ባሕላዊ ሕክምና ሀገር በቀል የሆነና በልምድ የዳበረ እንዲሁም በህብረተሰቡ ተቀባይነት ያገኘ እውቀት ሆኖ የእጽዋትንና የእንስሳትን ተዋጽኦ ወይም ማዕድናትንና የእጅ ጥበብን በመጠቀም የሚሰጥ የሕክምና አገልግሎት እንደሆነ ይነገራል። በኢትዮጵያ የባሕል ሕክምና ከጥንት ጀምሮ የነበረና ዘመናዊ ሕክምና ወደ ሀገሪቱ ከመግባቱ በፊት ሕዝቡ በስፋት ሲገለገልበት የቆየ ነው። ዘመናዊ ሕክምና በኢትዮጵያ ከተስፋፋም በኋላ ከ85 በመቶ በላይ የሚሆነው የማህበረሰብ ክፍል የዚሁ የባሕል ሕክምና ተጠቃሚ መሆኑን ጥናቶች ያረጋግጣሉ።
ከዚህ ቀደም በኢትዮጵያ የባሕል ሕክምና ሙያ ያላቸው አዋቂዎች በተናጠልና በተበታተነ ሁኔታ አገልግሎቱን ለህብረተሰቡ ሲሰጡ ቆይተዋል። ህብረተሰቡም ከዘመናዊው ሕክምና ባልተናነሰ መልኩ የዚሁ ባሕላዊ ሕክምና አገልግሎት ተጠቃሚ ነበር። ሕክምናው በሳይንሳዊ መንገድ ተፈትሾና ተረጋግጦ ለማህበረሰቡ እንዲቀርብ ሲደረግ የነበረው ጥረትም ያን ያህል አልነበረም።
በአሁኑ ወቅት ግን በተለይ የአዲስ አበባ የባሕል ሕክምና አዋቂዎች ማህበር ተበታትነው እየሠሩ ያሉ በርካታ የባሕል ሕክምና ባለሙያዎችን በማሰባሰብና የማህበሩ አባል እንዲሆኑ በማድረግ ከሚመለከተው አካል ፍቃድ አግኝተው ለህብረተሰቡ የተሻለ አገልግሎት እንዲሰጡ እየሠራ ይገኛል። ከዘመናዊው ሕክምና ጋር እንዲቀራረብም ከአዲስ አበባ ከተማ ጤና ቢሮ፣ ከአዕምሯዊ ንብረት ባለሥልጣንና ከአርማወር ሃንሰን የምርምር ኢንስቲትዩት ጋር በጋራ እየሠራ ነው።
ሐኪም መኳንንት ብርሃኑ የባሕል ሐኪም ናቸው። ባሕላዊ ሕክምናን ለማዘመን በሚደረገው ጥረት ሙሉ ፍቃደኛ ሆነው ከአዲስ አበባ ጤና ቢሮና ጉዳዩ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በትብብር ሲሰሩ ቆይተዋል። የባሕል ሕክምና በአግባቡና በሳይንሳዊ መንገድ ከተሠራበት ጠቀሜታው ከፍተኛ መሆኑን በመረዳትና ለዚህም ተባባሪ በመሆን በተለይ እንደ አዲስ አበባ ከተማ የባሕል ሕክምና አዋቂዎች ማህበር አባል በመሆን ሕክምናው እንዲሻሻል ከፍተኛ ጥረት ሲያደርጉ ቆይተዋል።
እርሳቸው እንደሚሉት፤ የባሕላዊው ሕክምና ከዘመናዊው ጋር እንዲቀራረብና በጋራ ለመሥራት እንደ ማህበር እቅድ ተይዟል። የባሕል ሐኪሞች እውቀታቸውንና ሙያቸውን ለአዕምሯዊ ንብረት ባለሥልጣን እንዲያስመዘግቡም እየተደረገ ነው። እርሳቸውም የባሕል ሕክምና እውቀታቸውን ለአዕምሯዊ ንብረት ባለሥልጣን አስመዝግበው እየሠሩ ይገኛሉ። ለእውቀታቸው ጥበቃ አግኝተውም ሥራቸውን እንዲሰሩ ሆነዋል።
ባሕላዊ ሕክምናን ለማሳደግ፣ ለማዘመንና ራሱን የቻለ ለማድረግ እንደ ማህበር ጥረቶች እየተደረጉ ይገኛሉ። በትምህርት ደረጃም የባሕል ሕክምና ሙያን ለማሳደግ ሥራዎች እየተከናወኑ ሲሆን፤ ከእነዚህ ውስጥ አንዱ ትምህርት ቤት ለመክፈት እየተደረገ ያለው ዝግጅት ነው። ከዚህ በተጓኝ በአዲስ አበባ ጤና ቢሮ፣ በአዕምሯዊ ንብረት ባለሥልጣንና በአርማወር ሀንሰን የምርምር ኢንስቲትዩት በኩል ሕክምናው የአዕምሯዊ ባለቤትነት እንዲኖረው በሳይንሳዊ መንገድ ተደግፎ አገልግሎት እንዲሰጥበት የተጀመሩ ሥራዎች አሉ። እነዚህ ሥራዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ ተብሎ ይጠበቃል።
ልጃቸው በላብራቶሪ ሳይንስ መመረቁን የሚናገሩት ሐኪም መኳንንት፤ ባሕላዊ ሕክምና ዘመናዊ መልክ ተላብሶ እንዲሰራበት ካላቸው ፍላጎት የተነሳ ልጃቸው አብሯቸው እንዲሠራ ማድረጋቸውን ይገልፃሉ። ለሕክምናው ግብዓት የሚውሉ አንዳንድ መሳሪያዎችን ከውጭ ለማስመጣት ጥረት እያደረጉ እንደሆነም ይናገራሉ። በእነዚህ መሳሪያዎች አማካኝነት ለምርምር የሚያቀርቧው መድኃኒቶች እንደሚኖሩም ነው ሐኪም መኳንንት የገለጹት። በሌላ በኩል ደግሞ የእፅዋት ግብዓት ችግር እንዳለም ጠቅሰው፤ በተለይ ሀገር በቀል እፅዋት እየጠፉ መሆናቸውንና ያሉትንም ለማግኘት ከቦታ ቦታ መንቀሳቀስ አስቸጋሪ መሆኑን ያስረዳሉ። እንዲያም ሆኖ ግን ከጉለሌ እፅዋት ማዕከል ጋር በመነጋገር ለባሕል ሕክምና መድኃኒት ግብዓትነት የሚውሉ እፅዋት በአንድ ቦታ የሚተከሉበት ሁኔታ እንዲመቻች ቃል እንደተገባም ይናገራሉ።
አቶ ለሜሳ ነገራ በአዲስ አበባ ጤና ቢሮ የመድኃኒትና የሕክምና አቅርቦትና አገልግሎት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ስር የባሕል ሐኪሞች አስተባባሪ ሆነው ይሰራሉ። እርሳቸው እንደሚናገሩት፤ የባሕላዊ ሕክምናን ከዘመናዊው ጋር ማቀራረብ ሲባል ሥራውን ዘመናዊነት በተላበሰ መልኩ እንዲያከናውኑ ነው። በባሕላዊ ሕክምና ሕዝቡ የሚያውቃቸው መድኃኒቶች አሉ። ለምሳሌ፡- ጤና አዳም፣ ነጭ ሽንኩርትና ፌጦ የመሳሰሉት በአብዛኛው ኢትዮጵያውያን ዘንድ የሚታወቁና ለመድኃኒትነት ጥቅም ላይ የሚውሉ ናቸው።
በሌላ በኩል ደግሞ አብዛኛው ሕዝብ የማያውቃቸው ነገር ግን የባሕል ሐኪሞች ብቻ የሚያውቋው መድኃኒቶች አሉ። እነዚህ መድኃኒቶች እንዳይዘረፉና እንዳይጠፉ በአዕምሯዊ ንብረት ባለሥልጣን እንዲመዘገቡ የማድረግ ሥራ እየተከናወነ ይገኛል። ይህም አራት መሠረታዊ ሃሳቦች አሉት። አንደኛው የቅጂ መብት ነው። ሁለተኛው የራስ መብት መሆኑን የሚያሳይ ነው። ሶስተኛው የራስ መብትንና የአዕምሯዊ ንብረት ባለቤትነትን አጣምሮ የሚይዝ ነው። አራተኛው ደግሞ የጂኦግራፊያዊ መብት መሆኑን ይጠቁማል። እነዚህ የባሕላዊ ሕክምናን ምስጢራዊነት ለመጠበቅ ድጋፍም ያደርጋሉ።
ከዚህ አንፃር ባሕላዊ ሕክምናን ወደ ዘመናዊ ለማምጣት የተሠሩ ሥራዎች አሉ። አንዱና ዋነኛው ከአርማወር ሀንሰን የምርምር ኢንስቲትዩት ጋር በመሆን ያላቸው የመድኃኒት ቅመማ እውቀት ወደ ክሊኒካል ሙከራ አልፎ ወደ ምግብና መድኃኒት ቁጥጥር ባለሥልጣን ሄዶ ወደ ሥራ የሚገባበት እድል አለው። ለምሳሌ፡- ኢትዮጵያ አብዛኛውን ዘመናዊ ስታርች ከውጭ ሀገር ታስገባለች። ይሁንና ኢትዮጵያ ውስጥ በጣም ቀላል በሆነ ዘዴ በስኳር ድንች ስታርች ማምረት ይቻላል። በዚህም የስኳር ድንችን በስፋት በማምረት የካሳቫ ዘይት ማምረት ተችሏል። በተመሳሳይ ነጭ ባሕር ዛፍ ላይ ዘይት በማውጣት ለጉንፋንና ሌሎች በሽታዎችን ለመከላከያ እንዲውል የማድረግ ጅምር ሥራዎች አሉ። ከዚህ አንፃር ወደ ዘመናዊነት እየተመጣ ነው ማለት ይቻላል።
ከዚህ ባለፈ ባሕላዊ ሕክምና ወደ ዘመናዊነት እንዲመጣ ሕክምናውን በፖሊሲ መደገፍ ያስፈልጋል። ሀገር አቀፍ ፖሊስ በመንግሥት ማቋቋሚያ አዋጅ ላይ ባሕላዊ ሕክምናን ስለማሻሻል ይጠቅሳል። ይህም አጀንዳው ትልቅ መሆኑን ያሳያል። ሀገር በቀል እውቀቶችን ማለትም ሕክምናውን፣ እደ ጥበቡን፣ ሸማውን ጨምሮ ለማሻሻል ትልቅ የሆነ አጀንዳ የብሔራዊ ፖሊሲ ላይ መኖሩ ከፍተኛ ፋይዳ ይኖረዋል።
አስተባባሪው እንደሚሉት፤ የባሕል ሕክምናው ሥርዓተ ትምህርትም ያስፈልገዋል። የባሕል ሐኪሞች እውቀታቸው እስከምን ድረስ ነው የሚለው መታወቅ አለበት። ለምሳሌ፡- የባሕል ሐኪም ሆኖ ለመሥራት ቢያንስ መጽሐፍ ማንበብ እንዳለባቸው ሕጉ ይገልፃል። ነገር ግን መጽሐፍ ማንበብ ብቻ በቂ አይደለም። ወደ ምርምር ሲኬድ የባሕል ሐኪሙ አብሮ ምርምር ማድረግ ይጠበቅበታል። ለባሕላዊ ሕክምና የትምህርት ሥርዓት መቅረፅም ሌላኛው ዘርፉን የማዘመኛ መንገድ ነው። ለዚህም የአርማወር ሀንሰን የምርምር ኢንስቲትዩት፣ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ፣ ጉለሌ እፅዋት ማዕከል ከአዲስ አበባ ጤና ቢሮ ጋር በጋራ እየሠሩ ይገኛሉ።
የባሕል ሐኪሞች ያላቸውን እውቀትና ምስጢር መጠበቅ ግን መብታቸው ነው። በግዴታ አሳዩ ሊባሉ አይችሉም። ሕክምናውን ለማሳደግና ለማዘመን ግን በትብብር መሥራት ይቻላል። ለምሳሌ የባሕል ሐኪሞች ያሏቸውን እውቀት በጋራ ወደ ምርመር ማምጣት ይችላሉ። የባሕል ሕክምና ማህበራት አለን የሚሉትን እውቀት በራሱ በአንድ ቦታ ተሰባስቦ ጥናትና ምርምር ሊካሄድበት ይችላል።
በሌላ በኩል ደግሞ የባሕል ሐኪሞች የሚሰሩባቸው የሕክምና ዘርፎች እንዳሏቸው ይታወቃል። ከዚህ አኳያ ሥርዓተ ትምህርት ያስፈልጋቸዋል። ለአብነት በጋና በባሕላዊ ሕክምና ላይ ትምህርት የሚሰጡ ሶስት ዩኒቨርሲቲዎች አሉ። በተመሳሳይ በናይጄሪያ፣ ደቡብ አፍሪካና በሌሎችም የአፍሪካ ሀገራት የባሕል ሕክምና የሚያስተምሩ ዩኒቨርሲቲዎች ይገኛሉ። ስለሆነም በእነዚህ ሀገራት የባሕል ሕክምና በጤና መድህን ሥርዓት ውስጥም ጭምር ገብተዋል። የባሕል ሕክምና ከዘመናዊ ሕክምና ጋር እንዲቀራረብ እያደረጉ ያሉት ጥረትም የሚደነቅ ነው።
በተቃራኒው ግን በኢትዮጵያ ያለው የባሕል ሕክምና ከዘመናዊው ጋር እንዲቀራረብ እየተደረገ ያለው ጥረት አናሳ ነው። አሁን ላይ ሕክምናውን ለማዘመን ግን በርካታ ሥራዎች እየተከናወኑ ይገኛሉ። በተለይ የባሕል ሐኪሞችን ማስተማርና የማብቃት ሥራ እየተሠራ ነው። የባሕል ሐኪሞቹ ከማንበብ በዘለለ ጠለቅ ያለ እውቀት ኖሯቸው የባሕል ሕክምናውን በዘመናዊ መንገድ እንዲከውኑ ለማድረግ መጠነኛ የትምህርት ሥርዓት ማዘጋጀት የግድ ይላል። ለዚህም ለምሳሌ፡- የሰውነት መዋቅር /anatomy/ ላይ ስልጠና እንዲወስዱ ከትምህርት ሚኒስቴር ጋር በመሆን የተጀመሩ ሥራዎች አሉ።
ብዙ ጊዜ የባሕል ሐኪሞች ብዙ ዓይነት ህመሞችን ቢጠየቁ ሁሉንም እንደሚያውቁና ማከም እንደሚችሉ ይናገራሉ። ይሁንና ይህ አሁን ላይ አይፈለግም። ለምሳሌ፡- የባሕል ሐኪሙ ወጌሻ ከሆነ ወጌሻ ላይ ብቻ ነው መሥራት ያለበት እንጂ በሌሎች ሕክምናዎች ላይ ገብቶ መሥራት አይጠበቅበትም። ለዚህም ከሚመለከተው የመንግሥት አካል የአዕምሯዊ ንብረት ባለቤትነት መብት መስጠት አይቻልም። ስለዚህ የባሕል ሐኪሞቹ የባለቤትነት መብት ካገኙ በኋላ ወደ ምርምር ይመጣሉ። በአዲስ አበባ ከተማም አብዛኛው የባሕል ሐኪም እውቀቱ በአዕምሯዊ ንብረት ባለሥልጣን ተመዝግቧል።
ወርልድ ኢንተሌክችዋል ፕሮፐርቲ ኦርጋናይዜሽን ከኢትዮጵያ የአዕምሯዊ ንብረት ባለሥልጣን ጋር በመተባበር ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ የባሕል ሐኪሞች በሙሉ እውቀታቸውን በአንድ የሕክምና ዘርፍ ብቻ እንዲያስመዘግቡ እየተደረገ ነው። በዚሁ መሠረትም የባሕል ሐኪሞቹ ሥራቸውን እያከናወኑ ይገኛሉ። ይህም የባሕል ሕክምናን አንድ ርምጃ ከማራመድ አኳያ ጉልህ ሚና ይኖረዋል።
አስተባባሪው እንደሚያብራሩት፤ የባሕል ሐኪሞች በፖሊሲ ደረጃ የመጀመሪያ ሕክምና አገልግሎት ይሰጣሉ እንጂ ከፍተኛ ደረጃ ያለውን ሕክምና እንዲሞክሩ አይፈቀድም። ፖሊሲውም ሆነ የቢሮ አሠራርም ይህንኑ ነው የሚደግፈው። ከዚህ ባለፈ ግን እንሠራለን የሚሉ የባሕል ሐኪሞች አሉ። ይህ ሲሆን የባሕል ሐኪሙ ስፔሻል ዘርፍ አለኝ ብሎ እንዲመጣና በአዕምሯዊ ንብረት ባለሥልጣን እንዲመደብ ይደረጋል። የጉበት ሕክምና ከሆነ ጉበት ላይ ብቻ እንዲያተኩር ይሆናልም።
ከዚሁ ጋር በተያያዘም የአዲስ አበባ ጤና ቢሮ ለባሕላዊ ሐኪሞች የአቅም ግንባታ ሥልጠና ከጤና ሚኒስቴርና ከምግብና መድኃኒት ባለሥልጣን ጋር በመሆን ይሰጣል። የባሕል ሐኪሞቹ በሚሰሩባቸው ቦታዎች ላይ ከምግብና መድኃኒት ባለሥልጣን ጋር በመሆን አሟልተው እንዲሠሩ ዝቅተኛውን ደረጃ ድጋፋዊ ክትትል ያደረጋል። ባሉበት ቦታ ከክፍለ ከተሞች ጋር ተገናኝተው ተጨማሪ ድጋፍ እንዲያገኙም እድሉን ይፈጥራል።
አስናቀ ፀጋዬ
አዲስ ዘመን ህዳር 21/2017 ዓ.ም