ጠላት ኢትዮጵያን የማፈራረስ አጀንዳ ይዞ ሲነሳ የመጀመሪያ ተግባሩ ሕዝብ ከሕዝብ ጋር ወይም ሕዝብ ከመንግሥት ጋር ያለውን ጠንካራ መስተጋብር መናድ፣ አንድነቱን ማጥፋት ነው፡፡ ይህን ካደረገ ያሰበውን ሁሉ ለማሳካት መንገዶች ሁሉ አልጋ በአልጋ ይሆኑለታል፡፡ በዚሁ ስሌቱ መሰረት ሕዝብ በመንግሥት ላይ አመኔታ እንዳይኖረውና እርስ በእርሱም እንዳይተማመን የሚያደርጉ በርካታ ሴራዎችን እየጎነጎነ ከፍተኛ የሕዝብ ድጋፍ ያለውን መንግሥት ለማስጠላት ብዙ ርቀት ሄዷል፡፡
ዛሬ በሀገራችን የተለያዩ አካባቢዎች ጸረ ኢትዮጵያ ሃይሎች እኩይ ተግባር በፈጸሙ ቁጥር የጠላትን ተለዋዋጭ ባህሪ የመረዳት ክፍተት ያለብን አንዳንድ ሰዎች በማወቅም ይሁን ባለማወቅ ጉዳዩን ከማይመለከተው ማህበረሰብ ጋር ወይም ከመንግሥት ጋር እያስተሳሰርን እንኮንናለን፡፡ ይህ አለመረዳታችን ታዲያ ወትሮም ኢትዮጵያ እንድትበታተንና እንድተፈራርስ ለሚፈልጉት ጠላቶቻችን ምቹ ሁኔታ ስለፈጠረላቸው በየጊዜው ቦታና አጀንዳ እየቀያየሩ ማህበራዊ አንድነታችንን እንዲያናጉት እድል እየሰጣቸው ይገኛል፡፡
ያልተማርንና ስለፖለቲካ ምንም አይነት ግንዛቤ የሌለን ሰዎች ብቻ ሳንሆን ሕዝብን ወክለው በምክር ቤት ወንበር ላይ የተቀመጡ ሰዎች ሳይቀሩ በማወቅም ይሁን ባለማወቅ ጸረ ሰላም ሃይሎች የሚፈጽሙትን የንጹሓን ጭፍጨፋ የመንግሥት ባለስልጣናት እንዳስደረጉት አድርጎ የመውሰድ አዝማሚያም ይስተዋላል፡፡ እንዲህ አይነቱ በበቂ ማስረጃ ያልተረጋገጠ አሉባልታ ደግሞ በሕዝብና በመንግሥት መካከል ያለው ግንኙነት እንዲሻክር ከማድረግና የጠላትን ዓላማ ከማሳካት ባሻገር ፋይዳ አይኖረውም፡፡ ይልቁንም ህብረታችንን ያፈርሳል፤ ተሰባስበን ጠላቶቻችንን እንዳን መክት አቅም ያሳጣናል፡፡
በእርግጥ በመንግሥት ተቋማት ውስጥ እየሠሩ ከጸረ ሰላም ሃይሎች ጋር በመመሳጠር የመንግሥትን አቅም ለማዳከም የሚዶልቱ፤ የጠላትን ተልእኮ ተቀብለው ደፋ ቀና የሚሉ ጥቅመኞች የሉም ማለታችን አይደለም።አሉ። በመንግሥት ጉያ ስር ተሸጉጠው መዋቅሩን ለማዳከም ወይም ሕዝብና መንግሥትን የማለያየት ተልእኮ ተቀብለው በኅቡዕ የሚንቀሳቀሱ ጸረ ሕዝቦች በየተቋሙ መሰግሰጋቸው ለማንም ግልጽ ነው፡፡
ከዚህ የምንረዳው ኢትዮጵያን የማፈራረስ አጀንዳ ያነገቡትና መንግሥትን እየተገዳደሩ ያሉት የውጭ ሃይሎችና በይፋ የትጥቅ ትግል እያደረጉ ያሉት ብቻ አለመሆናቸውን ነው፡፡ እነዚህ በመንግሥት እቅፍ ውስጥ ያሉ የጭቃ ውስጥ እሾኾች በማር የተሸፈነ ውጫዊ ማንነት ይዘው ውስጣቸው ግን መርዝ ነው፤ እግራቸውን በመንግሥት መዋቅር ውስጥ ተክለው የዚያኛውን ወገን ፍላጎት ያስፈጽማሉ፤ ከጎናችን የቆሙ ሲመስለን ከኋላችን ይገኛሉ፤ የኢትዮጵያን ሰላምና ብልጽግና ለማረጋገጥ ብዙኋኑ የሚያደርገውን ትግልና የልማት ግስጋሴ ወደ ፊት ይገፋሉ ሲባል ወደ ኋላ ይጎትታሉ። እነዚህን በየቢሮው የተሰገሰጉ አስመሳዮች የትጥቅ ትግል እናደርጋለን እያሉ ንጹሓን ወገኖቻችንን ከሚጨፈጭፉትና ለብዙዎች መፈናቀልና ለሃብት ውድመት ምክንያት ከሆኑት ጠላቶቻችን ነጥለን ልንመለከታቸው አይገባም፡፡
እነዚህ ጥቅመኞች ከመቶ ሚሊዮን በላይ የሆነውን ሰላም ወዳድ ሕዝብን አሸንፈው መውጣት ይችላሉ ባይባልም፤ ለጊዜውም ቢሆን የመንግሥትን እልፍኝና ጓዳ ተቆጣጥረው መልካቸውን እንደ እስስት እየቀያየሩ በሚፈጽሙት ደባ ሀገርና ሕዝብን ማወካቸው አይቀርምና አደብ እንዲገዙ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡
የነዚህ አስመሳዮች ተለዋዋጭ ባህሪ ከእስስት ተፈጥሮ ጋር በከፊል ይዛመዳል፡፡ እስስት በተፈጥሮ ምግቧን ለማደን ስትል መልኳን ትቀያይራለች፡፡ ቅጠል ላይ አረንጓዴ፤ አፈር ላይ ግራጫ ሆና እያደነች ሕይወቷን ታኖራለች። ከዚህ አንጻር በኅቡዕ የሚንቀሳቀሱ ጸረ ሰላም ሃይሎች አስመስሎ የመኖር ባህሪያቸው ከእስስት ተፈጥሮ ጋር የሚመሳሰል ነው፡፡ እስስት እራሷን ከቅጠል ጋር አመሳስላ የምትፈልጋቸውን ነፍሳት እንደምታጠቃ ሁሉ እነርሱም እራሳቸውን ከሕዝብና ከመንግሥት ጋር አመሳስለው የፈለጉትን አካል ያጠቃሉ፡፡
ከሰሞኑ በመንግሥት ተቋማት ውስጥ የሚሠሩ ጥቂት ግለሰቦች የፈጸሙት መጥፎ ድርጊት መነጋገሪያ እንደነበር የሚታወስ ነው፡፡ በተለይም ሀገራችንን ካለችበት ችግር ለማውጣት ብዙኃኑ ኢትዮጵያዊ ርብርብ በሚያደረግበት በዚህ ወቅት የተሰጣቸውን ከፍተኛ የመንግሥት ሃላፊነትና የሕዝብ አደራ አሸቀንጥረው በመጣል ሀገርን ያስኮረፈ ጸያፍ ሥራ መሥራታቸው ጉዳዩን የከፋ አድርጎታል፡፡
እንዲህ አይነቱ ፍላጎትና ድርጊት ሕዝብን በመንግሥት ላይ ለማሳመጽና የመንግሥትን መዋቅር ለማዳከም ያለመ ይመስላል፡፡ በጦርነት ምክንያት ተፈናቅለው ለምግብና ለመጠለያ ችግር የተጋለጡ በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠሩ ወገኖቻችን እጃቸውን ዘርግተው የመንግስትና የወገን ያለህ በሚሉበት በዚህ አንገብጋቢ ሰዓት በስማቸው የተመጸወተውን ርዳታ ሸጦ ለግል ጥቅም የሚያውል የመንግሥት ሃላፊን ተመልክቶ ጉዳዩን ከተራ ሌብነት ጋር ብቻ ማያያዝ የዋህነት ነው፡፡ የዚህ አይነቱ ስርቆት ዓላማ የራስን ጥቅም ከማስጠበቅ ባለፈ ፖለቲካዊ አሻጥር ያለበት ለመሆኑ መጠራጠር አያስፈልግም፡፡ ያ ባይሆን ኖሮ ሀገር በፈተና ውስጥ እያለች ለተረጂዎች የተሰፈረውን ቀለብ ሸጦ ለግል ጥቅም ማዋል ባልተገባ ነበር፡፡
የዚህ አይነቱ ሴራ ዓላማ ችግርን ማባባስና የተረጂዎችን መከራ ድምጽ ከፍ ማድረግ፣ ከዚያም መንግሥትን ጫና ውስጥ ማስገባት፤ መንግሥት አፋጣኝ ምላሽ አልሰጠም ተብሎም ሕዝብ በመንግሥት ላይ ትችትና ተቃውሞ እንዲያነሳ ማድረግ ፤ ቀጥሎም ለሕዝብ ችግር የማይደርስ ግድ የሌለውና አቅመ ደካማ የሆነ መንግሥት ተደርጎ እንዲታይ ማደረግ ነው፡፡ እንግዲህ ለዚህ ነው የአደጋ ስጋትና ችግርን ይፈታል ተብሎ የተቋቋመው ‹‹ብሄራዊ የአደጋ ስጋትና ሥራ አመራር ኮሚሽን›› አደጋ መፍታቱን ትቶ አደጋ ፈጣሪ የሆነው፡፡ ይህ ሲባል ግን ችግሩ የተቋሙ ነው ማለት አይደለም፤ ይልቁንም ተቋሙን ሲመሩ የነበሩትን የበላይ አመራር ማለት እንጂ፡፡
በተመሳሳይ በአዲስ አበባ ከተማ ኮንዶሚኒየም ቤቶች እጣ አወጣጥ ላይ የተፈጸመው ማጭበርበርም ከዚሁ ጋር የሚዛመድ ነው፡፡ ጥፋቱን የፈጸሙት ፖለቲካዊም ሆነ ኢኮኖሚያዊ ፍላጎት ያላቸው ግለሰቦች እንጂ መንግሥት አይደለም፡፡ መንግሥት ቢሆንማ ኖሮ የእጣውን መጭበርበርና መሰረዝ ይፋ አድርጎ ዳግም ትክክለኛ እጣ ለማካሄድ ባልተዘጋጀ ነበር፡፡ ይልቅስ እንዲህ አይነቱ ጉዳይ መንግሥት ከታጠቁ ሃይሎች ጋር ብቻ ሳይሆን በጉያው ከተሰገሰጉት ከሃዲዎች ጋርም እየታገለ ስለመሆኑ አንድ ማሳያ ሊሆን በተገባ ነበር፡፡ ጠላት አስርጎ ባስገባቸው አባላቱ የመንግሥትን አሠራር ለማበላሸትና መዋቅሩን ለማዳከም የሚደርገውን ሴራ እየተመለከትን ከመንግሥት ጎን ቆመን መታገል ሲገባን መንግሥትንና በጉዳዩ እጃቸው የሌለበትን የመንግሥት አመራሮች እየተቸን የጠላት አጀንዳ አስፈጻሚዎች ልንሆን አይገባም፡፡
ምክንያቱም አጥፊዎቹ ምንም እንኳን በመንግሥት ተቋማት ውስጥ በሃላፊነት ተመድበው የሚሠሩ ቢሆንም ግለሰቦች እንደመሆናቸው፤ የግለሰቦችን የተበላሸ አስተሳሰብና አሠራር የመንግሥት ጥፋት አድርጎ መመልከት ተገቢ አይሆንም፡፡ ካለንበት የሽግግር ወቅት አንጻር የተለያየ ፖለቲካዊ ፍላጎት ያላቸው ግለሰቦች በየተቋማቱ መኖራቸውን መርሳት አያስፈልግም፡፡ የሚመለከተው አካል ተቋማትን እየፈተሸ ተገቢ ሰዎችን በተገቢው ቦታ የማስቀመጥ ሃላፊነቱን ግን መወጣት ይኖርበታል፡፡ መንግሥት ሥራውን ይሥራ፤ እኛም እናግዘው፤ ያን ጊዜ ሰላማችንን እና እድገታችንን ማረጋገጥ እንችላለን፡፡ ከዚያ ውጭ ግን በየቢሮው ከጠላት በተሰጣቸው ተልእኮ መሰረት ሕዝብና መንግሥትን ለማለያየት የሚሰሩ አካላት በተጋለጡ ቁጥር መንግሥትን ተባባሪና ደጋፊ ማድረጋችን ወይም በጉዳዩ የሌሉ ሹመኞችን መውቀሳችን ‹‹ላም ባልዋለበት ኩበት ለቀማ›› ይሆንብናል፡፡ ከዚህም በላይ ጠላት በቀደደልን ቦይ ሰተት ብለን እየፈሰስን መሆኑን በማወቅ በጉዟችን ሁሉ ምክንያታዊ እንሁን፡፡
ሜላት ኢያሱ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 27 ቀን 2014 ዓ.ም