የምስለ ባሩድ ወግ፤
ደጋግመን ከምንሰማቸውና ውስጣችንን እያወኩ ጤና ከሚነሱን “መንግሥታዊ ዜናዎች” መካከል በቀዳሚነት የሚጠቀሰው፤ “ይህንን ያህል የጦር መሣሪያ በሕገ ወጥ መንገድ ሲዘዋወር በቁጥጥር ሥር ዋለ” የሚለው ቀዳሚውን ሥፍራ ይይዛል። “በባሩድ” የመስለነውም ይህንን አሳሳቢ ወቅታዊ ጉዳይ ነው። ለሕዝብ የሚደርሰውን እንዲህ አይነቱን መረጃ “ዜና” ብሎ ከመጥራት ይልቅ “መርዶ” ማለቱ ይቀላል። “ለምን ቢሉ?” በቁጥጥር ሥር በዋሉት የጦር መሣሪያዎች አማካይነት አዘዋዋሪዎቹ ሴረኞች የተመኙት ድርጊት ባይፈጸም እንኳን የመጓጓዙ ዓላማ የብዙዎችን ነፍስ ለመንጠቅ ታቅዶ ስለሆነ “እሳት ካየው ምን ለየው!” ነውና “መርዶ” ቢሰማኝ አያስከፋም።
“በሕገ ወጥ መንገድ ሲዘዋወር” የሚለው የተለምዶ አገላለጽም “ሕጋዊ የጅምላ የጦር መሣሪያ ዝውውርስ አሁን እያስተዋልን ባለው መልኩ ይፈቀዳልን?” ብለን እንድንጠይቅ እንገደዳለን። ከሕጋዊ የጸጥታ ተቋማት አሠራር ጋር ለመለየት ታስቦ ከሆነም ይህ ጉዳይ ለሚመለከታቸው ተቋማት ኃላፊነታቸው ብቻም ሳይሆን የተሰጣቸው መብትም ጭምር ስለሆነ በማነጻጸሪያነት መቅረቡ “አግባብ ይሆንን?” ብለን ደግመን እንሞግታለን።
የትውፊታችን መዘዝ፤
የ “ሕገ ወጥ የጦር መሣሪያ ዝውውሩን” የዜና አቀራረብ በተመለከተ በበርካታ ጉዳዮች ግራ ሲያጋቡን ለሚውሉት ለሀገራችን ሚዲያዎች እና “ዜናውን አስተላልፉልኝ” በማለት መልዕክቱን ለሚልከው ክፍል እንተወውና ወደ ዋናው ጉዳያችን እንመለስ። የሀገር ወግ ናቸው ብለን በእለት ተእልት ኑሯችን እንኮኮ እያልን ተሸክመንና በስሜታችን ጀርባ ላይ አዝለን እንደ በኩር ልጅ እሶሶ የምንላቸው የአንዳንድ ነባር ባህሎቻችን ጉዳይ እንዲህ በዋዛ የሚታረም ስላልሆነ ከዋናው ርእሳችን እንዳያርቀን በመስጋት ከመነሻ ርእሳችን ጋር የሚጎዳኘውን አንዱን ጉዳይ ብቻ ነጥለን እናስታውሳለን።
እንደ መርግ ተሸክመን ካጎበጡንና አልላቀቅ ብለው ከተጣቡን አንዳንድ የባህላዊ ትውፊቶቻችን መካከል በተለይም ከጦር መሣሪያ ጋር የተቆራኘንበት ፍቅር ወደር ያለው አይመስልም። ከገጠር እስከ ከተማ በመሣሪያ “ቃንዛ” (ጥዝጣዜ፣ ሕመም) ያልተለከፈ ዜጋ ይኖራል ብሎ ለማሰብ እስከሚያዳግት ድረስ “አፍቃሬ መሣሪያ” ሆኖ መታየት የብዙዎች መለያ ነው።
“ገዳይ እወዳለሁ፣ ተኳሽም አልጠላ
ሲደክመኝ አርፋለሁ፣ በጎፈሬው ጥላ። ”
እየተባለ እስክስታ በሚወረድበት ሀገር እየኖርን ስለ “ሕገ ወጥ የጦር መሣሪያ ዝውውር” እና ስለ አፍቅሮተ መሣሪያ ምርር ብለን ብንተች ጅራፉ መልሶ የሚያንባርቀው በራሳችን ብዕር ላይ እንደሚሆን አይጠፋንም። “ና ደሞ ገዳይ! ገዳይ ደሞ!” እየተባለ በሰርክ የዘፈን ግጥም “ገዳይነት” በሚሞገስበት ሀገር እየኖርን “ሞት ቢረክስብን” ምን ያስደንቃል? እኛው በፈጠርነው ጉዳይ ፈጣሪን ማስቸገር አይገባም ካልተባለ በስተቀር አንዱ ፈውስ ፈላጊ ሕመምተኛው የባህላችን ክፍል ኪነጥበቡ ስለሆነ እግረ መንገዳችንን “ፈጣሪ እንዲፈውስልን” ተማጥኖ አኑረን ብናልፍ አይከፋም።
የጥንቶቹ ምንሽርና ዲሞትፎር ሳይቀሩ ዘመነ ሥልጣኔ በእርጅና ምክንያት ከውድድር ውጭ ካደረጋቸው በኋላና በተፈበረኩበት ሀገርም ሳይቀር ባይተዋር እስከ መሆን ደርሰው እያለ በእኛ ቀኤ ግን “እሹሩሩ” እየተባሉ በዜማ መሞገሳቸወ አልቀረም። በእነዚህ ምክንያቶች የተነሳም በባሩድ ጭስ መታጠንን አጥብቀን ስንኮንንም የምናገኘው ምላሽ “ሥራችሁ ያውጣችሁ” እንዳይሆን ሥጋት ገብቶናል።
ለጉድ በጎለታቸው አንዳንድ መንግሥታዊ ሚዲያዎች ሳይቀር “ገዳይ ደሞ” በሚል የዜማ አዝማች ተለብጦ አንድ የሕጻናት ወተት ማስታወቂያ በይፋ ደጋግሞ ሲተላለፍ እንደነበር አንዘነጋም። ቆሽታችን ደበነ አልደበነ ማን ግድ ሰጥቶት? ማስታወቂያው ዛሬም ድረስ እየተላለፈ ከሆነ በርግጥም እንደ ሀገር ለመደንቆራችን ጥሩ ማሳያ ሊሆን ይችላል።
በየቤታችን ያሉትን ሕጻናት የምናሳድግበት ወተት “በገዳይ ደሞ” ማስታወቂያ መድመቁ እንደተጠበቀ ሆኖ ለልጆቻችን ልደት ወይም ለፍቅራችን መግለጫነት በስጦታ የምናበረክትላቸው መጫዎቻዎች ሳይቀሩ አርቴፊሻል ሽጉጦችና የዘመናዊ ጦር መሣሪያ አምሳያዎች መሆናቸውን በትዝብት የምናልፈው “ቤቱ ይቁጠረው” በማለት ነው።
ዛሬ በአርቴፊሻል የጦር መሣሪያ ስጦታ በደስታ የምናስፈነድቃቸው ልጆቻችን ነግ ተነገ ወዲያ ነፍስ ሲያውቁ በምሩ የጦር መሣሪያ ፍቅር ወድቀው ለመራር ለቅሶ ምክንያት ቢሆኑን ልንፈርድባቸው እንዴት ይቻላል? ልብ ቢኖረን ከሕገ ወጥ የጦር መሣሪያ ጋር ተያይዞ በአሜሪካ ትምህርት ቤቶች የሚፈጸመው የንጹሐን ተማሪዎች የእልቂት ትራዤዲ ትምህርት በሆነን ነበር። ከግል ገመና ወደ ሀገር ጓዳ፤
ምልከታችንን ሰብሰብ እናድርግና “በባሩድ ጭስ” በመሰልነው የጊዜያችን ፈተና ጥቂት እንቆዝም። ሚዲያዎቻችንን ያጨናነቀው “የሕገ ወጥ” የጦር መሣሪያ ዝውውር “መርዶ” ለምን ሊበራከት እንደቻለ ጥናትን መሠረት አድርጎ በሚመለከተው ክፍል በኩል ሊደርሰን የሚገባው መረጃ ሩቅ ስለሆነብን እኛ የምንሰጠው መላምት “የቢቸግር መልስ” መሆኑን ልብ ይሏል።
ምክንያት አንድ፤ ተደጋግሞ እንደሚገለጽልን “በሕገ ወጥ” መንገድ የጦር መሣሪያዎችን የሚያጓጉዙት የሽብር ተልዕኮ የተጠናወታቸው የሰላም ፀር ተላላኪዎች ናቸው።
ምክንያት ሁለት፤ በሰላም ወጥቶ መግባት ያሳሰባቸው ዜጎች ለነፍሳቸውና ለንብረታቸው ሲሉ የጦር መሣሪያ አጥብቀው ስለሚፈልጉ ነው። ምክንያት ሦስት፤ ህሊናቸውን ለከንቱነት ያስገበሩ፣ ከሆዳቸው ውጭ የማያስቡና ጊዜያዊ ሀብት አጋብሶ በአቋራጭ ለመክበር የሚፈልጉ ዜጎች መበራከት ለጦር መሣሪያ ዝውውሩ እንደ ምክንያትነት ሊጠቀስ ይችላል። እነዚህ ሦስት መላምቶች በጥናት የተደገፉ ሳይሆኑ በይሆናል ግምት የተሰነዙሩ መሆናቸው ይሰመርበት።
ለማንኛውም በሀገሪቱ ውስጥ በፈጣን ዝውውር ላይ ያለው የጦር መሣሪያ ብዛትና ዓይነት እንኳንስ እኛን ተራ ዜጎች ቀርቶ ጉዳዩ ጉዳዬ ነው የሚሉ ተጠሪ መንግሥታዊ ተቋማትን ሳይቀር በእጅጉ እንደሚያሳስብ አይጠፋንም። በየጊዜው የምንሰማው “በሕገ ወጥ የሚዘዋወሩ” የጦር መሣሪያዎች ዓይነትና ብዛት በዜጎች ላይ ሊያሳድር የሚችለው ሥነ ልቦናዊ ተጽእኖ ቀላል እንደማይሆንም መገንዘብ አይገድም። ሽጉጦች፣ ክላሽንኮቭና የስናይፐር ጠብመንጃዎች፣ መትረየሶች፣ ብሬኖችና እነዚህ መሣሪያዎች የሚጎርሷቸው ጥይቶች፣ ቦንቦች ወዘተ. በመቶዎችና በሺህዎች (በተለይም ጥይቶቹ በሚሊዮን) ሲቆጠሩ ማየት ምን ዓይነት አሉታዊ ስሜት ሊፈጥር እንደሚችል መገመቱ አይከብድም።
በዚህ አስጨናቂና ክፉ ክስተቶች ቀለባችን ሆነው ኑሮው አቅል ባሳጣን፣ ፖለቲካውም ጨቅይቶ ድጥና ማጡ ስጋት ላይ በጣለን ወቅት፣ ማሕበራዊ ሚዲያውም ከጥቅሙ ይልቅ ጥፋቱ አይሎ “በአሉ ተባባሉ” ዐውሎ ነፋስ እየተነዳን ባለበት “ዘመነ ግርምቢጥ (ሀሰት የበዛበት)”፣ የሃይማኖት ክብር ተቃሎ “እግዚኦታችን ፀባኦትን በሚነቀንቅበት”፣ ማሕበራዊ ተራክቦውም በጥርጥርና ባለመተማመን በተሳከረበት በዚህ ወቅት “መከራችን ያነሰ ይመስል” ይህንን መሰሉን “የጦር መሣሪያ የገፍ ዝውውር” “መርዶ” ቀን በቀን ማድመጡ “ወየው ለነገ!” አሰኝቶ ቢያሸብረን ሊፈረድብን አይገባም። ለክፋቱ ደግሞ የአዘዋዋሪዎቹ መኪኖች ታርጋ እንጂ እነማን እንደሆኑ ያለመገለጹም ሌላው አሳሳቢ ጉዳይ ነው። ጥፋቱ ተገልጦ አጥፊው መሸሸጉም ግራ ያጋባናል። ይመለከተናል ባዮቹ ክፍሎች አሳማኝ ነው የሚሉትን ምክንያት ቢያስረዱን ስሜታችን ገርገብ ሊል ይችላል።
የባሩድ ሱሰኞቹ ግብ፤
የባሩድ ሽታ ሱስ ከሌሎች ሱሶች እጅግ የከፋ ስለመሆኑ የእኛ ሀገር ተሞክሮ ለሌሎች ሀገራትም ሳይቀር በጥሩ ማሳያነት ሊጠቀስ የሚችል ይመስለናል። በረሃ ውስጥ ተወልደውና አድገው ለመከራችን ምክንያት የሆኑ “በሞት ንግድ ላይ የተሰማሩ” አሸባሪ ድርጅቶችን ታሪክ ወደ ኋላ ዞር ብለን ብንፈትሽ ያለምንም ጥርጥር መዳረሻችን የባሩድ ሱሰኛ ብቻ ሳይሆኑ ሱሱ አልለቅ ብሎ የሚያቅበዘብዛቸው በሽተኞች መሆናቸውንም ጭምር እንረዳለን።
በባሩድ ጭስ ታጥኖ ሀገር ለማፈራረስ መሞከር እብደት ተብሎ ብቻ የሚታለፍ አይደለም። ሌላ ቃል ሊገልጻቸው ስለማይችል ይህንኑ የተለምዶ ቃል እንጠቀምና እነዚህ የባሩድ ጭስ አምላኪዎች ሀገርን የውጥር ይዘው ለመከራ የዳረጓት በእውነት የሕዝብ ጥቅም ግድ ብሏቸው ነው? በፍጹም።
ከባእዳን ጠላቶቻችን ጋር በማበር ሰላማችንን እያወኩ ያሉት የሽብር ቡድኖች ሲላቸው በሰሜን፣ አልሆን ሲላቸው በምዕራብ፣ የበረቱ ሲመስላቸው በደቡብ፣ ክንፋቸው ሲሰበር በምሥራቅ የሀገሪቱ ክፍሎች እየተፈናጠሩ የሽብር ተልእኳቸውን የሚያስፈጽሙት፣ ንጹሃንን እየጨፈጨፉና ንብረት እየዘረፉ በማውደም የሚያቅራሩት በርግጡ ለሕዝብ አርነት አስበው ነው? ወይንስ በጠላቶቻችን ማማለል ተማርከው? መልሱ አጭርና ግልጽ ነው።
ሀገር በማፍረስ ያለ ሀገር መኖር የሚቻል መስሏቸው ከሆነ ጅልነት ነው። በንጹሃን ደም እጃቸውን እየተለቃለቁ መኖር እጥፍ ዋጋ እንደሚያስከፍል አልተገነዘቡት ከሆነም የእጃቸውን ሲያገኙ እውነቱን ይረዱታል። ዳሩ የሚያቅበዘብዛቸው የባሩድ ጭስ ሱስ ወደ ህሊናቸው እንዲመለሱ መች ያበረታታቸዋል።
ስለ ሰላም እንዳያስቡ ስምሪት ሰጪዎቻቸው ጠላቶቻችን ከኋላ ሆነው ጠብመንጃ ደቅነውባቸዋል። ስለዚህ ምርጫው አንድና አንድ ነው፤ በተጠመቁበት የባሩድ ጭስ እየናወዙ ማለቅ። በቅርቡ በተለያዩ የሀገራችን ክፍሎችና በሶማሌ ክልላችን ውስጥ የመከነው “የጥፋት ኦፕሬሽን” ለዚህ እውነታ ጥሩ አብነት ይሆናል።
በባሩድ ጭስ ጉልበትንና አሸናፊነትን መመዘን እንኳን በቤታችን ውስጥ ለተፈለፈሉት አሸባሪዎች ቀርቶ በዘመናት ውስጥ ሀገሪቱን ለወረሩት ባዕዳን ጠላቶቻችንም ቢሆን አልበጃቸውም። የሚሻለው የጦር መሣሪያዎችን እየተሽሎከለኩ ለማቀበል የሚንደፋደፉ ዜጎች ወደ ህሊናቸው ቢመለሱና ለተዘረጋላቸው የሰላም እጅ በጎ ምላሽ ቢሰጡ ነው። ያለበለዚያ ግን እንኳንም በሌሊትና በድቅድቅ ጨለማ “አዩኝ አላዩኝ” እየተባለ በሕገ ወጥነት መሣሪያ ለሚቀባበሉት ቀርቶ በአዋጅና በትእቢት ዘመናዊ የጦር መሣሪያቸውን በመረከብና በአውሮፕላን እያጓጓዙ ሀገሪቱን ለመውረር ለሞከሩ ታሪካዊ ጠላቶቻችንም ቢሆን በፍርሃት መንበርከክን ስላልለመደብን የቤት ውላጅ የጥፋት ኃይሎች ወደ ቀልብያቸው ተመልሰው ውስጣቸውን ቢያደምጡና ለታሪክ ክብር ቢሰጡ መከራው ሊቀልላቸው እንደሚችል እንገምታለን።
ዜና ሳይሆን “መርዶ አከል” መረጃ የሚሰጡን የሚዲያ ተቋማትም አቀራረባቸውን ቢፈትሹ አይከፋም። “ዜና ላኪው” መንግሥታዊ ክፍልም ቢሆን “ይህንን ያህል ሺህ የጦር መሣሪያዎች በቁጥጥር ሥር ዋሉ” ብሎ ማስነገሩ ምን ፋይዳ ሊኖረው ታስቦ እንደሆነ ደጋግሞ ቢያስብበት አይከፋም። “እውነት የሆነ ነገር ሁሉ አይነገርም” እንዲሉ “መርዶው” ምን ተጽእኖ እንደሚያመጣ በአግባቡ ሊታሰብበት ይገባል። ለሕዝብ ሥነ ልቦና ጥንቃቄ ይደረግ የመልእክታችን ማሳረጊያ ነው። የተያዙት ግለሰቦችና ቡድኖችም ምን ሕጋዊ እርምጃ እንደተወሰደባቸው ቢገለጽልን እንጠላም። ወንጀሉን ገልጦ ወንጀለኛውንና ፍርዱን ማድበስበሱም ጥቅም ያለው አይመስለንም። ይሄው ነው። ሰላም ይሁን!
ሀገር በማፍረስ ያለ ሀገር መኖር የሚቻል መስሏቸው ከሆነ ጅልነት ነው። በንጹሃን ደም እጃቸውን እየተለቃለቁ መኖር እጥፍ ዋጋ እንደሚያስከፍል አልተገነዘቡት ከሆነም የእጃቸውን ሲያገኙ እውነቱን ይረዱታል። ዳሩ የሚያቅበዘብዛቸው የባሩድ ጭስ ሱስ ወደ ህሊናቸው እንዲመለሱ መች ያበረታታቸዋል
ማረሚያ
በትናንት እትማችን የተስተናገደው ነጻ ሃሳብ እርእስ “የብራና አረንጓዴ ጎርፍ ” የተባለው በስህተት ስለሆነ ፤ ርእሱ “የብራ (ዝናብ የሌለበት) ጎርፍ ” በሚል ይስተካከል። ለተፈጠረው የቴክኒክ ስህተት አዲስ ዘመን ይቅርታ ይጠይቃል።
አዲስ ዘመን ሐምሌ 23 ቀን 2014 ዓ.ም