
የዛሬው የዘመን እንግዳችን የፌዴራል ማረሚያ ቤት ኮሚሽን ኮሚሽነር ጄኔራል የኑስ ሙሉ ናቸው:: ከኮሚሽነሩ ጋር ባደረግነው ቆይታ የማረሚያ ቤቶች ሪፎርም ሥራዎች ያስገኙትን ውጤት፣ የታራሚዎች አያያዝን፣ የኮሚሽኑን የ2017 ዓ.ም. በጀት ዓመት አፈጻጸም እና ሌሎች ተጨማሪ ጉዳዮችን አንስተናል፤ መልካም ቆይታ!
አዲስ ዘመን፡- ማረሚያ ቤቶች እንደ ተቋም እንዴት ይገለጻሉ ?
ኮሚሽነር ጀኔራል የኑስ፡- የፌዴራል እና የክልል ማረሚያ ቤቶች በፍትህ ዘርፉ ውስጥ የሚገኙ ቁልፍ ተቋማት ሲሆኑ በአዋጅ የተሰጣቸውም ተልዕኮም ግዙፍና የፍትህ ዘርፉ ከወንጀል ፍትህ አስተዳደር አንፃር የምርመራ፣ የክስ፣ እና የፍርድ ሂደትን አልፎ ረዥም ጊዜ የሚቆዩበት እና ከቀላል እስራት እስከ ዕድሜ ልክ ፅኑ እስራት የተፈረደባቸውን ዜጎች ዓለም አቀፍ ስታንዳርዶችንና ሀገራዊ ሕጎችን መሠረት በማድረግ የሚታረሙባቸው ተቋማት ናቸው::
ማረሚያ ቤቶች በፍርድ ቤት ውሳኔ አግኝተው የሚላኩ የሕግ ታራሚዎችን ተቀብለው ደህንነታቸው ተጠብቆ፣ ሰብአዊ መብታቸው ተከብሮ፣ መሰረታዊ ፍላጎታቸው አቅም በፈቀደ መጠን ተሟልቶ፣ የተለያዬ የሥነ-ልቦና፣ የንቃተ-ሕግ፣ የሥነ-ምግባር ትምህርት እና ድጋፍ አግኝተው፣ በመደበኛ ትምህርት፤ በቴክኒክና ሙያ ስልጠና በዕውቀትና በክህሎት ዳብረው፣ በተለያዩ የኢንዱስትሪና የግብርና ምርት ሥራዎች ዘርፍ ተሰማርተውና መጠነኛ ገቢ አግኝተው፣ ታርመው፣ ታንፀው፣ አምራችና ሕግ አክባሪ ዜጎች ሆነው ወደ ማኅበረሰቡ እንዲቀላቀሉ በማድረግ ወሳኙን ሚና የሚጫወቱ የአጠቃላይ የፍትህ ዘርፉ ሂደት ሥራ ማሳረጊያና የመጨረሻ መውጪያ በር በመሆናቸው የሁሉንም አጋርነት የሚሹ ተቋማት ናቸው::
አዲስ ዘመን፡- የኢትዮጵያ የማረሚያ ቤቶች ታሪክ እንዴት ያለ ነው ?
ኮሚሽነር ጀኔራል የኑስ፡- የኢትዮጵያን የማረሚያ ቤቶች ታሪክ ስንመለከት ከአክሱማይት ዘመን እንደተጀመረ ከተለያዩ የታሪክ ድርሳናት መረዳት ይቻላል:: በአክሱማይት ዘመን ደብረ ዳሞ፤ በመካከለኛው ዘመን ግሸን እና በጎንደር ዘመን ወህኒ አምባ የሚባሉ እስር ቤቶች እንደነበሩና ዋና ተግባራቸውም ነገሥታት ዙፋናቸው ላይ እስኪደላደሉ ድረስ ተቀናቃኞችን አስሮ ማቆያ እንደነበሩ ይነገራል:: ከነዚህ ሶስት ታዋቂ እስር ቤቶች በተጨማሪ ሌሎች በርካታ እስር ቤቶች የነበሩ ሲሆን በእነዚህ እስር ቤቶች ጥፋት ያጠፉ ሰዎች ጭካኔ በተሞላበት ሁኔታ ከአካል መጉደል እስከ ሞት ቅጣት የሚደርስ ከባድ ቅጣት ይፈጸምባቸው ነበር::
በታሪካችን ለረጅም ጊዜ በዘለቀው የማሰቃያ ቅጣት እና የጨካኝ ሕጎች ተጽእኖ ምክንያት እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ኢትዮጵያ ውስጥ መታሰር ከባድ ፈተና እና ሲኦል እንደመውረድ ሲቆጠር ቆይቷል። እንደየ ሥርዓቱ የቅጣት አይነቶች በሕግ እየተሻሻሉ የመጡ ቢሆንም እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ማረማያ ቤቶች ለማኅበረሱቡም ሆነ መንግሥታዊና መንግሥታዊ ላልሆኑ ድርጅቶች በራቸውን ዘግተው ታራሚዎችን ምቹ ባልሆኑ ማጎሪያ ቤቶች ዘግተው የአካልም የመንፈስም የሰብአዊ መብት ጥሰት ሲፈፀምባቸው ቆይቷል::
አዲስ ዘመን፡- ከለውጡ ወዲህ ያለው የማረሚያ ቤቶች ሁኔታ እና የታራሚዎች አያያዝ ምን ይመስላል ?
ኮሚሽነር ጀኔራል የኑስ፡- ከሀገራዊ ለውጡ ማግሥት በፍጥነት መሠረታዊ የሆነ ሪፎርም ከተካሄደባቸው የፌደራል የፍትህ ዘርፍ ተቋማት መካከል ማረሚያ ቤቶች ግንባር ቀደም ሲሆኑ በዚህም መሠረት ተግባራዊ በመደረግ ላይ ያለው ተቋማዊ ሪፎርም ላለፉት ስድስት ተከታታይ ዓመታት ተግባራዊ ሲደረግ ቆይቷል:: የሪፎርም ዕቅዱ ካስቀመጣቸው የትኩረት መስኮች መካከል በሰብኣዊ መብት አያያዝና በሌሎችም በተወሰኑ የትኩረት መስኮች መልካም ውጤት ማስመዝገብ የተቻለ ሲሆን፣ በአሁኑ ሰዓት ማረሚያ ቤቶች በሚገኙ ዜጎች ሲከሰሱ የነበሩ ማረሚያ ቤቶች የሰብአዊ መብት ጥሰት የማይከሰሱበት ደረጃ ላይ ደርሷዋል::
መንግሥት የማረሚያ ቤቶችን በር ክፍት በማድረጉና ለማረሚያ ቤቶች ትኩረት በመስጠቱ በአንዳንድ የክልል የማረሚያ ቤቶች አዋጅና ደንቦች ማሻሻያ ተደርጓል:: የታራሚዎችን ቀልብ በማሻሻል፤ የተለያዩ የመንግሥትና የሕብረተሰብ ክፍሎች ማረሚያ ቤቶችን በመጎብኘትና የሎጀስቲክስ ድጋፍ በማድረግ፤ ለታራሚዎች የሞራል ድጋፍ በማድረግ፤ ሃይማኖታዊ አስተምህሮ በመስጠት ታራሚዎች ከፈጣሪ ጋር እንዲገናኙ የማረጋጋት ሥራዎች በመሥራት የታራሚዎች ሰብአዊ መብት አያያዝ እንዲሻሻል እና የማረሚያ ቤቶች ሁኔታ እንዲለወጥ ማድረግ ተችሏል::
አዲስ ዘመን፡- በማረሚያ ቤቶች በሰብአዊ መብት መጠበቅ አንጻር የታራሚዎች አያያዝ እንዴት ይታያል ?
ኮሚሽነር ጀኔራል የኑስ፡- ሰዎች ሲታሰሩ በነጻነት የመንቀሳቀስ መብታቸውና አንዳንድ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ መብቶቻቸው ከመገደቡ ውጪ ሰብአዊ ክብራቸውና ሌሎች መብቶቻቸው የሕግ ጥበቃ እንዳላቸው በሚገባ ተገንዝበን በማረሚያ ቤቶቻችን የሚከናወኑ የጤና፤ የተሃድሶ ሥራዎች፣ የታራሚዎችን የሥራ ባሕል የሚያሳድጉ ኢንዱስትሪ ሥራዎች፤ አምራችና ሕግ አክባሪ ዜጋ እንዲሆኑ የሚያስችሉ የቀለም ትምህርት የሙያ ስልጠና እንዲያገኙ ሌት ከቀን ጥረት ማድረግ ይጠበቅብናል:: ምንም እንኳ ጥፋተኛ ቢሆኑ በእውቀታቸውና በገንዘባቸው ማረሚያ ቤቶችን የሚያግዙና የሚደግፉ ብዙ ጥሩ ሰዎች በማረሚያ ቤቶች እንዳሉም መዘንጋት የለበትም::
በመሆኑም በሁሉም ደረጃ የምንገኝ የማረሚያ ቤት አመራሮችና መላ ሠራተኞች ከታራሚዎች ጋር ቀጣይነት ያለው ግንኙነትና የሃሳብ ልውውጥ በማድግ ፍርሃትንና ግጭትን በማስወገድ፤ በመረጃ ላይ የተመሰረተ ከስሜታዊነት የጸዳ ብልህነት የተሞላበት ፈጣንና ፍትሃዊ ውሳኔዎችን በመወሰን፤ ታማኝነትና ጥሩ ሥነምግባር በመላበስ የሰብአዊ መብቶችን በማክበር ሞዴል በመሆን፤ የቡድን ሥራን በማጠናከር እንዲሁም በመከባበር ውጤታማ የማረም ማነፅና የመልሶ ማቀላቀል ሥራ መሥራት ይጠበቅብናል::
ከነዚህ መርሆች ባፈነገጠ አኳኋን የታራሚን ሰብአዊ መብትና ክብርን መግፈፍ፤ ከታራሚ ጋር አላስፈላጊ የጥቅም ትስስር በመፍጠር የተከለከሉ ነገሮችን ወደ ማረሚያ ቤቶች ማስገባት፤ በብሄርና በሃይማኖት እርስ በርስ እንዲሁም ከታራሚ ጋር በመደራጀት መንቀሳቀስ፤ ከሙያ ዲሲፕሊን ባፈነገጠ መንገድ አንድን የፖለቲካ ቡድን በመደገፍ መንቀሳቀስ፤ እንዲሁም ሌብነትና ሙስና የማረሚያ ቤቶች ቀይ መስመር በመሆናቸው ከነዚህን ድርጊቶች በሚፈፅም በየኛውም ደረጃ ላይ በሚገኝ አመራርም ሆነ አባል ኮሚሽኑ የማይታገስ መሆኑን መግለፅ እወዳለሁ::
አዲስ ዘመን፡- ታራሚዎች በማረሚያ ቤት በሚኖራቸው ቆይታ በሁለንተናቸው በትክክል ታርመው እንዲወጡ ለማድረግ ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር በትብብር በመሥራት ረገድ ምን አይነት ጥረቶችን ታደርጋላችሁ ?
ኮሚሽነር ጀኔራል የኑስ፡- ማረሚያ ቤቶችን የማረም ማነፅ ሥራ በመደገፍ በኩል ሕብረተሰቡና የተለያዩ ሀገር በቀልና ዓለም አቀፍ ተቋማት የማይናቅ አስዋፅኦ እያደረጉልን ይገኛሉ:: በቅርቡ ባካሄድነው 19ኛው የፌደራልና የክልል ማረሚያ ቤት የኮሚሽነሮች ጉባዔ “ማረሚያ ቤቶችን በአዲስ አስተሳሰብ ወደ አዲስ ምዕራፍ!” በሚል መሪ መልዕክት ላይ ተመስርተን የተለያዩ ባለድርሻ አካላት ከጎናችን እንዲቆሙ ጥሪ አቅርበናል::
የፌደራልም ሆነ የክልል ማረሚያ ቤቶች ባላቸው አነስተኛ በጀትና የሰው ኃይል የተሰጣቸውን ተልዕኮ በመፈፀም ላይ ቢሆኑም የተሟላ የማረም ማነፅና የልማት ሥራዎችን ለመሥራት የማኅበረሰብ ተሳትፎ የማይተካ ሚና አለው:: የማኅበረስብ ተሳትፎ ሚና የተሻሻለ ተሀድሶና ማረም ማነፅ ታራሚዎች ክህሎትን እና አወንታዊ ባህሪን እንዲያዳብሩ ለማድረግ ያግዛል:: የትምህርት ፕሮግራሞችን፣ የሙያ ሥልጠናዎችን እና የምክር አገልግሎቶችን በመስጠት የተሳካ የመልሶ መቀላቀል እድላቸውን በመጨመር ረገድ የተለያዩ አካላት ተሳትፎ እጅግ አስፈላጊ ነው::
ታራሚዎች ወደ ማኅበረሰቡ ሲቀላቀሉ የማኅበረሰብ ድርጅቶች የቀድሞ ታራሚዎች ማኅበራዊ ድጋፍ እንዲያገኙና እንደገና ወንጀል የመስራትን አደጋን ለመቀነስ፤ ተጎጂዎችን እና ወንጀል ፈጻሚ አካላትን በውይይት መርሃ ግብሮች ውስጥ ማሳተፍ ወንጀለኞችን እና ማኅበረሰቡን በማስታረቅ ከረጅም ጊዜ እስራት ይልቅ በተመጣጣኝ ዋጋ እርቅ በመፈጸም በማረሚያ ቤቶች ላይ ያለውን ጫና ይቀንሳሉ::
የማኅበረሰብ ቁጥጥር እና ተሳትፎ የበለጠ ግልፅነትን በማረጋገጥ በታራሚዎች ላይ በማረሚያ ቤቶች ውስጥ የሚደርስባቸውን ጥቃት፣ አድልዎ ወይም ቸልተኝነትን በመቀነስ፤ ታራሚዎች ወደ ማኅበረሰቡ ሲቀላቀሉ የሚገጥማቸውን የተዛባ አመለካከትና የመገለል ስጋት በማስቀረት ወሳኝ ሚና ይጫወታሉ:: በሌላ በኩል ደግሞ የእምነት ተቋማት፤ መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች በጎ ፈቃደኛ ባለሙያዎች የማረሚያ ቤት አስተዳደርና ሠራተኞች የሚጎድሏቸውን ሃብትና ክህሎት በማምጣት ቁልፍ አስተዋጽኦ ያደርጋሉ::
አዲስ ዘመን፡- በቅርቡ በተካሄደ አንድ መድረክ ላይ የታራሚዎች መልሶ መቀላቀል ሥራ ረቂቅ አዋጅ በዝርዝር ቀርቧል:: አዋጁን እንዴት ተመለከቱት ?
ኮሚሽነር ጀኔራል የኑስ፡- የታራሚዎች መልሶ መቀላቀል ሥራን እንደ ሀገር ውጤታማ በሆነ አሠራር መምራት የሚያስችለው ረቂቅ አዋጅ መዘጋጀቱ ባለድርሻ ተቋማቱ ተልዕኳቸውን የበለጠ ውጤታማ እንዲሆን ዕድል የሚሰጥ ነው:: በእኛ በኩል የታራሚዎች መልሶ
መቀላቀል ሥራ ከስንት ዓመት በላይ ፍርደኛ የሆኑ ታራሚዎች ላይ ቢሠራ ውጤታማ ሊሆን እንደሚችል የጋራ መግባባት ተፈጥሮ፣ የባለድርሻ አካላትም ኃላፊነት በአዋጁ ላይ በዝርዝር መቀመጥ እንዳለበት ጠቁመናል፡ በረቂቅ አዋጁ ዙርያ የተሰጡ ግብዓቶች ተካትተውበት በአጭር ጊዜ ውስጥ ለሁሉም ክልሎች ተልኮ ግብረመልስ ከተሰበሰበበት በኋላ የመጨረሻው ረቂቅ እንደሚዘጋጅ ስምምነት ላይ ተደርሷል::
አዲስ ዘመን፡- የፌዴራልና የክልል ማረሚ ቤቶች የእርስ በርስ የልምድ ልውውጥ የሚያድርጉበት የግንኙነት መድረክ አላቸው ?
ኮሚሽነር ጀኔራል የኑስ፡- የፌዴራል ማረሚያ ቤት ኮሚሽን ከክልሎች ጋር በየግማሽ ዓመቱ በሚዘጋጁ ጉባዔዎች እና በየጊዜው በሚፈጠሩ መድረኮች ተቀራርበን በመሥራት እርስ በርስ የልምድ ልውውጥን በማዳበር መንግስት ባስቀመጠው የአንድ ዕቅድ አንድ ሪፖርት የአሰራር አቅጣጫ መሰረት በፌዴራልና በክልል ማረሚያ ቤቶች መካከል ተቀራራቢ አሠራር ለመፍጠር ጥረት በማድረግ ማረሚያ ቤቶች ሀገራዊ ፋይዳ ያለው ሥራ ማከናወን እንዲችሉ የተጠናከረ ቅንጅታዊ አሠራር ላይ ተመስርተን በመሥራት ምርጥ ተሞክሮዎችን በመቀመር አንዱ ከሌላው የሚማማሩበት መድረክ በመፍጠር ለተግባራዊነቱ እየተጋን እንገኛለን::
አዲስ ዘመን፡- ቴክኖሎጂን በመጠቀም አሠራርን ለማዘመን በማረሚያ ቤቶች አካባቢ የሚደረጉ እንቅስቃሴዎች አሉ ?
ኮሚሽነር ጀኔራል የኑስ፡- ቴክኖሎጂ በደህንነት፣ በተሃድሶ፤ የአስተዳደርና ማኅበራዊ አገልግሎት አስጣጥን በማዘመን ረገድ እየተጫወተ ያለው ሚና ከፍተኛ እንደሆነ ይታወቃል። በዚህ ረገድ ማረሚያ ቤቶቻችን ከሌሎች ሀገራት ማረሚያ ቤቶች ጋር ሲነጻጸሩ ገና በጅምር ላይ ያሉ በሚፈለገው ደረጃ ላይ ያልደረሱ በብዙ መልኩ የደህንነት ስጋት ላይ የሚገኙ ናቸው::
በማረሚያ ቤቶች የቴክኖሎጂ አስፈላጊነት የሕግ ታራሚዎችን ባዮሜትሪክ ዳታ በመያዝ፤ የኤሌክትሮኒክስ መከታተያና መለያ መሳሪያዎችን በመጠቀም የታራሚዎችን የማምለጥና የደህንነት አደጋ የማድረስ ሁኔታዎችን ለማስቀረት፤ በሌላ በኩል የማረሚያ ቤት ሰራተኞች በታራሚዎች ላይ ሊያደርሱባቸው የሚችሉትን ሰብአዊ ጥቃቶች በመከላከል፤ ማረሚያ ቤቶችን ዲጂታላይዝ በማድረግ እና አውቶሜትድ ሲስተሞች በመጠቀም የታራሚዎችን የፍትህ አስተዳደር ለማሻሻል፤ የሀብት አያያዝንና ብክነትን ለማሻሳል፤ በሰዎች የሚፈጸሙ ስህተቶችን በመቀነስና የማረሚያ ቤቶችን አስተዳደራዊ ሸክሞችን በመቀነስ፤ ደህንነቱ የተጠበቀ የቪዲዮና የድምፅ እና የኤሌክትሮኒክስ የመልእክት መላላኪያ ግንኙነቶችን ለማድረግ፤ በኢ-ለርኒግ ታራሚዎች የትምህርት እና የሙያ ስልጠና እንዲከታተሉ በማድረግ ክህሎታቸውን እና የሥራ እድል በማስፋት፤ በቴሌሜዲሲን የርቀት ጤና አጠባበቅ ታራሚዎች ከእስር ቤት ሳይወጡ ከሐኪሞች ጋር እንዲማክሩ በማስቻል ረገድ ወሳኝ ነው::
በተጨማሪም የደህነነት ስጋትን በመቀነስና ወጪን መቆጠብ በማስቻሉ እና የማረሚያ ቤት ኃላፊዎች በማረሚያ ቤቶች ሊከሰቱ የሚችሉ የደህንነት ስጋቶችን በመቆጣጠር፤ የአመፅ አዝማሚያ መረጃዎችን በመሰብሰብ፤ በመተንተንና በመተንበይ ፈጣን ውሳኔዎችን እንዲወሰኑ ይረዳቸዋል:: በመሆኑም በአሁኑ ወቅት ቴክኖሎጂ ምርጫ ሳይሆን ግዴታ የሆነበት ደረጃ ላይ የደረስን በመሆኑ በዚህ ዘርፋ ማረሚያ ቤቶች በፍጥነት ወቅቱን የዋጁ የቴክኖሎጂ መሰረተልማቶች ሊሟሉላቸው እንደሚገባ ለፌደራልም ለክልልም የሚመለከታቸው አካላት ጥያቄ እያቀረብን ነው::
አዲስ ዘመን፡- የመገናኛ ብዙሃን ኮሚሽኑ የሚሠራቸውን ሥራዎች በማገዝ ረገድ የሚኖራቸውን ሚና እንዴት ይገልጹታል ?
ኮሚሽነር ጀኔራል የኑስ፡- የመገናኛ ብዙሃን ማረሚያ ቤቶችንና ማኅበረሰቡን በማገናኘት በኩል የሚጫወቱት ሚና የጎላ ነው:: በማረሚያ ቤቶች የሚፈጸሙ ብልሹ አሠራሮችን በማጋለጥ ግልፅነትና ተጠያቂነት እንዲኖር በማድረግ፤ ዘጋቢ ፊልሞችን፤ የዜና ዘገባዎችን እንዲሁም መጣጥፎችን በማቅረብ የማረሚያ ቤቶችን እውነታ በማሳየት ማኅበረሰቡን ያስተምራሉ:: በዚህም አሉታዊ አመለካከቶችን በመለወጥ፤ የታረሙና የታነጹ ታራሚዎችን ስኬት በማቅረብ ተሃድሶና መልሶ መቀላቀልን በመደገፍ፤ ማኅበረሰቡ፤ ሲቪል ማኅበራት ድርጅቶችንና ፖሊሲ አውጪዎችን ከማረሚያ ቤቶች ጋር በተያያዙ ጉዳዮች በማሳተፍ የተሃድሶ ፕሮግራሞችን እንዲደግፉ በማበረታታት ትልቅ እገዛ ያደርጋሉ:: በተጨማሪም በማረሚያ ቤት የሚገኙ ዜጎች ስለመብቶችና ግዴታዎቻቸው፤ የማረሚያ ቤት ደንቦችና መመሪያዎች እንዲያውቁና የሕግ ግንዛቤ ኖሯቸው ከማረሚያ ሲወጡ የተሳካ ሂወት እንዲመሩ የሚጫወቱት ሚና ከፍተኛ ሆኖ እናገኘዋለን::
ማረሚያ ቤቶች እንደሌሎች ሴክተር መስሪያ ቤቶች የዘገባ ሽፋን አግኝተው ለማረምና ማናጽ እንዲሁም ወደ ሕብረተሰቡ መልሶ ለመቀላቀል በሚደረገው ጥረትና ሕብረተሰቡ ስለማረሚያ ቤቶች አስፈላጊው መረጃ ኖሮት ለታራሚዎች አስፈላጊውን ድጋፍ እንዲያደርግ መረጃ በማቀበል ሚዲያዎች ማኅበራ ግዴታቸውን መወጣት ይኖርባቸዋል ብለን እናምናለን::
አዲስ ዘመን፡- እየተጠናቀቀ ባለው የ2017 ዓ.ም. በጀት ዓመት የኮሚሽኑ ዕቅድ አፈጻጸም ምን ደረጃ ላይ ይገኛል ?
ኮሚሽነር ጀኔራል የኑስ፡- 2017 በጀት ዓመት በዋነኝነት ተንከባለው የመጡ የአሠራር ክፍቶች፥ የሥራ አፈጻጸም ድክመቶች፥ የዲስፕሊንና የሥነ-ምግባር ጉድለቶችን እና ተያያዥ ችግሮችን መልክ ለማስያዝ ሰፊ የሆነ የአመራርና የፈጻሚዎች ግምገማና የማጥራት ውጤታማ ሥራዎች የሠራንበት ነው:: ከማጥራት ቀጥሎም የበርካታ መንግሥታዊ ተቋማት አመራሮችና ባለሙያዎች ጭምር በማሳተፍ መጠነ ሰፊ የሆኑ የስልጠናና አቅም ግንባታ ሥራዎች በስፋት ሰጥተናል:: የማረሚያ ቤቶች ተልዕኮ አፈጻጸምን በዘመናዊ ቴክኖሎጂ ለመደገፍ እንዲቻል የአርተፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት፥ ኢንሳና ከመሳሰሉ የሀገራችን የቴክኖሎጂ ተቋማት ጋር በመቀራረብና ስምምነቶችን በመፈራረም ትላልቅ ቴክኖሎጂ ተኮር ሥራዎች የተጀመሩበት የበጀት ዓመት ነው:: በአጠቃላይ ለቀጣዮቹ ስድስት ዓመታት ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ አፈጻጸም ምቹ ሁኔታን የሚፈጥር መደላደል የተፈጠረበት በጀት ዓመት ተደርጎ ሊወሰድ የሚችል ነው።
በማረሚያ ቤቶቻችን የተመዘገቡ ውጤቶች እንደተጠበቁ ሆነው በማረሚያ ቤቶች ሊሠሩ የሚገቡ መጠነ ሰፊ ሥራዎች ተሠርተው ተጠናቀዋል ወይም ማረሚያ ቤቶች መሆን ከሚገባቸው ደረጃ ላይ ደርሰዋል ማለት ግን አይደለም:: በቀጣይ ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር እንዲሁም ከከፍተኛ የፌደራልና የክልል አመራሮች ጋር በመቀናጀት የምንሠራቸው ብዙ የጋራ ጥረትና መደጋገፍ የሚጠይቁ ተግዳሮቶች አሉብን።
አዲስ ዘመን፡- ኮሚሽኑ በሚያስበው ልክ ነገሮችን ማስኬድ እንዳይችል ተግዳሮት የሆኑበት ጉዳዮች ምንድን ናቸው ?
ኮሚሽነር ጀኔራል የኑስ፡- ተቋማዊ ሪፎርሙ በሚፈለገው ልክና በተሟላ መልኩ ተግባራዊ እንዳይሆንና የተፈለገውን ያህል ውጤት ላለማምጣቱ ምክንያት ከሆኑት መካከል ከፍተኛ የሆነ የዲስፕሊንና የሥነምግባር ችግር በአባላት አሁንም ያለ መሆኑ፤ በዓለም አቀፍ እና ሀገራዊ ወቅታዊ ሁኔታዎች ከፍተኛ ዋጋ ጭማሪ ምክንያት በተፈቀደው በጀት የእስረኞች የመሰረታዊ ፍላጎት አቅርቦት ዋጋ ንረት፣ በፕሮጀክት ግብዓት አቅርቦት እና በሌሎች ግብዓት ዋጋ መጨመር በአገልግሎት አሰጣጥ ላይ ከፍተኛ የበጀት ዕጥረት እና በእቅድ አፈፃፀም ላይ ጫና መፍጠሩ፣ ቀላል የማይባል የአመራር ክፍተት መኖሩ በዘመናዊ ቴክኖሎጂ አጠቃቀም ወደ ኋላ የቀረን መሆናችን እና የተጀመሩ የግንባታ ፕሮጀክቶች በከፍተኛ ሁኔታ የተጓተቱ መሆናቸው የሪፎርሙን ዓላማ ለማሳካት ተግዳሮት ሆነው ይገኛሉ::
አዲስ ዘመን፡- በቅርቡ ያካሄዳችሁት ጉባዔ መሪ መልዕክት የሆነው “ማረሚያ ቤቶችን በአዲስ አስተሳሰብ ወደ አዲስ ምዕራፍ ለማሸጋገር እንተጋለን” ምንን የሚያመላክት ነው ?
ኮሚሽነር ጀኔራል የኑስ፡- ይዘናቸው የመጣናቸውን የተሳሳቱ አመለካከቶች እና ደካማ የሥራ ባሕል በማስተካከል አዳዲስ ፈጠራ በማከል የተጀመሩ መልካምና በጎ ሥራዎችን በማጠናከር በአስተሳሰብም በተግባርም የተለወጡና ያደጉ ማረሚያ ቤቶችን ሰላማዊ የተሃድሶ ተቋማት በማድረግ ለመጪው ትውልድ ለማስተላለፍ ያለመ ነው:: ስለ ሕግ ታራሚዎች የሰብዓዊ መብት አያያዝ፣ የመሰረታዊ ፍላጎት አቅርቦት እና የማረም ማነፅ ተሃድሶ ልማት አገልግሎት አሰጣጦች እንዲሁም እየተከናወኑ ስላሉ የማረሚያ ቤቶች የሪፎርም ሥራዎች፣ ተወያይተን የጋራ መግባባት ላይ በመድረስ በአዲሰ የለውጥ አስተሳሰብና የአጋርነት መንፈስ የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ ቃል በመግባት መሆን ይገባዋል ከሚል የሚነሳ ነው።
አዲስ ዘመን፡- በቅርቡ በሞሮኮ ራባት በተካሄደው የአፍሪካ ማረሚያ ቤቶች ማኅበር ኮንፈረንስ ላይ የነበርዎ ተሳትፎ ምን ይመስል ነበር?
ኮሚሽነር ጀኔራል የኑስ፡- ኮንፈረንሱ የቴካሄደው የአፍሪካ ማረሚያ ቤቶችን በዘመናዊ ቴክኖሎጂ ማስተዳደር በሚል መሪ ሀሳብ ነው:: በኮንፈረንሱ ላይ የኢትዮጵያ ልዑክ በመምራት ተሳትፌያለሁ:: የኮንፈረንሱ አንዱ ዓላማ ማረሚያ ቤቶቻችን በዘመናዊ ቴክኖሎጂ በማስታጠቅና አሠራራሮችን በማዘመን አውቶሞቲ በማድረግ ፈጣንና ቀልጣፋ አገልግሎት መስጠት ይገባናል የሚል ነው:: በእኛ በኩል ይህንኑ መሰረታዊ ጉዳይ በሚደግፍ መልኩ በኮሚሽኑ የትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ውስጥ ማረሚያ ቤቶቻችን በዘመናዊ ቴክኖሎጂ በማዘመን አገልግሎት አሰጣጡን ቀልጣፋ ለማድረግ በስፋት እየተሠራ ነው::
የማረሚያ ቤቶች የግብርና ሥራ ከኋላ ቀር አሠራር ተላቆ ወደ ዘመናዊ አሠራር መግባት አለበት የሚለው ሌላው የኮንፈረንሱ ዓላማ ነው:: የሜካናይዜሽን እርሻ በመሥራት የታራሚዎችን የምግብ ዋስትና ከማረጋገጣቸው በላይ የሀገራቸውን ገበያ ለማረጋጋት ከፍተኛ ሚና እየተጫወቱ መሆኑን ልምድ ካካፈሉ ሀገራት መረዳት ችለናል:: የፌዴራል ማረሚያ ቤት ኮሚሽን የግብርና ሥራን በትራክተር ደረጃ እያካሄደ ነው:: የእህል መዝሪያ፣ የመሰብሰቢያና የመውቂያ ማሽነሪዎች ላይ ግን ገና ብዙ ሥራ ይጠይቀናል:: ይህን ልምድ እንደ አንድ ግብዓት በመውሰድ ከታራሚዎች አልፎ ለገበያ ለማቅረብ ምን ዕድል አለን የሚለውን ለማየት ኮንፈረንሱ አግዞናል::
የማኅበሩ እንቅስቃሴ ማጠንጠኛው የሕግ ታራሚዎች እንደ ሌሎች የማኅበረሰብ ክፍሎች መሠረታዊ የሆኑ አገልግሎቶች የማግኘት መብት አላቸው:: የተገደበው አካላዊ እንቅስቃሴያቸው እንጂ ሰብአዊ መብታቸው አይደለም:: የፍርድ ውሳኔያውን አጠናቀው ወደ ማኅበረሰቡ ሲመለሱ መልካም ሥነ ምግባር እንዲኖራቸው ማረሚያ ቤቶች የሚጫወቱት ሚና ከፍተኛ በመሆኑ ትኩረት ይሰጣቸው የሚል ነው:: በብዙዎቹ ሀገራት እንደ ችግር የተነሳው ለማረሚያ ቤቶች በመንግሥታት የሚሰጠው ትኩረት አነስተኛ ነው የሚል ነው::
አዲስ ዘመን፡- ለነበረን ቆይታ በዝግጅት ክፍሉ ስም አመሰግናለሁ!
ኮሚሽነር ጀኔራል የኑስ፡- እኔም አመሰግናለሁ!
ተስፋ ፈሩ
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ግንቦት 30 ቀን 2017 ዓ.ም