በመንግሥት መስሪያ ቤቶች ውስጥ የሚሠሩ ማናቸውም ሠራተኞች ኅብረተሰቡን የማገልገል ግዴታ አለባቸው። በተጨማሪም መንግሥትና ሕዝብን የሚያገናኙ ድልድዮች ናቸው። ይህን ሁኔታ ተረድቶ ኃላፊነቱን የሚወጣ ሠራተኛ ምን ያክሉ ነው ቢባል መልሱ እንደየአከባቢው የተለያየ መሆኑ እሙን ነው። በአሁኑ ወቅት በመንግሥት መስሪያ ቤቶች ቢኬድ ተገልጋይ ሲንገላታና አስታዋሽ አጥቶ በየጥጋጥጉ መመልከት የተለመደ ነው። ለምን ቢባል አገልጋይ ሠራተኛ በማጣቱ መሆኑን ሀቅ ነው።
ወደ ዋናው ጉዳይ ከመገባቱ በፊት ግን የመንግሥት ሠራተኛ ማለት ምን ማለት ነው? የሚለውን እንመልከት። በፌዴራል የመንግሥት ሠራተኞች አዋጅ ቁጥር 515/99 አንቀጽ 2(1) ስር እንደተደነገገው የመንግሥት ሠራተኛ ማለት በፌዴራል መንግሥት መስሪያ ቤት ውስጥ በቋሚነት ተቀጥሮ የሚሠራ ሰው ነው። ከዚህ ትርጉም የምንረዳው አንድ ሰው የመንግሥት ሠራተኛ ነው የሚባለው በመንግሥት መስሪያ ቤት ማለትም ራሱን ችሎ በአዋጅ ወይም በደንብ የተቋቋመ እና ሙሉ ለሙሉ ወይም በከፊል ከመንግሥት በሚመደብለት በጀት የሚተዳደር ሆኖ በሚኒስቴሮች ምክር ቤት በሚወጣው የመንግሥት መስሪያ ቤቶች ዝርዝር ውስጥ የተካተተ የፌዴራል የመንግሥት መስሪያ ቤት ሲሠራ ነው። በተጨማሪ በየክልሉ ባሉ የመንግሥት መስሪያ ቤት ውስጥ ተቀጥረው የሚሠሩ ሠራተኞችም የመንግሥት ሠራተኛ ይባላሉ።
ታዲያ በፌዴራልም ሆነ በክልል የመንግሥት ሥራ አስፈፃሚዎችና ሠራተኞች ዋነኛ አገልግሎት የሚሰጡት ለሕዝቡ ነው። ሠራተኞቹ ሕዝቡ የሚፈልገውን አገልግሎት ከመስጠት ባለፈ የኅብረተሰቡን ችግር የሚቀርፉ ሀሳቦችን የማመንጨትና የመተግበር ግዴታ ተጥሎባቸዋል። ለምሳሌ ያክል በአንድ ወረዳ የሚኖር ግለሰብ ከመኖሪያ ቤት፣ ከመፀዳጃ እና ከማብሰያ ቤት ጋር የተያያዙ ጉዳዮች ሲኖሩት የሚኖርበት ወረዳ የሚመለከተው ሠራተኛ በአግባቡ ጥያቄውን ተመልክቶ የመፍታት ግዴታ አለበት። በሌላ በኩል ደግሞ ማንኛውም ሰው በሚኖርበት አካባቢ ሰላም የማግኘትና ሠርቶ የመግባት መብቱ እንዲጠበቅ በመንግሥት መዋቅር ውስጥ ያሉ የፀጥታ አካላት ኃላፊነት አለባቸው።
ሆኖም እነዚህ ነገሮች በሚፈለገው ልክ በተግባር አይታዩም። ለምን ቢባል የተሰጠውን ኃላፊነት የሚወጣ ሠራተኛ እየጠፋ በመምጣቱ ነው። በተለይ የሕዝብ አገልግሎት በሚበዛባቸው አካባቢዎች የሚገኙ ሠራተኞች ሕዝቡን ለማልገል ሳይሆን በወር የሚከፈላቸው ገንዘብ እንዳይቆረጥ ቢሮ የሚገቡ የሚመስሉም ተበራክተዋል። በዚህም ለሕዝቡ አገልግሎት ለመስጠት ‹‹ጉቦ›› እንደ ግዴታ እየተቆጠረ ይገኛል። ገንዘብ ያልሰጠ ተገልጋይ መብቱን ማግኘት እንደማይችልም በአደባባይ እስከመታወጅ ደርሷል። ለዚህ ማሳያ ደግሞ የነዋሪነት መታወቂያ ለማደስም ሆነ ለማውጣት ያለውን ውጣ ውረድ መመልከት በቂ ነው። አንድ ነዋሪ ከተሰጡት መብቶች አንዱ የነዋሪነት መታውቂያ ማግኘት ነው። ነገር ግን ይሄን መብት ለማግኘት የግድ ገንዘብ መክፈል ይጠበቅበታል። እዚህ ላይ መስተዋል ያለበት ጉዳይ መታወቂያውን ለማግኘት የሚከፈለውን የአገልግሎት ክፍያ አያጠቃልልም።
ሌላው የምንመለከተው ከከተማ እስከ ወረዳ የሚገኙ የመንግሥት ሠራተኞች ቢሮ ውስጥ ወንበር ከማሞቅ በዘለለ ምን እየሠሩ እንደሚገኙ የሚከታተልና የሚቆጣጠረው አካል ማን እንደሆነ አለመለየቱ ነው። በየመስሪያቤቶች ቢኬድ ቁጥሩ የማይናቅ ሠራተኛ ለሥራ ተቀምጦ ኢንተርኔት ሲጠቀም፣ በቡድን ሲወራ ወይም ከቢሮ ውጪ በረንዳ ላይ ተሰብስቦ ነው የሚታየው። በነዚህ ወቅት ተገልጋይ ሲመጣ ትኩረት ሰጥቶ የሚያዳምጠውም፤ ችግሩን የሚፈታለት ሰው አያገኝም። ሠራተኛው የሚከፈለኝ ደመወዝ አነስተኛ ነው በሚል ተገልጋይ ማጉላላቱን እንደ መፍትሄ ይዞታል። የሚያስገርመው ደግሞ ተገልጋይ ሆኖ የሚመጣው ሰው በተገላቢጦሽ በሚሠራበት መስሪያ ቤት ተገልጋይ የሚያጉላላ መሆኑን ሲታይ ነው። አንድ ሰው በመንግሥት መስሪያ ቤት ሲቀጠር ለቦታው የሚከፈለውን ደመወዝ ተቀብሎ ነው። የሚከፈለው አነሰም በዛም የተቀመጠበትን ኃላፊነት የመወጣት ግዴታ አለበት።
ሆኖም ሁሉም ሰው አማራሪ፣ ተቺ እና መፍትሄ ከሰው የሚጠበቅ በመሆኑ መሠረታዊ ለውጥ ማምጣት አልተቻለም። በመንግሥት መስሪያቤት የሚሠራ ሰው እራሱ መንግሥት መሆኑን ስለማይረዳ መሥራት የሚችለውን ወይም መፍትሄ መስጠት የሚገባውን ነገር ሌላ አካል እንዲሠራለት ይጠብቃል።
የሲቪል ሰርቪስ አስተዳደርም ሠራተኛን በአግባቡ ይዞ ከማሠራት ይልቅ የሰዓት ፊርማ ላይ ያተኮረ በመሆኑ ሠራተኛው ለፊርማ ሲል እንጂ ሥራውን ለመሥራት ወደ ቢሮ እንዲገባ እያደረገው አይመስልም። ከዚህ በዘለለም ሠራተኛው ለመንግሥት ሥራ ከመልፋት ይልቅ ከቢሮው ወይም ከወንበሩ አለመጥፋትን እንደ ልማድ እየወሰደው ይመስላል። በዚህ የተሳሳተ እሳቤም በመንግሥት መስሪያ ቤት ውስጥ ከሥራ ይልቅ የሰዓት ፊርማ ትኩረት ተሰጥቶታል። ኅብረተሰቡም የትኛውንም አገልግሎት ለማግኘት መመላለሱን እንደ በጎ ቆጥሮ እየተንቀሳቀሰ ነው።
በዚህ ረገድ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመፍታት መንግሥት በተደጋጋሚ ቃል እየገባ ወደ ትግበራ ቢገባም የተለወጠ ሲቪል ሰርቫንት ማግኘት ባለመቻሉ የሕዝቡን ጥያቄ መመለስ አዳጋች እንደሆነበት ይታያል። ከዚህም ባለፈ ስታንዳርዱን የጠበቀ የአገልግሎት አሰጣጥ ለመፍጠር የመጡ ጥናቶች ለውጥ ሳያመጡ እየተረሱ ይገኛሉ። ሠራተኞችን የመመዘን ሥራውም ከሥራ ይልቅ ግለሰብ ጥላቻ ላይ ያተኮሩ በመሆናቸው ለውጥ አምጪ ሠራተኛ ከመፍጠር ይልቅ የመበቃቀያ መንገድ ሆነው እያገለገሉ ናቸው።
በየመስሪያቤቱ የሚገኙ ሠራተኞች የሕዝቡን ችግር የሚፈታ መፍትሄ ከመስጠት ከተገልጋዩ የሚመጣላቸውን ጥያቄ አይሆንም፤ አያስኬድም በሚል የሚመልሱ ሆነዋል። ሠራተኞቹ ‹‹ሰጪም ነሺም›› በሚመስል መልኩ ሥራቸውን እያከናወኑ ሲሆን፤ በተለይ ይሄ ጉዳይ በክፍለከተማና ወረዳዎች ላይ ይስተዋላል። አገልግሎት ለማግኘትም ገንዘብ መክፈል ግዴታ እንደሆነ መዘንጋት የለበትም። ለዚህ እንደማሳያ ብዙ ነገር መጥቀስ ቢቻልም፣ በመንግሥት መስሪያ ቤቶች ውስጥ እየተከናወነ ያለውን ሁኔታ ለማስቆምም ሆነ ለማስተካከል ጊዜው አልረፈደም።
በተለይ በአገልግሎት መስጫ ተቋማት ውስጥ ያለውን ብልሹ አሠራር ለማስተካከል የሚጠይቀው ቁርጠኝነት እንደመሆኑ ማስተካከል ይቻላል። ለዚህ ደግሞ አስፈፃሚ አካላት በተለያዩ ጊዜያት ስለ ጉዳዩ ብዙ መፍትሄ ሀሳቦች አቅርበው ውይይት አድርገዋል። ብልሹ ሥነ ምግባር ያላቸውን ሠራተኞች ላይም እርምጃ መውሰድ ጀምረዋል። ይሄው ርምጃ በተጠናከረ መልኩ መቀጠል አለበት። አገልግሎት የሚያገኘው ኅብረተሰብም ብልሹ አሠራሮችን በሚመለከትበት ወቅት ተባባሪ ከመሆን በመቆጠብ ለሚመለከተው ጥቆማ መስጠትን እንደ ግዴታው መቁጠር ይኖርበታል። ከሕግ አካላት ለሚቀርብለትም የትብብር ሥራ ቀና የሆነ ምላሽ መስጠት አለበት። የሲቪል ሰርቪስ አስተዳደር አዋጆችም ሆኑ መመሪያዎች በአግባቡ ተግባራዊ እንዲሆኑ እንዲሁም እስካሁን ያለው አሠራር የሚፈተሽበት ሁኔታ መፈጠር አለበት። በየመስሪያቤቱ የሚገኙ ሠራተኞች ከፊርማ ይልቅ በሥራ የሚመዘኑበት ሁኔታ ላይ መስራት ይኖርባቸዋል።
ልዑል መርዕድ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 28 ቀን 2014 ዓ.ም