ያኔ ድሮ ድሮ..፣ እንደ አሁኑ በዘርና በጎሳ ሳንከፋፈል በፊት፤ ሀገራችን በእኛ እኛም በሀገራችን ነበር የምንታወቀው። ያኔ ድሮ..እንደ አሁኑ በብሄርና በሀይማኖት ከመለያየታችን በፊት አንድ ህዝቦች፣ አንድ አብራኮች ነበርን። አሁን ሁሉም ነገር ሌላ ነው። አንድነት ያቆነጀው ኢትዮጵያዊ መልካችን ዘርና ጎሳ፣ ብሄርና ሀይማኖት ገብቶበት ወይቧል። ስማችን ጠፍቶብናል። ማናችሁ ስንባል ኢትዮጵያዊ ነን ብለን በኩራት እንዳልተናገርን፤ ዛሬ ማናችሁ ላለን የምንናገረው ብዙ ጥላቻ ወለድ ስሞችን አትርፈናል። በአንድ ያቆሙን ኢትዮጵያዊ ስሞቻችን ዛሬ ላይ ከምንም በላይ የሚያስፈልጉን የሰላማችን ቀንዲሎች ናቸው። የወየብነው እውነትን ሰውረን በሀሰት ስላጌጥን ነው። ከኢትዮጵያዊነት በፊት ያሉ ስሞች ሁሉ የሀሰት ስሞች ናቸው። ያደመቀን፣ ሶስት ሺ ዘመናትን በታሪክና በስልጣኔ ያሻገረን ኢትዮጵያዊነት ነው። ኢትዮጵያ የሚለው ስም። ይሄ ስም መቅደም አለበት።
ድሮ ኢትዮጵያዊ ብቻ ነበርን፣ ድሮ ሀገር ብቻ ነበርን። አሁን ብዙ ነን። አንዷን ሀገራችንን ከፋፍለን አማራና ኦሮሞ፣ ትግሬና ጉራጌ አድርገናታል። ድሮ ሰው ነበርን፣ ድሮ አለም ያደነቀን የእውነትና የፍትህ ሚዛኖች ነበርን፤ አሁን ሌላ ነን። ወንዝ የማያሻግሩንን ፖለቲካ ወለድ ስሞችን ተነቅሰን ለጠየቀን ሁሉ እኔ አማራ ነኝ፣ እኔ ኦሮሞ ነኝ፣ እኔ ትግሬ ነኝ ስንል በአንድነታችን ውስጥ መርዝ እንረጫለን። ድሮ ሩህሩህ ነበርን፣ አይደለም እርስ በርስ ልንገዳደል ቀርቶ የተማረኩ የጠላት ምርኮኞችን አብልተንና አጠጥተን ተንከባክበን የምንሸኝ የአምላክ ባሮች ነበርን። ዛሬ ሌላ ነን። መግደል የሚያረካን፣ ማሰቃየት የሚያስደስተን የሳጥናኤል ጭፍሮች ወጥቶናል። በጋራ ብንኖርባት የምትበቃንን፣ በፍቅር ብንኖርባት የምትሰፋንን አንዷን ኢትዮጵያ ብዙ ቦታ ከፋፍለን እንዳትበቃን እንፈራገጥባታለን። እንገፋፋባታለን። ተንፈራግጠን..ተንፈራግጠን እኛ ወድቀን ሌሎችንም እንጥላለን። ተጋፍተን ተጋፍተን ማንም የማይኖርባትን ሀገር እንፈጥራለን። ትርፋችን ይሄ እኮ ነው። የመንፈራገጥ..የመጋፋት ትርፉ ተያይዞ መውደቅ ነው። ተያይዞ መቆም እያለ፣ ተቃቅፎ መኖር እያለ ለመውደቅ መገፋፋት ምን የሚሉት ብሂል እንደሆነ አልገባኝም።
መንፈራገጥ አንድም ለመውደቅ አንድም ለመላላጥ ነው። ብሄሩን ትልቅ አድርጎ ሀገሩን ያሳነሰ፣ ዘሩን ኩሩ አድርጎ ሰውነቱን ያኮሰሰ የኋላ ኋላ ከመውደቅ የሚያግደው አይኖርም። አለም ላይ ከሀገራቸው ብሄራቸውን ያስቀደሙ፣ ከሰውነታቸው ዘራቸውን ያስቀደሙ ግለሰቦችም ሆኑ ቡድኖች የወደቁ ናቸው። ውሻ በጨው የማይቀምሳቸው የታሪክ ነውረኛ ናቸው። የእኛም በብሄር ስም መንፈራገጥ አንድም ለመውደቅ አንድም ለመላላጥ አንድም ነውረኛ ታሪክ ለመጻፍ ነው። ለሁላችን የምትበቃ ሀገር አለችን፣ በጋራ እሴት፣ በጋራ ባህል የተሳሰረ ማንነት አለን በዚህ እውነት ውስጥ ጸንቶ መኖር እንጂ ለመውደቅ መገፋፋት ትርፍ የለውም። ኢትዮጵያ ሀገራችን አንድ ናት..በአንድ ሀሳብ፣ በአንድ ህልም ያጸናናት የጋራ ቤታችን ናት። የአባቶቻችን አንድነት ምሰሶ ሆኖ፣ ዋልታና ማገር ሆኖ ያቆማት ናት። እኛ መዶሻ ሆነን በአንድነት ዋልታና ማገር የታነጸችውን ሀገራችንን ለማፍረስ መንፈራገጥ የለብንም። ቤታችን እንዳትጠበን በነፍሳችን ላይ የፍቅርን እሳት መለኮስ ግድ ይለናል። ብሄር ስም የምንለኩሰው እሳት መጀመሪያ እኛን ነው የሚያቃጥለን። መርዝ መጀመሪያ ብልቃጡን እንደሚጎዳ ሁሉ ክፉ ሀሳብም መጀመሪያ ባለቤቱን ነው የሚጎዳው።
ለማይጠቅመን ነገር መሮጥ ትተን በሚበጀን ነገር ላይ እንልፋ። አሁን የሚጠቅመን በጋራ ሀገር ማሳደግ ነው። ከአለም ድሀ የሆነችውን ሀገራችንን ማልማት፣ ማሰልጠን ነው። አሁን የሚጠቅመን በቀን ሶስት ጊዜ መብላት ያልቻለ ማህበረሰባችንን መታደግ ነው። የፖለቲካ ቅራኔዎችን በእርቅ መፍታት ነው። በዘር ተኮር ፖለቲካ ያጣናቸውን በረከቶቻችንን መፈለግ ነው። አሁን የሚጠቅመን ለወጣቱ የስራ እድል፣ ለዜጎች ደግሞ ምቹ ሀገር መፍጠር ነው። ህጻናት የሚያድጉባትን፣ አዛውንቶች የሚጦሩባትን ሀገር መገንባት ነው። አሁን የሚጠቅመን ትውልዱ የሚኮራበትን የጋራ እሴት መፍጠር ነው። በእርቅ ደም ማድረቅ ነው። በመነጋገር ችግሮቻችንን መፍታት ነው። አሁን የሚበጀን የዘር ፖለቲካ ያጠየመውን ኢትዮጵያዊነት ማስተካከል ነው። እኔነት አረም የበቀለበትን ሰውነታችንን ማከም ነው። እንዲህ ካልሆንን ንጋት አናይም። ኩርፊያና ጥላቻ ባጨለሙት ማምሻ ላይ ቆመን ንጋት መናፈቅ ሞኝነት ነው። መጀመሪያ ልቦቻችንን ለብርሀን እናዘጋጅ። መጀመሪያ አይኖቻችን ንጋት እንዲናፍቁ እናድርግ። በመጠላላት የመሹብን ንጋቶች፣ በዘር እሳቤ የዘገዩብን ተስፋዎች ከእርቅ በኋላ የሚነጉ ናቸው። እንዲነጋልን መታረቅ አለብን። መግባባት አለብን።
እስከመቼ በማይጠቅመን ነገር ላይ እየለፋን እንኖራለን? እስከመች አንድ ቦታ እየረገጥን እንደ ቀንድ አውጣ ስናዘግም እንኖራለን? የማይጠቅሙንን ስንከተል የሚጠቅሙን እያጣን እንደሆነ ቢገባን እላለው። አሁን ላይ ከገቡን ይልቅ ያልገቡን ብዙ ናቸው። የገቡን ይሄን ያክል ካሰቃዩን ያልገቡን ጠቃሚዎቻችን እንደሆኑ መረዳት አይከብደንም። እስኪ የገቡንን ትተን ወዳልገቡን እንራመድ። ያልገቡን በረከቶቻችን ስለመሆናቸው ገብተውን ካሰቃዩን መከራዎቻችን መረዳት እንችላለን። ያልገቡን ቢገቡን ኖሮ በዚህ ልክ ዋጋ ባልከፈልን ነበር። ገብቶናል ባልንው እኔነት፣ ገብቶናል ባልንው የብሄር ፖለቲካ ለዘመናት ተሰቃይተናል። አሁንም እየተሰቃየን ነው። ገብቶናል ባልንው ዘረኝነት፣ ገብቶናል ባልንው ሀይማኖተኝነት የዘመናት እሴቶቻችንን አጥተናል። እስኪ ወዳልገቡን ደግሞ እንመለስ..እስኪ ወዳልተረዳንው እውነት እንመልከት። ምናልባት እኮ እነዛ ያልገቡን እውነቶች የመከራዎቻችን መፍትሄዎች ይሆናሉ። የህይወታችን አቅጣጫ ጠቋሚዎች ሊሆኑን ይችላሉ። ገብተውናል ባልናቸው ግን ደግሞ ባልገቡን ነውሮቻችን መሰቃየታችን ይብቃ። ያልገባን ፍቅር ነው..ያልገባን እኮ አንድነትና መቻቻል ነው። ያልተረዳንው እውነት ኢትዮጵያዊነት ነው። እስኪ ወዳልገቡን የፍቅርና የአንድነት መንፈሶች ዞር ብለን ደግሞ እንሞክረው። እስኪ ወዳልገባን ኢትዮጵያዊነት ተመልሰን ሰላማችንን እንፈልገው፣ ሞታችንን፣ ጉስቁልናችንን እንታደገው። ወዳልተረዳንው ዞረን በፍቅር ሞታችንን እንግደለው እላለው።
ተበልጠናል..ብሄርተኝነት ወልዶ ባሳደገው ምናምንቴ ጭንቅላት ስናስብ ተበልጠናል። የዘር ፖለቲካ ዘርቶ ባበቀለው ሰውነት ስንመጻደቅ ተበልጠናል። ጥላቻና ዘረኝነት ባስጎነበሰው ጎባጣ ጀርባና ትከሻ እየተራመድን ተበልጠናል። አሁን ሁሉም በልጠውናል። በሁሉም ተበልጠናል። ተለያይተን የተራመድንባቸው እነዛ የመጠላላትና የመገፋፋት ዘመኖች ዛሬ ላይ በብዙ ነገር ወደ ኋላ አስቀርተውን ለውጥ ናፋቂዎች አድርገውናል። ከአለም እኩል ለመሆን፣ ከአፍሪካ እኩል ለመቆም፣ ከጎረቤቶቻችን እኩል ለመሆን ዘረኝነትን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ መቅበር አለብን። እንደሚታወቀው ሩዋንዳውያን በብሄር ፖለቲካ መጥፎ ታሪክ ያላቸው ህዝቦች ናቸው። አሁን ላይ በሩዋንዳ ምድር ከሩዋንዳ በቀር ሌላ ብሄር አይጠራም። እኛም ይሄን የዘር ፍጅት ለማስቆም ከሩዋንዳ የምንኮርጀው ብዙ ነገር ሊኖር ይገባል ባይ ነኝ። ከኢትዮጵያ በቀር የምናውቀው ሌላ ስም ሊኖረን አይገባም። በዘር ፍጅት ታሪኳን ያጣችው ሩዋንዳ ዛሬ ላይ ያን ጊዜ ላለማስታውስ እኛ ሩዋንዳዊ ነን የሚሉ ናቸው። በሩዋንዳ ምድር ከሩዋንዳ በቀር ሌላ ብሄር የሚጠራ ዜጋ ዘብጥያ ከመውረድ በቀር አማራጭ የለውም። ይሄ ደግሞ ምዕራፍና አንቀጽ ሰጥታ በህገመንግስቷ የደነገገችው እውነት ነው። እንደ ሩዋንዳ ማናችሁ ስንባል እኛ ኢትዮጵያዊ ነን ስንል የምንመልሰው የአንድነትና የኩራት ስም ያስፈልገናል። እንደ ሀገር አንድ ሆነን መቆም ካለብን ኢትዮጵያ የሚለው ስም ያስፈልገናል። ከአማራና ኦሮሞ፣ ከትግሬና ጋሞ በፊት የምንጠራው..የምንኮራበት ኢትዮጵያዊ ማንነት ግድ ይለናል።
ከዘር ፖለቲካ ወጥተን በፍቅር የምንሞትባት ኢትዮጵያ ናፍቃኛለች። ሰው እኮ በፍቅር ይሞታል..ሰው እኮ ሌላውን በማፍቀር፣ ለሌላው በመኖር ይሞታል። ነፍስ እኮ ስለሌሎች ስቃይ ታልፋለች። በኢትዮጵያ ምድር የናፈቀኝ ይሄ ነው..በፍቅር መሞት። እስኪ በጥላቻ መሞት ቀርቶብን በፍቅር እንሙት። እስኪ በመዋደድ እንሙት፣ እስኪ በሌሎች መከራ፣ በሌሎች ስቃይ፣ በሌሎች ጉስቁልና እንሙት። በጥላቻ መሞት ስንችል በፍቅር መሞት እንዴት አቃተን? እስካሁን ገለን የምንሞት ነን፣ ጠልተን የምንሞት ነን። እንደ እየሱስ አፍቅሮ መሞት እንዴት ተሳነን? የሚበጀን ይሄ ነው። የሚበጀን በፍቅር መሞት ነው። እናም ከጥላቻ ወጥተን በፍቅር እንሙት እላለው። ህዝብ ለሀገር ሲሞት ሀገር ለህዝብ ትሞታለች። አንዱ ለአንዱ ሲታመም ሰውነት ያኔ ዋጋ ያወጣል። ያኔ ነው ሀገርና ህዝብ፣ ትውልድና ታሪክ እረባና የሚኖራቸው። ያኔ ነው እንደ ሀገር ወደ ፊት ለመሄድ ብርታት የምናገኘው። በፍቅር እንሙት..በሌሎች ስቃይ እንሰቃይ። የሌሎች ህመም ይመመን። የወገን ጉስቁልና ይሰማን..የፍቅር ሞት ያልኳችሁ ይሄንን ነው። እኔ በእናንተ ስታመም፣ እናንተ በእኔ ስትታመሙ ያኔ ሀገርና ህዝብ ትርጉም ያገኛል። የፍቅር ሞት ያልኳችሁ ይሄንን ነው። በአንዱ ውስጥ የአንዱ መብቀልን።
የፍቅር ሞት ህመም የለውም። የአንድነት ሞት ሞቶቻችንን ሁሉ የምንገልበት ጥበብ ነው። አሁን ላይ እየሞትን ያለንው በጥላቻ ሞት ነው። የጥላቻ ሞት ደግሞ ሌላ ሞት ይፈጥራል እንጂ ህይወት አይሰጥም። ሞቶቻችን የጥላቻዎቻችን ጽንሶች ናቸው። በዘር የፈጠርናቸው፣ በብሄር የጸነስናቸው ፋንድያዎች። የጥላቻ ሞት ትንሳኤ የለውም። የጥላቻ ሞት ዳግም ህይወትን አይሰጥም። በፈጣሪ ፊት በክብር አያስቆምም። ከፍቅር ርቀን ጠልተን ስንሞት በዚህኛውም አለም ሆነ በዚያኛውም አለም ትንሳኤ የለንም። ትንደሳኤ ያላቸው ነፍሶች በፍቅር ኖረው በፍቅር ያለፉ ናቸው። እናም እንዲህ እላችኋለው ስለሌላው በመኖር፣ ስለሌላው በማሰብ፣ ስለሌላው በመጨነቅ በፍቅር እንሙት። ያኔ ሌላ እንሆናለው..አሁን ከሆንው ሌላ።
ሀገራችን ኢትዮጵያ የብዙ ጥበቦች መገኛ ሀገር ናት። ሌላው ሀገር ሰላም ሲያጣ፣ አንድነት ሲርቀው ወደ ኢትዮጵያ ነበር የሚመለከተው። ኢትዮጵያን የሰላም ቀንዲል፣ የአንድነት ዋርካ አድርገው ሀርና ህዝብ የመሰረቱ በርካቶች ናቸው። ሀገራችንን ተስፋ አድርገው፣ ህዝባችንን ተማምነው ሀገር የሆኑ እልፍ ናቸው። ዛሬ ይቺ ብዙዎችን ያስጠለለች ዋርካ ሀገራችን ዛፍ መሆን ባልቻሉ ሀገራትና ግለሰቦች ሰላሟን ስታጣ ማየት ጥያቄን ይፈጥራል። ለሌሎች ተርፎና ተትረፍርፎ ለራስ መላ ማጣት ህመሙ በምን ቃል እንደሚገለጽ አላውቅም። ሌሎችን ሀገርና መንግስት ያደረገች ቀዳማይት ምድር ዛሬ ዘመን ባለፈባቸው ነውረኛ ድርጊቶች ስትናጥ ማየት ከማስገረም ባለፈ ምን ሊባል ይችላል? አፍሪካን አንድ ያደረገች ሀገር ዛሬ ላይ በወንድማማቾች ደም ስትታጠብ ማየት ከማስቆጨትም በላይ ያማል።
ሀገሩን የሚወድ ሁሉ በእርቅ ደም ያድርቅ። በፍቅር ጥላቻን እንዲገድል አደራ እላለው። በዚች ሀገር ብዙ የተማጽኖ አደራዎች ተሰምተዋል። ብዙ የይቅር፣ ብዙ የእርቅ ድምጾች አስተጋብተዋል። አባቶች ተናግረዋል፣ የሀይማኖት መሪዎች አደራ ብለዋል ግን ካልገቡን ይልቅ የገቡን ልቀው ጆሮ ዳባ ብለን በራሳችን ላይ መከራ ፈጥረናል። ካልተረዳናቸው መንፈሶች ይልቅ የተረዳናቸው የጥፋት እውነቶች ሚዛን ደፍተው ጸዳሎቻችንን ነጥቀውናል። እኔም አደራ እላለው..በእርቅ ደም እንዲደርቅ፣ በፍቅር ሞት እንዲቀር አደራ እላለው። የሚበጀን ይሄ ነው..በእርቅ ደም አድርቀን፣ ይቅር ለእግዜር ተባብለን ወደ ፊት መራመድ። መች እንደሚበቃን አላውቅም..ሀገር ፈርሳ መግቢያ ያለን ይመስል፣ ወገን ከድተን መጠጊያ ያለን ይመስል የጥፋት ሩጫችን ይገርማል። በዚች ሀገር ላይ ያልገቡን እንዲገቡን አደራ እላለው። ከፍቅር በቀር፣ ከአንድነት በቀር ሁሉም የገባን ህዝቦች ነን። ያልገቡን እንዲገቡን ልባችንን እንክፈት እያልኩ ላብቃ።
በትረ ሙሴ (መልከ ኢትዮጵ)
አዲስ ዘመን ሐምሌ 26 ቀን 2014 ዓ.ም