የእናትነት መስፍሪያ ልኩ ዓለም ላይ ያልተፈጠረ ይመስል ቃል ያጣል። እናትነት ደመነፍሳዊ ነው። እንዲህ ላድርግ፤ እንዲህ ልሁን ብለህ የምታደርገው ሳይሆን፤ ዝም ብሎ ከሴትነት ጋር ከመውለድ ጋር አብሮ የተሰጠ የተፈጥሮ ፀጋ ነው። እናት ስትሆን ልጆችህ በልተው መጥገባቸውን ማመን የማትችል፤ ወድቀው መነሳታቸው ተአምር የሚሆንብህ፤ የነገ ስኬታቸውን ስዕል በዓይነ ህሊናህ ስለህ ለዛ መሳካት ሌት ከቀን የምትደክምበት ጉዞ ነው።
ታዲያ ይሄን በተስፋና በፍቅር ያለድካም የሚደረግ ጉዞ፣ ሰዎች ነንና በተለያየ መንገድ ሲደናቀፍ ይታያል። ልጆች የፈለጉትን ጠይቀው አለማድረግ ህመም የሚፈጥርባት እናት፣ በጦርነት ምክንያት ቤቷ ተዘግቶ የልጆቿን የረሃብ ሲቃ እንድታዳመጥ የምትገደድበት ገጠመኝ ይፈጠራል። ነጋቸውን በአእምሮዋ ስላ ለስኬቱ የምትተጋው እናት፣ ልጆቿ ከትምህርት ገበታ ከተለያዩ ቀናት ብሎም ወሯት ከዛም ዓመታትን ስታስቆጥር ምን ያህል ሊያሳቅቃት እንደምትችል በእሷ ቦታ ሆኖ ማሰቡም ቀላል አይደለም።
መኖር ጥያቄ ውስጥ ገብቶ ልጆቿን መልሳ አትውጣቸው ነገር ግራ ገብቷት መደበቂያ መሸሸጊያ ጥጋት ያጣችውን እናት እንባ ማየት፤ እሷም ሰው ናትና ጠኔ እያዳፋት ከአፏ ነጥላ ልጆቿን ልታቃምስ የምትጥርን እናት፤ የእምነቷ ጥልቀት ተፈትኖ የፀሎቷ ምላሽ መምጫ እንደ ምፅኣት ቀን ለራቀባት እናት፤ ጭንቀትና ስቃይዋን ቦታ ላልሰጠኸው ለአንተ በሁለት ጎራ ቆመህ ቅድመ ሁኔታ እያልክ የሰላምን ቀን ለምታረዝመው ምን ትርጉም ይሰ ጥህ ይሆን?
ረሃብ ስንት ቀን እንደሚፈጅ ላልገባህ ለአንተ፤ ማጣት ትርጉሞ በእሷ እጦት ልክ ላልተገለፀልህ ለአንተ፤ መንገዱን ጀምረህ እንቅፋት ለምታኖረው ለአንተ፣ በሷ ጫማ ውስጥ ብትሆን ሕመሙ ምን ያህል ሊሰማህ ይሆን? ብዬ ልጠይቅህ ወደድኩ።
የአንድ እናት ልጆች፤ መጠሪያ ቋንቋቸው አንድ የሆነ፤ ቀለም ዘራቸው ያልተለየ፤ በአንድ ማህፀን ግፊያን ያቆሙ ዘንድ ለሰላም ንግግር ለመቀመጥ ይሁንታቸውን ሰጥተዋል የሚለውን ዜና ስሰማ እፎይ ብያለሁ። መሪዎቻችንም ሰላም ቋንቋችን ሊሆን ስለሰላም በጋራ ተነጋግረን ለመግባባት ፈቅደናል ብለውናል፤ ይህ ይበል የሚያሰኝ ውሳኔና ተግባር ነው።
ለሕዝብ ለወገናችን ስንል፤ ያሉት ነገሮች እስከሚስተካከሉበት ጥግ ድረስ ጥረታችንን አናቆምም ሲሉንም፤ እኛም «አቦ ያድርገው፣ እንዳፋችሁ ይሁንልን» ብለናል። ለመስማማት ማሰባችሁ እንደው የነገዋን ጀንበር ሳያያት በአጭሩ የሚቀጨውን ወገን ካስቀረልን፤ የሰቆቃ ድምፆችን ከየአቅጣጫው መስማት ከቀነሰልን ከፈጣሪ የተማከራችሁ ለሰላም ቅድሚያ የሰጣችሁ ዕድሜያችሁን ያርዝመው ስንል መርቀናል።
እርቁም የሚነገር ብቻ ሳይሆን የሚተገበር ይሆንልን ዘንድ ምኞታችን ነው። እንደውም ሰሞኑን በመዲናችን አዲስ አበባ አትሌቶቻችንን የጀግና አቀባበል ስናደርግላቸው ገሚሱ እንባ እንባ እያለው እልልታውን ሲያቀልጥ፤ ገሚሱ ምነው ይሄ ድል ጥላቻን አፈር ከድሜ አስግጦን በአንድነት ወደፊት የምንጓዝበት መንገድ መጥረጊያ ቢሆንልን እያለ ሲመኝ ነበር።
ከእግር እስከ እራስ በሚወር ኢትዮጵያዊ ስሜት፣ ድላቸው እንጂ ብሔራቸው ያልተጠየቀበት፤ አገርን ማስቀደማቸው እንጂ መምጫቸው ከየት ነው? እንዴት ነው ባልተባለበት ልክ ሙሉ የደስታ መንፈስ ፊታቸው ላይ እየታየ አስደስተው እንዳስለቀሱን ጀግኖች አትሌቶቻችን ፖለቲከኞቻችንም ጀግንነት ገድሎ መሞት እንዳልሆነ ተማሩልን እንላለን።
ምክንያቱም፣ ጀግንነት ከጦርነት የላቀ መፍትሄን አሻገሮ በመመልከት አንድ እርምጃ ወደ ፊት ማራመድ ሲችል፤ ጀግንነት ጦር ሜዳ ሳይዋል በፍቅር ገድሎ በዓለም መድረክ ላይ ቀና ሲያስብል፤ ወታደር አገር እንጂ ብሔር የለውም አገር ደግሞ ኢትዮጵያ ናት የኢትዮጵያ ልጆች ደግሞ በእኩልነት በአንድነት ይኖሩ ዘንድ ጀግና አሻጋሪዎች ያሿታልና መውጫ መግቢያው ተዘግቶባት ማጣፊያው ላጠራት እናት እስኪ ለሰላም የሚተጋ ጀግና ሆናችሁ አሳዩን።
ጥርጣሬን ከውስጣችሁ አውጥታችሁ አንድ ጠረጴዛ ላይ ለመቀመጥ እርስ በእርሳችሁ ተማመኑ። እምነት መስመማትን፤ መስማት ደግሞ መግባባትን፣ መግባባትም ሰላምን፣ ሰላም ደግሞ እርቅን ያመጣልና በቅድሚያ ወንድማማችነታችንን በማመን ልዩነቶቻችን የሚታረቁበት መንገድ ላይ ትኩረት ይደረግ።
ለዚህ ደግሞ ለሰላም ዓይኔን አላሽም ካላችሁ፤ ቅድሚያ መስፈርት መሆን የሚገባው የሕዝብ ጥቅም ነውና ልጆቼን ምን ላብላ ምን ላልብስ ያለችውን እናት አስባችሁ ልባችሁ ላይ የከበደውን ነገር ቀለል አድርጉት። ምክንያቱም የሰላሙ ጥረት አንድ ቀን በረዘመ ቁጥር እየጠፋ ያለውን ነፍስ እያሰባችሁ የማይታረቅ ነገር ውስጥ ከመግባታችን በፊት ፈጠን ያለ ጥረት በትህትና ለማድረግ ልባችሁን አዘጋጁ።
መቼስ እግርና እግርም ይጋጫል፤ እናም ሰው ለሰው ቢጋጭ ለምን ተጠላን የሚያስብል ነገር የለም። ፀባችንን በምን እንፍታው? ምን ብለን ምን አድርገን አገር ሰላም እንዲሆን ሕዝባችን በአማን እንዲያደር ልናደርገው እንችላልን? ከሁሉ በላይ ያለጥፋቱ ዋጋ የሚከፈለው ሕዝብ ባላየው ባልገባው ነገር ለሚማገደው ወጣት ነገ አገር ተረክበው አገሩን ከታላላቆቹ አገራት ተርታ ለሚያሰልፋት ሕፃን ስንል ሰከን ማለት ተገቢ ነው።
መቼስ ሰው ከላይ ሲሆን ራሱን ለማሳወቅ የተዘጋጀ ነው የሚል እምነት አለን። ከበላይ ያለው ግን ወደ ላይ ብቻ ማንጋጠጥ ሳይሆን ወደ ታቹም ወደ በታቹም በመመልከት የወገኑ ቁስል አካሚ፤ የተከፋችትን እናት እንባ አባሽ ሊሆን የተገባ ነው። ይሄን ማድረግ ካልቻለማ ምኑን ከላይ ሆነ?
ይሄንን ያህል «የቀበጣጠረኩት» መቼም ከእናንተ አውቄ ሳይሆን፤ ከትንሽየዋ የግንዛቤ ጓዳዬ ትዝ ያለኝን ሃሳብ ላስታውሳችሁ ብዬ ነው። ምክንያቱም እንደ ብዙዎቹ እንና እኔን መሰሎች ከፍቶናል፤ ማታ ተኝተን ነገ ስለሚሆነው ነገር በተስፋ መጠበቅ ቀርቶ የፈጣሪን ቸርነት እያመሰገንን ተስፋ በማጣት ውስጥ መንከላወስ ደክሞናል። ሞት በዝቶ እኛን ማስደንገጥ ካቆመ ሰነባብቷል፤ ችግር ሲበዛ አደንዝዞን ይሆን ሌላ ዝም ብሎ የእውር ድንብር መነዳት ሆኗል፤ እና ከዚህ መደናዘዝ ከዚህ ተስፋ ማጣት ውስጥ ታወጡን ዘንድ እንማፀናለን።
የረሀብን ልክ ዙሪያው ገባው እንደተዘጋባት እናት ያህልም ባይሆን አንድ ቀን ቢጎል የሚሰማንን አስበን ለሰላም ዝቅ እንበል። ከሰላሙ መንገድ በኋላ ተከታይ ጥያቄዎች ቢኖሯችሁ በሰላሙ ሜዳ ለመወያየት ቀነ ቀጠሮ ይዛችሁ በየቀኑ ለሚረገፈው ወገን ስትሉ አንድ እርምጃ ወደ ሰላም በመራመድ ጀግንነታችሁን አሳዩን።
ለእኔ ጀግና ለተከፋ ወገኑ ደራሽ፤ በኀዘን ለተቆራመደው እንባ አባሽ ነው። ለእኔ ጀግና እልህ ድንፋታውን ትቶ ስለ ሰላም ቆርጦ የሚራመድ ነው፤ ለእኔ ጀግና ዘር ቀለም ጎጥ ሳይለይ ሁሉን በአንድ የሚያይ፣ የሕዝብን የመከፋትና ተስፋ የማጣትን ባህር እንደሙሴ በበትሩ ለሁለት ከፍሎ ወደ ሰላም ደሴት የሚያሻግር ነው።
መሪም በመሪነቱ ልክ፤ ሕዝብም እንደሕዝብ ሆኖ አዲሱን ተስፋ በሰላም የምንቀበል፤ የእናት መሶብ ሞልቶ ለልጆቼ ምን ልስጥ ምን ልቁረስ ተረት የሚሆንበት፤ ወገን እንደቅጠል መርገፉ ቀርቶ ለልምላሜ ለተስፋ በመሥራት ወደ ከፍታው የምንሻገርበት ዘመን እንዲያመጣልን እየተመኘሁ የዛሬውን አበቃሁ። ለዚህ ደግሞ የሰላም መንገድ ጉዟችን ቅድመ ሁኔታችን የሕዝብ ጥቅም ይሁን፤ ይሄ ሲሆን ሰላም ከፍታዋን፤ ድንፋታም ውድቀቷን ይጎናጸፋሉ።
ብስለት
አዲስ ዘመን ሐምሌ 26 ቀን 2014 ዓ.ም