የዛሬው ‹‹የዘመን እንግዳችን›› ለረጅም ዓመታት የመረጃና ደህንነት ባለሙያ እንዲሁም ዲፕሎማት ሆነው ሀገራቸውን ያገለገሉ ጉምቱ ሰው ናቸው። እንግዳችን አቶ በላይ ገብረፃድቅ ይባላሉ። የተወለዱት አዲስ አበባ ከተማ ራስ ዳምጠው ሆስፒታል አካባቢ ሲሆን እድሜያቸው አስር ዓመት ከሆነ በኋላ ደግሞ ኮልፌ አካባቢ ነው ያደጉት። የመጀመሪያ እና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን አዲስ ከተማ ልዑል ወሰንሰገድ እንዲሁም ልዑል መኮንን እየተባሉ ይጠሩ በነበሩ ትምህርት ቤቶች ተከታትለዋል።
የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን እንዳጠናቀቁም አባዲና ፖሊስ ኮልጅ ገብተው በምክትል መቶ አለቅነት ማዕረግ በንጉሠ ነገሥቱ እጅ ተመርቀዋል። ከ1965 ዓ.ም ጀምሮ በወቅቱ የመከላከል መረጃ ተቋም ይባል በነበረው የህዝብ ፀጥታ ጥበቃ ዋና መሥሪያ ቤት ተመድበው አስፈላጊውን ሙያዊ ሥልጠና በዘመኑ ወዳጅ በነበሩት እስራኤሎችና አሜሪካውያን ከወሰዱ በኋላ አስተባባሪ በመሆን እስከ መሥከረም 1967 ዓ.ም ድረስ ሠርተዋል።
በመቀጠልም የመከላከያ መረጃ መምሪያ እየተባለ ወደሚጠራው የሥራ ክፍል ተዛውረው መስራት ጀመሩ፤ እዚህም መምሪያ ሳሉ የመረጃን ስራ ጨምሮ የበረራ ደህንነት ጥበቃን ማለትም ፀረ-አውሮፕላን ጠላፊዎችን ምድርና አውሮፕላን ላይ ሆኖ የመቆጣጠር ሃፊነት ተሰጥቷቸው ወደ ቀጣዩ የሲቪል እርከን እስከተዘዋወሩበት ጊዜ ድረስ በሠራዊቱ ውስጥ በሻምበልነት ማዕረግ አገልግለዋል። ከ1971 ዓ.ም ጀምሮ ለተከታታይ አራት ዓመታት ደግሞ አዲስ ተቋቁሞ በነበረው የሀገርና ሕዝብ ደህንነት ጥበቃ ሚኒስቴር በሚኒስትሩ ፅህፈት ቤት የመምሪያ ኃላፊ ፤ የሚኒስትሩ ልዩ ረዳትና የመረጃ ሰነዶች አስተባባሪ ሆነው ሰርተዋል። በዚህ ጊዜ በመረጃ ተቋም ሥልታዊ መረጃ ትምህርት ቤት ሙያዊ ክህሎት ላይ አስተምረዋል።
እንግዳችን የደርግ መንግሥት እስከ ወደቀበት ጊዜ ድረስ ደግሞ ወደ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ተዛውረው በዋሽንግተን የኢትዮጵያ ኤምባሲ አንደኛ ጸሃፊ ዲፕሎማት፤ በምስራቅ ጀርመን በርሊንና በመጨረሻም እስራኤል ቴላቪቭ አማካሪና ላይዘን ሆነው አገልግለዋል። ይሁንና በወቅቱ መንግሥታዊ ሥልጣኑን በተቆጣጠረው የሕወሓት ደህንነት በተፃፈ ደብዳቤ ከስራ በመታገዳቸው ወደ እንግሊዝ ለመሰደድ ተሰደዱ።
ጀርመን በነበሩበት ጊዜም በሥልጣን ላይ የነበረው መንግሥት ረጅሙን የአገልግሎት ዘመናቸው፣ ለስራው ያሳዩትን ታታሪነት፣ ሙያተኝነትና ለሀገራቸው ያላቸውን ፍፁም ታማኝነት ከግምት ውስጥ በማስገባት የሦስተኛ ደረጃ የሕብረተሰዊነት ኢትዮጵያ ጀግና ሜዳይ ተሸላሚ በማድረግ ካሉበት ሥፍራ ድረስ እንዲደርሳቸው ተደርጓል። ዲፕሎማት ሆነው በሚሰሩበት ወቅት በቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ዩኒቨርሲቲ ጀምረውት የነበረውንና ሦስተኛ ዓመት ላይ ያቋረጡትን ትምህርት በመቀጠል የመጀመሪያና ሁለተኛ ዲግሪያቸውን በኢኮኖሚክስና በሰው ሃይል እቅድ ትምህርት ዘርፍ ማግኘት ችለዋል።
በስደት ቆይታቸው በተለያዩ ሥራ ዘርፎች ላይ የሰሩ ሲሆን በዋናነትም በአማካሪ ድርጅት ውስጥ ተቀጥረው በጥናትና ምርምር ቀጥሎም በአንድ የክልል መንግሥታት አቅም ግንባታ መስሪያ ቤት በአማካሪነትና ለሥራ ፈላጊዎች ሥልጠና በመስጠት ተቀዳሚ ባለሙያ በመሆን አገልግለዋል። በቅርቡ ደግሞ ወደ ሀገራቸው ተመልሰው ‹‹የመረጃና ደህንነት ሙያና የኢትዮጵያ ገፅታው›› የተሰኘ መፅሐፍ ለአንባቢያን አድርሰዋል። በመፅሐፉና በኢትዮጵያ የመረጃና ደህንነት ዘርፉ ዙሪያ የመረጃና ደህንነት ባለሙያና ዲፕሎማት ከነበሩት ከአቶ በላይ ገብረፃድቅ ጋር ያደረግነውን ቃለ-ምልልስ እንደሚከተለው ይዘን ቀርበናል።
አዲስ ዘመን፡- ከሀገር ወጥተው የቀሩበትን አጋጣሚ ያስታውሱንና ውይይታችንን እንጀምር?
አቶ በላይ፡- እንደሚታወሰው ሕወሓት በ1983 ዓ.ም ሀገሪቱን ሲረከብ እኔንና 78 የሚሆኑ የኢትዮጵያ ዲፕሎማቶችን ውጭ እያለን ከስራ አሰናበተን። ወደ ሀገር ቤት እንድመለስ ብጠራም አጠራራቸው በጎ አይነት ስላልነበርና አዝማሚያው ስላላማረኝ ቤተሰቤን ይዤ ተሰደድኩኝ። በዚያ ጊዜ አሳዛኙ ታሪክ እነዚህ 78 የኢትዮጵያ ዲፕሎማቶች መሰደጃ ቦታ እንኳን እንዳያገኙ ደብዳቤ ተፅፎ የዲፕሎማቲክ ፓስፖርታቸው እንዳይሰራ ተደርጎ ሰርኩላር ተላልፎ ነበር። ግን እድለኛ ሆኜ የእንግሊዝ መንግሥት ያቀርብኩትን የጥገኝነት ጥያቄ ተቀበለው። ከዚያ ጊዜ ጀምሮ እንግዲህ በስደት ሕይወት ነው የቆየሁት። እውነቱን ለመናገር ግን እንግሊዝ ሀገር በቆየሁባቸው ዓመታት ሁሉ ይሄ ነው የሚባል ችግር አልደረሰብኝም። እንዲያውም ብዙ መማር እንድችል፤ ዴሞክራሲ ምን እንደሚመስል እንድረዳ አድርጎኛል። አድሎ የሚባል ነገር አላየሁኝም። ስለዚህ በቆየሁበት መልካም ዘመን ለሀገሩ ሕግና መንግሥት ምስጋና ይግባው እላለሁ። ምክንያቱም ስደት አፀያፊ ነገር ነው፤ ሌላ ቦታ ብሆን ደግሞ ችግር ሊያጋጥመኝ ይችል ስለነበረ ነው።
አዲስ ዘመን፡- በመረጃና ደሕንነት ሙያ ዙሪያ በቅርቡ ለንባብ ያበቁትን ሙያና ታሪክ ቀመስ መፅሀፍ ለመፃፍ ያነሳሳዎት ምክንያት ምን እንደሆነ ቢያስረዱን?
አቶ በላይ፡- በእኔ ግምት የመረጃ ተቋሙ፣ ሙያውና ሙያተኞቹ ለአንድ ሀገር ወሳኝ ግብዓቶች ስለሆኑ ሕብረተሰቡ በአግባቡ ሊያውቃቸው ይገባል። ምክንያቱም ስለዚህ ተቋም የሚባለውን አውቅ ስለነበር ነው። የሚገርምሽ በዚህ ተቋምና ሙያ ላይ የነበረው ጥላቻ ምንም ከማይረዳው ሕዝብ ብቻ ሳይሆን ከላይ የተቀመጡ ትልልቅ የመንግሥት ሃላፊዎችና የጉዳዩ ተጠቃሚ የሆኑ ሰዎች ሳይቀሩ ፍፁም የሆነ ጥላቻ ነበራቸው። ስለዚህ ይህ ሁኔታ መቀየር ስላለበት ሰዎች እንዳልኩት ተቋሙንም ሆነ ሙያውን እንዲሁም ሙያተኞችን በአግባቡ ሊረዱ ይገባል ከሚል መነሻ ነው የፃፍኩት። ይሄ ደግሞ በዝርዝር መፅሐፉ ውስጥ ስለተጠቀሰ አንባቢያን እንዲያነቡት እጋብዛለሁ። ሁለተኛ መውደድም ሆነ መጥላት እውነቱን ለመናገር በአጀብ ከሚሆን ይልቅ በምክንያት ቢሆን ይሻላል። አንዳንዶቻችን ሌላው የነገረንን ብቻ አምነን እንቀበላለን። ያ ከሚሆን ይልቅ በማወቅ ላይ ተመስርተን ነው መጥላትም ሆነ መውደድ ያለብን። ምክንያቱም በማወቅ ላይ የተመሰረተ ጥላቻ በራሱ የሚነቀፍ ባለመሆኑ ነው።
በመሰረቱ የመረጃ ደህንነት ተቋም የሀገርና ሕዝብ ጠባቂ እንጂ በየወቅቱ የሚቀያየሩ መሪዎች ጠባቂ አይደለም። ይህንን ስል እዚያ ተቋም ውስጥ መሪውን የሚጠብቅ ክፍል የለም እያልኩኝ አይደለም። ሌላው ግን በኢትዮጵያ ፖለቲካ፣ ኢኮኖሚ፣ ወታዳራዊ ጉዳዮችና ሕብረተሰብ ላይ ችግር እንዳይደርስ የሚከላከል ነው። ከዚያ ባሻገር ሙያው በእውቀት ላይ ተመስርቶ የሚሰራበት ነው። ስለሆነም ለሙያው የሚመጥኑና የሚችሉ ፍቃደኞች የሆኑ ወጣት ኢትዮጵያውያን በሙሉ በውስጡ መካተት አለባቸው። ምክንያቱም ሙያው ሀገር አድን በመሆኑ ነው። ይህንን የበለጠ ለመረዳት ግን መፅሐፉን ማንበብ የሚያስፈልግ ይመስለኛል።
በተጨማሪም ስለመረጃ ምንነት የሚያውቁ ካሉ የበለጠ እንዲያውቁ፤ የማያውቁ እንዲያውቁ፤ አውቀው ግር ያላቸው ደግሞ የበለጠ እንዲረዱ ያደርጋል ብዬ ስለማምን ነው ይህንን መፅሐፍ የፃፍኩት። ደግሞስ እኛ ትናንት የነበርነው ሰዎች ካልፃፍን ማን ይጻፈው?። በእኔ ግምት እስካሁን ድረስ ይህንን መሰል መፅሐፍ አልተፃፈም፤ ብዙ ነገሮችን ያካተተ መረጃ ያለው በመሆኑ ጠቃሚ ነው ብዬ በማሰብ ነው። በዋናነት ግን ለመፃፍ አነሳስቶኛል የምለው ቶድ ሄነሪ የሚባል ጸሃፊ መፅሐፉን ሲፅፍ የመፅሀፉን አርዕስት ‹‹ ባዶህን ሙት›› ብሎ ነው የሰየመው፤ ይህም ማለት ሁላችንም ወደዚህ ስንመጣ ምንም ይዘን እንዳልመጣነው ሁሉ ስንሄድም ምንም ይዘን አንሄድም፤ ስለዚህ እኔም ቢያንስ የማውቀውን ሰጥቼ ባዶዬን ልሙት ብዬ በማሰብ ነው።
አዲስ ዘመን፡- ስለ መረጃ ደህንነት ሙያና ስራ ሕዝቡ ላይ የተዛባ ግንዛቤ እንዲኖር ያደረገው ምንድን ነው ብለው ያምናሉ?
አቶ በላይ፡- አስቀድሜ እንደገለጽኩት እዚህ ሀገር ትልቁ ችግር በማህበር መውደድና መጥላት እንደባህል ሥር የሰደደ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ የተፈጠረ ነው የሚመስለኝ። ለጥላቻም ሆነ ለፍቅራችን ምክንያታዊ ያለመሆኑ ነገር አለ። ሙያው ሀገር አድን ነው፤ እኔ መፅሐፉን ስፅፍ ምክንያቶቼን እንደገለፅኩልሽ ከእነዚህ አንዱ ሙያውንም ሆነ ዘርፉን ሰዎች የሚጠሉት በቅጡ ስለማያውቁት ነው። ቢያውቁት ኖሮ ሀገር አዳኝ መሆኑን ይረዱ ነበረ። በጭራሽ ይሄ ተቋም የመንግሥት ዙፋን ጠባቂ አይደለም። ይልቁኑም የፖለቲካ አለመረጋጋት በሀገር ውስጥ እንዳይፈጠር መንግሥትን ይመክራል፤ የኢኮኖሚ ቀውስ እንዳይከሰት ያሉ ችግሮችን ያያል፤ ሕብረተሰቡ ያለበትን ችግር ይጠቁማል፤ ሊስተካከሉ በሚገቡ ፖሊሲዎች ላይ ሃሳብ ይሰጣል፤ ወታደራዊ ጉዳይን በሚመለከት ከወታደሩ ቀድሞ መረጃ በማግኘት ሀገርን ይታደጋል። ምክንያቱም ወታደሩ ከመዝመቱ በፊት የሚያስፈልገውን መረጃ ካላገኘ የእሳት ራት ነው የሚሆነው። መረጃው ከተገኘ ጠላት የሚሰበስባቸው መሳሪያዎች፣ ታንኮች፣ ሚሳኤሎች ሁሉ ልክ እንደልጆች አሻንጉሊት ሊቆጠሩ ይችላሉ። መረጃው ቀድሞ ከተገኘ የወገን ሃይል በቀላሉ የጠላትን መሳሪያ ማደባየት ይችላልና ነው።
ስለዚህ እኔ ሕብረተሰቡ መረጃ ላይ የተመሰረተ ጥላቻ አለው ብዬ አላምንም። ከዚህ በመነሳት ጥላቻው መሰረተ ቢስ ነው ባይ ነኝ። እርግጥ ነው፤ አንዳንድ ጊዜ እነዚህ የመረጃና ደህንነት ሰዎች ከሚገባው በላይ ሃይል በመጠቀም መረጃን ለማውጣጣት የሚያደርጉት ጥረት በሕዝብ ዘንድ ጥሩ ምልከታ እንዳይኖራው አድርጎ ሊሆን ይችላል፤ ሆኖም ይህንን የሚያደርጉት በተለይ የጠላት ምርኮኞች የሚፈለገውን መረጃ የሚደብቁ በመሆኑ ነው። ይህም ቢሆን ምክንያታዊ ነው ብዬ አላምንም፤ ሃይል ከመጠቀም ይልቅ ሰውን አለመጉዳትና ቀስ ብሎ በዘዴ ማውጣቱ ነው ተመራጭ።
አዲስ ዘመን፡- በመፅሐፎት ላይ እንደተጠቀሰው የመረጃና ደህንነት እንዲሁም የስለላ ስራ ከኢዛና ዘመነ-መንግሥት ጀምሮ የነበረ፤ በዚህ ዘርፍ ኢትዮጵያ ዘመናትን ያስቆጠረ ታሪክ እንዳላት ያነሳሉ። ለመሆኑ በየትኛው ዘመነ መንግሥት ነው የበለጠ የመረጃና ደህንነት ሥራ በሙያ ደረጃ ጎልቶ የወጣውና የዳበረው?
አቶ በላይ፡- እንግዲህ ታሪካዊ ሂደቱ ምን ይመስል እንደነበር መፅሐፉ ውስጥ በዝርዝር ተጠቅሷል። በሀገራችን በተለይም በዳግማዊ ምኒልክ ዘመነ-መንግሥት መሰረቱ ተጥሎ ነበር። እውነቱን ለመናገር እስከ ተወሰነ ጊዜ ድረስ ሰርቷል። ከዚያ በኋላ ቀዳማዊ ኃይለሥላሤ ሲረከቡት የተሻለ ተቋም ተገንብቷል። ምክር የሚሰጡትም ሰዎች ከሰለጠነው ዓለም አካባቢ የመጡ ስለነበሩ መረጃውን ዘመናዊ በሆነ መንገድ ለማቋቋም የሚቻለው ሁሉ የተደረገ ይመስለኛል። ይህም ስለሆነ በየዘርፉ የተደራጀ መረጃ በአግባቡና መልክ ባለው ሁኔታ የመረጃ ተቋሙ እንዲመሰረት የተደረገው። በዚያ ጊዜ ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማትና ከማሰልጠኛዎች ተማሪዎች ተመልምለው፤ ሰልጥነው ለስራ እንዲሰማሩ ተደርጓል። እንደየአስፈላጊነቱም ውጭ ሀገር እየተላኩ አስፈላጊውን ሥልጠና እንዲያገኙ ተደርጓል።
እናም በቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ዘመነ መንግሥት በተሻለ ሁኔታ የመረጃ ተቋሙ መልክ ኖሮት ተደራጅቶ ነበር ማለት ይቻላል። በዚህም ምክንያት ሀገራችን ውስጥ የነበሩ አንዳንድ ችግሮች በተለይም ከውጭ የሚመጡ ሰላዮችን ማምከን ችሏል። እናም የተዋጣለት የመረጃ ተቋም ነበርም ማለት ይቻላል። በቁጥር ደረጃ በጣም አነስተኛ ግን ደግሞ በአግባቡ የሰለጠነና ያወቀ፤ አመራሩም በጣም የጎለበተ እውቀት ያለው ስለነበረ በጥሩ ሁኔታ ተደራጅቶ ነበር ብዬ አምናለሁ። የደርግ መንግሥት ሲመጣ ግን የመረጃውን ተቋም የንጉሱ ዙፋን ጠባቂ አድርጎ ያየው ስለነበር አላስፈላጊ ጥላሸት ሲቀባው ለተወሰነ ጊዜ ከርሟል። ግን የውጭ ጠላቶች ይህንን አጋጣሚ በመጠቀም ከተማ ውስጥ በከፍተኛ ደረጃ ይርመሰመሱ ስለነበር፤ በተለይም ደግሞ አንድ ክስተት ከተፈጠረ በኋላ ክፍተቱ ስለታያቸው ነው ዳግሞ እንዲቋቋም ያደረጉት።
አዲስ ዘመን፡- ምን ነበር የተከሰተው?
አቶ በላይ፡- አንደኛ በጠላትነት የሚያዩን ሃይሎች ነበሩ፤ ይህ ምንም የማይታበል ነው። ምክንያቱም የአባይና የድንበራችንም ጉዳይ እንዲሁም በሱማሌ በኩል የነበረው የመሬት ቅሚያም በዚያን ጊዜ ይህንን አጋጣሚ በመጠቀም አላስፈላጊ ነገሮችን መፈፀም የመረጃው ተቋም ነበር የሚጠቁመው። ከዚያ ባሻገር ከተማ ውስጥ በሸማቂው ድርጅት አንዳንድ ቦታ ላይ ፍንዳታ እንዲፈፀም ሆነ። በዚህ ምክንያት የመረጃውን ተቋም ሲስተናገድ የነበረው አላግባብ ስለነበር ወደ ልቦናችን ተመልሰን የመረጃው ድርጅት እንዲሰራ ብናደርግ ይህ ሁኔታ ሊለወጥ ይችላል የሚል ድምዳሜ ላይ ተደርሶ ነው የመረጃውን ድርጅት እንደገና በተሻለ መልኩ ማቋቋም ሊያስፈልግ ይችላል ተብሎ ታምኖበት ሃሳባቸውን የለወጡት።
የሚያሳዝነው ግን በዚያን ጊዜ የነበሩ ከፍተኛ መኮንኖች ከንጉሱ ጋር ንክኪ አላቸው፤ ወይም ደግሞ በረጅም ጊዜ ቆይታቸው ይህንን ያህል ያስመዘገቡት ነገር የለም የሚል ሃሳብ መነሻ በማድረግ ሥልጣናቸውን እንዲለቁ በመደረጉ የመረጃው ድርጅት በጣም ሳስቶ ነበር። ስለዚህ ወደኋላው ላይ የሀገር ደህንነትን የማስጠበቁ ነገር ያለመረጃው ተቋም ምንም ሊደረግ እንደማይችል ግንዛቤ ተይዞ ድርጅቱ እንዲጠናከር ተደረገ። በውስጡ በርካታ ክፍሎች ያሉት፤ የመከላከል መረጃ ያለው፤ የውጭ መረጃን የሚያጠናቅር፤ የኢኮኖሚ መረጃን የሚያሰባስብ፣ የምርመራ ዘርፍ ኖሮት በከፍተኛ ደረጃ እንዲጠናከር ተደረገ።
ይሁንና ቀደም ሲል የነበረው የሰለጠነው የሰው ሃይል ስላልነበር ከውጭ የመጣው ሃይል የሚፈለገውን ያህል ለመስራት አልተቻለውም። ምክንያቱም ሰው ስለመጣ ብቻ ሥራውን ይሰራል ማለት አይደለም። ስለዚህ ለተወሰነ ጊዜ ጠንካራ የሚባል አልነበረም፤ ግን በሂደት ጥሩ እየሆነ ሄዶ እንዳውም ትክክለኛውን ምንጭ ባላስታውስም በአፍሪካ በሶስተኝነት ከሚመደቡ ጠንካራ የመረጃ ተቋም ውስጥ አንዱ ነበር። ባለፉት 27 ዓመታት ግን ብዙ የጠለቀ እውቀት የለኝም፤ ምክንያቱም አስቀድሜ እንደገለፅኩልሽ በወቅቱ የመረጃ ሃላፊ በአቶ ክንፈ ገብረመድህን ደብዳቤ የተባረርኩኝ በመሆኑ ከዚያ በኋላ ያለውን አላውቀውም። ከሰማሁት ነገር ተነስቼ ግን መናገር ያስቸግረኛል። ምክንያቱም ቦታው ላይ የነበረው ሰው ቢናገረው ነው የሚሻለው።
አዲስ ዘመን፡- የመረጃ ደህንነት ስራ በኢትዮጵያ ረጅም ታሪክ ያለው እንደመሆኑ ሙያውም ሆነ ተቋሙ የዚያኑ ያህል ማደግ ያልቻለበት ምክንያት ምንድነው ይላሉ?
አቶ በላይ፡- ለዚህ ትክክለኛውን ምክንያት ለመናገር መረጃና ማስረጃ ባላቀርብም ግን የሚሰማኝን ሃሳብ ነው የምሰጠው። በእኛ ሀገር አንዱ መንግሥት ሄዶ ሌላኛው ሲመጣ እያፈረሱ መገንባት ብዙ ነገር አሳጥቶናል ብዬ አስባለሁ። ለምሳሌ በንጉሡ ዘመነ-መንግሥት የነበሩ ትላልቅ ጉምቱ የነበሩ ሃላፊዎች ነበሩ። እንደኮሎኔል ሰለሞን ከድር፣ እንደ ጀነራል አምደሚካኤል በላቸው፣ እንደአቶ ነብየ ልኡል ክፍሌ የመሳሰሉ ሰዎች በአንድ ቀን የሚገኙ ወይም የሚመረቱ አይደሉም። ረጅም ጊዜ የወሰደ ትምህርት፣ ልምድ፣ የውጭ ተሞክሮ ያላቸው ሰዎች ናቸው። የመምራት ብቃት የነበራቸው ናቸው። እነዚህን ሰዎች በምንም አይነት በዓመታት መተካት አይቻልም። ደርግ እንደመጣ እነዚህን ሰዎች እንዲረሸኑ አድርጓል።
እነዚህን ሰዎች ማጣት ማለት ከፍተኛ ክስረት ነው። ከዚያም በኋላ በርካታ ሰዎችን በተዋረድ አጥተናል። እሱ ብቻ ሳይሆን እነዚህን ሰዎች ማጣት ከፍተኛ ክስረት ሆኖ ተቋማቱንም እንደዚሁ አፍርሰናል። እናም የመረጃው ተቋም ትናንት የነበረውን አፍርሶ መገንባቱ በርካታ ችግሮች ፈጥሯል። በደርግ ጊዜ ደግሞ ጠንካራ ተቋም ተቋቁሞ ብዙ ነገር የሰራ ቢሆንም ወያኔ ሲመጣ ፎቁንና የቴክኖሎጂ ቁሳቁሱን ወስዶ ሰዎቹን በሙሉ እስር ቤት ነው የከተተው። እናም ከዚህ በላይ የበለጠ ክስረት አይኖርም።
በመፅሐፌም ላይ ‹‹በሰፈሩት ቁና መሰፈር አይቀርም›› በሚል ርዕስ የካተትኩት ሃሳብ በሱማሊያ በኩል የነበረውን ችግር የፈታው የደህንነቱ መስሪያ ቤት ነው። ሌላው ይቅርና ከሸማቂዎች ጋር ድርድር እንዲኖር ሁኔታዎችን ያመቻቸው የመረጃው መስሪያ ቤት ነው። በርካታ ምክረ-ሃሳቦችን ከመረጃው ጋር የሰጠው ይኸው መስሪያ ቤት ነው። በአጠቃላይ በርካታ ሥራዎችን የሰራ ወደፊትም ሊሰራ የሚችል ተቋም ነበር። ያ በነበረበት ሁኔታ እንዲቀጥል ባለመደረጉ እንደሀገር ብዙ ጉዳት የደረሰብን ይመስለኛል። አሁንም ቢሆን ወደፊት እያፈረስን የምንገነባ ከሆነ በውስጡ ያሉትን ሰዎቻችንን እንደማይፈለግ እቃ የምንወረውራቸው ከሆነ ችግሩ የከፋ ነው የሚሆነው። ስለዚህ የሚመለከተው አካል ማስታወሻ ሊወስድበት የሚገባ ይመስለኛል።
አዲስ ዘመን፡- በመፅሐፎት ላይ ‹‹የሙያተኞችን ወኔ ሰላቢ ባለሥልጣናት›› ሲሉ ጠቅሰዋል፤ ለመሆኑ ይህን ሲሉ ምን ማለትዎ ነው?
አቶ በላይ፡- በመጀመሪያ እንዲያው ሊሆን የሚገባው በከፍተኛ ማዕረግና ሥልጣን ላይ ያሉ ሰዎች የመረጃ ‹‹ሀ፣ ሁ›› እንዲያውቁ ቢሆን መልካም ነው። ምክንያቱም መረጃው ተቋም የሚሰራውን የሚያውቁ ከሆነ ጥላቻው ቦታ እንደማይኖረው በቂ ማስገንዘቢያ ሊሆን ይችላል። አስቀድሜ እንዳነሳሁት በጅምላ የመጥላት ባህሉ ባለሥልጣናቶቻችን ዘንድ ሳይቀር ዘልቋል። አንድ ምሳሌ ልጥቀስልሽ፤ በአንድ ወቅት እኔ ማታ ላይ ከቢሮ ስወጣ መንገድ ላይ አንድ ሚኒስትር የመኪናቸው ጎማ ተንፍሶ ተመለከትኩኝ፤ እሳቸው ባያውቁኝም እኔ ስለማውቃቸው ዝም ብዬ ማለፍ ስላላስቻለኝ ከፊት መኪናዬ አቁሜ አጠገባቸው ሄጄ ጌታዬ ምን ልርዳዎት ስላቸው ፊት ለፊት ያቆምኩትን መኪና አይተው ‹‹ማን ነው የላከህ?፤ እከሌ ነው ወይ?›› ብለው ነው የጠየቁኝ። እንግዲህ አንድ ሚኒስትር ከተሰላይነት ውጪ ካላሰበ እኔ ተራው ሰው የፈለገውን ቢሆን ምንም ሊገርመኝ አይችልም።
ስለዚህ ጥላቻው ሕዝቡ ብቻ ውስጥ ያለ ሳይሆን ባለሥልጣናቱ ውስጥም ያለ መሆኑን ለማሳየት ነው። ወደፊትም ለመሄድ አንዱ ማነቆ ይሄ ይመስለኛል። እነሱ በስራው ካላመኑ፤ በሰዎቹ ላይ እምነት ካልጣሉ፤ ለሀገር ይበጃል ካላሉ ሌላው ተራው ሰው የፈለገውን ቢል ብዙ ሊደንቀን አይችልም። በከፍተኛ ሥልጣን ላይ የነበሩ ሰዎች ይህ አይነት ጥላቻ ነበራቸው። ግን ሁሉም ናቸው ለማለት ያስቸግራል።
አዲስ ዘመን፡- በባለሥልጣናቱ የነበረው እርስ በእርስ የመጠላለፉ ነገር የሀገር ደህንነት ላይ የጣለው አደጋ ምን ነበር?
አቶ በላይ፡- እውነቱን ለመናገር ተደጋግፎ በመስራት የሚገኘውን ውጤት ያህል በተናጠል የሚደረገው ሙከራ ውጤታማ ይሆናል ማለት ያስቸግራል። በጋራ ማሰብና መስራት ውጤታማ ያደርጋል። እኛ ስለተጠላን ሥራችንን አላቆምንም። ምክንያቱም የምንሰራው ለሀገርና ለሕዝብ ነው እንጂ ለግለሰቦች አልነበረም። ያ ማለት ጥላቻው ጫና አልነበረውም ማለት አይደለም፤ ግን ጫናም ቢኖረው የተሰጠንን አደራ ሀገርና ሕዝብ መጠበቅ ስለሆነ በአቅማችንና ሙያችን በሚፈቅደው መሰረት ሥራው ተሰርቷል። የበለጠ ግን መስራት ቢቻል ኖሩ ውጤቱ የተሻለ ይሆን ነበር። እናም ዝም ብለው የሚጠሉ ግለሰቦች አልጠፉም፤ ግን የመረጃው ተቋም በዚያ ጊዜ ከእነዚህ ሰዎች የጥላቻ ጦር ይወረወራል ብሎ ስራውን አላቆመም፤ ይሰራ ነበር። እናም መጠላለፉ ጎድቷል፤ ግን ሥራ እንዳንሰራ አላደረገንም።
አዲስ ዘመን፡- ይህ የመረጃ ተቋም ባለፉት 27 ዓመታት ኢትዮጵውያን ለደህነታቸው የሚተማመኑና ልክ እንደ ምዕራብውያና የስለላ ድርጅቶች የሚኮሩበት መሆን ያልቻለበት ምክንያት ምንድን ነው ይላሉ?
አቶ በላይ፡- ባለፉት 27 ዓመታት ስለነበረው አጠቃላይ ሁኔታ ዛሬ ባልመልሰው ደስ ይለኛል። ምክንያቱም ሁለተኛው መፅሐፌ ላይ በስፋት የተሄደበት ስለሆነ ነው። ደግሞም ከምሰማውና ከሚዲያ ከማየው ባለፈ ውስጡ ስልነበርኩኝና ተጨባጭ መረጃ በእጄ ሳይኖር ይሄ ነው፤ ያ ነው ብሎ ለመናገር ያስቸግረኛል። ምክንያቱም ክህሎቴም እምነቴም ተጨባጭ በሆነ ነገር ላይ መናገር በመሆኑ ነው። ያልተጨበጠ ነገር ደግሞ አሉባልታ ነው የሚሆነው። በጥቅሉ ግን ትናንትና የእኛን መስሪያ ቤት ሲያጠለሽ የነበረው ይሄኛው ቡድን እሱ ራሱ በዚያ ስህተት ውስጥ ተዘፍቆ እንደነበር እረዳለሁ። እሱ ሲያደርገው ምንም ችግር የለውም ብለው ነበር የሚያስቡት። እኛ በስደት ሳለንም ስለዚህ ተቋም ብዙ ሰዎች ብዙ ነገር ሲናገሩ አድምጠናል።
ወያኔ ተቋሙን ሆነ ሕዝቡን ይመራበት የነበረው አይነት አሰራር በአንድ ወቅት ምስራቅ ጀርመን በርሊን ሆኜ ምስስል ያለው ነገር አጋጥሞኝ ነበር። የመረጃ መስሪያ ቤቱ ሰዎችን ጠርንፎ መያዙ ነገር ተመሳሳይነት ነበረው። ያኛው የሚለየው በዘመናዊነቱ ነው። እንደሚታወሰው አንድ ለአምስት የሚባል ጥርነፋ ነበር። እዚያም ያን አይነት መልክ የነበረው የመረጃ ተቋም ስለነበር መጨረሻ ላይ እ.ኤ.አ 1985 እንደገና ማወቅር ስራ በመስራት ኮምዩኒዝምን የመተው ሁኔታ ሲመጣ ያ የተጠረነፈ ህዝብ እንዳለ ነቅሎ ወጥቶ ወደ መረጃው መስሪያ ቤት ነው የሮጠው። ያንን በአይኔ አይቻለሁ። እርግጥ እዚህ ያ አልሆነም፤ አለመሆኑ ጥሩ ነው። ምክንያቱም በመካከሉ ሊፈጠር የሚችለውን ችግር ማንም አያውቅምና ነው።
በአጠቃላይ ግን እንዳው በአይኔ ባላይም በጣም ብዙ በጎ ያልሆኑ ነገሮች እንደተደረጉ እረዳለሁ። ትናንትም እኛ በነበርንበት ጊዜ በተለያዩ ቦታዎች በተለይ እነሱ በነበሩበት ቦታ ላይ ሲደረግ የነበረ ነው። ይሁንና የመረጃ ተቋማት የሚቋቋሙት ሀገርና ህዝብን ለመርዳት እንጂ እንደዚህ አይነት የማይገባ ነገር ለማድረግ አይደለም። በመሆኑም ይህንን ሊቆጣጠር የሚችል አካል መኖር አለበት። ብዙ ጊዜ እንደምለውም ኢትዮጵያ ከ 115 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ አላት፤ ይህ ሕዝብ በሺዎች የሚቆጠሩ የመረጃ ሰራተኞች አይጠበቁም። ኢትዮጵያን የሚጠብቃት የኢትዮጵያ ሕዝብ ነው። በተቻለ መጠን በመረጃው ተቋም ውስጥ ያሉ ሰዎች የሕዝብ አሽከር ነው መሆን ያለባቸው። ምክንያቱም የሕዝብን ወገናዊነት ማግኘት እስካልተቻለ ድረስ የትኛውንም ጠላት መመከት አይቻልም።
አዲስ ዘመን፡- በመረጃ ደህንነት ተቋሙ በሚሰሩበት ጊዜ ቢሆን ብለው የሚቆጩበት ነገር አለ?
አቶ በላይ፡- አለ፤ አንደኛ የሚቆጨኝ ነገር አስቀድሜ እንዳነሳሁልሽ የመረጃው መስሪያ ቤት የሕዝብ ግንኝነት ስራ ሰርቶ ሕዝብን ከጎኑ ቢያሰልፍ ኖሮ ለእኔ ትልቅ ስኬት ነበር። ምክንያቱም እኛ መጨረሻ ላይ ሕዝብ ጠልቶን ነው፤ አይናችሁ ለአፈር ብሎን ነው። ያ ሊሆን አይገባውም። እናም ትልቁ ነገር ሕዝብን ወገናዊ አድርገው ቢሆን ኖሮ በእውነት ትልቅ ስራ ነበር።
ሁለተኛ አመራሩ ላይ ያሉ ባለሥልጣናትን መረጃውን አቅርበው መሪውን የመሞገትና የማሳመን በዚያ መሰረት ውሳኔ እንዲሰጥ አድርገው ቢሆን ኖሮ ትናንት የደረሰው ነገር አይደርስም ነበር። ምክንያቱም የእነሱ መድከም እውነት ይዘው በእጃቸው ማሳመን አለመቻል ትልቅ እንቅፋት ነው።
ሌላው በመስሪያ ቤት ውስጥ በአንድ ወቅት ከሙያው ጋር የማይገናኙ ሰዎች በብዛት እንዲመጡ ተደርጓል። እነዚያ ሰዎች እውነቱን ለመናገር የሚሰሩ ሳይሆን እዳ ሆነው ነው የቆዩት። ያም ስራ በመቻልና ባለመቻል መካከል ባለ ሰው አይሰራም። ብቃት፣ እምነት፣ ድፍረት፣ ንፁህና ከውሸት የፀዱ ሰዎች ያስፈልጋል። በሌላው ሰው መረጃ የሚሰበስብ አካል መጀመሪያ ራሱ የፀዳ መሆን አለበት። እናም በዚያ ጊዜ የማይችሉ ሰዎች ተቋሙን እንዲቀላቀሉ ባይደረግ ኖሮ ምንአልባትም የተሻለና ጥሩ ስራ በሰራን ነበር።
አዲስ ዘመን፡- በመፅሐፎት ላይ የደርግ አመራሮች ጥለው ከመውጣትና ሀገሪቱም በሕወሓት እጅ ሳትወድቅ፤ ኤርትራም ሳትገነጠል፤ ኢትዮጵያም ወደብአልባ ሳትሆን መደራደር ይቻል የነበረበት እድል እንደነበር አንስተዋል። ምን ነበር ያ እድል?
አቶ በላይ፡- በእግጠኝነት ድምዳሜ ላይ ባልደርስም ግን ምንም የማይቻል ነገር እንደሌለ እምነቴ ነው። ለምሳሌ ከሻቢያና ወያኔ ሸማቂ ቡድኖች ጋር ድርድር እንዲኖር መንገዱ የመረጃው መስሪያ ቤት ነው። ውይይቱ በእኛ መስሪያ ቤት ይጀመር እንጂ በአብዛኛው መሰል ችግር ያለባቸው ሀገራት በድብቅ ዲፕሎማሲ ግንኙነት ነው። በእኛ በኩል እስከ ተወሰነ ጊዜ ድረስ ተሞከረ፤ በሙከራ ላይ እንዳለን ፓርቲው በዚህ ጉዳይ ላይ ጣልቃ መግባት ፈለገ፤ እኛ የሌለበት ድርጅት ጨርሶ ሊሆን አይችልም የሚል አቋም ተያዘ። በመካከል የፓርቲ ወኪሎች እንዲገቡበት ተደረገ፤ እነሱ ሲገቡ ደግሞ ውጭ ሆነው የሚደራደሩት የሸማቂው ቡድን አባላት ከእነዚህኞቹ ጋር መደራደር አልፈለጉም። ከዚያ በኋላ የጉዳዩ ባለቤት እንዲሆን ፓርቲው ጉዳዩን በበላይነት እንዲመራ ተደረገ። ብዙ ጊዜ ሙከራ ቢደረግም ግን ምንም መፍትሄ አልተገኘም። ለማንኛውም ድርድር የሃይል የበላይነት ወሳኝ ሚና አለው። ሃይል ካለ ጠላት ያጎነብሳል። የምንፈልገውን የመደራደሪያ ነጥብም ማስቆጠር እንችላለን። ያ ግን አልሆነም። እኛ ሃይል ባለን ጊዜ ያንን ወቅት መጠቀም አልቻልንም። ለምሳሌ በቀይ ኮከብ ዘመቻ ጊዜ የእኛ ሃይል ከሚገባው በላይ ከፍተኛ ደረጃ ደርሶ ነበር። እንኳንስ ለአንድ ሽምቅ ተዋጊ ይቅርና ከዚያም የላቀ ሃይል ካለው አካል ጋር መጋፈጥ የሚችል ስለነበር ከውጊያ ይልቅ ሰላማዊ ድርድር እንዲኖር ሃሳብ ሲሰጥ እላይ ያለው አካል አሻፈረኝ አለ። ችግሩን በመከላከያ ሃይል ለመፍታት ነበር እቅዳቸው። ያ ባይሆን ኖሩ ድርድሩን እንዲቀበሉ ቢጠየቁ ኖሮ ያለንበትን ሁኔታ ያውቁ ስለነበር ምንም እንኳን መገንጠል የሚፈልጉ ቢሆንም በፌዴራል ሥርዓት መፈታት የሚችል እንደነበር ምንም የሚያጠራጥር አልነበረም። እንግዲህ ያ ሆኖ ቢሆን ኖሮ ኤርትራም አትገነጠልም፤ ኢትዮጵያ የባህር ወደብም አታጣም፤ የኤርትራ ወገኖቻችንም ከእኛ አይነጠሉም ነበር። ስለዚህ ስህተት ተፈጥሮ ነበር ማለት ይቻላል። ምክንያቱም ወቅት ባለመምረጣችን የተፈጠረ ነው። እውነቱን ለመናገር የነበረው መንግሥት ብዙ ነገር መልክ እንዲኖረው ሳይፈልግ አልቀረም። ግን መፈለግና ለማድረግ መቻል ወይም የአዕምሮ አቅምን መጠቀም መቻል የተለየ ነው። በዚህ ሁኔታ የምንፈልገውን ነገር ሳናገኝ ቀርተናል ብዬ አምናለሁ።
አዲስ ዘመን፡- ለሰጡን ማብራሪያ በአንባቢዎችና በዝግጅት ክፍሉ ስም ከልብ አመሰግናለሁ።
አቶ በላይ፡- እኔም አመሰግናለሁ።
ማህሌት አብዱል
አዲስ ዘመን ሐምሌ 23 ቀን 2014 ዓ.ም