አዲስ አበባ፡- መንግስት በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ዙሪያ ተጨባጭ፣ አግባብነት ያላቸው መረጃዎችን በወቅቱ ባለመስጠቱ የህዝባዊ ተሳትፎው እንዲቀዛቀዝ በማድረግ ረገድ ትልቅ ድርሻ እንደነበረው ተገለጸ።
አዲስ ዘመን ያነጋገራቸው የታላቁ ህዳሴ ግድብ ህዝባዊ አስተባበሪ ምክር ቤት አባላትና የመስኩ ባለሙያ እንደተናገሩት፤ ሁሉም ኢትዮጵያዊ የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ከተበሰረበት ዕለት ጀምሮ በባለቤትነት ሲሳተፍና የራሱን አሻራ ሲያሳርፍ ቆይቷል። ይሁንና ውሎ ሲያድር ግን መንግስት ፕሮጀክቱ የአፈፃፀም ችግር እንዳጋጠመው እያወቀ የተዛባ መረጃ በማስተላለፉና በወቅቱም እውነታውን ባለማሳወቁ የህዝቡ አመኔታው እንዲሸረሸር አድርጓል ብለዋል።
የምስራቅ ናይል የቴክኒክ አህጉራዊ ፅህፈት ቤት ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ፈቅ አህመድ ነጋሽ እንደተናገሩት፤ ግንባታው ከመዘግየቱ ጋር ተያይዞ በተለይም ካለፉት ሁለት ዓመታት ወዲህ በመንግስት ኃላፊዎች በተለያየ መንገድ ሲለቀቁ የነበሩት መረጃዎች የግድቡ ግንባታ ያለውን አገራዊ ፋይዳ ብሎም በህዝቡ ላይ የፈጠረውን የአንድነት ስሜት ከግምት ውስጥ ያስገቡ አልነበሩም። «ሁሉም ህዝብ የየራሱን አሻራ ያሳረፈበት ግድብ እንደመሆኑ ስለአፈፃፀሙ በቂና ትክክለኛ መረጃ የማግኘት መብት ቢኖረውም መረጃዎቹ የሚተላለፉበት መንገድ በጥንቃቄ አልታዩም» ብለዋል።
«በጣም የሚያሳዝነው ደግሞ እውነታው አፈትልኮ እስከሚወጣ ድረስ ግድቡ በቅርቡ ይጠናቀቃል፤ በከፊል ሃይል ያመነጫል የሚሉ መረጃዎች ይሰጡ ነበር። ይህ ሆኖ ሳለ ድንገት ግንባታው እንደተጓተተ በመነገሩ ህዝቡን በከፍተኛ ደረጃ ተስፋ እንዲቆርጥ አድርጎታል» ያሉት አቶ ፈቅ አህመድ፤ ይህም የሚመለከታቸው የመንግስት አካላት ኃላፊነታቸውን በሚገባ ካለመገንዘብ እንደሚመነጭ ጠቅሰው፣ ያደረሰው ጉዳት ግን በቀላሉ ሊታይ የማይችል መሆኑን አስረድተዋል።
በመሆኑም መንግስት የህዝቡን አመኔታ ለማግኘት ዳግመኛ በእውነታ ላይ የተመሰረተ፣ በአግባቡ የተጠናና ጥቅሙና ጉዳቱ በግልፅ የተለየ መረጃ ማስተላለፍ ይገባዋል ሲሉ አሳስበዋል። ህዝቡም ለቦንድ ግዥ የከፈለውን ገንዘብ ለማውጣት ከመፈለግ ይልቅ በባለቤትነት ስሜት የግድቡን አፈፃፀም መከታተል፣ መደገፍና ጠያቂ መሆን እንደሚገባም አስገንዝበዋል።
የታላቁ ህዳሴ ግድብ ህዝባዊ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ምክር ቤት አባል እና የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ምክትል ፕሬዚዳንት አትሌት ገብረእግዚአብሄር ገብረማርያም በበኩሉ፤ ግድቡ በአገሪቱ ላይ ህብረ ብሄራዊነት የፈጠረ በህዝቡ ህሊና ትልቅ ስፍራ ያለው አገራዊ ፕሮጀክት ሆኖ ሳለ አንዳንድ የመንግስት ኃላፊዎች በእውነታ ላይ ያልተመሰረተ መረጃ በመስጠት በህዝቡ ላይ ውዥንብር መፍጠራቸውን አስረድቷል።
በግንባታው አፈፃፀም ዙሪያም ሲሰጡ የነበሩት መረጃዎችም እርስ በርሳቸው የሚጣረሱ መሆናቸውን ያስታወሰው አትሌት ገብረእግዚአብሄር፤ ይህም የህዝቡን እምነት በመሸርሸሩ ከዚህ ቀደም ያደርግ የነበረውን ሁለንተናዊ ተሳትፎ እንዲገድብ ምክንያት መሆኑን ጠቅሷል።
«አንዳንድ የመንግስት ኃላፊዎች በግድቡ አፈፃፀም ማነስ ራሳቸው ተጠያቂ ሆነው ሳለ፤ እንደ መሪም አቅጣጫ የማሳየት ኃላፊነት እያለባቸው ግድቡ እስከ አስር ዓመት ላይጠናቀቅ ይችላል የሚሉ ተስፋ አስቆራጭ ንግግሮችን በመናገር ህዝቡ የነበረውን የባለቤትነት ስሜት እንዲያጣ አድርገውታል» ብሏል።
በመሆኑም በግድቡ ላይ የተሸረሸረውን የህዝብ አመኔታና ተሳትፎ ወደ ነበረበት ለመመለስና ግንባታው ከግብ እንዲደርስ መንግስት ትክክለኛ መረጃ በወቅቱና በአግባቡ በመስጠት የማነቃቃት ስራ መስራት እንደሚጠበቅበት አስገንዝበዋል። በዚህ ረገድ መገናኛ ብዙኃንም ለሌሎች ወቅታዊ ጉዳዮች ከሚሰጡት ትኩረት በላይ አገራዊ ፋይዳውን ተገንዝበው ሰፊና ተከታታይ ሽፋን ሊሰጡት እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ህዝባዊ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ምክር ቤት ጽህፈት ቤት ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ሮማን ገብረስላሴም የተነሳውን ሃሳብ እንደሚጋሩት ጠቅሰው፤ በተለይም የአፈፃፀሙ ደረጃ ልዩነት በህዝቡ ዘንድ ከፍተኛ ጥርጣሬ አሳድሮ እንደቆየ አስረድተዋል። በዋናነትም በሜቴክ ይሰራ የነበረው የኤሌክትሮ ሜካኒካል ስራ መዘግየት ጉዳይ በወቅቱ ለህዝቡ ይፋ አለመደረጉ በህዝቡ ዘንድ ቅሬታ እንዳስከተለም ተናግረዋል።
«በፕሮጀክቱ መዘግየት ምክንያት 48 በመቶ የሆነው ህዝብ ግድቡን መንግስት ራሱ ሊቀጥለው ይገባል የሚል እምነት መያዙን ያደረግነው ጥናት ያሳያል» የሚሉት ወይዘሮ ሮማን፣ የተቀረው ህዝብ ግን የተከፈለው መስዋእትነት ተከፍሎ ግድቡ ሊቀጥል ይገባል የሚል እምነት እንዳለው ተናግረዋል። በተጨማሪም በ2011ዓ.ም ስድስት ወራት ብቻ 484 ሚሊዮን ብር የሚሆን ቦንድ መገዛቱ አብዛኛው ህዝብ ግድቡ ከዳር እንዲደርስ ያለውን ፅኑ ፍላጎት የሚያሳይ እንደሆነም አስረድተዋል።
«መንግስት ለግድቡ ግንባታ በቂ ትኩረት እየሰጠ አይደለም» ተብሎ የተነሳው ሃሳብ በተወሰነ መልኩ አግባብነት ያለው መሆኑን ጠቁመው፤ ይህም የሆነው በአገሪቱ ባለፉት ሁለት ዓመታት ተከስቶ በነበረው የፖለቲካ አለመረጋጋት ምክንያት ለሰላምና ማረጋጋቱ ስራ ቅድሚያ በመስጠቱ እንደሆነም አስረድተዋል። ይሁንና መንግስት ግድቡ ከተጀመረበት ዕለት ጀምሮ የአስተዳደርና የግልፀኝነት ችግር መኖሩን አምኖ እንደታሰበው በአጭር ጊዜ ውስጥ በማጠናቀቅ ሰፊ ርብርብ እያደረገ መሆኑን አስረድተዋል።
ፅህፈት ቤቱም ገቢ ከማሰባሰብ ይልቅ የተዳከመውን የህብረተሰብ ተሳትፎ ለማነቃቃት ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ በመሆኑ፤ በዋናነት የተሸረሸረውን ህዝባዊ አመኔታ ለመመለስ የሚያስችሉ ተግባራት በተከታታይ እየተሰራ መሆኑን አስገንዝበዋል።
የታላቁ ህዳሴ ግድብ ማስተባበሪያ ምክር ቤት ፅህፈት ቤት መረጃ እንደሚያመለክተው የግድቡ ግንባታ አፈፃፀም 66 በመቶ የደረሰ ሲሆን እስካሁን 98 ቢሊዮን ብር ወጪ ተደርጓል። ከዚህ ውስጥ 12 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር እንዲሁም በውጭ ከሚገኙ ኢትጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን 46 ሚሊዮን ዶላር የቦንድ ግዥ በመፈፀም ድጋፍ አድርገዋል። በቀጣይም ግድቡን ሙሉ ለሙሉ ለማጠናቀቅ እስከ 130 ቢሊዮን ብር ያስፈልጋል ተብሎ ይጠበቃል።
አዲስ ዘመን ቅዳሜ መጋቢት 21/2011
በማህሌት አብዱል