ፋሽን በወንዶች ጸጉር ቁርጥ

የወንዶች ጸጉር እንክብካቤና ቁርጥ ቀድሞ በቤተመንግሥትና በከፍተኛ ባለሥልጣናት እንደተጀመረ ይነገራል። ነገሥታትና የነገሥታት ልጆች ጸጉራቸውን በተለየ መልኩ አሳምረውና አበጅተው ሕዝብ ፊት ይቀርቡ እንደነበርም የታሪክ መዛግብት ያስረዳሉ። ይህ የጸጉር ቁርጥ ልምድም ቀስ በቀስ ወደ ከቤተ መንግሥት በመውጣት ወደ ማህበረሰብ ወርዶ በበርካቶች ዘንድ ደርሷል።

በተለይ ከ19ኛው ክፍለ ዘመን መገባደጃና 20ኛው ክፍለ ዘመን መጀመሪያ ላይ በተለያየ አይነትና ምርጫ በተለይ ወንዶች ጸጉራቸውን ተስተካክለውና አስተካክለው ውበትን ተላብሰው መታየት ጀምረዋል። በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ላይ ወታደሮች ይቆረጡት የነበረው የጸጉር ቁርጥም ለብዙ ዓመታት የበርካታ ወንዶች ምርጫ ሆኖም ቆይቷል።

በአሁኑ ወቅት ዛሬ ፋሽን መልከ ብዙ ሆኗል። የወንዶች የጸጉር ቁርጥ ዘመኑ ባፈራቸው መሣሪያዎች ታግዞ ማስዋብ ቀላል ሆኗል። ወንዶችም ጸጉር መድመቂያና ውበትን መሆኑን ተገንዝበዋል። ለጸጉር አቆራረጣቸውም ልዩ ትኩረት መስጠት ጀምረዋል።

በርካቶችም ከዘመንና ወቅት ጋር፣ ለበዓላትና ለአዘቦት ቀን ለተለያየ ወቅትና ቦታም ሁኔታው የሚፈቅደውና በዚያ ሥፍራ የተለመደ መልክና ቀለም ያለው የጸጉር አቆራረጥ “ስታይል” ምርጫቸው ሲያደርጉም እያስተዋልን እንገኛለን።

ኢትዮጵያውያን ለዘመናት በራሳቸው የጸጉር አሠራር ፋሽን ሲከተሉ ኖረዋል። ጥንት ወጣቶች ጸጉራቸውን አጎፍረው አንዳንዴም ሹሩባ ተሠርተው ይታዩ ነበር። የህፃናትና ታዳጊዎች ቁንጮ እንዲሁም የነገሥታቱ ሹሩቧም ለዚህ ማሳያዎች ናቸው።

ዛሬ ላይ በየመንደሩ በዘመናዊ መልክ እየተለመዱ የመጡ የጸጉር አሠራር ፋሽኖች፤ ትናንት ኢትዮጵያውያን በራሳቸው ይዋቡባቸው ከነበሩት የጸጉር አሠራሮች ጋር እጅጉን የተቀራረበ መሆኑን ማየት ይችላል። ለዚህም በኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች ዛሬም ድረስ ሳይቋረጡ ያሉት የጸጉር ማስዋብና እንክብካቤዎችን መጥቀስ ይቻላል።

ለዘመናት የአፋር ወንዶች ጸጉራቸው በተለያየ ዕፅዋት በመንከባከብ በመጠቅለልና ወዛማና አንፀባራቂ እንዲሆን የማድረግ ጥበብ ዛሬም ድረስ ከተሜዎች መጠነኛ ለውጥ በማድረግ በፋሽንነት ይተገብሩታል።

አሁን ላይ ለጸጉራቸው ልዩ ትኩረት የሰጡት ወንዶች ጸጉራቸውን ዘመኑ ባፈራቸው የተለያዩ ማሽኖችና የጸጉር ቁርጥ መሥሪያ ቁሳቁሶች በመታገዝ በውበት ባለሙያዎች ወይም የጸጉር አስተካካዮች ይዋባሉ። አብዛኞቹ ወንዶችም የጸጉር ቁርጥ ፋሽን ተከታይ ሆነዋል። ወንዶቹ ከሌሎች ተመልክተው አልያም ጸጉር ቤት ገብተው የሚፈልጉትን የጸጉር አስተካካይ ለባለሙያዎቹ በመንገር ይዋባሉ።

ሰመረ ካሳ በአዲስ አበባ ፒያሳ አካባቢ ደንበኞቹን በፈለጉት እና ወቅቱ ባመጣቸው መሣሪያዎች በመጠቀም ላለፉት ለስምንት ዓመታት በጸጉር አስተካካይነት ሙያ እየሠራ ይገኛል። በሙያው በቆየባቸው ዓመታትም በየወቅቱ የተለያየ ፋሽን ያላቸው የጸጉር ቁርጦች ቢኖሩም በአብዛኛው በወንዶች ዘንድ የሚመረጠው የፀጉር ቁርጥ ግን ተመሳሳይ መሆኑን ይናገራል።

የጸጉር ቁርጥ አይነቶቹ በእድሜ እና በሰዎቹ ፍላጎት የሚወሰን መሆኑን የሚናገረው ሰመረ፤ በተለይ ህጻናቱ በራሳቸው ምርጫ የሚስተካከሉት አልፎ አልፎ ቢሆንም በአብዛኛው ግን በወላጆቻቸው ምርጫ ላይ ተመሥርተው መሆኑንም ይገልፃል። ብዙዎች በተለይ በእድሜ ገፋ ያሉት አንድ ቁጥር ወይም ኖርማል የተሰኘው ቁርጥ እንደሚመርጡ ይናገራል።

እንደ ባለሙያው ገለፃ፣ በበርካታ ወጣቶች ዘንድ እንደ ፋሽንነት የሚወሰደውና የሚወደደው ‹‹ፍሪዝ›› የሚባለው አይነት ነው። ከስር ዙሪያውን ምልጥ ተደርጎ ወይም በጣም በአጭሩ ተቆርጦ ከፍ እያለ ሲሄድ ጥቁረቱ እየጨመረ ሙሉ በሙሉ በመተውና ቀንሶ በማስተካከል ብቻ በተለያዩ ቅባቶች ጸጉሩን መጠቅለል (መፈረዝ) ነው።

ከፍሪዝ ባሻገር አዲስና በተለያዩ የመገናኛ ብዙሃን የተመለከቱትን የጸጉር ቁርጥ አይነት ምርጫቻቸው የሆነ ደንበኞችም አሉት። ከተለያዩ ማህበራዊ ሚዲያዎችና ድረ ገጾች በተመለከቱት የጸጉር ቁርጥ መስተካከልም እየተለመደ መጥቷል። በተለይ ቅርፆችና ምስሎች በጸጉራቸው ላይ በተለየ መልኩ እንዲሳልላቸው ወይም በልዩ ሁኔታ እንዲሠራላቸው የሚፈልጉም በርካታ ናቸው።

በተለያዩ ፀጉር ማስተካከያ ቤቶች ውስጥም በፎቶግራፍ በተደገደ መልኩ የጸጉር ቁርጦች ስታይል በ‹‹ሜኖ›› መልክ ይሰቀላል። ሰመረ እንደሚያስረዳው፣ የጸጉር ቁርጦቹ አይነትና እና ስያሜ ከቦታ ቦታ እንዲሁም ከቤት ቤት ይለያያል።

ከዋና ዋናዎቹ የጸጉር ቁርጥ አይነቶች መካከልም ፓንክ (በወጣቶች የሚመረጥ)፣ የላይኛው የጸጉር ክፍል ሳይነካ ከስር ብቻ ማስተካከልና ቅርጹን ማስተካከል (ፍሪዝ)፣ ዜሮ በአንድ ቁጥርና በሁለት ቁጥር (የማስተካከያ ማሽን ጥርሶች ናቸው) መካከለኛ አጭር ቁርጥ፣ አፍሮ (ቀደም ሲል በብዛት የነበረና አሁንም አልፎ አልፎ ያለ)፣ ጆንትራ ቮልታ፣ ባላቶሊ የተለመዱና ጎልተው የሚጠቀሱ ናቸው።

‹‹የወንዶች ጸጉር ቁርጥ በዘመናት ሂደት ውስጥ እየተለዋወጠ አንዴ ፋሽን ሆኖ ቆይቶ እየጠፋ መልሶ ከመጠነኛ ለውጥ ጋር የሚመጣ ነው የሚለው›› ባለሙያው፣ አንድ የጸጉር ቁርጥ አይነት ለበርካታ ዓመታት ፋሽን ሆኖ ሊቆይ እንደሚችልና የሴቶቹን ያህል በዘመን ሂደት ውስጥ የጎላ ለውጥ ሲኖረው እንደማይታይም ይጠቅሳል።

ባለሙያው እንደሚያስረዳው፣ ወንዶች የሚቆረጡት የጸጉር ቁርጥ እንደ እድሜያቸው ምርጫቸውም የተለያየ ነው። በየጊዜው የሚለመዱ የጸጉር ቆረጣ ስልቶች ወይም ፋሽኖች በአብዛኛው በወጣቱ ዘንድ ይዘወተራሉ። እድሜያቸው ከፍ ያሉትና በአነስተኛ የእድሜ ደረጃ የሚገኙ ወንዶች በአንፃሩ የተለመደና ብዙም ወጣ ያላለ አቆራረጥን ምርጫቸው ያደርጋሉ።

የጸጉር አቆራረጥ ስልቶች በእድሜ እንደሚለያይ ሁሉ ወቅት ወይም ክረምትና በጋን መሠረት አድርጎም ሊመረጥ ወይም ሊወሰን ይችላል። ክረምት ላይ አሳጥሮ መቁረጥ ይቀንሳል። ከዚህ ይልቅ ጸጉር ባለበት መንከባከብና ቅርጹን ማስተካከል በብዙዎች ይዘወተራል። በአንጻሩ ደግሞ በጋ ላይ አሳጥሮ በተለያየ ቅርጽ መሠራትን ብዙዎች ያዘወትራሉ። ይህም የብርድና የሙቀት ወቅት መሆን የሚፈጥረው ምርጫ ነው።

በአዲስ አበባ ተዘዋውረን በተመለከታቸው የወንዶች የውበት ሳሎኖች ውስጥ የፀጉር ቁርጥ ዋጋ በአማካይ ከ40 ብር እስከ 500 ብር እንደሆነ ታዝቧል። ለዋጋው መለያየትም የሚጠቀሙዋቸው የፀጉር ማስተካከያ መሣሪያዎች ጥራት፣ የውበት ሳሎኖቹ የሚገኙባቸው ቦታና የፀጉር አስተካካዮችን ልምድ መሠረት ያደረገ እንደሆነም መረዳት ችሏል።

በጋዜጣው ሪፖርተር

አዲስ ዘመን ሰኞ ሚያዝያ 27 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You