በሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች የተወገዘው የዓለም ዋንጫ

የዓለምን እግር ኳስ የሚመራው ፊፋ እአአ በ2030 እና 2034 የዓለም ዋንጫ አዘጋጅ ሃገራትን ማሳወቁን ተከትሎ ትችቶችን በማስተናገድ ላይ ይገኛል። ትችቱ በተለይ ያተኮረው ደግሞ የሳውዲ አረቢያ እአአ የ2034ቱን ዓለም ዋንጫ አዘጋጅነት መረከብ ላይ ሲሆን፤ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች ተቃውሞውም አይሏል። በሃገሪቷ ያለው በረሃማ የአየር ሁኔታ የቅሬታው ሌላኛው አካል ቢሆንም ፊፋ ኳታር ላይ እንዳደረገው የዓለም ዋንጫ የሚካሄድበት ወቅት ላይ ማስተካከያ እንደሚያደርግ አስታውቋል።

ሳውዲ አረቢያ ዓለም ዋንጫን የማስተናገድ ዕድል ያገኘች ሁለተኛዋ የመካከለኛ ምስራቅ ሃገር (አረብ ሃገር) ሆናለች። እአአ በ2022 ዓለም ዋንጫን በስኬት ያካሄደችው ኳታር በዝግጅት ወቅት መሰል ወቀሳ ሲቀርብባት ነበር። ይሁንና የውድድሩ ባለቤት ፊፋ ምንም ዓይነት እርምጃም ሆነ ማስተካከያ ሳይወስድ በስኬት ሊጠናቀቅ ችሏል። በሳውዲ ላይ እየተነሳ ያለው ነቀፋና እግር ኳስን የሚመራው አካል ዝምታም ተመሳሳይ አካሄድን የተከተለ ይመስላል። የፈርጣማ ኢኮኖሚ ባለቤቷ ሃገር ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በቢሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ በስፖርት ላይ እያፈሰሰች ትገኛለች። በተለይ ጎልፍ፣ ቦክስ፣ የሞተር ስፖርት እንዲሁም በኢንተርኔት የሚደረጉ ስፖርታዊ ውድድሮች ላይም አተኩራለች።

የሳውዲ ባለሀብቶች በተለይም ንጉሳዊ ቤተሰቦች በተወዳጁ ስፖርት እግር ኳስም በተመሳሳይ ከፍተኛ መዋዕለ ነዋይ በማፍሰስ እንደ ኒውካስትል ዩናይትድ ያሉ የእንግሊዝ ፕሪምየር ሊግ ክለቦችን መግዛታቸው ይታወቃል። በሊጋቸው ውስጥም እንደ ክርስቲያኖ ሮናልዶ፣ ካሪም ቤንዜማ እና ኔይማር ያሉ እግር ኳስ ዓለም ከዋክብትን በውድ ዋጋ ወደ ክለቦቻቸው መቀላቀላቸውም የሚታወቅ ነው። ይህንን ተግባር እየመሩ የሚገኙት አልጋ ወራሹ ልኡል መሐመድ ቢን ሰልማን ደግሞ ከፊፋው ፕሬዚዳንት ጂያኒ ኢንፋንቲኖ ጋር ጥብቅ ጓደኝነት መመስረታቸው የአደባባይ ምስጢር ነው።

ከገልፍ ሃገራት ጋር ወዳጅነታቸውን ያጠናከሩት ፕሬዚዳንቱ በሙስና እና የአሰራር ብልሽት ለሕይወት ዘመን ከስፖርት የታገዱትን የቀድሞ የእግር ኳስ ቁንጮ ሴፕ ብላተርን አሰራር ለመከተላቸው ማሳያ ተደርጎባቸዋል። ኢንፋንቲኖ የዓለም ግዙፉን ስፖርታዊ ውድድር የማስተናገድ ኃላፊነትን ለሁለተኛ ጊዜ ለአረብ ሃገር የሰጡ ሲሆን፤ ሳውዲ ባለፈው ዓመትም የፊፋ ክለቦች ዓለም ዋንጫን ማስተናገዷ የሚታወስ ነው። በሌላ በኩል መንግስታዊው ግዙፍ የነዳጅ ድርጅት አራምኮ ፊፋን ስፖንሰር ማድረጉም ከዚሁ ጋር ሊያያዝ የሚችል ጉዳይ ነው። እአአ ከ2021 አንስቶ ባሉት አራት ዓመታት ውስጥም 5ቢሊየን ዶላር ለስፖርት ኢንቨስትመንት ብቻ ወጪ ያደረገች ሲሆን፤ ለዓለም ዋንጫው አንድ ከተማን ጨምሮ 15 የሚሆኑ ስታዲየሞችን በአምስት ከተሞቿ ላይ እንደምታስገነባም ይጠበቃል።

አምንስቲ ኢንተርናሽናል ባለፈው ወር ባወጣው መግለጫው ፊፋ የውድድር አዘጋጁን ሃገር ከማሳወቁ አስቀድሞ በጉዳዩ ላይ እንዲያጤን በተደጋጋሚ ማሳሰቡን የፍራንስ 24 ዘገባ ያትታል። የሳውዲ አረቢያ ንጉሳዊ አስተዳደር ውድድሩ የሚስተናገድባቸው ስታዲየሞች ግንባታ በሚካሄድበት ሥፍራ ያለውን የሰራተኞች ሰብዓዊ መብት አያያዝ ጨምሮ የመናገር ነጻነት እንዲሁም በሴቶች ላይ የሚደርሰውን የመብት ጥሰት አመላክቶ ነበር። ጆሮ ዳባ ልበስ ያለው ፊፋ ግን ሃገሪቷ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በተለይ በስፖርቱ እያደረገችው ያለውን እንቅስቃሴ ከግምት በማስገባት አዘጋጅነቱን ሰጥቷታል። በዚህም አምንስቲ ኢንተርናሽናል የጀመረውን ንቅናቄ 21 የሚሆኑ ሌሎች መሰል ተቋማት ተቀላቅለውታል። ከእነዚህም ውስጥ የሳውዲ አረቢያ ዳያስፖራ ሰብዓዊ መብት ድርጅት፣ የኔፓልና ኬኒያ ስደተኛ ሰራተኞች ማኅበር፣ ዓለም አቀፍ የንግድ ሕብረት ሥራ ማህበር ተጠቃሽ ናቸው።

የአምንስቲ ኢንተርናሽናል የሰራተኞች መብትና ስፖርት ኃላፊ ስቴቭ ኮክበርን ‹‹የፊፋ ግድየለሽ ውሳኔ የበርካቶችን ሕይወት አደጋ ላይ የሚጥል ነው›› ሲሉም ነው በመግለጫቸው የጠቆሙት። ከዚህ ቀደም መሰል ታላላቅ የስፖርት ውድድርን ያላስተናገደችው ሃገሪቷ በርካታ ስታዲየሞችን በማስገንባት ላይ ትገኛለች። ይህንንም ተከትሎ በተገኘው የሥራ ዕድል ስደተኞች የተሰማሩ ሲሆን ሃገሪቷ ‹‹ቅድሚያ ትሞታለህ ከዚያ እከፍልሃለሁ›› የሚል አካሄድ መከተሏን የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾቹ ጠቁመዋል።

ፊፋ እአአ በ2017 መተዳደሪያ ሕጉ ላይ የሰብዓዊ መብት ፖሊሲን ያካተተ ሲሆን፤ ውድድሮችን ለማስተናገድ ፍላጎት የሚያሳዩ ሃገራትን የሰብዓዊ መብት አያያዝ የሚመዝንበት የራሱ አሰራር አለው። ይሁን እንጂ ገንዘብ ከሞራላዊ ጥያቄ ያመዘነበት የጂያኒ ኢንፋንቲኖ አመራር ቸልታን በመምረጡ ራሱ ያወጣውን ሕግ ሲያከብር አይታይም። እንዲያውም በሳውዲ ያለው የሰብዓዊ መብት አያያ መካከለኛ ደረጃ ላይ ያለ ነው በማለት ጉዳዩን ለማለባበስ ጥረት እያደረገ ነው። በሚሊየን የሚቆጠሩ ስደተኛ ሰራተኞች ያሉባት ሳውዲ ከደሞዝ አከፋፈልና ሌሎች የሰራተኛ መብት መጓደል እስከ ሞት የሚያደርስ የአያያዝ ጥሰቶች ሰለባ መሆናቸውንም ዓለም አቀፍ የመገናኛ ብዙሃን ያመላክታሉ።

ብርሃን ፈይሳ

አዲስ ዘመን  ታኅሣሥ 13 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You