«… በዛሬው ቀን መላው ዓለም አተኩሮ ይመለከተናል አካባቢያችንም በተጠራጣሪዎችና ተስፋ በሚያስቆርጡ የተመላ ነው። አፍሪካውያን እርስ በእርሳቸው በመጣላት የተለያዩና የተከፋፈሉ ናቸው የሚሉ አሉ። ጉዳዩ እውነትነት አለው። ይህ መጥፎ አስተያየት ያላቸው የተሳሳተና ሃሳባቸው ሁሉ ከንቱ መሆኑን በስራችን እናሳያቸው የሚሉም አሉ። ሌሎች ደግሞ አፍሪካውያን ባለፉት ዘመናት የደረሰባቸውን ጭቆና በማሰብ የሕዝቦቻቸው የወደፊት እድል የተቃና እንዲሆን ተጣጥረው ለመስራት ቆርጠው ተነስተዋል ይላሉ።
እነዚህ ለኛ ለአፍሪካውያን በጎነት የሚያስቡ ደግሞ ያልተሳሳቱ መሆናቸውንና በእኛም ላይ የጣሉት እምነት የሚገባ መሆኑን በተግባራችን እንመስክር። አፍሪካ ከትናንትናው አፍሪካ ወደ ነገው አፍሪካ በመሸጋገር ላይ ትገኛለች። የዛሬውም ሁኔታ እየተሻሻለ ካለፈው ጊዜ እየራቅን እያደር ወደ ገነነው ዓለም በመጠጋት ላይ እንገኛለን።
ክፍለ ዓለማችንን በተሻለ ሁኔታ እናቃርባለን ብለን የተነሳንበት ስራ ሊቆይ አይችልም ብንፈልግም እንኳን ልናዘገየው አንችልም ማድረግ የሚገባን ይልቅ ጊዜው ሳያልፍብን የኛን መፈጸም ነው። …..» ይህን ዲስኩር ግንቦት አስራ አራት ቀን አስራ ዘጠኝ ሃምሳ አምስት ዓ.ም ቀዳማዊ አጼ ኃይለ ስላሴ የአፍሪካ አንድነት ድርጅት የምስረታ በአል በአዲስ አበባ ሲካሄድ በመክፈቻ ሥነሥርዓቱ ላይ በጉባኤው ለታደሙ ነጻ የአፍሪካ ሀገራት መሪዎች የተናገሩት ነበር።
ይኸው ዛሬም ከሃምሳ ዘጠኝ ዓመት በኋላ አፍሪካውያን የራሳቸውን ችግር በራሳቸው የመፍታት አቅም የላቸውም የሚለው የተንሸዋረረ እይታ ያልተለያቸው ሀገራት በጉዳያችን እየገቡ ከመፈትፈት አልታቀቡም። በመሰረቱ እነዚህ አገራት በችግር ፈቺነትም ሆነ በረጂነት ወደ አህጉራችን ሲመጡ ሁሌም የራሳቸውን ድብቅ ጥቅም የሚያስጠብቅላቸውን ቅድመ ሁኔታ አስቀምጠው ነው።
ይህ እንግዲህ በአፍሪካ ሀገራት ከሚከሰት እያንዳንዱ ችግር በስተጀርባ ነገር ከመጠንሰስ መሳሪያ እስከማስታጠቅ ያላቸውን ጣልቃ ገብነት የአደባባይ ሚስጥር ሳናነሳ ነው። አፍሪካውያን የቀኝ ግዛት ዘመን ከመከሰቱ በፊት ተፈጥሯዊም ሆነ ሰው ሰራሽ ችግሮቻቸውን በራሳቸው አቅም በራሳቸው ልጆች እየፈቱ በሺዎች የሚቆጠሩ ዓመታት ማሳለፋቸው እስኪዘነጋ ድረስ ዛሬ መፍትሄዎችን የሚሻ ጆሮና አይን ሁሉ የሚያዘነብለው ወደ ምእራቡ ዓለም (አሜሪካና አውሮፓውያን) ነው።
ቀዳማዊ ኃይለ ስላሴ የዛሬ ስልሳ ዓመት ግድም እንዳሉት ሁሉ ከቀናት በፊት ለይፋዊ የስራ ጉብኝት አዲስ አበባ የተገኙት የሩስያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌይ ላቭሮቭ ያረጋገጡትም ይህንኑ ሀቅ ነው። የውጭ ጉዳይ ሚንስትሩ ግልጽ በሆነ ቋንቋ ሀገራቸው ሩስያ «ለአፍሪካዊ ችግሮች፤ አፍሪካዊ መፍትሄዎች» የሚለውን መርህ በቁርጠኝነት እንደምትደግፍ አስታውቀዋል። ይህ አካሄድ አገም ጠቀም ለሆነው የእነ አሜሪካን ጣልቃ ገብነትም ትልቅ መልእክት የሚያስተላልፍ ነው።
ምእራቡ ዓለም በአፍሪካ ሀገራት የውስጥ ጉዳይ የሚያደርጉትን ጣልቃገብነት እንደ አንድ በዓለም አቀፍ ሕግ የተቀመጠ መብታቸው አድርገው በመውሰድ በልበ ሙሉነት እየሄዱበት ከሆነ ውሎ አድሯል። ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ደግሞ ከፍ ባለ ጣልቃ ገብነት በአንድ ሀገር የውስጥ ጉዳይም ሁሉም ነገር ይመለከተናል በሚል እየተንቀሳቀሱ ነው። ለዚህ አይነቱ ፈር የለቀቀ ጣልቃ ገብነት ላለፉት አራት ዓመታት በኢትዮጵያና በኢትዮጵያውያን ጉዳይ ምን እንዳደረጉና እያደረጉ እንዳሉ ማየት በቂ ነው ።
ምእራቡ ዓለም ከቅኝ አገዛዝ በኋላ በአፍሪካውያን መካከል የተነሱ የድንበር ግጭቶች ውስጥ (የኢትዮ- ኤርትራን ጨምሮ) እራሳቸውን በአደራዳሪነት በመሰየም በቅኝ ግዛት ዘመን ውሎችና ሰነዶችን ሲቆምሩ ማየት የተለመደ ነው። በዚህ ቁማር አፍሪካውያን የቱን ያህል ዋጋ እንደከፈሉና አሁንም እየከፈሉ እንደሆነ የአደባባይ ሚስጥር ነው።
ከታላቁ ህዳሴ ግድብ ጋር በተያያዘም ያለው እውነታ ከዚህ የተለየ አይደለም። ችግሩ በአፍሪካውያን በራሳቸው የጋራ ተጠቃሚነት መርህ ሊፈታ የሚችል ሰፊ እድል እያለው ፤ይህንን እድል የሚያጨነግፉ ጣልቃ ገብነቶች ተበራክተው ይታያሉ። በአፍሪካ ህብረት ማእቀፍ ውስጥ ድርድር እየተካሄደበት ባለው በዚህ አፍሪካዊ ጉዳይ በአሜሪካና በአውሮፓውያን በኩል በኢትዮጵያ ላይ ከማስፈራሪያ እስከ ግልጽ ዛቻ ሲሰነዘርበት ቆይቷል።
በተለይም የአሜሪካው የቀድሞ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ «ግብጽ የህዳሴውን ግድብ በሚሳኤል ልታፈነዳው/ ልታፈርሰው» ትችላለች የሚለው ማስፈራሪያ አዘል መልእክታቸው እነሱ ጉዳያችንን ምን ያህል ጉዳያቸውና የጥቅማቸው ማስጠበቂያ እንዳደረጉት አመላካች ነው። በዚህ ሂደት ውስጥ በጣም የሚገ ርመው ግን እንደ አንድ አፍሪካዊ ወንድማማች ሕዝብ በመተያየት ብቻ ሳይሆን የአባይ ውሃም የህዳሴው ግድብም ጉዳይ በቀጥታ የሚመለከታቻው ስምንቱ የላይኞቹ ተፋሰስ (ኬንያ፣ ዩጋንዳ፣ ታንዛኒያ፣ ኮንጎ፣ ብሩንዲ፣ ሩዋንዳ፣ ደቡብ ሱዳን እና ኤርትራ) ሀገራት በሚጠበቀው ደረጃ ለጉዳዩ ትኩረት ሰጥተውና አንድ አቋም ይዘው ተሳታፊ አለመሆናቸው ነው።
የምእራቡ ዓለም ጣልቃ ገብነት ጥቅማቸውን ከማስጠበቅ አልፎ አፍሪካን በመከፋፈልና በማተራመስ ብቻ የሚቆም አይደለም። በተለይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየገነገነና ከቀን ወደቀን እየጨመረ የመጣው በሀገራት የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ የመግባት አባዜ ዘላለም የበላይ ሆነን መኖር አለብን የሚል አይነት ነው። አንዳንድ ጊዜ በሰብአዊ መብት ጥሰት ስም የግለሰቦችን ጉዳይ ሳይቀር በማንሳት ከመንግሥት ጋር ሲነታረኩም ይታያል።
በአሁኑ ወቅት ሃያ ሰባት ዓመት እንዳሻቸው ሲጋልቡት ለነበረው አሸባሪው ሕወሓትን ነፍስ ለማዘራት የተደረጉ ጥረቶች የዚሁ ጣልቃ ገብነት አንዱ ማሳያ ነው። ቡድኑ አሁንም የትግራይን ሕዝብ እንደ ማያዣ አድርጎ የፖለቲካ ቁማር እንዲቆምር እድል ሰጥቶታል። ሀገርና ሕዝብ ያልተገባ ዋጋ እንዲከፍሉ የልብ ድንዳኔ ሆኖታል ።
መንግሥት ለአፍሪካዊ ችግሮች አፍሪካዊ መፍትሄ በሚል የያዘው አቋም ፤ አፍሪካዊ ችግሮችን ለመፍታት ስትራቴጂክ አቅም የሚፈጥር ነው። አስተሳሰቡ የውስጥ ችግር ላለባቸው ብቻ ሳይሆን በተለያዩ ምክንያቶች እሰጥአገባ ውስጥ ላሉና ግጭት ላንዣበበባቸው የአፍሪካ ሀገራትም ለራስ ችግር በራስ ልጆች መፍትሄ መሻት እንደሚቻል አመላካች ነው።
አሸባሪው ሕወሓትም ሆነ በሀገር ውስጥና በሌሎች ዓለማት የሚገኙ የሃሳብና የተግባር ደጋፊዎቹ ለውጭው ዓለም ተላላኪ በመሆንና በጣልቃ ገብነታቸው በመተ ማመን የጀመሩትን ጉዞ ደግመው ደጋግመው ሊፈትሹት ይገባል።
በተጨማሪም ዛሬም ድረስ በአፍሪካ ሀገራት መካከል ከቀኝ ግዛት ጋር የተያያዙና ሌሎችም በርካታ ችግሮች እንዳሉ እሙን ነው። ይህም ሆኖ የአፍሪካውያንን ፖለቲካዊም ሆነ ኢኮኖሚያዊ ችግር ለመቅረፍ እውቀት ብቻ ሳይሆን አፍሪካዊ ሥነ ልቦና ያስፈልጋል። ይህ አፍሪካዊ ሥነ ልቦና ያለው ደግሞ እኛው አፍሪካውያን ዘንድ ነው። በመሆኑም በምንም አይነት ሁኔታ ወስጥ ብንሆን እኛ አፍሪካውያን የችግራችንን መፍትሄ ከራሳችን ልጆች ከራሳችን አማላጅና ሽማግሌዎች ልንጠብቅ ይገባል እላለሁ።
ራስወርቅ ሙሉጌታ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 24 ቀን 2014 ዓ.ም