የሰው ልጅ በመኖር ሂደት ውስጥ ሀብት ማፍራቱ የተለመደ ነው። የሀብት ባለቤትነቱን ደግሞ ህጋዊ ለማድረግ ህጋዊ ሰነድ የሚያገኝበት ተቋም ያስፈልገዋል። ሀብትን በአግባቡ ለማስተዳደር ከባለቤትነት መብት ጀምሮ የተለያዩ 51 አይነት አገልግሎቶችን የሚሰጠው ተቋም የሰነዶች ማረጋገጫና ምዝገባ አገልግሎት በመባል ይታወቃል።
ከተቋሙ ዋና ዳይሬክተር ከአቶ ሙሉቀን አማረ ጋር በተቋሙ ስለሚታዩ የመልካም አስተዳደር ችግሮች፤ በተለይ ከአገልግሎት አሰጣጥ ጋር ተያይዞ እያጋጠመ ስላለው ችግርና (ሀሰተኛ መረጃ)፣ ሙስናን የሚመለከት እንዲሁም ሌሎች ጉዳዮችን በተመለከተ ቃለመጠይቅ አድርገናል። ከእርሳቸው ጋር የነበረንን ቆይታ እንደሚከተለው አጠናቅረነዋል፡፡
አዲስ ዘመን፤ የሰነዶች ማረጋገጫና ምዝገባ አገልግሎት አሁን ያለበት ቁመና ምን ይመስላል?
አቶ ሙሉቀን፡- የሰነዶች ማረጋገጫ የፌዴራል ተቋም ነው። ተቋሙ ሰነድ የማረጋገጥና የምዝገባ አገልግሎት የሚሰጥበት ነው። ተቋሙ አገልግሎት የሚሰጠው በፌደራል ደረጃ ነው ሲባል አዲስ አበባና ድሬዳዋ ከተማ ላይ ከትሞ የሚሰራ ተቋም ነው። በተመሳሳይ ይህን አገልግሎት በተቀሩት ክልሎች የሚሰጡት የፍትህ ቢሮዎች ናቸው። ሰነድ የማረጋገጥና የምዝገባ አገልግሎት ሲባል በርካታ አገልግሎቶችን በውስጡ ያየዘ ነው። በቁጥር ይህ ነው ባይባልም ዋናው ከሀገሪቱ ሕግ ጋር የማይጣረስ ካለን ሀገራዊ ሞራል ጋር የተጣጣመ ሰነድ የማረጋገጥ አገልግሎት ይሰጣል።
እስካሁን ባለው ሂደት ወደ 51 አይነት አገልግሎቶች ወደ ተቋሙ ሰነድ ይረጋገጠልኝ ሲሉ ይመጣሉ። በቀጣይም ይረጋገጥልኝ የሚባል ሰነድ ቢመጣ የሀገሪቱን ሕግና ሞራል ከጠበቀ ይስተናገዳል። ከ51ዱ አይነት አገልገሎቶች ውስጥ ደግሞ አብዛኛው የውክልና አገልግሎቶች፣ የንብረት ማስተላለፍ ውሎች፣ የኪራይና የብድር ውል እንዲሁም የኩባንያዎች መመስረቻና ማሻሻያ ቃለ ጉባኤዎች ሰፊውን ስፍራ ይይዛሉ።
አሁን ባለው ሁኔታ ተቋሙ በቴክኖሎጂ የታገዘ አገልግሎት እየሰጠ በአዲስ አበባ አስራ አራት ቅርንጫፍ በድሬዳዋ ያለውን አንድ ጨምሮ በድምሩ አስራ አምስት ቅርንጫፍ ያለው፤ በኦንላይንም ጭምር እየታገዘ አገልግሎት እየሰጠ ያለ ተቋም ነው። ተቋሙ ከባንኮችና ከመሳሰሉት መንግስታዊና መንግስታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች ጋር በቴክኖሎጂ በመተሳሰር እየሰራ ነው። በሁሉም ቅርንጫፎች በድምሩ በቀን እስከ 6 ሺህ 700 ተገልጋዮችን እያስተናገደ ሲሆን፣ ይህም በአማካይ የተቀመጠ የተገልጋይ መጠን ነው።
አዲስ ዘመን፡- ቀደም ሲል ተቋሙ በተለያዩ ጊዜዎች ተሸላሚ ነበር፤ ይህ የስራ ጥንካሬ ግን ለአንድ ሰሞን ነው ወይስ በትክክል የአስራር ስርአቱን ጠብቆ የህዝብ እርካታውን ይዞ እየሄደ ነው ?
አቶ ሙሉቀን፡- ይህ ተቋም በአስራ ዘጠኝ ዘጠናዎቹ መጀመሪያ አካባቢ በቀን ሰላሳ ሰው የሚያስተናግድ አቅም ነበረው ። አሁን ደግሞ ወደ 6 ሺ 700 ከፍ ብለናል። ይህ ቁጥር ግን በአንድ ጊዜ የተደረሰበት ሳይሆን በሂደት መጥራት ያለባቸው አሰራሮች እየጠሩ፤ የተለያዩ ደረጃዎችን እያለፈ ነው እዚህ ደረጃ የደረሰው። ተቋሙ ቀደም ሲል በአገልግሎት አሰጣጡ በርካታ ቅሬታዎችን የሚያስተናግድ ተደራሽ ያልነበረ በአንድ ማእከል አገልገሎት ይሰጥ የነበረ ነው ። በ2001 ዓ.ም አካባቢ ተቋሙ በሰራው ሪፎርም በሀገር አቀፍ ደረጃ የኢትዮጵያ ጥራት ስራ ድርጅት ተወዳድሮ ተሸላሚ ሆኗል።
ከሽልማቱ በኋላ ግን ስራ ማቆም ሳይሆን ተደማሪ ለውጦችን ለማምጣት እየተጋ ይገኛል። አዳዲስ ስራዎችን መስራት፤ ተጨማሪ የአገልግሎት ክፍተቶችን በመመልከት ማሻሻያዎችን እየሰራ ይገኛል። የኦንላይን አገልግሎቶች፣ ቅርጫፎችን የማስፋት ስራ፣ የህዝቡን ፍላጎት በማየት አገልግሎት ብዛትን መጨመርና ሌሎች ስራ እየተሰሩም ይገኛሉ። ከነበረው ላይ ወደኋላ መመለስ ሳይሆን ወደፊት እየተጨመረ የተገልጋይን እርካታ ለመጨመር በትጋት ወደ ከፍታ ግስጋሴውን ቀጥሏል።
አዲስ ዘመን፡- ከየሰነዶች ማረጋገጫና ምዝገባ አገልግሎት በአብዛኛው ከንብረት ጋር የተያየዙ ስራዎችን ይሰራል፤ በዚህም በርካታ ህገወጥ ሰነዶች ሊቀርቡ ይችላሉ፤ ይሄ እንዴት ይለያል? ከፍትህ አካላት ጋርስ በቅርበት የመስራቱ ጉዳይ ምን ይመስላል?
አቶ ሙሉቀን፡- አንድ ሰው ሰነድ ሊያረጋግጥ ሲመጣ ዋነኛው የሚጠበቅበት ነገር መታወቂያ ይዞ መምጣት ነው። ለሁሉም አገልግሎቶች የሚጠየቀው የታደሰ የነዋሪነት መታወቂያ ነው። በዚህም ከመታወቂያ ጋር ተያይዞ የሚደረጉ ማጭበርበሮች ለተቋማችን ከፍተኛ ፈተና የሆነ ጉዳይ ነው። ከመታወቂያው በተጨማሪ የጋብቻና ያላገባ መረጃዎች እንዲሁ በሃሰተኛ ሰነድ ከሚቀርቡት ማስረጃዎች መካከል የሚጠቀሱ ናቸው።
እነዚህ ሰነዶች ለማጭበርበር ተጋላጭ የሆኑበት ምክንያትም ንብረት የማስተላለፍ ተግባር ላይ ባለትዳር ከሆነ የትዳር አጋሩን ይሁንታ የሚጠይቅ፤ ባለትዳር ካልሆነ ደግሞ ያላገባ መሆኑን ማስረጃ ማምጣት ይኖርበታል። ብዙ ሰዎች ከትዳር አጋር ለመሸሽ ወይም የትዳር አጋርን እውቅና ላለመሰጠት ሲሉ ያላገባ ማስረጃ በሀሰት ያዘጋጃሉ።
ያላገባ ማስረጃና መታወቂያ ለተቋሙ ከፍተኛ ፈተና እየሆነበት ያለ ችግር ነው። ከዚህ ጋር በተያያዘ በቁጥር ለመግልፅ ያህል ባለፈው በጀት አመት ከሀምሌ 2013 ዓ.ም ጀምሮ እስከ ግንቦት 30ቀን 2014 ዓ.ም ድረስ 581 ሀሰተኛ ሰነድን ለመያዝ ተችሏል። ከ581 ሃሰተኛ ሰነዶች መካከል 411ዱ መታወቂያ ነው። በሀሰተኛ መታወቂያ በአብዛኛው ለውክልና አገልግሎት ነው የሚውለው። በዚህም ከባንክ ገንዘብ ማውጣት ሊሆን ይችላል። የሰው ንብረት መሸጥ ሊሆን ይችላል፤ ይህ ሁሉ ወንጀል ይሰራበታል።
ከባንክ ጋር ለሚፈጠሩ ችግሮች ሙሉ ለሙሉ ዘግተናል። አንድ ሰው ውክልና ሲሰጥ ፎቶ ይነሳል፤ የያዘው መታወቂያም ይያያዛል፤ ሲኩሪቲ ኮድም አብሮ ይኖራል፡፡ በዚህም ሀገሪቱ ውስጥ ያሉ ሁሉም ባንኮች የዚህን ተቋም የመረጃ ቋት መመለከት ይችላሉ። በውክልና ገንዘብ ማውጣት ሲፈለግ ውክልናው ከዚህ ተቋም መገኘቱን ያረጋግጣሉ። ይሄ የባንኮችን መጭበርበር ቀንሷል።
እንደ ባንኮቹ ሁሉ የተሽከርካሪ ሽያጭ ስም ከሚያዞረው ተቋም ጋር ተቋማችን ተሳስሯል። የአዲስ አበባ አሽከርካሪ ተሽከርካሪ ፍቃድ ጋር ባለው ትስስር ያለውን ሽያጭ ውልና ውክልናን መመልከት ይችላል።
ሌላው ማጭበርበርን ለመከላከል ሁሉም ህዝብ ውክልና ወቅት ላይ ያለውን ኪዋር ኮድ በሞባይል አፕሊኬሽን ኪዋር ኮዱን በማንበብ እራሱን ከመጭበርበር መጠበቅ ይችላል።
በአጠቃላይ ተቋሙ ያለው ስልጣን የያዛቸውን ሀሰተኛ ሰነዶች በቀጥታ ለፖሊስ በማስረከብ ተጠያቂ እንዲሆን እስከማድረግ ድረስ ብቻ ነው። ይሄ ለያዝነው ሀሰተኛ መረጃ ነው፤ ያልያዝነውም ሊኖር ይችላል። ተይዘው ወደ ፖሊስ የቀረቡት በጥፋታቸው ልክ እየተቀጡ ስለመሆኑ ጥናት ቢጠየቅም በተሰራው ልክ ግን እየተቀጡ አለመሆኑ እየታየ ነው። የፍትህ አካላት ግን ይህን ሀሰተኛ ሰነድ ይዘው የሚገኙ አጥፊዎች እንዳይበረክቱ ቅጣቱ ላይ ትኩረት ቢያደርጉ የተሻለ ውጤት ይመጣል ብዬ አስባለሁ።
አዲስ ዘመን፡- አንድ ተገልጋይ ወደ ተቋሙ ሲመጣ መብትና ግዴታውን ያውቃል? እናንተስ አገልግሎት መስጠት ግዴታችሁ መሆኑን ታውቃላችሁ? በእጅ መንሻ አገልግሎት የሚፈልጉ ተገልጋዮች ካሉስ እንዴት ነው ይሄንን የምትከላከሉት?
አቶ ሙሉቀን፡- እውነት ለመናገር ማህበረሰቡ ተገቢ አገልግሎት አገኝበታለሁ ብሎ በልበ ሙሉነት ከሚመጣበት ተቋም አንዱ ይህ ተቋም ነው። ለዚህም መረጃው ተደራሽ መሆኑና በተቋሙ ሄዶ መገልገል መብቱ እንደሆነ የሚያዉቅበት መሆኑ በራሱ ማህበረሰቡ በተቋሙ እምነት አሳድሯል።
በዚህ ተቋም ለነገ የሚባል ስራ አለመኖሩንም ተገልጋዩ ያውቃል፤ እንኳን ለቀጣዩ ቀን ሊቀጠር ቀርቶ ጠዋት መጥቶ ከሰዓት ተመለስ ቢባል ፍቃደኛ አይደለም። ሌላው እዚህ ተቋም ላይ አገልግሎት እየሰጠ ያለ አንድ የተቋሙ ሰራተኛ አላገለግልም ቢል ተገልጋዩ የት መሄድ እንዳለበት ያውቃል። አቤቱታውን ተቀብሎ የሚያስተናግደው ሰው በቦታው በመኖሩ ሁሉም በር ለተገልጋዩ ክፍት ነው። ይህም በሁሉም የስራ ቀን ባለጉዳዩ ቅሬታውን ማቅረብ በራሱ የመረጃ አለመሟላት አገልግሎት ሳያገኝ ካልሄደ በስተቀር ማንም ተገልጋይ ሳይገለገል ወደቤቱ አይመለስም።
ሌላው በማንኛውም ሰዓት ኃላፊዎች ዘንድ ቢደወል የስልክ ጥሪውን የማይመልስ የለም፤ ባለጉዳይ ሲደውልም ሲያመለክትም ወዲያው እርምጃ ይወሰዳል። ለዚህም ማስረጃ እናንተ ናችሁ። በደወላችሁበት ቅፅበት ስልካችሁን መልሰናል። ከዚህ አልፎ ያልተገባ ተግባር የሚያከናውን ባለሙያ ቢገኝ ተገቢውን ቅጣት ይቀጣል። ይህ ሲባል ይህንን ተግባር የፈፀመ ባለሙያ በስራው ላይ ብናቆየው ስራው ላይ አደጋ ያመጣል ተብሎ ሲታሰብ በቀጥታ ከስራው ታግዶ የማጣራት ስራ ይሰራል። ለምሳሌ አንድ ሙስና ተጠየቅኩኝ የሚል ተገልጋይ አመልክቶ እያለ ማስረጃ አቅርቦ እያለ ያንን ባለሙያ መቀመጫው ላይ ማየት ተገቢ አይሆንምና ታግዶ የማጣራት ስራ ይሰራል። በዚህም አካሄድ እስከ አስራ ሁለት ባለሙያዎች በዲሰፕሊን የተቀጡም አሉ።
ተገልጋዮች ከሚሰጡት ጥቆማ በተጨማሪ በደህንነት(በሲኩሪቲ) ካሜራ ክትትል የሚደረግ ሲሆን፣ በዚህም እጅ ከፍንጅ የመያዝ ስራ ይሰራል። በካሜራው አገልግሎት አሰጣጥ ላይ መቀዛቀዝ ሲኖር፣ የማንቃት ክፍተት ሲኖር የመሙላት ስራም ተቋሙ በቀዳሚነት የሚያከናውነው ተግባር ነው።
አዲስ ዘመን፡- በስራ ሂደት ውስጥ ተቋሙ የሚያጋጥመው ትልቅ ፈተና ምንድን ነው?
አቶ ሙሉቀን፡- አስቀድሜ እንደገለጽኩት የተቋሙ ትልቁ ፈተና ሀሰተኛ ሰነድ ነው። በዚህ ተቋም እያጋጠመ ያለ ወደ ፊትም እያጋጠመ የሚቀጥል ይመስለኛል። በተለይ ከሀሰተኛ ሰነዶች ትልቁን ድርሻ የሚይዘው መታወቂያና ያለገባ ማስረጃ ነው። መታወቂያ የሚሰጠው አካል ማለትም ወሳኝ ኩነት ጋር በትብብር እየሰራን ቢሆንም የዜጎች የሁሉም መረጃ ዳታ ላይ አለመኖሩ ትንሽ ፈታኝ አድርጎታል።
ሌላው ፈተና የሀሰተኛ ሰነድ የያዙ ሰዎች ወደ ተቋሙ ሲመጡ ተደራጅተው የሚመጡ መሆኑ ነው። ወንጀለኛውን ይዞ ፖሊስ ጣቢያ እስከሚደርስ ድረስ የማምለጥ የተለያዩ አደጋዎችን የማድረስ ሁኔታዎችም ይታያሉ። ይህ ሲባል የፀጥታ ሀይሎች በቋሚነት በተቋሙ አካባቢ አለመኖራቸው ትንሽ ችግር ፈጥሯል። ከዚህ ውጪ ተቋሙ ይህ ነው የሚባል ፈተና ገጥሞት አያውቅም።
አዲስ ዘመን፡- አንዳንድ ተቋማት ሙሉ ውክልና የተሰጠው አካል የውክልና ማስረጃውን ይዞ እያለ የኛ ተቋም በውክልናው ላይ ስላልተገለፀ ተወክላችሁ አገልግሎት አትወስዱም ሲሉ ይታያልና እዚህ ጉዳይ ላይ ምን ይላሉ?
አቶ ሙሉቀን፡- ይህ ትክከል ያልሆነ ጉዳይ ነው። ይህ የውክልና አረዳድ ማነስ ነው። መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆነ ተቋም ውስጥ ጉዳዬን ይፈፅምልኝ
ማለት ብቻ በቂ መሆኑን ህብረተሰቡ ሊረዳ ይገባል። ተቋሙ የራሱ የቅድም ተከተል ሒደት ከሌለው በስተቀር በሀገሪቱ ያሉ ሁሉም ተቋማትን መጥቀስ እጅግ ፈታኝ በመሆኑ በጥቅሉ በመረዳት አገልግሎቱን ማግኘት ይገባቸዋል። ተቋማትም ሁሉም መጥቀስ የማይችሉ መሆኑን ግምት ውስጥ በማስገባት ከተቋሙ አሰራር ጋር አገልግሎታቸውን መቃኘት ይገባቸዋል።
አንዳንዴ ግን ተገልጋዮች ይህ ችግር ገጠመን ብለው ሲመጡ ተቋሙ መልሱ አይመለከተኝም ሳይሆን የመለሳቸውን አካል ስለአሰራሩ በማስረዳት መመሪያቸውን መፈተሽ ካለባቸው በመፈተሽ ስራው የተሳለጠ እንዲሆን የማድረግ ስራ ይሰራል።
አዲስ ዘመን፡- በተቋሙ ከሚሰጡ አገልግሎቶች መካከል ኑዛዜን የመቀበል ተግባር አለ፤ ሟች ከመሞቱ በፊት ያደረገው ኑዛዜስ እንዴት ወደ ህጋዊ ሰነድነት ሊቀየር ይችላል?
አቶ ሙሉቀን፡- ኑዛዜ አንድ ሰነድ ነው። ሰዎች በሰነዶች ማረጋገጫ መጥተው ኑዛዜ መስጠት ይችላሉ። ህጉ እራሱን የቻለ አካሄድ ቢኖረውም አንድ ሰው ግን በተቋሙ መጥቶ ኑዛዜውን ልስጥ ሲል ኑዛዜ መቀበል በተቋሙ ከሚሰሩት ሰዎች መካከል በጥንቃቄ የሚከወን ነው።
ኑዛዜ በተናዛዥ ወገን የሚሰጥ ሲሆን፣ በተቋሙ የተካሄደ ኑዛዜ በህግ ዘንድ ተቀባይነት አለው። ሂደቱ ኑዛዜ አድራጊው የታደሰ መታወቂያ በማምጣት ኑዛዜውን የሚያደረግ ሲሆን፣ ተናዛዥ ሲያልፍ ያንን የኑዛዜ ወረቀት የሚመለከታቸው አካላት ሊጠቀሙበት ይችላል።
አዲስ ዘመን፡- ቀደም ሲል በሰፈር ሽማግሌ ፊት የተደረገ ኑዛዜ አይፀናም የሚል ውሳኔ በፍርድ ቤት ሲወሰንበት ይታያል፤ በእናንተ ተቋም የተደረገ ኑዛዜስ ይህ ችግር አይገጥመውም?
አቶ ሙሉቀን፡- ኑዛዜ ይፅና አይፅና የሚለው በፍርድ ቤት የሚወሰን ጉዳይ ነው። ፍርድ ቤቱ ተናዛዥ በሚያልፍበት ጊዜ ሊያይ የሚገባቸው አካሄዶች አሉት። በዚህ ተቋም የተሰጠ ኑዛዜ ግን ከሌሎቹ የሚለየው ተናዛዥ ኑዛዜ ሲያደርግ በማጭበርበር ሊቀርብ የሚችሉ ኑዛዜዎችን ሊከላከል ይችላል።
አዲስ ዘመን፡- ተቋሙ የተለያዩ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም የተሳለጠ አገልግሎት እየሰጠ ነው ብለዋል፤ የተቋሙ አገልግሎት ከቅሬታ የፀዳ ነው ልንል እንችላለን?
አቶ ሙሉቀን፡- እሱማ ከስድስት ሺ በላይ ሰው እየተስተናገደ ከቅሬታ የፀዳን ነን ብንል የቅሬታ ማስተናገጃ ባለቋቋምን ነበር። ባለፉት አስራ አንድ ወራት ውስጥ ወደ አስራ ሰባት ሺ ሰዎች አቤቱታ አቅርበዋል። ግን ብዙ ቅሬታዎች ከተቋሙ የሚነሱት ማለትም ከአስራ ሰባት ሺው ከ95 በመቶ በላይ የሆኑ ቅሬታዎች ቅሬታውን እዛው ሰምተው በመረዳት እዛው የሚፈቱ ቅሬታዎች ናቸው። የቀረው አምስት በመቶ በአሰራር ክፍተት ሲሆን፣ እሱንም በአጭሩ ለማስተካከል ይሰራል።
ከዚህ በስተቀር ግን ያልተሟሉ መረጃዎችን ይዘው መጥተው ካልተስተናገድኩ በሚሉ አካላት የሚፈጠር ነው። አንዳንዴም ሕጋዊ መታወቂያ ኖሯቸው ግን ሳይታደስ ጥቂት ቀናት ያለፋቸውና ሌሎች ነገሮች ገጥመው ቅሬታ ሲነሳ ባለሙያው ቁጭ ብሎ ከባለ ጉዳዩ ጋር በመነጋገር ሊፈታ የሚችልበት አካሄድ አለ።
ለምሳሌ አንድ ሳምንት ሳይታደስ ያለፈ መታወቂያ ኖሮት ያላሳደሰበት ምክንያት አሳማኝ ከሆነና ወደ ተቋሙ የመጣበት ጉዳይ ፋታ የማይሰጥ ከሆነ ከሚደርሰው ጉዳት አኳያ በማሰብ አስተዳደራዊ መፍትሄ ይሰጥበታል። ይህ አስተዳደራዊ መፍትሄ ከተሰጠ በኋላ መታወቂያ አድሶ እንዲመጣ ይደረጋል ማለት ነው።
የቅሬታው መሰረት በራሱ መረጃ ያለሟሟላት ሆኖ ጉዳዩ ተስተካክሎላቸው ሲሄዱ፤ አንዳንዶች ደግሞ ከባለሙያ ጋር ተነጋግረው ያልተስተናገዱበት ምክንያት ሲነገራቸው እንዲህ አልመሰልኝም ብለው የሚሄዱም አሉ። ሌሎች ደግሞ መገልገል እየቻሉ ከአቅም ማነስ፣ ባልተገባ የባለሙያ ስነ ምግባርና ሌሎች እክሎች ሲኖሩ ግን ለመፍትሄ የተጋ አመራር መኖሩን ልናገር እወዳለሁ።
አገልግሎት ሰጪ ተቋም ሆኖ ግን ከቅሬታ የፀዳን ነን ማለት ትክክል ነው ብዬ አላምንም፤ ነገር ግን ቅሬታው በምን መልኩ እየተስተናገደ ነው የሚለውን፤ ምላሾቹና መፍትሄዎቹ ምን ይመስላሉ የሚሉትን በማየት የከፋ ችግርም የማይፈታ ቅሬታም ኖሮ አለማወቁን ልናገር እወዳለሁ።
አዲስ ዘመን፡- የሙያተኞች ስነ ምግባር ላይ የሚታዩ ክፍተቶች መኖራቸውን አንዳንድ ተገልጋዮች ይናገራሉ፤ ለምሳሌ ባለጉዳይን በትህትና ተቀብሎ ተገቢውን መረጃ ከመስጠት አንፃርና ሌሎች ጉዳዮች ላይ ያሉ ክፍተቶች እንዴት ይታያሉ?
አቶ ሙሉቀን፡- ስነ ምግባር መከታተያ ዳይሬክተሩ የተቋሙ ዋና የስራ ሂደት ነው። በሌሎች ተቋማት እንደ ዋና የስራ ሂደት አይታይም። ዋና የስራ ሂደት ስንል በቃል ብቻ ሳይሆን በቦታው የተመደቡ ሰራተኞች ዋና የስራ ሂደት የሚያገኘውን ደመወዝ ያገኛሉ። እንዲህም ሲባል በዋና የስራ ሂደት ደረጃ ስራቸውን እንዲያከናውኑ ማለት ነው።
ተጠሪነታቸውም ለዋና ዳይሬክተር ነው። እነዚህ ብዙ ጊዜ ስራቸው ያልተቋረጠ ተከታታይነት ያለው የስነ ምግባር ስልጠና በተቋሙ እንዲሰጥ ማድረግ ነው። በተለይ ህዝብን የሚያገለግል ሰው ተከታታይነት ያለው ስልጠና ይሰጠዋል። እዚህ ተቋም ላይ ማንኛውም አይነት ስልጠና ቢሰጥ ጎን ለጎን የስነ ምግባር ስልጠና ይሰጣል። የስነ ምግባር ስልጠና አንዴ ብቻ የሚሰጥ ሳይሆን በድግግሞሽ ተሰጥቶ ያ አገልጋይ ስነ ምግባርን ባህሉ እስኪያደርገው ድረስ ይሰራል።
የተቋሙ ተገልጋዮች ጠዋት ከገቡ በኋላ የሻይ እረፍት የሚባል ነገር የለም። እስከ ምሳ ሰአት አንዴም ያለማቋረጥ ለደንበኞች አገልግሎት ሲሰጡ ይውላሉ። አንዳንድ ሰው ከመድከሙ የተነሳ ቁጡ አይነት ባህሪ ሊያሳያ ቢችሉም በስልጠና እና የተለያዩ ምቹ ሁኔታዎችን በመፍጠር አገልጋዮች ሳይሰለቻቸው አገልግሎቱን የሚሰጡበት አካሄድ እንዲኖር ይሰራል።
ነገር ግን ከስር ከስር በየቅርንጫፉ የስነ ምግባር መከታተያ የቅሬታ መስሚያ ዴስክ ስላለ ስራቸው የተገልጋዩ ቅሬታ እንዳይኖር ማድረግ ነው። በዴስኩ መረጃ መስጠት ችግር ካለ እዛው እንዲፈታ የማድረግ ስራ ይሰራል። በተረፈ ደግሞ ተገልጋዩ እንዲያውቃቸው የሚገቡ ጉዳዮች በትልልቅ ቦርዶች በየቅርንጫፍ ፅህፈት ቤቱ በመለጠፋቸው በማንበብ አስፈላጊውን ማስረጃ አሟልተው ተገቢውን አገልግሎት ማግኘት እንደሚችሉ ለመናገር እወዳለሁ።
አዲስ ዘመን፡- ውድ ጊዜዎን ሰውተው በቀና ትብብር ለቃለመጠይቁ ፈቃደኛ ስለሆኑልን እጅግ በጣም እናመሰግናለን።
አቶ ሙሉቀን፡- እናንተም ተቋማችንን መርጣችሁ ስለመጣችሁ አመሰግናለሁ። በዚህ አጋጣሚ በማንኛውም ሰአት ማቅረብ ለምትፈልጉት ጥያቄ በራችን ክፍት መሆኑን ልገልጽላችሁ እወዳለሁ።
አስመረት ብስራት
አዲስ ዘመን ሐምሌ 27 ቀን 2014 ዓ.ም