
“MISS WORLD ETHIOPIA” በመባል የሚዘጋጀውን ዓለም አቀፍ የቁንጅና ውድድር ላይ ለመሳተፍ ሞዴሊስት ሀሴት ደረጀ ወደ ስፍራው ከማቅናቷ አስቀድሞ ሰሞኑን በቦሌ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ በቪአይፒ ሳሎን በክብር ተሸኝታለች።
ሞዴሊስት ሀሴት ደረጀ በሜካኒካል ኢንጂነሪንግ ሁለተኛ አመት የአዲስ አበባ ሳይንስ እና ቴክኖሎጅ ተማሪ ናት። ዘንድሮ በሕንድ ሃይድራባድ የሚዘጋጀውን ዓለምአቀፍ የቁንጅና ውድድር ከመቶ ሠላሳ በላይ ሀገሮች የሚሳተፉበት ትልቅ የቁንጅና ውድድር ሲሆን በዚህ ውድድር የኢትዮጵያን መልካም ገፅታ ለማስተዋወቅ መንግሥት እየሠራ የሚገኘውን ሥራ ከማስተዋወቅ አንፃር ለውጭ ዓለም ለማስተዋወቅ የሚረዳ ትልቅ ዓለም አቀፍ የቁንጅና ውድድር ነው፡፡
ይህ ዓለም አቀፍ የቁንጅና ውድድር ከ2014-2024 እ.ኤ.አ ድረስ ፕሮግራሙን ያዘጋጁት ተቋማት ኢትዮጵያ ቢዊቲ ኩንስ እና ፓሽን ፕሮሞሽን እና ኢቨንት ኃ/የተ/የግ/ማህበር በጋራ ያዘጋጁት ዓለም አቀፍ የቁንጅና ውድድር ነው፡፡
ኢትዮጵያን በዓለም አቀፍ የቁንጅና ውድድር መድረክ የወከለችው ሀሴት ባለፈው ታህሳስ ወር “The Miss World Ethiopia 2024” ውድድር ላይ አንደኛ ሆና በማሸነፏ ለቀጣይ ሁለት ሳምንታት በህንድ በሚካሄደው 72ኛው “Miss World Festival” ኢትዮጵያን ወክላ ለመቅረብ ችላለች።
ወጣቷ ሞዴሊስት ባለፈው ታህሳስ “Miss World Ethiopia” አሸንፍ ይህን እድል ባገኘችበት ወቅት “ትምህርቴ ላይ ትኩረት ባደርግም ሁሌም ሕይወት ከትምህርትና ከመፅሐፍ የተሻገረ ትርጉም እንዳለው አምናለሁ” በማለት ተናግራለች። በዚህም ከትምህርት ሰዓቷ ውጪ ያላትን ጊዜ ሙዚቃ በማድመጥ፣ በሞዴሊንግ ሙያና በህብረተሰብ በጎ ፍቃድ አገልግሎት በማዋል ታሳልፋለች።
ወጣቷ ሞዴሊስት ከዚህ ቀደምም በአንድ ዓለም አቀፍ የሞዴሊንግ ውድድር ተሳትፋ ሁለተኛ ሆና ነበር ያጠናቀቀችው። “ያ አጋጣሚ ራሴን ፈልጌ እንዳገኝና ወደተሻለ የእድገት ደረጃ እንድሸጋገር ጥሩ ልምድ ቀስሜበታለሁ” በማለት ተናግራለች።
ሕይወት ትርጉም የሚሰጠው በሌሎች ሰዎች ላይ አዎንታዊ ተፅዕኖ ማሳደር ሲቻል ነው ብላ የምታምነው ወጣቷ ሞዴሊስት፣ በልደታ የካቶሊክ ካቴድራል ትምህርት ቤት ውስጥ ሳለች በተለያዩ ክበቦች ውስጥ በመሳተፍ በአየር ንብረት ለውጥና መሰል እንቅስቃሴዎች ውስጥ የራሷን አስተዋፅኦ በማበርከት ትታወቃለች። በወጣትነት እና በሴቶች ላይ በማተኮር በህብረተሰብ እና ሠብዓዊነትን በተመለከቱ ጉዳዮች ላይም ተሳታፊ ነች። ዛሬ ለደረሰችበት ደረጃና ለገነባችው ማንነትም ይህ ማህበራዊ ተሳትፎዋ እንደሠራት ትናገራለች።
ሴቶችን በተለይም ወጣት ሴቶችን ስለቴክኖሎጂና የዲጂታል እውቀት እንዲሁም ስለ ፆታ እኩልነት ማስተማርና በዚህም ተጠቃሚ እንዲሆኑ ማበረታታት ተፅዕኖ ፈጣሪነታቸውን እንደሚያጎላና ወሳኝ ሚና እንዲኖራቸው ያደርጋል የምትለው ወጣት ሞዴሊስት፣ ሀገሯን በዓለም አቀፍ መድረክ መወከሏ ሌላ ተጨማሪ የሕይወትና የሙያ ልምድ የምትቀስምበትን አጋጣሚ እንደሚፈጥርላት ታምናለች። ይህም ሌላ የተሻለ ነገር ለመፍጠር መጀመሪያ እንጂ መጨረሻ አይደም የሚል አመለካከት አላት። ይህ የመጀመሪያ ጉዞዋ እንደመሆኑ ለቀጣዩ ይበልጥ ተነሳሽነትን እንደሚፈጥርባትም ገልፃለች።
በጋዜጣው ሪፖርተር
አዲስ ዘመን ሰኞ ግንቦት 4 ቀን 2017 ዓ.ም