ዘካሪያስ ዶቢ
ኢትዮጵያውያን ከጥንት አንስቶ ለጀግኖቻቸው ታላቅ ክብር አላቸው። ይህንንም በተለያዩ መንገዶች ሲገልጹ ነው የኖሩት። በተለይ ለጀግኖች አትሌቶች የሚሰጠው ክብር ሁሌም ይታወሳል። ከሚሰጡት ልዩ ክብር አንዱ ድል አድርገው ሲመለሱ ደማቅ አቀባበል ማድረግና መሸለም ነው። ይህንንም ትናንት በደማቅ ስነስርአት ፈጽመውታል።
ኢትዮጵያውያንና መንግስታቸው በአሜሪካ ኦሪጎን በተካሄደው 18ኛው የአለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ተሳትፈው አንጸባራቂ ድል የተቀዳጁትን የአትሌቲክስ ጀግኖቻቸውን ጉሮ ወሸባዬ፣ ጉሮ ወሸባ፣ ዘማች ድል አድርጎ ሲገባ፣ እኛም ኮራን በናንተ፣ ወዘተ እያሉ በማዜም በደማቅ ስነስርአት ተቀብለዋቸዋል፤ ሽልማቶችም አበርክተውላቸዋል። አትሌቶቹ በተለይ ከትናንት በስትያ ሙሉ ቀኑን በአቀባበልና በሽልማት ስነስርአት ውስጥ ነው ያሳለፉት።
ህዝቡ በአዲስ አበባ ከተማ ዋና ዋና ጎዳናዎች ተገኝቶ ደማቅ አቀባባል አድርጎላቸዋል። መንግስት ደግሞ በብሄራዊ ቤተመንግስት ደማቅ አቀባበልና የሽልማት መርሀ ግብር አካሂዷል፤ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርም ሜዳሊያ ላስገኙት አትሌቶች ቦታ፣ ለልኡካን ቡድኑም 10 ሚሊዮን ብር ሸልሟል። በሁሉም በኩል የተካሄደው አቀባበልና ሽልማት በእጅጉ ደማቅና ክብሩን የሚመጥን ነው።
አትሌቶች ድሎችን አስመዝግበው በተመለሱ ቁጥር ደማቅ አቀባበሎች ሲደረጉላቸው ነው የኖሩት። የአሁኑ አቀባበል ግን በእጅጉ ደማቅና ታሪካዊ ሊባል የሚገባውም ነው። አቀባበሉም ሽልማቱም ድሉን የሚመጥን ነው ብሎ መውሰድ ይቻላል።
መንግስት አደራ ሰጥቶ ወደ ውድድሩ ስፍራ እንደሸኘ ሁሉ ድል በድል ሆነው ለተለመሱት የአትሌቲክሱ ጀግኖች ደማቅ አቀባበልና ሽልማት አድርጓል። አትሌቶቹም አደራቸውን በሚገባ ተወጥተው መጥተዋል፤ ታላቅ ድል አስመዝግበው ነው የተመለሱት። ይህን ድል የሚመጥን ታላቅ ምስጋና ተደርጓል።
ኢትሌቶቹ አራት የወርቅ አራት የብርና ሁለት የነሀስ በአጠቃላይ አስር ሜዳሊያዎችን በማግኘት፣ ከአለም ከአማሪካ ቀጥሎ ሁለተኛ፣ ከአፍሪካ አንደኛ ሆነው በማሸነፍ አገራቸውንና ህዝባቸውን አኩርተዋልና አቀባበሉ በእርግጥም ይገባቸዋል። ድሉ ይህ ብቻም አይደለም፤ በአለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ድል ከፍተኛው የተባለ የሜዳሊያዎች ብዛት የተመዘገበበት እንዲሁም ክብረወሰኖች የተሰባበሩበት ድልም ነውና አቀባበሉና ምስጋናው ድሉን የሚመጥን ከፍታው ከፍ ያለ ታሪካዊ ሊባል የሚገባውም ነው።
የኢትዮጵያ አትሌቶች በአንድነት ሆነው እየተናበቡ ነው ድል ሲያስመዘግቡ የኖሩት። ያ ታሪክ ዘንድሮም ተደግሟል። ይህ መሆኑም ኢትዮጵያ ተጨማሪ ሜዳሊያዎችን እንድታገኝ በር የከፈተ ታላቅ ስራ የታየበት ነው። ለአገር እንጂ ለግል ማንነት የሚደረግ ውድድር እንደሌለ በዚህ ሻምፒዮናም በሚገባ እንዲታይ አርገዋል።
የውድድሩ ወቅት በአገር ውስጥም በውጭ አገሮች የሚገኙ ኢትዮጵያውያንን ብቻ ሳይሆን ሌሎች የኢትዮጵያ ወዳጅ አገሮች ዜጎች ከኢትዮጵያ ጋር ያላቸው ትስስር ጥንካሬ የታየበት ሆኗል፤ በእያንዳንዱ ውድድር ኢትዮጵያውያን አብረው ሮጠዋል፤ ሲያሸንፉም አብረው ፈንድቀዋል።
ይህ የአንድነትና ተናቦ ድል የማስመዝገብ ተግባር በተለይ አገሪቱ በምትገኝበት በዚህ የፈተና ወቅት ትልቅ ስፍራ ይሰጠዋል። ኢትዮጵያውያን አንድ ሆነው የማያስመዘግቡት ድል፣ የማይንዱት ተራራ እንደሌለ በሚገባ አመልክቷልና። የኢትዮጵያ አሸናፊነት የማይገሰስ፣ ሁሌም የሚኖር መሆኑን ለመላ አለም ጭምር መልእክት የተላለፈበት ነው። ኢትዮጵያ በተለያዩ መስኮች ወትሮውንም አሸናፊ ናት፤ ይህ ድል ደግሞ በጦር ሜዳ ውሎም በልማቱም መስክ እየተመዘገበ ካለው ድል ጋር ሲቀናጅ የኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን አሸናፊነትና ተሻጋሪነት ሌላ ጉልህ መገለጫ ይሆናል።
አቀባበሉም ሌላ የኢትዮጵያውያን አንድነት በጉልህ የታየበት ሆኗል። የኢትዮጵያውያን አንድነት ሌላ ማሳያ ትልቅ መድረክ መሆንም ችሏል። እንደዚህ አይነት መድረኮች ለጠላትም ለወዳጅም ከሚኖራቸው ትልቅ ፋይዳ አኳያ ኢትዮጵያን እናፈርሳለን ለሚሉት ጠላቶቿ መሪር መርዶ ይሆናል፤ ኢትዮጵያ የማትፈረስ ስለመሆኑ ሌላ ትልቅ ማሳያ ነውና፤ ለወዳጆቿ ደግሞ ይበልጥ አብረውን አንዲዘልቁ ማድረግ የሚያስችል አቅምን ይፈጥራል።
ይህን ታላቅ ድል ያስመዘገቡት አገር በፈታኝ ሁኔታ ውስጥ በቆየችበት ወቅት እንደመሆኑም የአይበገሬነት መገለጫ ነው፤ እንደሚታወቀው አገራችን ባለፈው አንድ አመት ለብዙ ፈተናዎች ተዳርጋለች፤ ሁሉንም ግን በድል እየተወጣች ትገኛለች። በጦር ሜዳና በልማቱ መስክ
እየታዩ ያሉት ታላላቅ ድሎች በፈተና ውስጥ ተሆኖም አገርን ማሻገር እንደሚቻል ያመላከቱ ናቸው። አገር ፈተናዎችን ወደ እድል እየቀየረች ነው እነዚህን ድሎች ያስመዘገበችው።
የስፖርቱም ዘርፍ በፈተናዎች ውስጥ ነው የሚገኘው። አትሌቶቹም በዚህ ፈታኝ ሁኔታዎች ውስጥ ሆና ነው አለምን ጭምር ያስደነቀ ድል ያስመዘገቡት። እንደሚታወቀው ስታዲዮሞቻችን የፊፋን ዝቅተኛ የአለም አቀፍ ስታዲየም መስፈርት አያሟሉም ተብለው ምንም አይነት አለም አቀፍ ጨዋታ እንዳያስተናግዱ በካፍ እገዳ ተጥሎባቸዋል። በዚህ የተነሳም ለአፍሪካ ዋንጫም ይሁን ለአለም ዋንጫ የሚደረጉ ማጣሪያዎችን በሌላ አገር ሜዳዎች ስታደርግ ቆይታለች። ስታዲዮሞቹ መመዘኛውን እንዲያሟሉ በሚል ለሚካሄድ እድሳት ተዘጋጅተዋል።
ይህ ሁኔታ እግር ኳሱን በአያሌው የጎዳ ቢሆንም፣ አትሌቲክሱም አልተጎዳም ተብሎ አይታሰብም። የትራክ ውድድሮችና ልምምዶች የሚካሄዱበት የአዲስ አበባ ስታዲየም ለእድሳት ከተዘጋ ከአመት በላይ ሆኖት አትሌቲክሱ አይጎዳም ተብሎ አይታሰብም!!
አትሌቶቹ ይህን ፈተና ሁሉ አልፈዋል። ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያን በእጅጉ ያኮሩት በእዚህ እና እንደ አገር ባሉ በርካታ ጫናዎች ውስጥ አልፈው ነውና ድላቸው የኢትዮጵያንና ኢትዮጵያውያንን አይበገሬነት አሁንም ማሳየት ያስቻለ ታላቅ ድል ነው።
ኢትዮጵያውያን እነዚህን ጀግኖች ጎዳና ወጥተው በመቀበል ጉሮ ወሸባዬ….. እኛም ኮራን በናንተ… ወዘተ እያሉ በማዜም አቀባበል ማድረጋቸውና ምስጋናቸውን ማቅረባቸው መንግስትና የተለያዩ አካላት ሽልማቶችን መስጠታቸው ለድሉ የሚመጥን ታላቅ ምላሽ ተደርጎ ይወሰዳል። የቀደሙትን ድሎች ማሰብም ያስችላል፤ በቀጣይም የላቁ ድሎች እንዲመዘገቡ አደራ መስጠትም ይሆናል። አትሌቶች በአትሌትክሱ ዘርፍ ፍልሚያ ገጥማችሁ ድል በድል ሆናችሁ ተመልሳችሁዋልና ጀግኖች ናችሁ። እናም
ጉሮ ወሻባዬ ፣ ጉሮ ወሸባ ፣
ጉሮ ወሸባዬ፣ ጉሮ ወሸባ፣
ጉሮ ወሸባዬ ወሸባ
ዘማች ድል አድርጎ ሲገባ›› የሚለው ይመጥናችሁዋል፤ እንኳን ደስ አላችሁ፤ አንኳን ደስ አለን።
አዲስ ዘመን ሐምሌ 23 ቀን 2014 ዓ.ም