ወላይታ ሶዶ፡- ከተረጂነትና ከጠባቂነት አስተሳሰብ የተላቀቀ ሀገር የሚያለማ ማህበረሰብ ለመፍጠር የሁሉም ባለድርሻ አካላት ቁርጠኝነትና በቅንጅት መሥራትን የሚጠይቅ መሆኑን በግብርና ሚኒስቴር የምግብ ዋስትና ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት አማካሪ ወይዘሮ ሰዒዳ ከድር አስታወቁ።
ወይዘሮ ሰዒዳ ከድር ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንዳስታወቁት፤ መንግሥት በልማታዊ ሴፍቲኔት ፕሮግራም የዜጎችን የምግብ ክፍተት ከመሙላት ባሻገር ከተረጂነት እንዲወጡና ሥራ ፈጥረው ሀገር እንዲያለሙ ከፍተኛ ትኩረት ሰጥቶና በጀት መድቦ እየሠራ ነው። በዚህም አበረታች ውጤቶች ቢገኙም የጠባቂነት አስተሳሰቡን በሚፈለገው ደረጃ መቅረፍ አሁንም ትኩረት ይሻል።
እንደ እርሳቸው ገለጻ፤ የገጠር ልማታዊ ሴፍትኔት ፕሮግራሙ በ1997 ዓ.ም ከተጀመረ ወዲህ የኅብረተሰቡን የምግብ ክፍተት ከመሙላት ባሻገር የተጠቃሚዎችን የኑሮ ሁኔታ ለማሻሻል የሚያስችሉ በርካታ ተግባራትን አከናውኗል። በተለይም ማህበረሰቡ በመንግሥት የሚደረገውን ድጋፍ ተጥቅሞ በቤተሰብ ደረጃ ጥሪት በመፍጠር ኑሮውን እንዲያሻሽል በተደረገው ጥረት አበረታች ውጤቶች ተመዝግበዋል።
ሦስት ነጥብ ዘጠኝ ሚሊዮን የገጠር ልማታዊ ሴፍትኔት ተጠቃሚዎችን ከመርሀ ግብሩ ማስመረቅ መቻሉን አመልክተው፤ይህ እንዳለ ሆኖ “ባለፉት አራት ምእራፎች የተመዘገቡ ውጤቶች ቢኖሩም የማስፈፀም አቅም ውስንነት፣ በኃላፊነትና በተጠያቂነት መንፈስ ሥራን ያለማከናወን ችግሮች ተስተውለዋል” ብለዋል፡፡
በተጨማሪም በሌሎች የልማት ፕሮግራሞች የሴፍትኔት ተጠቃሚዎችን አካታች ያለማድረግና ትስስር መፍጠር ያለመቻሉ ጎልተው የታዩ ክፍተቶች መሆናቸውን አማካሪዋ አመልክተዋል። ከዚህም ባሻገር ተደጋጋሚ የተፈጥሮ አደጋ መከሰቱና የብድር አቅርቦት እጥረት ማጋጠማቸው የመርሃ ግብሩ አፈፃፀም ላይ የራሱ አሉታዊ ተፅዕኖ እንደነበረው አንስተዋል፡፡
በዘንድሮ ዓመት የትግበራ ዘመኑ በሚጠናቀቀው አምስተኛው የመርሃ ግብር ምዕራፍ ከቀደሙት ዓመታት የተገኙ ተሞክሮዎችን በመቀመር፣ ለውጦችን በማጠናከር በተለየ መልኩ የወደፊት አቅጣጫ ተቀምጦለት ጭምር መቀረፁን ወይዘሮ ሰዒዳ አስገንዝበዋል፡፡
በየአንዳንዱ የምዕራፉ ዓመታት መንግሥት ለመርሃ ግብሩ የሚያደርገውን ትኩረትና ድጋፍ እያሳደገ መምጣቱን ጠቁመው፤ በተለይም ዘንድሮ “ከተረጂነት ወደ ምርታማነት” በሚል መርሆ ከምግብ ዋስትና ድጋፉ በተጓዳኝ ራሳቸውን ችለው ከተረጂነት የሚላቀቁ የኅብረተሰብን ቁጥር ከፍ ለማድረግ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራ መሆኑን አብራርተዋል፡፡ ዘላቂነት ያለው ውጤት እንዲመጣና ሀገር የሚያለማ ማህበረሰብ ለመፍጠር ሁሉም ባለድርሻ አካለት ኃላፊነታቸውን ሊወጡ እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡
በዘንድሮው ዓመት ዋነኛው ትኩረት በማህበረሰብ ሥራ ከተፈጥሮ ሀብት ጥበቃው በተጨማሪ በውሃ ማሰባሰብ ሥራ እና በአነስተኛ መስኖ ሥራ ላይ ትኩረት መስጠቱን አማካሪዋ አስገንዝበዋል፡፡
እንዲሁም ከቤተሰብ የኑሮ ማሻሻያ መርሃ ግብር ጋር በማስተሳሰርና የአንድ ጊዜ ድጋፍ ተጠቃሚ በማድረግ፣ የብድር አገልግሎት በመስጠትና ተጠቃሚዎቹ ጥሪት በመፍጠር ከፕሮግራሙ እንዲመረቁ ማድረግ መሆኑንም አብራርተዋል።
ከምግብ ዋስትና ማስተባበሪያው ጽሕፈት ቤት ያገኘነው መረጃ እንደሚያመለክተው፤ የልማታዊ ሴፍቲኔት ፕሮግራም መርሃ ግብር በ11 ክልሎች በ492 ወረዳዎች የሚገኙ ስምንት ሚሊዮን ተጠቃሚዎችን አካቶ እየተሠራ ይገኛል፡፡ ከዚህ ውስጥ 85 በመቶ በማህበረሰብ ሥራ ላይ የተሰማሩ ሲሆን ቀሪው 15 በመቶ ቀጥታ ተጠቃሚዎች መሆናቸው ታውቋል፡፡
ዘንድሮ ለሴፍቲኔት ማስፈፀሚያ 80 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር የተመደበ ሲሆን፤ ከዚህ ውስጥ 45 ቢሊዮን ብር በመንግሥት የተመደበ ነው፡፡ ቀሪው 35 ቢሊዮን ብር ደግሞ ከዓለም ባንክና ከሌሎች ለጋሽ ሀገራት የተገኘ መሆኑ ተገልጿል፡፡
ማህሌት አብዱል
አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 13 ቀን 2017 ዓ.ም