“The Condemned” ወይም “ፍርደኛው” ብዬ ወደ አማርኛ የመለስሁት በስኮት ዊፐር ጸሐፊነትና ዳይሬክተርነት ፤ በዘግናኝ ድርጊቶች የተሞላ ፣ በኩይንስላንድ ተቀርጾ ፣ በፈረንጆች አቆጣጠር በ2007 ዓ.ም ለዕይታ የበቃ ፊልም ነው ። ስቲቭ ኦስቲን ፣ ቪኔ ጆንስ ፣ ሮበርት ማሞን ፣ ቶሪ ሙሴት ፣ ማድሊን ዌስትና ሪክ ሆፍማን ተውነውበታል ። አስር የሞት ፍርደኞች ተገደው ሕይወትን እስከመጠፋፋት የሚያደርስ ሕገ ወጥ ፍልሚያ ውስጥ ሲገቡ በቀጥታ የቴሌቪዥን ስርጭት ማስተላለፍ የፊልሙ ዋና ማጠንጠኛ አጽመ ትይንት ነው ።
ፊልሙ ኢያን ብሬኬል የተባለ የናጠጠ ሀብታም የቴሌቪዥን አዘጋጅ (ፕሮዲውሰር) 40 ሚሊዮን ተመልካቾችን በቀጥታ ስርጭት ለማግኘትና ክብረወሰን ለመስበር ሲል በቀረጸው በዚህ የቴሌቪዥን ቅርጽ (ፎርማት) የሄደበትን የጭካኔና የግብዝነት ጥግ ያሳያል ። ከሚያስገኝለት ገንዘብና ዝና ውጭ የሰው ልጅ ክቡር ሕይወት ግድ የማይሰጠው ኢያን በዓለማችን በሙስና ከሚታወቅ አንድ የሳልቫዶሮ እስር ቤት የሞት ፍርደኛ የሆነውን አሜሪካዊውን ጃክ ኮናርድን ይገዛና በመላው ዓለም ከሚገኙ ሌሎች እስር ቤቶች ከተገዙ ዘጠኝ የሞት ፍርደኞች ጋር በደቡብ ፓሲፊክ ወደ ሚገኝ ምድረ በዳ ደሴት ይወስዳቸዋል ።
በሕይወታቸው ተወራርደው በሚያደርጉት ፍልሚያ መጨረሻ ላይ አሸንፎ በሕይወት የሚተርፈው ፍርደኛ የሞት ፍርዱ ተሽሮለት ቀሪ ዘመኑን በቅንጦት የሚመራበት ዳጎስ ያለ የገንዘብ ሽልማት ይበረከትለታል ። በሁሉም ተፋላሚዎች ቁርጭምጭምት ላይ ደግሞ 30 ሰዓታትን ጠብቆ የሚፈነዳ ፈንጂ አስጥምዶባቸዋል ። አሸናፊ ሆኖ በሕይወት የተረፈ ፈንጁ ይመክንለታል ።
ፍልሚያው በበይነ መረብ በቴሌቪዥን ለመላው ዓለም በቀጥታ ይሰራጫል ። ኢያን እነዚህ ፍርደኞች ሕይወታቸውን ለማትረፍ የሚያደርጉትን ለማየት የሚዘገንን ትንቅንቅና ፊልሚያ ቀጥታ እያሰራጨ ስቱዲዮ ቁጭ ብሎ የቀጥታ ስርጭቱ ተመልካች ቁጥር በደቂቃዎች መቶ ሺዎችን አልፎ ሚሊዮን ፣ 10 ሚሊዮን ፣ 20 ሚሊዮን ሲገባ በደስታ ይፈነድቃል ። የፍርደኞቹ መገዳደል ለእሱ ጉዳዩ አይደለም ።
በሮማን ኢምፓየር ነገሥታት በአፊ ቴአትር በዙፋናቸው በግርማ ተኮፍሰው ባሪያዎች እርስ በርስ በሰይፍ ተቃልተው ፣ በፋስ ተፋልጠው ፣ በሳንጃ ተሞሻልቀውና በአራዊት ተዘንጥለው ሲሞቱ ወይናቸውን እየተጎነጩ እንደሚዝናኑት እንደሚያውካኩት ፤ ኢያንም በ21ኛው መክዘ ዘግናኝ ፍልሚያ በቀጥታ በቴሌቪዥን በማሰራጨት ዘግናኝ ሰቆቃንና ሞትን ይነግዳል ። ጭካኔን ይሸቅጣል ።
የሚያሳዝነው ይህ በፈጠራው ዓለም ያወገዝነው እኩይ ተግባር በሀገራችን በየዕለቱ በገሀድ የሚፈጸም መሆኑ ነው ። ለነገሩ ፈጠራ የገሀዱ ዓለም ነጸብራቅ ነው አይደል የሚባለው ። በዛሬዋ ኢትዮጵያ ቢያንስ አራት ኃይላት የሞት ፍርደኛ የሆኑ እስረኞቻችንን ፈተው መልቀቃቸው ሳያንስ አይዟችሁ እያሉ የሞራል ስንቅ እየቋጠሩ ፤ ቀለብ እየሰፈሩ ፣ ተልዕኮና ስምሪት እየሰጡ ሀገራችንን ወደ ለየለትና የማያባራ የእርስ በርስ ግጭት በመዝፈቅ ለማፍረስ ተናበውና ተቀናጅተው ሌት ተቀን ያለ እረፍት እየሰሩ ነው ።
አራቱ ኃይላት ካልኋቸው የመጀመሪያው በታሪካዊ ጠላታችን ግብጽ የሚዘወረው ሲሆን ፤ ሁለተኛው አፍቃሪ ሕወሓት የሆነውና በአሜሪካ የሚሽከረከረው የምዕራባውያን ሚዲያ ፣ የሰብዓዊ መብት ተቆርቋሪ ነን ባዮች እነ አመነስቲን ጨምሮ ሕወሓት አገዛዝ ላይ እያለ በየዓለምአቀፍ ተቋማቱ የሰገሰጋቸውን እነ ዶ/ር ቴዎድሮስ አድሀኖንምና እንደ ማርቲን ፕላውት ያሉ ምንደኞችን ሲያካትት ፤ ሶስተኛው ኃይል ደግሞ ሕወሓትና የእሱ ተላላኪዎች ሲሆኑ አራተኛው ኃይል ደግሞ ከፍ ብሎ በተጠቀሰው ፊልም እንደተመለከተው እንደ ኢያን ብሬኬል ገንዘብና ዝና እስካስገኘለት ድረስ ንጹሐን ቢጨፈጨፉ ፣ ቢፈናቀሉ ፣ ቢዘረፉና ሀገር ብትተራመስ እንጥፍጣፊ ርህራሄና ደንታ የሌለው “ጋዜጠኛ” ፣ “አክቲቪስት” ፣ ዩቲውበርና በማሕበራዊ ሚዲያው ስድ የተለቀቀ ጭፍራ የተሰባሰበበት ነው ።
እነዚህ ኃይላት እንደ ሀገርና ሕዝብ ለሀገራችን ሕል ውና ፣ ሉዓላዊነትና የግዛት አንድነት ጠንቅ ናቸው ብለን ፤ ከኋላቀርነትና ከድህነት እንዳንላቀቅ እንቅፋት ሆነውብናል ብለን ፤ አብሮነታችንን ፣ አንድነታችንን ከፍ ሲልም ኢትዮጵያዊነታችንን አደጋ ላይ ይጥሉብናል ብለን ሞት ፈርደን ያሰርናቸውን እንደ ኢያን ብሬኬል እየፈቱና እየገዙ ሊያበጣብጡንና ሀገራችን ሊያፈርሱ በሙሉ ኃይላቸው ተነስተውብናል። ለመሆኑ ለ3ሺ ዓመታት እንደ ሀገር በአብሮነት እንድንቀጥል እንቅፋት እንዳይሆኑብን ሞት ፈርደን ያሰርናቸው ፍርደኞች እነማን ነበሩ!? የሁሉንም እስረኞቻችንን ስም ለመዘርዘር ጊዜው ባይበቃንም ዋና ዋናዎችን እናንሳ ።
እንደ ሀገርና እንደ ኢትዮጵያዊ ለዘመናት የኖርነው ጥላቻን ፣ ጎሰኝነትን ፣ ልዩነትን ፣ ቂመኝነትን ፣ በቀልን ፣ ፖለቲካዊ ሟርትን ፖለቲካዊ ጥንቆላንና ፖለቲካዊ ቡዳነትን ፣ የደባና የሴራ ፖለቲካን ፣ መጠፋፋትን ፣ ቅናትን ፣ ስስትን ፣ ውሸትን ፣ የፈጠራ ትርክትን ፣ የታሪክ ምርኮኝነትን ፣ ክህደትን ፣ ወዘተረፈ አስረንና ቀፍድደን ፤ የሀገርና የሕዝብ ፍቅርን ፣ ሰላምን ፣ መተሳሰብን ፣ አንድነትን ፣ መቀባበልን ፣ ይቅርባይነትን ፣ ንግግርን ፣ መመካከርን ፣ መከባበርን ፣ ወዘተረፈ ተንከባክበንና አቅፈን ነው ጥንታዊት ሀገርና ሀገረ መንግሥት ሊኖረን የቻለው ። ይሁንና ለግማሽ ክፍለ ዘመን ያህል በተለይ ደግሞ ላለፉት 30 ዓመታት ተቋማዊና መዋቅራዊ ሆኖ የተዘራው ጎሰኝነት ፣ ሀሰተኛ ትርክት ፣ የፈጠራ ቁጭትና የመበላላት ፖለቲካ በመሀላችን ልዩነትን ፣ መጠራጠርንና ጥላቻን በመጎንቆሉ መግቢያዬ ላይ የጠቀስኋቸው አራቱ ኃይላት እንደ መልካም አጋጣሚ በመጠቀም በብርቱ እየፈተኑን ይገኛል ።
በተለይ ሞትንና ግጭትን በመሸቀጥ በንጹሐን ጭፍጨፋ ፣ መፈናቀልና መዘረፍ እንጀራቸውን የሚያሰፉ ፤ ትዳርን በማፍረስ ልጆችን በመበተን ፤ ያልሞተውን ሞተ ፣ ያልታመመውን የአልጋ ቁራኛ ሆነ ፤ ያልታሰረውን ታሰረ ፤ የታሰረውን ተፈታ ፤ የተሾመውን ተሻረ ፤ የተሻረውን ተሾመ ፤ ተጠርጣሪ ወንጀለኛ ሲያዝ ፋኖ ተከበበ ፤ ወዘተረፈ የሚል በሬ ወለደንና የሴራ ፖለቲካን የሚያራግቡ በላይክ ፣ በሼርና በቪው ብዛታቸው የሚታበዩ አክቲቪስት ፣ ፖለቲከኛና ዩቲውበር ተብዬዎች በየደቂቃው በሚቀፈቅፉት ሟርትና ጥንቆላ ኢትዮጵያ የምትባል ሀገር ፤ ኢትዮጵያዊ የሚባል ዜጋ ፣ ጋራው ፣ ሸለቆው ፣ ተራራው ፣ ሜዳው ፣ ምንጩ ፣ ጅረቱና ወንዛወንዙ ፣ ወዘተረፈ ጠፍተው ፣ ፈልሰውና ተሰደው አልቀው ምድረ በዳ ሆነዋል ።
እንደነሱ በመላ ሀገሪቱ ጭፍጨፋ ፣ ግጭትና ጦርነት ነግሷል ። በየቀኑ መርዶ ፣ ሟርትና ቀውስ በርክ ቷል ። እንደነዚህ ኃይላት ሟርት የኢትዮጵያ ነገ በድቅድቅ ጨለማ የተዋጠ ነው ። ይህን ስል በሀገራችን ችግር የለም ለማለት አይደለም ። ችግሩ ሳይጋነን በሴራና በደባ ፖለቲካ ሳይታጀል በገለልተኝነት ከእነምንጩ መታየት ሲገባው የሰብስክራይብ ፣ የቪው ፣ የላይክና የሸር ቁጥርን ለማብዛት በሚደረግ ስግብግብነት ሀገር አደጋ ላይ እየወደቀች ነው ። አበው እማው በእንቅርት ላይ ጀሮ ደግፍ እንዲሉ ሀገራችን ከውጭም ሆነ ከባንዳዎች ዕለት ዕለት የሚቀፈቀፍባት ችግር ሳያንስ እነዚህ ከግል ጥቅማቸውና ዝናቸው ውጭ ሌላ የማይታያቸው እኩያን ሀገራችንን ከማመስ እንዲቆጠቡ እንደ አንድ ሀገር ወዳድ ዜጋ እማጸናለሁ ።
ሀገራችን ከግብጽ ፣ ከሱዳንና ከባንዳው ሕወሓት ጋር በቀጥታም በውክልናም ጦርነት ላይ ናት ማለት ይቻላል ። ለዛውም የለየለት የመረጃና የዲፕሎማሲ ጦርነት ላይ ። ሀሰተኛ መረጃን ደግሞ እንደ ከሀዲውና እፉኝቱ ትህነግ የጦር መሳሪያ (ዌፐናይዝ) ያደረገ ድርጅትም ሆነ ሀገር የለም ። በዓለማችን እንደ ራሽያው የስለላ ተቋም ኤፍኤስቢ መረጃን እንደ ጦር መሳሪያ የተጠቀመ ወይም የሚጠቀም የለም ቢባልም የትህነግ ርዝራዥና የዲያስፖራ ጭፍራ ግን በገገማነትና በገልጃጃነት አሳምሮ ይበልጠዋል ።
ላለፉት 47 ዓመታት ርካሽ የፖለቲካ ትርፍ ለማግኘት ሀሰተኛ መረጃን ከክላሹ መሳለመሳ በስፋት ተጠቅሟል ። እንደሸሚዝ ከሚቀያይረው ርዕዮት ዓለም ይልቅ ለሀሰተኛና የተዛባ መረጃ እንዲሁም ለፈጠራ ትርክት መታመን ይቀለዋል ። በውንብድናውም ሆነ በአገዛዙ ጥሩ አርጎ ያረጋገጠልን ይሄን እኩይ ማንነቱን ነው ። በሕግ ማስከበርና የህልውና ዘመቻውም ሆነ በኋላ ሆን ተብሎ በተዛባና በሀሰተኛ መረጃ የጸረ ኢትዮጵያ ፕሮፓጋንዳና የማጠልሸት ዘመቻውን በመደበኛና በማህበራዊ ሚዲያው እያፈራረቀና እያጃመለ ተያይዞታል። መደበኛውም ሆነ ማህበራዊ ሚዲያው በሀገር ቤትም ሆነ በውጭ በተጠና ፣ በተቃናጀ ፣ በተናበበና በተመጋገበ አግባብ መዋቅራዊና ተቋማዊ ሆኖ ይመራል ።
ይህ ጸረ ኢትዮጵያ ፣ ጸረ እውነትና ጸረ ፍትሕ የሕዝብ ግንኙነትና የሚዲያ ከፍ ሲልም የዲፕሎማሲ ደባና ሻጥር በሀገር ውስጥ በጌታቸው ረዳ ይመራል ። አሁን ግን በበላይነት የሚዘውረውና የሚያሽከረክረው በምንደኛውና ጥቅሙ በተነካበት እብሪተኛና ማንአህሎተኛ (chauvinist) የትህነግ ርዝራዥና ጭፍራ ዲያስፖራ ነው ። ለዚህ እንዲያግዘው ደግሞ ፤” የትግራይ ወዳጅነት አገናኝ ቢሮ “( Tigray Friendship Liaison Office ) በተሰኘ ተቋም አማካኝነት በቀድሞው ዲፕሎማት ወንድሙ አሳምነው እንደሚመራ መስፍን አማን የተባሉ ጸሐፊ በፍትሕ መጽሔት ፤ 3ኛ አመት ፣ ቁ111 ፣ ታህሳስ እትም ላይ ፤” ከወታደራዊ ሽንፈት ወደ ዲፕሎማሳያዊ ትንቅንቅ “ በሚል ርዕስ ባስነበቡን ማለፊያ መጣጥፍ ተረድተናል ።
በመንግሥታቱ ድርጅት የዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ቴዎድሮስ አድሀኖም በጀኔቭ በመንግሥታቱ ድርጅት ሕዝብ ልማት ፈንድ ባልደረባው ዶ/ር ኪዳኔ አብርሃ ከአምባሳደር ብርሃነ ገብረክርስቶስ ጋር በመቀናጀት የአውሮፓውን የዲፕሎማሲና የዓለምአቀፍ ሚዲያውን እጅ ለመጠምዘዝ በተደረገው ርብርብ የአንበሳውን ደርሻ ወስደዋል ። ከአትላንቲክ ማዶ በአሜሪካ ያለው ተመሳሳይ እንቅስቃሴ ለአምባሳደር ፍስሐ አስግዶም በአደራ መሰጠቱን እኝሁ ጸሐፊ ጠቁመዋል ። የቀድሞው ታጋይ ሙሉጌታ ገብረህይወት (ጫልቱ ) ከመለስ ዜናዊ ወዳጅ አሌክስ ዲወል ጋር በመሆን የትህነግን ተስካር ለማሳመር እየባዘኑ ነው ። የኦባማ የብሔራዊ ደህንነት የቀድሞ አማካሪና የአዲሱ የባይደን አስተዳደር ተሿሚ ሱዛን ራይስ ፣ የአሜሪካ የልማት ተራድኦ (ዩኤስኤይድ) ዳይሬክተር ጌይል ስሚዝ ፣ የሒውማን ራይትስ ዋች ኃላፊ ኬኔትስ ሮዝ ከእነ የማነ ኪዳኔ ( ጀማይካ )ጋር በመሆን ዓለምአቀፍ ሚዲያውንና የሰብዓዊ መበት ተሟጋቾች ላይ ተጽዕኖ በማሳደር ስራ ተጠምደዋል ።
በትግራይ ክልል የተካሄደውን የሕግ ማስከበር ዘመቻ ከዘር ማጥፋትና ማጽዳት ጋር ለማጣረስ እየኳተነ ያለው ሌላው ከሀዲ ዶ/ር መሀሪ ታደለ ነው ። በዚያ ሰሞን በመደበኛውና በማህበራዊ ሚዲያው ስለወሬሳው ትህነግ ሽንጡን ገትሮ ሲሟገት የነበረው ማርቲን ፕላውት ፤ የቢቢሲ የአፍሪካ አርታኢ ዊል ሮስ ቢቢሲ አማርኛንና ትግርኛን በትህነግ ካድሬዎችና ደጋፊዎች በመሙላት እና ኖርዌያዊው ሸተል ትሮንቮል እንደነ ቢቢሲ ባሉ ዓለምአቀፍ ሚዲያዎች በመቅረብ ለከሀዲው ትህነግ በመወገን የተዛባና የሐሰት መረጃ በመንዛት ትህነግ አፈር ልሶ እንዲነሳ እየማሰኑ ነው ።
የቀድሞው ፓትሪያሪክ የአቡነ ጳውሎስ ልዩ ረዳት ስታሊን ገብረስላሴ (ስምን መልዓክ ያወጣዋል እንዲሉ ፤ ጆሴፍ ስታሊን በአስር ሚሊዮኖች የሚቆጠሩ የሶቪየት ዜጎችን የጨፈጨፈ ሰው በላ ገዥ ነው ፤ ) ፣ አሉላ ሰለሞንና፣ ዳንኤል ብርሃኔና ሌሎች የትግራይ ሚዲያ ሀውስ ሰዎች ደግሞ የሀገር ቤቱንና የውጭውን የትህነግን የፕሮፓጋንዳ ማሽን መካኒኮች ናቸው ። የትግራይ ጦርነት ባህላዊ ጨዋታው ነው ። ትግራዋይ ሁሉ ትህነግ ነው ሲሉ ካለማፈራቸው ባሻገር በሀገሪቱ ከተፈጸሙ ጭፍጨፋዎች ጀርባ እጃቸው አለበት ።
ከፍ ብየ የጠቃቀስኋቸው የቀድሞ ታጋዮች ፣ አምባሳደሮች ፣ በዓለምአቀፍ ተቋማት የሚሰሩ ፣ የውጭ ሀገር ዜጎች ፣ አክቲቪስቶች በመማጸኛ ከተማው መሽጎ ከነበረው ከሀዲው የትህነግ ስብስብ እና አዲስ አበባን ጨምሮ በመላው ሀገሪቱ ካሰማራቸው ጭፍራዎቹ ጋር በመቀናጀትና በመናበብ የፈጠራ ትርክታቸውን ከመለፈፋቸው ባሻገር የተዛባና ሐሰተኛ መረጃ በመደበኛውና በማህበራዊ ሚዲያው በመንዛት ሀገራችንን በጦር መፍታት ቢሳናቸው በወሬ ለመፍታት ሌት ተቀን እየተረባረቡ ነው ። በዋናነት ትግራይ ሚዲያ ሀውስን (TMH ) ፣ ትግራይ ፈርስት ፣ አይጋ ፎረም ፣ ትግራይ ፕሬስ ፣ ቮይስ ኦፍ ትግራይ ፣ ትግራይ ኦን ላይንና ሰሞኑን ደግሞ እንደአሸን የፈሉ ድረ ገጾችና ዩቲውቦች ሀሰተኛ መረጃውን ሌት ተቀን ያንበለብላሉ ። የአጋሮቻቸውን መደበኛና ማሕበራዊ ሚዲያዎችን በተውሶ ይጠቀማሉ ።
ማሕበራዊ ሚዲያዎችን አቀናጅቶ የሚጠቀመው በተለምዶ ዲጂታል ወያኔ በመባል የሚታወቀው የከሀዲው ትህነግ ጭፍራ በሺዎችና በአስር ሺዎች የሚቆጠር የፌስ ቡክ ፣ የቲዊተር ፣ የቴሌግራም ፣ የኢንስታግራምና የዩቲውብ ሀሰተኛ አካውንት በመክፈት ጥላቻን ፣ ልዩነትን ፣ ዘረኝነትንና ልዩነትን የሚያቀነቅኑ የፈጠራ መረጃዎችን በመደበኛና በማሕበራዊ ሚዲያዎች ያለረፍት ሌት ተቀን ይነዛሉ ።
ለጊዜውም ቢሆን አመነስቲ ኢንተርናሽናልን ፣ ሒውማን ራይትስ ዋችን ፣ በመንግሥታቱ ድርጅት የሰብዓዊ መብት ኮሚሽንን ፣ በመንግሥታቱ ድርጅት የሰብዓዊ ረድኤት ማስተባበሪያ አገናኝን /ዩኤንኦቻ/ ፣ የባይደንን አስተዳደር ፣ ዓለምአቀፍ ሚዲያውን ፣ ወዘተረፈ በማሳሳት ግዳይ ጥለዋል ። እውነትንና ፍትሕን ታቅፈን እንድንቀር አድርገዋል ። ውሸት እውነትን ፣ ጨለማ ብርሃንን ረቷል ። ደካማው የኮምንኬሽንና የዓለምአቀፍ ግንኙነት ስራችን ውድ ዋጋ አስከፍሎናል ። ሉዓላዊነታችን ተደፍሯል ። በፈተና ላይ የነበረው ለውጥ ጠልሽቷል ።
ዙሪያችንን ከበው አሰፍስፈው ሊውጡን ደጅ ቆመው ለሚጠብቁን እንደ ግብጽ ላሉ ታሪካዊና ወቅታዊ ጠላቶቻችን የልብ ልብ እንዲሰማቸው አድርጓል። እውነት ለመናገር እንደ ሀገር ወዳድ ዜጋ ያበግናል ። ያብሰከስካል። አሁንም ካለፈው ስህተታችን ተምረን ስትራቴጂካዊ በሆነ አግባብ እየሰራን አለመሆናችንና ዛሬም አስተባባይና ተከላካይ መሆናችን በማያዳግም አግባብ ሊታረም ይገባል ።
ሀገራችን ኢትዮጵያ በጀግኖችና በሀቀኛ ልጆቿ ታፍራና ተከብራ ለዘላለም ትኑር !!!
አሜን።
በቁምላቸው አበበ ይማም (ሞሼ ዳያን)
fenote1971@gmail.com
አዲስ ዘመን ሐምሌ 24 ቀን 2014 ዓ.ም