አዲስ አበባ፡- ኢትዮጵያ እና ህንድ ዘመናትን ያስቆጠረ የሁለትዮሽ ወዳጅነት ያስቆጠረ ቢሆንም በንግድ ሚዛንና ተጠቃሚነት በእጅጉ ለህንድ የሚያዳላ መሆኑ ተገለፀ።
ሦስተኛው የሰሜን፣ ምስራቅ አፍሪካ እና ህንድ ጉባኤ ትናንት በአዲስ አበባ በተጀመረበት ወቅት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ማርቆስ ተክሌ እንዳሉት፤ የኢትዮጵያና ህንድ ወዳጅነት ዘመናትን የተሻገረ ነው። በንግድና ሌሎች ትስስሮች ላይ የጋራ ተግባራት ላይ በስፋት ተከናውኗል። በተለይም የህንድ ባለሃብቶች በስኳር ፋብሪካዎች፣ በጨርቃጨርቅ ኢንዱስትሪዎችና በከፍተኛ የትምህርት ዘርፍ በስፋት እየተሳተፉ ነው።
እንደ ሚኒስትር ዴኤታው ገለፃ ላለፉት 10 ዓመታት የህንድና ኢትዮጵያ የንግድ ግንኙነት በአማካይ 20 በመቶ እየተመነደገ ሲሆን፤ በፈረንጆቹ አቆጣጠር 2017 የሁለቱ አገራት የንግድ ፍሰት 1ነጥብ3 ቢሊዮን ዶላር ደርሷል። ሆኖም የንግድ ግንኙነት ሚዛኑን ያልጠበቀና ወደ ህንድ ያደላ ነው። በመሆኑም የሁለቱ አገራት የንግድ ሚዛን የጠበቀ ሥራ ለማከናወን እንደሚሠራ ገልፀዋል።
በኢትዮጵያ የህንድ አምባሳደር አኑራግ ሲሪቫስተቫ በበኩላቸው፤ መርሐ ግብሩ የህንድና አፍሪካ ፎረም አንዱ አካል ሲሆን የአፍሪካና ህንድን ወዳጅነት የበለጠ ለማጠናከር የታሰበ ነው። ህንድ ለሚቀጥሉት አምስት ዓመታት በአፍሪካ ለ50ሺ አፍሪካውያን ነፃ የትምህርት ዕድል የምትሰጥ ሲሆን፤ 10 ቢሊዮን ዶላር ኢንቨስት ታደርጋለች።
በተጨማሪም 600 ሚሊዮን ዶላር እርዳታ የመለገስ ውጥን አላት። እስካሁን ባለው ሂደት ህንድ በአፍሪካ ውስጥ 54 ቢሊዮን ዶላር ኢንቨስት ያደረገች ሲሆን፤ አፍሪካ ውስጥ ኢንቨስት ካደረጉ የዓለም አገራት መካከል በአምስተኛ ደረጃ ላይ ያስቀምጣታል። የሁለቱ አካላት ንግድ ትስስርም 63 ቢሊዮን መድረሱን ተናግረዋል።
በዚህ ውስጥም የኢትዮጵያ ሚና ጉልህ መሆኑን ጠቁመው፤ ሁለቱ አገራት በኢንቨስትመንት፣ ንግድ፣ ትምህርት፣ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ብሎም ሌሎች የጋራ አጀንዳዎች ላይ በጋራ እየሠሩ ነው። በቀጣይም ከኢትዮጵያ ሆነ ከአፍሪካ ጋር የሚደረገው ግንኙነት ሁሉንም ተጠቃሚ ባደረገ መልኩ በስፋት እንደሚከናወንም አረጋግጠዋል።
በመርሐ ግብሩ ላይ የሁለቱን አገራት ወዳጅነት አስመልክቶ ፅሁፍ ያቀረቡት አቶ መላኩ ሙሉዓለም በበኩላቸው፤ ህንድ እና ኢትዮጵያ የሁለትዮሽ ግንኙነት ብቻ የተገደበ ሳይሆን ዓለም አቀፍ በሆኑ ጉዳዮች ላይ በስፋት እንደሚሠሩ ጠቁመዋል። ለአብነት ሽብርተኝት በመዋጋት፣ በሠላም ማስከበርና በዓለም አቀፍ ተልዕኮዎች ላይ ጠንካራ አቋም ያላቸው አገራት መሆናቸውን አስረድተዋል።
ትናንት በአዲስ አበባ የተጀመረው የሰሜን፣ ምስራቅ አፍሪካ እና ህንድ ጉባኤ ቀደም ሲል ዳሬሰላም እና አክራ መካሄዱ ይታወሳል።
አዲስ ዘመን ቅዳሜ መጋቢት 21/2011
በክፍለዮሐንስ አንበርብር