ጥሩ የሆነ ጓደኛችን ሌላው ቀርቶ በጣም የምንቀርበው ጓደኛ ፍጹም ስላልሆነ የሚጎዳንን ነገር ሊናገር አሊያም ሲያደርግ ልንመለከት እንችላለን። እኛም ብንሆን ፍጹም እንዳልሆንን የታወቀ ነው። በዚህ ምክንያት የሆነ ሰውን ባልተገባ ሁኔታ የጎዳንበትን ጊዜ ማስታወስ ንዴትን መለስ ለማድረግ ጠቃሚ ነው። አንዳንድ ጊዜ፣ እጅግ በጣም አናዶን የነበረው ነገር ያን ያህል ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ጉዳይ እንዳልነበረ ከጊዜ በኋላ ስንገነዘብ ምናለ ያን ጊዜ ስሜቴን በተቆጣጠርኩ የሚያሰኝ አጋጣሚ ይፈጠራል።
ይሄንን ጉዳይ እንዳነሳ ያደረገኝ የጓደኝነት ልክ የሆኑ ጓደኛሞች በተራ ንዴት ያልተገባ ድርጊት ውስጥ መግባታቸውን ልነግራችሁ ስለወደድኩ ነው። መተያየታቸው ብቻ ደስታን የሚሰጣቸው፤ ለመጠራሪያቸው ሙሉ ስማቸውን መጥራት የሚከብድባቸው እገልዬ የሚለው ቃል ከአፋቸው የማይጠፋው፤ ነግቶ እስኪተያዩ የሚነፋፈቁ ጓደኛሞች ናቸው። ከጓደኝነት በላይ ጓዳ ሸፋኝ ገበና ሸሻጊም እንደሆኑ ይነገርላቸዋል።
በአብሮነት ጎዳና ለመጓዝ ፍቅር ያስተሳሰረው ጓደኝነት፤ ጊዜ እያጠበቀው መቻቻልን መተጋገዝን እያሳየ በጥሩ ፍቅር፤ ቀልድና ጨዋታ፤ ጥልና ኩርፊያ በሙሉ በጓደኝነት መስመር ውስጥ የሚያስጉዝ መንገድን በመቻቻል በደስታ ያሳልፋሉ።
አንዱ ሌላውን በክፉ አይን ለማየት ቀርቶ አጠገባቸው ያለ ሰው የአንዱ ስም በክፉ የሚያነሳውን መስማት ወባ እንደያዘው ሰው የሚያንቀጠቅጣቸው አገር ምድሩን የሚያስቀና የጓደኝነት መስመርን የሚጓዙ፤ ከአንድ ማህፀን የወጡ እስኪመስል ድረስ አብሮነታቸው የጠነከረ የእውነተኛ ጓደኝነት ተምሳሌት ናቸው።
ተናፋቂው ጓደኝነት
ጥር ወር 1996 ዓ.ም አዲስ አበባ የካ ክፍለ ከተማ ቀበሌ 15 ነዋሪ አንዳንች አንከን የማይወጣለት ፍቅር ያላቸው ናቸው ይላል ለአመታት በመቀራረብና በመተሳሰብ የዘለቁት ጓደኛሞች ፍቅራቸው ለብዙሃን ምሳሌ ሆኖ ኖሯል። በመካከላቸው ያለው የእምነት ልዩነት፤ የህይወት ፍልስፍና አለመገናኘት፤ የቤተሰብ ሁኔታ አንድ አለመሆንና ሌሎቹም የጋራ ያልሆኑ መለያዎቻቸው ቢበዙም ከዚህ ሁሉ በላይ ገዝፎ የወጣ የጓደኝነት ፍቅራቸው ሁሉን አስረስቷቸው አንድ አድርጓቸዋል።
እንደ ብዙዎቹ እምነት የጓደኝነት ሙሉ ትርጉም ስፍራ ይዞ የሚታየውና ጎልቶ የሚንፀባረቀው በእነዚህ ሰዎች ነው። ሁለቱ ወዳጆች አብረው የሚበሉ አብረው የሚጠጡ ብቻ መሆናቸው አይደለም ጓደኛ የሚለውን ስያሜ ያሰጣቸው። ሁለቱም አብሮ ከመብላትና ከመጠጣት ያለፈ የህይወታቸውን ክፍተት የሚሞሉበት ፍቅርእና መተሳሰብ ያላቸው መሆኑ ነው።
አንዱ ሲቸግረው ሌላው ይደርስለታል። አይዞህ ካለን ላይ ተካፍለን ብሎ ያጽናናዋል። የጎደለውን ሞልቶ የነበረ የጓደኛውን ስሜት ይመልሳል። አንዱ ሲጨንቀው ሌላው እያየው አንዱ ደስ ሲለው ከሌላው እየተካፈሉ እየተጋሩት ኖረዋል። መወለድ ቋንቋ ነው እስከሚባል ድረስ ሁለቱ ወዳጆች አምሳልነታቸውን አንድ አድርገው ዘልቀዋል። አመታትን የተሻገሩትና የወዳጅነት ዘመን ቱርፋታቸውን የተቋደሱት በመካከላቸው ባለው ፍቅርና መቻቻል ነው። ለዚህም ይሆናል አንዱ ሌላውን ጓደኛዬ ነው የሚለው ቃል የማይገልፅለት የማይመስለው።
ብዙዎች የእነዚህን ወዳጅነትና ፍቅር ይቀኑበት ነበርና የአብሮነታቸውን ሳይንስ ለማወቅ ይጥሩ ነበር። ከሁለቱም ጋር የቅርብ እውቂያ የነበረው ወጣት ጓደኛሞቹን አንድ ያደረጋቸው ነገር ሁለቱም ቀልድና ጨዋታ መውደዳቸው ነው። ቀልድና ጨዋታ ከመውደዳቸው የተነሳ እንደ ህፃን ልጅ ይላፋሉ፤ ይደባደባሉ። ሰዎች እስኪገርማቸው ድረስ አይለያዩም። እንዲያውም አንዱ አንዱን ካጣው ሳላይህ ስውል ትናፍቀኛለህ የሚባባሉ ወጣቶች ናቸው።
ይህ ቅርርባቸው አንዱ ሌላውን የራሱን ያህል እስኪያውቀው ድረስ ልብ ለልብ ያጣመራቸው ሁኔታም ነበር። የሚያውቋቸው አልፎ አልፎ ቢጋጩም ፀባቸው ብዙም አይከርም ይሏቸው ነበር። ሁለቱም ለሳቅና ለጨዋታ ቅርብ የመሆናቸውን ያህል ለኩረፊያም ቅርብ ናቸው። ነገር ግን ኩርፊያቸው እራሱ የቀልድ ስለሆነ የሚያመር አልነበረም። ለምን አኮረፍከኝ ብሎ መጠያየቅም ሆነ ሽማግሌ መካከላቸው ማስገባት ብሎ ነገር አልነበረም። እንደ ወንድማማች ወይም ታላቅና ታናሽ ይጋጫሉ መልሰው ይነጋገራሉ። ኩርፊያው ውሎ አያድርም፤ ቂም አያስቋጥርም።
ክፉ ቃል
ጥር 23 ቀን 1996 ዓ.ም ቀን ላይ ሁለቱም ከየዋሉበት መጥተው ተገናኙ። የዋሉበትም እዛው ቀበሌ 15 ክልል ኬር ኢትዮዽያ እርዳታ ድርጅት አካባቢ ነው። ቀናቸውን የቀጠሉት በተለመደው ፍቅርና በወዳጅነት ስሜት ነው ። የሚያውቋቸው ሰዎች በሁለቱም ላይ ከወትሮው የተለየ ስሜት እንደላዩባቸው ይናገራሉ።
ሁሉም ነገር እንደተለመደው ነበር፤ የተለመደው ሳቅ፤ የተለመደው ጫወታ፤ የተለመደው ልፊያ፤ የተለመደው መጎነታተል አለ። ያያቸው ማንነታቸውን እንኳን ከማወቁ በፊት የአብሮነታቸው ፍቅር ከፊታቸው የሚቀዳባቸው ሁለቱ ጓደኛሞች ዛሬም ከቀኑ አስር ሰአት ያሳለፉት ከወትሮው ባልተለየ ሁኔታ ነበር። መጨረሻ ላይ ግን አንድ ቃል ከሁለት ፍቅር መሃል ጥልቅ አለች።
̋ ሸፋፋ ̋ የምትል ቃል ነበረች። ተናጋሪው የዘወትር ንግግሩን ውጤት እየጠበቀ ከፈገግታና ከተለመደ ጫወታ ውስጥ ነው። አንደኛው እግሩ በመጠኑ ዞር ያለ መሆኑን አይቶ ነው ሌላውን ሸፋፋ ብሎ የሰደበው። በእርግጥ ከዚህ ቀደም ይሄንን ቃል ተጠቅሞት አያውቅም ነበር። ተሰዳቢው ሸፋፋ የሚለውን የቀልድ ስድብ ሲያዳምጥ ውስጡ አንዳች ቁጣ የተተራመሰ መሰለው።
ዘወትር እንደሚያደርጉት ለመተራረብ ነውና ተናጋሪው ከአፉ ላወጣው ቃል ትኩረት አልሰጠውም። የጓደኛውን ስሜት ይጎዳል ብሎም አልጠረጠረም። ነገር ግን እቺ ክፉ ቃል በልቡ ውስጥ ቤት ሰርታለቸ። የጥላቻ ቤት፤ የመጠላላት ቤት። ሆኖም የእለቱ የፍቅር ውሏቸው ተቋጨና ተለያዩ። ተናጋሪው በውስጡ ነገን እየናፈቀና አብረው የሚውሉበትን ሰአት እየጠበቀ ወደ ቤቱ ሲገባ ̋ሸፋፋ ̋ የተባለው ደግሞ ከራሱ ጋር እያወራና ብስጭቱ ያመጣበትን ግልፍተኝነት ለማረጋጋት እየሞከረ ሄደ። ጥቂት ሰአታት አለፉ።
የሞት ጥሪ
ተናጋሪው ሰው ከቤቱ ወጣ፤ አወጣጡ ሚስቱና ልጁን ሰላም ብሎ ወደ ጎረቤት ለመሄድ ነበር፤ ምክንያቱ ደግሞ ቴሌቪዥን ለማየት ነው። በቤቱ ቴሌቪዥን ስላልነበረ ጎረቤት ወዳለ ጓደኛው ዘንድ ቴሌቪዥን ለመመልከት ሄደ። እዛም እየተጫወተና ቴሌቪዥን የሚተላለፈውን ሙዘቃ እየኮመኮመ ቁምነገር ዜናውን እያደመጠ ቆየ። ቀኑ እየመሸ ነበርና ልቡ ወደ ቤቱ በመሄድና እዛው በመቆየት መካከል ነበር።
ልቡ በልሂድና በአልሂድ መካከል ሲወላውል ከውጭ የተጠራ መሰለው። የትንሽ ልጁ ድምፅ ነበር። ̋ አባዬ ና ትፈለጋለህ ̋ አለው። ይህን የአስር አመት ህፃን የላከው የአባቱ የልብ ጓደኛ የሆነው ያ ̋ሸፋፋ ̋ የተባለው ሰው ነው። በልቡ ያሰበውን እኩይ ተግባር አንግቦ ወደዚህ ወዳጁ ቤት ሲመጣ በዛ እሳት በለበሰ ስሜቱ ሆኖ የፈለገውን ማግኘት አልቻለም። የሰውየው ሚስት ባልሽ የት ሄደ? ተብላ ስትጠየቅ ነገሩ ስላላማራት ቤት እንደሌለ ተናገራች። ምንም የማያወቀው የአስር አመት ህፃን ልጅ ግን ብቅ ብሎ ጎረቤት ቴሌቪዥን ሊያይ ሄዶ ነው በማለቱ ጥራው ተብሎ ተላከ።
የሚፈልገው ሰው ማን እንደሆነ ለማየት ብቅ ያለው ወጣት ጓደኛው መሆኑን ሲመለከት ተናገረ። ̋ምነው በሰላም ነው አብረን ውለን የፈለግከኝ ̋ ብሎ በመጠየቅ ወደ ቆመበት ተጠጋ። ይህ ሁሉ ሲሆን ሚስትና ህፃን ልጅ ቆመው ይመለከታሉ።
ወደ ጠሪው ሲቃረብ ያ ጥሩልኝ ያለው ወጣት በጥፊ ተቀበለው። እራሱን ለመከላከል ሙከራ በሚያደርግበት ወቅት ደግሞ ያላሰበውን ጩቤ ከጎኑ አውጥቶ አንገቱ ላይ ሽጦበት ሩጦ ሄደ። ልጁና ሚስቱ በሁኔታው ተደናግጠው ሲጮሁ የተወጋው ሰው ጥቂት ለመንገታገት ሞክሮ ባለመቻሉ በቁሙ ተዘረረ። ጎረቤቶች ጩኸት ሰምተው ሲወጡ ከተጎጂው አንገት ስር የመጣው ደም አካባቢውን ሞልቶት ነበር። ወደ ህከምና ሊወስዱት ሲያነሱት ግን ህይወቱ አልፋለች።
ማንም ባላሰበውና ባልገመተው ሁኔታ ገዳይ ‹‹ ሸፋፋ›› አለኝ በሚል ምክንያት ቤቱ ገብቶ ጩቤ ታጥቆ ለገድያ መውጣቱ ብዙዎችን አስገርሟል። ቀናቸውን በመተራረብና በመሳሳቅ የሚያሳልፉ ሁለት ጓደኛሞች በግድያ የቆየ የወዳጅነት ፋይላቸውን እስኪዘጉ ድረስ ጓደኛው ገደለው መባሉ ለብዙዎቸ እንቆቅልሽ ሆኖ ነበር።
ተጠርጣሪው ከሸሸበት በህዝብ ትብብር ተይዞ ሲጠየቅ ̋በፈለገው ነገር በቀልድ ምንም አይመስለኝም ነገር ግን እንዴት በተፈጥሮዬ ይቀልዳል ̋ አለ። ሁሌም የለመዱት መተራረብና መሰዳደብ ለዚህ ላልታሰበ ድርጊት ያደርሳቸዋል ብሎ የጠረጠረ አልነበረም። ሟችም አገር አማን ብሎ የተቀመጠ እንኳን በጓደኛ በሌላ ሰው እጠቃለሁ ብሎ የማያስብ እንዲሁም እስከመጨረሻ ለገዳዩ የነበረው ፍቅር ያልቀነሰ ምስኪን ነው።
በአንዲት ቃል ህይወት ጠፋ። የጓደኛው ሞት ያሳዘነው የሚመስለው ገዳይ ̋ሳላስበው ሰይጣን አሳስቶኝ ያደረኩት ነገር ነው ̋ አለ። የሁለቱ ፍቅር በመቃብርና በእስር መደምደሙ ግን ግድ ሆነ። እናትና ልጅም ፊታቸው እያዩት የተነጠቁትን አባወራቸውን አፈር አለበሱ።
ውሳኔ
በበቂ ማስረጃዎችና መረጃዎች ተጠናክሮ የቀረበለትን ክስ ሲመረምር የቆየው የፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት የካ ምድብ ችሎት በተከሳሹ ላይ የመጨረሻውን ፍርድ ለማሳለፍ በቀጠሮ ተገኝቷል። ፍርድ ቤቱ ቀደም ሲል ተከሳሹ በቀረበባቸው ክስ ጥፋተኛ መሆናቸውን አረጋግጦ የክስ መከላከያቸውን እንዲያቀርብ ዕድል ሰጥቷል። ተከሳሹም ሰይጣን አሳስቶኝ ነው ከማለት በስተቀር ስለ ወንጀሉ ፈጽሞ አላስተባበለም።
ፍርድ ቤቱ በዕለቱ በሰጠው የመጨረሻ ውሳኔ ሁለቱ ባልንጀሮች በአጋጣሚ ግጭት አንዱ አጥፊ አንዱ ጠፊ መሆናቸውን ግምት ውስጥ በማስገባት ገዳይ እጁ ከተያዘበት ጊዜ አንስቶ በሚታሰብ የ12 ዓመት ጽኑ እስራት ‹‹ይቀጣልኝ›› ሲል ውሳኔውን በማሳለፍ መዝገቡን ዘግቷል።
አሥመረት ብሥራት
አዲስ ዘመን ሐምሌ 23/2014