“የኮሪደር ልማቱ አንድ የቱሪስት ከተማ ማሟላት ያለባትን መስፈርት አዲስ አበባ እንድታሟላ አስችሏታል ” – ሂሩት ካሳው (ዶ/ር) የአ.አ ባህል፣ኪነጥበብ እና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ

ከተመሰረተች ከ130 ዓመታት በላይ የሆናት አዲስ አበባ የብሔር ብሔረሰቦች መናኸሪያ፤የኢትዮጵያ ዋና ከተማ የአፍሪካ መዲና እና የተለያዩ አህጉር እና ዓለም አቀፍ ተቋማት መገኛ ነች። ከ90 በላይ ኤምባሲዎችን በማቀፍም በዓለም ላይ ካሉት ጥቂት የዲፕሎማቲክ ማዕከል ከሆኑት ከተሞች ውስጥ ግንባር ቀደሟ ነች።

አዲስ አበባ፣ ከአሜሪካዋ ኒውዮርክና ከሲውዘር ላንድ ጄኔቫ በመቀጠል ልዩ ልዩ ዓለም አቀፋዊ ውሳኔዎች የሚተላለፉባት፤ የዓለም ሦስተኛዋ የዲፕሎማሲ ማዕከል ከተማ ሆና በባለብዙ የትብብር መስኮች አገልግሎት እየሰጠች ነው። ሆኖም ከተማዋ የእድሜዋን ያህል ባለማደጓ እና ጭራሹንም ልማቷ የኋሊት ሲጓዝ የቆየ በመሆኑ ከአፍሪካ ህብረት መቀመጫነቷ ጭምር ለማንሳት በርካታ ሙከራዎች ነበሩ።

ሆኖም የመንግሥትን ለውጥ ተከትሎ ከተማዋ ባገኘችው ትኩረት አዲስ አበባ እንደ ስሟ ውብ አበባ የመሆን እድል አግኝታለች። የኢትዮጵያ ዋና ከተማ ብሎም አፍሪካ መዲና የሆነችው አዲስ አበባ እንደ ስሟ አዲስ የሆኑ የልማት ስራዎች እየተከናወኑባት ነው። ከተማዋ በተለይም ካለፉት አምስት ዓመታት ወዲህ ከቱሪስት መተላለፊያነት ወደ ቱሪስት መዳረሻነት የሚያበቋት የተለያዩ መሰረተ ልማቶችና የመዝናኛ ስፍራዎች በስፋት እየተከናወኑባት ይገኛሉ። የአንድነት ፓርክ፤የወዳጅነት አደባባይ፤ እንጦጦ ፓርክ የመሳሰሉት የቱሪስት መዳረሻዎች ከተማዋ እንደገና እንድታንሰራራ አድርገዋታል።

በመጀመሪያው ዙር የአዲስ አበባን ገጽታ ከመሰረቱ የሚለውጥ የኮሪደር ልማት በአምስት አቅጣጫዎች ተተግብሮ አዲስ አበባን ውበት አላብሷታል። በአሁኑ ወቅትም ሁለተኛው ዙር ኮሪደር ልማት በመፋጠን ላይ ይገኛል። የኮሪደር ልማቱ የተጎሳቆለውን አዲስ አበባ ገጽታ ለመቀየር ከማስቻሉም በላይ አዲስ አበባ ከአቻ ከተሞች ጋር መሳ ለመሳ እንድትቆምና የቱሪዝምና የኢንቨስትመንት ማዕከል የመሆን እድል አግኝታለች። አስገራሚ በሆነ መልኩም የኮንፈረንስ ቱሪዝም መናኸሪያ ለመሆን በቅታለች።

የኮሪደር ልማቱ ትሩፋቶች የሆኑት የዓድዋ ሙዚየም፤ልዩ ልዩ የመስህብ ቦታዎች እና ማራኪ እይታዎች እና የመሰረተ ልማት ዝርጋታዎች ለስብሰባ የምትመረጥ ከተማ እንድትሆን አድርጓታል።

የአዲስ ዘመን ዝግጅት ክፍልም አዲስ አበባን እንደ ስሟ ውብ እና አዲስ ለማድረግ እየተሰሩ ያሉ ስራዎች ለቱሪዝም ዘርፉ ምን አዲስ እድል ይዘው መጥዋል በሚል ከአ.አ ባህል፣ኪነጥበብ እና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ ሂሩት ካሳው(ዶ/ር) ጋር ቆይታ አድርጓል። መልካም ንባብ።

አዲስ ዘመን፦ በአዲስ አበባ ባህልን፣ ጥበብንና ቱሪዝምን ለማሳደግ እየተሰሩ ያሉ ሥራዎች ምንድናቸው?

ዶክተር ሂሩት፦ አዲስ አበባ ከዚሁ ጎን ለጎንም የመንገድ ዳርቻዎች ኮሪደር ልማት፤ የወንዝ ዳርቻዎች አዋሳኝ የተፋሰስ ልማት፣ የብስክሌትና ሞተር አልባ የትራንስፖርት አገልግሎቶች ልማት፣ ዘመናዊ የትራንስፖርት ተርሚናሎች ግንባታ፣ አገናኝ የኮሪደር ልማት ድልድዮች፣ ማሳለጫዎችና የመጋቢ መንገዶች ልማት፣የመንገድ ዳር የሕዝብ መፀዳጃ ቤቶች፤ ፋውንቴኖች እና የሕዝብ መናፈሻ ስፍራዎች፣ ወጥ የህንጻ ቀለምና የከተማ ማብራት፣ ደረጃቸውን የጠበቁ ፓርኪንጎች፣የመኪና መጫኛና ማውረጃ አገልግሎቶችን ጨምሮ የአረንጓዴ ልማት ስራዎች የአዲስ አበባ መለያዎች ሆነዋል።ይህ የአዲስ አበባ ውበት እና ምቹነት ብዙዎችን ወደ ከተማዋ እንዲሳቡ እያደረጋቸው ነው።

ባለፉት ሶስት ወራት ብቻ ከ30 በላይ ዓለም አቀፍ ጉባኤዎችን በማስተናገድ ከወዲሁ የኮንፈረንስ ቱሪዝም መዳረሻነቷን አስመስክራለች። ባለፉት ሶስት ወራትም ከርሃብ ነፃ ዓለም ጉባኤ፣ የካፍ ጉባኤ፣ ዓለም አቀፍ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ፣ የአፍሪካ ንግድ ሚኒስትሮች ጉባኤና ሌሎች ጉባኤዎችን በስኬት ማስተናገድ ችላለች። በዚህም ከአፍሪካ አልፎ የዓለም የኮንፈረንስ ቱሪዝም መዳረሻ የመሆን አቅም ያላት ከተማ መሆኗን አስመስክራለች።

በአጠቃላይ አዲስ አበባን እንደ ስሟ ውብና አዲስ ለማድረግና አልፎ ተርፎም ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነትን ያሟላች ከተማ ለማድረግ የሚደረገው ጥረት ተስፋ ሰጪ ነው። የአዲስ አበባ ከተማ ገጽታ መለወጥም የአፍሪካ መዲናነቷን ለማጽናት ከማስቻሉም ባሻገር ከተማዋን የቱሪዝምና ኢንቨሰትመንት መዳረሻ በማድረግ ለሀገሪቱ ኢኮኖሚ መነቃቃት የማይተካ ሚና እንድትጫወት አድርጓታል።

ከዚሁ ጎን ለጎን ባህል እና ጥበብ ለማልማትና ለማሳደግ መሰረታዊ የሚባሉ መሠረተ ልማቶች በስፋት የተሰሩበትና የተመቻቹበት ጊዜ ነው። በተለይም ደግሞ ከአምስት ዓመት ወዲህ በቱሪዝም ዘርፍ የተሰራው የመስህብ ልማት ለኪነጥበቡና ለባህሉ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ ነው። ቀደም ሲል በነበረው አስተሳሰብ ለባህል ብቻ ትኩረት ይሰጥ ነበር። አሁን ደግሞ ለቱሪዝም ተብለው የተሰሩ መስህቦችና መሠረተ ልማቶች ባህላዊ መቀራረብን እየፈጠሩ ይገኛሉ። በከተማዋ የሚሰሩ የመስህብ ስፍራዎችም የተለያዩ ባህሎችን እንዲያንጻበርቁ ተደርገው በመሰራታቸውም ለባህል እድገትም ሆነ ለቱሪዝም መስፋፋት ከፍተኛ አስተዋጽኦ በማበርከት ላይ ይገኛሉ።

ነባር የምንላቸውን የጥበብ ቦታዎችን እንደ የሀገር ፍቅር አይነቱን በማደስ፤ የአዲስ አበባ ባህልና ትያትር አዳራሽን ዘመናዊ የሆነ የትያትር ቤት እንዲሆን በማድረግ፣ ራስ ትያትርን በሰፊ ቦታ ላይ በአዲስ እንዲገነባ ቦታዎችንና የመሬት ይዞታን በማስተካከል በዘመናዊ መልኩ ለመስራት እየተደረጉ ያሉ ጥረቶች ከተማዋ የባህል፣ የኪነጥበብ እና የቱሪዝም ማዕከል እንድትሆን አድርጓታል።ለረጅም ዘመን ትኩረት አጥቶ የቆው የራስ ቲያትር ቤት ግንባታ ዲዛይን እያለቀ ነው። አሜሪካ ግቢ አካባቢ ግንባታውን ለማከናወን የመሠረተ ድንጋይ ተቀምጧል፤ በግዝፈቱ እና ዘመናዊነቱም ምናልባት እስከአሁን ካሉን ትያትር ቤቶች የተሻለ ነው።

ከዛ ውጪ የሕፃናትና ወጣቶች ትያትር ቤት ዕድሳት ከተጀመረ ቆይቷል። ማዕከል አካባቢ እየተገነባ ያለው ይኸው ማዕከል ግንባታው ለረጅም ዓመታት ተጓትቶ ቆይቶ በቅርቡ ነው የተጠናቀቀው። ይሄ እራሱ የጥበብ ሥራን የሚያሳድግ ነው። በተለይ ከታች ትውልዱን ኮትኩቶ የሚያመጣ ተተኪ ሕፃናትንና ወጣቶችን ኮትኩቶ የሚያወጣ (የጥበብ ፔዳጎጅካል ማዕከል) እንዲሆን ተደርጎ እየተሰራ ያለ ነው። በጣም ብዙ ማሰልጠኛዎች አሉት፤ መለማመጃዎች አሉት። የሕፃናት ፖምፔት ማሰልጠኛ፣ የስዕል፤ የዘመናዊና ባህላዊ ውዝዋዜ፣ የድምፅ፣ የትያትር፣ የድርሰት፣ ማሰልጠኛዎችንና መለማመጃዎችን የያዘ ነው። ሁለት ሲኒማ ቤቶችን እና ቤተመጻሕፍትን የያዘ ነው።

 አዲስ ዘመን፡- በባህል፣ኪነጥበብ እና ቱሪዝም ዘርፉ እየተሰሩ ያሉ ስራዎች ለከተማዋ ምን ትሩፋት ይዘው መጡ?

ዶክተር ሂሩት፡– በአጠቃላይ በአዲስ አበባ እየተገነቡ ያሉ የባህል፤ኪነጥበባት እና የቱሪዝም ማዕከላት ከተማዋ በሀገር ውስጥ ሆነ በውጪ ጎብኚዎች ተፈላጊ እንድትሆን አድርገዋታል።ወደፊት ደግሞ በእርግጠኝነት የአፍሪካ የአርትና የባህል ማዕከል ትሆናለች። እንደሚታወቀው አዲስ አበባ ሞዛይክ ናት፤ ሁሉም የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች የሚኖሩባት፤ የሁሉም ብሔር ብሔረሰብ ባህል ማንነት የሚገለፅባት ከተማ ናት። የሕዝብ ለሕዝብ ትስስር እና የጋራ የወል ትርክት የምንፈጥርባት ከተማ ነች።በዚህ ረገድ እየተሰሩ ያሉ ስራዎች ለሀገራችን መሰረት መጣል ብቻ ሳይሆን ከእኛም አልፈን ለአፍሪካ ምሳሌ የምንሆንበት ስራ እየተሰራ ያለበት ሁኔታ ነው ያለው።

አዲስ ዘመን፡- ካለፉት አምስት ዓመታት አዲስ አበባን የቱሪዝም ማዕከል ለማድረግ እየተሰሩ ያሉ ስራዎች ከተማዋ ለቱሪዝም ተመራጭ እንድትሆን ምን ያህል አስተዋጽኦ አበርክተዋል?

ዶክተር ሂሩት፡- ከአምስት ዓመታት በፊት ለቱሪስት አዲስ አበባ መስህብ አላት ልሂድ ልጎብኝ ብሎ የሚመጣበት ምክንያት አልነበረውም። አዲስ አበባ ወደ ሌሎች ክልሎች ለሚደረጉ የቱሪስት ጉዞዎች መሸጋገር እንጂ መቆያ አልነበችም። ሆኖም ከመንግሥት ለውጥ ወዲህ ለዘርፉ በተሰጠው ትኩረት የአዲስ አበባ የቱሪዝም ትንሳኤ ሆኗል።

በአምስት ዓመታት ውስጥ ለአዲስ አበባ ቱሪዝም እምርታ የመጀመሪያ ተደርጎ የሚወሰደው ገበታ ለሸገር ነው። ከአንድነት ፓርክ ፣ ወዳጅነት ፣ እንጦጦ፣ ሳይንስ ሙዚየም፣ ዓድዋ መታሰቢያ ከተገነቡ በኋላ ግን የሀገር ውስጥም ሆነ የውጪ ቱሪስቶች አዲስ አበባ ውስጥ የሚገበኙ ነገሮች መኖራቸውን በመረዳት ከተማዋ ላይ ትኩረት አድርገዋል። በፊት መሸጋገሪያ ብቻ የነበረችው ከተማ ዛሬ እስከ 15 ቀናት ድረስ ሊገበኙ የሚችሉ ሀብቶችን በውስጧ አቅፋለች። ይህ ደግሞ አዲስ አበባን የመውጪያ መግቢያ የቱሪስት መዳረሻ እንድትሆን አስችሏታል።

እነዚህ ቦታዎች መስህብ ብቻ አይደሉም። ለምሳሌ አንድነት ፓርክ በርካታ ጎብኚዎች የሚያዩት ነገሮችን የያዘ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያለው ነው። አንደኛ ታሪክ አለው ፤ የኢትዮጵያ የሀገረ መንግሥት ግንባታ ከየት ተጀምሮ የት ይደርሳል የሚለው ታሪክ ይዟል። አደረጃጀቱ ታሪክን በመዝገብ ብቻ ሳይሆን በመስህብ ደረጃም አርትስቲክ በሆነ መንገድ የተቀመጠ ነው። ሁለተኛው ራሱ ቤተ መንግስቱን መጎብኘት ይቻላል። በዚህም የኢትዮጵያ ቤተመንግሥት ምን ይመስል ነበር ? አሁንስ ምን ይመስላል? የሚለውን ለማየት ያስችላል።

ሶስተኛው ተፈጥሮም ተጨምሮበታል። ቦታው የተለያየ ሀገር በቀል እጽዋት በርካታ የዱር እንስሳት አሉበት። በጥቅሉ ተፈጥሮን ይዟል። በተጨማሪም በተወሰነ ደረጃ የተለያዩ ብሔር ብሔረሰቦችን የአኗኗር እና የአመጋገብ ሁኔታን ያሳያል። ለምሳሌ የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች ቤት አሰራርና የተለየ መገለጫቸው የሆኑ ነገሮች አሉ። እነዚህን ነገሮች ሁሉ በአንድ ቦታ ማግኘት መቻል ትልቅ ነገር ነው። ይህ በቱሪዝም መስፈርትም ትልቅ የቱሪስት ማዕከል ያሰኘዋል።

በሌላ በኩል ደግሞ ተፈጥሮን ለፈለገ ደግሞ ወደ እንጦጦ ማምራት ይቻላል። በዚህ ቦታ በአዲስ አበባ ያሉ ተፈጥሯዊ እጽዋትን እንዲሁም ከፍታ ቦታ ላይ በመሆን አጠቃላይ የከተማዋን ገጽታ ለማየት የሚያስችልም ነው። በዚህ ውስጥ ደግሞ ከፈረስ ግልቢያ ጀምሮ ሕፃናትንም የሚያካትቱ በርካታ መዝናኛዎች አሉ። ደረጃቸውን የጠበቀ የሆቴልና ካፍቴሪያ አገልግሎትም ጎብኚዎች በዚህ ውስጥ ሊያገኙ ይችላሉ።

ወደ ወዳጅነት ፓርክ ሲመጣ ደግሞ የተለየ መልክአ ምድር ነው። የተለየ መዝናኛ በተለየ ሁኔታ ሰው ራሱን ሊያዳምጥበት የሚችል ቦታ ሆኖ ይገኛል። ከዚህም ባለፈ ከትልልቅ ኮንሰርቶች ጀምሮ ሠርግ፣ ስብሰባ፣ ስፖርት፣አትር እና ሌሎች ኩነቶችም ሊዘጋጁበት የሚቻል ነው።

ወደ ሳይንስ ሙዚየም ስንመጣ ደግሞ ዘመኑን የሚመጥን፤ የእውቀት መስመራችን ወዴት እየሄድ እንደሆነ የሚያሳይና የወደፊት የቱሪዝምን አቅጣጫም የሚያመላክት ነው። በዚህ ውስጥም ትልቅ የአውደ ርእይ የኮንፈረንስ ማእከል ይገኛል።

ወደ መስቀል አደባባይ ስንመጣ ደግሞ ለኮንሰርት፤ ለሕዝብ መሰብሰቢያ ፣ለስፖርት ማዘውተሪያ የተለያዩ በዓላት ማክበሪያ ለኢግዚቢሽን የሚሆኑ ዝግጅቶች የሚከናወኑበትን ዕድል ይዞ መጥቷል። ቦታው ሰዎች በጥንድም በተናጠልም ሊዝናኑበት የሚችል ቦታ ነው።

እነዚህ ቦታዎች በአጠቃላይ አዲስ አበባ ትክክለኛ የቱሪዝም መዳረሻ እንድትሆን ለማስቻል የተሰሩ ቦታዎች ናቸው። እነዚህም ስራዎች ዘመን ተሻጋሪ ከመሆናቸውም ባሻገር በየትኛው ዓለም ከሚገኙ የቱሪስት መስህቦች የሚስተካከል ውበት እና ዘመናዊነትን አጣምረው የያዙ ናቸው።

አዲስ ዘመን፡- ከጠቃቀሷቸው በተጨማሪ አዳዲስ የቱሪስት መስህቦችም እየተገነቡ ነው። ለአብነትም የኢዮቤልዩ ቤተመንግሥትን ማንሳት ይቻላል።

ዶክተር ሂሩት፡– አዲስ አበባ ላይ የቱሪስት መስህብ የሚሆኑ መዳረሻ ቦታዎች ዝግጅት የሚቀጥል ይሆናል። ቅድም ያላነሳሁልህና ትልቁ የኮንፈረንስ ቱሪዝም መናኸሪያ የሆነው አድዋ ድል መታሰቢያ ማእከል ነው። ይህ ማእከል ኢትዮጵያውያን በጋራ ሀገርን ለመገንባት ያደረጉትን ታሪክ ፤ያገኙትን ድል ለትውልድ የሚያስተዋውቅ ነው። የዓድዋ ድል መታሰቢያ ሙዚየም እርስ በእርስ የሚያስተሳስር ገመድ ሆኖ ትውልድ የሚማርበት ራሱን የሚገነዘብበት ነው። ከዚህም በላይ ደግሞ ማእከሉ በአሁኑ ወቅት ራሱን ችሎ የመስህብ ቦታ ለመሆን በቅቷል። በአሁኑ ወቅት በርካታ ቱሪስቶች እየጎበኙት ይገኛል። በከተማዋ እየተካሄዱ ካሉት ኮንፈረንሶች ዘጠና በመቶ የሚሆኑት በዚሁ ማእከል የተካሄዱ ናቸው።

ዓድዋ መታሰቢያ ማእከል በከተማ አስተዳደሩ የተገነባ ሲሆን፤ ከህዳሴው ግድብ ቀጥሎ ትልቁ ፕሮጀክት ነው። ይህም እስካሁን ከተገለጹት በላይ ለአዲስ አበባ ከተማ የቱሪዝም እንቅስቃሴ ትልቅ እምርታ ያመጣ ነው። በአሁኑ ወቅት ደግሞ የአንድነት ፓርክ ሁለተኛ ክፍል የሆነው የኢዮ ቤልዩ ቤተ መንግሥት እየተጠናቀቀ ይገኛል። እሱ ሲመረቅ ደግሞ ትልቅ የቱሪስት መስህብ ለመሆን ይችላል።

የአዲስ ቱሞሮ ማዕከል ግንባታ ደግሞ ለአፍሪካውያን ጎብኚዎች ትልቁ የቱሪስት መዳረሻና መስህብ ሊሆን የሚችል ነው። ከአውሮፕላን ላይ ተሁኖ የሚታይና የአፍሪካ ቅርጽ የያዘም ነው። ይህም ሌላኛው ትልቁ መስህብ ይሆናል።በዚህ ማዕከል ውስጥ በርካታ ሆስፒታሎች ስለሚገነቡ ከተማዋ የጤና ቱሪዝም ማዕከል እንድትሆን የሚያደርጋት ነው። ዘመናዊ የሆነው የአፍሪካ የስብሰባ ማዕከል (አፍሪካ ኮንቬንሽን ሴንተር ) ሌላኛው የከተማዋን የኮንፈረንስ ቱሪዝም እድገት የሚያፋጥን ነው።

በአጠቃላይ የአዲስ አበባ አቧራ እየተገለጠ ነው።አቧራ ለብሰው የነበሩ ታሪኮች ጸጋዎች እየተገለጡ ሲወጡ በየደረስንበት ሁሉ ደረጃቸውን የጠበቁ የቱሪስት መስህቦችን እናገኛለን ማለት ነው። አዲስ አበባ የኢትዮጵያ ዋና ከተማ እንደ መሆኗ እና የኢትዮጵያን ታሪክ በውስጧ ከመያዟ አኳያ በሀገር ውስጥም ሆነ በውጭ ሀገር ጎብኚዎች ዘንድ ተፈላጊ ከተማ እንድትሆን ያደርጋታል። አሁን እየተሰሩ ያሉ ስራዎች ጎብኚዎች ከአስራ አምስት ቀን እስከ አንድ ወር ሊቆዩበት የሚችሉባት ከተማ እየሆነች ነው።

አዲስ ዘመን፡- አዲስ አበባ ከሌሎች አቻ ከተሞች አንጻር ያለችበት የመስህብ ደረጃ ምን ላይ ደርሷል ?

ዶክተር ሂሩት፡– አዲስ አበባ በአሁኑ ወቅት ከየትኛውም ከተማ በተሻለ ቱሪስቶችን የሚያማልል መስህብ አላት። በዓለም ላይ ያሉ የቱሪዝም አይነቶችን በአንድ ከተማ ውስጥ ማግኘት አይታሰብም፤ በአንድ ከተማ ውስጥ ሁለት ቢበዛ ሶስት አይነት የቱሪስት መስህብ ቢኖር ነው። አዲስ አበባ ግን ከአስር የበለጠ መስህብ ያላት ከተማ ነች።የስፖርት ቱሪዝም ፣ የንግድ ቱሪዝም፣ የትምህርት ቱሪዝም ፤ የባህል የተፈጥሮ ቱሪዝም ፤ የታሪክ፣ የቅርስ የቱሪዝም አይነቶች በአዲስ አበባ ይገኛሉ።ይሄን የትኛውም ከተማ ውስጥ ልናገኘው አንችልም። ከዚህ በላይ በአሁኑ ወቅት የኮንፈረንስ ቱሪዝም ለአዲስ አበባ ትልቁ ቱሪዝም ሆኗል፤ በአንድ ወር ውስጥ ብቻ ከ20 በላይ አህጉራዊ እና ዓለም አቀፋዊ ኮንፍረንሶችን አካሄደናል:: በሩብ ዓመት ከ40 በላይ አህጉራዊና ዓለም አቀፍ ኮንፈረንስ አካሂደናል።

የምግብ ቱሪዝምን ብንወስድ ወደ ባህላዊ ሬስቶራንቶቻችን የሄደ ቱሪስት ተደስቶ ነው የሚመለሰው። ምን አልባት እጥረት ያለብን የውሃ ቱሪዝም ብቻ ነው።ይሄ ደግሞ ወደ ፊት በትኩረት ከሚሰሩት ውስጥ ነው። ሆኖም ፍል ውሃ ከፍተኛ የጤና ቱሪዝም የሚሆን ነው።

የጤናን ጉዳይ ካነሳን ባሉን ሆስፒታሎች በርካታ የውጭ ሀገር ዜጎች እየመጡ እየታከሙ ነው። ለምሳሌ ኤርትሪያ፣ ጅቡቲ፣ ሶማሊያ፣ ሱዳን፣ ደቡብ ሱዳን፣ የመሳሰሉ ሀገራት ዜጎች እዚህ መጥተው ይታከማሉ፣ በተለያዩ ሆስፒታሎቻችን ዳታው ስላለን ነው። ይህም በቀጣይ ተጠናክሮ የሚቀጥል ነው።

በአጠቃላይ በአንድ ሀገር ወይንም በአንድ ከተማ ውስጥ የቱሪስት መዳረሻዎች በአይነትም በመጠንም መብዛት ሁለት ጠቀሜታዎች ይኖሩታል። አንደኛው በዓለም ላይ ያሉ ቱሪስቶችን ፍላጎት ለማሟላት የሚያስችል ይሆናል። አንዳንዱ ቱሪስት ማየት የሚፈልገው ተፈጥሮን ይሆናል። ሌላኛው ደግሞ መዝናኛ ይፈልጋል፤ ሌላው ደግሞ ታሪካዊ መዳረሻዎችን ወይንም ቅርሶችን ማየት ይፈልጋል። አንዳንዶች ደግሞ ለምግብና ለስፖርት ብቻ ብለው የሚንቀሳቀሱም አሉ። በመሆኑም ሁሉንም ነገር ማካተት ከቻልን የቱሪስቶች አይን ወደእኛ መዞሩ አይቀርም።

ሁለተኛው ደግሞ የቱሪስት ቆይታ ጊዜ ረዘም ያለ መሆኑ ነው። ከቱሪስት መዳረሻነት የሚገኙ ተጠቃሚነቶች ሲታሰቡ አንድ ቱሪስት ወደ ሀገር ቤት ለጉብኝት መምጣቱ ብቻ ሳይሆን የሚቆይበትም ጊዜ ወሳኝ ነው። በዚህ ሁኔታ በርካታ ደረጃቸውን የጠበቁ መዳረሻዎች ሲኖሩ ቱሪስቶች መቆያ ጊዜያቸውን ለማራዘም ይገደዳሉ። ይህ ደግሞ ብዙ ገንዘብ ኢንቨስት እንዲያደርጉ የሚያስችል ይሆናል። አሁን ላይ አዲስ አበባ እንደ ከዚህ ቀደሙ በሶስት ቀን ቆይታ የሚሰናበቷት መሆኗ ቀርቶ ከአስራ አምስት ቀን በላይ የሚሰነብቱባት ከተማ ለመሆን በቅታለች ።

አዲስ ዘመን፡- የኮሪደር ልማቱ ለቱሪዝም ዕድገቱ ምን እያበረከተ ነው

ዶክተር ሂሩት፡– ኮሪደር ልማት ከቱሪዝም ጋር ከፍተኛ ቁርኝት ያለው የመሰረተ ልማት ስራ ነው። የኮሪደር ልማቱ ቅርሶቻችንን አጉልቶ በማውጣት፣ የበለጠ በመጠበቅ፣ በማደስ፣ በመጠገን ፊት ለፊት መጥተው እንዲታዩ የሚያደርግ ዘመናዊ አሰራር ነው። በተለይ በአዲስ አበባ የተሰራ የኮሪደር ልማት የቱሪዝምን ደረጃ በሚያሳድግ መልኩ ነው የተከናወነው። የኮሪደር ልማቱ አንድ የቱሪስት ከተማ ማሟላት ያለባትን መስፈርት እንድታሟላ አስችሏታል።

የኮሪደር ልማቱ የቱሪስቶችን ደህንነት እንዲጠበቅ የሚያደርግ ነው። መሰረተ ልማቱ ከመንገድ ባሻገር መብራቶች እና የደህንነት ካሜራዎች የተሟሉለት ነው። ቱሪስቶች በማታ መንቀሳቀስ ሊፈልጉ ይችላሉ። ቱሪስት በተሽከርካሪ ብቻ ሳይሆን በእግሩም በተለያዩ ቦታዎች እየተንቀሳቀሰ የመስህብ ቦታዎችን ለመጎብኘት ይፈልጋል። ለዚህ ደግሞ አካባቢው ውብ መሆን ብቻ ሳይሆን ንጹህ መሆን ያስፈልገዋል። ደህንነቱ የተጠበቀም ሊሆን ይገባል። በዚህ ረገድ አዲስ አበባ በቀን ብቻ ሳይሆን በማታም በብርሃን የተንቆጠቆጠች ሆናለች። ይህም ከውጪ ሀገራት ለሚመጡ እንግዶች ብቻ ሳይሆን ዜጎችም በእነዚህ አካባቢዎች ያለ ስጋት ንጹህ በሆነ ቦታ በነጻነት ለመንቀሳቀስ ያስችላቸዋል።

የኮሪደር ልማቱ መከናወንም ለቱሪስት የሚያስፈልገውን መሰረተ ልማት ለማሟላት ያስቻለ ነው። ከደህንነት ጀምሮ የተመቻቸ መንገድ እንዲኖር አስችሏል። መስህቡ እያለ እነዚህ ነገሮች ባይሟሉ ኖሮ ቱሪስት የሚመጣበት እድል አይኖርም ነበር።

አዲስ ዘመን፦ በቱሪዝም ረገድ አንዲት ከተማ ማሟላት ያለባት ምንድን ነው ?

ዶክተር ሂሩት፦ የመጀመሪያው መስህብ ነው። ሳቢ ነገር ያስፈልጋል። ማለትም ቱሪስቱ ወደዚህ ሀገር ለመምጣት የሚስበው ነገር ያስፈልጋል። ለምሳሌ የሚጎበኝ ባህላዊ ነገር አለ ወይ? ተፈጥሮ አለ ወይ? ከሌላው ሀገር የተለየ እኛ ጋር ምን ተፈጥሮ አለን? የሚሉት መመለስ አለባቸው።ከዚህ አንጻር ከላይ እንዳነሳሁት አዲስ አበባ ሀብታም ነች።

ለምሳሌ መርካቶ ለእኛ አንዱ መስህባችን ነው። መርካቶ እቃ ለመግዛትና እቃ ለመሸጥ ተብሎ በሀገራችን የትኛውም አቅጣጫ ያለው ማህበረሰብ ብቻ ሳይሆን ከአፍሪካም ከቻይናም ከቱርክም የሚመጡ ሸቀጦች መርካቶ ይገኛል። ስለዚህም መርካቶ የቱርክም የቻይናም ከተማ ነች።

ሌላው መስህባችን ስፖርት ነው። አሁን አሁን ታላቁ ሩጫ የሀገራችን ገጽታ ለሌላው ዓለም እያስታወቀ ነው። ኢትዮጵያ የስፖርተኞች ሀገር ከመሆኗ አንጻር በርካታ የስፖርት ቱሪዝም የሚኖራት ሀገር ነች። ባህላዊ አልባሳት፣ባህላዊ ምግብ ፣ነባር ቅርሶች ወዘተ አዲስ አበባን ተመራጭ ያደርጓታል።

ከዚሁ ጎን ለጎን ደግሞ መሰረተ ልማት ወሳኝ ነው። ከመስህቦቹ ጋር አንደኛ መንገድ መኖር አለበት፤ ሁለተኛ ትራንስፖርት ከአውሮፕላን እስከ ታክሲ አጠቃላይ የትራንስፖርት አይነቶች መሟላት አለባቸው፤ ሌለው ትልቁ ነገር ሆቴል ነው። የሆቴል አገልግሎት መኖር ለቱሪዝም እንቅስቃሴ ወሳኝ ነው።

በአሁኑ ወቅት ደግሞ ቴክኖሎጂ መሰረታዊ ነገር ነው። ኢንተርኔት አለ ወይ? የተለያዩ የማህበራዊ ሚዲያ አመራጮች ማግኘት እችላለሁ ወይ? የሚሉ ጉዳዮች በቱሪስቶች የሚነሱ ጥያቄዎች ናቸው። መብራት፣ ውሃ የመሳሰሉትም አንድ የቱሪስት ከተማ ልታሟላቸው የሚገቡ መሠረታዊ ነገሮች ናቸው። በዚህ ረገድ አዲስ አበባ ከሞላ ጎደል ብዙዎቹን ታሟላለች።

አዲስ ዘመን ፡- ለነበረን ቆይታ አመሰግናለሁ።

ዶክተር ሂሩት፡- እኔም አመሰግናለሁ።

እስማኤል አረቦ

አዲስ ዘመን ህዳር 21/2017 ዓ.ም

Recommended For You