የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ መንግሥት፣ በታሪካዊ ጠላቶቻችንና በቡችሎቻቸው በየአቅጣጫው እንደ ቆዳ ተወጥሮ እያለ፤ የኢትዮጵያ ታላቁ የሕዳሴ ግድብ በሙስና፣ በብልሹ አሠራርና በኮንትራት አስተዳደርና አመራር ድክመት ተደቅኖበት ከነበረ የለየለት ክሽፈት ታድጎ ኃይል ማመንጨት መጀመሩ እና ለ3ኛ ዙር ውኃ ሙሊት ማብቃቱ፤ የሁለተኛው ተርባይን ፍተሻም እያገባደደ መሆኑ እጅግ የሚደነቅ አፈጻጸም ከመሆኑ ባሻገር ከክሽፈት ወደ ከፍ ያለ ልዕልና እምርታ የተደረገበት ሽግግር ነው ማለት ይቻላል። ከዚህ ጎን ለጎን የአገራችንን ጨምሮ የዓለም ኢኮኖሚ በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ጫና ስር ወድቆ እያለ ሜጋ ፕሮጀክቶች ሳይስተጓጎሉ ማስቀጠል መቻሉ በልኩ እውቅና ሊቸረው ይገባል። ለመጀመሪያ ጊዜ 375 ሜጋ ዋት ኃይል ማመንጨት ከጀመረ በርካታ ወራት ያለፉት የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሰሞኑን ደግሞ የሦስተኛ ዙር ውሃ ሙሌት ወደ መጠናቀቁ ነው። ሙሌቱ በተጀመረበት 2012 ዓ.ም የግድቡ ቁመት (ከባህር ወለል በላይ) 565 ሜትር ሆኖ 4ነጥብ9 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ውኃ ይዟል። በቀጣዩ ዓመት የግድቡ ቁመት(ከባህር ወለል በላይ) 595 ሜትር ደርሶ 13ነጥብ5 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ውኃ ተያዘ። በዚህም ግድቡ የያዘው የውኃ መጠን 18.4 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ደረሰ። በሦስተኛው ዓመት ላይ የግድቡን ቁመት(ከባህር ወለል በላይ) 608 ሜትር ከፍታ ላይ በማድረስ 10ነጥብ5 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ውኃ የመሙላት እና አጠቃላዩን የውኃ መጠን 28ነጥብ9 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር የማድረስ ግብ ተጥሎ ሌት ተቀን የተሠራው ሥራ ግድቡን ወደ አዲስ ምዕራፍ አሸጋግሮታል።
ከፍ ብዬ ለመግለጽ እንደሞከርሁት በክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩ አመራር ግድቡ ገጥመውት የነበሩ ስር የሰደዱ ብልሹ አሠራሮች፣ ሙስናና ደካማ የኮንትራት አስተዳደር ተለይተው የእርምት እርምጃዎች ባይወሰዱ ኖሮ ታላቁን የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ ከክሽፈትና ከለየለት ውድቀት መታደግ ስለማይቻል ኢትዮጵያውያን ለዚች ታሪካዊ ቀን አይበቁም ነበር። በመጪው ትውልድ ዘንድም ተወቃሽ ይሆኑ ነበር። በሴራ ፖለቲካ፣ በተላላኪውና በባንዳው በጣት በሚቆጠር የትህነግ ገዢ ቡድንና ተባባሪዎች ደባ በየዕለቱ ቅርጹንና ይዘቱ እየቀያየረ በሚቀፈቀፍ ቀውስ ውስጥ ኢትዮጵያውያን ተስፋ የሚያሰንቅ መልካም ዜና በናፈቃቸው በዚህ ቀውጢ ወቅት የ3ኛ ዙር ግድቡን ውኃ የማስያዝ ጥረት በስኬት የመጠናቀቁን ብስራት ለመስማት ከጫፍ መድረስ ምንኛ ተስፋን ያለመልማል።
በብዙ እየተፈተነ ላለው ዜጋም ትልቁን የኢትዮጵያን ስዕል እየተመለከተ ብልፅግናዋን እውን ለማድረግ አቅም ይሆነዋል፡፡ ቅኝ ካለመገዛት ጋር ብቻ ተያይዞ የነበረውን ነፃነትና ሉዓላዊነት በኢኮኖሚያዊ ነፃነትና ብልፅግና ለመድገምም መስፈንጠሪያ ሰሌዳ (ስፕሪንግቦርድ) በመሆን በድህነትና በተመፅዋችነት አንገታቸውን ደፍተው የነበሩ ዜጎች አንገታቸውን ቀና አድርገው በኩራት እንዲራመዱ የሚያደርግ ብሔራዊ (ፍላግሺፕ) ፕሮጀክት ነው። ነጋድራስ ገብረሕይወት ባይከዳኝ እንዳሉት በድህነትና በኋላ ቀርነት የሚማቅቅ ሕዝብ የተሟላ ሉዓላዊት ሊኖረው አይችልምና፡፡ ስንዴ እየለመኑ፣ እየተመጸወቱ ሉዓላዊነቷን ያላስደፈረች፤ በነፃነት ታፍራና ተከብራ የኖረች አገር ብሎ መመጻደቅን ምሉዕ አያደርገውም፡፡ ከድህነትና ከኋላቀርነት ለመውጣት ከሚያበረክተው የላቀ አስተዋጽኦ ባሻገር አገራችን በቀጣናው የሚኖራትን ጂኦፖለቲካዊ ስፍራ በእጅጉ እየለወጠው ይገኛል። ኢትዮጵያ ኤርትራንና ቀይ ባህርን ካጣች በኋላ በቀጣናው የነበራት ስፍራ ፍጹም እንደተቀየረው ሁሉ፤ የኢትዮጵያ ታላቁ የሕዳሴ ግድብም በቀጣናው የሚኖራትን ጂኦፖለቲካዊ ስፍራ በእጅጉ ከፍ አድርጎታል።
የአረቡ ዓለም የነዳጅ ባለቤት መሆኑ ከተረጋገጠ እኤአ በ1948 ዓ.ም እሥራኤል የአይሁዶች መንግሥት ሆና ከቆመች፣ ከ1993 ዓ.ም የመስከረም 1 ቀን የሽብር ጥቃት በኋላ የአሜሪካ የምዕራባውያንና የዓለምአቀፍ ተቋማት የውጭ ግንኙነትና ዲፕሎማሲ ማጠንጠኛ ነዳጅ፣ የእሥራኤል ደህንነት እና የጸረ ሽብር ዘመቻ ሆነ፡፡ ለእነዚህ የውጭ ግንኙነት ፖሊሲዎች እና ስትራቴጂዎች ተግባራዊነት ዳግም ከአረቡ ዓለም ግብፅ ቀዳሚዋ ስትራቴጂካዊ አጋር ሆና ተመርጣለች። ግብፅን ተመራጭ ያደረጋት ለምዕራባውያን የጡት ልጅ እሥራኤል ጎረቤት መሆኗ፤ መልክዓ ምድራዊ አቀማመጧ በተለይ የስዊዝ ቦይ ባለቤት መሆኗ፤ የእስላማዊ ትምህርት ማዕከል እና የአረብ ብሔርተኝነት አቀንቃኝ መሆኗ፤ ዜጎቿ ከሌላው የአረብ ዓለም ጋር ሲነጻጸር በዓለማዊም ሆነ በእስላማዊ ትምህርት የገፉ በመሆናቸው በምዕራባውያንም ሆነ በእስላማዊው ዓለም ዘንድ ሞገስ አግኝታለች፡፡ ይህን ሞገሷን የአረቡን ዓለም ጨምሮ የአረብ ሊግን እንዳሻት ለማሽከርከር ትጠቀምበታለች፡፡
በልዩነትና በክፍፍል የሚንጠራወዘው የአረቡ ዓለም ግብፅ ከፍ ብላ እንድትታይ ረድቷታል፡፡ ይህን መከፋፈል እሥራኤልን ጨምሮ አሜሪካውያን ሆኑ ምዕራባውያን ይፋ ባያወጡትም የሚደግፉት ስለሆነ ግብፅ ሽብልቅ ሆና እንድታገለግል አሞሌ እያላሱ (ብድርና እርዳታ እየሰጡ) በአናቱ የጦር መሣሪያ እያስታጠቁና ወታደራዊ ስልጠና እየሰጡ ይንከባከቧታል፡፡ አሜሪካ ብቻ በየአመቱ በቢሊዮኖች የሚገመት የጦር መሣሪያ እርዳታ፣ ወታደራዊ ድጋፍና የልማት ድጋፍ ታደርግላታለች፡፡
ግብፅ በአጸፋው ይህን ውለታ ከግምት ያስገባ እና እኤአ በ1979 በአንዋር ሳዳትና በእሥራኤል መካከል የተፈረመውን የሰላም ስምምነት መሠረት ያደረገ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ቀርጻለች፡፡ የአገሪቱን ኢኮኖሚ፣ ደህንነትና ፖለቲካ በመዳፉ የጠቀለለው የግብፅ ጦርና ደህንነት የውጭ ጉዳይ ፖሊሲን ተግባራዊነት ያረጋግጣል፤ በዓይነ ቁራኛም ይከታተላል፡፡ ከአረቡ አብዮት በኋላ በምርጫ የፈርኦኖችን በትረ ስልጣን ጨብጠው የነበሩ የመጀመሪያው የእስላም ወንድማማቾቹ አባል ፕሬዚዳንት ሞሐመድ ሙርሲ እንኳ የድርጅታቸውንም ሆነ አክራሪ እስላሞች ግፊት ተቋቁመው የግብፅና እሥራኤልን የሰላም ስምምነት ማክበር ችለዋል። መጀመሪያ በመፈንቅለ መንግሥት በኋላ በምርጫ ወደ መንበሩ የመጡት ፕሬዚዳንት አብዱልፈታህ አልሲሲም ከሳዳት፣ ከሙባረክና ከሙርሲ በላይ የሰላም ስምምነቱን እያስፈጸሙ ነው። የእሥራኤል ጉዳይ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲያቸው ቀኖና ነው ማለት ይቻላል፡፡ ከእሥራኤል ጀርባ ደግሞ አሜሪካ አለች፡፡ ግብፅ ናይል የህልውናዬ ጉዳይ ነው ብላ በሕገ መንግሥቷ ብታካትተውም በውስጠ ታዋቂ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲዋ የማዕዘን ራስ ቢሆንም በግላጭ ትኩረቱ እሥራኤል፣ ፍልስጤምና አሜሪካ ላይ ነው፡፡
ግብፅ ዓባይን ከምንጩ ለመቆጣጠር፣ አገራችንን ቅኝ ለመግዛት እና ጠንካራ ሉዓላዊ አገር ሆና እንዳትወጣና ይህ ቀን (ዓባይ የተገደበበት ቀን) እውን እንዳይሆን ከ11 ጊዜ በላይ ለወረራ መጥታብናለች፡፡ በስውር ደግሞ ምን አልባት ለሺህ ወይም ለሚሊዮን አመታት አሲራለች፡፡ በተለይ ከ20ኛው ክ/ዘ ወዲህ ደግሞ በእነ ሶማሊያ፣ ሱዳን፣ ጀብሀ፣ ሻዕቢያ፣ ትህነግ ፣ ኦነግና የኦጋዴን ነፃ አውጭ በመጠቀም የውክልና (proxy) ጦርነት በማካሄድ አገራችንን ስታዳክም ኖራለች። አሁንም አልሻባብን ፣ ሕወሓትን ፣ ኦነገ ሸኔንና የተለያዩ ታጣቂዎችን ተጠቅማ አገራችንን ለማተራመስ ሌት ተቀን እየማሰነች ነው። በምሥራቁ የአገራችን ክፍል አልሻባብ ድንበር ተሻግሮ የከፈተብን ጥቃት በግብጽ ቡራኬና ስፖንሰር አድራጊነት መሆኑ የአደባባይ ምስጢር ነው። የቀደመ እኩይ አላማዋ ከሞላ ጎደል በመሳካቱ የቤት ሥራዋን በማጠናቀቋ ዝቅ አድርጋ ስታየን ኖራለች፡፡ ከታሪካዊዋ ሐምሌ 15 ቀን 2012 ዓ.ም ጀምሮ ግን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ሁኔታዎች ተቀይረዋል፡፡ ይቺ ታሪካዊ ቀን የሕዳሴው የመጀመሪያ ዙር ሙሊት የተካሄደባት መሆኑን ልብ ይሏል። በሴራና በደባ በቀጣናውም ሆነ በዓለምአቀፍ መድረክ ያሳጣችን ጂኦ ፖለቲካዊ እና ስትራቴጂካዊ ስፍራ ከ30 ዓመታት በኋላ መልሰን ተረክበናል፡፡ ምርኳችንም ተመልሷል፡፡
የቀጣናው ጂኦ ፖለቲካዊ አሰላለፍ በታላቁ የህዳሴ ግድብ እንደ አዲስ ተበይኗል የምለው ለዚህ ነው። ከዚህ በኋላ የአገራችን ስትራቴጂካዊ ጠቀሜታና ጂኦ ፖለቲካዊ ስፍራ ከ1983 ዓ.ም በፊት ወደነበረው ከመመለሱ ባሻገር፤ ከግብፅ የሚተናነስ አይደለም። ታዋቂው የግሪክ የታሪክ ሰው ሔሮዶተስ እንዳለው ግብፅ የአባይ (የኢትዮጵያ) ስጦታ ሆነች፡፡ በተላላኪዋና በአስካሪሷ ትህነግ የተነጠቅነውን አንድነት ደግሞ በአጭር ጊዜ መልሰን ወደ ቀደመው ገናና ከፍታችን በኩራት እንመለሳለን፡፡
ከፍ ብሎ ለመግለጽ እንደተሞከረው በለውጡ ማግስት የኢትዮጵያ ታላቁ የሕዳሴ ግድብ ገጥሞት ከነበር ውስብስበ ሙስናና ብልሹ አሠራር ተላቆ ከክሽፈት መዳኑ ሲረጋገጥ፤ ግብጽ ያለ የሌለ ኃይሏን አቀናጅታና አሟጣ አገራችን ላይ የዲፕሎማሲ፣ የሚዲያና እንደ ሕወሓትና ኦነግ ሸኔ ያሉ ቡችሎቿን በመጠቀም የእርስ በርስ ግጭት ለመቀስቀስና አገራችንን ለማተራመስ ያልፈነቀለችው ድንጋይ የለም። ከሕወሓት የሰሜን ዕዝ ጥቃትና ከቀሰቀሰው ጦርነት፤ ከሸኔና ከጀሌዎቹ የንጹሐን ጭፍጨፋ፤ ከጅግጅጋው ጭፍጨፋ፤ ከኦሮሚያና ከሱማሌ ግጭት፤ ከአፋርና ከኢሳ ግጭት፤ በየዩኒቨርሲቲዎች ይቀሰቀሱ ከነበሩ ግጭቶች፤ ከድምጻዊ ሀጫሉ ግድያና እሱን ተከትሎ ከተፈጸመው ግፍና ሰቆቃ፤ ከኢኮኖሚ አሻጥሩ፤ ከምዕራባውያን የተቀናጀና የተናበበ ጸረ ኢትዮጵያ ዘመቻ፤ ከእነ አምነስቲና ሒውማን ራይትስ ዋች የስማ በለው ሪፖርት፤ ከሀሰተኛና መርዘኛ መረጃዎች፤ ወዘተረፈ ጀርባ የግብጽና የተላላኪ ባንዳዎች እጅ አለበት።
ሰሞኑን በተላላኪዋ አልሻባብ በሱማሌ ክልል በተቃጣው ተደጋጋሚ ትንኮሳም ሆነ በሌላው ተላላኪዋ ሸኔ በምዕራብና ቄለም ወለጋ እንዲሁም በጋምቤላ በተፈጸሙ ግፎችም እጇ አለበት። ከሳውዲ አረቢያ የዜጎቻችን ግፍ ጀርባም የግብጽ ረጅም እጅ አለበት። በዚህ አራት አመት እንደአገርና ሕዝብ የገጠመን ፈተና በታሪክ ታይቶም ሆነ ተሰምቶ አያውቅም። በአንድም በሌላ በኩል ኅልቆ መሳፍርት የሌለው ሰቆቃ የሁሉንም ቤት አንኳኩቷል። ሁሉም ዋጋ ከፍሏል። ይሄን ሁሉ ዋጋ እየከፈልን ያለነው አባቶቻችን ያቆዩንን ነፃነትና ሉዓላዊነት ለማስከበርና ለማስቀጠል ነው። የተፈጥሮ ሀብታችንን አልምቶ ለመጠቀም ነው። በድህነትና በኋላቀርነት እየማቀቁ ነፃነትና ሉዓላዊነት ሙሉዕ ስለማይሆን ነው ይሄን ሁሉ መከራ የተቀበልነው። ወደፊትም የትኛውንም ፈተና ለመጋፈጥ ዝግጁ የሆነው። በአንድ መጣጥፌ የሕዳሴው ግድብ እየሆንለት ያለው ነገር ሁሉ ይገባዋል (worth it) የምለው ለዚህ ነው ።
እንደጀመርን እንጨርሰዋለን !
በቁምላቸው አበበ ይማም (ሞሼ ዳያን)
fenote1971@gmail.com
አዲስ ዘመን ሐምሌ 28 ቀን 2014 ዓ.ም