ሲያደብር፡- በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ሲያደብርና ዋዩ ወረዳ የጋሹ አምባ ቀበሌ የሚገኘው የጫንጫ ዋሻ ሰባት ትውልዶች ኖረውበታል። አሁን እያስተዳደሩት የሚገኙት አቶ አጥናፉ በቀለ ይባላሉ።
የ78 አዛውንቱ አቶ አጥናፉ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለፁት፤ በሲያደብር ቀበሌ መጥሪያ በምትባል ጎጥ ጫንጫ በተባለው ዋሻ ውስጥ የተወለዱ ናቸው። ከእርሳቸው ቀደም ብሎም ስድስት ትውልዶች በዋሻው ውስጥ ኖረውበታል።ይሁን እንጂ ትክክለኛ የዋሻውን ስፋትና ጥልቀት እስካሁን ድረስ እንደማያውቁ ይናገራሉ።
የደርግ ሥርዓት አገሪቱን ማስተዳደር እንደጀመረ ከዕለታት በአንድኛው ቀን የዋሻውን ጥልቀት ለማወቅ ከታላቅ ወንድማቸው ጋር ወደ ዋሻው ውስጥ መግባታቸውን ያስታውሳሉ። በወቅቱ ግማሽ ቀን
ሙሉ ተጉዘው የዋሻውን መጨረሻ ለማግኘት አልቻሉም። ይሁንና አንድ ለየት ያለ ጦር ከዋሻው ውስጥ አግኝተው ተመልሰዋል። ይህ በሆነ በሳምንቱ ግን ሁለት ፍየሎቻቸው ወደ ዋሻው ገብተው የውሃ ሽታ ሆነው መቅረታቸው አሁንም ድረስ የእግር አሳት ሆኖባቸዋል።
አቶ አጥናፉና ወንድማቸው ዋሻው ውስጥ በገቡ በሳምንቱ ፍየሎቹ እንደገቡ መቅረታቸው ወላጆቻቸውን ያስቆጣ ሲሆን፤ ለግርፋትም ዳርጓቸው እንደነበር ይናገራሉ።ዋሻው ውስጥ መሬቱ በዱላ መታ መታ ሲደረግ የሚያረገርግና የባህር ደምጽ እንደሚሰማ ገልጸው፤ ፍየሎቹ እዚያ ውስጥ ገብተው ሊሆን ይችላል በሚል ጥርጣሬ ወደ ዋሻው የሚወስደውን መንገድ መዘጋቱን አስታውሰዋል።
«ፍየሎቹ አንድ ቀን ከዋሻው ይወጣሉ ብለን ብንጠብቅም፤ መዳረሻቸው ወዴት እንደሆነ ሳናውቅና ምላሽ ሳናገኝ ግማሽ ክፍለ ዘመን ተቃርቧል፤ እኛም ዓጂኢብ እንዳሰኘን እየኖርን ነው። ነገሩን ለሰዎች ስንናገርም ግራ እየገባቸውና ጥያቄ እየሆነባቸው ዘመናት ተቆጥረዋል» ብለዋል።
አቶ አጥናፉ በዚሁ ዋሻ ውስጥ ተወልደው ጥርስ የነቀሉበት፣ ልጅ የዳሩበትና የኳሉበት መሆኑን ጠቁመው፤ ዋሻው ያኔ ሁለቱን ፍየሎች የውሃ ሽታ ካደረገባቸው ወዲህ ግን የከፋ ነገር ሳያስከትል በሰላም እየኖሩበት መሆኑን ተናግረዋል።
በአሁኑ ወቅትም ዋሻው በፍቅር እንስሳትና ሰዎችን አቅፎ የሚያኖር ነው። እርሳቸውን ጨምሮ ሰባት ትውልድ እንደኖሩበት የሚነገርለት ይህ ዋሻ በውስጡ ምን እንደያዘ የሚያረጋግጥ ሁነኛ ተመራማሪ ቢመጣ ለኢትዮጵያ አንዳች የጥናትና ምርምር ግኝት ሊሆን እንደሚችልም ተስፋ ያደርጋሉ። የአቶ አጥናፉና የዋሻውን ሙሉ ታሪክ በቅርቡ «በእንዲህም ይኖራል» አምዳችን እናስነብባችኋለን።
አዲስ ዘመን ቅዳሜ መጋቢት 21/2011
በክፍለዮሐንስ አንበርብር