«ኮንትራክተሩ በራሱ ፈቃድ ነው ጥሎ የወጣው» የቡሌ ሆራ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር ጫላ ዋታ
አዲስ አበባ፡- የቡሌ ሆራ ዩኒቨርሲቲ ያለአግባብ ግንባታ አቋርጬ እንድወጣ በማድረጉ ለኪሳራና ህመም ዳርጎኛል ሲሉ ግንባታውን ያካሂዱ የነበሩ ኮንትራክተር አቶ ከተማ ኢቲቻ ገለጹ። ዩኒቨርሲቲው በበኩሉ ያቋጡት በራሳቸው ፈቃድ ነው ብሏል።
ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ ቅሬታቸውን ያቀረቡት አቶ ከተማ ኢቲቻ እንደተናገሩት «በውላችን መሠረት ዲዛይን ሳይሰጠኝ ግንባታ መፈፀም እንደማልችል በመግለፄ ምክንያት ሁለት ሕንፃ የገነባሁበት ክፍያ ሳይፈፀምልኝ፤ ንብረቴም ተወርሶብኝ ግንባታውን አቋርጬ እንድወጣ ተደርጊያለሁ፤ በዚህም ምክንያትም ለከፍተኛ ኪሳራ እና ለአምስት ዓመታት ለህመም ተዳርጌያለሁ» ብለዋል። የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ዶክተር ጫላ ዋታ በበኩላቸው ኮንትራክተሩ ሥራቸውን አቋርጠው የወጡት በገዛ ፈቃዳቸው ነው በማለት ምላሻ ሰጥተዋል።
አቶ ከተማ ኢቲቻ እንደተናገሩት፤ ትምህርት ሚኒስቴር ከ2000 ዓ.ም ጀምሮ አሰልጥኖ ወደ ሥራ ካስገባቸው ኮንትራክተሮች አንዱ ሲሆኑ ባላቸው ብቃት ከ2002 ዓ.ም ጀምሮ በቡሌ ሆራ ዩኒቨርሲቲ ግንባታ ላይ የመሳተፍ ዕድሉን አግኝተዋል። ወደ ግንባታ ሲገቡም በውላቸው መሠረት ዩኒቨርሲቲው ዲዛይን እንዲሰጣቸው በተደጋጋሚ ቢጠይቁም «ዝም ብለህ ሥራ፣ ጀምር ዲዛይን ይሰጠሃል» የሚል ምላሽ ተሰጥቷቸዋል።
ከነገ ዛሬ ዲዛይን ይሰጠኛል በሚል ሁለት ሕንፃዎችን እያፈረሱ ሲገነቡ ቆይተው በ2004 ዓ.ም እንደምንም አጠናቀው አስረክበዋል። ወደ ቀጣዩ ምዕራፍ ለመሸጋገር ግን ዲዛይኑ ሊሰጠኝ ይገባል ብለው ሲጠይቁ የሠሩበት አምስት ሚሊዮን ብር ሳይከፈላቸውና ያፈሯቸው በርካታ የግንባታ ማሽኖች እንዲሁም አንድ የጭነት ተሽከርካሪያቸውን ጥለው ሳይቱን ለቀው እንዲወጡ ተደርገዋል።
«ያለ አንዳች ህጋዊ ደብዳቤ የሠራሁት ሳይከፈለኝና ንብረቴን ወርሰው ካስወጡኝ በኋላም በውጪ ሆኜ በተደጋጋሚ ቅሬታዬን ባቀርብም መልስ የሚሰጠኝ አላገኘሁም» የሚሉት አቶ ከተማ በመቀጠል፤ለኦሮሚያ ቤቶችና ኮንስትራክሽን ቢሮ፤በወቅቱ የትምህርት ሚኒስቴር ለነበሩት ለአቶ ሽፈራው ሽጉጤ፤ ለቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ በተዋረድ አቤቱታቸውን በፅሑፍ ማቅረባቸውን አመልክተዋል።
ግለሰቡ ይብሱንም በዩኒቨርሲቲው ውስጥ የነበሩ አንዳንድ አመራሮች መኖሪያ ቤታቸው ድረስ ሰው እየላኩ ማስፈራሪያና ዛቻ ሲያደርሱባቸው እንደነበር ገልጸዋል። በተሽከርካሪያቸው ውስጥ እየተጓዙ ባለቡት አንድ ቀንም ባልታወቁ ኃይሎች በርካታ ሰነዶችና ማስረጃዎች የተዘረፉባቸው መሆኑን አስረድተዋል።
«በዚህ መሠረትም በቀድሞው የትምህርት ሚኒስትር አቶ ሽፈራው ሽጉጤ 2006 ዓ.ም ጥቅምት 17 ቀን ጉዳዩን የሚያጣራ ኮሚቴ ተዋቅሮ ውሳኔ አስተላልፈው ነበር» በማለት አቶ ከተማ ተናግረዋል። የተቋቋመው ኮሚቴም ጉዳዩን አጣርቶ በእርሳቸው ላይ የተፈፀመው በደል ተገቢነት እንደሌለውና ወደ ሥራቸው እንዲመለሱ ውሳኔ ቢያስተላልፍም ዩኒቨርሲቲው አሻፈረኝ ብሎ መቅረቱን አብራርተዋል።
ጉዳዩን ወደ ፍርድ ቤት ለመውሰድ ለምን እንዳልሞከሩ ተጠይቀው «ዩኒቨርሲቲው ኮንትራክተሮችን ወደ ሥራ ከማስገባቱ በፊት በሚያስፈርመው ውል መሰረት ማንኛውም ኮንትራክተር ከአሠሪው ጋር ካልተስማማ መክሰስ የሚችለው የግንባታውን ሙሉ ወጪ መሸፈን ከቻለ ብቻ ነው የሚል በመሆኑ ወደ ህግ አካል ብሄድም አቅም ስለሌለኝ ተስፋ ቆርጬ ተቀምጫለሁ» ብለዋል።
የአራት ልጆች አባት መሆናቸውን የሚናገሩት አቶ ከተማ በደረሰባቸው ኪሳራና በደል ሳቢያ አዕምሯቸው በመታወኩ ለአምስት ዓመታት በህመም ላይ መቆየታቸውን ጠቁመዋል። ባለቤታቸው ህመምተኛ በመሆኗ ልጆቻቸውን የሚያስተምሩላቸው እና የሚደግፏቸው ጓደኞቻቸው መሆናቸውን አስታውሰው፤ በአሁኑ ወቅት ግን በከፋ ሁኔታ ለችግር መዳረጋቸውንና የሚመለከተው አካል እንደ ዜጋ ፍትህ እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል።
ግለሰቡ ባቀረቡት ቅሬታ ላይ ተመስርተው ምላሽ እንዲሰጡ ያነጋገርናቸው የቡሌ ሁራ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር ጫላ በበኩላቸው፣ ወደ ቦታው ከመጡ አንድ ዓመት ብቻ ማስቆጠራቸውንና ስለጉዳዩም ምንም መረጃ እንደሌላቸው ተናግረዋል። ይሁንና ተፈፀመ የተባለውን በደል በሚመለከት አሁንም ለማየት ፈቃደኛ መሆናቸው ገልፀዋል።
ባደረጉት ማጣራት ግለሰቡ በገዛ ፈቃዱ ሥራውን ለቆ መውጣቱን መረዳታቸውን አመልክተዋል። አዲስ ዘመን ጋዜጣ ግለሰቡ ሥራውን በገዛ ፈቃዳቸው ለቀው ስለመውጣቸው የሚያሳይ ዝርዝር መረጃ ከዩኒቨርሲቲው ለማግኘት ተደጋጋሚ ጥረቶች ቢያደርግም ፕሬዚዳንቱን ጨምሮ የሚመለከታቸው ኃላፊዎች መረጃ ለመስጠት ፈቃደኛ ሳይሆኑ ቀርተዋል።
በተመሳሳይ የኦሮሚያ ቤቶችና ኮንስትራክሽን ቢሮም ስለጉዳዩ ተጠይቆ በአሁኑ ወቅት በቦታው ላይ ያሉት ሁሉም አመራሮች አዳዲስ በመሆናቸው ጉዳዩን የሚያውቅ አካል አለመኖሩን ተናግረዋል።
በጉዳዩ ዙሪያ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ምላሽ እንዲሰጥበት አዲስ ዘመን ጋዜጣ ለሁለት ሳምንታት ያህል ጥረት ሲያደርግ ቆይቷል። በመጀመሪያው ሳምንት ዘርፉን የሚመሩት ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ሳሙኤል ክፍሌ ሥራ አልገቡም፣ ስብሰባ ላይ ናቸው፣ እንደመጡ እንነግራቸዋለን የሚል ምላሽ ከፀሐፊያቸው በተደጋጋሚ ተሰጥቶናል።
በሁለተኛው ሳምንትም ከብዙ የስልክ ልውውጥ በኋላ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊው በአካል ከሚኒስትር ዴኤታው ጋር እንድንገናኝ ነግረውን በቀጠሯችን ብንገኝም እንደተለመደው ሁሉ ሚኒስትር ዴኤታው ስብሰባ ላይ ናቸው የሚል ምላሽ ተሰጥቶን ጉዳዩን በዝዝር ገልጸን በማስታወሻ እንድንጽፍና በማግስቱ ቀጠሮ እንደሚያዝልን ተነግሮን ወጣን። በተባለው ቀንም ብንደውልም ሚኒስትር ዴኤታው መረጃውን ከዩኒቨርሲቲው እንድትወስዱ መርቶበታል የሚል ምላሽ ከህዝብ ግንኙነት ኃላፊው ተሰጥቶታል።
አዲስ ዘመን ቅዳሜ መጋቢት 21/2011