ባለፈው ሳምንት የታኅሳስ ግርግርን አይተናል። የታኅሣሥ ግርግር የፖለቲካ አብዮት እንዲፈጠር በር መክፈቱን እንደ አበባው አያሌው ያሉ የታሪክ ተመራማሪዎች ይናገራሉ። ለሺህ ዘመናት የኖረውን እና ከፈጣሪ ቀጥሎ አይነኬ የነበረውን ንጉሣዊ ሥርዓት ‹‹መንካት ይቻላል እንዴ ለካ?›› የሚል እሳቤ ፈጥሮ ከ14 ዓመታት በኋላ ንጉሣዊ ሥርዓቱ ተገርስሷል።
ለሺህ ዘመናት የኖረውን ንጉሣዊ ሥርዓት የገረሰሰው ደርግ ለዘመናት የኖረውን ‹‹የፊውዳል›› ሥርዓት በሶሻሊዝም (ሕብረተሰባዊነት) ሥርዓት ቀየረው። ይህን ያደረገው ደግሞ ንጉሳዊ ሥርዓቱን በገረሰሰበት በ100ኛው ቀን ከ50 ዓመታት በፊት በዚህ ሳምንት የታኅሣሥ 11 ቀን እና 12 ቀን 1967 ዓ.ም ነበር።
በዛሬው ሳምንቱን በታሪክ ዓምዳችን 50 ዓመታትን ወደ ኋላ መለስ ብለን በዚህ ሳምንት ታኅሳስ 11 እና 12 ቀን 1967 ዓ.ም የተከናወኑ የደርግ የሕብረተሰባዊት ኢትዮጵያ አዋጅ፣ የዕድገት በሕብረት የዕውቀትና የሥራ ዘመቻ እና ሌሎች የደርግ እንቅስቃሴዎችን እንቃኛለን።
ከዚያ በፊት ግን ሁለት የዚህ ሳምንት ታሪኮችን እናስታውስ። ከ88 ዓመታት በፊት በዚህ ሳምንት ታኅሳስ 12 ቀን 1929 ዓ.ም ፋሺስት ኢጣሊያ ኢትዮጵያን በወረረችበት ወቅት ለሀገራቸው ክብርና ነፃነት በአርበኝነት ሲታገሉ የነበሩት ወንድማማቾቹ ደጃዝማች አበራ ካሣ እና ደጃዝማች አስፋወሰን ካሣ ተገደሉ።
በአውሮፓውያኑ የዘመን ቀመር ዲሴምበር 21 ቀን 1972 ለሁለት አሥርት ዓመታት ያህል ቀዝቃዛ ጦርነት ሲያደርጉ የነበሩት ምሥራቅ ጀርመን እና ምዕራብ ጀርመን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ይፋ አደረጉ። ይህ ታሪካዊ ስምምነታቸው ተሳክቶ ምዕራብና ምሥራቅ ጀርመን ለማዋሃድ በቁ። የተዋሀዱበትን ጊዜም በመስከረም ወር በየዓመቱ በደማቁ ያከብሩታል።
በዝርዝር ወደምናየው የእድገት በሕብረት የዕውቀትና የሥራ ዘመቻ ታሪክ እንለፍ።
የታሪክ ተመራማሪው ፕሮፌሰር ባሕሩ ዘውዴ በዚህ በታኅሳስ ወር አጋማሽ አካባቢ የነበሩ የሕብረተሰባዊት ኢትዮጵያ አዋጅና አጠቃላይ እንቅስቃሴዎችን በተመለከተ የሚከተለውን ታሪክ ጽፈዋል።
በ1966 ዓ.ም አጋማሽ ላይ አራተኛ ክፍለ ጦር መሽገው፤ የሀገሪቱ የወደፊት ዕጣ ፈንታ ምን ይሁን ብለው ሲመክሩ፣ ሳይንሳዊ ሶሻሊዝምን በኢትዮጵያ ውስጥ ሰርጎ የማስገባቱ ጉዳይ ከአብዛኛዎቹ ሕሊና እጅግ የራቀ ነበር።
መመሪያቸው ያደረጉት «ኢትዮጵያ ትቅደም›› የሚለው መፈክር ግፋ ቢል አገር ወዳድነትን የሚጠቁም ነበር። በታኅሣሥ ወር በአብዛኛው የእድገት በኅብረት ዘማቾችን ለማስደሰት ሲባል ወደ ‹‹ኅብረተሰብዓዊነት» ሲጎለምስም ዓላማው ኢትዮጵያዊ ሶሻሊዝምን እንጂ ሳይንሳዊ ሶሻሊዝምን ለማስረፅ አልነበረም። ይሁንና ደርግ ፈራ ተባ ሲል የያዘው የሶሻሊስት ፈር ወደፊት የሚከተለውን የርዕዮተ ዓለም አቅጣጫ አመልካች ነበር።
ያንን ፈር መልቀቁ እያደር አስቸጋሪ ብቻ ሳይሆን የማይታሰብ እየሆነ መጣ። የዚህንም ዋነኛ ምክንያት ለመረዳት ተማሪዎች በኢትዮጵያ አብዮት አመጣጥና ሂደት ላይ የነበራቸውን ወሳኝ ሚና ማጤን ያስፈልጋል። እንደ እውነቱ ከሆነ መለዮ ለባሹ በየካቲት 1966 ያለው በአመዛኙ ከሙያው ጋር የተያያዙ ብሶቶችን ይዞ ነው። የደመወዝ ጭማሪ፣ የኑሮ ሁኔታ መሻሻል፣… ወዘተ ማለት ነው።
ጥቅማቸውን አስከብረው ወደ ካምፓቸው ለመመለስ ሲያስቡ «ወቴ {ወታደር} ደሞዟን አስጨምራ ወደ ካምፕ ተመለሰች›› የሚለው የተማሪዎችና የሌሎች ሲቪል ወገኖች ጉንተላ፣ ሹፈትና ወቀሳ ነው መለዮ ለባሹን ወደ ፖለቲካው መድረክ የገፋፋው። እያደርም ደርግ ሥልጣን ለመያዝ ብቻ ሳይሆን በሥልጣን ላይ ለመቆየት ከፈለገ እየገነነ ከመጣው ማርክሳዊ ርዕዮት ውጭ አማራጭ ሕዝባዊ አመፅ እንደሌለው እየተገነዘበ መጣ።
ከ1966 እስከ 1968 ድረስ ባሉት ሁለት ዓመታት ደርግ ከዚህ ርዕዮት ጋር ለመተዋወቅ ብቻ ሳይሆን ከማንም ያላነሰ ክሕሎት አለኝ ለማለት ያላሰለሰ ጥረት ማድረግ ነበረበት። ሁልጊዜ አንድ እርምጃ ወደፊት ቀድሞ ከሚገኘው የግራ ክንፍ ኃይል ጋር ለመስተካከልና ብሎም ለማለፍ የነበረው ትግልና ጥረት ቀላል አልነበረም፤ ጥረቱም ተሳክቶ በሚያዝያ 1968 ዓ.ም ደርግ የመጨረሻውን ርዕዮተ ዓለማዊ እመርታ በማድረግ፣ የብሔራዊ ዴሞክራሲያዊ አብዮትን በመመሪያነት አወጀ። በዚህ ድርጊቱም እየቀደመ ሲያስቸግረው ከነበረው የግራ ክንፍ የፖለቲካ ቡድን ጋር ተስተካከለ ማለት ይቻላል። ከዚያ የሚቀጥለው እርምጃ ራሱን የሠፊውንና የጭቁኑን ሕዝብ ትግል በግንባር ቀደምነት ለመምራት በታሪክ የታጨ ብቸኛ የፖለቲካ ኃይል አድርጎ ማየቱ ነው።
ይህን አስደናቂ የደርግ የርዕዮተ ዓለም ጉዞ ካሰመረለት አንዱ፤ የግራ ክንፉ ተከፋፍሎ ወደ አብዮቱ መድረክ መውጣት ነው። በተለይም ከሀገር ውጭ የሚገኘው የተማሪው ንቅናቄ አካል አብዮቱ ሲፈነዳ በሁለት አክራሪ ጎራዎች ተሰልፎ ነበር። ኋላ ገሀድ እንደ ወጣው እነዚህ ሁለት ጎራዎች የኢሕአፓና የመኢሶን ድርጅቶች ተከታዮች ነበሩ። እነዚህ ሁለት አንጋፋ የግራ ክንፍ ኅቡዕ ድርጅቶች በተማሪ ድርጅቶች ሽፋን ደጋፊዎቻቸውን ማብዛትና ማጠናከር ተያይዘው ነበር። በአብዮቱ ዋዜማ ሁለቱ ጎራዎች በዓለም አቀፉ የተማሪዎች ድርጅት አወቃቀር ላይ ሳንጃ ቀረሽ ክርክር እያደረጉ ነበር። የኢሕአፓ ወገኖች በአዲስ መልክ የተዋቀረውን ዓለም አቀፍ የኢትዮጵያ ተማሪዎች ፌዴሬሽን ሲደግፉ፣ የመኢሶን ተከታዮች ደግሞ በቁጥጥራቸው ስር የነበረው ዓለም አቀፍ የኢትዮጵያ ተማሪዎች ማኅበር እንዲቀጥል ይሟገቱ ነበር።
በዚህ ሁሉ ውጥንቅጥ ውስጥ ያለው ደርግ ‹‹ሕብረተሰባዊት ኢትዮጵያ›› ዘመቻውን በተለያዩ ዘርፎች ማጧጧፍ ቀጥሏል።
ታኅሳስ 11 ቀን 1967 ዓ.ም በደርግ ወታደራዊ ምክር ቤት የሕብረተሰባዊት ኢትዮጵያ አዋጅ ሲታወጅ፤ በነጋታው ታኅሳስ 12 ቀን 1967 ዓ.ም ደግሞ የዕድገት በሕብረት የዕውቀትና የሥራ ዘመቻ አዋጅ፤ በአዋጅ ቁጥር 11/1967 ለሕዝብ ይፋ ሆነ።
የዕድገት በሕብረት ዘመቻ ኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለማርያም በተገኙበት በጃንሜዳ በይፋ በተጀመረበት ዕለት (ታኅሳስ 12) የነበረውን ሁነት ገስጥ ተጫኔ ‹‹ነበር›› በተሰኘው መጽሐፉ እንዲህ ያስታውሰዋል።
‹‹ታህሳስ 12 ቀን 1967 የእድገት በኅብረት የዕውቀትና የሥራ ዘመቻ የክተት በዓል በመላ ሀገሪቱ ተከበረ። ለዘመቻው የተዘጋጁ 60 ሺህ ተማሪዎችን የወከሉ የአዲስ አበባ ዘማቾች በዓሉን ለማክበር በጃንሜዳ ተሰለፉ። ሰልፉን ለመጎብኘት እና በዓሉን በጋራ ለማክበር ብርጋዴር ጄኔራል ተፈሪ በንቲና ሻለቃ መንግስቱ ኃይለማርያም በሥፍራው ተገኝተው ነበር። ሰልፈኛው በየተመደበበት የዘመቻ ቀጠና በረድፍ እንደቆመ ጃንሜዳን ከምዕራባዊ ጫፍ እስከ ምስራቃዊ ጫፍ ሞልቶት ነበር። ››
ፍቅረሥላሴ ወግደረስ ደግሞ ‹‹እኛና አብዮቱ›› በሚለው መጽሐፋቸው ሁነቱን ሲገልጹ፤ ‹‹መለዮአቸውን በማውለብለብ በሆታና በጭፈራ ‹‹ቪቫ መንግሥቱ! ‹‹ቪቫ መንግሥቱ!›› እያሉ ሲቃ እየተናነቃቸው በመጮህ አለፉ፤ አንዳንዶቹ የመንግሥቱን እጅ ለመጨበጥ ወደ ትሪቡን የሚመጡ ነበሩ!››
በዚሁ ዕለት ዘማቹ፡-
ፋኖ ተሰማራ
ፋኖ ተሰማራ
እንደ ሆቺ ሚኒ እንደ ቼ ጉቬራ!
በደስታ በዕልልታ እንደሸኘናችሁ
በሳቅ በፈገግታ እንቀበላችሁ
በሕይወት ግቡ በሕይወት
ዘመቻ የምትሄዱ ለዕድገት በሕብረት!
እየተባለ እስከ መስቀል አደባባይ ደረስ ሰልፍ ተደርጓል። ይህ የደርግ የዕውቀትና የሥራ ዘመቻ ሲካሄድ፤ ኢሕአፓንና የትጥቅ ትግል የሚያደርጉ ኃይሎችን የሚደግፉ ወጣቶች ‹‹ደርግ እኛን ገጠር ልኮ እሱ በከተማ ሊጠናከር ነው›› በማለት ዘመቻውን ተቃወሙ። ሌሎች ደግሞ ከሕዝባችን መሐል ገብተን ፊደል ማስቆጠር አለብን በማለት ዘመቻውን ደገፉ።
ፍቅረሥላሴ ወግደረስ እንደሚሉት፤ 60 ሺህ (ቁጥሩ ላይ ልዩነቶች አሉ) የሁለተኛ ደረጃና የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ከመምህሮቻቸው ጋር በመሆን በመላ አገሪቱ በሚገኙ ስድስት ቀጠና ማስተባበሪያ ማዕከላት፣ 57 የክፍለ አገር ማስተባበሪያዎች፣ 517 ምድብ ጣቢያዎችና እያንዳንዳቸው 30 ተማሪዎች ወዳቀፉ ጣቢያዎች ለመላክ ታቅዶ ነበር።
ከአንድ ዓመት በኋላ መንግሥት ያወጣው ሪፖርት ግን ዘማቾች በ51 ማዕከላትና 397 ጣቢያዎች መዝመታቸውን፤ ቁጥራቸውም 48 ሺ ብቻ መሆኑን ይፋ አድርጓል።
የዕድገት በሕብረት የዕውቀትና የሥራ ዘመቻ ዘማቾች በመላ አገሪቱ የገጠር ክፍሎች ተሰማርተው ሥራቸውን ጀመሩ። ገበሬውን በእርሻ ሥራና በዕለት ተዕለት ኑሮው እያገዙት ማንበብና መጻፍን አስተማሩት። ፖለቲካዊ ንቃት እንዲኖረው ለማድረግና መብቱን እንዲጠይቅ አሰለጠኑት። በሂደቱ የራሳቸውን ትግል ጀምረው የፖለቲካ እንቅስቃሴ በማድረጋቸው በርካቶች ታስረዋል።
ቀስ በቀስ ደግሞ በየጣቢያው ነገሮች ከቁጥጥር ውጭ መሆን ጀመሩ። በዚህም በርካቶች ጣቢያቸውን ጥለው ወደ ቤተሰቦቻቸው ተመለሱ። በዚህ ጊዜ ደርግ ‹‹ወደ ዘመቻው ተመለሱ›› ሲል ጥሪ አቀረበ። ጥሪውን ተከትሎም ጥቂቶች ወደ ዘመቻ ተመለሱ። በቁጥር ላቅ የሚሉት ግን ሳይመለሱ ቀሩ።
የዕድገት በሕብረት የዕውቀትና የሥራ ዘመቻ በመላ አገሪቱ ለሁለት ዓመታት ያህል የዘለቀ ነበር። የመጀመሪያው ዙር ዘመቻ በወጉና በሥርዓቱ እንዳይፈፀምና ሌላ ዙር ዘመቻ እንዳይቀጥል ኢሕአፓ ተፅዕኖ ሲያደርግ እንደነበር የተለያዩ ጸሐፍት እና በወቅቱ የታተሙ የፓርቲው (ኢሕአፓ) ልሳን ጋዜጣ ጽሑፎች ያሳያሉ።
በኢሕአፓ፣ በሕወሓት እና በሌሎች በደርግ ላይ ባመፁ የውስጥ ትግሎች፤ እንዲሁም ፕሮፌሰር ባሕሩ ዘውዴ እንደሚሉት ደርግ ከሶሻሊዝም ሳይንስ ይልቅ ሶሻሊዝምን ለማስረፅ በአገር ወዳድነት ስሜት ብቻ በመጓዙ ሊሆን ይችላል የደርግ ሥርዓት መቀጠል ሳይችል ቀረ።
ታኅሳስ 11 ቀን 1967 ዓ.ም የታተመው ‹‹ዘ ኒው ዮርክ ታይምስ›› የተሰኘው የአሜሪካ ዕለታዊ ጋዜጣ ይህን የደርግ የሕብረተሰባዊነት (ሶሻሊዝም) አዋጅ አስመልክቶ ሰፊ ሐተታ አውጥቷል። ሙሉ መረጃው እንዴት እንደደረሰውና በዕለቱ እንዴት መታተም እንደቻለ ባይታወቅም በዚያ ኢትዮጵያ ውስጥ የኢንተርኔት አገልግሎት በሌለበት ዘመን ጋዜጣው ‹‹ዛሬ›› እያለ ነበር የሚያትት።
ዘ ኒው ዮርክ ታይምስ በወቅቱ እንደዘገበው፤ ደርግ የሕብረተሰባዊነት (ሶሻሊዝም) አዋጅ ያወጀው በአንድ ፓርቲ (አሃዳዊ) ሥርዓት ብቻ ነበር። ሥርዓቱ የማኅበር የግብርና ሥራዎችን መሰረት ያደረገ ቢሆንም የአገሪቱ ሀብቶች ግን በመንግሥት ቁጥጥር ሥር ነበሩ።
እንደ ጋዜጣው ማብራሪያ፤ ‹‹ኢትዮጵያ ትቅደም›› ማለት ሕብረተሰባዊነት ማለት ነው። ሕብረተሰባዊነት ማለት ደግሞ የራስን ዕጣ ፋንታ መወሰን መቻል፣ የመሥራት እና ሀብት የማግኘት መብት ማለት ነው። ይህም ‹‹ፊውዳል›› ይባል የነበረውን የባላባትና የከበርቴ ሥርዓት በመናድ ሁሉንም እኩል የማድረግ ሥርዓት ማለት ነው።
በዚሁ ጋዜጣ ዘገባ፤ የደርግ ምክር ቤት የውጭ ባለሀብቶች (ኢንቨስተሮች) የአገሪቱን የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ስለሚያሳድጉ እንዲገቡ ፈቅዷል። ወደ ሀገር ውስጥ የሚገቡ ምርቶች ለአገር አደገኛ ከሆኑ ግን በጥብቅ የተከለከሉ መሆናቸውንም አሳውቋል። የውጭ ግንኙነትን በተመለከተ ከጎረቤት አገራት በተለይም ኬንያ፣ ሶማሊያ እና ሱዳን በጋራ እና በትብብር እንደሚሰራ ቃል ገብቷል።
ወታደራዊ ምክር ቤቱ ሥርዓቱ ብዙ ፓርቲዎች እንዲኖሩት አልፈቀደም ነበር፤ ምክንያት ያደረገውም ከሕዝብ ጥቅም ይልቅ ለግል ጥቅማቸው ይሰራሉ የሚለውን ነው። ብቸኛ የፖለቲካ ድርጅት የነበረው ደርግ ‹‹ተራማጅ ኃይል›› የሚለውን ስብስብ የያዘው ምክር ቤት ብቻ ነው።
ዘ ኒው ዮርክ ታይምስ እንደሚለው፤ የደርግ ምክር ቤት አባላት ከፍተኛ የትምህርት ደረጃ ያላቸው ቢሆኑም በመንግሥታዊ ጉዳዮች ላይ ግን ልምድ የሌላቸው እና የፖለቲካ ግንዛቤያቸው አነስተኛ የሆኑ ናቸው። በዚህም ምክንያት መጨረሻው ጦርነት ሆኗል።
ሁሌም እንደምንለው፤ ታሪክን ስናስታውስ ለመገረሚያነት ወይም ለመዝናኛነት ወይም ለመናደድ ሳይሆን ከጥንካሬውም ሆነ ከድክመቱ ለመማር ይሁን!
ዋለልኝ አየለ
አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 13 ቀን 2017 ዓ.ም