ክረምት መጥቶ ክረምት በሄደ ቁጥር የምንሰማው ተመሳሳይ ነገር፤ “የዘንድሮ ክረምት ይለያል” የሚል ነው። እኔም የዘንድሮ ክረምት ይለያል ብዬ ለመጀመር አሰብኩ። በእርግጥ የዘንድሮው ክረምት ይለያል። የአየር ንብረት ለውጡን በትክክል እየተመለከትን ያለነው በክረምት እና በበጋ መፈራረቅ ውስጥ እየሆነ ነው። የአዲስ አበባ መንገዶች በደቂቃ ውስጥ በዘነበ ዝናብ ከአስፓልትነት ወደ ባህርነት ሲቀየሩ እናያለን። የብርዱ አይነት ተለውጦ ጥዝጣዜው ከአካላችን ጋር ተጣብቆ መላቀቅ የሚከብደውም ይመስላል። ይህን ስናይ የዘንድሮ ክረምት የተለየ ነው ብንል የተሳሳተ አንሆንም።
የዛሬው መንደርደሪያ ታሪካችን በመንገድ ዳር በቆሎ በመሸጥ ልጆቿን የምታሳድግ ብርቱ እናት ጋር ይወስደናል። በጎልማሳነት እድሜ ክልል የምትገኝ የጉሊት ሰራተኛ ነች። በክረምትም በበጋም ያዋጣኛል የምትለውን ይዛ ወደ ጉሊት ትወጣለች። ሰሞኑን በቆሎ ይዛ እየወጣች ነው። በቆሎና የክረምት ወቅት ያላቸው ቁርኝት ለአንባቢው መግለጽ ለቀባሪው ማርዳት ነው። እናም አንድ ቀን በተለመደው የበቆሎ ስራዋ ላይ ነች። መንገድ ዳር ከሰል አቀጣጥላ ከሰሉ ላይ ያስቀመጠቻቸው በቆሎዎችን እያገላበጠች ለደንበኞቿ እንደሚሆን እያደረገች ትገኛለች።
የደረሰውን በቆሎ እየሸጠች ሌላውን በቆሎ እንዲሁ እየጠበሰች ትቀጥላለች። በዚህ ተግባሯ ላይ ሳለች ልጇ እየሮጠች ከቤት መጣች። የልጇም መልእክት እቤት እንግዳ እንደመጣባት የሚገልጽ ነበር። ማንነቱን መግለጥ ያልፈለገ እንግዳ መሆኑንም ተረዳች። ስራዋንም አጠገቧ ላለች የጉሊት ሥራ ባልደረባዋ አደራ ሰጥታ ወደ ቤቷ ሄደች።
እቤት የጠበቃት እንግዳ ባለችበት ደርቃ እንድትቆም አደረጋት። ለእርሷ ወደ ጎዳና ንግድ መውጣት ምክንያት የሆነው ከዓመታት በፊት የት እንደገባ የማታውቀው ባለቤቷ ነበር። በብዙ መንገድ ተንከራታ ብትፈልገውም ልታገኘው ያልቻለችው ግለሰብ ዛሬ ከፊት ለፊቷ ቆሟል። ሕጻናት የነበሩት ልጆቹም አድገው ለእናታቸው መላላክም ላይ ደርሰዋል። እንግዳውን ሰው ግን አላወቁትም።
ሁለቱም የተደበላለቀ ስሜት ውስጥ ሆነው ይተያያሉ፤ ልጆች ግን የሚሆነው አልገባቸውም። ከሁለቱም ዓይን እምባ ይፈሳል። አንዱ የሌላኛውን እምባ ማበስ የሚችልበት ሁኔታ ውስጥ ግን አልነበረም። ያለ ድምጽ እንዲሁ በእምባ ብቻ እያወሩ ነው፤ ደቂቃዎች ሄዱ። ግለሰቡ ያወጣው የመጀመሪያ ቃል “የህይወት ክረምት የህይወቴን መንገድ አበላሸው” የሚል ነበር። ሚስት አልገባትም፤ ግን ደግሞ ከአቅም በላይ የሆነ ነገር ገጥሞት እንደሆነ ተረድታለች።
ደቂቃዎቹ ወደ ሰዓታት አደጉ፤ ሰዓታት ወደ ቀናት የሆነውን ሁሉ እየተረከላት ሰነበቱ። ሁሉም ነገር በእውን የሆነ ሳይሆን ፊልም ይመስላል። የተዋጣለት የፊልም ደራሲ የደረሰው፤ የተዋጣለት የፊልም ዳይሬክተር ዳይሬክት ያደረገው፤ የተዋጣለት ተዋንያን የተወኑበት በኦስካር መድረክ ላይ ቢቀርብ ማሸነፉ አይቀሬ የሚመስል ፊልም። የህይወት ክረምት ውስጥ የተገኘ።
እርሷም ያለፉትን ዓመታት እንዴት እንዳለፈች ስትተርክ ተመሳሳይ ነገር ነበር፤ አስደማሚ ምስክርነት። ሰው ከሰው ሲለይ የሚገጥም፤ ሰው ከሰው ጋር አብሮ በመኖርና በመለያየት ውስጥ የሚገጥም የህይወት ከፍታና ዝቅታ። ሁለቱም ያለፉበት የህይወት ክረምት በሚገባ ተረዱ። ከጥንዶቹ ታሪክ ውስጥ የቀደመው ትምህርት በሁለቱም ውስጥ በህይወት በየትኛው ቅጽበት ምን እንደሚሆን የሰው ልጆች የማናውቅ ትልቅ ውስንነት ያለብን መሆናችንን የሚያሳይ ነው።
የሰው ልጅ ትልቁ ውስንነት
እኛ የሰው ልጆች የበዛ ውስንነት አለብን፤ ከውስንነቶቻችን መካከል ግንባር ቀደሙን የሚይዘው በህይወታችን ውስጥ ቀጥሎ ምን እንደሚገጥመን የማናውቅ መሆኑ ነው። በየሰፈሩ ያሉ የጥንቆላ ቤቶችም ይህን ውስንነት ለመድፈን ሲባል እንደሚሰሩ በማህበረሰቡ ውስጥ የሚገኝ አስተሳሰብ ነው። በአገራችን ከተራ ግለሰብ እስከ ታዋቂ ሰዎች የጥንቆላው ቀጠና ውስጥ ተገኝተው የነገውን እጣፈንታቸውን ዛሬ ላይ አውቀው ለመኖር ሲጥሩ ይስተዋላል። ለንግዳቸው የቱንም ያህል ካፒታል ቢኖራቸው ስለ ነገ ሰግተው ወደ ኢንሹራንስ ከመሄድ ወደ ጥንቆላ ሄደው ግብራቸውን ማውጣት የሚቀናቸውንም ቤት ይቁጠራቸው። የሃይማኖት ድንበር ሳያጥራቸው በየጨለማው፤ በየመንደሩ የሚገኙ ጥቂቶች አይደሉም። “እከሌ እኮ እዚህ ቦታ ነው ያስጠነቆለው” የሚል ወሬ ለእኛ እንግዳም የማይሆነው ለዚህ ነው።
የሰው ልጅ ያለበትን ውስንነት በጥረቱ ለመድፈን ከሚያደርጋቸው ነገሮች መካከል አንዱ ነገሮችን ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ መተንበይ መቻል ነው። የአገራት ኢኮኖሚ በምን ያህል ሁኔታ ሊያድግም ሆነ ሊቀነስ እንደሚችል ይተነበያል። በአየር ንብረት ዙሪያም ሙቀትና ዝናብ ስለመሆኑ ወይንም ከፊል ደመናማ እንደሚሆንም እንዲሁ። ስለዚህ ትንበያው የመሳካት አቅሙ ሳይንስ የደረሰበትን ደረጃም ያሳያል።
በጤናም፤ በሕዝብ ብዛትም፤ በሌሎችም ዘርፎች ሳይንሳዊ የሆነ ትምበያዎች ይሰጣሉ። የዚህ ሁሉ ጥረት ነገን ዛሬ ላይ ሆኖ በማወቅ ለነገ ጉዞ ለመዘጋጀት ነው። ጥረቱ የቀጠለ ቢሆንም አሁንም በመሰረታዊነት የሰው ልጅ ነገን ባለመረዳት ውስንነት ውስጥ የመኖሩን እውነት ግን ሊሽረው አልቻለም። የህይወት ክረምት ከደጃችን ቆሞ በአካል ስናገኘው ያኔ ውስንነታችንን እንረዳለን። ውስንነት ይዞት የሚመጣውን እድልን አሻግረው የተመለከቱ ደግሞ የተለዩት ናቸው።
የውስንነታችን እድሎች
ውስንነት እድል ሊሆን አይችልም፤ በእርግጥ ግን እድል ሊሆን ይችላል። የተጣረሰ ሙግት። አንድን ነገር በፊትለፊት በሚታየው መንገድ ስናየው በትክክል የሚጠቅመን አለመሆኑን እንረዳ ይሆናል። ነገር ግን በዓለማችን ላይ ለሰው ልጆች የሚጠቅሙ ታላላቅ ግኝቶች የተከሰቱት ውስንነትን ወደ እድል ለመቀየር እምነት አድርገው በሰሩ ሰዎች ነው። እኒያ ሰዎች በውስንነት ወቅት የሚያደርጉት ጥረት ለሌሎች እጅና እግራቸውን አጣጥፈው ለተቀመጡት ሰዎች እንደ መሳቂያ የሚቆጠር ነው። ይሁን እንጂ በእነርሱ ሥራ ወይም ውስንነትን ማለፍና ወደ ተራራው ጫፍ መድረስ ብዙዎች መ ጠቀም ይጀምራሉ።
ውስንነት ነገሮች ባልታዩበት መንገድ ማየትን ይጠይቃል። ዛሬ ነገሮችን የምናይበት፤ አውጥተን የምናወርድበት መንገድ ከውስንነት ማዶ ያለንን መዳረሻ ያሳየናል። የሰው ልጅ በፍጹም ነገን አለማወቁ የፈጣሪ ፈቃድ ቢሆንም ነገ እንዲህ ቢሆን ብሎ አስቦ ዝግጅት ቢያደርግ እንዲሁ የፈጣሪ ፈቃድ አይሆንም ሊባል አይችልም። የሰው ልጅ በሰፊው ሳይንሳዊ ምርመራ እያደረገ ለነገ ዛሬ ቢዘጋጅ ተጠቃሚ እንጂ ተጎጂም እንደማይሆን እሙን ነው።
አንባቢው ዛሬ በህይወቱ ውስጥ ያሉትን ውስንነቶችን በመዘርዘር እንዴት ነገሮችን ባልታዩበት መንገድ በማየት ወደፊት ለመዘርጋት እንደ እድል እንደሚጠቀምባቸው ማሰብ አለበት። ነገሮች ባልታዩበት መንገድ በማየት ውስጥ ፈተናዎችን ተጋፍጦ ማለፍ አለ። የሰው ልጆች በምድር ላይ የሚያሳልፈው መከራ ሁሉ መጥፊያው ሳይሆን መልሚያውም ጭምር ነው። ካለበት ወደሚቀጥለው የሚሸጋገርበት ድልድይም ነው።
ውስንነት በተጨባጭ ውስን የሚሆነው ለተቀማጭ ብቻ ነው። ‹‹ለተቀማጭ ሰማይ ቅርብ ነው›› እንደሚባለው። ዛሬ በምናልፍበት የህይወት ውጣውረድ ውስጥ ነገሮችን በብልህነት እያዩ ማለፍ የግድ ነው። ያለንበት ዘመን ውስንነታችንን ይበልጥ እያገዘፈ የመጣ ዘመን ይመስላል። ከትላንት ዛሬ የምድር ፈተና ይቀላል ሲባል እየተወሳሰበ፤ ሳይንስ በዘመነ ቁጥር ምድርን ሰላማዊ ሳይሆን በስጋት ውስጥ የምትኖር እያደረጋት ይገኛል። የዓለም አጀንዳው ተጠቃሎ ወደ አንድ ግለሰብ ህይወት ውስጥ ሲመጣ ያለውን ተጽእኖ ለመቀነስና ወደፊት በጽናት ለመጓዝ ከውስንነት ባሻገር መሄድን መልመድ ያስፈልጋል። የህይወት ክረምት ወቅቶች ባህሪያት ውስጥ ስናልፍ ይህን እንረዳለን። እኝኝ የሚለው ዝናብን መነሻ አድርገን እንቀጥል።
እኝኝ የሚለው ዝናብ
ማይከል ጆርዳን ከሚጠቀስለት አባባሎች መካከል አንዱ እንዲህ ይላል፤ “I’ve failed over and over and over again in my life — and that is why I succeed.” በአጭሩ ማይክል ጆርዳን ስኬታማ የሆነው ደጋግሞ በመውደቁ ነው።
የክረምት አንዱ ማሳያ የማያቋርጠው ዝናብ ነው፤ እኝኝ የሚለው። በተጨባጭ እኝኝ የሚለው ዝናብ የክረምት ወጉን እየፈጸመ ነው፤ በህይወት ክረምት ውስጥ ግን አሉታዊነት ማሳያ ሆኖ እንረዳዋለን። በህይወታችን ውስጥ አንዱን መከራ አለፍን ስንል ሌላ መከራ የሚከታተልበት ወቅት ውስጥ እናልፋለን። ተዘጋ ያልነው ሽንቁር አቅጣጫውን ቀይሮ ሊመጣ ይችላል። ሁሌም ባይሆን በህይወታችን እንዲህ ያለወቅት ያጋጥመን ይሆናል።
በመነሻ ታሪካችን ድንገት የትዳር አጋሯን ያጣች ሴት ምናልባትም የጉልት ንግድን በህልሟም በውኗም አስባው የማታውቅ ይሆናል። ከየአቅጣጫው የመጣው ጦር ግን ወደ ጉሊት ገፍቷታል። ይህ ውስንነትን ማሸነፊያ ማሳያ እንጂ የመሸነፉ አይደለም። ነገርግን ተስፋ ቆርጣ ሌሎች መንገዶችን ብትሄድ ተሸናፊ ነበረች። ገላዋን ሸጣ ለማደር ከራሷ ጋር ብዙ ተሟግታለች። ነገርግን ልጆቼ የሚያፍሩበትን ታሪክ አላስቀምጥም ብለ በተከበረችበት መንደር የጉሊቱን ስራ ጀመረች። እኝኝ የሚለውን ክረምት በጽናት ማለፍ ትችል ዘንድም በረታች። በብርታት መንገድ ላይም ሳለች ድንገት ይሆናል ያላለችው ሆነ፤ የትዳር አጋሯ ከዓመታት በኋላ ከቤቷ በር ላይ ደረሰ።
መገፋት፣ መገለለ፣ አለመታመን፣ ብቸኝነት፣ ተስፋ የሚደረግ መጥፋት፣ ቃልን መከዳት ወዘተ እኝኝ በሚለው ክረምት ይመሰላል። ህይወትን በብልሃት የሚመሩ ግን እኝኝ ከሚለው የህይወት ክረምት ባሻገር በጽናት ተጉዘው ከፊትለፊታቸው ያለን የውስንነታቸው ተቃራኒ ገጽ ማሳያ የሆነው ቀን ላይ ይደርሳሉ፤ ብሩሁ ቀን ላይ። ከጎርፉ በኋላ በጉልህ የሚታየው ቀን።
ከጎርፉ በኋላ
ዝናቡ ደጋግሞ ዘንቦ፤ ምናልባትም ጎርፍ ሆኖ ጥፋትም አድርሶ፤ የሰፈሩን ቆሻሻ ሆነ መልካሙንም ሁሉ ይዞት ሄዶ በስተመጨረሻ አስጨናቂው የጎርፍ ወቅት አልፎ የብርሃን ቀን ይመጣል። የብርሃን ቀኑ ወደ ውጤት የመድረስ ማሳያ የሆነ ቀን ነው። የብርሃኑ ቀን ዛሬ ላይ ካለንበት የመከራ ጎርፍ አንጻር ስናስተያየው እንደሚመጣ ያልጠበቅነው ቀን ነው። ከፊት ባሉት ቀናት ውስጥ ክረምቱ አልፎ የሚመጣ የብርሃን ቀን ማሳያ። ያንን የብርሃን ቀን ተስፋ አድርጎ ዛሬን በጽናት መቆየት ታላቅነት ነው።
ከጎርፉ በኋላ ያለውን ቀን አሻግሮ ማየት አሁንም በሰውነት ውስንነት ውስጥ ማየት ይከብድ ይሆናል። ነገርግን ወደ ውስጥ ተመልከት፤ በልብህ ውስጥ ድምጽ ይኖራል። ከራስህ ጋር ሁን፤ ለራስሽ ጊዜን ስጪ፤ ነፍስሽን በጥሞና አድምጪያት፤ ከበዛው ግርግር ወጣ ብሎ ውስጥን በማዳመጥ አሻግሮ ከጎርፉ በኋላ ያለውን ቀን መመልከት ያስችላል። በግርግር ውስጥ ህይወታቸውን ለመምራት ለወሰኑ ይህ ቀላል ተግባር አይደለም። በራቸውን ዘግተው ልባቸውን ከፍተው ከፈጣሪያቸው ጋር ከሚገናኙት ጋር ግን ይህ ይሆናል፤ ከጎርፉ በኋላ ያለውን መመልከት።
ህይወታቸውን ላመኑበት ዓላማ ለፖለቲካም ይሁን ለሃይማኖት የሚሰጡ ሰዎች አንድ የሚያደርጋቸው ነገር ቢኖር ዛሬ ካሉበት ነገር አሻግረው መመልከት የቻሉ ሰው መሆናቸው ነው። በጦር ሜዳ የተሰለፈ አንድ ወታደር ከጦርነቱ ማዶ ሰላምን ይናፍቃል፤ ከጦርነቱ ማዶ አሸንፎ ውጤት እንደሚሆን አምኖ ይፋለማል።
በህይወት ክረምት ውስጥ ጎርፉ ላይ ብቻ ቆሞ መቅረት የለም፤ ከጎርፉ በኋላ ሌላ ታሪክ አለ፤ ህይወት ገጽ ላይ ተጽፎ የሚገኝ ሌላ ታሪክ፤ የታገሱና አሻግረው ማየት የቻሉ ብቻ የሚመለከቱት ታሪክ፤ በአግባቡ የተኳለ ዓይንን የሚፈልግ እይታ።
ጎርፉ ካለፈ በኋላ የሚመጣው የብርሃን ዘመን ላይ ወድቀው የሚገኙ ግን ጥቂት አለመሆናቸውን ማሰብ አንዳንዴ የህይወት ክረምት ምነው በቆየ ያስብላል። የህይወት ክረምት በማይመች ሁኔታ ውስጥ ለህይወት ዘመን የሚመች ምርት የሚዘጋጅበት ነው። ዝናቡ ለአርሶአደሩ ለስራው የሚመች ባይሆንም ለበጋው የሚሆነውን ስንቅ የሚሰንቅበት ከአስቸጋሪው ክረምት ማዶ ብራን የሚያይበት ነው። ድልን መጠበቅ ሳይችሉ በድላቸው ወቅት ወድቀው የሚገኙ ሰዎችን ቀጥሎ ባሉት ቃላት ውስጥ ተመልክተን ስለ ህይወት ክረምት የከፈትነውን ገጽ እናጠናቅ።
የብርሃን ሰለባዎች
የጨለማው ወቅት ታልፎ፤ የህይወት አደይ አበባም ፍክት ብላ፤ የጓዳ ውስጥ ችግር ተፈቶ፤ የጤና እክልም ተቀርፎ ነገሮች መስመር ውስጥ ናቸው በሚባልበት ጊዜ ምንያህሉ በምስጋና ህይወት ውስጥ ይገባል፤ ምንያህሉስ ከእዚህ ቀደም ያልሞከረውን በመሞከር ስሌት የመጥፊያ መንገዱን አንድ ብሎ ይጀምራል።
በዩኒቨርሲቲ ተማሪነት ወቅት በተማሪዎች መካከል የሚስተዋል አጉል ልማድ ምንጩ የጓደኞች ተጽእኖ፣ የቤተሰብ ከተገቢው በላይ የሚላክ ገንዘብ እና ሌሎች ምክንያቶችም ይቀርባሉ። በገንዘብ ተቸግሮ ያደገ አባት ለልጁ የእርሱን ችግር ለመበቀል በማለት የሚሰጠው የተጋነነ ገንዘብ ልጁን ያልተገባ ህይወት ውስጥ እንዲገባ በር ይከፍትለታል። እንደውም በአንዳንድ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ልጆች ቤታቸው ካሉት ከባባድ መጠጦች መካከል በቦርሳቸው አድርገው ትምህርትቤት ሄደው የሚገኙበት አጋጣሚ እንዳለም እንሰማለን።
ዛሬ በምንም አቅጣጫ ይሁን ሊናገር የሚችለው ዛሬን ግፋ ካለም ትላንትን እንጂ ነገን ሊናገር አይችልም። ነገ ውስጥ ከጨለማው ወደ ብርሃን መሸጋገር አለ፤ በተመሳሳይ ሁኔታ ከብርሃንም ወደ ጨለማ መመለስ አለ። ከብርሃን ወደ ጨለማ የሚሆነው መመለስ ብርሃንን በአግባቡ ካለመያዝ የሚመጣ ሲሆን ሃዘኑ ድርብርብ ይሆናል።
“ከተራበ ይልቅ ለጠገበ አዝናለሁ” የሚለው አገራዊ ብሂል የሚሰጠን መልእክት ከፍ ያለ ነው። ብሂሉ የሚሰጠንን ትርጉም ይዘን ለአፍታ ቆም ብለን በህይወታችን ውስጥ በምን ደረጃ እየታየ እንደሆነ መመርመሩ አይከፋም። የብርሃን ሰለባ ላለመሆን በመጠንቀቅ፤ ዛሬ ላይ በምንገኝበት ሁኔታ ባለመሰማራት፤ በመጽናት ከፊታችን ያሉት ቀኖች ከውስንንነታችን በላይ የምንራመድባቸው ይሁንልን። የህይወት ክረምት መንገድ አድካሚ ቢሆንም ወደ ውስጣቸው የሚመለከቱ ግን በድል ይወጡታልና።
በአገልጋይ ዮናታን አክሊሉ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 23/2014