የኦፓል ማእድን ወደ ውጭ ሀገር በመላክ ንግድ ተሰማርቶ እየሰራ ነው፤ በዚህ ስራ እስከሚሰማራ ድረስ ግን ብዙ ፈተናዎችን አሳልፏል። ፈተናዎቹን አሸንፎ፣ ተጠምዶባቸው ከነበሩ ሱሶች ከማውጣት አልፎ፣ ራሱን ከፍታ ላይ ማስቀመጥ ችሏል። ለዜጎች የስራ እድል መፍጠር ለሀገሪቱ የውጭ ምንዛሬ ግኝት የበኩሉን አስተዋጽኦ እያደረገም ነው። ማእድን ላኪው አቶ በላይ ደምሌ።
እኛም አቶ በላይ ያለፈባቸው የሕይወት ውጣ ውረዶችና በተለይም የበርካታ ወጣቶች ሕይወት በከንቱ ባክኖ እንዲቀር የሚያደርገውን የሱስና የሱሰኝነት እስር ቤት ሰብሮ አሁን ለሚገኝበት ስኬት የበቃበት የሕይወት መንገድ እጅግ አስተማሪ ነውና አቶ በላይን የዛሬ የስኬት አምድ እንግዳችን አድርገነዋል።
ተወልዶ ያደገው ደቡብ ወሎ፤ ደላንታ ወረዳ ወገል ጤና ከተማ ነው። ከአንደኛ እስከ ሰባተኛ ክፍል ያለውን ትምህርቱን በወገልጤና ትምህርት ቤት ተከታትሏል፤ ከስምንተኛ እስከ አስረኛ ክፍል የተማረውም በዚያው በወገልጤና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ነው።
የመሰናዶ ትምህርቱን ደሴ በሚገኘው ሆጤ መሰናዶ ትምህርት ቤት እየተከታተለ ባለበት ወቅት አንድ ማስታወቂያ ይመለከታል። አስራ አንደኛ ክፍል እያለ። የፌዴራል ፖሊስ የሥራ ማስታወቂያ ነው። ወጣቱ ከልጅነቱ ጀምሮ ለስፖርት ልዩ ዝንባሌ ያለውና ስፖርታዊ እንቅስቃሴዎችንም አዘውትሮ የሚሠራ ቁመናውም ለእዚህ የሰጠ ነበርና ማስታወቂያውን በዋዛ አልተመለከተውም፤ ለፖሊስነት ተወዳድሮ አለፈናም በ1994 ዓ.ም ፌዴራል ፖሊስን ተቀላቀለ። በስራው አዲስ አበባ ተመድቦ ከመጣ በኋላም እስከ 1999 ዓ.ም ድረስ ፌዴራል ፖሊስን አገለገለ።
“አዲስ አባባ ውስጥ ፌዴራል ፖሊስ ሆኜ እያገለገልኩ ሳለ በተለያዩ ምክንያቶች የተነሳ በሕይወቴ ደስተኛ አልነበርኩም›› የሚለው አቶ በላይ ፣ ከዚህ ሕይወት ዞር ያለ እየመሰለው ጫት መቃም፣ ሲጋራ ማጨስና አልኮል መጠጣት ውስጥ ይገባል። ቀስ በቀስም በእነዚህ ሱሶች በእጅጉ እየተጠመደ የመጣበትን መጥፎ አጋጣሚ ያስታውሳል። እንደ ዋዛ የተጀመረው የሱስ አምጭ ነገሮች ልምምድ እየሰፋ መጣ፤ አዕምሮና አካሉ መሸከም ከሚችለው መጠን በላይ የሱስና የሱሰኝነት የመከራ ቀንበር አረፈበት፤ ሱስና ሱሰኝነት ብቻ ሳይሆን እሱ የወለደው መዘዝ እየተወሳሰበና እየገዘፈ መጥቶ ከአቅሙ በላይ ሆነበት፤ ሕይወቱ እጅጉን ተመሰቃቀለ።
በዚህ የተነሳም የፖሊስነት ሥራውን በአግባቡ መሥራት የማይችልበት ደረጃ ላይ ደረሰ። የተከበረውንና የሚወደውን የፖሊስነት ሙያውን ትቶ ወደ ትውልድ አገሩ ወገል ጤና ደላንታ ተመለሰ። በዚያም ከአስጨናቂው የሱስና የሱሰኝነት ሕይወት ጋር እየታገለ በትንሿ የወገል ጤና ከተማ በተላላኪነትና በደላላነት ኑሮን እንደ አዲስ “ሀ” ብሎ ጀመረ።
የሱስሰኝነት ልክፍቱ ግን የፖሊስነት ሥራውን በቀላሉ እንደተወው በቀላሉ ሊተወው የሚችለው አልሆንለት አለው። ሥራውን ለቆ ወደ ትውልድ ሀገሩ መመለሱ እንኳንስ ለችግሩ መፍትሔ ሊሆነው አንድ ጊዜ አግኝቶ ሁለተኛ ለመድገም ቀናትን መጠበቅ ግድ እንዲሆንበት አደረገው፤ የዕለት ጉርስን አግኝቶ ማደር ጀብዱ በሆነበት የደላላነት ሥራ፣ ራስን ከመምራት አስቸጋሪ የኑሮ ግብግብ ጋር ተደማምሮ ከመሻሻል ይልቅ የሱሰኝነት ደረጃው ይበልጡኑ ተባብሶ በእርሱ አገላለጽ “ከሰውነት ተራ እስኪወጣ” አደረሰው።
ችግሩ ከሱሰኝነትም አልፎ እጅግ አስከፊ የሚባል የጤና ችግርን አስከተለ፤ እያደር ራሱን በሕልውና ስጋት ውስጥ ያገኘው ጀመር። “የነበርኩበትን ሁኔታ በምን ቃል እንደምገልጸው ይከብደኛል። ሱስ ከሰውነት ተራ እስከመውጣት ብቻ አይደለም ለአእምሮ ህመም ጭምር እንድዳረግ ጭምር አርጎኝ ነበር፤ በተደጋጋሚ ራሴን ለማጥፋት ሞክሬ እግዚአብሔር አትርፎኛል” በማለት ያን የመከራ ጊዜውን ያስታውሰዋል።
ፌዴራል ፖሊስ ሆኖ ማገልገል ከጀመረበት 1994 ዓ.ም አንስቶ ሥራውን እስከለቀቀበት 1999 ዓ.ም ፣ ከዚያም በወገል ጤና ከተማ እስከ 2007 ዓ.ም ድረስ ለሰባት ዓመታት በድለላ ሥራ እስከቆየበት በጥቅሉ ከአሥራ ሁለት ዓመታት በላይ በከባድ ተስፋ አስቆራጭ ሕይወት ቆይቷል፤ አንድ ቀን ግን “የሞት ያህል ቢከብደኝምም ከዚህ አስከፊ የሱሰኝነት ሕይወት፣ ራሴ ከገባሁበት አስፈሪ ማጥ እንደምንም አሸንፌ ለመውጣትና ለተሻለ ሕይወት መውለድ አለብኝ ብዬ ወሰንኩ” ይላል። “ከዚያም በውሳኔዬ ፀናሁ፤ እግዚአብሔር ተጨምሮበት ከእብደትና ከሞት ደረጃ አድርሶኝ ከነበረው ከዚህ አስከፊ የሱሰኝነት ሕይወት ወጣሁ” ሲል አቶ በላይ ይገልጻል።
ሕይወቱን የሚለውጥበትን የተሻለ ሥራ መሥራት እንዳለበት ከራሱ ጋር ይማከር ጀመር። ለዚህም ከሁሉም የተሻለ ሆኖ ያገኘው ደግሞ በደላላነት ዘመኑ የተዋወቀውን የኦፓል ንግድ ሆነ።
የትውልድ አካባቢው የኦፓል ማእድን በስፋት የሚገኝበትና የሚመረት ነው። በርካታ የአካባቢው ነዋሪዎችም በዚህ የጌጣጌጥ ማእድን ማውጣት ስራ ተሰማርተው ይገኛሉ። አንዳንዶቹ ማእድኑን በቀጥታ ለነጋዴዎች የሚሸጡ ሲሆኑ አንዳንዶቹ ደግሞ እሴት ጨምረው ነው የሚሸጡት። ሌሎች ደግሞ ኦፓሉን ከአምራቾች እየሰበሰቡ ለሀገር ውስጥና ለውጭ ገበያ ያቀርባሉ። አቶ በላይ ይህን ግብይት ነው የተቀላቀለው።
የኦፓል ንግድን እያወቀው በመጣ ቁጥር ከፍተኛ ፍቅር አድሮበታልና፣ ‹‹ብሠራው እለወጥበታለሁ›› ሲል የኦፓል ማዕድን ንግድ ላይ አተኮረ። አቶ በላይ ከነበረበት የሱሰኝነት ሕይወት ብቻ አይደለም በጥረቱ የወጣው፤ አሁን ከፍተኛ ማማ ላይ ላስቀመጠው የኦፓል ማእድን ላኪነት ልምድና እውቀት እንዲጨብጥ ያደረገውንም የድለላ ስራውን በ2008 ዓ.ም የደላላነቱን ሥራ በመተው የኦፓል ማዕድን ንግድ ሥራውን በራሱ መሥራት ጀመረ።
ኦፓል የሚወጣበት አካባቢ የትውልድ አካባቢው ነው፤ በዚያ ላይ በደላላነት በሠራባቸው ዓመታት ስለሥራው ሁኔታ በቂ ዕውቀትና ልምድ አካብቷል፤ ከብዙ ሰዎች ጋርም ተዋውቋል። እናም ‹‹ስራው ያን ያህል አልከበደኝም›› ብሎ በስራው ገፋበት። የመጀመሪያ ስራውም ተስፋውን አለመለመለት። ‹‹በመጀመሪያ ሙከራዬም በሦስት ሺ ብር የገዛሁትን ኦፓል፣ ሃያ ሺ ብር ሸጥኩት” በማለት የኦፓል ማዕድን ንግድ ሥራ አጀማመሩን ያስታውሳል።
ከ2008 ዓ.ም ጀምሮ እስከ 2012 ዓ.ም ድረስ ከደላንታ አዲስ አባባ እየተመላለሰ ለአራት ዓመታት ያህል በአገር ውስጥ በኦፓል ማዕድን ንግድ ሥራ ተሰማርቶ ሰራ፤ ከ2012 ዓ.ም ጀምሮ ደግሞ ሥራውን የበለጠ በማስፋፋትና አዲስ አበባ ላይ “በላይ ደምሌ ኤክስፖርተር” በሚል ድርጅት ከፍቶ ኦፓል ወደውጭ መላኩን ተያያዘው።
የማዕድን ሥራ ከፍተኛ ዕውቀት የሚጠይቅ መሆኑን በላይ ይናገራል። “ደላላ ሆኜ በማሻሽጥበት ወቅት ከማገኛት አነስተኛ ሳንቲም በላይ ሥራው እንዴት እንደሚሠራ ለማወቅ ነበር ከፍተኛ ጥረት የማደርገው። ›› የሚለው አቶ በላይ፣ የማዕድን ሥራ ዝም ተብሎ የሚገባበት ሥራ አይደለም፤ ዕውቀት ይጠይቃል ሲል ይገልጻል። ያለዕውቀት ከሆነ የሚገባበት በከፍተኛ ደረጃ ሊያከስር ይችላል›› ሲል ስራው ምን ያህል እውቀትና ልምድ እንደሚፈልግም ይጠቁማል።
በዕውቀት የሚሠራ ከሆነ ደግሞ ማዕድን ለሚሠራው ሰው ብቻ ሳይሆን ለሀገር ዕድገትም ከፍተኛ አስተዋፅኦ ሊያበረክት እንደሚችል አቶ በላይ ይገልጻል። እሱ ከደላላነት ጀምሮ ሥራውን ከተዋወቀበት ጊዜ አንስቶ ሥራውን በደንብ ለማወቅና በአግባቡ ለመሥራት ጥረት አደርጓል፤ ጥረቱ ከበርካታ የዘርፉ ባለሙያዎች ጋር አስተዋውቆታል፤ በዚህም ጠቃሚ ዕውቀትና ልምድ መቅሰም ችሏል።
በዚህም ከሀገር ውስጥ ባለሙያዎች በተጨማሪ ከሀገር ውጭ በተለይም ከህንዳውያን የማዕድን ባለሙያዎች ጋር በመተዋወቅና አብሮ በመሥራት ጭምር ዕውቀቱንና ልምዱን ይበልጥ ማዳበር እንደቻለም ይናገራል፤ እነዚህ ሁሉ በሥራው የበለጠ ተጠቃሚ እንዲሆን አስችለውታል።
“ሕንዳውያንን የመረጥኩበት ምክንያት እነርሱ ለማዕድን ያላቸው ፍቅር የተለየ በመሆኑ ነው፤ ለማዕድን ትልቅ ክብርና ፍቅር አላቸው። ›› የሚለው አቶ በላይ፣ ከህንዳውያኑ ጋር መስራቱ በብዙ መልኩ እንደጠቀመው ነው የሚናገረው። ‹‹ከእነርሱ ባገኘሁት ዕውቀት ጥሬ ማዕድኑን በመላክ ብቻ ሳይሆን የተለያዩ ዘዴዎችን በመጠቀምና ማእድናቱን በማስጌጥ እሴት ጨምሬባቸው የምሸጥበት ዕድል ተፈጥሮልኛል” ሲል ያብራራል።
ሥራውን በልምድ ከመሥራት አውጥቶ በዘመናዊ መንገድ ለማከናወንና ወደተሻለ የዕድገት ደረጃ መውሰድን በተመለከተም ምን ሃሳብ እንዳለው ላቀርብንለት ጥያቄ አቶ በላይ በሰጠው ምላሽ፤ የማዕድን ሥራ ከፍተኛ እውቀትን የሚጠይቅ በመሆኑ በቀጣይ በዘርፉ የሚሰማሩት ዘመናዊ ትምህርት የተማሩ ቢሆን የሚመረጥ መሆኑን መክሯል።
ልምድም ቀለል ተደርጎ መታየት እንደሌለበት ነው የገለጸው። ‹‹እስካሁን በልምድ እየሰራን የምንገኘውም ከዘርፉ ባለሙያዎች ጋር በመገናኘት ዘመናዊ ዕውቀት መቅሰምና ራሳችንን የበለጠ ማሳደግ ይኖርብናል” ይላል።
ከሀገር ውስጥ ባለሙያዎች በተጨማሪ ከሀገር ውጭ በተለይም አብረውት ከሚሰሩት ህንዳውያን የማዕድን ባለሙያዎች ዕውቀቱንና ልምዱን ይበልጥ ማዳበር እንደቻለና፣ ከህንዶቹ ያገኘውን እውቀት፣ ቴክኖሎጂና ልምድ ለሀገር ውስጥ ሠራተኞቹና የሥራው ባልደረቦቹ ሽግግር ለማድረግ መሞከሩንም ይናገራል። በዚህም በሥራው የበለጠ ተጠቃሚ ከመሆኑ በተጨማሪ ለሀገሩም ተጨማሪ የውጭ ምንዛሬ የሚያስገኝበት ሁኔታ እየጨመረ መምጣቱንም ይገልጻል።
ቀደም ሲል በማዕድን ዘርፉ በርካታ ችግሮች እንደነበሩ አቶ በላይ ያስታውሳል። እሱም በሥራው ወቅት ከፍተኛ ችግር ያጋጥመው ነበር። ፈቃድ ለማውጣትና በህጋዊ መንገድ በዘርፉ ተሰማርቶ ለመሥራት በከፍተኛ ውጣ ውረድና አሰልቺ የአሠራር ሂደት ውስጥ ማለፍ የግድ ነበር። ሰዎች ወደ ህገ ወጥነት እንዲሄዱና ኮንትሮባንድ እንዲስፋፋ የሚያደርግ አሠራርም እንደነበረም ያስታውሳል። “ይሁን እንጂ ዞሮ ዞሮ ህገ ወጥነት መጨረሻው ጥፋት በመሆኑ እኔ በበኩሌ ችግሩን ሁሉ ችዬ ህጋዊውን መንገድ ተከትዬ በመስራቴ ተጠቃሚ እንጂ ተጎጂ አልሆንኩም” ይላል።
በአሁኑ ወቅት ግን መንግሥት በዘርፉ ከፍተኛ ማሻሻያዎችን ማድረጉን ጠቅሶ፣ በዚህም አብዛኞቹ ችግሮች እየተቀረፉ መምጣቸውን ይገልጻል። በማሻሻያዎቹ ምክንያት ማዕድናትን ለመላክ ከፍተኛ ጊዜና ወጪን የሚጠይቁ ውጣ ወረዶች እንዲያጥሩና እንዲቃለሉ ተደርገዋል።
ማሻሻያዎቹን ተከትሎ ከዚህ በፊት በኮንትሮባንድ በኬንያና በሱዳን በኩል በከፍተኛ ደረጃ ይወጡ የነበሩ ማዕድኖች በአሁኑ ወቅት በቀጥታ በጉምሩክና በኢትዮጵያ አየር መንገድ አማካኝነት ወደውጭ እየተላኩ ናቸው። ይህም ለላኪዎቹም ለሀገሪቱም ከፍተኛ ጥቅም አለው፤ በሥራው ላይ ትልቅ ለውጥ እንዲመጣ አስችሏል ይላል። ወደፊት በዘርፉ መሰማራት ለሚፈልጉትም በጣም አበረታች ይሆንላቸዋል። ስለሆነም የማዕድን ሚኒስቴርም ሊመሰገን ይገባዋል” ሲል ያስረዳል።
በላይ በአሁኑ ወቅት የተለያየ ዓይነት የኦፓል ማዕድን ምርቶችን ወደ ህንድ፣ አሜሪካ፣ ጀርመንና ፈረንሳይ እየላከ ይገኛል። ለማዕድን ሥራው የሚያግዙት አሥር የውጭ ሀገር ዜግነት ያላቸው የማዕድን ባለሙያዎችን ቀጥሮ ያሰራል። ስምንት የሀገር ውስጥ ሠራተኞችም አሉት። በአዲስ አበባ የራሱ መኖሪያ ቤትና መንቀሳቀሻ ዘመናዊ መኪና አለው።
አጠቃላይ የሀብት መጠኑንም አስር ሚሊዮን ብር አድርሷል። አሁን ላይ ለበርካታ ዓመታት ሕይወቱን አመሰቃቅሎና ከሰውነት ተራ ከመውጣት አልፎ እስከ ተስፋ መቁረጥ አድርሶት የነበረውን እጅግ አስቸጋሪ የሱሰኝነት ሕይወት በሚደንቅ ጥረትና በከፍተኛ ቆራጥነት አሸንፎ፣ ከእጅ ወደአፍ ከማይዘለው የደላላነት ሥራ ተነስቶ ከራሱ አልፎ ለሌሎች የሚተርፍ ሥራ ባለቤት መሆን ችሏል።
አቶ በላይ ሌላም ራእይ አለው። “ከራሴ፣ ከቤተሰቦቼና ከጥቂት ሰዎች አልፌ ሥራዬን የበለጠ በማስፋፋት በዘርፉ ሀገሬንም ይበልጥ የመጥቀም ፍላጎት አለኝ” ይላል፤ ከኦፓል በተጨማሪ በሌሎችም ማዕድናት ላይ ተሰማርቶ ራሱም ጠቅሞ ሀገሩንም የመጥቀም ራዕይ እንዳለው ይናገራል። እኛም እንግዳችን ራዕዩ እንዲሳካለት መልካሙን እንመኝለታለን። አበቃን።
ይበል ካሳ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 23/2014