝ ጋር በአንድ ጠረጴዛ ዙሪያ ተሰባስበው እየጠጡ ያወራሉ።አቶ ተገኝ ‹‹ ሰው ያላገር መሬት ያለዘር ምንም ትርፍ የለውም›› አለ።ዘውዴ ከተገኝ አፍ ከተል አድርጎ ‹‹ትክክል ብለሃል። ምንም ቢሆን በአገር መኖር ብቻውን ትልቅ ትርፍ ነው።ይህንኑ አውቀን ብንራብም ፤ ብንጠማም ነፃነታችን ቢነፈግም፤ በገዛ አገራችን ብንገፋም ከአገራችን አንወጣም ብለን ሙጭጭ ያልነው በአገር መኖር ያተርፋል ብለን ነው።ትርፉ ትልቅ መሆኑን ስላወቅን ነው›› ሲል ተሰማ መንግስቴ በሁለቱም ሃሳብ ባለመስማማት ኮስተር ብሎ ያዳምጣል።
ተሰማ ፊቱን እንዳጨፈገገ ‹‹የእኛ ችግር ሁሉንም ነገር አጠቃለን በአንድ ቅርጫት ውስጥ መክተታችን ነው።በአንድ ቅርጫት ውስጥ አንድ እንቁላል ከገማ ሁሉንም ያበላሻል።ነጥለን ማስቀመጥ ነጣጥለን ማሰብ ይጠበቅብናል።ከአገር ወጥቶ መኖር ሙሉ ለሙሉ ኪሳራ እና ውድቀት ነው ማለት አይቻልም።በአገር ውስጥም መኖር ብቻውን ትርፋማ ወይም ተጠቃሚ አያደርግም።ውጪ በመኖርም ብዙ ትርፍ አለ። ኢትያጵያ ውስጥ ሁላችንም ማለት ባይቻልም ብዙዎቻችን ለሥራ የምንሰጠው ቦታ ዝቅተኛ ነው።እንደሚታወቀው ደግሞ የተለየ ታታሪ ሰው ካልሆነ በስተቀር በሰነፍ ሰው የተከበበ ‹ሰነፍ ያሰንፋል› እንደሚባለው መስነፉ አይቀርም።የውጪዎቹ ደግሞ ጎበዞች ታታሪ ሰራተኞች ስለሆኑ ኢትዮጵያዊው አገሩ ላይ ሰነፍ ሆኖ ቢኖርም ውጪ ሔዶ ይጎብዛል›› አለ።ተገኝ በሰማው ቢቃወማቸውም በሃሳቡ እንደሚስማማ ጭንቅላቱን እያንቀሳቀሰ አሳየ።
ዘውዴ ግን መከራከር ፈለገ።አንተ ስትሆን ሁሉም ነገር ትክክል ነው።ሌላው ሰው የሚናገረውም ሆነ የሚሠራው ትክክል አይደለም።‹‹ሁሉንም ለምን ጨፍልቃችሁ ታያላችሁ? ›› እያልክ ትጠይቃለህ።በተመሣሣይ መልኩ በድጋሚ ራስህ ሁሉንም ትጨፈልቃለህ።አንተስ ልክ ነህ ? ሲል ጥያቄ አቀረበ።ተሰማ በበኩሉ ፊቱን ‹‹ምናጠፋሁ›› በሚል መልክ አኮሳትሮ የዘውዴ ጥያቄ እንዳልገባው አስመሰለ፡፡
‹‹ ኢትዮጵያውያን ሰነፍ ናቸው እያልክ ነው።ይህ ተገቢ አይደለም።እኛ የቸገረን የሚያሠራ ከባቢ ነው።የሚያሠራ ከባቢ ካለ ማንም ቢሆን መሥራቱ አይቀርም።የሚያሠራ ከባቢ ሳይፈጥሩ ሰነፍ ብሎ መሳደብ በበኩሌ ትክክል አይደለም፡፡›› እያለ ደረቱን እየገፋ መደንፋት ፈለገ።ተገኝ በመሃል ሆኖ ‹‹ሁለታችሁም ትክክል ናችሁ›› አለ።ዘውዴ በበኩሉ ‹‹ ተገኝ አሁን አንተም ተሳስተሃል።ተቃራኒ ሃሳብ እየተናገርን ሁለታችንም ትክክል መሆን አንችልም፡፡›› አለ።
ተሰማ የተገኝ ሃሳብ ላይ ምንም ተቃውሞ ሳያሰማ፤ ከዘውዴ ቀበል አድርጎ ‹‹የሚያሠራ ከባቢ የለም ምን ማለት ነው ? በቅድሚያ ይህን አብራራልኝ›› ሲል ለዘውዴ ጥያቄ አቀረበ።ለምሳሌ የእኔ ወንድም አመሸ ንግድ ፈቃድ አውጥቶ የሆነ ሥራ ለመሥራት ፈለገ።ነገር ግን በዚህ ንግድ ፈቃድ ይህንን መሥራት አትችልም ተብሎ ተከለከለ።በተቃራኒው ሌላ ሰው በተመሳሳይ መልኩ የንግድ ፈቃድ አውጥቶ እንደአመሸ መሥራት ፈልጎ አልተከለከለም።ስለዚህ አንዱ በብሔሩ ወይም በሃይማኖቱ እየተገፋ ሌላው እየተጠቀመ ይኖራል።ይሔ ማለት ምቹ ከባቢን አለመፍጠር ነው ሲል ምላሽ ሰጠ።
ተሰማ በበኩሉ ‹‹ለሁሉም ነገር የብሔር ታርጋ ባትሰጡ ይሻላል።ምናልባት ወንድምህ አመሸ ያላሟላው ያ ፈቃድ የተሰጠው ሰው ደግሞ ያሟላው ነገር ሊኖር ይችላል።የተከለከለው በህግ ይሆናል።›› ሲል ግምቱን ገለፀ።ዘውዴ ተበሳጨ ‹‹ሕጉ ለሁሉም እኩል ይስራ!›› አሁን በየቦታው ያለው አንዱ ላይ ተግባራዊ የሚደረገው ሕግ ሌላው ላይ ተግባራዊ አለመደረጉ ነው።መድሎ ከበዛ ሕዝብ ይቀየማል።ማንም ቢሆን ሊቋቋመው የማይችለው የሕዝብ መአበል ደግሞ አገር ያፈርሳል፤ የኔ ስጋት ይህ ነው ሲል በረዥሙ እየተነፈሰ ሃሳቡን ገለፀ፡፡
‹‹ዛሬ ላይ ቆሞ ነገን ከመሥራት ይልቅ፤ ዛሬ ላይ ሆኖ ነገን ለማፍረስ መዳዳት ለማንም አይበጅም።በየምክንያቱ ብሶት እየፈጠሩ ሰዎች እሳት ውስጥ እንዲገቡ ከመቀስቀስ ይልቅ መንግስትን ተረድቶ የጋራ ህልም ይዞ በጋራ ትግል አገር መገንባት ሲገባ ምክንያት እየፈጠሩ ነገሮችን በአግባቡ ሳይረዱ ሕዝብ ቅራኔ ውስጥ እንዲገባ ማድረግ የታሪክ ተወቃሽነትን ያስከትላል፤ ችግር ካለ ብሔር ሳይሆን የግለሰብ ስም ተነስቶ ይወቀስ አስፈላጊም ከሆነ ይከሰስ፡፡›› ሲል ተሰማ በተከታታይ ሃሳቡን ተናገረ።
ተገኝ ጉሮሮውን ለንግግር እየጠራረገ ቀጠለ ‹‹ በየትኛውም አጋጣሚ በሰዎች መካከል አለመግባባት ሊፈጠር ይችላል።ነገር ግን አለመግባባቱ የሚፈታበት መንገድ በደንብ የታሰበበት ሊሆን ይገባል።እፈታለሁ ብሎ ይበልጥ ማወሳሰብም ያጋጥማል።ሆነ ብሎ ሲመቸው ብሔርን፤ ብሔር ካልተመቸው ደግሞ ሃይማኖትን መሸሸጊያ እያደረገ እና ተከታዮችን እንደአሸን እያፈላ የሚንጎማለል ኢትዮጵያዊ ነኝ ባይ አሜሪካንም አለ።ይህ ሥራው ሱስ ሆኖበት ኢትዮጵያን ለማፍረስ የሚፈልጉ የውጪም ሆነ የአገር ውስጥ ሃይሎችን እየደገፈ መሆኑን አይረዳም።እርሱ ሳይገባው የተናገረውን ተከታዮቹም አምነው አብረውት ይጮሃሉ፤ ዓላማው ለእርሱም ግልፅ አይደለም።ተከታዮቹም አይገባቸውም።በዚህ አጋጣሚ ችግር ለመፍታት በሚል ሰበብ ነገር ማራጋብ ይታያል›› አለ።
ዘውዴ ይህንን ሃሳብ ቢደግፍም ሊታይ ይገባል ብሎ የሚያምንበትን መናገር ጀመረ ‹‹የሰው ልጅን የወደፊት ሕይወት ለማቃናት በሚል ሰበብ መፍትሔ አፋላልጎ ሰዎችን ከድህነት ከማውጣት ይልቅ፤ በየአጋጣሚው በብዙ መቶ የሚቆጠሩ ሰዎች በግፍ ሲገደሉ ማየት ያሳምማል፤ ሰው እንዲናገር፤ ሰው ተናጋሪውን እንዲደግፍ ያስገድዳል።መቀራረብ በእኩልነት በወዳጅነት በጋራ መረዳዳት እና በጎ ግንኙነትን ይበልጥ በማጠናከር ወንድማማችነትን ማሳደግ ሲገባ አጉል ነፃነትን እና ልቅነትን ባልለየ መልኩ አንዱ ሌላው ላይ ሲባልግ አንዱ ሌላውን ሲገድል ሲታይ ምንም እንኳን ግልፅ አላማ ባይኖርም ይህ ብዙሃንን ያስቆጣል።ያለ ዓላማ አንዱ ሌላውን እንዲቃወም እና እንዲደግፍ ያስገድዳል፤ ይህን ጉዳይ በቀላሉ መዝጋት ‹ኢግኖር› ማድረግ አይገባም›› አለ።
‹‹የኢትዮጵያ ችግር ለዘመናት የተጠራቀመ በመሆኑ በአንድ ጊዜ ልንወጣው እንደማንችል መረዳት አለብን።ዋነኛው ችግራችን ድህነት ነው።ለድህነታችን መፍትሔው ሥራ ነው።ከሠራን በረከት እናገኛለን። በረከት ሲኖር ስግብግብነት ይቀንሳል።ስግብግብነት ከቀነሰ ደግሞ በብሔርም ሆነ በሃይማኖት ስም ተከታይ እየፈለፈለ የሚግበሰብሰው አካል አደብ ይገዛል።ማንም በስግብግብነት ማንንም አያፈናቅልም፤ ወይም አያሳድድም›› በማለት የተናገረው ተሰማ፤ እርሱ በዋናነት ለኢትዮጵያ መፍትሔው ሥራ እና ገቢን ማሳደግ ነው።ይህ ሲሆን ችግሮች በሂደት ይቃለላሉ የሚል እምነት እንዳለው ገለፀ።
ዘውዴ ግን በበኩሉ ‹‹ስጋ ወድቆ ያለትቢያ አይነሳም›› እንደሚባለው ሁሉ አንድ ስህተት መፈፀም ችግር ሊያስከትል ስለሚችል ቀድሞ መጠንቀቅ ይገባል።ሥራ ብቻውን ሳይሆን አንዳንዶች ሃላፊነት እያለባቸው የሚፈጥሩት ስህተት ቆሻሻውን ከስጋው ለመለየት እንዳይቻል ያደርጋል።ከቆሸሸ ደግሞ ስጋም ቢሆን ላይበላ ስለሚችል ቀድሞ ማሰብ ይገባል ሲል የውስጡን ገለፀ።አክሎም ‹‹ሲሞላ ይፈሳል፤ ሲከር ይበጠሳል›› ዛሬ ላይ ሰዎች ሁሉንም ነገር እየታዘቡ ቢያልፉም ነገ ሲበዛባቸው መነሳታቸው አይቀርም።ብሔር ብሔር እያሉ እያከረሩ ያሉ ሰዎችም ሲያከሩ ተበጥሰው የሚወድቁበት አጋጣሚ ሊፈጠር ይችላል።ስለዚህ አክራሪ ብሔርተኞች ራሳቸውን ከማጥፋት መቆጠብ ይኖርባቸዋል ።ሲል ተሠማ በበኩሉ ብድግ ብሎ አጨበጨበ።ቀድሞም ቢሆን እኔም ያልኩት ይህንን ነበር በማለት ሲናገር ተገኝ ግራ ተጋባ።
ተሰማ ‹‹በሕዝብ መሃል ያሉ ቅራኔዎችን ለመፍታት ከማክረር ይልቅ ማላላት፤ ሰጥቶ መቀበል ወይም እኔ ብቻ ወይም ለእኔ ብቻ ከማለት ይልቅ ፤ የመደብ ትግል ንቅናቄ እያሉ ራስን ነጥሎ ተበዳይ ከማስመሰል መላቀቅ ያስፈልጋል፡፡›› አለ።አሁን ደግሞ ዘውዴ በበኩሉ ቆሞ አጨበጨበ።በመጠጥ ቤት ውስጥ ያለው ሰው ዘውዴ እና ተሰማ ተራ በተራ እየተነሱ ማጨብጨባቸው ግራ አጋብቷቸዋል።ዘውዴ እየሳቀ ተቀምጦ ንግግሩን ቀጠለ።
‹‹ማጣትን እና ጥይትን ተኝቶ ማሳለፍ ነው›› ብሎ ለጥ ያለውን ሕዝብ ቀስቅሳችሁ ማዕበል አስነስታችሁ ትልቅ ለውጥ ውስጥ ካስገባችሁን በኋላ፤ ስትፈጭር የነበረች ማንጓለል አቃታት እንደሚባለው ከባዱን ሥራ ተወጥታችሁ ትንሿ ሥራ እያስማጠች ወገባችሁን ልትይዛችሁ አይገባም አለ።ተገኝ ግራ ተጋባ ተሰማ እና ዘውዴ የተስማሙ መስለዋል።ነገር ግን ጠያቂ ማን ነው? ለጥያቄው ምላሽ መስጠት ያለበት ማን ነው? ሁለቱም ጠያቂ መሆናቸው ግር አሰኝቶታል።ተሰማ የትልቁ ስልጣን ባለቤት ነው።ዘውዴም ቢሆን አንድ ወረዳን በመምራት ላይ እንደሚገኝ ያውቃል።ነገር ግን ሁለቱም የሚናገሩት ሌላ ሰው እንዲሠራላቸው ነው።
ተገኝ ‹‹ እስኪ መናገሩን ተናገራችሁ።እናንተ በየስልጣናችሁ የተናገራችሁትን ትተገብራላችሁ? በእርግጥ በህግ ፊት ሁሉንም እኩል ታስቀምጣላችሁ? ›› ሲል ሁለቱንም ጠየቀ።ዘውዴ ፈጠን ብሎ ዋናው ችግር ያለው እነተሰማ አካባቢ ነው።እኔ በበኩሌ ከምንም በፊት አገሬን ስለማስቀድም የምሰራው በጥንቃቄ ነው።ያለ ልዩነት ሕዝቡን እያገለገልኩ ነው።በዚህ ልክ ካልተጠነቀቅኩ እና ሕዝብ ከተማረረ ችግሩ ተደምሮ አገር ላይ ይደርሳል የሚል ስጋት ስላለብኝ የምሠራው እንደምናገረው ነው።እምነቴ ይኸው ነው ሲል ምላሽ ሰጠ።
ተሰማ በበኩሉ በእርግጥም ያለልዩነት ለመሥራት ጥረት አደርጋለሁ።ነገር ግን ፍፁም ነኝ ለማለት እቸገራለሁ።የሚሠራ ሠው ይሳሳታል።ስህተቱን ብሔር ላይ መለጠፍ አይገባም።በእኔ በኩል አላሠራ ያሉኝ ሰዎች ሁሉ ጥፋቴንም ልማቴንም ብሔር ላይ በመለጠፋቸው ነው።ሰዎች የሰዎችን ብሔር ሳይሆን ግለሰቦችን ብቻ ማየት እያለባቸው በተቃራኒው መሆናቸው ቢያስከፋኝም ለአገሬ የአቅሜን እየሠራሁ ነው ሲል ተናገረ።
ተገኝ በበኩሉ ሁለታችሁም በትክክል እየሠራችሁ ከሆነ መልካም ነው።ነገር ግን ሥራችሁ ላይ በቸልታ የሚታለፉ ነገሮች የሚያስከፍሉት ዋጋ ቀላል አይደለም።ለሁሉም እኩል ነፃነትን መስጠት፤ ልቅነትን መከላከል፤ የአገርን አንድነት ማረጋገጥ የግድ ነው።ከንግግራችሁ ጀምሮ የብሔረሰቦችን ጉዳይ በማራገብ አንዱ እንደተበደለ ወይም እየተበደለ እንዳ ለ፤ አንዱ እየተጠቀመ እንዳለ ከመናገር ጀምሮ ተጨባጭ መረጃ ሳይኖራችሁ ሃሳቡን ማራመድ ከቀጠላችሁ የአገርን አንድነት ከማናጋት አይተናነስም።
የብዝበዛ ሃሳብ መኖር የለበትም።የብዝበዛ ሃሳብ ከነበረም ማክተም አለበት።በዚህ በኩል አሁንም ስህተት ካለ ችግር ይፈጠራል።ግለሰብም ሆነ ብሔር መበዝበዝ የለበትም።ግለሰብም ሆነ ብሔር በዝባዥ መሆን የለበትም።ያለበለዚያ ቀድሞም እንደታየው የመበዝበዝ ስህተት የፈፀመ እንደወደቀ ስጋ በትቢያ ስለሚለወስ ቆሻሻ ነው ተብሎ ስለሚጣል ቀድሞ መጠንቀቅ ያሻል በማለት በብርጭቆ የተቀዳውን መጠጥ ጨርሶ ጨለጠ፡
ምሕረት ሞገስ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 28 ቀን 2014 ዓ.ም