ከሩጫው ማዕድን የተመረቱ ወርቆች፤
ሰሞኑን ኢትዮጵያ ፈጣሪዋን ጎላ ባለ ድምጽ እያመሰገነች፤ ልጆቿም እርሷን እያመሰገኑ መደናነቁ ደመቅ ብሏል። መከራ ያቆራመዳት አገር እጆቿን በምሥጋና ወደ ጸባኦት ዘርግታ ደስታዋን ስትገልጽ ከማየት የበለጠ ምን እርካታ ይኖራል። ለጀግኖቹ አትሌቶቻችን፣ ለአሰልጣኞቻቸው፣ ለስምሪት ሰጪዎቻቸውና በልዩ ልዩ ጉዳዮች ዙሪያ ድጋፍ ላደረጉላቸው በሙሉ ምስጋናችን ይድረሳቸውና በኀዘንና በልቅሶ በተሸበሸበው የአገሬ አንገት ላይ የወርቅ፣ የብርና የነሐስ ሜዳሊያዎች ተገጥግጠው ከማየት የበለጠ ምንም የሚያስደስት ነገር የለም። እናት ዓለም! እንኳንም የሐምሌው ጭጋግ ብራ ሆኖልሽ በደስታ ፈገግ አልሽ።
እኛ ብቻ ሳንሆን 18ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ምክንያት ሆኖ በአሜሪካዋ ክፍለ ግዛት በኦሪገን ሰማይ ላይ የናኘውን የኢትዮጵያን አሸናፊነት ገድል፣ ጩኸትና አድናቆት በዘመናዊ የዴሲብል ሜትር መለካት ቢቻል ኖሮ ምን ያህል ከብሮና ገዝፎ አየሩን እንዳደመቀው መገመት አይከብድም። አሜሪካ ሆይ እንኳንም ብዙ ትርጉም ለሚሰጠን የደስታችን ምስክር ለመሆን አበቃሽ።
ጀግኖቹ አትሌቶቻችን ሜዳሊያውን በአንገታቸው ላይ ሲያጠልቁና አሸናፊነታቸው ሲረጋገጥ ቀድሞ በክብር ከፍ ከፍ ብሎ የሚገንነው የኢትዮጵያ ስም ሲሆን፤ የምትወከለውም በብሔራዊ ሰንደቅ ዓላማዋና በብሔራዊ መዝሙሯ ነው። ባለ ወርቃማ እግር አትሌቶቿ የአገራቸውን አንገት በወርቅ፣ በብርና በነሐስ ሜዳሊያ ስላንቆጠቆጡ ልጆቻችን ሆይ ደግመን ደጋግመን ምሥጋናችን ይድረሳችሁ እንላለን። ኢትዮጵያ ሆይ! እንኳንም በልጆችሽ ደስ ተሰኝተሽ ደስ አሰኘሽን። ፈጣሪያችን ሆይ! ለአትሌቶቻችን ሙሉ ጤንነትና ብቃት ሰጥተህ የደስታችን ምንጭ ስላደረግሃቸው ክብር ምሥጋና ይድረስህ።
የወርቃማ ባለ አእምሮዎች ትሩፋት፤
የዛሬዪቱ ኢትዮጵያን መልክ በየዘመናቱ እየቀረጹና እያበጃጁ እዚህ ያደረሷትን የወርቃማ አእምሮና አገልግሎት ባለፀጎችን ትሩፋትና ዝና ማስተጋባት ያለብን ሁኔታዎች ሲቀሰቅሱንና ሲያባንኑን ብቻ መሆን ያለበት አይመስለንም። ሁሌም የአዋጅ ያህል መመስከር፣ ለልጆቻችንም መንገር፣ ልጆቻችንም ለልጆቻቸው እንዲያሳውቁ ማበረታታት ግድ የሚል ይመስለናል። እስኪ ይህንን የመመሠጋገን ሳምንት ምክንያት በማድረግ ከብዙዎቹ ጥቂቶቹን የወርቃማ አእምሮ ባለተሰጥኦዎች እያስታወስን እናመስግናቸው።
ስምና ዝናቸውን ቀድመን ከምንተርክላቸውና ከምናወድሳቸው የአገርና የሕዝብ ባለውለታዎች መካከል የጦር ሜዳ ጀግኖቻችን ቀዳሚውን ስፍራ ይይዛሉ። በዘመናት ውስጥ ለአገራቸው ነፃነትና ክብር ሲሉ ከጠላት ጋር እየተናነቁ በጀግንነት የወደቁት ዜጎቻችን በቁጥር የሚገለጹ አይደሉም፤ ይሞከርም ቢባል የሚቻል አይሆንም። «እነ እከሌ» ብለን እንዘርዝር ቢባልም «ዐባይን በጭልፋ» ይሉት ብጤ ይሆንብናል። በየፍልሚያው ጎራ የወደቁና ቀባሪ አጥተው የረገፉ አጽሞች ዛሬም እንደ ተከላካይ ዘብ በጽናት ቆመው ለኢትዮጵያ ክብር ሐውልት ስለሆኑ ክብርና ሞገስ ይሁንላቸው። ቀድሞውንስ ቢሆን…
«የወታደር እናት ታጠቂ በገመድ፣
ልጅሽን አሞራ እንጂ አይቀብረውም ዘመድ»
የሚለው ትንቢት እንደሚፈጸምባቸው ያውቁት የለ? ሥጋቸው ላሞራና ለዱር አራዊት ቀለብ የሆነ፤ ክቡሩ አጽማቸውም በየጉድባውና ተረተሩ እንዳልባሌ ነገር ተበታትኖ የቀረው ጀግኖቻችን የከፈሉልን ዋጋ ከግምት በላይ ስለሆነ ኒሻንና ሜዳሊያ በአንገታቸው ላይ ማጥለቅ ባይቻልም ፈጣሪ ስለ ከፈሉልን መስዋእትነትና ስለዋሉልን ውለታ ለነፍሳቸው ክብርን እንዲያጎናጽፍ በሰርክ ፀሎታችንና በቀጣዩ ታሪካችን አድምቀን ልናስታውሳቸው ይገባል። ትውልድም በየዘመኑ እንዲህ እያለ ይቀኝላቸዋል።
በአንተ ዓላማ – በደም ትልምህ፣
በአንተ ትግል – በሞት ገድልህ፣
ይኸውና «ሰው» – ሆንኩልህ።
ደስ እንዳለኝ – ደስ ይበልህ፣
«የእኔ ጋሻ – የእኔ ወንድም፣
የእኔ እህት – የእኔ ክብር።
የሀገር ምድር – የሀገር ሰማይ፣
የሀገር ጀምበር – የሀገር ፀሐይ፤
የሀገር ዙሪያ – ክቡር አጽም፣
የእኔ ጋሻ – የእኔ ወንድም።
(ከሻለቃ ክፍሌ አቦቸር፤ «የእኔ ጋሻ» የግጥም መድበል)
ዛሬም ንዳድና ቁር ሳይበግራቸው በግዳጅ ወረዳቸው ላይ ዘብ ለቆሙ ጀግኖቻችን በአገር ልብና በሕዝብ ፍቅር አክብሮታችን ይድረሳቸው። አእምሯቸው ከወርቅ የከበረ፣ ውለታቸው ከእንቁ ዋጋ የላቀ ነውና ሁሌም በክብር እንዘክራቸዋለን። ለቀጣዩ የጀግንነት ውሏቸውም እንዲህ እያልን አደራችንን እናጸናለን።
ምሥራቅ ድንበሩ ላይ ጋሻ ሆኖ ላለው፣
ደቡብ ድንበሩ ላይ በጽናት ለቆመው፣
ሰሜን ድንበሩ ላይ ሰንደቅ ሆኖ ላለው፣
ምዕራብ ድንበሩ ላይ አጥር ሆኖ ላለው፣
በወደቁት ጀግኖች በደማቸው መሃላ፣
ውድ እናታችንን ኢትዮጵያን አደራ፣
አትዮጵያን አደራ! ኢትዮጵያን አደራ።
ክብር በነፍሳቸው ተወራርደው ነፃነት ላጎናጸፉን። ክብር ዘብ ሆነው ለጋረዱን ጀግኖቻችን ይሁን።
የብሩህ ባለ አእምሮዎች ወግ፤
በርካታ ምዕራባውያን አገራት በልዩ ልዩ የሙያ ዘርፎች ለሕዝባቸው ውለታ የሚውሉ ዜጎቻቸውን የሚያሞጋግሱት «የውብ አእምሮ (Beautiful Minds) ባለ ፀጎቻችን» በሚል ማሞካሻ ነው። አድናቆታቸው በአጠራር ብቻም ሳይሆን በበርካታ የሆሊውድና የየአገሩ ፊልሞችም ሳይቀር ይከበራሉ፤ ይሞካሻሉ፤ በሽልማቶችና በስጦታዎችም ይንበሸበሻሉ።
ይህ አገላለጽ ይቆጨውና ያንገበግበው የነበረው አፍሪካዊው የጋና ደራሲ አዪ ኩዌ አርማህ እ.ኤ.አ በ1968 “The Beautyful Ones Are Not Yet Born” በሚል ርእስ አንድ ተወዳጅና ተደጋግሞ ለህትመት የበቃ መጽሐፍ ለንባብ አብቅቶ ነበር። ይህ ደራሲ በመጽሐፉ ውስጥ ደመቅ አድርጎ ለመሄስ የሞከረው የድህረ ኮሎኒያሊዝምን የጋናውያን ሕይወት ነበር።
እንደ ደራሲው እምነት ጋና ከቅኝ ገዢዎች መዳፍ ነፃ ወጥታ ድል ከተቀዳጀች በኋላ ዜጎቿ ባህላቸውንና ታሪካቸውን ንቀውና አኮስሰው እንደምን ለምዕራባውያን ቁሳቁስና ባህል ተገዢና አምላኪ እንደሆኑ ለማሳየት ሞክሯል። «እኛ ጋናውያን ገና ባለ ውብ አእምሮ ዜጎችን ማፍራት አልቻልንም፤ ለማፍራትም ዘመናት ይጠይቁናል» በማለትም አገሩንና ሕዝቡን ሞግቷል። «አካላችን ብሔራዊ ነፃነትን ቢጎናጸፍም አእምሯችን ግን ገና በእስራት ውስጥ ነው» ሲልም አገሩንና ሕዝቡን በጥበብ ሥራው አማካይነት ሄሷል።
ታሪካቸውን፣ ባህላቸውን፣ ወጋቸውን፣ ክብራቸውንና ለነፃነታቸው ምክንያት የሆኑትን የአባቶቻቸውን ገድልና ፈለግ ከመከተል ይልቅ በምዕራባውያኑ የሕይወት ዘይቤ ተማርከው አካላቸው በአገራቸው ጋና፣ መንፈሳቸውና ስሜታቸው አውሮፓና ሰሜን አሜሪካ ለሚንጠራወዘው የዘመኑ ትውልድንም «ገና ከተጨማለቀ የአስተሳሰብ አረንቋ ውስጥ በአሸናፊነት ስላልወጣ ትውልዱ አእምሮው አልተፈወሰም» ሲልም «የውብ አእምሮ ባለፀጋ ትውልድ ሆይ ወዴት አለህ!» በማለት በድርሰት ሥራው ውስጥ አጉልቶ ይጠይቃል።
እኛስ?
እኛማ! ክብር ለአገራችን ቀዳሚና ተከታይ ጀግኖቻችን ይሁንና ኢትዮጵያችንና ልጆቿ የቅኝ ገዢዎች ተንበርካኪ፣ የብሩህ አእምሮም ድሃ አልነበረችም፤ ሆናም አታውቅም፤ ልጆቿም እንደዚያው። በጀግንነቱ መስክ ብቻ ሳይሆን በሳይንስና በኪነጥበባት፣ በትምህርትና በምርምሩ መስክ ብዙ አርአያ ሰብ ዜጎችን አምጣ ወልዳለች።
አክሱም፣ ላሊበላ፣ የፋሲል ግንብ፣ የሐረር ጀጎል ጥንታዊ ከተማ፣ ውብ መስጊዶችን፣ አብያተ ክርስቲያናትንና አብያተ መንግሥታትን ያነጹት ባለ ውብ አእምሮ ልጆቿ የሥልጣኔያቸውን አሻራ ያቆዩልን ያለማንም አጋዥና የዕውቀት ብድር ነበር። የባህልና የቅርስ ባለፀጎች ያደረጉን፣ የኩራትና የክብር መደነቂያ እንድንሆን የተጉልን፣ ትናንትን ዛሬንና ነገን በሦስት የጊዜ ቀለበት አስተሳስረው ከዘመን ዘመን ዓለም በአድናቆት እየተጠቋቆመብን እንድንዘልቅ የታሪካችንን ጎዳና ያሰመሩልን እነዚሁ የክብራችን ጉልላቶች ናቸው። ሞገስና አድናቆታችን ሁሌም አብሯቸው ይዘልቃል።
የአውሮፓን ወራሪ ኃይላት መመከት ብቻም ሳይሆን ሽንፈትን እንደ ውርደት ቆጥረን ለቀጥታም ሆነ ለእጅ አዙር አገዛዝ ባዕድ ሆነን በባዕዳን ጭምር እንድንሞገስ ምክንያት ለሆኑን ሁሉ ሙገሳና አድናቆት ቢያንስባቸው እንጂ የሚበዛባቸው አይደለም። እናት ዓለም ኢትዮጵያ ታሪኳም ሆነ ገድሏ እንደ ከዋክብት የበዛና የደመቀ ስለሆነ ዝርዝሩን ጀምረን ለመጨረስ የሚያዳግቱን የብዙ ትሩፋቶች ባለቤቶች ነን። ምሥጋናችን ከታላቅ አክብሮት ጋር ይድረስልን።
ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ልክ እንደዚህ ጸሐፊ በእስራኤል ታሪክ ውስጥ በመልካም ተጽእኖ ፈጣሪነት የሚጠቀሱ «የእምነት ጀግኖቻቸውን» በስምና በግብር ለመዘርዘር ሞክሮ አልሆን ሲለው «እንግዲህ ምን እላለሁ? …ሁሉንም እንዳልዘረዝር ጊዜ ያጥረኛል። እነዚህን የሚያህሉ ምስክሮች እንደ ደመና በዙሪያችን ከበውናል» ብሎ ሃሳቡን እንዳጠቃለለ ሁሉ፤ ይህ ብዕረኛም ይህንኑ ተግዳሮት በመጋራት ከብዙዎች መካከል ጥቂቶቹን ብቻ ቆንጥሮ በማስታወስ ሃሳቡን ሊገታ ግድ ይላል።
ደጋግመን ለመጥቀስ እንደተሞከረው መቼውንም ቢሆን «ከታሪክ መሰዊያ ላይ አመዱን ሳይሆን እሳቱን መጫር በብዙ ይመረጣል።» ታሪካችን የድል ነሺዎች ገድል የታጨቀበት ብቻ ሳይሆን፤ በብዙ ማሳያ ማረጋገጥ እንደሚቻለው ድል ተነሺነትም በስፋት እንደነበር የሚካድ አይደለም። የሚያኮሩ ብቻም ሳይሆኑ የሚያሸማቅቁ ታሪኮችም ሞልተውናል። በአጭሩ ባለ ምጡቅ አእምሮ ጀግኖች ያሉንን ያህል ትውልድን «ያመከኑ የሾተላይ ባለ አእምሮዎችም» ታሪክ የታሪካችን ሌላው ምዕራፍ መሆኑን አንክድም። ቢሆንም ግን ገፈቱን እያጠለልን በወለላ ታሪካችን ላይ ማተኮሩ የበለጠ የተሻለ ይሆናል።
አገርን ተዳፍሮ በጅምላ መውቀሱ የበጎ ሥነ ምግባር ባህርይ ባይሆንም ስህተትን መጠቆሙ ግን ለመታረም ይበጃል። ብዙ ባለ ወርቃማ አእምሮ ዜጎቻችን በአረም በሚመሰሉ አንዳንድ «ራስ ወዳድ ዜጎች» ተሸፍነውና ተጋርደው ማስተዋል ያማል፤ ያስተክዛል። ሽልማቱና ሹመቱ እንኳን ቢቀር በአደባባይ ላለማመስገን ድብብቆሽ መጫወት አገራዊ ባህላችን ለመሆን እየተንደረደረ ያለ ይመስላል። ከአሁን በፊት «አንድ ሰው ስንት ነው?» ብለን ለመጠየቅ እንደሞከርነው አንድ ሆኖ እንደ ብዙ ሰው በጓዳም ሆነ በአደባባይ እኔነትን ብቻ አንግሶ ራስን የአሸናፊዎች ሁሉ ቁንጮ ማድረግ ተዋራጅነት እንጂ የሚያስመሰግን አይደለም።
ማንም ሰው የሚከበረው ሌላውን ሲያከብር ነው። ነዎሩ የሚሰኘውም ሌላውን ፊት ሲያስቀድም ነው። አሁን አሁን እየታየ ያለው ይህን መሰሉ ልማድ ግን ለአገርም ይሁን ለታሪክ የሚበጅ ስላልሆነ በጊዜ መታረሙ አይከፋም። ምሥጋና ለሚገባው ምስጋናን፣ ክብር ለሚገባው ክብርን መስጠት ያስከብራል፤ የመልካም ስብዕና መገለጫም ነው። ስለዚህም የወርቃማ አእምሮ ባለፀጎቻችንን እናክብራቸው፤ የበጎነታቸውን ውለታም ሳንሰስት እንዘክርላቸው።
ሰላም ይሁን!
(ጌታቸው በለጠ /ዳግላስ ጴጥሮስ)
gechoseni@gmail.com
አዲስ ዘመን ሐምሌ 27 ቀን 2014 ዓ.ም