ሰዎች በሕይወት ዘመናቸው ማድረግ የሚፈልጉት አልያም መተግበር የሚያልሙት አቢይ ጉዳይ ይኖራቸዋል። ይህ ጉዳይ የሰዎች የዘወትር ሕልም አልያም ማሳካት የሚፈልጉት ዓላማና ግባቸው ነው። ይህን ግብ ደግሞ ሰዎች የመጨረሻ የስኬታቸው ጥግ አድርገው ሊወስዱት ይችላሉ። በዚህም ሐሴትን እንጎናፀፋለን ብለው ያምናሉ። ዘወትር የሚያልሙት ሕልማቸውና ብርቱ መሻታቸው ከተሳካ፤ የደስታ እርካብ ላይ የሚያደርሳቸው ይመስላቸዋል። በዚህም ዓላማቸውን ለማሳካት አልያም ግባቸው ላይ ለመድረስ ያገኙትን ሁሉ አጋጣሚ ይጠቀማሉ።
ለዓላማቸውና ለግባቸው መሳካት የማይፈነቅሉት ድንጋይ፤ የማይቧጥጡት ተራራ አይኖርም። ታዲያ ሰዎች ለግባቸው መሳካት ጥረት የሚያደርጉት ሁሌም አስበውና እቅድ አውጥተው ላይሆን ይችላል። ለዚህ ግባቸው አልያም እቅዳቸው መሳካት አውቀውም ይሁን ሳያውቁ ትግል ያደርጋሉ። ትልቅና ወሳኝ ያሉት መሻታቸውን ለማሳካት ጥረት ያደርጋሉ። ወደዚያ የሚያደርሳቸው የትኛውንም አጋጣሚ ለመጠቀም ይሞክራሉ።
ለዚህ ደግሞ ውስጣዊ የሆነ የተለየ ግፊት ያድርባቸዋል። ይህ ደግሞ ለግባቸው መሳካት ትልቅ አቅምና እድል ይፈጥርላቸዋል። ይህ አቅም የፈጣሪ ስበት ነው። ስበቱ ደግሞ ብርቱ ፍላጎትና ምኞታችን የፈጠረው በጥረታችንና ትጋታችን የፋፋ ኃይል የሚፈጥርልን ልዩ ሚስጥር ነው። የኛው የሆነ ነገር ግን የማናውቀው የሚያበረታን ኃይል፤ ጥረታችንን የሚደግፍ ፍላጎታችንን ለማሳካት ስንኳትን የሚረዳን ነው።
እኔ በዚህ አጥብቄ አምናለሁ። ሰው ማሳካት የሚፈልገውን ነገር ለማሳካት ሁሌም ይማስናል። ያገኘውን አጋጣሚ ሁሉ ወደዚያ እንዲያደርሰው ይተጋል። አውቆም ይሁን ሳያውቅ ወደመሻቱ ለመቃረብ ሁሌም ይጥራል። አንድ ሰው ግቡን ለማሳካት በጣረ ቁጥር ወደ መሻቱ ይበልጥ ይሳባል። በዚህ ውስጥ አንድ ነገር ማንሳት ፈለኩ።
እኛ እንደዜጋ ለሀገራችን በጎ ነገርን አጥብቀን እንመኛለን። ለሀገራችን ሰላምና እድገት፣ ለሕዝባችን ለውጥና ስምረት እንዲቃረብ እንጓጓለን።
ይህ መሻታችን ደግሞ ወደፊት ልናየው የምንፈልገውን ብሩህ ገፅታ ያስናፍቀናል። የሚገጥሙንን መሰናክሎች ሁሉ ተቋቁመን ወደፊት የተለወጠና ህዳሴውን ያረጋገጠ ማኅበረሰብ እንዲሁም ሀገር እንዲኖረን ከተመኘንና ለዚህም የጋራ የሆነ መሻት ውስጣችን ካሳደርን ተግባራዊ ማድረጉ የሚከብድ አይመስለኝም። እንደ አገር ማሳካት የምንፈልጋቸው ትልልቅ ጉዳዮች፣ ልንደርስባቸው የምንፈልጋቸውን በጎ ገፅታዎች ለማሳካት የጋራችን ሆነው ለግብ ያንደረድሩን ዘንድ መሥራት ይኖርብናል።
በእርግጥ የበዙ ጉዳዮች ላይ እናብራለን። በጎም ክፉም የተባሉ ጉዳዮቻችን ላይ በአንድነት ስቀናል፤ አልቅሰናልም። ይህ አብሮነት የጋራ ግብ እንዲኖረን ወደፊት የምንደርስበት ሀገራዊ ህዳሴ እንዲሳካ ጥሩ መሠረት ነው። ይህ አንድነት ወደምንፈልገው ነገር ለመሳብ ጥሩ እድል ይፈጥራል። የጋራ እቅድ ወጥነን፣ ልንደርስበት የምንፈልገው ሀገራዊ በጎ ገፅታ ተረድተን ካበርን ማሳካት እጅጉን ይቀላል።
ለግባችን መሳካት አንድ ሆኖ መቆም ያሻል። በአንድነት ውስጥ የሚገኘው ኃይል ደግሞ ብርቱ ነው። በዚያ አንድ ሆነን በመቆማችን ውስጥ የምንቀዳጀው ድል ይቃረብ ዘንድ ደግሞ ልዩነትን አጥቦ ወደ መግባባት የሚያቃርብ ሀሳብ እናራምድ። በጎ ነገራችን ላይ ትኩረት እናድርግ። ይህቺን ታላቅ ሀገር፣ ይህንን ሰፊ ሕዝብ ይዘን እንዴት አንድ ሆኖ መቆም ተሳነን ብለን እራሳችንን አንውቀስ። የሃሳብ ልዩነት በብዝኃነት ውስጥ ተፈጥሯዊ ነው። ይልቁንም የጋራ ሆነ ነገራችን ከሚያለያየን እጅጉን ይሰፋልና እዚያ ላይ እናተኩር። በጎው ላይ በጋራ እንረባረብ። የጋራ የሆነ ግብ አስቀምጠን፤ የጋራችን የሆነችው አገራችንን እናሻግር። ወደፊት ማሳካት የምንፈልጋቸው ብርቱ ሀገራዊ ጉዳዮችን እውን ለማድረግ አንድ እድር የሚያቆሙን ትልልቅ ሀሳቦችን እንከተል።
ስለ ሀገራችን ያለን ልዩ ስሜትና ሀገራዊ ፍቅር ትርጓሜው ጥልቅ ነው። ኢትዮጵያዊ አገሩን ለመውደዱ ማሳያ ከሰሞኑ ሁነቶች ውስጥ እንዱን መዞ ማየት በቂ ነው። ኢትዮጵያውያን አገር መውደዳቸውና ለሀገራቸው አንድ ሆነው መቆማቸው ማሳያው ብዙ ነው። የትላንት በስቲያው ግን ይለይ ነበር። የሆነ ለየት ያለ ስሜት። የአንዳችንን ሐሴት ሌላችን ላይ የሚያጋባ ድንቅ ስሜት።
ሳናውቀው ከውስጥ ፈንቅሎ የወጣና ስለሀገር ያለንን ልዩ ስሜት ያንፀባረቀ ሁነት። ከትላንት በስቲያ የአዲስ አበባ ጎዳናዎች በደስታ ተፍለቅልቀው፣ በጀግኖች አትሌቶታችን ድል ፈክተው፣ በነዋሪዎች አሸብርቀው አርፍደዋል። በ18ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ላይ ተሳታፊ የነበረው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ቡድን ከዚህ በፊት ከነበሩት የዚህ አይነት የውድድር ተሳትፎዎቹ የተሻለ ውጤት ይዞ በመመለሱ የተደረገለት ደማቅ አቀባበል፤ የሕዝባችን ደስታ መናፈቅ ቁልጭ አድርጎ ያሳየን ክስተት ከመሆኑ ጋር አንድ ነገር እንዳስብ አደረገኝ።
እንዲህ በአንድነት የምትሰበስብን አንድ ሆነን የምንዘምርላት፤ ያለ ልዩነት ድሏን ስንሰማ የምንደሰትባት ሀገር እያለችን ስለምንድነው ፍካቷ እንዳይቋረጥ ማድረግ የተሳነን? ብዬ አሰብኩ።
በነገራችን ላይ ኢትዮጵያዊ ለአገሩ ያለው ጥልቅ ስሜት እንደዚህ አይነቱ ገጠመኝ በሚፈጠርበት ጊዜ ነው የሚለየው። እኛ መልካችን ሁለት ነው፤ በእነዚህ ሁለት ጉዳዮች ለይ ፍንትው የሚል ገፅታ አለን። አንድም ሀገር በጠላት ተጠቃች ሲባል ያለ ልዩነት ዘራፍ ለሀገሬ ብለን በአንድነት ቆፍጠን ማለታችን። ሁለትም ልክ እንደሰሞኑ በተለያየ አጋጣሚ ድል ተቀዳጅተን ብስራቱን ስንሰማ አጋጣሚው ወደ አንድነት ያስጉዘንና በጋራ መፈንጠዛችን፤ ድላችን ማጣጣማችን።
ክፉ በሰማ ጊዜ ስለአገሩ ተንበርክኮ የሚለምን ሀገር ወዳድ ሕዝብ ያላት አገር፤ የድል ዜና ሲሰማ አልያም ባንዲራውን ሲመለከት ተንበርክኮ በፍቅር የሚያነባ ትውልድ የሞላባት ታሪካዊት ሀገር፣ የለውጧ መሠረት የሆነው አንድነት ላይ መታጠቅ እንዴት ይሳነን? እንደ ዜጋ መጠየቅ ያለብን ዋንኛ ጉዳይ ይህ ነው። አንድ ሆነን ቆመን ማሳካት የምንፈልገው ሀገራዊ ግብ ላይ እንድንደርስ ዘንድ፤ አልፎ አልፎ የሚታዩና እኛ የምንፈጥራቸው ልዩነቶች ሳይሆን አንድ አድርጎ የሚያዘልቁን ላይ ትኩረት እናድርግ።
ሁነቶች ውስጥ የሚንፀባረቀው አንድ መሆናችን ነው። የእኛ እውነተኛ ማንነትና ባህሪ ነው። ይህንን ነው ኃይል አድርገን መጠቀም ያቃተን። ይህንን ነው ወደምንመኘው ሁለንተናዊ ለውጥ የሚያዳርስ ገፊ ጉልበት ማድረግ ያቃተን። ያለንን መጠቀም ያቃተን የሌለንን ማቅረብ እንዴት ይቻለናል?። ዛሬ ድረስ አብሮነታችን እንዲደረጅ ያደረገው የአንድነት መንፈስ ለጋራ ግባችን መሳካትና ለሀገራዊ ሁለንተናዊ ለውጥ መስፈንጠሪያ ማድረግ ብንችል አስባችሁታል? ውጤቱ ያጓጓል። በዚህ መንፈስ በአንድነት ስለ ሀገራችን የምናደርገው ያልተቋረጠ ጥረትና ጽኑ ፍላጎታችን የሚፈጥረው ልዩ ኃይል የኢትዮጵያን ህዳሴ የሚያረጋግጥ ይሆናል።
ተገኝ ብሩ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 23/2014