ደብረ ብረሃን፡- በደብረ ብርሃን ከተማ በ2011 ዓ.ም ሁለት ቢሊዮን ብር ካፒታል ኢንቨስትመንት ለመሳብ ቢታቀድም በሰባት ወራት ብቻ ከእቅዱ በ345 በመቶ የበለጠ ኢንቨስትመንት መገኘቱን የከተማዋ አስተዳደር አስታወቀ።
የደብረ ብርሃን ከተማ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ ደስታ አንዳርጌ በተለይ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለፁት፤ ከተማዋ በ2011 ዓ.ም ሁለት ቢሊዮን ብር ካፒታል ያላቸው ኢንቨስተሮችን ለማስተናገድ ማቀዷን አስታወሰው፤ ባልተጠበቀ መንገድ ኢንቨስተሮች እየጎረፉ መሆኑን ጠቁመዋል። ምንም እንኳን ዓመታዊ እቅዷ ሁለት ቢሊዮን ብር ካፒታል ኢንቨስትመንት መሳብ ቢሆንም፤ ባለፉት ሰባት ወራት 6ነጥብ9 ቢሊዮን ካፒታል ያስመዘገቡ ባለሃብቶች ወደ ኢንቨስትመንት ሂደት መግባታቸውን ጠቁመዋል። እነዚህም 57 ፕሮጀክቶችን ያካተቱ ሲሆን፤ ለሰባት ሺህ ዜጎች ቋሚ የሥራ ዕድል ይፈጥራሉ።
እንደ አቶ ደስታ ገለፃ፤ በአሁኑ ወቅትም በርካታ ባለሃብቶች ወደ ደብረ ብርሃን ከተማ እየመጡ ሲሆን፤ ከፍተኛ መዕዋለ ንዋይ
ያስመዘገቡና ትልልቅ ፕሮጀክቶች ላይ የተሠማሩ ባለሃብቶች እየተበራከቱ ነው። ለአብነትም እስከ 1ነጥብ3 ቢሊዮን ብር ያስመዘገቡ ኢንቨስተሮች መኖራቸውን ጠቁመዋል።
«ኢንቨስተር ወደ ከተማዋ ስለመጣ ብቻ ዕድል አንሰጥም» ያሉት አቶ ደስታ፣ ይልቁንም
የሥራ ዕድል የሚፈጥሩ፣ ቴክኖሎጂ ሽግግር የሚያሳልጡ፣ ከአካባቢ ብክለት የፀዳ ሥራ የሚሰሩና የውጭ ምንዛሪ የሚያስገኙ ባለሃብቶች ቅድሚያ ይሰጣቸዋል። ቀደም ሲል ወደ ሥራ ገብተው በአግባቡ በማይሠሩት ላይ ደግሞ እርምጃ መወሰድ ተጀምሯል።
እንደ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ገለፃ፤ በቅርቡ 82 ሄክታር መሬት ለእነዚሁ ኢንዱስትሪዎች ሲባል ተከልሏል። ከዚህ ውስጥ 54 ሄክታር የሚሆነው መሬት 36 ሚሊዮን ብር ካሳ የተከፈለ ሲሆን፤ ቀሪው ደግሞ በኢንዱስትሪ ዞን የተካለለ ነው። በአሁኑ ወቅት ባለሃብት በራሱ የመሬት ካሳ ከፍሎ ወደ ሥራ እንዲገባ እየተደረገ ሲሆን፤ ኢንቨስተሮችም ፈቃደኛ መሆናቸውን አብራርተዋል። ለአብነትም በቅርቡ ቻይናዎች 42 የጨርቃጨርቅ ሼዶችን በአክሲዮን ደረጃ ሊገነቡ አስበው 400 ሄክታር መሬት ጠይቀዋል። ከዚህም ውስጥ ለ200 ሄክታር መሬት ካሳ ለመክፈል ዝግጅት ጨርሰው ርክክብ ሊደረግ መሆኑንም አስታውሰዋል።
ቀልጣፋ አሠራር መዘርጋቱ፣ በአካባቢው ሠላምና መረጋጋት አስተማማኝ መሆኑ፣ ባለሃብቶች ላይ ይደርስ የነበረው እንግልት መቀነሱ፣ የቢሮክራሲ ውስብስብነት መቃለሉ ብሎም በደብረ ብርሃንና አካባቢው ከፍተኛ የኢንቨስትመንት መዳረሻ አቅም መኖሩ የባለሃብቶች ቀልብ ለመግዛት ትልቅ አበርክቶ እንዳለውም አስገንዝበዋል።
አዲስ ዘመን ቅዳሜ መጋቢት 21/2011
በክፍለዮሐንስ አንበርብር