እሳቸውም ሆኑ መላው የቤተሰባቸው አባላት በጠንካራ የስራ ባህል ተኮትኩተው ማደጋቸውን ይናገራሉ። በሥራው ዓለም አርአያዬ የሚሏቸው የወላጅ አባታቸውን ትጋት እና የስራ ፍቅር እያዩ ማደጋቸው አሁን ላሉበት ደረጃ ወሳኝ መሰረት ጥሎላቸዋል።
አባታቸውን ብርቱ እና ሃገር ወዳድ ሲሉ ይገልጧቸዋል። አባታቸው በትምህርቱም ሆነ በንግድ ስራ የጠለቀ እውቀት እንዲኖራቸው በማድረግ የላቀውን ድርሻ እንደሚይዙ የዛሬው የስኬት አምድ እንግዳችን የኬ መቅድም አጠቃላይ አስመጪና ላኪ ድርጅት ዋና ስራ አስኪያጅ ዶክተር ሙሉጌታ ኪዳነ ማርያም ይመሰክራሉ። ከልጅነታቸው ጀምሮ የተለያዩ የእህል አይነቶችን ከአርሶ አደሮች እየገዙ የመሸጥ የንግድ ስራዎች እየሰሩ ይገኛሉ።
የተወለዱትም ሆነ ያደጉት አዲስ አበባ ከተማ ነው። ከነጋዴ ቤተሰብ የተወለዱት እኚህ ሰው በጠንካራ ስራ ባህል ተኮትኩተው ቢያድጉም በትምህርትም ገፍተው እንዲሄዱ ወላጅ አባታቸው ከፍተኛ ድጋፍ የደርጉላቸው እንደነበር ያስታውሳሉ። በዚህም በእንስሳት ሕክምና ትምህርት ዘርፍ ዶክትሬት ዲግሪያቸውን ይዘዋል።
ይሁንና አባታቸውን ለማገዝ በነበራቸው ጽኑ ፍላጎት መሰረት እንደተመረቁ ኬ መቅድም አጠቃላይ አስመጪና ላኪ በተሰኘው የአባታቸው ድርጅት ውስጥ ተቀጥረው ሁመራ በሚገኘው የሰሊጥ ማዘጋጃ ቅርንጫፍ ስራ አስኪያጅ ሆነው ማገልገላቸውን ያስታውሳሉ።
‹‹እኛ ቤት ሁላችንም ሚዛን መዛኞች ነበርን፤ እንደአሁኑ ምርቱን በምርት ገበያ በኩል መላክ ሳይጀመር ግዢ ላይ ልናደርግ የሚገባንን ጥንቃቄ በቅጡ ተገንዝበን አድገናል፤ እኔም ጎበዝ መዛኝ ነበርኩ። ከፍተኛ ትምህርቴን እንደጨረስኩ ሁመራ የቅርንጫፍ ማናጀር ሆኜ ስመደብ የሰሊጥ ጆንያውን እየወጋሁ ጥራቱን እያየሁ፤ እየመዘንኩ በመግዛት ስራ ጀመርኩ›› ይላሉ።
ከተመሰረተ ከ29 ዓመታት በላይ በሆነው በዚሁ የአባታቸው ላኪና አስመጪ ድርጅት ውስጥ ሙሉ ለሙሉ መስራት ከጀመሩ ወዲህ በተለይም ድርጅቱ የሚታወቅበትን የሰሊጥ ንግድ በከፍተኛ ደረጃ ማሳደግ ችለዋል። ስራውን በኃላፊነት መምራት ሲጀምሩ ድርጅቱ ሰሊጥ ምንም አይነት እሴት ሳይጨምር ከመላክ በዘለለ እሴት የተጨመረበትን ምርትም በመላክ ለሃገር የውጭ ምንዛሬ ግኝት እድገት የበኩላቸውን አስተዋፅኦ ለማበርከት ቆርጠው ተነሱ።
ይህንን ሕልማቸውን ለማሳካት ያስችላቸው ዘንድም በኢትዮጵያ የመጀመሪያ የተባለውን የሰሊጥ ማቀነባበሪያ ፋብሪካ ከአሜሪካ ድርጅት ጋር በመተባበር ከፈቱ። እናም የኢትዮጵያን የሰሊጥ ቂቤ (ታሂኒ) በአውሮፓ መስፈርት (ስታንዳርድ) መሰረት በጥራት በማምረት ወደ ተለያዩ የዓለም ሃገራት መላክ ጀመሩ።
ጃፓን ቀዳሚዋ የድርጅታቸው ምርት መዳረሻ ሃገር መሆንዋን ጠቅሰው፣ በሌሎችም የዓለም ሃገራት ምርቱ ከፍተኛ ተቀባይነት ማግኘቱን ያስረዳሉ። ይሁንና በተለይ ባለፉት ዓመታት በሰሜን ኢትዮጵያ አካባቢ በተከሰተው አለመረጋጋት ምክንያት የሰሊጥ ምርትና ምርታማነት መቀዛቀዝ ውስጥ ገባ፤ ሁመራ የሚገኘው ፋብሪካቸውም ተዘጋ። በዚህ የተነሳም የሰሊጥ ቂቤ (እሴት የተጨመረበት) ምርቱን በገበያው ፍላጎት መጠን ለማምረት አለመቻሉን ያስረዳሉ።
ይህን ሀገራዊ ነባራዊ ሁኔታ ተከትሎ በድርጅታቸው ላይ የተፈጠረው ጉዳት ብዙም አላስደነገጣቸውም። ከዚህ ይልቅ የድርጅታቸው ገቢ በእጅጉ እንዳይቀንስ ለማድረግ ይበልጥ ማውጣት ማውረድ ጀመሩ፤ የተለያዩ ስትራቴጂዎችን ነድፈው በመስራትም ድርጅታቸውን ከኪሳራ መታደጋቸውን ያመለክታሉ። በተለይ እንደ ሚዲያ ማቀዝቀዣ ያሉ የኤሌክትሮኒክስ እቃዎችን ከሚመረቱባቸው ሀገሮች በቀጥታ በማስመጣትና ለሃገር ውስጥ ገበያ የሚያከፋፍል እህት ድርጅት በመክፈት የድርጅታቸውን አቅም ማጎልበት መቻላቸውን ይጠቁማሉ።
‹‹የድርጅታችን ዋና ስራ የኢትዮጵያ የግብርና ምርቶች በዓለም ገበያ ተወዳዳሪ እንዲሆኑ በማድረግ ለሀገር ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ማስገኘት ነው›› የሚሉት ዶክተር ሙሉጌታ፤ በአሁኑ ወቅት ድርጅታቸው ሁመራ እና ወለጋ የተባሉ ምርጥ የሰሊጥ ዝርያዎችን እንዲሁም የተፈተገውን ሰሊጥ እየላከ መሆኑን አስታውቀዋል።
እነዚህ ምርቶች ጃፓን ላይ ትልቅ ገበያ እንዳላቸው ጠቅሰው፣ እንደሃገር ለጃፓን ከሚሸጠው ሰባት ሺ ሜትሪክ ቶን ውስጥ ትልቁን ድርሻ የሚይዘው የእሳቸው ድርጅት የሚልከው ሰሊጥ መሆኑን ይጠቅሳሉ። ‹‹የእኛ ድርጅት እስከ 15 ሺ ቶን ሰሊጥ የመላክ አቅም ነበረው፤ በዓለም ገበያ ያለው ተቀባይነትም ከፍተኛ ነበር። ሆኖም በተለያዩ ሃገራዊ ችግሮች ምክንያት የምንልከው መጠን ቀንሷል። ባለፋት ዓመታትም የላክነው ሶስት ሺ ሜትሪክ ቶን ሰሊጥ ብቻ ነው›› ሲሉ ያብራራሉ።
በመሆኑም ድርጅታቸው በተያዘው ዓመት ወደ ውጭ የሚልከውን የሰሊጥ ምርት መጠን በከፍተኛ ደረጃ ለማሳደግ እርሳቸውም ሆኑ መላው የድርጅቱ ባልደረቦች ትኩረት ሰጥተው እየሰሩ መሆናቸውን ጠቁመዋል። ‹‹ ለዚህም ይረዳን ዘንድ አሁን ላይ በአዲስ አበባ የራሳችንን ዘመናዊ ማበጠሪያ ቤት ገንብተን ጨርሰናል። ስለዚህ የነበረብን የማበጠሪያ ቤት ችግር ስለተፈታ እንዲሁም ገበያው እጃችን ላይ ስላለ በያዝነው ዓመት ወደ ቀድሞ አቅማችን እንመለሳለን ብለን እናስባለን›› ሲሉም ያስረዳሉ።
ዶክተር ሙሉጌታ ድርጅቱን ከአባታቸው ሲረከቡ ስምንት ያህል ሰራተኞች ብቻ ነበሩት፤ እሳቸው ግን ከመላው ቤተሰባቸው ጋር በመሆን ተጨማሪ ድርጅቶችን ከፍተዋል። እነዚህ ድርጅቶችም የሰሊጥ ቂቤ ማምረቻ ኢንዱስትሪ (ታሂኒ)፣ የቡና ማበጠሪያ፣ ሪል ስቴት እና የኤሌክትሮኒስክ አስመጪ ድርጅቶች ናቸው። በእነዚህ ድርጅቶችም የቋሚና የጊዜያዊ ሰራተኞችን ብዛት ወደ 500 ማሳደግ መቻሉን ያመላክታሉ። የድርጅቱን የተመዘገበ ካፒታል ከ10 ሚሊዮን ወደ 400 ሚሊዮን ብር ማድረስ መቻሉን ጠቅሰው፣ በዚህ ስራም የእሳቸው ሚና የጎላ ነው ብለው እንደሚያስቡ ተናግረዋል።
ድርጅታቸው ማህበራዊ ኃላፊነትን በመወጣት በኩልም እየሰራ መሆኑን ይጠቅሳሉ። ማንኛውም የግል ድርጅትም ሆነ ዜጋ ያስተማረውን ማህበረሰብ እና ሃገር መደገፍ አለበት ብለው በጽኑ እንደሚያምኑ አስታውቀው፣ ድርጅታቸው ለበርካታ ሥራ አጥ ወጣቶች የስራ እድል ከመፍጠር በዘለለ በአካባቢው ያሉ ዝቅተኛ ገቢ ያላቸውን የተለያዩ ነዋሪዎችን በመርዳት ማህበራዊ ኃላፊነቱን እየተወጣ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
በተለይም በንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር አስተባባሪነት ለአቅመ ደካሞችና አነስተኛ ገቢ ላላቸው የሕብረተሰብ ክፍሎች በተከናወነው የቤት ግንባታ መርሃ-ግብር ድርጅታቸው ከአንድ ሚሊዮን ብር በላይ አስተዋፅኦ ማድረጉን ጠቅሰዋል። ከዚያም ባሻገር ስራውን የሚመራው ኮሚቴ አካል ሆነው ግንባታው እውን እንዲሆንም ያደረጉትም አስተዋጽኦ ከፍተኛ ስለመሆኑንም አስታውቀዋል።
በሌላ በኩልም የሰሊጥ ምርትና ምርታማነት እንዲጎለብት፤ ሀገሪቱ ወደ ተለያዩ ሀገራት የምትልከውም ምርት በጥራትም ሆነ በመጠን እንዲያድግ ድርጅታቸው ቋሚ የሆነ የድጋፍ መርሃግብር እንዳለው ዶክተር ሙሉጌታ ይናገራሉ። በዋናነትም በኮንትራት እርሻ ለተሰማሩ የተወሰኑ ገበሬዎች ድጋፍ እየሰጠ መሆኑን ጠቅሰው፣ ‹‹የፋይናንስም ሆነ የምርት ግብዓት በማቅረብ አምራቾቹ ምርታማነታቸውን እንዲያሳድጉ፤ ወደ ውጭ የሚላከውም ምርጥ ጥራቱ የተጠበቀ እንዲሆን ለማድረግ የበኩላችንን ጥረት እያደረግን ነው›› ሲሉ ተናግረዋል።
ከዚህም ባሻገር ዘርፉን በመሰረታዊነት ማሳደግ ይገባል የሚል እምነት ያላቸው ዶክተር ሙሉጌታ፤ የኢትዮጵያ ሰሊጥ በዓለም ገበያ ተፈላጊ፣ የጥራትና የዋጋ መለኪያ ሆኖ እንዲቀጥል ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር ተቀናጅተው በመስራት ላይ እንደሚገኙም ይገልጻሉ። በዋናነትም እርሳቸው የቦርድ አባል በሆኑበት የኢትዮጵያ ጥራጥሬና ቅባት እህሎች ማህበር አማካኝነት ከምርምር ተቋማት እንዲሁም ከግብርና ኤክስቴንሽን ሰራተኞች ጋር በመሆን ተደራሽነቱን ለማስፋት በዝግጅት ላይ መሆናቸውን ገልጸዋል። ለዚህም ይረዳ ዘንዳ ከንግድ ሚኒስቴር እና ከሌሎችም መንግስታዊ ድርጅቶች ጋር ጠንካራ ግንኙነት በመፍጠር ለዘርፉ መጎልበት የበኩላቸውን አስተዋፅኦ በማበርከት ላይ መሆናቸውን አስረድተዋል።
ከሁሉም በላይ ኢትዮጵያ ጥሬ ሰሊጥ ወይም እሴት ያልተጨመረበት ሰሊጥ ወደ ውጭ መላክ በማቆም እና እሴት ጨምራ በመላክ አሁን ከምታገኘው በላቀ የውጭ ምንዛሬ እንድታገኝ ማድረግ ይገባል የሚል ፅኑ እምነት አላቸው። በዚህ ረገድም በእሳቸው ፈርቀዳጅነት የተከፈተውን የሰሊጥ ቂቤ ማምረቻ ኢንዱስትሪን ለማስፋፋት እቅድ አላቸው። በተለይም አቅሙን በማጎልበት የሚያመርተውን ምርት በማስፋት የመዳረሻ ሀገራትን ቁጥር ለመጨመር እቅደው እየሰሩ መሆናቸው ይጠቁማሉ።
መንግስት የኢትዮጵያን ምርት ወደ ተለያዩ ሃገራት ለሚልኩም ሆነ በኢንዱስትሪ ልማት ለተሰማሩ ባለሃብቶች ከፍተኛ ድጋፍ እያደረገ መሆኑንም መስክረው፣ ‹‹በተለይም ላኪዎች የሚያጋጥሟቸው ችግሮች እንዲፈቱ ከመንግስት ጋር በቅርበት ሆነን እየሰራን ነው›› ሲሉም አስታውቀዋል።
ዶክተር ሙሉጌታ ድርጅታቸው አሁን ከጀመረው የሰሊጥ ቂቤ (ታሂኒ) ምርት በተጨማሪ ወደፊት በሌሎችንም ምርቶች እሴት ጨምሮ በማምረት ወደተለያዩ ሃገራት የመላክ እቅድ አለው። ለዚህም ይረዳው ዘንድ በተለያዩ ዓለም አቀፍ አወደ ርዕዮች ላይ በመሳተፍ ተሞክሮ በመውሰድ፤ የኢትዮጵያን ምርቶች በማስተዋወቅ የደንበኞችን መጠን ለማሳደግ ከወዲሁ አልመው እየሰሩ ስለመሆናቸውም ተናግረዋል።
‹‹በአሁኑ ወቅት የታሂኒ ምርታችን አነስተኛ ነው፤ በገበያ ላይ ያለውን ፍላጎት የማሟላት ስራ ከሰራን በኋላ ሌላ ማስፋፊያ ስራ መስራት እንፈልጋለን፤ በዚህም 140 ለሚደርሱ ዜጎች ተጨማሪ የስራ እድል እንፈጥራለን ብለን እናስባለን›› የሚሉት ዶክተር ሙሉጌታ፤ ከዚህም ባሻገር ኢትዮጵያ ወደ ሃገር ውስጥ የምታስገባቸውን ምርቶች በሃገር ውስጥ እንዲመረቱ ለማድረግ ፕሮጀክት ቀርፀው እየሰሩ መሆናቸውንም ያመለክታሉ።
‹‹እዚሁ ሃገር ቢያንስ በከፊል ያለቁ እቃዎችን በራሳችን የሰው ኃይል ገጣጥመን በማምረት ሀገሪቱ እነዚህን ምርቶች ለማስገባት የምታወጣውን የውጭ ምንዛሬ ለማስቀረት እቅድ ይዘን እየሰራን ነው›› በማለትም ያብራራሉ። በዚህም ትልቅ ኢንቨስትመንት ከ400 እስከ 500 የሚደርሱ ሰዎችን የስራ እድል ተጠቃሚ የማድረግ ፍላጎቱ አላቸው። በአሁኑ ወቅት እነዚህን ትላልቅ የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች እውን ለማድረግ ወደ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ለመግባት ከመንግስት ጋር ድርድር በማድረግ ላይ መሆናቸወን ገልጸዋል።
ማህሌት አብዱል
አዲስ ዘመን ህዳር 21/2017 ዓ.ም