በዛሬው ዕትማችን የወቅታዊ አምድ ዋነኛ ማጠንጠኛ የሳይበር ደህንነት እና የሳይበር ጥቃቶችን
ማዕከል ያደረገ ነው። በዚህም ከአገር እስከ ዓለም ሁኔታዎችን ለመዳሰስ ሙከራ አድርገናል፡፡ በጉዳዩ
ዙሪያም የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር ምክትል ዋና ዳይሬክተር ከሆኑት ከአቶ ሰለሞን ሶካ
ጋር ቆይታ አድርገናል፡፡
አዲስ ዘመን፡- የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር (ኢመደአ) እንደ አገር ከተቋቋመለት ዓላማ አኳያ ምን ተግባራትን እያከናወነ ነው?
አቶ ሰለሞን፡- የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር (ኢመደአ) የአገሪቱን የኢንፎርሜሽን እና ኢንፎርሜሽን መሠረተ ልማት ከሳይበር ጥቃት ለመከላከል የተቋቋመ ነው።ለመከላከል ደግሞ አገራዊ አቅምን በመፍጠር በዓለም አቀፍ ምህዳር ኢ-ተገማችና ተለዋዋጭ ከመሆኑ አንፃራዊ ዘርፉን የሚመጥን የሰው ኃይል ልማት፣ ተቋማዊ አደራጃጀትና በርካታ ተግባራትን ለመከወን በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ከ15 ዓመት በፊት ራዕይ ተሰንቆ የተቋቋመ እና ዓላማውንም እየፈጸመ ያለ ተቋም ነው።በተለይም ከለውጡ በኋላ የተለያዩ ማሻሻያዎች በማድረግ ሕዝብ፣ አገርና መንግሥትን የሚያገለግል ተቋም ሆኗል።ከዚህ በፊት ለአንድ ፓርቲ ብቻ የሚያገለግል ነበር።አሁን ግን ተቋሙ ብዙ የኢትዮጵያ ምሁራን የአገር መሪዎች የፈሩበትም ተቋም ነው፡፡
አዲስ ዘመን፡- እንደ አገር የሪፎርም ሥራዎች ከተጀመሩ ወዲህ የተገኙ ውጤቶች ምን ነበሩ፤ በአሁኑ ወቅትስ ምን ደረጃ ላይ ይገኛል?
አቶ ሰለሞን፡- ኢመደአ ከተቋቋመለት ዓላማ አንፃር የአገሪቱን የኢንፎርሜሽን እና ኢንፎርሜሽን መሠረተ ልማትን ከሳይበር ጥቃት በመጠበቅ የኢንፎርሜሽን የበላይነትን የማረጋገጥ ሥራ ያከናውናል።ከተቋቋመበት ጊዜ አንስቶ የቴክኖሎጂ ባለቤትነትን ከማረጋገጥ አንፃር ዘርፈ ብዙ ሥራዎችን አከናውኗል።አገሪቷም ብዙ ክልከላዎች ያሉበት ቴክኖሎጂዎች ላይ ትኩረት አድርጎ በመሥራት የቴክኖሎጂ ባለቤት እንድትሆን አድርጓል።ባለፈው ሥርዓትም የአንድ ፓርቲ መዘወሪያ ሆኖ ነው የቆየው።ምንም እንኳን ጥሩ የሚባሉ ሥራዎችን ይሠራ የነበረ ቢሆንም አንዳንድ ከሕግ ወጣ ያሉና ዜጎችን የማስፈራራት ነገሮች ይታዩበት ነበር።የሪፎርሙ አንዱ ዓላማ ይህ ተቋም ኢትዮጵያን እንዲመስል ማድረግ ነው።ይህም ማለት የአንድ ፓርቲ መዘወሪያ ሳይሆን ሁሉም ኢትዮጵያውያን ገብተውበት ባላቸው እውቀትና የአገር ፍቅር ለአገራቸው የሚያገለግሉበት ተቋም መሆን አለበት በሚል የአደረጃጀት ለውጥ ተደርጓል፡፡
በዚህም የሙያተኞች ድልድል ተደርጓል።አንድ ፓርቲ ተኮር ከመሆንና ሁሉም ኢትዮጵያውያን እንደ ሁለተኛ ዜጋ ሳይሆን ቀጥታ ማገልገል እንዲችሉ ምቹ ሁኔታዎች ተፈጥረዋል።ሪፎርሙን የሚመጥን ስትራቴጂካል ፕላንም ተዘጋጅቷል።ተቋሙ አሁናዊና መፃዒ ችግሮችን እንዲቋቋም ተደርጎ ተሠርቷል።በዚህ ረገድ በአጭር ጊዜ ውስጥ ተቋማዊ ለውጥን ሪፎርም በማድረግ በሰሜኑ የአገሪቱ ክፍል የተከሰተውን የሕግ ማስከበርና የሕልውና ዘመቻ ተቋሙ በጣም በአጭር ጊዜ ራሱን ሪፎርም በማድረግ ከፍተኛ ሚና ተጫውቷል።በዚህ ረገድ ለሕዝብና ለአገር ኩራት መሆን ችሏል።ሌላው ለውጥ አመጣን የነገውንም ትውልድ ታሳቢ ያደረገ ጉዞ ነው የምንለው የሳይበር ታለንት ማዕከል ተቋቁሟል።በዚህ ማዕከል ውስጥ የተለያዩ ልጆችና ታዳጊ ወጣቶች ባላቸው ልዩ ተሰጥዖ ተቋሙ ዘንድ መጥተውና ተሰጧቸው ለምቶ የተለያዩ የቴክኖሎጂ ምርቶችና የሥራ ውጤቶች እንዲወጡና የአገሪቱ ሳይበር እና ዲጂታል ሉዓላዊነቷ የተጠበቀ እንዲሆን ከወዲሁ የሳይበር ሰራዊት እያለማን እንገኛለን።
ሌላው ከታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የውሃ ሙሌት፤ የህልውና ዘመቻ እና ሌሎች የኢትዮጵያን ዕድገት በማይፈልጉ ታሪካዊ ጠላቶች ባላቸው ፍላጎት ከፍተኛ ቁጥር ያለው የሳይበር ጥቃት ደርሶብናል።ባለፈው ዓመት የነበረው 2ሺ897 የሳይበር ጥቃት ሲሆን በዚህ ዓመት በሦስት እጥፍ አድጎ ወደ 8ሺ845 ደርሷል።በ2012 ዓ.ም ከነበረው አሁን ያለው ልዩነቱን ብንመለከት በአምስት እጥፍ አድጓል።ስለዚህ የጥቃቱ ሂደት ሲታይ በጣም እያደገ ነው።በመሆኑም ጥቃቱን የሚመጥን ተቋማዊ መዋቅር ሊኖረን ይገባል።በተጨማሪም በየጊዜው ተለዋዋጭ፣ ኢ-ተገማች የሆነና በማንኛውም ሰዓት ምን ጥቃት እንደሚደርስ በማይታወቅበት ሁኔታ በጣም ንቁ ሆኖ የአገሪቱን ኢንፎርሜሽንና ኢንፎርሜሽን መሠረተ ልማት ከሳይበር ጥቃት የሚከላከል የሰው ኃይል ዝግጁነትና አቅም ማጎልበት መሠረታዊ ሥራ መሆኑ ታምኖበታል። በአጠቃላይ በሪፎርሙ እነዚህን ውጤቶችና ድሎች አግኝተናል፡፡
አዲስ ዘመን፡- ኢትዮጵያ ላይ የደረሱ የሳይበር ጥቃቶች በማን፣ መቼ እና ከየት እንደሆነ በትክክል ማወቅ ይቻላል?
አቶ ሰለሞን፡- በሳይበሩ ዓለም ልክ እንደ ኮንቬንሽናል ጦርነት እንደሚደረገው አይደለም።‹‹ኮንቬንሽናል ጦርነት ፊት ለፊት የሚደረግ ጦርነት ነው።የት እንደምትዋጋ፣ ከማን ጋር ውጊያው እንደሚካሄድ፣ መቼ እንደምትዋጋ ይታወቃል።በሳይበር ዓለም እንደዚህ የለም።ከአሜሪካ ጥቃቱን ወርውሮ ከግብጽ የተደረገ ማስመሰል ይቻላል።ስለዚህ ከዚህ ነው ማለት አይቻልም።ነገር ግን ትኩረት ከሚያደርጉበትና ከሚደርሰው አቅጣጫ ወይንም ጥቃት አንፃር ትንተና ተደርጎ ይህ ሊሆን ይችላል ይባላል፤ እንጂ ከዚህ ነው ሊባል አይችልም፡፡››
ለማንኛውም ኢትዮጵያ ላይ ከደረሱት ጥቃቶች መካከል የታላቁን ህዳሴ ግድብን የውሃ ሙሌት በሚመለከት ‹‹ብላክ ፕራሚድ ዋር›› የሚባል ጥቃት ደርሶብናል።ይሄ የግድቡን የውሃ ሙሌት ለማስተጓጎል የተደረገ ሙከራ ነው።37 ሺ እርስ በእርሳቸው የተሳሰሩ ኮምፒዩተሮች ላይ አደጋ ለማድረስ የተቃጣ ቢሆንም በሳይበር ሰራዊታችን ማክሸፍ ተችሏል።ከዚህ ባሻገር በርካታ ጥቃቶች ተፈፅመዋል።ከ8ሺ845 ጥቃቶች ውስጥ 45 ከመቶ የሚሆኑት ቁልፍ መሰረተ ልማት ወይንም የኢንፎርሜሽን እና ኢንፎርሜሽን መሠረተ ልማት ቅኝት ወይንም ስለላ ላይ ያነጣጠሩ ናቸው።ከጥቃቶች 20 ከመቶ የሚሸፍኑት ደግሞ የድረ ገፅ ጥቃቶች ናቸው።ከእነዚህም አብዛኞቹ መክነዋል።ሆኖም የተወሰኑ ጥቃት ደርሰዋል።18 ከመቶ የሚሆነው የሳይበር ጥቃት ደግሞ ‹‹ራን ሰምዌር አታክ›› ነው።በአጠቃላይ ሲታይ ተቋማት የሳይበር መከላከል አቅም በዚህ ዓመት 97 ከመቶ መድረስ ተችሏል፡፡
አዲስ ዘመን፡- ኢትዮጵያ ውስጥ በሳይበር ጥቃት ማዕከል የተደረጉ ተቋማት እነማን ናቸው?
አቶ ሰለሞን፡- ዒላማ የተደረጉ ተቋማትን መንገር እንችላለን።ጥቃት አድራሻቹንም ፍላጎትና የሚመጣው ተፅዕኖ ማየትም ተገቢ ነው።የአገሪቱ ቁልፍ መሰረተ ልማትና በኔትወርክ የተሳሰሩትን ያማከለ ነው።ለአብነት የኢትዮ- ቴሌኮም መሰረተ ልማት፣ የህዳሴው ግድብና ሌሎች የኃይል ማመንጫ እና ማስተላለፊያ መስመሮች የጥቃቱ ዒላማዎች ነበሩ።የአገሪቱ የመወዳደሪያ አቅም የምንላቸው የኢትዮጵያ አየር መንገድ የመሳሰሉትም በዚህ የሚታዩ ናቸው፡፡
ቁልፍ መሰረተ ልማት ላይ ጥቃት ሲደርስ በርካታ ኢንዱስትሪዎችና የሕዝብ አገልግሎት የሚሰጡ ተቋማትን ማናጋት ነው።በዚህም 45 ከመቶ የሚደርሰው ጥቃት ቁልፍ መሰረተ ልማትን ዒላማ ያደረገ ነበር።በመቀጠል የፋይናንስ ተቋማት ዒላማ ነበሩ።ዓላማው ገንዘብ ለማግኘት ነው።በዚህም ሲስተሙን በመያዝና በማመሳጠር ብሎም በማገት ገንዘብ እንዲከፈል የመደራደር ጥቃት ነው።ሦስተኛው የሳይበር ጥቃት ዒላማ የገቡት መገናኛ ብዙኃን አውታሮች ናቸው።ይህ ከህልውና ዘመቻው ‹‹ግራጫ ጦርነት የተባለው›› ጋር የሚያያዝ ነው።የመንግሥት የፖለቲካ አደረጃጀቶችን ከፌዴራል እስከ ክልል የደረሰ ነው።ዩኒቨርሲቲዎችና የጤና ተቋማትም የሳይበር ጥቃቱ ዒላማዎች ሆነው ተገኝተዋል።ይህን ጥቃት የሚያደርጉትም የግለሰቦችን መረጃ ጭምር ለመመንተፍ አሲረው የሚሠሩ ናቸው፡፡
አዲስ ዘመን፡- ከሳይበር ጥቃቶቹ በስተጀርባ በአገር ውስጥ ተባባሪዎች ወይንም ባንዳዎች ይኖሩ ይሆን?
አቶ ሰለሞን፡- በቴክኖሎጂ ላይ ይብሳል።በሠራተኞችና በዜጎች የሚከሰተውን በሦስት ከፍለን ማየት እንችላለን።አንደኛው ስለጉዳዩ ጥልቅ እውቀትና ግንዛቤ ባለመኖሩ፤ ሁለተኛው ለሳይበር ጥቃት አጋላጭ የሚያደርገውና ስለጉዳዩ እያወቁ ትኩረት አለመስጠት ወይንም ንዝህላል መሆን ሲሆን ሦስተኛው ሆን ተብሎ ከውስጥ ጉዳት የሚያደርሱና ለአጥቂዎቹ መረጃ አሳልፈው የሚሰጡ ባንዳዎችና ጥቃት እንዲደረስ የሚያደርጉ ናቸው።ከጥቃቶች 65 ከመቶ በላይ በዚህ ሳቢያ የሚፈጠሩ ናቸው።
አዲስ ዘመን፡- በኢትዮጵያ ከሳይበር ጥቃቶቹ በስተጀርባ ያሉ ተባባሪዎችን ለመለየት የተደረገ ሙከራ አለ?
አቶ ሰለሞን፡- ይህ 65 ከመቶ የሳይበር ጥቃት በኢትዮጵያ ብቻ ያለ ለሕዝብ ሳይሆን አጠቃላይ በዓለም አቀፍ ደረጃ በሳይበር አግባብ ጥናት ሲካሄድ ባለማወቅ፣ እያወቁ ትኩረት አለመስጠትና በውስጥ ባንዳዎች ከ65 እስከ 90 ከመቶ የሚደርሱ የሳይበር ጥቃቶችን አሀዝ ያመለክታል።በአገራችን ሲታይ በሳይበር ጥቃት ወይንም ደህንነት የመከላከል አቅምን በሚመለከት በርካታ ተቋማት ራሳቸው ግንዛቤ የሌላቸው ናቸው።ጉዳዩን እያወቁም ዝም ያሉ አሉ።ሁኔታውን ተረድተው እየሠሩ የሚገኙም አሉ።
እኛ ግን እንደተቋም የሳይበር ደህንነት ለመጠበቅ የሚያስፈልጉ ሥራዎች አሉን።የሳይበር ደህንነት ፖሊሲና ስትራቴጂ አሠራርና መስፈርት አለ።በዚህ ዓመት ብቻ ስድስት ሰነዶችን ቀጥታ ለቀናል።በመሆኑም ተቋማት እነዚህን ሰነዶች ወስደው በተቋማቸው መተግበር አለባቸው።በትግበራ ሂደት ውስጥ ስልጠና እንሠጣለን፤ እናማክራለን፤ እንደግፋለን።በዚህም የተጠቀሙ በርካታ ተቋማት አሉ።ተቋማት የሳይበር ደህንነት አስተዳደር ሥርዓት መተግበር አለባቸው።ይህ አንደኛው ሥራ ነው።ሁለተኛው የሳይበር ደህንነት ፍተሻ እና ግምገማ ወይንም ኦዲት የሚባል ሥራ አለ።ይህን አውቀው ከተቋማችን ጋር የሚሠሩ አሉ።በተለይም በፋይናንስ ዘርፍ ያሉ የመንግሥትና የግል ቁልፍ መሠረተ ልማቶችን የያዙ ተቋማት ከተቋማችን ጋር በቅርበት እየሠሩ ነው።ምክንያቱም በአንድ ጊዜ የሚመጣ ክስተት ወይንም ጥቃት ከፍተኛ ጉዳት ስለሚያደርስ በትኩረት እየሠራን ነው፡፡
በሁለተኛ ደረጃ ተቋማት የኦዲትና ግምገማ ሥራ ማሠራት ይኖርባቸዋል።ሦስተኛው ተቋማት በተከታታይ በዓመት ሁለት ጊዜ ለሠራተኞቻቸው የግንዛቤ ማስጨበጫ
መስጠት አለባቸው።በዓመት አንድ ጊዜ ደግሞ የኦዲትና ግምገማ ሥራ መሥራት ይጠበቅባቸዋል።የሚሰጣቸውን ምክረ ሐሳብ በመመርኮዝ የሳይበር ደህንነት ፖሊሲያቸውን፣ ስታንዳርዳቸውንና መመሪያቸውን ጊዜውን በጠበቀ፣ ቴክኖሎጂውን በሚመጥን አግባብ ማሻሻል ይኖርባቸዋል።በዚህ ረገድ የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር (ኢመደአ) በቂ የሆነ የአሠራር ሥርዓትና የአገልግሎት ሥርዓትን ዘርግቶ እያገለገለ ይገኛል።በሁሉም ተቋማት ተደራሽ ለመሆንና በአካል ሄዶ ስልጠና መስጠት ከፍተኛ የሆነ የሰው ኃይል አቅም ስለሚጠይቅ፤ በሚቀጥለው ዓመት በዲጂታል ቴክኖሎጂ በመታገዝ ተግባራዊ እናደርጋለን፡፡
አዲስ ዘመን፡- ተቋማትን ለሳይበር ጥቃት ተጋላጭ ያደረጉና ተባባሪ የሆኑትን የመለየት ሥራ ተከናውኗል?
አቶ ሰለሞን፡- አሁን በነገርኩህ የአሠራር ሥርዓት ተቋማት ሲተገብሩ የራሳቸው የሆነ የደህንነት ኦፕሬሽን ማዕከል ይኖራቸዋል።ቀጥታ በኦዲትና ፎረንሲክ ለማግኘት የሚሰጡ አገልግሎቶች በፖሊስ መረጃ ሲመጣ የምንሰጠው አገልግሎት ነው።አሁን ግን እየተናገርኩ ያለሁት ተቋማት ውስጥ ጉዳዮችን ለመጠበቅ ማድረግ የሚጠበቅባቸውን ነው።ተቋማት የሳይበር አስተዳደር መተግበር ብሎም በተከታታይ ግምገማ እና ኦዲት ማስደረግ አለባቸው።መሰል አሠራር ሲኖር ማን ምን እንዳደረገ በግልጽ ይታያል ማለት ነው።ይህ በሌለበት ግን ሌላ አገልግሎትም እንሰጣለን፡፡
ለምሳሌ በቅርቡ በአዲስ አበባ የጋራ መኖሪያ ቤቶች (ኮንዶሚኒየም) ዕጣ አወጣጥ የተደረገው የቴክኖሎጂ ውንብድና ከተከሠተ በኋላ ልክ እንደፖሊስ ወንጀል ምርመራና ኦዲት ይደረጋል።በተጨማሪም የዲጂታል ፎረንሲክ ምርመራ ይደረጋል።በዚህም ድርጊቱን ማን ፈፀመ የሚለውን መለየትና ጉዳዩ ለሚመለከተው የሕግ አካል፣ ለፖሊስ ወይንም ለፍርድ ቤት ተቋሙ መረጃ ያቀርባል።እነዚህን መሰል አገልግሎቶችንም እንሰጣለን፡፡
አዲስ ዘመን፡- የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር የ99 ተቋማትን የሳይበር ኦዲት ማድረጉ ይታወቃል።በኦዲት ምን ክፍተቶች አገኘ?
አቶ ሰለሞን፡- ያየናቸው ክፍተቶች ኢንፎርሜሽን መሠረተ ልማት ሲዘረጉ የሳይበር ደህንነትን ታሳቢ አለማድረግ ወይንም የመዘናጋት ጉዳይ መኖሩን ነው።አንድ ሶፍትዌር ሲበለፅግ ደህንነቱ የተጠበቀ እንዲሆን የራሱ የሆነ ሥርዓት አለው።ይህን ከዌብ ሳይታችን ላይ (secure software development cycle) የሚል ጋይድላይን ማግኘት ይቻላል።በተጨማሪም ደህንነቱ የተጠበቀ ስለመሆኑ እኛ ዘንድ ኦዲት ቢያስደርጉ ወይንም የደህንነት ሰርተፍኬት ቢያገኙ ደህንነታቸው የተጠበቀ ይሆናል፡፡
የዳታ ማዕከል፣ ኔትወርክና የመሳሰሉትን መሠረተ ልማቶች ሲዘረጉ፤ ከመዘርጋታቸው በፊት ከፍተኛውንና ዝቅተኛ ደረጃ ዲዛይን ቢያስመረምሩ በተቋማችን አማካይነት ደህንነቱን ቢያስመረምሩ እንዲሁም ከዘረጉም በኋላ ‹‹ሪስክ አሰስ›› ኦዲት ቢደረግላቸውና የደህንነት ሰርተፍኬት ቢያገኙ ቢያንስ ለአንድ ዓመት ደህንነታቸው የተጠበቀ ይሆንላቸዋል።ይህ በየዓመቱም መቀጠል ይኖርበታል።ቴክኖሎጂዎችን ገዝቶ መጠቀም እንጂ ደህንነቱ የተጠበቀ ነው ወይ የሚለው ላይ መዘናጋት አለ።በተለይም ‹‹ኦን ፕሪሚስ›› እና ‹‹ክላውድ›› ላይ ነው፤ የራሴ ተቋም ስለሆነ ማን ያጠቃኛል በሚል በርካታ ጥፋቶች ይኖራሉ፡፡
ሌላው በዘርፉ የተሰማሩ የአይ.ቲ ተቋማት ራሳቸው ደህንነቱን ማረጋገጥ ይኖርባቸዋል።ሶፍት ዌር የሚያለማ የአይ.ቲ ተቋም የአገሪቱን ደህንነቱ የተጠበቀ ሶፍትዌር ደረጃን ያሟላ ስለመሆኑ የእኛን የደህንነት ሰርተፍኬት ቢያገኝ ገበያው ላይ ተቀባይነትም ይኖረዋል።የዳታ ማዕከል የሚገነባ ተቋም የደህንነት ሰርተፍኬት ወይንም የአይ.ኤስ.ኦ እውቅና ቢኖረው ኢንዱስትሪው ላይ ትልቅ ጥቅም ያገኛል።ይህ ካልሆነ ዝም ብሎ አገልግሎት የሚሰጥ ሶፍት ዌር መጠቀምና የተቋማትን ምስጢር የማይጠብቅ ከሆነ አደጋው የከፋ ነው።መረጃዎቹም በመንታፊዎች እጅ ይገባል፡፡
አዲስ ዘመን፡- ሶፍትዌሮችን በማልማትና በመጠቀም ረገድ ሩቅ ባለመጓዛችን በነፃ ከጎግል በማውረድ የሚጠቀሙ በርካታ የአገራችን ተቋማት አሉ።ኢትዮጵያን ይህን መሰናክል አልፋ ቴክኖሎጂ ወደ ውጭ የመላክ ውጥን አላት ይሆን?
አቶ ሰለሞን፡- በጣም ቁልፍ ጥያቄ ነው ያነሳኸው።ተቋማትን ለሳይበር ጥቃት ተጋላጭ ከሚያደርጉ ምክንያቶች አንዱ የተበተነ ሶፍት ዌር መጠቀም ነው።መሰል ሶፍት ዌር መጠቀም ነፃ ቢመስልም ነፃ ግን አይደለም።መረጃዎች በእጃቸው ያስገባሉ።ይህ የመላ አፍሪካውያን ችግር ነው።ይህ ቴክኖሎጂን ከመግዛት አቅም ጋር ይያያዛል።ይህን ለማቃለልና የሳይበር ጥቃት ተጋላጭነትን ለመጠበቅ የተቋማችን ፍልስፍና የቴክኖሎጂ ባለቤትነትን ማረጋገጥ ነው።ይህ ማለት አንድ አካል ራሱ የፈጠረውና የሠራውን ሥራ በራስ ቁጥጥር ሥር ማድረግ ነው።በመሆኑም የሳይበር ጥቃትን ለመከላከል በተቋማችን ሆነ በሌሎች ተቋማት ወይንም በግል ድርጅቶች የሚለሙትንና አገር በቀል የሆኑ የቴክኖሎጂ ውጤቶችን በጣም እናበረታታለን።
አገር በቀል ቴክኖሎጂዎችን የመጠቀም ባህሪ መዳበር አለበት።ተቋማት የተበተነ ወይንም የተሰረቀ ሶፍትዌር ከሚጠቀሙ የግል ድርጅቶች አልምተው በእኛ ደህንነቱን ያረጋገጠ ሶፍትዌር ቢጠቀሙ ይመከራል።የሌላን አገር ሶፍት ዌር በዶላር ከመግዛት በአገር ቢዝነስ በቂ የሆነ እና አዳጊ የሚሆን ሶፍት ዌር መጠቀምና የግሉን ዘርፍ ማገዝም ይገባል።በእኛ ረገድ የኢንተርፕራይዝ አፕሊኬሽኖች በቴክኖሎጂ ባለቤትነት ብለን በርካታ ምርቶችን አምርተናል።ይህንን ወደ ግሉ ዘርፍ እንለቃለን።የግሉ ዘርፍ በአገር ደረጃ የሥራ ዕድል ችግር አለ ይባላል።ይህም በዲጂታል ኢኮኖሚ ከፍተኛ የሥራ ዕድል ይፈጥራል።እነዚህን ምርቶች ለእነርሱ አሳልፈን ብንሰጥ አገር ተጠቃሚ ትሆናለች፡፡
በአገሪቱ ዩኒቨርሲቲዎች የተመረቁ በርካታ የኮምፒዩተር ኢንጂነሪንግ ባለሙያዎች አሉን፤ በርካታ ተቋማትም አሉን።ከዚህም በተጨማሪ ዘርፉ ድንበር የለሽ ነው።በመሆኑም በሥራ ዕድል ፈጠራው በርካታ ቁጥር ያለው የሰው ኃይል ማፍራት ይቻላል።ለምሳሌ በእኛ አቅም የለማ እና የተተገበረ ኢ.አር.ፒ አለ።ይህ ብዙ የሥራ ዕድል ይፈጥሯል።አንድ የሕንድ ኩባንያ ኢ.አር.ፒ በማልማቱ ብቻ በ90 አገራት ላይ የኢንተርፕርይዝ ሲስተሞችን በመተግበሩ ለ120ሺ ሰዎች የሥራ ዕድል ፈጥሯል።በመቶ ሺዎች የሥራ ዕድል የሚፈጥርም ነው።በኢትዮጵያ ውስጥ በተሳካ ሁኔታ የምናደረገው ነገር በሌሎች ተቀባይነት ለማግኘት ይረዳል።አፍሪካን መያዝ እንችላለን።አንድ ምርት ማለት በጣም ትልቅ ነው።አብዛኛዎቹ የአፍሪካ አገራት ከእኛ የበለጠ ሥርዓት የላቸውም።በመሆኑም ጠንክረን ከሠራን ብዙ የውጭ ምንዛሪ የምናገኝበት ነው፡፡
አዲስ ዘመን፡- በኢትዮጵያ የተመረቱና ለአብነት የሚነሱና የተሞከሩ የደህንነት ቴክሎጂዎች አሉ?
አቶ ሰለሞን፡- እንደ ኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር የደህንነት ምርቶች የሞከርናቸው አሉ።ግብረ መልሱም በጣም ጥሩ ነው።ይቻላል የሚለው ነገር አይተናል።እኛ የምንጠቀመውን ምርት ለሌላ የአፍሪካ አገር ሸጠን ጥሩ ግብረ-መልስ አግኝተናል።እኛም እነርሱም እየተጠቀምን ነው፡፡
የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር ቀጣይ ዕይታ ሁለት ነው።በመሆኑም ኢትዮጵያ በ2023 ዓ.ም ስትራቴጂ ቀርፃ እየሠራች ነው።በዚህም ተቋሙ ላለፉት 15 ዓመታት ያረጋገጣቸውን የቴክኖሎጂ ባለቤትነት ይቀጥላል፤ የተወሰኑትን ደግሞ ወደግሉ ዘርፍ በማዞር የዲጂታል ትራንስፎርሜሽኑ እንዲሳለጥ ሚናውን ይወጣል፡፡
የዲጂታል ትራንስፎርሜሽኑን የሚመጥኑ ቴክኖሎጂዎች ላይ በተለይም ተራማጅና ነገን ታሳቢ ያደረጉ ቴክኖሎጂዎችን የምርምርና የልማት ሥራዎች ይቀጥላል።ይህ የዲጂታል ትራንስፎርሜሽኑን ከማገዝ አኳያ እንደአንድ ሳይበር ደህንነት ተቋም የምናደረገው የትኩረት መስክ ነው፡፡
ሁለተኛው ኢትዮጵያ በ2023 ዓ.ም ዲጂታል ትሆናለች ሲባል፤ የዲጂታል ሉዓላዊነት የሚባል ጥያቄ ምላሽ ሊኖረው ይገባል።ዲጂታል በሆንን ቁጥር የዜጎቻችን ሕይወት በጣም እየቀለለ፣ የተሳለጠ እና ብልፅግና የምንለው ነገር ቀላል ይሆናል።እንደሌላው ዓለም ዜጎቻችንም ቴክኖሎጂን እንደቅንጦት ሳይሆን እንደ ዕለት ተዕለት ኑሯቸው የሚጠቀሙበት፤ መልካም አስተዳደርንና ግልጽነትን የሚያሰፍን፣ ሕይወትን የሚያሳልጥ ይሆናል።በዚያው ልክ ደግሞ ተጋላጭ መሆንም ይኖራል።ተጋላጭነት ደግሞ ከዲጂታል ሉዓላዊነት ጋር ይያያዛል።በመሆኑም ተቋሙ የዲጂታል ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ ከወዲሁ በስትራቴጂ የተደገፈ አብሮ የሚሄድና የሚያድግ የሳይበር ደህንነት እየተገበረ ነው፡፡
በሂደት ደግሞ ሳይበር ታለንት ወይንም የነገ ትውልድ መሆንና መፈጠር አለበት።ይህ ተቋም የዛሬ 15 ዓመት በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ተቋቋመ።በአሁኑ ወቅት በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ዜጎች በዚህ ተቋም ውስጥ ይሠራሉ።በአገር ህልውና ላይ የተጋረጠውን ጦርነትም መመከት የቻለና የራሱን ከፍተኛ አስተዋፅኦ ያደረገ ተቋም ተገንብቷል።በወቅቱ ጥቂቶች ባለሙያዎች ነበሩ፤ አሁን ላይ እየሠሩ ያሉት ባለሙያዎች ትናንት ከነበሩት ይለያሉ።ለነገው ደግሞ ከአሁኑ እንሠራለን፤ መልካም ዘርም እንዘራለን።ታለንት ማዕከል ዓላማው ይህ ነው።ነገ ላይ ኢትዮጵያን የሚጠብቁና ሊከላከሉ የሚችሉ እንዲሁም በሳይበር ደህንነት ከተከታይነት ወደ መግራት ወይንም መሪነት ሊያሸጋግር የሚችል ትውልድ የመቅረጽና ማፍራት አደራ ስላለብን ከወዲሁ በትኩረት እየሠራን ነው።
አዲስ ዘመን፡- በሳይበር ደህንነት በአገራትና ተቋማት መካከል ትብብር ይጠይቃል።ኢትዮጵያ በዚህ ረገድ ምን እየሠራች ነው?
አቶ ሰለሞን፡- ይህ በጣም ቁልፍና ወሣኝ ጥያቄ ነው።የሳይበር ደህንነት በባህሪው ተለዋዋጭና ድንበር የለሽ ነው።አሁን የሳይበር ደህንነት አጥቂዎች ተበራክተዋል።አገራትም በሳይበር ደህንነት የመወዳደሪያ አቅም አድርገው ይሠራሉ።ስፖንሠር የሚያደርጉ አታከሮች አሉ።ነገር ግን ግለሰቦች ደግሞ በጣም ልቀዋል።በመሆኑም በሳይበር ደህንነት የአንድ አገር ጉዳይ መሆኑ ቀርቶ የዓለም ጉዳይ ሆኗል።በመሆኑም በትብብር መሥራት የህልውና ጉዳይ ነው፡፡
በመሆኑም የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር ከሁሉም የፀጥታ ተቋማት ጋር ይሠራል።ዒላማ የተደረጉ ቁልፍ መሠረተ ልማት ከሚያስተዳድሩ አካላት ጋር፣ ከመገናኛ ብዙኃን ተቋማት፣ ከፋይናንስ፣ ከትምህርትና ጤና ተቋማት ጋር እየሠራን ነው።እንዲሁም ከዜጎች ጋር መሥራት አለብን ብለን አቅደን ዜጎቻችን የሳይበር ወታደር መሆን አለባቸው በሚል በ2015 ዓ.ም የምናስተዋውቀው ዜጎች የራሳቸውን ሳይበር ደህንነት ተጋላጭነት የሚፈትሹበት፣ ስልጠና የሚወስዱበት፣ በመወዳደር ለአገራቸው የሳይበር ሰራዊት የሚቀላቀሉበትን ሥርዓት ገንብተናል።የሳይበር ደህንነት የሁሉም ድርሻ መሆን አለበት በሚል እየሠራን ነው።በዓለም አቀፍ ደረጃ ደግሞ የሳይበር ዲፕሎማሲ አንገብጋቢ አጀንዳ ሆኗል።አብዛኞቹ አገራት በዚህ ላይ የሰው ሀብት እያለሙ ይገኛሉ፤ እኛም እየሠራንበት ነው፡፡
በቅርቡ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን ወደ ሳውዲአረቢያ ጉብኝት አድርገው ነበር።አንዱ የመወያያ ነጥባቸው የነበረው የሳይበር ደህንነት ጉዳይ ነው።የሳይበር ደህንነት ይህ ዓለምን ስላስተሳሰረ አንድ ቦታ የተፈጠረ ችግር ወደ ሌላ ቦታ የመዛመት ዕድሉ ሰፊ ነው።ስለዚህ አገራት፣ ተቋማትና ዜጎች የየራሳቸውን ሚና እንዲወጡ አብሮ የመሥራቱ ጉዳይ በጣም ወሳኝ ነው።እኛም እንደተቋም በዚህ ላይ ከሌሎች አገራት ጋር እየሠራን ነው።በዓለም አቀፍ ደረጃ የተደራጁ ማህበራት አሉ፤ አባል ለመሆንም ሂደት ላይ ነን።በአገራትና ተቋማት መካከል የ‹‹ሳይበር ኢንተለጀንስ ሼሪንግ›› መኖር አለበት።ምክንያቱም የሳይበር አጥቂዎች ከተቋማት የመከላከል አቅም በላይ እየሆነ በመምጣቱ በጋራና በትብብር መሥራት ብሎም ዲፕሎማሲው ላይ መሥራት ይገባል፡፡
አዲስ ዘመን፡- ኢትዮጵያ ያለችበት የምሥራቅ አፍሪካ ቀጣና ሽብርተኝነት አንዱ ሥጋት ነው።የሳይበር ቴክኖሎጂን በመጠቀም ኢትዮጵያን ለማተራመስ የሚደረገውን ሴራ በማክሸፍ የሚኖረው ሚና እና ቀጣይ ሥጋቶችን በተመለከተ የተቋማችሁ ትንተና ምን ይመስላል?
አቶ ሰለሞን፡- አንደኛው የሳይበር ደህንነት የአገሪቱን የኢንፎርሜሽን እና ኢንፎርሜሽን መሠረተ ልማት ከሳይበር ጥቃት ለመከላከል ነው።ሌላው የኢንፎርሜሽን እና ኢንፎርሜሽን መሠረተ ልማት በመጠቀም ለዕኩይ ዓላማ የሚያውሉትን አካላት የመቆጣጠር ሥራ እንሠራለን።ሽብርተኞች ለመገናኘት የሚጠቀሙት ሌላ ሳይሆን፤ የሳይበር ቴክኖሎጂን ነው፡፡
ዋናው ዓላማ የአገሪቷን ሠላም ማረጋገጥ ነው።ከፀጥታ አካላት ጋር እንሠራለን ሲባል የአገር መከላከያ የሚፈለገውን መረጃ እንደግፋለን ማለት ነው።‹‹በሳይበሩ ዓለም የምናገኛቸውን የሽብርተኞች መረብ፣ የጂኦ-ፖለቲካውን ፍላጎትና ኢኮኖሚውን ባገናዘበ መልኩ ትንተናዎች ይደረጋሉ››።አስፈላጊ መረጃ ተተንትኖ ለሚመለከተው የውሳኔ ሰጪ አካል ይቀርባል።ይህም አስፈላጊውን እርምጃ ለመውሰድ ዕድል ይፈጥራል።መሬት ላይ ከአሸባሪዎቹ ጋር የሚዋጉት ይህን መረጃ በማድረግ ነው።ዝም ተብሎ ስልክ በመደዋወል ብቻ የሚሆን ሳይሆን ትልቅ እገዛ ያስፈልጋል።ኢትዮጵያን ይህንን የማድረግ አቅምና ዝግጁ ነበራት፣ አላት ለወደፊትም ትኩረት ሰጥታ ትሠራለች፡፡
አዲስ ዘመን፡- ተቋማችሁ 2014 በጀት ዓመት የተሠሩ አንኳር ተግባራት ምንድን ናቸው፤ ቀጣይ ትኩረታችሁስ?
አቶ ሰለሞን፡- በበጀት ዓመቱ ዘጠኝ ወራት ብቻ 8ሺ845 ሳይበር ጥቃት ደርሶብናል።ከእነዚህ ውስጥ 96ነጥብ7 ከመቶ የሚሆነውን መመከት ተችሏል።በዘጠኝ ወራት ተጽዕኖው ተገምግሞ 5ሺ864 ጥቃት ነበር።በዚህም 1ነጥብ4 ቢሊዮን ብር ማዳን ተችሏል።29 ሚሊዮን ብር የሚገመት ደግሞ ኢትዮጵያ አጥታለች።ይህ እንደአገር በጣም ትልቅ ስኬት ነው።ሌሎች አገራት ይህን የመሰለ የመከላከል አቅም ሲገነቡ በጣም ያጩኹታል።ይሁንና ጉዳዩ ኢ-ተገማችና ተለዋዋጭ በመሆኑ የምንኩራራበት አይደለም።ነገ የሚሆነውን አናውቅም፤ ሁልጊዜም ለቀጣይ ስጋት ራሳችንን ዝግጁ እናደርጋለን፡፡
በሳይበር ደህንነት ላይ በአሁኑ ወቅት እንደልምድና ስጋት የመጣው ግለሰቦች በጣም ጎልተው የወጡበት የዲጂታል ሀብትን በመያዝና በማገት ገንዘብ እየጠየቁ ሲሆን ይሄ ለዓለም ሥጋት ነው።ስለዚህ ለመከላከል ዜጎችን የማንቃት ሥራ መሠራት አለበት።ተቋማት የሳይበር ኦዲት ማስደረግ ላይ መሥራት አለባቸው።መፍትሄዎች ላይ እየሠራን ነው።አገራትን እያፈረሰ ያለው ሌላው ሶሻል ምህንድስና ነው።የማህበራዊ ምህንድስና ጥቃት ዓይነት ቴክኒካልና (የኮዲንግ እውቀት ሳያስፈልግ የሰውን ልጅ ማህበራዊና ሥነ-ልቦናዊ ማሳመኛ ዘዴዎችን በመጠቀም የሚፈጸም የሳይበር ጥቃት ዓይነት ነው። የኢንፎርሜሽን የበላይነት በመያዝም አደጋ እየፈጠረ ነው።ሊቢያ እና ሌሎች አገራትም የፈረሱት በዚህ ነው።
ጥቃት አድራሾች የጥቃታቸው ዒላማ ያደረጉትን አካል በቀላሉ በማሳመን የሚፈልጉትን ነገር በቀላሉ ካለ ግለሰቡ ፈቃድና እውቅና ውጪ ምስጢራዊ የሆኑ መረጃዎችን የማግኘትና ጥቃት የመፈፀም ዘዴ ነው።መረጃዎች እንደሚያሳዩት፤ በዓለማችን ከተከሰቱ የሳይበር ጥቃቶች ውስጥ ከፍተኛውን ቁጥር የሚይዘው በሰው ልጅ ንቃተ ህሊና ማነስና የሰውን ልጅ ደካማ ጎን ተከትለው የሚፈጠሩ ስህተቶች ናቸው።
አዲስ ዘመን፡- የማህበራዊ ሚዲያዎች ተፅዕኖን ለመቋቋም፤ በራሳችን ለመዘወርና ባለቤትነት ለማረጋገጥ ብሎም የአገር ደህንነትን ለማስጠበቅ ምን እየተሠራ ነው?
አቶ ሰለሞን፡- ሶሻል ሚዲያን በሚመለከት አቅሙ አለ።ዋትስአፕን የሚተካ፤ ‹‹ስርኩን›› የሚባል ኢትዮጵያዊ ምርት አለን።‹‹ደቦ›› የሚባለው ደግሞ ዙም ይተካል።ያሆ፣ ጂሜልን፣ ኢሜል የሚተካ ደግሞ ‹‹ኤርጋ›› የሚባል አለን።እነዚህ በትክክል በመጠቀም አገርን የታደጉ ምርቶች ናቸው። ቴክኖሎጂው አለን።ግን ይህን በስፋት ለማልማት እጅግ ከፍተኛ ሀብት ይጠይቃል።መንግሥት ብቻውን አያለማም።ሶፍት ዌር አለን።ባለሀብቶች ተሰባስበው ዳታ ማዕከሉን ካለሙ እንሰጣቸዋለን፤ የሕዝብ ሀብት ይሆናል።ሁሉንም ነገር መንግሥት ላይ አይተውም።በተጨማሪም ተቋማት ጋር የሶሻል ሚዲያን ‹‹ሬጉሌት›› ማድረግ ላይ ትኩረት አድርገን እየሠራን ነው።ይህም በሕጋዊ መንገድ የሚሠሩትን ለማበረታታት ጥፋት ውስጥ የገቡትን ለማረም ይጠቅማል።
አዲስ ዘመን፡- ከዝግጅት ክፍላችን ጋር ላደረጉት ቆይታና ለሰጡን ሙያዊ ማብራሪያ እናመሰግናለን።ተጨማሪ መልዕክት አለዎት?
አቶ ሰለሞን፡- እኔም አመሰግናለሁ።ለኢትዮጵያ ሕዝብ ያለኝ መልዕክት የሳይበር ደህንነት የሁላችን ኃላፊነት ነው።እያንዳንዱ ሰው ስማርት ስልክ ካለው ለሳይበር ጥቃት ተጋላጭ ነው። ስለዚህ ንቃተ-ህሊናቸውን ማሳደግ አለባቸው።ተቋማችን ይህንኑ አስመልክቶ በተለያዩ ሚዲያዎች የሚተላለፉ መልዕክቶችን እንዲጠቀሙ በአክብሮት እጠይቃለሁ።የአገራችን ምጣኔ ሀብት ስለሚያሳድግና ብዙ የሥራ ዕድል ስለሚፈጥር ወጣቶችንም የዲጂታል ቴክኖሎጂን በጎ ጎኑን እንዲጠቀሙ በትህትህና አሳስባለሁ።ተቋማችን በዘርፉ ጠንካራ ለሆኑ የሥራ ዕድል ይፈጥራል፤ ቢዝነስ መሥራት ለሚፈልጉት ወይንም የራሳቸው ምርት ያላቸውን በታለንት ማዕከላችን ከሳይበር ደህንነት ጋር በተያያዘ ሙያዊ እገዛ እናደርግላቸዋለን።በተረፈ ለአገራችን ልማት፣ ሠላምና የጋራ ዓላማ እንድንቆም ጥሪ አቀርባለሁ።
ክፍለዮሐንስ አንበርብር
አዲስ ዘመን ሐምሌ 28 ቀን 2014 ዓ.ም