ከአንድ ምእተ አመት በላይ ያስቆጠረው የኢትዮጵያና የሩሲያ ህዝቦች ግንኙነት በየወቅቱ እየታደሰ አሁን ላይ በአዲስ የታሪክ ምዕራፍ ላይ ይገኝል። ግንኙነቱ ከኢትዮጵያም አልፎ አፍሪካዊ መልክ እየተላበሰ ይገኛል። ይህንንም ተከትሎ የአገሪቱ የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌ ላቭሮቭ ኢትዮጵያን ጨምሮ በአፍሪካ አገራት የሚያደርጉት ጉብኝት ከፍ ያለ ትኩረት የሚቸረው ነው።
አገራችን ኢትዮጵያ አስቸጋሪ በሆነ የውጪ ጫና ውስጥ በነበረችባቸው ያለፉት አራት ዓመታት የሩሲያ ሕዝብና መንግስት ለኢትዮጵያ ህዝብና መንግስት ያለውን አጋርነት በአደባባይ በተጨባጭ አሳይቷል። በእነዚህ ጊዜያት በአገሪቱ ላይ የተሸረቡ ዓለም አቀፍ ሴራዎች አቅም እንዳያገኙም ተደርገዋል።
በተለይም በለውጡ ኃይል ላይ ጫናዎችን በመፍጠር ታሪካዊ ጠላቶቻችንም ሆኑ የለውጡ አካሄድ ያልተመቻቸው ኃይሎች የተባበሩት መንግስታት ድርጅትን በመጠቀም በአገሪቱ ላይ ጫናዎችን ለማሳደር ያደረጉትን የተደጋገሙ ጥረቶች እንዳይሳኩ የሩሲያ መንግስት ያሳየው አጋርነት በኢትዮጵያውያን ልብ ውስጥ በደማቅ ቀለም የተጻፈ ነው።
ቀደም ባለውም ዘመን ቢሆን ሩሲያውያን ኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን በአስቻጋሪ ሁኔታ ውስጥ በሚገኙበት ወቅት ፈጥነው በመድረስ አጋርነታቸውን ያሳዩ የክፉ ቀን ወዳጆች መሆናቸው ይታወሳል። የዚያድባሬ ወራሪ መንግስት የውስጥ ክፍተቶችንና ዓለም አቀፍ ሁኔታውን ተመልክቶ የከፈተውን የግዛት ማስፋፋት ወረራ በአጭር ጊዜ ለመቀልበስ በተደረገው ርብርብና ተጋድሎ ከፍ ያለ ስፍራ እንደነበራቸው ይታወሳል።
ኢትዮጵያውያን እንደ አገር የመከዳት አደጋ ውስጥ በገቡባቸው ወቅቶች ሁሉ የሩሲያ ህዝብ እና መንግስት ለኢትዮጵያና ለኢትዮጵያውያን ፈጥኖ በመድረስ ያሳዩትና ዛሬም እያሳዩት ያለው አጋርነት፤ ኢትዮጵያውያን በክፉ ቀናቶቻችው አጋር እንዳላቸው በእርግጠኝነት እንዲያስቡ አቅም እየሆናቸው መጥቷል።
ይህ የሩሲያ አጋርነት ከኢትዮጵያ አልፎ “ለአፍሪካዊ ችግሮች አፍሪካዊ መፍትሄዎች በሚል “አፍሪካዊ መንፈስ ተላብሶ ብቅ ብሏል። ይህም ለመላው አፍሪካውያን እንደ አንድ ትልቅ የብስራት ዜና እየተቆጠረ ነው።
የሩሲያ አዲሱ አፍሪካዊ አጋርነት በርግጥም አፍሪካውያን ችግሮቻቸውን በራሳቸው የመፍታት አቅምና ብቃቱ እንዳለቸው ያመላከተና፤ ለረጅም ዘመናት ሰፍኖ የቆየውን ስለ አፍሪካና አፍሪካውያን ያለውን የተዛባ አመለካከት ማረቅ የሚያስችል እንደሆነም ይታመናል።
ይህ ኢትዮጵያዊም ሆነ አፍሪካዊ መንፈስ ያላቸው አፍሪካውያን በሙሉ የሚጋሩት መርህ፤ አፍሪካውያን ለችግሮቻቸው መፍትሄ ብቻ ሳሆን የችግሮቻቸውን እውነተኛ ምንጮች ተረድተው ቀጣይ እጣ ፈንታቸውን ብሩህ የሚያደርጉበትን ዕድል ሊፈጥር የሚችል መልካም አጋጣሚ ነው።
በቅኝ ገዥዎች ስለ አፍሪካና አፍሪካውያን ሲተረኩ የነበሩ የተዛቡ ትርክቶችን፤ ትርክቶቹ የወለዱትን የስነልቦና ጫናና ጫናው የፈጠረውን የማንነት መደበላለቅ በማጥራት፤ አፍሪካውያን የእጣ ፈንታቸው ሰሪዎች መሆናቸውን የሚያመለክትም ነው።
ይህ የሩሲያ አጋርነት ይህን ትልቅና ለዘመናት የተደበቀን እውነት አደባባይ አውጥቶ አፍሪካን ወደ አዲስ የታሪክ ምእራፍ ለመውሰድ የሚደረገውን ጥረት አቅም የሚያላብስ፤ ለመላው አፍሪካውያን እንደ አንድ ታሪካው ድል ተደርጎ ሊቆጠር የሚችል የ21ኛው ክፍለ ዘመን ስኬት ነው።
ዓለም ባልተገባ መልኩ በተዛቡ ትርክቶች ከተወሰደበት የተሳሳተ መንገድ መመለስ የሚያስችል፤ አፍሪካውያንም የበለጸገች አለም በመፍጠር ሂደት ውስጥ ያላቸውን አስተዋጽኦ እንዲወጡ በር ከፋች ነው።
በተለይም በቅኝ ግዛት ዘመን ቅኝ ገዥዎች አፍሪካውያን የጋራ እጣ ፈንታቸውን በጋራ እንዳይወስኑ፤ አገራትና ህዝቦች በጥርጣሬና በጠላትነት እንዲተያዩ የዘረጓቸውን ሴራዎች በጣጥሶ በመተማመንና በወንድማማችነት መንፈስ አዲስ የታሪክ ምዕራፍ እንዲከፍቱ ወሳኝ አቅምም ነው።
ይህን የሩሲያ ቀና መንገድ አለም አቀፉ ህብረተሰብ እንደ መልካም ተሞክሮ ሊወስደው፤ አፍሪካውያን ችግሮቻቸውን በራሳቸው የሚፈቱበትን አድል ሊያመቻቹ፤ ይህ እድል የበለጸገች አፍሪካን በመመስረት ሂደት ውስጥ አልፋና ኦሜጋ ተደርጎ ሊወሰድ ይገባል!
አዲስ ዘመን ሐምሌ 23 ቀን 2014 ዓ.ም