መቼም ሰው ሆኖ የማይፈራ ሰው የለም። የምንፈራው ነገር ሊለያይ ይችላል እንጂ ሁላችንም የሆነ ነገር እንፈራለን። አንዳንዴ ግን የምንፈራው ነገር ሌላ ቢሆን ብዬ እመኛለሁ። እስኪ አሁን ክረምት ነውና በክረምት ከምንፈራው ዋነኛ ነገር እንጀምር። ዝናብ። ብዙ ሰው ዝናብ ይፈራል። አንዳንዱ ሰው ዝናብ ሲጀምር የሚሮጠው ሩጫ ለተሰንበት ግደይን ያስንቃል። ይወነጨፉታል ነው የሚባለው። አንዳንዱ ደግሞ መንገድ ላይ በአግባቡ እየሄደ ዝናብ ጠብ ጠብ ሲል ከመቅጽበት የሚመነጠቀው ነገር ማርሽ ቀያሪው ምሩጽ ይፍጠርን የሚያስንቅ ነው። የብዙው ሰው አሯሯጥ ዝናብ የጀመረ ሳይሆን ተኩስ የተጀመረ ነው የሚመስለው።
ዝናብ የምንፈራውን ያህል ግን ሁከትን ብንፈራ ጥሩ ነበር። የኛ ሰው በተቃራኒው ነው፤ ዝናብ ሲጀመርብን ብሎ የሚበታተነው ህዝብ ብጥብጥ ሲጀመር ግን በተቃራኒው ወደ ብጥብጡ አቅጣጫ ይሰበሰባል። የሚሰበሰበው ብጥብጡን ለማረጋጋት ወይም ለማሸማገል አይደለም፤ የሚሰበሰበው በቦታው ነበርኩ፤ አይቻለሁ ብሎ ለማውራት ነው።
ደሞ አይጥ የምንፈራ ሰዎች አለን። አይጥ የሚባል ነገር ማየት ቀርቶ አይጥ የሚባለውን ስም ሲሰሙ የሚደነግጡ ሰዎች ብዙ ናቸው። እውነቱን ለመናገር አይጥ የምትወደድ ፍጥረት አይደለችም። ግን ደግሞ ያው ፍጥረት ናት። ስለዚህ አብዝቶ መውደድም ሆነ መጥላት አስቸጋሪ ነው። ቢሆንም አይጥ በብዙ ሰው ትጠላለች።
የአንዳንዶች ፍርሀት አይጥ ሲያዩ ከገዛ ቤታቸው ሸሽተው እስከመውጣት ድረስ ይደርሳሉ። ነገር ግን ሰዎች አይጥ የመጥላታችንን ያህል ቤታችን ውስጥ ልንጠላው የሚገባ ጉዳይ ብዙ አለ። ቤታችን ውስጥ ከአይጥ በላይ አሳፋሪ እና አስፈሪ የሆነ ብዙ ነገር አለ። እንዲያውም ብዙ ነውሮች የሚፈጸሙት በጓዳ ውስጥ ነው። እነዚያን ጉዳዮች ከጓዳችን ማውጣት ሳንችል የስነ ፍጥረት አካል የሆነችውን አይጥ መፍራት እና መጸየፍ አግባብ አይደለም።
የከፍታ ፍርሀት ያለበት ሰውም ብዙ ነው። ፈረንጆቹ ይሄን ፍርሀት አክሮፎቢያ (acrophobia) ይሉታል። ብዙ ሰው ከመሬት ከፍ እያለ ሲሄድ ፍርሀት እየወረረረው፤ እግሩ እየተንቀጠቀጠ፤ እያላበው ይሄዳል። በተለይም አጎንብሶ መሬቱን ሲያይ ራሱን ሊስት ሁሉ ይችላል። የፍርሀቱ ምንጭ በአብዛኛው አእምሮአችን የሚፈጥረው የስጋት ፈጠራ ነው። ብንወድቅ አጥንታችን ሲሰባበር፤ ሰውነታችን እንደ ቲማቲም ሲፈርጥ፤ ለቀባሪ እንኳ የማይመች ሆነን ስንገኝ እያሰብን ነው የምንሰጋው።
ይህ ተፈጥሮአዊ ፍርሀት ስለሆነ በስነ ልቦና ሀኪሞች እገዛ ሊስተካከል ይችላል። ነገር ግን ከፍታን የሚፈራው ብዙ ሰው ሌላኛውን ከፍታ ስልጣንን ቢፈራ የበለጠ መልካም ነበር። በተለይ በኛ አገር ብዙ ሰው ስልጣንን ለመቀበል ምንም ስጋት የለበትም። እውቀቱም፤ ልምዱም፤ ዝግጅቱም፤ ስብእናውም ባይኖረው ና ስልጣን ውሰድ ሲባል አያልበውም፤ እግሩ ብርክ ብርክ አይልም፤ ልቡ ድውድው አይልም፤ ያለምንም ማንገራገር እሺ ብሎ ይቀበላል።
ከከፍታ በላይ ግን መፍራት ያለብን ስልጣንን ነበር። ምክንያቱም ከፍታ ላይ ከወጣ ሰው ተከስክሶ የመሞት ስጋት ያለበት ሁኔታ በመቶኛ ቢሰላ ኢምንት ነው። ስልጣን ላይ ወጥቶ በአደገኛ ሁኔታ የመከስከስ እድል ግን ከሀምሳ በመቶ በላይ ነው። እንዲያውም እሱም ተከስክሶ ህዝብንም ይዞ ገደል የመግባት እድሉ ከፍተኛ ነው።
በሰው ፊት የመናገር ፍርሀት ደግሞ አለ። ይሄ የባህላችን ፍሬ ነው። ገና ከልጅነታችን ዝም በል እየተባልን ነው ያደግነው። ስለዚህም በሰው ፊት መናገር ለብዙዎች ቀላል አይደለም። እንዲያውም ብዙ ሰው ንግግር አድርግ ከምትለው አለት ፍለጥ ብትለው ይቀለዋል። መናገር እየፈለገ እንኳ ነገር ግን ከልምድ ማነስ በሚመጣ ፍርሀት ብዙ ሰው ራሱን መግለጽ ሳይችል ብዙ ነገር ያጣል። እውነቱን ይዞ ንግግር ባለመድፈር የተነሳ በቀጣፊ አፈ ጮሌዎች የሚቀደም እና የሚረታም ብዙ ነው።
ነገር ግን ንግግር ማድረግ አስፈሪ አልነበረም። መፍራት እና መሸሽ የነበረብን ከንግግር ሳይሆን ከውሸት እና ከጥላቻ ንግግር ነበር። አሁን ላይ ኢትዮጵያ ውስጥ በፊትለፊት ንግግር ለማድረግ የሚፈሩ ነገር ግን በማህበራዊ ሚዲያ አስደንጋጭ እና አሳፋሪ ነገር በመናገር ቀዳሚ የሌላቸው ብዙ ሰዎች ተፈጥረዋል።
እንዲያውም አንዳንዶቹን በአካልም ስለምናውቃቸው የሚፅፉትን ስናይ እነሱ ናቸው ወይስ ሌላ ናቸው የሚል ጥያቄ እናነሳለን። እነዚያ ተናገሩ ሲባል አፋቸው የሚያያዝ ነገር ግን በፌስቡክ አገር የሚያውኩት ሰዎች በሰው ፊት መናገርን መፍራት ትተው ሀሳባቸውን ፊትለፊት በነጻነት መግለጽ ቢለምዱ እንዲሁም በፌስቡክ እነሱም ሆነ ሌሎች የሚያደርጉትን ድንፋታ ቢፈሩ እና ቢጸየፉ መልካም ነበር።
የመርፌ ፍርሀት ደግሞ አለ። መርፌ ከመፍራት የተነሳ ሀኪም ቤት ሲሄዱ መድሀኒቱ የሚዋጥ ይሁንልኝ በሚል ከሀኪሞች ጋር ክከርክር የሚገጥሙ ብዙ ሰዎች አሉ። ጥይት የማይፈሩ ሰዎች መርፌ ላለመወጋት ሲንቀጠቀጡ ተምልከተናል። ታዲያ አስገራሚው ነገር ብዙ ሰው የሚፈራው መርፌውን እስኪወጋ ድረስ ነው። ሲወጋ ግን ፍርሀቱ የነበረው ነገር በሙሉ ይጠፋል። የፍርሀቱ ምንጭ አእምሮ ውስጥ የሚፈጠር አስፈሪ ምስል ነው።
የመርፌው ቀስት ቆዳን ሰንጥቆ ሲገባ ማሰብ ብዙ ሰውን ያስበረግገዋል። ነገር ግን ነርሷ ዳበስ ዳበስ አድርጋ መርፌውን አስገብታ ስታስወጣ ያ ሁሉ ስጋት ፉርሽ መሆኑ ይታወቃል። የሚገርመው ነገር ግን እነዚያ መርፌን የሚፈሩ ሰዎች የጥይት ቃታ ለመሳብ ወይም ጩቤን በሰው ሰውነት ውስጥ ለማስገባት ምንም ስጋት የለባቸውም። በዚህም የተነሳ ነው አሁን በአገራችን የንጹሀን ሞት ቀላል ጉዳይ የሆነው። መሆን የነበረበት በተገላቢጦሽ ነበር። መፍራት ያለብን መርፌን ሳይሆን ቃታን ነበር። መሸሽ ያለብን በሀኪም እጅ ያለ መርፌን ሳይሆን በአሸባሪ እጅ ያለ ገጀራን ነው።
ብቻ ሲጠቃለል የምንፈራቸው ነገሮች በሙሉ ልንፈራቸው የሚገቡ አይደሉም። መፍራት የሚበረታታ ባይሆንም በልኩ መፍራት ግን አግባብ ነው። ከፈራን አይቀር ደግሞ መፍራት ያለብን እውነተኛውን አደጋ እንጂ አእምሮአችን የፈጠረውን መሆን የለበትም።
ቸር እንሰንብት!
አቤል ገ/ኪዳን
አዲስ ዘመን ሐምሌ 25/2014