‹‹መልካም ስም ከመልካም ሽቶ ይበልጣል›› እንዲሉ አበው ስም ከተግባር እንዲጣመርባት የተደረገችውን የአሁኗን አዲስ አበባ መጥቀስ ይገባል። አዲስ አበባን ልክ እንደ ስሟ ውብና አበባ ለማድረግ ታስቦ እየተከናወነ ባለው የኮሪደር ልማት በእርግጥም ስምን ከተግባር ማገጣጠም ተችሏል።
አዲስ አበባ ከተማ እንደ ስሟ ሳትሆን ዘመናትን ስለማስቆጠሯ ነዋሪዎቿ ብቻ ሳይሆኑ እንግዶቿም የሚናገሩት ሀቅ ነው። የከተማዋ ውበት ስሟ ላይ ብቻ የቀረ ስለመሆኑ እኛም አሳምረን እናውቃለን። ከተማዋ ጥቂት ጥሩዎች አልነበሯትም ማለት አይቻልም፤ አሏት፤ ይሁንና በመጥፎቿ በመሸፈናቸው መገለጫዋ ጉድለቷ ሆኖ ኖሯል። አብዛኛው የከተማዋ ክፍል ስሟን፤ የሀገሪቱ፣ የአፍሪካ ህብረት፣ የዓለም አቀፍ ተቋማት መቀመጫ ከተማነቷን ጨርሶ የማይመጥን ሆኖ ቆይቷል።
ከተማዋ እንደ አፍሪካ ህብረት አይነት ጉባዔዎችን ለማካሄድ ስትዘጋጅ ጎዳናዎቿ ሲጸዱ፣ ህንጻዎቿ ቀለም ሲቀቡ፣ መብራቶች ሲገጠሙላት፣ መንገዶች ሲጠገኑ፣ ዛፎችና አበቦች ሲተከሉ ዓመታት አልፈዋል። እነዚህ ሁሉ ጥረቶች ለሰሞን ካልሆነ በቀር ከተማዋን እንደ ስሟ አበባ ማድረግ አልቻሉም።
ለእዚህም ነው ከተማዋን እንደ ስሟ አበባ ለማስመሰል መንግሥት ቁርጠኛ አቋም ይዞ ወደ መሥራት የገባው። በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አቢይ አሕመድ ዶ/ር አነሳሽነትና በከተማዋ አስተዳደር ያላሰለሰ ጥረት ይህን ውጥን መሬት ላይ ለማውረድ ባለፉት ወራት በኮሪደር ልማቱ ከፍተኛ ርብርብ ተደርጓል።
ይህን ተከትሎም ከተማዋ ዛሬ ከስሟ ጋር ሊጣፃም የሚችል ልማት ማየት ጀምራለች። ከተማዋ ሰፊ ከመሆኗ አኳያ ገና ብዙ መሰራት ያለባት ቢሆንም፣ የኮሪደር ልማቱ በተከናወነባቸው በርካታ ሥፍራዎች የታየው ለውጥ ከተማዋን እንደ ስሟ ውብ ማድረግ መጀመሩን በሚገባ አመላክተዋል። ለውጥ ስትናፍቅና ስትሻ የኖረችው ጥንታዊቷ ከተማ አዲስ አበባ እየተዋበች ፣ እያማረችና እያበበች ያለችበት ሁኔታ ይህን ይጠቁማል።
ከተማዋ ዘመኑን የዋጀች እንድትመስል ለማድረግ ሰፋፊ ሥራዎች ተከናውነዋል፤ እየተከናወኑም ይገኛሉ። በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ የነበሩ ነዋሪዎቿን ወደ አዳዲስ መንደሮች ማዛወር ላይ በስፋት እየተሠራ ነው። በዚህ አይነት መንገድ የተለቀቁ ቦታዎችን ለመንገድና ለመሳሰሉት መሠረተ ልማቶች በማዋል ከተማዋን ባለሰፋፊ ደረጃቸውንም የጠበቁ የተሽከርካሪና የእግረኞች መንገድ ባለቤት ማድረግ ተችሏል።
የአካል ጉዳተኞች፣ የሞተር አልባ ተሽከርካሪዎች መንገዶችም ተካተውባቸዋል። ሰፋፊ አረንጓዴ ሥፍራዎች፣ መዝናኛዎች፣ መጸዳጃ ቤቶች፣ ፋውንቴኖች፣ የተሽከርካሪ ማቆሚያዎች፣ የታክሲና አውቶብስ ተርሚናሎች ተገንብተዋል።
የስልክ፣ የኤሌክትሪክ፣ የፍሳሽ ቆሻሻና የመጸዳጃ ቤት ፍሳሽ መስመሮች ከመዝረክረክ ወጥተው ከምድር በታች በስርአቱ እንዲዘረጉ መደረጉ፣ የድህንነት ካሜሪዎች ተገጥመዋል፤ የመሬት ውስጥ የእግረኞች ማቋረጫዎች፣ ወዘተ ተገንብተዋል።
‹‹አይን አይቶ ልብ ይፈርዳል›› እንዲሉ አበው አዲስ አበባ ከተማ በእርግጥም እንድትለወጥ እንድታሸበርቅ ተደርጋለች። አምራም፣ ተለውጣም፣ አሸብርቃም በአይናችንን በብረቱ ተመልክተናል፤ ለእዚህ የአይን ምስክሮች ነን። ባማረው ባሸበረቀው የከተማዋ ክፍል እየገባን እየወጣን ልማቱን ማጣጣም ከጀመርን የቆየንም ነን። አዲስ አበባን እንደ ስሟ ይሏል እንዲህ ነው!
ለውጡን አይቶና ተመልከቶ ሳያደንቁ ማለፍ ተገቢ አይደለም፤ የውጭ ዜጎችን ጨምሮ መላው ህብረተሰብ የመሰከረለትን ይህን ታላቅ ተግባር አለማድነቅ ተገቢ አይደለም፤ የአዲስ አበባን አዲስ መሆን መጀመር አድንቀናል። አዲስ አበባ ሰፊ፣ ችግሮቿም እጅግ ውስብስብ እንደመሆናቸው የተጀመረው ከተማዋን ውብና ለነዋሪዎቿ፣ ለጎብኚዎቿና እንግዶቿ ምቹ የማድረጉ ሥራ በሁለተኛው ምእራፍ የኮሪደር ልማት ተጠናክሮ እንዲቀጥልም ተመኝተናል።
የኮሪደር ልማቱ ከተካሄደባቸው ጎዳናዎች አብዛኞቹ ሕዝብ በብዛት የሚንቀሳቅሳባቸው እንደመሆናቸው በባለጉዳዮች፣ በባለአሽከርካሪዎች ብቻ የሚታወቁ አይደሉም፤ ለጤና ብለውም ይሁን ለሌላ ጉዳይ የእግር ጉዞ በሚያደርጉም በሚገባ የሚታወቁ ገዝፈው የሚታዩ ሀውልቶች ሊባሉ የሚችሉ ናቸው።
አሁን አዲስ አበባ እንዲህ ተውባና ደምቃ መታየት ጀመረች እንጂ የቀድሞ ገጽታዋ የአፍሪካ ህብረት ዋና መዲናና የዲፕሎማቶች መቀመጫ ለሆነችው አዲስ አበባ ፍጹም የማይመጥንና ከዘመኑ ጋር አብሮ የማይሄድ ነበር። የጽዳት ጉድለትን በመጥቀስ በተደጋጋሚ ሲያስወቅሷት አልፎም ተርፎ ይህን የአፍሪካ ህብረት መዲናነቷን ሊቀሟት የዳዳቸው እንደነነበሩም ይታወሳል።
በወቅቱ በተደረጉ የዲፕሎማሲ ሥራዎች ከተማዋ የአፍሪካ ህብረት ዋና ከተማ ለመሆን በቅታለች። ይህን እውነታ በመረዳት በከተማዋ ላይ ለውጥ ለማምጣት በቀደሙት አመታት የከተማዋን መሠረተ ልማት፣ ጽዳትና ውበት የተመለከቱ ሥራዎች ቢካሄዱም፣ መሰረታዊ ለውጥ ያመጡ ግን አልነበሩም።
ከለውጡ በኋላ በተለይ ካለፈው ዓመት ጀምሮ ከተማዋን ለማደስና ለማዘመን የሚያስችልና ማስቻልም የጀመረ የኮሪደር ልማት ሥራ ውስጥ በሰፊው ተገብቷል። ልማቱ በምዕራፍ ተከፋፍሎ እየተከናወነ ከመሆኑም በላይ የከተማዋን ገጽታ መቀየር ያስቻለ ሥራ ተሰርቶበታል፤ እየተሠራበትም ነው። በተጠናቀቀው የመጀመሪያው ምዕራፍ የኮሪደር ልማት ሥራ ከፍ ሲል የጠቀስኳቸውን ስኬቶች ማጣጣም ተችሏል፤ የሁለተኛው ምዕራፍ ሥራም በፍጥነት እየተከናወነ ይገኛል።
ይህ ስኬታማ ተግባር በዜጎች፣ በከተማ ልማት ባለሙያዎች፣ በዲፕሎማቶች፣ ወዘተ አድናቆት እየተቸረው ሲሆን፣ አድናቆቱ ከሀገር ውጭ ጭምር እየመጣ ነው። በቅርቡም የአዲስ አበባ ከተማ የአፍሪካ ስማርት ከተሞች አዋርድ ተሸላሚ የሆነችበት ሁኔታም ይህንን ያመለክታል። ከተማዋ ከሌሎች ስማርት የአፍሪካ ከተሞች ጋር ተወዳድራ ነው ተሸላሚ ለመሆን የበቃችው።
ለከተማዋ ይህ ሽልማት ሊሰጥ ከቻለባቸው ዋንኛዎቹ ምክንያቶች መካከል በኮሪደር ልማት ለነዋሪዎቿ ምቹ እና ተስማሚ ከተማ መልሳ ለመገንባት ያከናወነችው ሥራና የተገኘው አመርቂ ውጤት እንዱ መሆኑ ተጠቁሟል፤ በአረንጓዴ ዐሻራ መርህ ግብር የአየር ለውጥ ተጽዕኖን ለመቀነስ እየተተገበረ ያለው ተምሳሌታዊ ተግባርም ሌላው ምክንያት መሆኑ ተመላክቷል።
በተመሳሳይ የአፍሪካ ሀገራት ከተሞችን የዕድገት ደረጃ የሚገልጸው ኢኮኖሚስት ኢንተለጀንስ ዩኒት የተሰኘው ድርጅት በ2024 ባወጣው ሪፖርትም እንዲሁ አዲስ አበባ ከተማን በፈጣን ዕድገት ላይ የምትገኝ ሲል ጠቅሷታል።
ይቺ በእድገት ጎዳና ላይ ያለች ከተማ የዓለምን ቀልብ እየሳበች በመሆኗ በርካታ አህጉርና ዓለም አቀፍ ሁነቶችን ለማስተናገድ እድሉ ተፈጥሮላታል። በ2017 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ሩብ ዓመት ብቻ ከ30 በላይ አህጉርና ዓለም አቀፍ ሁነቶች በብቃት ማስተናገድ ችላለች። በዚህም ብዙ ሁነቶች የማስተናገድ አቅምና ብቃት እንዳላት እያስመሰከረች ትገኛለች። ከወራት በኋላም እንዲሁ የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባዔን በተሻለ ሁኔታ ለማስተናገድ እየተዘጋጀት ስለመሆኗ መረጃዎች ያመላክታሉ።
ከተማዋ ከሌሎች ከተሞች ይልቅ እነዚህን አህጉርና ዓለም አቀፍ ሁነቶች እንድታስተናግድ የተመረጠችባቸው ምክንያቶች ብዙ ቢሆኑም፣ የከተማዋን ገጽታ ለመቀየር እየተከናወኑ የሚገኙ ተግባሮችና እነሱን ተከትሎ የታዩ ለውጦች ናቸው። በቀጣይም ከተማዋን የቱሪዝምና የኮንፈረንስ ማዕከል ለማድረግ የተጀመረውን ሥራ አጠናክሮ ማስቀጠል ይገባል። በተለይ ኢትዮጵያዊ ጨዋነትንና እንግዳ ተቀባይነታችንን አጉልተን በማሳየት፣ የቱሪዝም መስህቦቿ እንዲተዋወቁ ማድረግ ላይ በትኩረት መሥራት ያስፈልጋል።
ከተማዋ ገና ብዙ መሥራት ይጠበቅባታል፤ ይህ በእንዲህ እንዳለም የተሠሩትንና እየተሠሩ ያሉትን ውጤቶች አስጠብቆ ማስቀጠል ሌላው ሥራ ሊሆን ይገባል። ይህ እንዲሆን የሚመለከታቸው አካላት ቀጣዩን ሥራቸውን ማወቅና መሥራት ይኖርባቸዋል።
በከተማዋ መሠረታዊ ለውጥ ማምጣት የተጀመረው በኮርደር ልማቱ ስለመሆኑ የተከናወኑ ተግባሮች ይናገራሉ። ከተሞች ዘመናዊነትን መላበስ ባለባቸው በዚህ ወቅት ከተማ ማደስ ብቻ በቂ ላይሆን ይችላል፤ በርካታ ከተሞች ዘመኑን የዋጀ አዲስ ከተማ እስከመገንባት ደርሰዋል። የኢትዮጵያ መንግሥትን በጫካ ፕሮጀክት ስማርት ከተማ እየገነባ መሆኑ ይታወቃል። ይህን ሲያደርግ ግን አብዛኛው ሕዝብ ያለባትን ከተማ ወደ ጎን መተው አልፈለገም። አብዛኛው ሕዝብ የሚኖርባቸውን የከተማዋን ክፍሎች ማደሱን በስፋት ተያይዞታል።
በመልሶ ልማቱ መሠረተ ልማት ብቻ ሳይሆን የለማው ሰውም ጭምር ነው። በደካከሙ ቤቶች ይኖሩ የነበሩ የከተማዋን ነዋሪዎች በዘመናዊ ቤቶች መኖር የሚያስችላቸውን ሁኔታ ፈጥሮላቸዋል። ልማቱ ሰው ተኮር የተባለውም ለእዚህ ነው።
ትንሳኤ አበራ
አዲስ ዘመን ኅዳር 21 ቀን 2017 ዓ.ም