አርሶ አደሩ ወገቡን ጠበቅ አድርጎ የመኸር የግብርና ሥራውን በሚያከናውንበት በዚህ ወቅት በግብአት አቅርቦት፣ በሙያዊ ድጋፍና በመሳሰሉት ከጎኑ የሚሆን ያስፈልገዋል። ድጋፉ ማዳበሪያና የተለያዩ ግብአቶችን በማቅረብ ብቻ ሳይወሰን የግብርና ሥራውን ለማዘመን የሚያግዙ እንቅስቃሴዎች ማካተት ይኖርበታል።
በተለይም በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል ባጋጠመው ጦርነት፣ በኦሮሚያና ሶማሌ ክልል በተከሰተው ድርቅና በደቡብና በሌሎችም አካባቢዎች የበልግ ወቅት ዝናብ አለመጣልን ተከትሎ በግብርና ስራው ላይ የተከሰቱ ችግሮችን በመፍታት በኩልም ራሳቸውን የቻሉ ድጋፍ እና ክትትል የማድረግ ስራዎች በሚያስፈልጉበት ወቅት ላይ እንገኛለን።
በተጠቀሱት ችግሮች በግብርናው ዘርፍ የታዩ የምርት ጉድለቶችን በሚያካክስ መልኩ በርብርብ መስራት ይጠበቃል። በአጠቃላይ በአገራዊ የኢኮኖሚ እድገት ላይ ከፍተኛ ደርሻ ያለውን የግብርና ዘርፍ በክትትልና ድጋፍ በማጠናከር በዚህ የመኸር ወቅት ሥራዎች እንዴት እየተከናወኑ ስለመሆናቸው ባለፈው ሳምንት የአማራና ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልሎችን የክትትልና ድጋፍ ስራዎች ማስቃኘታችን ይታወሳል፤ በዛሬው የግብርና አምዳችን ደግሞ የኦሮሚያና የደቡብ ክልሎችን እንቅስቃሴ እንቃኛለን።
ኦሮሚያ
የኦሮሚያ ክልል ግብርና ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ጌቱ ገመቹ እንደገለጹት፤ ቢሮው የመኸር እርሻ ሥራውን ከዝግጅት ምዕራፍ ጀምሮ ክትትልና ድጋፉን ባለማቋረጥ እየሰራ ይገኛል። በተለይም ኩታገጠም (ክላስተር) የአስተራረስ ዘዴ በቅድመ ዝግጅት ወቅት ትኩረት በመሰጠቱ ክልሉ በዚህ የመኸር ምርት ዘመን ወደ ስድስት ነጥብ ሶስት ሚሊየን ሄክታር መሬት ለማረስ ከያዘው ዕቅድ ውስጥ 75 በመቶ ወይም ወደ አራት ሚሊየን ሄክታሩን በክላስተር ለማከናወን እየሰራ ይገኛል።
በክልሉ በበልግ ወቅት ዝናቡ ዘግይቶ በመግባቱና ፈጥኖም በመውጣቱ በበልግ የተስተጓጎለው የግብርና ሥራ በዚህ የመኸር ወቅት የማካካስ ሥራንም ታሳቢ በማድረግ ነው ወደ ተግባራዊ እንቅስቃሴ የተገባው ይላሉ አቶ ጌቱ። ለዘር የተዘጋጀው መሬት በዘር እየተሸፈነ ይገኛል። ከሶስት ነጥብ ስምንት ሚሊየን ሄክታር መሬት በላይ በተለያየ የሰብል ዘር ተሸፍኗል። ወቅታዊው የዝናብ ሽርጭትም ለግብርና ሥራው ተስማሚ ሆኖ በመገኘቱ ከክልሉ ባሌ፣ ቦረና እና ጉጂ ዞኖች በስተቀር ሁሉም ዞኖች ይህን የዝናብ ስርጭት በመጠቀም የግብርና ሥራቸውን እያከናወኑ ይገኛሉ።
በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል ካጋጠመው ጦርነት ጋር ተያይዞ በአገሪቱ በተፈጠረው አለመረጋጋትና በአንዳንድ የክልሉ አካባቢዎችም የተከሰተው ድርቅ፣ የውጭ ምንዛሪ እጥረት፣ ከዓለም ሁኔታ ጋርም ተያይዞ በዩክሬይንና ሩሲያ መካከል ጦርነት የተከሰተውን ጦርነት ተከትሎ የግብርና ግብአቶች ዋጋ ማሻቀብ፣ ሌሎችም ተያያዥ ክስተቶች በክልሉ የግብርና እንቅስቃሴና ምርትና ምርታማነት ዕድገት ላይ አሉታዊ ተጽእኖ ማሳደራቸው እንደማይቀር ምክትል የቢሮ ሃላፊው ይጠቁማሉ።
አሁንም የክልሉ የተወሰኑ አካባቢዎች በፀጥታና ባለመረጋጋት ስጋቶች ውስጥ መገኘታቸውን ጠቅሰው፣ ለግብርና ሥራ አስቸጋሪ በሆኑት ምዕራብ ወለጋ፣ ቄለም ወለጋ፣ ሆሮጉዱሩ ወለጋ፣ ምሥራቅ ወለጋ እንዲሁም ጉጂና ምዕራብ ጉጂ እንዲሁም የእርስበርስ ግጭት ባለባቸው የቤንሻንጉል ጉሙዝ ድንበሮችና ተፈናቃይ ዜጎች በሰፈሩባቸው አካባቢዎች የምርት መጠን እንደሚቀንስ ይገመታል ይላሉ።
አካባቢዎቹ ችግር ቢኖርባቸውም ገፍቶ እየተሰራባቸው መሆኑንም ነው የተናገሩት። እንደ እሳቸው ገለጻ፤ የቅድመ ዝግጅት ሥራው የፀጥታ ችግር ያለባቸውን አካባቢዎችንም ታሳቢ ያደረገ ነው። በአካባቢዎቹ የዞንና የወረዳ አመራሮችና ባለሙያዎች አማካኝነት አስፈላጊው ሁሉ ለአርሶ አደሩ ቀርቦ የግብርና ሥራው እንዲከናወን እየተደረገ ነው።
በተከሰቱት ችግሮች ሳቢያ ክትትልና ድጋፉ ከሌሎች የክልሉ ዞኖችና ወረዳዎች እኩል እንዳልሆነም ጠቅሰው፣
በአካባቢው የሚገኙት ባለሙያዎችና አመራሮች በሚችሉት ርብርብ እያደረጉ ነው ይላሉ። እኩል ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ እንቅስቃሴ ሲደረግ፤ በቅድመ ዝግጅት ሥራው ላይ ክፍተቶችን በመለየት ውጤታማ ሊያደርጉ በሚችሉ ሥራዎች ላይ ትኩረት አድርጎ መንቀሳቀስም ሌላው አቅጣጫ በመሆኑ ስጋቱን ለመቀነስ ጥረት መደረጉን ነው ያመለከቱት። የክላስተር የግብርና ዘዴን በማጠናከር ክፍተቱን ለመሙላት ጥረት እየተደረገ መሆኑንም ጠቅሰው፣ በዚህ ረገድም ወደ ሥራው ከመገባቱ በፊት ለባለሙያዎች ተገቢው ስልጠና ተሰጥቷል ብለዋል።
እንደ እሳቸው ገለጻ፤ በአየር ንብረት መዛባት ምክንያት ድርቅ ያጠቃቸው አካባቢዎችን በተመለከተ፤ በየአካባቢው የሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች፣ የምርምር ተቋማት፣ ግብረሰናይ ድርጅቶች ምርጥ ዘርና ማዳበሪያ በመግዛትና የተለያዩ ድጋፎችን በማድረግ የተጠናከረ እንቅስቃሴ ተደርጓል። ለአብነትም መደወላቡ ዩኒቨርሲቲ ባሌ በድርቅ የተጎዱ ቆላማው አካባቢዎች ላይ፣ ኦዳቡልቱ ዩኒቨርሲቲ ምዕራብ ሐረርጌ ላይ፣ ቡሌሆራ ቦሮናና ጉጂ ዞኖች ላይ፣ ሐሮማያና ሌሎችም ዩኒቨርሲቲዎች ከፍተኛ ድጋፍ አድርገዋል። በተጨማሪም የክልሉ የወጣቶች ሊግ ተደራጅቶ በማገዝ ያደረገው እንቅስቃሴ የአርሶአደሩን የዘር አቅርቦት ችግር ለመፍታት የተደረገ ርብርብ አንዱ ማሳያ ነው።
የግብርና ግብአት አቅርቦትን በተመለከተ አቶ ጌቱ እንደገለጹት በምርት ዘመኑ ወደ ስምንት ነጥብ አራት ሚሊየን ኩንታል ማዳበሪያ ለማቅረብ ዕቅድ ቢያዝም፣ የግዥው ዋጋ በመናሩ በእቅዱ ልክ ማግኘት አልተቻለም፤ እንዲያም ሆኖ ግን ቀደም ሲል ከነበረ ክምችትና አርሶአደሩ ካዘጋጀው ወደ 46ሚሊየን ሜትሪክ ቶን ማዳበሪያ ጋር ተደራሽነትን ለማጣጣም በመሞከሩ በአቅርቦቱ ላይ ሊኖር ይችላል የተባለው ክፍተት እንደተሰጋው አልሆነም። ዋጋውንም ቢሆን መንግሥት ድጎማ በማድረግ አረጋግቷል።
አርሶ አደሩም በራሱ ምርጥ ዘር የማዘጋጀት ባህል በማዳበሩ የነበረውን የበቆሎ ምርጥ ዘር በአገር በቀል ምርጥ ዘር አቅራቢዎች በኩል አንዲቀርብ በማድረግ ክፍተቱን ለመሙላት ተሞክሯል። አርሶ አደሩም በራሱ ምርጥ ዘር የማዘጋጀት ባህል በማዳበሩ በአቅርቦቱ ላይ በክፍተት የሚነሳ ነገር አላጋጠመም።
በአጠቃላይ በማዳበሪያ አና ምርጥ ዘር አቅርቦት ላይ መንግሥት ጣልቃ ገብቶ በማገዝ እየሰራ በመሆኑ አርሶ አደሩ በዚህ በኩል ችግር ይገጥመዋል የሚል እምነት ባይኖርም፣ ዩሪያን በዘር ወቅትና ከዘር በኋላ የመጠቀም ሁኔታ ስላለ ምናልባት በዚህ በኩል እጥረት እንደሚገጥም ግምት አለ። ይህንንም ቢሆን፣ከህብረት ሥራ ማህበራት ጋር በመሆን ተደራሽ ለማድረግ ጥረት እየተደረገ ነው።
ክልሉ በተለያየ መንገድ ምርትና ምርታማነት እንዲጨምር እየሰራ መሆኑን አቶ ጌቱ ጠቁመዋል። ደቡብ ምራብ ኦሮሚያ፣ ወለጋ፣ ቡኖበደሌ አካባቢዎች በክላስተር የአስተራረስ ዘዴ በቆሎ በስፋት ተዘርቶ በጥሩ ሁኔታ ላይ እንደሚገኝ ጠቅሰው፣ እነዚህ አካባቢዎች በፀጥታ ስጋት ውስጥ ሆነው ውጤቱ እንደተገኘም ነው ያስታወቁት።
‹‹ከግብአት አቅርቦት መካከል አንዱ ሜካናይዜሽን መጠቀም ነው።›› ያሉት አቶ ጌቱ፣ ይህም ከበጋ መስኖ ልማት ጀምሮ እየተተገበረ ይገኛል ይላሉ። ሙሉ ለሙሉ ሜካናይዜሽን ሥራ ውስጥ ባይገባም በትራክተር የማረሱ ሥራ ተጠናክሯል ሲሉም ይገልጻሉ። ከሁለት አመት በፊት ቁጥራቸው ከ2000 የማይበልጥ ትራክተሮች ናቸው የነበሩት፤ በአሁኑ ጊዜ ግን በቁጥር ወደ 5000 ከፍ ብሏል ሲሉ አብራርተዋል።
የምርት መቀነስን ለማስቀረት በምርት መሰብሰብና መውቃት ወቅትም ኮምባይነሮች ጥቅም ላይ እንዲውሉ እንደሚደረግ ጠቁመዋል። የአንዱ ዞን ከሌላው የተለያየ የምርት መጠን እንዳይፈጠር ሜካናይዜሽንን ማጠናከር ይገባል›› ሲሉን አስረድተዋል። የክልሉ በዚህ ጥረቱም በምርት ዘመኑ ወደ 205 ሚሊየን ኩንታል ምርት ለማምረት የያዘውን እቅድ ለማሳካት እንደሆነ ገልጸዋል።
ደቡብ
የደቡብ ክልልም በዚህ የመኸር የግብርና ሥራ ዋና ዋና በሆኑ የሰብል ልማቶች ወደ አንድ ነጥብ ሁለት ሚሊየን ሄክታር መሬት በዘር በመሸፈን 56ነጥብ8 ሚሊየን ኩንታል ምርት ለመሰብሰብ አቅዶ እየሰራ መሆኑን የደቡብ ክልል ግብርና ቢሮ ኃላፊ አማካሪና የእርሻ ልማት ዘርፍ ተወካይ አቶ ዓለምይርጋ ወልደስላሴ ይገልጻሉ። በጋው በመራዘሙ በወቅቱ ሊከናወን የነበረው የግብርና ሥራ የሚፈለገውን ያህል እንዳልሆነ ጠቅሰው፣ ይህንንም በዚህ የመኸር መደበኛ የእርሻ ሥራ ለማካካስ በቅድመ እቅድ ዝግጅቱ ላይ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ እንደሆነ አመልክተዋል።
አቶ ዓለምይርጋ እንዳሉት፤ በበጋው መራዘም በበልግ ወቅት በዘር ያልተሸፈኑና ያልታረሱ የእርሻ መሬቶችን ጭምር በመለየት የመኸር ግብርና ስራው እቅድ አካል ተደርጎ እየተሰራ ነው። በበልግ ወቅት ከክልሉ አመታዊ እርሻ 50 በመቶው ድርሻ ያለው ወይንም ከአንድ ሚሊየን ሄክታር መሬት በላይ በበልግ ይሸፈን ነበር። የበጋው መራዘም በበልግ የግብርና ሥራው ላይ ተጽዕኖ አሳድሯል። በአንዳንድ አካባቢዎች ዘርም አልተከናወነም። የተወሰኑት ደግሞ ከዘር በኋላ ዝናብ በመጥፋቱ በሰብል ላይ ጉዳት ደርሷል።
እስካሁን በተከናወነው ሥራም 53 በመቶ ማሳ ታርሶ ከ80 ሺ ሄክታር መሬት በላይ በዘር ተሸፍኗል። ከአጠቃላይ ዕቅድ ውስጥም 458ሺ ሄክታር መሬት የሚሆነው በኩታ ገጠም (ክላስተር) ዘዴ በመጠቀም ነው ቅድመ እቅዱን ለማሳካት ጥረት እየተደረገ ያለው።
በትራክተር አጠቃቀም ላይም በተመሳሳይ ጥረቶች ተጠናክረዋል ያሉት አቶ አለምይርጋ፣ በመስኖ፣ በበልግና በመኸር ከ1200 በላይ ትራክተሮች በግዥና በኪራይ ጥቅም ላይ እንዲውሉ ተደርጓል ሲሉ ያብራራሉ። በዚህ የመኸር ወቅትም 288ሺ ሄክታር መሬት በትራክተር ለማረስ ነው የታቀደው።ለኩታገጠምና ለሜካናይዜሽን ልዩ ትኩረት ተሰጥቷል።
ተወካዩ ከግብአት አቅርቦት አንጻርም እንዳስረዱት፤ ከ650ሺ ኩንታል በላይ የአፈር ማዳበሪያ በመሰራጨት ሂደት ላይ ሲሆን፣ ግብአቱን በዞን፣ በወረዳና በቀበሌ ውስጥ ዳሰሳ በማድረግ አቅርቦቱ በሌለባቸው አካባቢዎች እንዲዳረስ በማድረግ ክፍተት የመሙላት ሥራ እየተሰራ ነው።
የፌዴራል መንግሥትንም ትብብር በመጠየቅ በተቻለ መጠን በውጭ ምንዛሬ እጥረትና በዓለም ዋጋ መናር ምክንያት የሚያጋጥም ችግርን ለመፍታት ክልሉ ጥረት እያደረገ ነው። ድጋፍና ክትትሉም ሆነ የግብአት አቅርቦቱ በተደራጀ ሁኔታ በተመረጡ የሰብል አይነቶች ላይ ትኩረት እንዲያደርግ በቅድመ እቅዱ የተቀመጠ ሲሆን፣ በዚሁ መሠረትም በመኸሩ ዋና በተባሉ ስንዴ፣ ጤፍ፣ ገብስ፣ ቦለቄ፣ በቆሎ በመሳሰሉት የአዝርእት ሰብሎችና ስድስት የአትክልት የዘር አይነቶች ትኩረት ተደርጎ እየተሰራ ነው።
ተወካዩ የዝናብ ስርጭቱንም በተመለከተ ሲያብራሩ፤ ይህን መረጃ እስከ ሰጡበት ያለፈው ሳምንት ድረስ በነበሩት ቀናት በክልሉ ደቡብ ምሥራቅ የሚገኙ ኮንሶ፣ ደራሼና ሌሎችም፣ ደቡብ ኦሞና አማሮ አካባቢዎች በስተቀር ሁሉም አካባቢዎች ከበቂ በላይ ዝናብ ማግኘታቸውን ጠቅሰው፣ ይህን ተከትሎም የእርሻ ሥራው እየፈጠነ መሆኑን ይገልጻሉ።
እንደ ተወካዩ ገለጻ፤ በበልግ ወቅት ያጋጠመውንም ችግር አስመልክተው ተወካዩ እንደገለጹት፤ በክልሉ ከአመታዊው እርሻ 50 በመቶው ድርሻ ያለው ወይንም ከአንድ ሚሊየን ሄክታር መሬት በላይ በበልግ ይሸፈን ነበር። የበጋው መራዘም በበልግ የግብርና ሥራው ላይ ተጽዕኖ አሳድሯል። በአንዳንድ አካባቢዎች ዘርም አልተከናወነም። የተወሰኑት አካባቢዎች ደግሞ ከዘር በኋላ ዝናብ በመጥፋቱ በሰብል ላይ ጉዳት ደርሷል። ይህን ጉዳት የሚያያካክስ ተግባር በመኸሩ ወቅት ለማከናወን የሚያስችል እቅድ በመኸሩ አቅድ ውስጥ ተካቶ እየተሰራ ይገኛል።
አሁንም በክልሉ ደቡብ ምሥራቅ አካባቢዎች ዝናብ አለመገኘቱ ጫናውን ከፍ እንዳያደርገው ተወካዩ ስጋት አድሮባቸዋል። የእርሻ ሥራውን ለመጀመር የሚያስችል የአፈር ማዳበሪያ ቢኖርም በቂ እንዳልሆነም ይጠቁማሉ። ጉራጌ ስልጤ፣ ሀዲያና ጠንባሮ አካባቢዎች ማዳበሪያ በመጠበቅ ላይ መሆናቸውን ገልጸው፣ ችግሩን ከማእከላዊ መንግሥት ጋር ለመፍታት ጥረት እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።
የተፈጥሮ ማዳበሪያን አዘገጃጀትና አጠቃቀም ላይ የተፈጠረውን ንቅናቄ በጠንካራነት የጠቀሱት ተወካዩ፣ ይህንንም ማዳበሪያ በአነስተኛ ማሳ ላይ በመጠቀም የሚያበረታታ ውጤት መታየቱን ይገልጻሉ።
እንደ አቶ ዓለምይርጋ ገለጻ፤ በክልሉ ከ400ሺ ቶን በላይ የተፈጥሮ ማዳበሪያ ተዘጋጅቷል። ግብአቱ በስፋት ካለበት አካባቢ ወደሌለበት አካባቢ በማዳረስ ክፍተቱን ለመሙላት ጥረት እየተደረገ ነው። ካለፈው በመነሳት በየደረጃው ያለው አመራር በተደራጀ ሁኔታ መንቀሳቀሱም እቅዱን ለማሳካት ተስፋ ሰጪ ነገር ተፈጥሯል። በአጭር ጊዜ ውስጥ ከ80ሺ ሄክታር መሬት በላይ በዘር መሸፈን ተችሏል፤ ይህ የሆነው በጋራ በመሰራቱ ነው። በኩታገጠም የግብርና ዘዴ መከናወኑ ደግሞ ለእስካሁኑ ውጤታማነት አግዟል።
ምርት ተሰብስቦ ጎተራ እስኪገባ በመካከል ላይ የሚያጋጥሙ ነገሮችን ከወዲሁ መገመት ባይቻልም፣ እስካሁን ባለው እንቅስቃሴ ክልሎቹ ዘርፉን በመደገፍ እያደረጉ ያለው ጥረት፣ የዝናብ ስርጭቱና በአጠቃላይ መንግሥት ለዘርፉ የሰጠው ትኩረት በግብርናው ዘርፍ የተያዙ የመኸር ወቅት እቅዶች ውጤታማ እንደሚሆኑ መገመት ያስችላሉ።
ለምለም መንግሥቱ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 25/2014