የፋሽን ኢንደስትሪ በዓለም ኢኮኖሚ ላይ ትልቅ ተፅዕኖ ማሳረፍ የቻለ ግዙፍ ዘርፍ ነው። በዘርፉ የተሰማሩ ታላላቅ ዓለም አቀፍ የፋሽን ኩባንያዎች በየዓመቱ በርካታ ቢሊየን ዶላሮችን ያንቀሳቅሳሉ። ከዚህ ባሻገር ኩባንያዎቹ የሚፈጥሩት ሰፊ የስራ እድል ዘርፉ በዓለም ኢኮኖሚ ላይ ትልቅ ሚና እንዲጫወት ማድረጉን መረጃዎች ይጠቁማሉ። እኤአ በ2017 ዓለም አቀፉ የፋሽን ኢንደስትሪ 5.91 በመቶ ማደጉን የሚያስቀምጡ ዓለም አቀፍ መረጃዎች አሉ።
ባለፈው 2020 ይህ ኢንደስትሪ በዓለም አቀፍ ደረጃ ከሁለት ቢሊየን ዶላር በላይ ገንዘብ ያመነጫል ተብሎ የተገመተ ቢሆንም በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት ግቡን መምታት እንዳልቻለም የሚጠቁሙ ጥናቶች አሉ። ይሁን እንጂ ኢንደስትሪው ከወረርሽኙ ተፅዕኖ ጋር እየታገለ በ2022 713 ቢሊየን ዶላር ያመነጫል ብለው የዘርፉ ዓለማቀፍ ባለሙያዎች ግምታቸውን አስቀምጠዋል።
ኢትዮጵያን ጨምሮ በየጊዜው የዓለም ሕዝብን በሚያስደንቅ ደረጃ አዳዲስ ፋሽን ብቅ ማለቱን ቀጥሏል። የቦርሳ፣ የጫማ፣ የልብስ፣ የፀጉር ዓይነት (ስታይል)፣ አረማመድ፣ አነጋገር እንዲሁም የፎቶና የቪዲዮ ምሥሎች ፋሽን የሚለው ጽንሰ ሐሳብ የሚገለጽባቸው ናቸው። የፋሽን ኢንዱስትሪው ከዘመን ዘመንን ተሻግሮ ግዙፍ ገንዘብ የሚንቀሳቀስበት ዘርፍ ከሆነ ሰንብቷል። የፋሽን ኢንዱስትሪ በኢትዮጵያ ከጊዜ ወደ ጊዜ በማኅበረሰቡ ዘንድ ተቀባይነት እያገኘም መጥቷል።
ለዚህ ደግሞ በየጊዜው የሚደረጉ የፋሽን ሳምንቶች ሚና ትልቅ መሆኑን ባለሙያዎች ይናገራሉ። ያም ሆኖ ኢንደስትሪው በኢትዮጵያ ገና ዳዴ የሚል እንጂ በአገር ኢኮኖሚ ላይ ያለውን አቅም ያህል ተፅዕኖ ማሳረፍ እንዳልቻለ ለማንም ግልፅ ነው።
የፋሽን ሳምንት በኢትዮጵያ ከተጀመረ ከአሥር ዓመታት በላይ ሆኖታል። በእነዚህ ዓመታት ውስጥ በኢትዮጵያ የፋሽን ዕድገት ትንሽ የማይባል ለውጥ ማሳየቱ ግን አይካድም። በተለይም በዘርፉ የኢትዮጵያ የሆኑ አልባሳት በተለያዩ ቀለሞችና ዲዛይኖች መምጣት መጀመራቸውን ተከትሎ በማኅበረሰቡ ዘንድም በይበልጥ ተቀባይነት አግኝተዋል ማለት ይቻላል። ለዚህ ደግሞ በኢትዮጵያ የፋሽን ዲዛይን ውስጥ ረዥም ዓመታት ያስቆጠሩ ባለሙያዎችም ትልቁን ድርሻ እንደሚይዙ ወጣት ባለሙያዎች በተለያዩ መድረኮች አስተያየት ሲሰጡ ይታያል።
የኢትዮጵያን የፋሽን ኢንደስትሪ ካለፉት አሥር ዓመታት በላይ ጉዞ የሚቃኙ የዘርፉ ምሁራን ብዙ ለውጦች እንደተስተናገዱ ያምናሉ። ከአለባበስ ጀምሮ በተለይም በከተሜው ማህበረሰብ ዘንድ የጫማ፣ የፀጉርና ሌሎችም የፋሽን ዓይነቶች በየጊዜው ይንፀባረቃሉ። ፋሽኖቹ ከጊዜ ወደ ጊዜ ደግሞ የባህላዊ ዕደ ጥበቦች የዘመኑበትና ሁልጊዜ ተለባሽ ተደርገው እየተሠሩ ይገኛል። የዚህ የፋሽን ዕድገት ከሚታወቁ የልብስ ዓይነቶች ውጪ የሆኑትንም ጭምር ይዞ ብቅ ያለ መሆኑን ገበያዎች ላይ መቃኘት ይቻላል። ከአልባሳትና መሰል የፋሽን ዓይነቶች በተጨማሪ የፎቶና የቪዲዮ ባለሙያዎች ሥራቸውን የሚያዳብሩበት ዘርፍም ነው።
የፋሽን ሳምንታት አዳዲስ ዲዛይነሮች ሥራዎቻቸውን ይዘው የሚቀርቡበት መድረክ ነው። ከዚህ በተጨማሪ ዓለም አቀፍ ዲዛይነሮችና ሞዴሎች ሥራዎቻቸውን የሚያቀርቡበት በመሆኑ ለአዲሶች ጥሩ ልምድ የሚያገኙበት ትልቅ አጋጣሚ ነው። በፋሽን ሳምንቱ በዋናነነት ከሚሠሩ ሥራዎች ውስጥ ነባር ዲዛይነሮች ለአዲስ ባለሙያዎች የመማርያ መድረክ መዘጋጀቱ አንዱ ነው። በኢትዮጵያ እንደ የአካባቢው የአየር ጠባይ የተለያዩ አልባሳት ይለበሳሉ። ይህ ለዲዛይነሮች ምቹ ነው።
የተለያዩ የፋሽን ዲዛይኖችን እንደሚገኙበት ማሳያ ነው። ነገር ግን እነዚህን አልባሳት ዲዛይን ተደርገው፣ ጥሬ ዕቃዎች ከውጭ ገብተውና ሌሎችም ነገሮች ሲታከሉበት ደንበኞች እጅ እስኪደርሱ ድረስ ውድ ይሆናሉ። በዋነኝነት በእጅ የሚሠሩ የትኛውም ምርቶች ውድ ናቸው። የትም አገሮች ላይ የሚሠሩ አልባሳት፣ ጌጣጌጦች፣ ቦርሳዎችና ሌሎችም የእጅ ሥራ ውጤቶች እጅግ ውድ መሆናቸው ይታወቃል። በኢትዮጵያ ውስጥም በተመሳሳይ መልኩ የእጅ ሥራ ውጤቶች የሆኑ ነገሮች ሁሉ ውድ ናቸው። ይህንን የዋጋ መናር እንዲቀንስ የሚደረገው በብዛት በማምረትና ተጠቃሚውን በማብዛት ነው።
በኢትዮጵያ የፋሽን ኢንዱስትሪው በተፈለገው ደረጃ ላለማደጉ ብዙ ምክንያቶች ይጠቀሳሉ። ከችግሮቹ ውስጥ አንዱ በራስ ግብዓት ያለመጠቀም ነው። ሌላው የፋሽን ኢንዱስትሪውን ትኩረት የሚሰጡት ግለሰብ ብቻ መሆናቸው ነው። በዚህም የፋሽን ዲዛይነሮችና በዘርፉ የሚሳቡ ሰዎች ብቻ የሚንቀሳቀሱበት በመሆኑ በተፈለገው ልክ እንዳያድግ ምክንያት ሆኗል። በሌሎች ዓለማት የፋሽን ኢንዱስትሪ ብዙ ገንዘብ የሚንቀሳቀስበትና ለኢኮኖሚም ቢሆን ከሌሎች ዘርፎች ባልተናነሰ ሁኔታ አስተዋጽኦ የሚያደርግ ነው።
ወደ እኛ አገር ስንመለስ ዘርፉ አሁን አሁን የመነቃቃት ሁኔታ ቢታይበትም መንግስት የሚፈለገውን ትኩረት ሰጥቶታል ለማለት አያስደፍርም። የፋሽን ዘርፍ እንዲያድግና ለአገር ብዙ ጥቅም እንዲሰጥ፣ የግል ድርጅቶችና በመንግሥት ትልቅ ትኩረት መስጠት እንደሚገባቸው ባለሙያዎች ደጋግመው ሲናገሩ ይደመጣል። ለዚህ ደግሞ የፋሽን ሳምንት ዓይነት መድረኮች በብዛት ያስፈልጋሉ። የመንግሥት፣ ባለሀብቶች በፋሽን ሳምንቱ በመጋበዝ ስለፋሽን ዘርፍ እንዲረዱትና ከተጠቀምንበት ብዙ ሀብት የሚገኝበት መሆኑን ለማስረዳት እንደሚያስችልም ያምናሉ።
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 25/2014