ከተፈጥሮ ጋር ቁርኝት ከልጅነት እስከ እውቀት

የተባበሩት መንግስታት የዓለም አቀፉ የዘረመል ምሕንድስና እና ባዩቴክኖሎጂ ማዕከል የቦርዱ ምክትል ፕሬዚዳንት ናቸው። በባዮና ኢመርጂንግ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት በዋና ዳይሬክተርና በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በመምህርነት ያገለግላሉ። በእጽዋት ዘረመልና ማዳቀል እንዲሁም በባዮ ቴክኖሎጂ ዘርፍ በማማከር እና በምርምር ሥራቸው ይታወቃሉ።

ፕሮፌሰር ካሳሁን ተስፋዬ የኢትዮጵያን የቡና መገኛነትን ለዓለም ያሳወቁ ተመራማሪምና የ2023 በአፍሪካ ውስጥ ባዮ ቴክኖሎጂ ላይ ከፍተኛ አስተዋጾ ያደረጉ በሚል ተመርጠው “የአፍሪካ አሸናፊ” በሚል የተሸለሙ ናቸው። የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተፈጥሮ ሳይንስ ኮሌጅም በ2022 በዓመት ከ24 በላይ የምርምር ሥራዎችን በማሳተም ከፍተኛ አፈጻጸም ያላቸው በሚል ሸልሟቸዋል።

ፕሮፌሰር ካሳሁን የተለያዩ ተቋማትን በመመስረትም ይታወቃሉ። የባዮና ኢመርጂንግ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩትም የእሳቸው አሻራ ውጤት ነው። ሌላው ደግሞ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የባዮ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ሲሆን፤ በዘርፉ የሦስተኛ ድግሪ መርሃግብር በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ እንዲጀመር ያደረጉ ሰው ናቸው። አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ለመጀመሪያ ጊዜ የዳጉሳ ምርጥ ዘርን እንዲያወጣ ያስቻሉ ተመራማሪ እንደሆኑም ይነገርላቸዋል። የፕሮፌሰር ካሳሁን የሕይወት ተሞክሯቸው፣ የትምህርት ዝግጅታቸውና የሥራ ልምዳቸው ብዙዎችን የሚያስተምር በመሆኑ የዛሬው ‹‹ የሕይወት ገጽታ›› አምዳችን እንግዳ አድርገናቸዋል።

የሁሉም ልጅ

በገጠራማዋ፣ በተፈጥሮ በተዋበችው፣ በግብርና ምርቷ በምትታወቀው የአትሌቶች መፍለቂያ አርሲ ዋና ከተማ አሰላ ውስጥ ተወልደው አድገዋል። ተፈጥሮ ለእርሳቸው ሁሉ ነገራቸው ነው። ተፈጥሮ ምግብ፤ አየር፣ መጠለያም ብቻ ሳይሆን ኑሮአቸው የነገ መድረሻቸው ነው። አባታቸው ደግሞ ለዚህ ባህሪያቸውና ተፈጥሮ ወዳድነታቸው ጥንስስ የተውላቸው መሆናቸውን ይናገራሉ።

እርሳቸው ሥራ ሲጀምሩ በግብርና ሰራተኝነት ነበር። አነስተኛ ሔክታር መሬት ላይ የመስክ ተግባራትን ያከናውናሉ። እሁድ ቅዳሜ ሳይሉም ይሰራሉ። ትንሹ ካሳሁንም ትናንሽ ጉዳዮችን በጥልቀት እንዲያዩ እና እንዲመረምሩ እንዲሁም ተፈጥሮን እንዲወዱ የሆኑትም ከዚህ በመነሳት ነው። ከአባታቸው እግር ስር ተከትለው ስለተፈጥሮ እንዲያስቡ ሆነዋል። ይህም የዛሬውን ማንነት አላብሷቸዋል።

‹‹ልጆች ነጭ ወረቀቶች ናቸው›› የሚባለውም ከዚህ የተነሳ ይመስላል። የእንግዳችን አባት ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ሕግ በማጥናታቸው የሕግ ባለሙያ ሲሆኑ፤ ፕሮፌሰር ካሳሁን ግን የትናንቱን አልተውም። ይልቁንም ከተፈጥሮ ጋር አቆራኝተው ቀጥለዋል። በዚህም በልጅነታቸውም ምን መሆን እንደሚፈልጉ ሲጠየቁ መልሳቸው ከተፈጥሮ እና ግብርና አይዘልም ነበር። ይህ ደግሞ ያሰቡት ደረጃ ላይ እንዳደረሳቸው ትናንትን በትውስታ አጫውተውናል።

እንግዳችን በልጅነት እድገታቸው የሁሉም ማኅበረሰብ ጡብ ያረፈባቸው ናቸው። ከአባታቸው ሲጀመር ዛሬያቸውን ሰጥተዋቸዋል፤ ቆራጥነትን፤ ዘወትር መስራትን ተምረውባቸዋል። ከእናታቸው ደግሞ ትህትናን፤ ለሰው ማዘንንና ደግነትን፤ ከእህቶቻችው ርህራሄን ተምረው የሕይወት መርሃቸው አድርገዋል። በየደረጃው ከአስተሯቸው መምህሮቻቸውም የወሰዱት ብዙ ነገሮች አሉ። ዋና ዋናዎቹ ያለን እውቀት ሳይሰስቱ መስጠትንና ዋጋ ከፍሎ ለተማሪዎቻቸው ውጤታማነት መስራት የሚሉት ናቸው።

ፕሮፌሰር ካሳሁን በዘወትር ንግግራቸው ውስጥ አንድ ቃል አይጠፋም ‹‹እኔ የብዙዎች ውጤት ነኝ›› የሚል። ትናንት ጠንካራ ሰራተኛ ፣ የአቋም ሰው መሆንን ከእነዚህ የማኅበረሰብ ክፍሎች ባይማሩ ኖሮ ዛሬ ላይ እንደማይደርሱ ያውቃሉና ስለተደረገላቸው መልካም ነገር ሁሉ ያመሰግናሉ።

በልጅነታቸው ነገሮችን በትኩረት እና በጥልቀት መመልከት ይወዳሉ፤ ይህም ከእፀዋቱ ውጫዊ ገፅታ አልፈው ዘረመል እንዲያጠኑ ሳያደርጋችው እንዳልቀረ ይናገራሉ። ኃላፊነትን ለመቀበል አይቸኩሉም። ነገር ግን ኃላፊነቱን ከተረከቡ የተሰጣቸውን ሥራ ካልጨረሱ እረፍትን አያውቁም። እስከ መጨረሻው ይታገላሉ፤ ውጤቱንም ማየት ይፈልጋሉ። ይህ የሥራቸው ውጤት መጥፎም ቢሆን አይከፉም፤ ይማሩበታል እንጂ። ከዚህ ጋር በተያያዘም የልጅነት አጋጣሚ አላቸው።

ነገሩ እንዲህ ነው። ለቤታቸው ቅርብ የሆነ ዘመናዊ ንብ ማነቢያ አለ፤ በወቅቱ አሰላ ከተማ ቀበሌ 12 የሚገኝ ነው። ልምድ ለመቅሰም በዚህ ብዙዎች ጉብኝት ያደርጋሉ። ለምን የሚለው ጥያቄ ዘወትር ከውስጣቸው ያቃጭል ነበርና አንድ ቀን ከጓደኞቻቸው ጋር በመሆን ማየት እንዳለባቸው ይወስናሉ። ውሳኔያቸውንም በተግባር ለመቀየር ጸጥ ረጭ እስኪል ድረስ ይጠብቃሉ። አስጎብኝ በሌለበትም ነገሮችን በራሳቸው ለማድረግ ወደ ውስጥ ይዘልቃሉ። ለጉብኝት ሁሌ ተመራጭ ወደ ሆነው ዘመናዊ ቀፎ ያመራሉ። ሁሉም በመስተዋት ውስጥ ሆኖ ያያሉ።

እንግዳችንና ጓደኞቻቸው ነገሩን ሳይረዱና ንቦቹ ምን እንደሚያደርጓቸው ሳያውቁ በቀጥታ እንደገቡ የንቦቹን መስተዋት ይከፋፍታሉ። መጀመሪያ ላይ የከፈቱት መስታወት የማር እንጀራው የሚቀመጥበት በመሆኑ ምንም አልሆኑም። ሁለተኛ የከፈቱት መስታወት ግን የንቦቹ መኖሪያ በመሆኑ ንቦቹ ሰፈሩባቸው። ብዙም ሳይጎዷቸው ተሯሩጠው ወደ ቤታቸው ገቡ። ሆኖም ትንሹ ካሳሁን ከሌሎቹ ጓደኞቹ በይበልጥ በንቦቹ ተነድፏል። ከንፈሩ ከሚጠብቀው በላይ አብጦም ነበር። ጥዝጣዜው ደግሞ ይበልጡን አሰቃየው። እያለቀሰ በመሄድም ለእህቶቹ አሳያቸው።

በወቅቱ የእህቶቹ ምላሽ ግን የጠበቀውን አልሆነለትም። ይባሱን አናደደው። ትንሽ ያጽናናው የእናቱ አይዞህ ባይነት ነበር። መደረግ ያለበትን አድርገውለት እንዲቀመጥ ቢታዘዝም ወዲያው ወደ መስታወት ነበር ያመራው። ራሱን ሲመለከተውም በእጅጉ ተገረመ። ራሱ በራሱ ላይ ሳቀ። ይህ ደግሞ እህቶቹን ከማኩረፉ አተረፈው። የሰራው ሥራ የነበረውን የማወቅ ጉጉት የፈጠረበት በመሆኑ አልተጸጸተም። ነገር ግን እህቶቹን ስላስቀየማቸው ይቅርታ ጠየቃቸው።

ትንሹ ካሳሁን ከሚወዳቸው ጨዋታዎች መካከል የእግር ኳስ ግንባር ቀደሙን ይይዛል። ከዚያ በአቅራቢያቸው በሚገኘው ‹‹አርዱ›› የተባለ የግብርና ተክል ደን ውስጥ ከጓደኞቹ ጋር እየተሯሯጠ መጫወት ይመቸዋል። ከፍ እያለ ሲሄድ ደግሞ ምርጫው ተፈጥሮን ማድነቅ፤ ከቻለ በፎቶ ማስቀመጥ ሆነ። በእያንዳንዱ የተፈጥሮ ኡደት ውስጥ የሚኖሩ ክዋኔዎች ለእርሱ ትርጉም ያላቸው መልዕክቶችን ይሰጡታል። በዚህም ከጥናት በኋላ ዘወትር በተፈጥሮ መመሰጥን ሥራው ያደርጋል።

ከጭላሎ እስከ ጀርመን

የፕሮፌሰር ካሳሁን አባት ከፍተኛ የአስም ሕመም ያለባቸው በመሆኑ በአንድ ቦታ ላይ ለረጅም ጊዜ መቆየት አይችሉም። በዚህም የተነሳ ቤተሰቡን ይዘው ከአንዱ ቦታ ወደሌላኛው እንዲዘዋወሩ ግድ ይላቸዋል። ይህ ደግሞ እንግዳችንን በተለያየ ትምህርት ቤት እንዲማሩ አድርጓቸዋል። በሴሚስተር ጭምር ከአንዱ ቦታ ወደ ሌላኛው የሚዛወሩበትን ሁኔታ ነበር። ይሁን እንጂ አብዛኛውን ትምህርታቸውን የተከታተሉት በሁሩታ ከተማ ውስጥ ነው።

ትምህርትን አሀዱ ያሉት በጭላሎ ተራራ ትምህርት ቤት ሲሆን፤ እስከ ሰባተኛ ክፍል የመጀመሪያ ሴሚስተር ድረስ በዚያው ቆይተዋል። ከሰባተኛ ክፍል ሁለተኛ ሴሚስተር በኋላ ደግሞ እስከ 12ኛ ክፍል ድረስ በሁሩታ ከተማ በሚገኘው ሁሩታ አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ትምህርታቸውን ለመከታተል ችለዋል።

ፕሮፌሰር ካሳሁን እስከ አራተኛ ክፍል የደረጃ ተማሪ አልነበሩም። ከክፍል ክፍል ማለፍን እንጂ ለደረጃ ተማሪነት ብዙም ትኩረት አይሰጡም። እንደውም ከዚያ ይልቅ ጊዜያቸውን በጨዋታ ማሳለፍ ያስደስታቸዋል። ከአራተኛ ክፍል በኋላ ግን ነገሮች ተቀየሩ። ሙሉ ትኩረታቸውን ወደ ትምህርታቸውም አደረጉ። ማንበብ ግዴታቸው እንደሆነ አምነውም በእቅድ ወደ መመራቱ ገቡ። ይህ ጥረታቸውም ጎበዝ የሚለውን ስሜት ከተለያዩ አካላት አጎናጸፋቸው። ቤተሰቦቻቸው፤ መምህሮቻቸውና ጓደኖቻቸው ጭምር የሚኮሩባቸው፣ የሚሳሱላቸው ሆኑ።

ጎበዝ መባል ብዙ ትርጎሞችንም እየሰጣቸው መጣና ከክፍል ብቻ ሳይሆን ከትምህርት ቤትም ጭምር የደረጃ ተማሪ ሆነው መገኘት እንዳለባቸው አሳሰባቸው። በዚህም 12ኛ ክፍልን እስኪያጠናቅቁ ድረስ የደረጃ ተማሪ ሆነው ዘለቁ። ይሄ ጉብዝናቸው ዩኒቨርሲቲም ተከተላቸው። የተሻለ ተማሪ ከሚባሉት ጎራ ተመድበውም እስከ ሦስተኛ ድግሪ ድረስ ተማሩ። በዚህም የተለያዩ ሽልማቶችን አገኙ፤ አንዱ የትምህርት እድል ነበርም።

ፕሮፌሰር ካሳሁን የልጅነት ሕልማቸውን ማሳካት እንዳለባቸው ለራሳቸው ቃል ገብተዋል። ለዚህም የተፈጥሮ ሳይንስ ትምህርትን ምርጫቸው አድርገዋል። የትኞቹ ትምህርቶች ወደ ሕልሜ ያደርሱኛል የሚለውን ለይተውም ማጥናት ጀምረዋል። ሌላው ደግሞ በለዩዋቸው ትምህርቶች የተሻለ ውጤት ማስመዝገብ ላይ ነው። እናም ሁሉም ትምህርት ላይ እኩል ብቃት ቢኖራቸውም ከሁሉም ግን ባዮሎጂና ኬሚስትሪ ትምህርቶችን አብልጠው ይወዱና ያነቡ ነበር። ውጤታቸውም በጣም ጥሩ ነበር።

የእንግዳችን የዩኒቨርሲቲ ጉዞ የጀመረው በያኔው የግብርና ዩኒቨርሲቲ በአሁኑ ሐሮማያ ዩኒቨርሲቲ ነበር። ዩኒቨርሲቲውን ሲቀላቀሉ እንደከዚህ ቀደሙ በቀጥታ የትምህርት መስክ የሚመርጡበትን እድል አያገኙም ነበር። ስለዚህም ትምህርት መስክ ለመምረጥ የግድ አንድ ሴሚስተር መማር ይኖርባቸዋል። ከዚህ አንጻርም የመጀመሪያውን ሴሚስተር ሲማሩ ምን ትምህርት መማር እንዳለባቸው ለይተው ለዚያ የሚያበቃ ውጤት ለማምጣት ይታትሩ ነበር።

የተፈጥሮ ሳይንስ ትምህርትን ለመማር ቋምጠው የነበሩት እንግዳችን፤ ከዚህ የተሻለ እድል እንዳላቸው ሲሰሙ መተው አልቻሉም። ምክንያቱም እርሳቸውን ይበልጥ የሚያስደስታቸው አዲስ ነገር መሞከር ነው። እናም በጊዜው አዲስ ትምህርት ክፍል ይከፈታልና ከፍተኛ ውጤት ያላችሁ ተማሪዎች ተመዝገቡ ሲባሉ ፈጥነው ተመዘገቡ። ከእረፍት መልስ ግን ያሰቡት አልሆነም። የትምህርት ክፍሉ በፈንድ ምክንያት መቀጠል እንደማይችል ተነገራቸው። ስለዚህም ወደ ነባር ፍላጎታቸው ተመለሱ። በእጽዋት ሳይንስ የትምህርት መስክም ተምረው የመጀመሪያ ድግሪያቸውን ያዙ።

በእርሳቸው እምነት የትምህርት ዘርፍ መመረጥ ያለበት ልዩ ፍላጎትን በማየት ነው። ይህ ያበላል ብዙ አይመቻቸውም። ዋጋ እንደሚያስከፍላቸውም ያስባሉ። ስለዚህም ምርጫቸውን ሲያስቡ ቀድመው የሚያዩት እወደዋለሁ ወይ የሚለውን ነው። በዚህ ደግሞ ብዙ እንደተጠቀሙ ያምናሉ። ብዙ መልካም አጋጣሚዎችን አግኝተውበታል፤ ረጅም ሰዓት ቆመው በቤተ ሙከራ ውስጥ ሲሰሩም በተመስጦ ስለሆነ እንዳይደክማቸው አግዟቸዋል። ዓላማ ያለው ሥራም እንዲሰሩ እድል የሰጣቸው ሆኖ አግኝተውታል።

ፕሮፌሰር ካሳሁን በሚፈልጉት ትምህርት እስከመጨረሻው መጽናትን ይፈልጋሉ። በዚያ ዘርፍ ስፔሻሊስት መሆንን ያልማሉ። ምክንያታቸው ደግሞ በአንድ ጉዳይ ላይ አመርቂ ውጤት ማምጣት ይቻላል፤ ብቁ ለመሆንም እድል ይሰጣል ብለው ስለሚያስቡ ነው። በዚህም ሁለተኛ ድግሪያቸውን ለመማር ወደ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ሲገቡ በያዙት የትምህርት መስክ ለመቀጠል ነው። ስፔሻላይዝድ ያደረጉትም በአፕላይድ ጀነቲክስ ነው።

የምርምር ሥራቸውም በወቅቱ አዲስና ማንም ያልሰራበትን የአጃ ምርምር (Emmer wheat) ያደረጉትም መሰረታቸው እጽዋት በመሆኑ ነው። የሁለተኛ ድግሪ ትምህርት ትኩረቱ ጥናትና ምርምር ላይ በመሆኑ ምርምራቸውን ሲሰሩ ከሚያውቁት ነገር እንዲነሱ ሆነዋል። በእርግጥ በአጃ ላይ በወቅቱ የተሰራ ምንም አይነት ምርምር አልነበረም። ሊያግዛቸው የሚችል መረጃም በቀላሉ ማግኘት አይችሉም። አንድ ነገር ግን ያምናሉ። መጀመሪያ ላይ ያላቸው እውቀት እንደሚያግዛቸው። ስለዚህም ምንም ሳይፈሩ ወደ ሥራቸው ገቡ። ያሰቡትንም አሳኩ።

የጥናታቸው ትኩረት የአጃ ዝርያ እና የማኅበረሰቡ እውቀትን የሚዳስስ በመሆኑም ለብዙዎች ተረፉ። ይህም ቀጣይነት ያለው ምርምር ለሚያደርጉ መሰረት የሆኑበት፤ ማኅበረሰቡ ጥቅሙን ተረድቶ ምርታማነቱን እንዲጨምር ያገዙበት፤ ስርዓተ ምግብንም በተሻለ መልኩ እንዲከናወን ያስቻሉበት ነው። ለዚህም ማሳያው የሲናና ምርምር ማዕከልን በሥራ አስኪያጅነት ሲሰሩ ምርምራቸውን አስቀጥለው የመጀመሪያውን የአጃ ምርጥ ዘር እንዲያወጣና ማኅበረሰቡ እንዲያገኝ ያደረጉበት ነው።

የፕሮፌሰር ካሳሁን የትምህርት ጉዞ የሚቋጨው ጀርመን ውስጥ ቦን ዩኒቨርሲቲ ነው። በዩኒቨርሲቲው ረጅም ዓመታትን አሳልፈዋል። የመጀመሪያው ሦስተኛ ድግሪያቸውን የተማሩበትና በቡና ላይ የተለያዩ ምርምሮችን የሰሩበት አራት ዓመቱ ሲሆን፤ ሁለተኛው ሌላ የምርምር እድል አግኝተው የፖስት ዶክትሬታቸውን የሰሩበትና ተጨማሪ በቡና ላይ ምርምር አድርገው ለሀገራቸው ግልጽ ማረጋገጫ የሰጡበት ነው።

እንግዳችን ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ላይ ባለው የቡና ዝርያ ትኩረት አድርገው የሦስተኛ ድግሪያቸውን የሰሩ ሲሆን፤ በምርምሩም ስኬታማ ነበሩ። እርሳቸው እንደሚሉት፤ ቡና በተፈጥሮ ከሁለት ዝርያዎች የተዳቀለ ነው። በዚህም እናቱና አባቱን መለየት፤ ዝርያው ከየትና ከየት እንደመጣ ማወቅ የግድ ይሆናል። ጊዜው ግን አጭር በመሆኑ እናቱ ማነው የሚለውን ማየቱን ፈለጉ። በምርምራቸውም ኢጂኖይዲስ የሚባለው የቡና ዝርያ (Coffea eugenioides) አንዱ የቅርብ የእናትነት ዝምድና እንዳለው አረጋገጡ። ይህም ለበርካታ መላምቶች መልስ አስገኝቷል።

በሁለተኛው የትምህርት ቆይታቸው ምርምር ያደረጉት ደግሞ በደቡብ ምእራብ፣ በምዕራብና በባሌ በኩል ያለው የኢትዮጵያ ቡና ምን ያህል የጫካው አካል ነው የሚለውን ሲሆን፤ በዚህ አካባቢ ያለው ቡና “ከጓሮ ያመለጠ እንጂ የጫካው ወይም የተፈጥሮ ቡና አይደለም” የሚል እሳቤ የሚሞግት ነበር። እሳቤው ሄዶ ሄዶ ኢትዮጵያ የቡና መገኛ አይደለችም ወደሚለው ይወስዳልና ለዚህ ምላሽ የመስጠት ግዴታ የእርሳቸው እንደሆነ አምነውም ምርምራቸውን ሰርተዋል። ውጤቱም ብዙዎች መልስ ያገኙበት ሆኗል። የኢትዮጵያን የቡና መነሻነት በግልፅ አሳይተዋል።

ከጥናታቸው በመነሳትም የኢትዮጵያ ደቡብ ምዕራብ ያለ ቡና ተለያይነቱ ከፍተኛ እንደሆነም በማሳየት ለዓለም አቀፍ የቡና ኢንዱስትሪው አስፈላጊ መሆኑን፤ ጥበቃ እንደሚያስፈልገው ማመላከት የቻሉ ናቸው። በዚህም እንደያዩ ቡና፤ የከፋ ቡና እና ሌሎች የጫካ ቡናዎች በሀገራችን እና በዩኔስኮ ደረጃ እውቅና ተሰጥቷቸው እና ተመዝግበው እንዲጠበቁ ሆኗል።

እንግዳችን በትምህርታቸው ረጅም ጉዞ በማድረጋቸው የተነሳ በእጽዋት ዘረመል ምርምር በቂ ልምድ አካብተዋል። በርከት ያሉ ጥናትና ምርምሮችን ሰርተዋል። ሥራዎቻቸውን በታዋቂ ጆርናሎች ያሳተሙ በመሆናቸው እና በመሰል ስራዎቻቸው ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፕሮፌሰርነት ማዕረግ አግኝተዋል።

ከባኮ እስከ አዲስ አበባ

በእያንዳንዱ ሥራቸው የትምህርት ውጤታቸው ይታያል። የመምህሮቻቸው ድጋፍና የቤተሰቦቻቸው እገዛም እንዲሁ። እነርሱ ትናንት ሰርተዋቸዋል። ለስኬታቸውም ታግለውላቸዋል። በተራቸው እርሳቸውም የተደረገላቸውን ለመክፈል ተዘጋጅተዋል። ወደ ሥራ በመግባትም ብዙዎችን ብቁ ዜጋ እያደረጉ ይገኛሉ። የመጀመሪያው የሥራ ሀሁ የጀመሩት በኦሮሚያ ክልል ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ስር በሚገኝው የባኮ ግብርና ምርምር ውስጥ ነው። እዛ ብዙም ሳይቆዩ ባሌ ወደ ሚገኘው ሲናና ግብርና ምርምር ተዛወሩ።

ፕሮፌሰር ካሳሁን በሲናና ግብርና ምርምር ማዕከል አምስት ዓመታትን በሥራ አሳልፈዋል። በእጽዋት ማዳቀል ዘርፍ ተመድበው የመጀመሪያውን ሦስት ዓመት አገልግለዋል። በመቀጠል የሁለተኛ ድግሪ ትምህርት እድል አግኝተው ወደ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አመሩ። ከትምህርት መልስ በቀጥታ የምርምር ማዕከሉ ሥራ አስኪያጅ በመሆን ወደ ሥራ ገቡ።

ከጀርመን ሀገር መልስ በኋላ ደግሞ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲን ተቀላቀሉ። በመጀመሪያ ድግሪ መምህርነት በረዳት ፕሮፌሰርነት የመጀመሪያ ሥራቸውን ጀመሩ። ከዚያ ብቃታቸው እየጨመረ ሲመጣ ሁለተኛና ሦስተኛ ድግሪ ተማሪዎችን ወደ ማማከሩና ማስተማሩ ገቡ። ከባኮ ግብርና የምርምር ማዕከል ጋር በመሆን አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የመጀመሪያውን ዝርያ እንዲለቅ ያስቻሉት እንግዳችን፤ ለምዕራቡ የኢትዮጵያ እህል አብቃይ ለሆነው ማኅበረሰብ የሚጠቅም በምርታማነት በሽታን በመቋቋም የተሻለውን የዳጉሳ ዝርያን ለማኅበረሰብ ጥቅም ላይ እንዲውል ያደረጉ ናቸው።

በአዲስ አበባዩ ዩኒቨርሲቲ የባዮቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት እንዲመሰረት ከማድረግ አልፈው የመጀመሪያው የኢንስቲትዩቱ ዳይሬክተር የሆኑ እንዲሁም በባዮቴክኖሎጂ ትምህርት መስክ ለመጀመሪያ ጊዜ በሦስተኛ ድግሪ እንዲሰጥ በር የከፈቱ ናቸው።

የግላቸውን የእጽዋት ዝርያ ቤተ ሙከራ በመክፈትም ከ50 ያላነሱ የሁለተኛና ሦስተኛ ድግሪ ተማሪዎችን በማስተማርና በማማከር የማስመረቅ እድሉን ያገኙ፤ አሁንም ይህንን ተግባራቸውን ያስቀጠሉ ሲሆኑ፤ እነዚህ ተማሪዎች ደግሞ የሀገር ውስጥ ብቻ አይደሉም። በተለያዩ የውጪ አገራት ዩኒቨርሲቲ ትምህርታችውን የሚከታተሉና የመስክ ሥራቸው በሀገር ውስጥ ያደረጉ ናቸው። ለአብነት ከኔዘርላንድ፤ ከኬኒያ፣ ናይጄሪያ ዩኒቨርሲቲ የመጡ ተማሪዎች በዋናነት ይጠቀሳሉ።

እንግዳችን የኢትዮጵያ ባዮና ኢመርጂንግ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩትን ከማቋቋም በተጨማሪ፤ የኢትዮጵያ ወጣቶች የሳይንስ አካዳሚ መስራች አባል ናቸው። አሁን ላይ ከጎልማሶቹ ተርታ በመመደባቸው የኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ አባል ሆነዋል። በዚህም ጥሩ የሚባል ሥራ ሰርተዋል። ተማሪዎችንም ለሳይንሱ ዓለም እንዲዘጋጁና ብቁ እንዲሆኑ ማድረግ ችለዋል።

ኢትዮጵያ የተባበሩት መንግስታት የዓለም አቀፉ የዘረመል ምሕንድስና እና ባዩ ቴክኖሎጂ ማዕከል (International Centre for Genetic Engineer­ing and Biotechnology) አባል እንድትሆን እና ከሚሰጠውም የአቅም ግንባታ ድጋፍ ተጠቃሚ እንድትሆን ያደረጉ ሲሆኑ፤ በአሁኑ ሰዓት በአባል አገራት ተመርጠው የቦርዱ ምክትል ፕሬዚዳንት በመሆን እአአ ከታህሳስ 2024 ጀምሮ እያገለገሉ ይገኛሉ።

የሕይወት ፍልስፍና

‹‹በራሴ ላይ እንዲደርስ የማልፈልገው ነገር በሌሎች ላይ እንዲፈጸም አልፈልግም”። ለእኔ የሆነ ለሌሎችም መሆን አለበት የሚል አቋም አለኝ። በእኔ አቅም መሆን የሚችል ሁሉ መደረግ እንዳለበትም አምናለሁ። በግዴለሽነት ሌሎች እንዲሰቃዩ አልፈቅድም። ከዚያ ይልቅ ለሰዎች በሬን ሁልጊዜ ክፍት በማድረግ ማገዝን እሻለሁ። ነገሮች በውይይት እንዲፈቱም መልካም ፈቃድ አለኝ። በሥራዬ ከጀርባ የሚባል ሥራ እንዲኖር አልፈልግም፤ ምስጢር ሳይሆን ፊት ለፊት እየተነጋገሩ መስራት ይመቸኛል። ቀና መሆንም ያስደስተኛል።

ከእኔ ዘንድ ያለ ሌሎችን የሚጠቅም ነገር ከሆነ እንቅልፍ ጭምር ሳይኖረኝ መስራትና ምላሹን እንዲያገኙ ማገዝም አንዱ የሕይወት ፍልስፍናዬ አካል ነው። ሰዎች ረድተውኝና ደግፈውኝ እዚህ እንዳደረሱኝ ሁሉ ለዚህ ምላሹን መስጠት እንዳለብኝ አምናለሁ። ስለዚህ ሰዎችን መርዳት እና መደገፍ ያረካኛል።

ገጠመኝ

በርከት ያሉ ገጠመኞች አሏቸው። ከአዕምሯቸው የማይጠፋው ግን ሦስተኛ ድግሪያቸውን በሚሰሩበት ጊዜ የቡና ናሙናዎችን ለመሰብሰብ ሲጓዙ የገጠማቸው ነው። የመጀመሪያው ወደ ሚዛን እና ቴፒ መሀል የገጠማቸው ሲሆን፤ ቦታውን የሚያሳያቸው የአካባቢው ማኅበረሰብ የሆነ ሰው ለአካባቢው እና ለጫካው ያለውን የባለቤትነት ስሜት ያዩበት ነው። የያዘው መሳሪያ ጦር እና ገጀራ ሲሆን፤ ጫካውን አቆራርጠው ሲሄዱ ድንገት እጅብ ያለ ኮረሪማ አገኙ። ከዚያ ውስጥ ገለጥ አድርጎ አንዷን ፍሬ ወስዶ ሌሎቹን ኮትኩቶ ትቷቸው ሄደ።

በወቅቱ ግራ ስለተጋቡም ለምን ይህንን እንዳደረገና ሁሉንም ለምን እንዳልወሰዳቸው ጠየቁት። የእርሱም መልስ አንድ ነበር። ‹‹ይህም የእኔ ስለሆነ ነው›› የሚል። እናም እነርሱም በወቅቱ የአካባቢያችን ጸጋዎች የእኛ ናቸው የሚል ማኅበረሰብ ቢኖር እንዲህ ተራሮቻችን እርቃናችውን ባልቀሩ ነበር በሚል ተገርመው ተጓዙ።

ሌላኛው ገጠመኝ የእግር ጉዞ ለአንዳንዱ ቀላል ለአንዳንዱ ከባድ የሚሆንበትን ሁኔታ ያዩበት ነው። ቦታው በዳዎሮ ባንጃ የሚባል የቡና ጫካ ውስጥ የተከሰተው ነው። የግብርና ባለሙያው የሚሄዱበትን በጣም ቅርብ አድርጎ ይነግራቸዋል። እንደውም ከሰዓት በኋላ እንዲሄዱና እንዲመለሱ ሲጋብዛቸውም ነበር። ሆኖም ረጅም ጉዞ ቀደም ብለው ስለሄዱ በሀሳቡ አልተስማሙም። ጠዋት እንደሚሄዱ ነግረውት ተለያዩ። በቀጠሯቸው ጠዋት ተገናኙናም በመኪናቸው የተወሰነውን ርቀት ተጓዙ።

ከመኪናው ከወረዱ በኋላ ግን መንገዱ አልገፋም አላቸው። የያዙት ውሃ አልቆ የወንዝ ውሃ እየጠጡም ነበር መጨረሻ ላይ ባንጃ የቡና ጫካ የደረሱት። ሰዓቱም ስምንት ሰዓት ሆኗል። እናም መመለሳቸው እያሳሰባቸው ከአርሶ አደሩ ቤት አረፍ ብለው ምሳ በልተው ጫካውን በድቅድቅ ጨለማ አቆራርጠው ከምሽቱ 2 ሰዓት አካባቢ መኪናቸው ጋር ደረሱ። መኪናው ግን አልነበረም። ምክንያቱም መሽቶ ስለነበር አድረዋል በሚል ሄዷል። መምህራን ቤት አድረውም ነው ጠዋት መጥቶ የወሰዳቸው።

ከእናት መንደር ሌላ እናት

የውሃ አጣጭን በፍለጋ አሊያም በእቅድ ማግኘት የማይቻል ነው። ልብ ከልብ በድንገት ካልተገናኘ። ፍቅር ደግሞ እያደር በመግባባትና በመገናኘት የሚመጣ ይሆናል። የፕሮፌሰር ባለቤታቸው ምርጫና እጣ ፋንታም ከዚሁ ጋር የሚገናኝ ነው። ድንገት የእናታቸውን ቤተሰብ ሊጠይቁ በሄዱበት ልባቸው በአንዲት እንስት ላይ አረፈ። ልባቸውም ደነገጠላት። ግን በወቅቱ ምንም አላሉም ነበር። ስሜታቸውን ተቆጣጥረው ወደ ቤታቸው ተመለሱ። ልባቸው ግን እዛው ቀርቷል።

‹‹ይህቺ ሴት ሌላኛዋ እናቴ ናት›› ሲሉ በሀሳባቸው ሁሉ ተመኙዋት። ማንነቷንም አጣርተው ለትዳር አጯት። ዛሬ የቤታቸው ሞገስ ናት፤ የሦስት ልጆቻቸው ደስታ። በእርሷ ሁሉ ነገር ይደምቃል። እርሷ ካለች ቤቱ ሙሉ ነው። አይዞህ ባያቸው፤ በሥራቸው ደጋፊያቸው ሆናላቸዋለች። እርሷ ‹‹ትችላለህ›› ስትላቸው የማይፈጽሙት የመሰላቸው ነገር ሁሉ ይቀልላቸዋል። ስለባለቤታቸው አንስተው አይጠግቡም። ስለዚህም ስለ እርሷ ሲናገሩ ‹‹ሌላዋ እናቴ ናት›› በማለት ይገልጿታል።

ቀጣይ እቅድ

የጠንካራ ኃላፊ መገለጫ የሚመራውን ተቋም ከሀገር አልፎ ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪና ታዋቂ እስከማድረግ የሚያደርስ ነው። በዚህም ይህ እውን ይሆን ዘንድ ማማከር ላይ በስፋት እሰራለሁ። ሰዎችን ማብቃት፤ አመራሮችን ማፍራት፤ ሳይንቲስቶችን መፍጠር ላይ መስራትም እመኛለሁ። ሳይንስ በየጊዜው ተለዋዋጭ በመሆኑ ራሴንም በዚያ ልክ ማስኬድን አስባለሁ። በተጨማሪም ፖሊሲ ለሁሉም መሰረት ስለሆነ ሳይንስን መሰረት ያደረገ ፖሊሲ ላይ በስፋት የመስራት ፍላጎት አለኝ። ከዚህ በኋላ ባለኝ ቆይታ በአብዛኛው ልምድ ማካፈል፤ ለዘርፉ ጠቃሚ የሚሆኑ የተለያዩ መጽሐፎችን መጻፍና የፖሊሲ ሥራዎች ላይ በስፋት መስራት እሻለሁ። እነዚህ ሁሉ የወደፊቶቹ ዋነኛ እቅዶቼ ይሆናሉ ብዬ አምናለሁ ይላሉ።

የዓምዳችን ገጽ ገደበን እንጂ የፕሮፌሰር ካሳሁን ተስፋዬ ቆይታ በዚህ የሚቆም አልነበረም።

ጽጌረዳ ጫንያለው

አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 13 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You